ጥያቄና መልስ

የብሉይ ኪዳን ጥናት ክለሳ

የብሉይ ኪዳንን የተለያዩ መጻሕፍት ስናጠና ቆይተናል። የእያንዳንዱ መጽሐፍ ጸሐፊ ማን እንደሆነ፥ የመጽሐፉን ታሪካዊ ሥረ-መሠረት፥ ዓላማና ዐበይት ትምህርቶች ተመልክተናል። እያንዳንዱን መጽሐፍ ያጠናነው በግል ስለሆነ በመጨረሻ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሙሉ በአንድነት እንዴት እንደተዋሀዱ ለመረዳት ጠቃሚ የሆነውን የመጻሕፍቱን ክለሳ መመልከት አስፈላጊ ነው።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) በብሉይ ኪዳን የሚገኙ መጻሕፍት ስንት ናቸው? ለ) የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ዋና ዋና ክፍሎች ጥቀስና በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍት ዘርዝር።

1. ፔንታቱክ (አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት)

ብሉይ ኪዳን በአራት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላል። የመጀመሪያው ዋና ክፍል ፔንታቱክ ወይም አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት የሚባለው ሲሆን፥ የብሉይ ኪዳንን የመጀመሪያ አምስት መጻሕፍት የያዘ ነው። እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረጋቸውን ቃል ኪዳኖች ስለሚገልጹ በብዙ አንጻር በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ መጻሕፍት ሁሉ እጅግ አስፈላጊ መጻሕፍት ናቸው። እነዚህ ቃል ኪዳኖች ብሉይና አዲስ ኪዳን የተመሠረቱባቸው መሠረች ናቸው።

ከፔንታቱክ መጻሕፍት ግማሽ ያህሉ ታሪካዊ መጻሕፍትን የያዘ ነው፡- (ዘፍጥረት፥ ዘጸአት፥ ዘኁልቁ)። ቀሪው ግማሽ ያህል ደግሞ ይኖሩበት ዘንድ እግዚአብሔር ለአይሁድ የሰጣቸውን ቃል ኪዳንና ሕግጋት የያዘ ነው (ዘጸአት፥ ዘሌዋውያን፥ ዘዳግም)። ታሪክ የሚጀምረው ስለ ፍጥረታት አጀማመር የሚናገሩ ታሪኮችን በያዘው በኦሪት ዘፍጥረት ነው። ይህ መጽሐፍ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከአንድ ሰው፥ ማለትም ከአብርሃም በመጀመር፥ በግብፅ ታላቅ ሕዝብ እስኪሆኑ ድረስ እንዴት እንደበዙ ያሳየናል።

የኦሪት ዘጸአት የመጀመሪያ ግማሽ ክፍል፥ እግዚአብሔር ሕዝቡ በግብፅ የነበሩበትን ቀንበር ለመስበርና ነፃ ለማውጣት በኃይልና በሥልጣን እንዴት እንደሠራ ያሳየናል። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ወዳደረገበት ወደ ሲና ተራራ መራቸው። የመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል ይህን ቃል ኪዳን በዝርዝር ያሳየናል። ቃል ኪዳኑ በቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ስለነበር ለሕጉ በመታዘዝ ሲኖሩ እግዚአብሔር እንደሚባርካቸው፥ ካልታዘዙት ደግሞ እንደሚቀጣቸው ተናግሮ ነበር። የቃል ኪዳኑ ማዕከል በመካከላቸው የእግዚአብሔርን ዙፋን መገኘት የሚያመለክተው የቃል ኪዳኑ ታቦት የነበረበት የመገናኛው ድንኳን ነበር። እስራኤላውያን የሲናን ተራራ ከመልቀቃቸው በፊት ዕቅዱ በእግዚአብሔር የተነደፈውን የመገናኛ ድንኳን ሠሩ።

ኦሪት ዘሌዋውያን፥ እስራኤላውያን በእግዚአብሔር የተመረጡ ቅዱስ ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያሳዩ ሕግጋትን ይዟል። እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለማምለክ ሊያቀርቧቸው ስለሚገቡ የተለያዩ መሥዋዕቶች ይገልጻል። ሕዝቡ እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ነገሮች የሚያስታውሱባቸው የተለያዩ የሃይማኖት በዓላትን ይደነግጋል። ካህናት ደግሞ ሕዝቡን በተቀደሰ አምልኮ መምራት ይችሉ ዘንድ እንዴት መኖር እንዳለባቸው ይዘረዝራል። አይሁድ ሁሉ በየዕለቱ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሁኔታ እንዴት እንደሚኖሩና የእግዚአብሔርን በረከቶች ለማግኘት እንዴት እርግጠኛች መሆን እንደሚችሉ ግልጽ መመሪያዎችን ይሰጣል።

ኦሪት ዘኍልቍ የሚያተኩረው የእግዚአብሔር ሕዝብ በተስፋዪቱ ምድር ያሉ ጠላቶቻቸውን ለማሸነፍ በእግዚአብሔር መታመን ስላቃታቸው በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት መንከራተታቸውን በሚናገረው አሳዛኝ ታሪክ ላይ ነው፡፡ አንድ ትውልድ ባለመታዘዙ ምክንያት ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን የሚናገር ታሪክ ነው። ኦሪት ዘኁልቁ የሚጠናቀቀው አይሁድ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ የሚገኘውን ምድር ወርረው በማሸነፍ እግዚአብሔር ወደሰጣቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት እንደተዘጋጁ በመናገር ነው።

በኦሪት ዘዳግም ውስጥ ሙሴ በሲና ተራራ የተሰጡትን ሕግጋት ለአዲሱ ትውልድ በድጋሚ ሲናገር እንመለከታለን። ሙሴ የተስፋይቱን ምድር ከሩቅ አሻግሮ ቢመለከትም እንኳ ወደ ከነዓን ሳይገባ ሞተ።

የፔንታቱክ ታሪክ የሚጀምረው እግዚአብሔር ምድርን ከፈጠረበት ካልታወቀ ጊዜ ሲሆን፥ የሚደመደመው ደግሞ በ1400 ዓ.ዓ. ገደማ ነው። 

2. የታሪክ መጻሕፍት

ከመጽሐፈ ኢያሱ እስከ አስቴር ድረስ ያሉት የሚቀጥሉት አሥራ ሁለት መጻሕፍት በብሉይ ኪዳን ዘመን የተፈጸመውን የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ የሚናገሩ ናቸው። ይህም ከነዓን ድል ከሆነችበት ከ1400 ዓ.ዓ. ጀምሮ፥ ከምርኮ መልስ የኢየሩሳሌም ቅጥር እስከተሠራበት እስከ 400 ዓ.ዓ. ድረስ የነበረውን ታሪክ ያጠቃልላል። 

ኢያሱ ስለ ከነዓን ድል መሆን ይናገራል። የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ላይ በነበራቸው እምነት ምክንያት አብዛኞቹን የከነዓንን ምድር ከተሞች ለማሸነፍና በዚያ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ማንበርከክ ችለው ነበር።

መጽሐፈ መሳፍንት የሚናገረው ግን እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ፍጹም ታዝዘው ከነዓናውያንን ባለማጥፋታቸው ምን እንደ ተፈጸመ ነው። አይሁድ ከከነዓናውያን ጋር ጎን ለጎን በመኖራቸው፥ ወዲያውኑ በባዕድ አምልኮ ኃጢአት ወደቁ። እግዚአብሔር በባርነት ይገዟቸው ዘንድ ለተለያዩ ከነዓናውያን መንግሥታት አሳልፎ በመስጠት ቀጣቸው። እስራኤላውያን ንስሐ በሚገቡበትና ወደ እግዚአብሔር በሚጮሁበት ጊዜ ከጠላቶቻቸው የሚታደጉአቸው የተለያዩ ተዋጊዎችን (መሳፍንትን) ያስነሣላቸው ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ወደ ቀድሞው የኃጢአት መንገዳቸው ይመለሱና እግዚአብሔር ይቀጣቸው ነበር። በዘመነ መሳፍንት ለእግዚአብሔር በታማኝነት የቆሙ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። ለዚህ ምሳሌ ከሚሆኑት መካከል ሩትና ቦዔዝ ይገኛሉ። ለእግዚአብሔር ተስፋ ታማኞች ሆነው በመቆየታቸው በእስራኤል ላይ ከነገሡ ነገሥታት ሁሉ በላይ የሆነው የንጉሥ ዳዊት አያቶች እንዲሆኑ እግዚአብሔር ፈቀደ።

1ኛ ሳሙኤል የሚያስተዋውቀን ከመሳፍንት ወደ ነገሥታት ዘመን የተደረገውን የሽግግር ወቅት ነው። የመጨረሻዎቹ ሁለት መሳፍንት ዔሊና ሳሙኤል ነበሩ። ይህ ማለት የግል ነፃነትን ማጣትና ከፍተኛ ግብር መገበር ማለት ቢሆንም እንኳ ሕዝቡ እንደቀሩት አሕዛብ ንጉሥ እንዲኖራቸው ፈለጉ። ሳኦል የእስራኤል ሕዝብ የመጀመሪያ ንጉሥ ነበር። ሳኦል አጀማመሩ መልካም ቢሆንም፥ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ባለመጠበቁ፥ መንግሥቱ ከእርሱ ተወስዳ ለዳዊት ተሰጠች። የ1ኛ ሳሙኤል አብዛኛው ታሪክ የያዘው ሳኦል፥ ዳዊት ንጉሥ እንዳይሆን ባደረበት ቅንዓት እርሱን ለመግደል ያደረጋቸውን የተለያዩ ሙከራዎች ነው።

2ኛ ሳሙኤል በእስራኤል ላይ ከነገሡት ነገሥታት ሁሉ በላይ የሆነውን የንጉሥ ዳዊትን ታሪክ ይናገራል። ዳዊት እግዚአብሔርን ይወድ ነበር። ምንም እንኳ በኃጢአት ቢወድቅም፥ ዝርያዎቹ የእስራኤልን ዙፋን እንደሚቆጣጠሩ የተስፋ ቃል በመስጠት እግዚአብሔር አከበረው። ይህም የዳዊት ልጅ በሆነው በመሢሑ በኢየሱስ ሙሉ ለሙሉ ይፈጸማል።

1ኛ መጽሐፈ ነገሥት የነገሥታትን ታሪክ መናገሩን ይቀጥላል። የሚጀምረው በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የላቀ ጥበበኛ በነበረው በዳዊት ልጅ በሰሎሞን ነው። ዳሩ ግን ሰሎሞን ለሴቶች የነበረው ፍቅር ወደ ጣዖት አምልኮ መርቶት፥ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንዲቀበል አደረገው። ከሰሎሞን ሞት በኋላ እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት የሰሜኑን ክፍል የእስራኤል መንግሥትና የደቡቡን የይሁዳ መንግሥት ተብሎ እንዲከፈል አደረገ፡፡ የቀረው 1ኛ እና 2ኛ መጽሐፈ ነገሥት እግዚአብሔር ሰሜኑ የእስራኤልን መንግሥት ወደ አሦር፣ ደቡቡ የይሁዳን መንግሥት ወደ ባቢሎን በምርኮ እንዲወሰድ ከማድረጉ በፊት የነበሩትን ነገሥታት ታሪክ በአጭሩ ያብራራል።

1ኛ- 2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ከዳዊት እስከ ምርኮ ድረስ ያለውን የደቡቡ የዳዊትን ዝርያ የሆኑ ነገሥታት ታሪክ በድጋሚ ይተርካል። እነዚህን ጊዜያት ከታሪክ አቅጣጫ ከመመልከት ይልቅ አንድ ንጉሥ እግዚአብሔርን በሚያከብርበት ጊዜ መንግሥቱና ሕዝቡ እንደሚባረክ። ንጉሡ ለእግዚአብሔርና ለሕግጋቱ በማይታዘዝበት ጊዜ መንግሥቱና ሕዝቡ እንደሚፈረድበት እነዚህ መጻሕፍት ይናገራሉ።

መጽሐፈ ዕዝራ፥ ነህምያና አስቴር የይሁዳ ሕዝብ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ስለተፈጸሙ ድርጊቶች የሚናገሩ ናቸው። መጽሐፈ ዕዝራ የሚገልጸው ከባቢሎን ወደ ምድራቸው ስለተመለሱት ሁለት የመጀመሪያ የአይሁድ ቡድኖች ጉዳይና ስለ ቤተ መቅደሱ መሠራት ነው። ነህምያ ደግሞ ወደ ምድሪቱ ስለተመለሰ ሌላ ቡድን ስለ ኢየሩሳሌም ቅጥር መሠራት ይናገራል። መጽሐፈ አስቴር በንጉሥ አርጤክስስ ዘመን እግዚአብሔር አይሁድን በአሕዛብ ፈጽመው ከመደምሰስ እንዴት እንደጠበቃቸው ይናገራል።

ከእዚህ አሥራ ሁለት መጻሕፍት በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ትረካ ያበቃል። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ለመኖር እስከመጣበት ጊዜ ድረስ 400 የጸጥታ ዘመናት ነበሩ። የእነዚህን የጸጥታ ዘመናት ታሪክ ሌሎች መጻሕፍት የዘገቡት ቢሆንም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለ እርሱ ምንም አይናገርም። 

3. የግጥምና የጥበብ መጻሕፍት

በብሉይ ኪዳን ውስጥ እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ መጻሕፍት መካከል አምስቱ የግጥምና የጥበብ መጻሕፍት ይገኛሉ። እነርሱም መጽሐፈ ኢዮብ መዝሙረ ዳዊት መጽሐፈ ምሳሌ፥ መጽሐፈ መክብብና መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ናቸው። መዝሙረ ዳዊት የአይሁድ የአምልኮ መዝሙራት መጽሐፍ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ መዝሙራት የተጻፉት ለእግዚአብሔር ምስጋናን በሚገልጡና እግዚአብሔር ክፉዎችን በመቅጣት ጻድቃንን እንደሚባርክ በሚያስረዱ መንገዶች ነው። ሌሎቹ መጻሕፍት የጥበብ መጻሕፍት በመባል ይታወቃሉ፤ ምክንያቱም አይሁድ እርሱን በሚያስከብር መንገድ እንዲኖሩ እግዚአብሔር ስለሰጣቸው ጥበብና በጊዜው ይቸገሩባቸው ስለነበሩ አንዳንድ የፍልስፍና ጥያቄዎች የሰጣቸውን መልስ ስለሚያስረዱ ነው። መጽሐፈ ኢዮብ የሚያስተምረን ጻድቅ ሰው ከቶ ባልታወቀ ምክንያት መከራን ቢቀበል እንኳ በእግዚአብሔር ታምኖ መከራውን በትዕግሥት ሊቀበለው እንደሚገባ ነው። መጽሐፈ ምሳሌ ደግሞ ማንኛውም የሕይወት ሁኔታ ውስጥ በጥበብ መኖር እንዴት እንደሚቻል የሚያሳዩ ቀለል ያሉ መመሪያዎችን የያዙ አጫጭር አባባሎችን አካትቷል። መጽሐፈ መክብብ ሕይወትን ከዓለም አመለካከት አንጻር ያያታል። ሰሎሞን ሰዎች ጠቃሚና አስፈላጊ ናቸው ብለው ያመኑባቸውን ነገሮች ሁሉ ተመልክቶ ሁሉም ከንቱ መሆናቸውን መሰከረ። ሕይወትን እውነተኛ ትርጉም ያለው የሚያደርግ እግዚአብሔርን ማወቅና ማምለክ ብቻ ነው። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን የፍቅር ታሪክ ሲሆን በወንድና በሴት መካከል ያለ ፍቅር የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ያስተምራል። 

4. የትንቢት መጻሕፍት

የእስራኤል ታሪክ ከምርኮ በፊት በነበሩት ዓመታት (ከ850-400 ዓ.ዓ.) ሊደመደም ገደማ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ወደገባው ቃል ኪዳን ይመለሱ ዘንድ አለበለዚያ ግን እንደሚፈረድባቸው ሕዝቡን እንዲያስጠነቅቁ ያስነሣቸው ነቢያት የተባሉ ቃል አቀባዮች ነበሩት። ነቢያት ስለሚመጣው ፍርድ ካሳወቁበት ከማስጠንቀቂያ መልእክታቸው ጋር ጽድቅና ቅንነት ያለበትን መንግሥት ስለሚያመጣው መሢሕ የሚያመለክቱ የተስፋ መልእክቶችም ነበሩ። ከእነዚህ ነቢያት አብዛኛዎቹ ያገለገሉት ታሪካቸው በ1ኛና 2ኛ ነገሥት እንዲሁም በ1ኛና 2ኛ መዋዕል ዜና ካልዕ በሚገኝ ነገሥታት ዘመን ነበር፡፡

ነቢያት በሁለት የተከፈሉ ናቸው፤ የመጀመሪያዎቹ፥ ታላላቅ ነቢያት የምንላቸው፡- ኢሳያያስ፥ ኤርምያስ (ከሰቆቃወ ኤርምያስ ጋር)፥ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ናቸው። እነዚህ ታላላቅ የተባሉበት ምክንያት መልእክታቸው ረጅምና ታላቅ ስለሆነ ነው። ሁለተኛዎቹ አሥራ ሁለቱ ታናናሽ ነቢያት ሲሆኑ፥ እነርሱም፡- ሆሴዕ፥ አሞጽ፥ ሚክያስ፥ ኢዩኤል፥ አብድዩ፥ ዮናስ፥ ናሆም፥ ዕንባቆም፥ ሶፎንያስ፥ ሐጌ፥ ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው።

ሀ. ታላላቅ ነቢያት

ኢሳይያስ፡- የእስራኤል መንግሥት ከመውደቁ በፊት ጽፎ እስራኤል በአሦር፥ ይሁዳ ደግሞ በባቢሎን እንደሚማረኩ ያመለከተ ነቢይ ነው። ኢሳይያስ ከየትኛውም ነቢይ በላቀ ሁኔታ ስለ መሢሑ መምጣትና እርሱ ስለሚያመጣው ሰላም ተናገሯል።

ኤርምያስ፡- በእግዚአብሔር የተጠራው ይሁዳ ከመማረክዋ ጥቂት ቀደም ብሎ ነበር። ሕዝቡን ስለ ኃጢአታቸው ቢያስጠነቅቅም እንኳ ንስሐ ለመግባት አልፈለጉም ነበር። ኤርምያስ ሕዝቡ በባቢሎን ሲማረክ አይቶ ነበርና የተሰማውን ኃዘን በሰቆቃወ ኤርምያስ ጽፏል። ኤርምያስ ስለ ሰባው ዓመት ምርኮና ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን መምጣት አስቀድሞ ተናገረ።

ሕዝቅኤል፡- በምርኮ ምድር በባቢሎን ካገለገሉት ሁለት ነቢያት አንዱ ነበር። ሕዝቅኤል ኢየሩሳሌም በመጨረሻ ከመውደቋ በፊት የይሁዳን ውድቀትና ምርኮ አስቅድሞ አመለከተ። አይሁድ ከምርኮ መቼ እንደሚመለሱና አንድ ሕዝብ ሆነው እንደሚዋሐዱም ተናግሯል። እግዚአብሔር በመካከላቸው እንደሚኖር፥ መሢሑ በእነርሱ ላይ እንደሚነግሥና ቤተ መቅደሱ እንደገና እንደሚሠራ ተናገረ።

ዳንኤል፡- በባቢሎን ያገለገለ ሁለተኛው ነቢይ ሲሆን አንዳንዶች «የትንቢት ቁልፍ» በማለት ይጠሩት ነበር። ለእግዚአብሔር ያለውን ታማኝነት የሚገልጥ ታሪክ ብቻ ሳይሆን፥ ከባቢሎን ጀምሮ እስከ ሮም ድረስ ያለውን የመንግሥታትን ታሪክና ክርስቶስ በመጨረሻው ዘመን እንደሚነግሥ የሚናገሩ ታሪኮችን ይዟል።

ለ. አሥራ ሁለቱ ታናናሽ ነቢያት

አሥራ ሁለቱ ታናናሽ ነቢያት በተለያዩ መንገዶች ሊመደቡ ይችሉ፡፡ አንደኛው መንገድ ከምርኮ በፊት ያገለገሉትን ዘጠኙንና ከምርኮ መልስ ያገለገሉትን ሦስቱን ሐጌ፥ ዘካርያስና ሚልክያስ) መዘርዘር ነው። ሌላው መንገድ መልእክቱ በቅድሚያ እንዲደርሳቸው በታቀደላቸው ሕዝቦች መሠረት መመደብ ነው፡-

1. እስራኤልን ያገለገሉ ነቢያት – ሆሴዕና አሞጽ 

2. ይሁዳን ያገለገሉ ነቢያት – ዕንባቆም፥ ኢዩኤል፥ ሚክያስና ሶፎንያስ 

3. አሕዛብን ያገለገሉ ነቢያት – ዮናስ፥ ናሆምና አብድዩ 

4. ከምርኮ በኋላ ያገለገሉ ነቢያት – ሐጌ፥ ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው 

እነዚህ መጻሕፍት እያንዳንዳቸው ማስጠንቀቂያና የሚማጣውን የበረከት ጊዜ የሚመለከቱ ትንቢቶችን የያዙ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሠላሳ ዘጠኙን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ስም ዘርዝር። ለ) እያንዳንዱ መጽሐፍ የሚናገረው ስለምን እንደሆነ ባጭሩ ጻፍ። ሐ) ለእያንዳንዱ መጽሐፍ አንድ ዓላማ ጻፍ። ም) በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ አንድ መንፈሳዊ ትምህርት ጻፍ።

ብሉይ ኪዳን በርካታ ጠቃሚ ትምህርቶችን የያዘ ቢሆንም፥ ከሁሉም በላይ ማስታወስ የሚያስፈልገው ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ነው። እግዚአብሔር ስለ ራሱ፥ ስለ መንገዶቹና ፈቃዱ፥ ለአይሁድ ዛሬም ለእኛ ለማስተማር የሰጠን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስሕተት የገባ አንድም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ የለም። ሁሉም መጻሕፍት አስፈላጊዎች ናቸው። ስለ ብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ይህን የጥናት መምሪያ ስንጽፍ፣ እያንዳንዱን መጽሐፍ እንድትወደው፥ ስለ ታላቁ እግዚአብሔርና እርሱ ለእኛ ስላለው ፈቃዱ የበለጠ ለማወቅ በእያንዳንዱ መጽሐፍ መጠቀምን እንድትማር በማሰብ ነው። አንተ ደግሞ በተራህ እነዚህን መጻሕፍትና በውስጣቸው ያሉትን እውነቶች ለቤተ ክርስቲያንህ አባላት ታስተምር ዘንድ ጸሎታችን ነው።

ኢየሱስ በሉቃስ 24፡44 ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፡- «በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል።» ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ትንቢተ ሚልክያስ ድረስ ብሉይ ኪዳን ወደ መሢሑ ወደ ኢየሱስ ያመለክታሉ። በሕይወታችን ዘመን ሁሉ ጌታችንና አዳኛችን ስለ ሆነው ስለ ኢየሱስና ስለ እግዚአብሔር አብ የበለጠ ለመማር እነዚህን መጻሕፍት ማጥናታችንን መቀጠል አለብን።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

አራት መቶ የጸጥታ ዓመታት

የብሉይ ኪዳን ታሪክ የሚደመደመው በመጽሐፈ ነህምያ ሲሆን፥ ትንቢታዊ መልእክቶች የሚጠቃለሉት ደግሞ በትንቢተ ሚልክያስ ነው። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለእስራኤላውያን የሚሰጠው መልእክት ተፈጸመ። እግዚአብሔር ኤልያስንና መሢሑን እንዲጠባበቁ ለእስራኤላውያን መልእክት ከሰጣቸው በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚያክሉት ሌላ ተጨማሪ መልእክት አልሰጣቸውም። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ከሚልክያስ ዘመን ጀምሮ (400 ዓ.ዓ.) ኢየሱስ እስከ መጣበት (5 ዓ.ዓ.) ድረስ የነበረውን ጊዜ «400 የጸጥታ ዓመታት» ብለው የሚጠሩት ስለዚህ ነበር። አይሁድ የአዋልድ መጻሕፍት (አፖክሪፋ) በመባል የሚታወቁ ሌሎች ተጨማሪ መጻሕፍት የጻፉ ቢሆንም፥ እነዚህ መጻሕፍት ከብሉይ ኪዳን 39 መጻሕፍት ጋር እኩል እንዳይደሉ ተገንዝበው ነበር። 

እነዚህ አራት መቶ ዓመታት ለአይሁድ እጅግ ወሳኝ ስለነበሩ በእነዚህ ዓመታት ምን እንደተደረገ ማወቅ አስፈላጊ ነው። እነዚህን አራት መቶ ዓመታት የበለጠ በተረዳን ቁጥር፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተፈጸሙትን አንዳንድ ነገሮች በይበልጥ እንረዳለን። ከጊዜና ከቦታ እጥረት የተነሣ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ጥቂት አሳቦች ብቻ ተጠቃልለው ቀርበዋል።

1. የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ግዛቶች (539-331 ዓ.ዓ.)፡- የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በተደመደመበት ጊዜ፥ የፋርስ መንግሥት ነገሥታት አይሁድን ራቅ ብሎ እንደሚገኝ የግዛታቸው ክፍለ ሀገር ይዙዋቸው ነበር። በፖለቲካ ረገድ ከታላቁ የፋርስ የሥልጣን ማዕከል እጅግ ርቀው ይገኙ ስለነበር የፋርስ መንግሥት አይሁዳውያንን የራሳቸውን ጉዳይ እንዲያከናውኑ ትተዋቸው ነበር። ኢየሩሳሌም ከፍተኛ የንግድ ዕከልና የጳለስጢን ዋናዋ የፖለቲካ ሥልጣን ቁንጮ ነበረች። በፋርስ የንጉሠ ነገሥት ግዛት የሥልጣን ዘመን ውስጥ፥ የኋላ ኋላ በአዲስ ኪዳን ዘመን ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ ብዙ ነገሮች ተፈጽመዋል። 

ሀ. አይሁድ በዓለም ዙሪያ ሁሉ መሠራጨታቸውን ቀጠሉ። አብዛኛዎቹ አይሁድ የሚኖሩት ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ውጭ ነበር። እንደ ሀገራችን የጉራጌ ብሔር አባሉች የተዋጣላቸው ነጋዴዎች በመሆን፥ በጥንቱ ዓለም በነበሩ በአብዛኛዎቹ ከተሞች ይገኙ ነበር። ይህ በየስፍራው ተበትኖ የመኖር ነገር በሚቀጥለው የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛትም እየጨመረ ሄዶ ነበር። በአዲስ ኪዳን ዘመን በግልጽ እንደሚታየው ጳውሎስ ወንጌልን ይዞ በተዘዋወረባቸው ስፍራዎች ሁሉ፥ በቅድሚያ ይሰብክ የነበረው የተበተኑት አይሁድ ወደሚሰበሰቡበት ምኩራብ በመሄድ ነበር።

ለ. የአይሁድ ዋና ቋንቋ ተለወጠ። አብዛኛዎቹ አይሁድ በእስራኤል ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ሳይቀሩ አራማይክ የተባለውን የንግድ ቋንቋ ይናገሩ ነበር። የብሉይ ኪዳን ቋንቋ የሆነውን ዕብራይስጥ ይጠቀሙ የነበሩት በአምልኮ ፕሮግራም ብቻ ነበር። ለምሳሌ የእግዚአብሔር ቃል በሚነበብበት ጊዜ ዕዝራ የተረጐመበት አንዱ ምክንያት ይህ ነበር (ነህምያ 8፡7-8)። ኢየሱስ አገልግሎቱን የሰጠው በአራማይክ ቋንቋ ነው። 

ሐ. የምኩራቦች አጀማመር፡- የአይሁድ ማኅበረሰብ ባሉበት ስፍራ ሁሉ፥ የማኅብረሰብ ማዕከልና ምኩራብ የተባለ የአምልኮ ስፍራ ይሠሩ ጀመር። በእነዚህ ምኩራቦች ውስጥ መሥዋዕት ባያቀርቡም እንኳ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ይሰበሰቡ ነበር። እነዚህ ምኩራቦች በኋላ የጣዖት አምልኮ የሰለቻቸው አሕዛብ ስለ እውነተኛው አምላክ ለመስማት የሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች ሆኑ። ጳውሎስና ሌሎች አገልጋዮች ወንጌልን ለመስበክ ወደ እነዚህ ስፍራዎች እንደሄዱ እነዚህ አሕዛብ ፈጥነው በክርስቶስ በማመን ተለወጡ፡፡ 

መ. የካህናት ሥልጣን እየጨመረ መምጣት፡- ገና ከመጀመሪያው በኢየሩሳሌም የነበረው የአይሁድ ማኅበረሰብ አንድ የፖለቲካ (ለምሳሌ ዘሩባቤል)፥ ሌላ የሃይኖት (ለምሳሌ ታላቁ ካህን ኢያሱ) መሪ የነበረው ቢሆንም፥ ካህናቱ የፖለቲካና የሃይማኖት መሪነቱን ጠቅልለው ለመያዝ ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር። ይህም ካህናቱ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ረገድ ከመምራት ይልቅ በፖለቲ ጉዳይ ላይ በማተኮር በሥልጣን እንዲባልጉ አደረጋቸው።

ሠ. “ጸሐፍት” የተባሉ አይሁድ ያሉብት መደብ ፈጠር፡- ጸሐፍት በሕግ እውቀትና ትርጓሜ ሥራ የተካኑ ነበሩ፡፡ እነርሱም የእስራኤል ቁልፍ የሕግ መምህራን ሆኑ፡፡ ሕዝቡ የብሉይ ኪዳንን ተዛዛት እንዳይጥሱ ለማረጋገጥ በመፈለጋቸው፣ ሕዝቡ ለተጻፉት ሕግጋት አንታዘዝም እንዳይሉ ለመጠበቅ ሲሉ እንደ “አጥር” የሚሆኑ ሌሎች ሕግጋትን ጨመሩ፡፡ በኋላ ለእነዚህ ሕግጋት ወግ ከመጀመሪያው የእግዚአብሔር ሕግ የበለጠ ስፍራ ይሰጣቸው ጀመር፡፡ ይህም ወዲያውኑ ይሑዲነትን ልባዊ ሳይሆን ሕጋዊነት ወደሚንጸባረቅበት “አድረግ፣ አታድርግ” የአይሁድ የሃይማኖት ሥርአት ለወጠው፡፡ ጸሕፍትም በተራቸው የፖለቲካ መሪዎች እስኪሆኑ ድረስ በስልጣን መጥቀው ሄዱ፡፡ በመጨረሻም ጸሐፍት፣ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሌዎች “ሸንጎ” የተባል ጉባኤ በማቋቋም የአይሁድን የአስተዳደር አካል መሠረቱ፡፡ 

ረ. የሳምራውያንና የአይሁድ ጥላቻ አጀማመር፡- እስራኤላውያን በአሦር እጅ በወደቁና በተማረኩ ጊዜ ከሌላ ስፍራ አሕዛብን ወደ እስራኤል በማምጣት ከቀሩት አይሁድ ጋር ለመቀላቀል እንደሞከሩ ታስታውሳለህ፡፡ አይሁድና አሕዛብ በመጋባታቸው ምክንያት የተወለዱት ልጆች ሳምራውያን ተባሉ፡፡ ከአይሁድ ወደባቢሎን ተወስደው የነበሩት አይሁድ ወደ እስራኤል በተመለሱ ጊዜ የእስራኤል ሃይማኖት ከይሁዲነትና ከአሕዛብ የጣዖት አምልኮ ጋር ተደባልቆ ነበር። እነዚህ ሳምራውያን ከአይሁድ ጋር ተባብረው ቤተ መቅደሱን ለመሥራት በመጡ ጊዜ አይሁድ ተቃወሙ። አምልኮአቸው ንጹሕ ሆኖ እንዲቆይ ይፈልጉ ነበር። ይህም ሳምራውያንን አስቆጣቸውና የአይሁድ ጠላቶች እንዲሆኑ አደረጋቸው። ቆየት ብለው ሳምራውያን ከአይሁድ ተለዩ። ገረዚም በተባለ ተራራ ላይ የራሳቸውን ቤተ መቅደስ ሠሩ። ከአይሁድ የአምልኮ ሥርዓት ጋር የሚመሳሰል የራሳቸው የአምልኮ መዋቅር አበጁ። በተቀዳሚ አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት የያዙ የራሳቸው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ነበሯቸው። ይህም አይሁድን እጅግ አስቆጥቷቸው ስለነበር በነጻነታቸው ጊዜ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሳምራውያንን ገደሉ። በአይሁድና በሳምራውያን መካከል የነበረው ይህ ጠላትነት፥ በአዲስ ኪዳን ዘመን ኢየሱስ በሰማርያ ሲያልፍና በተለይ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ሲነጋገር ደቀ መዛሙርቱ አይተው በመደነቃቸው ይስተዋላል (ዮሐንስ 4)። 

ሰ. ምሁራን የአይሁድ መሠረታዊ ትምህርቶች በአንዳንድ መንገዶች የፋርስ ሃይማኖት ተጽዕኖ አድሮባቸዋል ብለው ያስባሉ። በፋርስ ዘመን የፋርስ ሰዎች ያደርጉት እንደነበረው አይሁዶች በመለኮታዊ ፍርድ፥ በሙታን ትንሣኤ፥ በአጋንንትና በመላእክት ሕልውና፥ ወዘተ. ላይ ያተኩሩ ነበር። 

2. የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛት (331-142 ዓ.ዓ.)

የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛት በታላቁ እስክንድር መሪነት፥ በዓለም ላይ እስከዚያ ዘመን ድረስ ተነሥተው ከነበሩ መንግሥታት ሁሉ በላቀ ሁኔታ ተስፋፍቶ ነበር። የፋርስን የንጉሠ ነገሥት ግዛት በሙሉ ከመጠቅለል አልፎ፥ ወደ ታች ወደ ግብፅና ሕንድ ድረስ ተስፋፋ። በጥንት ታሪክ ለመጀመሪያው ጊዜ አንድ የአውሮፓ አገር ግዛቱን እስከ ትንሹ እስያ ድረስ በማስፋፋት፥ በአንዳንድ ረገድ ከነበረው ተመሳሳይነት በስተቀር በወረራቸው ሕዝቦች ላይ በእጅጉ የተለየ ባህል አመጣ። ሆኖም ታላቁ እስክንድር የፋርስን መንግሥት መዋቅርንም ሆነ የክልል መንግሥታት አደረጃጀትን ለመደምሰስ አልሞከረም። ታላቁ እስክንድር በዘመኑ የታወቁ የዓለም ክፍሎችን በሙሉ ወርሮ ከያዘ በኋላ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ገና በወጣትነት ዘመኑ በ323 ዓ.ዓ. ሞተ።

በ301 ዓ.ዓ. የታላቁ እስክንድር ጦር ሜጀር ጄኔራሎች እያንዳንዳቸው አንዳንድ ከፍል በመያዛቸው መንግሥቱ ለአራት ተከፈለ። በይሁዳ ላይ ተጽዕኖ አሳድረው የነበሩት ሁለቱ መንግሥታት ግብፅንና ሊቢያን ይዞ የነበረው የፕቶሎሜካዊ ንጉሠ ነገሥት ግዛትና ሶርያና ፋርስን ተቆጣጥሮ የነበረው የሲሉሲድ ንጉሠ ነገሥት ግዛት ነበሩ። በእነዚህ ሁለት የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛቶች መካከል ወዳጅነት አልነበረም። እነዚህ ሁለት መንግሥታት ጳለስጢናን ለመቆጣጠር በመምከር ያለማቋረጥ ይዋጉ ነበር። ይህ ማለት አይሁድ ያለማቋረጥ እርስ በርሳቸው በሚጋጩና አብረዋቸው እንዲምቱ በሚጠይቋቸው ባዕዳን ሠራዊት ይጠቁ ነበር ማለት ነው።

ከ320-200 ዓ.ዓ. ፕቶሎሚዎች ጳለስጢናን ተቆጣጠሩ። በይሁዳ ይኖሩ የነበሩትን አይሁድ እንደፈለጋቸው እንዲኖሩ ለቀቋቸው። በዚህ ጊዜ የአይሁድ ገዢዎች ካህናት ነበሩ።

ከ200-142 ዓ.ዓ. ሲሉሲዶች ጳለስጢናን ተቆጣጠሩ። ከፍተኛው ትኩረታቸው አይሁድ የግሪክን ባህል እንዲለምዱ ማድረግ ነበር። ቀረጥ እንዲከፍሉ አይሁድን አስገደዷቸው። በጭካኔ ከሁሉ የከፋው መሪ፥ ከ175-164 ዓ.ዓ. የገዛው አንቲዩከስ 4ኛ ኤፒፋነስ የተባለው ነው። አይሁድ የጣዖት አምልኮ ያካትት የነበረውን የግሪኮችን ባህል እንዲለማመዱ ለማስገደድ ሞከረ። በኃላፊነት ላይ የነበረውን የአይሁድ ሊቀ ካህን አባርሮ የግሪክን ባህል ለመቀበል ይፈልግ የነበረውን የራሱን አይሁዳዊ ሊቀ ካህን በሕዝቡ ላይ ሾመ። ከግብፅ ጋር ይዋጋ ለነበረው ጦሩ ለመክፈል በቤተ መቅደስ የነበረውን ገንዘብ ሁሉ ወሰደ። ሮማውያን ግብጽን ወርሮ እንዳይዝ በከለከሉት ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። በቤተ መቅደስ ውስጥ ይቀርብ የነበረው መሥዋዕት ሁሉ እንዲቆም በማድረግና በመሠዊያው ላይ አሳማ በመሠዋት መሠዊያውን አረከሰው። ዚዩስ ለተባለው የግሪክ ጣዖት መሥዋዕት ማቅረቢያ የሚሆን መሠዊያ በማሠራት ለዚዩስ መሥዋዕትን እንዲያቀርቡ አዘዘ። (በዳንኤል 11፡31-36 ስለዚህ ዘመን የተነገረውን ትንቢት ተመልከት)።

ከ167-164 ዓ.ዓ. ለሦስት ዓመታት በቤተ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ማንኛውም መሥዋዕት ቆመ፡፡ 

ይህ የአንቲዩከስ ተግባር አይሁድን ለዓመፅ አነሣማቸው፡፡ መቃብያን ተብለው ይጠሩ በነበሩ በአንድ ካህንና በሁለት ልጆቹ መሪነት አይሁድ በመካከላቸው የነበረውን የግሪክ ባህል መስፋፋት መቃወም ጀመሩ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ በነበሩት ዓመታት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አይሁድ ሕይወታቸውን አጡ። ዳሩ ግን በመጨረሻ በ162 ዓ.ዓ. ሴሉሲድስ የተባሉትን የሶርያ ግሪኮች በማሸንፍ በከፊል ነጻነታቸውን ለማግኘት ችለው ነበር። በ142 ዓ.ዓ. እስራኤል ሐስሞኒያንስ በሚባሉ ካህናት የምትመራ ነጻ መንግሥት ሆነች። አይሁድ ለ79 ዓመታት ከአሕዛብ ነጻ ሆነው ኖሩ።

ግሪኮች ይገዙ ከነበረበት ወቅት ቆይታ በአዲስ ኪዳን ዘመን ላይ ብዙ ተጽዕኖ ያሳደሩ በርካታ ነገሮች ተለውጠዋል። ከእነዚህም ዋናው የግሪክ ቋንቋ ሁሉም ስፍራ የሚነገር የንጉሠ ነገሥቱ ዋና ቋንቋ መሆኑ ነበር። በአይሁድ አፈታሪክ መሠረት በ250 ዓ.ዓ. 72 ምሁራን ብሉይ ኪዳንን በ72 ቀናት ውስጥ ወደ ግሪክ ቋንቋ ተረጐሙ። ይህም ሴፕቱዋጀንት በመባል የሚታወቀው የግሪክ ብሉይ ኪዳን፥ የዕብራይስጥ ወይም የአራማይክ ቋንቋ ለማይናገሩና ከጳለስጢና ውጭ ይኖሩ ለነበሩ አይሁድ ዋና መጽሐፍ ሆኖ ነበር። ደቀ መዛሙርት በሚገባ ያውቁትና በአምልኮአቸው ይጠቀሙበት የነበረው ይህንን ብሉይ ኪዳን ነበር፡፡ አዲስ ኪዳን በአጠቃላይ የተጻፈው በግሪክ ቋንቋ ነበር። ስለዚህ በግሪክ የነበሩ አብዛኛዎቹ ሕዝቦች ሊረዱት የቻሉ ሲሆን፥ በኋላም በሮም የንጉሠ ነገሥት ግዛት ውስጥ የወንጌል ሥራ በቀላሉ እንዲካሄድ ረድቶአል። 

3. በሐስሞኒያን ካህናት መሪነት ሥር የተገኘው ነፃነት (142-64 ዓ.ዓ.)

በመጨረሻ አይሁድ ነፃነታቸውን በተጎናጸፉ ጊዜ፥ ወዲያውኑ የአይሁድ ባህል እንቅስቃሴ ተጀመረ። የግሪክ ባህል የሚመስል ነገር ሁሉ ለጊዜው ተደመሰሰ፡፡ የሐሰት አምልኮ ይፈጽሙ የነበሩ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ሳምራውያን ተገደሉ። በእነዚህ ዓመታት ይሁዳ በጳለስጢና ውስጥ ከሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ ገናናዋ አገር ሆነች። እስከ ሶርያና ግብፅ ወደብ ድረስ የነበረውን ምድር ሁሉ አሸንፋ ያዘች። ይሁዳ፥ ሰማርያና ገሊላ በአይሁድ ቁጥጥር ሥር ሆኑ።

ዳሩ ግን ይህ ጊዜ የተለያዩ የአይሁድ ካህናት ለመሪነት የሚታገሉበት ጊዜ ነበር፡፡ ሥልጣን ለመያዝ ወይም የበላይ ለመሆን ብሎ አንዱ መሪ ሌላውን ያስገድል ነበር፤ ወይም ሌላኛውን መሪ ለመዋጋት ጦር ያደራጅ ነበር፡፡ የሃይኖትና የፖለቲካ መሪዎችና ቡድኖች እርስ በርሳቸው ይዋጉ ነበር፡፡ የራሳቸውን ጥቅም ከማራመድ ሌላ ስለተራው አይሁዳዊ ምንም ግድ አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህ ተራዎቹ አይሁዳውያን ከአሕዛብ አገሮች ነጻነታቸውን ያገኙ ቢሆኑ እንኳ እነዚህ ዓመታት ለእነርሱ የሰላም ዓመታት አልነበሩም፡፡ ሕዝቡ እነዚህን በሥነ-ምግባር የተበላሹና ሥልጣን የጠማቸውን መሪዎች በማየት የጽድቅና የሰላም መንግሥት የሚያመጣላቸውን የመሲሑን መምጣት እጅግ በጉጉት ይጠባበቁ ነበር፡፡

በእነዚህ ዓመታት በሕዝቡና በአዲስ ኪዳን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩ ሁለት የካህናት ቡድኖች መቋቋም ጀምረው ነበር፡፡ መጀመሪያ፥ የግሪክን ባህል በብዛት ያዛመዱ ካህናት የሚገኙበት ቡድን ነበር፡፡ እነዚህ ሀብታሞችና ዘመናውያን የነበሩት ካህናት የእስራኤልን የሊቀ ካህንነት ስፍራ ይዘው ነበር፡፡ ሀብታሞችና ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ቢሆኑም ብዙዎች አይሁድ ግን አያከብሯቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን ሕዝቡን በኃይል መምራት ችለው ነበር፡ ከአምስቱ የሙሴ መጻሕፍት በስተቀር በየትኞቹም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትና በሙታን ትንሳኤ አያምኑም ነበር፡፡ እዚህ ካህናት የፈሪሳውያን፥ የዮሐንስና ኢየሱስ ቀንደኛ ጠላቶች ነበሩ።

በሁለተኛ ደረጃ የፈሪሳውያንን ቡድን እናገኛለን። ፈሪሳውያን የዕዝራን፥ በኋላም የሃዚዲም የተባለውን ቡድን ባህልና ወግ የተከተሉ አክራሪ የአይሁድ ካህናት ነበሩ፡፡ ፈሪሳውያን የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት ለመከላከል ወይም ለማስጠበቅ የሚቀኑ ወግ አጥባቂዎች ነበሩ፡፡ ስለሆነም ማንም ሰው የብሉይ ኪዳን ሕግጋት እንዳይተላለፍና የእግዚአብሔርን ሕግጋት በመጠበቅ ጻድቅ ሆኖ ከፍርድ እንዲያመልጥ ይጠብቁታል ብለው ያመኑባቸውን በሺህ የሚቆጠሩ ሕግጋት አዘጋጅተው ነበር። የባዕድ የሆነውን ማንኛውንም ነገር ይቃወሙ ነበር። ፈሪሳውያን በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም እንኳ በጣም መንፈሳዊ ሰዎች ናቸው ብለው በሚያምኑባቸው መካከል እጅግ የተከበሩ ነበሩ። ባህላቸውን በመከተል ፈንታ፥ የአሕዛብን መንገዶች ስለተከተሉ ፈሪሳውያን ሰዱቃውያን ይጠሏቸው ነበር። እንደ ብዙዎቹ የሃይማኖት መሪዎች ትኩረታቸው እነርሱ ወይም ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት በማድረጋቸው ላይ ሳይሆን፥ ውጫዊ የሆኑ ሕግጋትን በመጠበቃቸው ላይ ነበር። በመሆኑም መንፈሳዊ ትዕቢት አድሮባቸው ነበር። መጥምቁ ዮሐንስና ኢየሱስ ውጫዊ የሃይማኖት መልካቸውን የሚቃወሙና ለእነርሱም ለመታዘዝ የማይፈልጉ ስለነበሩ ፈሪሳውያን ጠሉዋቸው። ኢየሱስ ክርስቶስን ለመስቀል ሤራውን ያቀነባበሩት እነርሱ ነበሩ። 

4. ጳለስጢና በሮምና በታላቁ ሄሮድስ አገዛዝ ሥር (64-4 ዓ.ዓ.)

አይሁድ ለጥቂት ጊዜ አግኝተውት የነበረውን ነፃነት በ64 ዓ.ዓ. ተቀሙ። የሮም ሠራዊት ወደ ኢየሩሳሌም በመግባት የይሁዳን ሕዝብና መንግሥት ተቋጣጠረ። ሮማውያን ወደ ቤተ መቅደሱ በመግባት ስላረከሱት በአይሁድ ዘንድ ጥላቻን አተረፉ። ሆኖም እነኝሁ ሮማውያን እስከ 70 ዓ.ም. ድረስ የፈለጉትን ጉዳይ እንዲፈጽሙ ለአይሁድ ሰፊ ነጻነት ሰጥተዋቸው ነበር። ሮማውያን ጳለስጢናን እንደ አንዲት ትንሽ ከፍለ ሀገር አድርገው ይቆጥሯት ነበር። አይሁድ ግን በሮማውያንም ሆነ በሌሎች አሕዛብ ቁጥጥር ሥር መሆናቸው አያስደስታቸውም ነበር። ነጻነትን ቀምሰው ነበር፡፡ ስለዚህ ሳይታክቱ ሮማውያንን አሽቀንጥረው ለመጣል ሞከሩ። ተቃወሚ የሆኑ ተዋጊዎች አብረዋቸው እንዲሰለፉ አይሁድን ለመሰብሰብ ጣሩ። በዚህም አይሁዳውያን ሕይወታቸውን አጡ። እንደነዚህ ካሉ የተቃዋሚ እንቅስቃሴዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የ«ቀናተኞች» ቡድን ሳይሆን አይቀርም። (ከደቀ መዛሙርት አንዱ የሆነው ስምዖን የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት ቀናተኛ ነበር፤ ማቴዎስ 10፡4።)

ከይሁዳ በስተደቡብ በኩል ኤዶምያስ የሚባል ስፍራ ነበር። ኤዶማውያን በከፊል አይሁዳውያን በከፊል ደግሞ አሕዛብ (ዐረቦች ወይም ኤዶማውያን) ነበሩ፡፡ አንቲፓተር የተባለው መሪያቸው ከሮማውያን ጋር ወዳጅ ሆነና የአይሁድ ገዥ ሆኖ ተሾመ። ልጁ ታላቁ ሄሮድስ ባዘጋጀው የማታለል ዘዴ ሮማውያን «የአይሁዳውያን ንጉሥ» ብለው እንዲሰይሙት አደረገ። እርሱም ከ40 ዓ.ዓ. ጀምሮ እስከሞተበት እስከ 4 ዓ.ዓ. ድረስ ይሁዳን፥ ሰማርያንና ገሊላን ገዝቷል።

ሄሮድስ ብርቱ መሪ ነበር። በጳለስጢና ብዙ ከተሞችን በድጋሚ ሠርቶ ነበር። ይሁዳን ወደ ብርቱ አገር ለመለወጥ ታላቅ ጦር አደራጀ፡፡ በጳለስጢና ውስጥ ታላላቅ የመታሰቢያ ሐውልቶችን ሠራ። በዋናነት የሚጠቀሰው ሥራው ግን የሄሮድስ ቤተ መቅደስ የሚባለውን ሕንጻ መሥራቱ ነበር። የቤተ መቅደሱ ሥራ የተጀመረው በ20 ዓ.ዓ. ነበር። ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ የቤተ መቅደሱ ሥራ ተጠናቀቀ። ቤተ መቅደሱን የማስዋብ ሥራ ግን እስከ 63 ዓ.ም. ቀጠለ። አይሁድ ሄርድስን ቢጠሉትም፥ እርሱ የሠራውን ቤተ መቅደስ ግን በጣም ይወዱት ነበር። ሄሮድስ አይሁዳውያንና ሃይጎኖታቸው በመላው የሮም ንጉሠ ነገሥት ዝት ውስጥ የተከበሩ እንዲሆኑ አድርጎ ነበር። በዚያን ጊዜ በርካታ አሕዛብ የይሁዲነትን እምነት በመከተል እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሆኑ። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ላይ አሉታዊ የሆነ ንግግር ሲያደርግ አይሁድ የተቆጡት ስለዚህ ነበር (ዮሐንስ 2፡18-19፣ ማርቆስ 14፡57-58)። ይህ ቤተ መቅደስ ሲጓተት ቆይቶ በተጠናቀቀ በ7 ዓመቱ ማለትም በ70 ዓ.ም. በሮማውያን ተደመሰሰ እስከ ዛሬ ድረስም አልተሠራም።

ዳሩ ግን ሄሮድስ ጨካኝ ንጉሥ ነበር። የአመራር ሥልጣኑን ለመጨበጥ ባደረገው ትግል ከ45 በላይ የሆኑ ሰዱቃውያን ካህናትን ገድሏል። ሄሮድስ በዕድሜው እየገፋ ሲሄድ፥ አንድ ሰው ዙፋኔን ይወስድብኛል ብሎ መስጋት ጀመረ። ከዙፋኔ ያፈናቅሉኛል ብሎ ያሰባቸውን አብዛኛዎቹን ልጆቹንና ሚስቱን ገደለ። «የአይሁድ ንጉሥ» በቤተልሔም ተወልዷል የሚለውን ወሬ በሰማ ጊዜ በዚያች ከተማ ውስጥ የነበሩትን የአይሁድ ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። ሄሮድስ በ4 ዓ.ዓ. ተገደለና ልጁ አርኬላዎስ ስፍራውን ወሰደ። ሄሮድስ የሞተው በ4 ዓ.ዓ. ስለሆነ ኢየሱስ የተወለደው ከዚህ በፊት መሆን አለበት። ምናልባትም ከ6-4 ዓ.ዓ. በነበረው ጊዜ ሳይሆን አይቀርም።

ማስታወሻ፡- ኢየሱስ የተወለደበት ጊዜ እኛ እንደምንጠብቀው 1 ዓ.ም. እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ያልሆነበት ምክንያት፥ የክርስቲያን ቀን አቆጣጠር እስከ 526 ዓ.ም. ድረስ ያልተጀመረ በመሆኑ ነው። ይኸውም ዛሬ አብዛኛው የዓለም ክፍል የሚጠቀምበትን የክርስቲያን የቀን አቁጣጠር የጀመረው መነኩሴ የቀን መቁጠሪያውን በሚወስንበት ጊዜ አምስት ዓመት ወደ ኋላ ሄዶ በመጀመሩ ነው።

በእነዚህ ዓመታት በአዲስ ኪዳን የተንጸባረቁ አንዳንድ ነገሮች ተፈጽመው ነበር፤ እነርሱም:-

1. አይሁድ መሢሑ እንዲመጣ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው። የሚጠባበቁት ስለ ኃጢአታቸው መመሞት የመጣ ትሑት መሢሕ አልነበረም፡፡ እነርሱ የሚጠብቁት መሢሕ በጠላቶቻቸው በአሕዛብ ላይ ድልን በመንሣት ለምድራቸው ሰላም የሚያመጣውን ነበር። መጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎቱን በጀመረ ጊዜ መሢሑ እንደተወለደና ቶሎ መግዛት እንደሚጀምር ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን ስለተጠቀመ ወዲያው ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፡፡ ዳሩ ግን  ኢየሱስ አገልግሎቱን የጀመረው ከተጠላው ከገሊላ ስለነበረና እንደ ድል አድራጊ ንጉሥም ሆኖ ስላልመጣ አልተቀበሉት፡፡ በእርሱ ላይ በመቆጣትም በመስቀል ላይ ቸነከሩት፡፡

አይሁድ ነጻ ለመውጣት በውስጣቸው ይቃጠል ነበረው ስሜት በመጨረሻ በ68 ዓ.ም. ፈነዳና በሮም ላይ አመጹ። እጅግ ከባድና አስቸጋሪ የሆነ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ በ70 ዓ.. ኢሩሳሌምና ቤተመቅደሱ ተደመሰሱ፡፡ የይሁዳ መንግሥት ህልውና አከተመ። አዲሲቱ እስራኤል በ1948 ዓ.ም. እስከ ተመሠረተች ድረስ አይሁድ በዓለም ሁሉ ተበትነውና የጥቃት ኢላማ ሆነው ለብዙ አመታት ኖሩ፡፡

2. በሃይማኖት መሪዎች መካከል ያለማቋረጥ ይታይ የነበረው ልዩነት፡- የሰዱቃውያንና የፈሪሳውያን አጀማመር እንዴት እንደነበረና በመካከላቸው የነበረውን ጥላቻ ተመልክተናል፡፡ በአዲስ ኪዳን ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደረ ኤሰነስ በመባል የሚጠራ ሌላ የሃይማኖት ቡድን ነበር። እነዚህም በአይሁድ ካህናትና ሕዝብ የፖለቲካና የሃይማኖት ሥነ-ምግባር የተሰላቹ ወገኖች ነበሩ፡፡ ስለዚህ በበረሃ የሚኖር አንድ አነስተኛ ማህበረሰብ አቋቁመው ነበር። ራሳቸውን እንደ እውነተኛ የእስራኤላ ቅሬታ በማየት በግል ቅድስና ላይ ያተኩሩ ነበር። መሢሑ በሚመጣበት ጊዜ በብርሃን (መልካም) እና በጨለማ (ክፋት) መካከል ስለሚካሄድ ጦርነት ያስተምሩ ነበር። ይህ ቡድን በመጥምቁ ዮሐንስና በኢየሱስ አገልግሎት ላይ ስላሳደረው ተጽዕኖ ምሁራን የተለያየ አስተያየት አላቸው። አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስና ኢየሱስ የዚህ እምነት ክፍል አባሎች ነበሩ ይላሉ፡፡ ይህ ግን የማይሆን ነው፡፡

3. የአዋልድ መጻሕፍት መጻፍ፡- አይሁድ በእነዚህ ዓመታት በአብዛኛው ወደሚመጣው መሢሕ የሚያመለክቱ የተለያዩ መጻሕፍትን ጽፈዋል። አብዛኛዎቹ መጻሕፍት የተጻፉት ከ200 ዓ.ዓ.-100 ዓ.ም. ነበር። አይሁድ እነዚህ መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል ናቸው አላሉም። ነገር ግን መጻሕፍቱን ሰብስበው በአንድ ላይ ጠረዟቸው። በኋላም አይሁድ እነዚህን መጻሕፍት ወደ ግሪክ በተረጐሙ ጊዜ ከጳለስጢና ውጭ የሚኖሩ አይሁዶችና ክርስቲያኖች መጻሕፍቱን ስለወደዷቸው በብሉይ ኪዳን ትርጉሞች ውስጥ አካተቷቸው። ከዓመታት በኋላ የኦርቶዶክስና የሮማ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል አድርገው ተቀበሏቸው። ፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ግን የቀድሞውን የአይሁድ (እንዲሁም የጥንት ክርስቲያኖች) አመለካከት በመያዝ፥ እነዚህ መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል አይደሉም በሚለው አቋም ጸንተዋል። እነዚህን መጻሕፍት በሚመለከት በጥንቃቄ የሚደረግ ጥናት፥ ከቀረው የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል ጋር የማይስማሙ ትምህርቶች እንዳሉባቸው ያረጋግጣል። በኦርቶዶክስና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ከሚከሰቱ ልዩ ትምህርቶች የአብዛኛዎቹ ምንጮች እነዚህ መጻሕፍት ናቸው (ለምሳሌ፡- ዐፀደ ንስሐን የሚመለከተው ትምህርት)።

የውይይት ጥያቄ፥ በ400 ዓመታት የተፈጸሙትን ታሪኮች የሚናገረውን ይህንን ክፍል ከልስ። እነዚህ ታሪኮች በኢየሱስ ዘመን በነበሩት አይሁድ ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሚልክያስ ዐበይት ትምህርቶች

1. ለቃል ኪዳኑ ሕግ መታዘዝ በማይኖርበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የገባነውን ቃል ኪዳን አንፈጽምም። ዳሩ ግን የገባነውን ቃል ኪዳን የምንፈጽመው መታዘዛችን ከንጹሕ ልብና ከትክክለኛ ዝንባሌ ሲሆን ነው። ለእግዚአብሔር የሚቀርብ እውነተኛ አምልኮ ትክክለኛ ድርጊቶችን (ተገቢ የሆኑ ሥርዓቶች) የሚያካትት ብቻ መሆን የለበትም። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ከሚገዛ ልብ የሚመነጭ፥ ለእግዚአብሔር ሕግ የሚታዘዝ፥ ከኃጢአት የነጻ፥ ከቤተሰብና ከጎረቤቶች ጋር ትክክለኛ በሆነ ግንኙነት መኖርን ጭምር የሚያጠቃልል ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰዎች እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ሳይሆን፥ ከአምልኮ ሥርዓት አንጻር ብቻ አምልኮአቸውን ሊያቀርቡ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ግለጽ። ለ) ይህን ዝንባሌ ለማረም ምን ማድረግ ትችላለህ?

2. ጋብቻና ፍቺ (ሚልክያስ 2፡10-16)፡- ከሚስቶቻችን ወይም ከባሎቻችን ጋር በትክክለኛ ግንኙነት ውስጥ ካልሆንን ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ በሆነ ግንኙነት ልንኖር አንችልም። ሚልክያስ ስለ ጋብቻ ሁለት ዐበይት እውነቶችን ያስተምረናል፡- 

ሀ) አንድ ሰው ማንን እንደሚያገባ ወይም ሴት ከሆነች ማንን እንደምታገባ ጠንቅቆ መወሰን አለበት ወይም አለባት። ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ካደረግነው ውሳኔ ቀጥሎ ያለን ከፍተኛ ውሳኔ ማንን እንደምናገባ መወሰን ነው። አንድን ሰው የማያምን ወይም ሥጋዊ ክርስቲያን ብቻ መሆኑን እያወቅን ለቤተሰብ ውርስ፥ ለመልክ፥ ለሀብት ስንል ብናገባ እጅግ አስቸጋሪና ከባድ በሆነ ሕይወት ውስጥ እናልፋለን። ዘይትና ውኃ ሊቀላቀሉ እንደማይችሉ ወይም ብርሃን ከጨለማ ጋር ሊስማማ እንደማይችል ሁሉ በዚህ ዓይነቱ ጋብቻ ውስጥ በፍጹም ስምምነት ሊኖር አይችልም (2ኛ ቆሮንቶስ 6፡14-16 ተመልከት)። በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረን ግንኙነት ይለወጥና እግዚአብሔርን በምንፈልገው መንገድ ሳናገለግለው እንቀራለን። እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ሊያከብር በማይችል ቤተሰብ ውስጥ ስለሚያድጉ ጉዳቱ ለልጆቻችንም ይተርፋል። የእግዚአብሔር ቃል ግልጽ ነው፡- የማያምን ሰው ልናገባ አይገባም። ሚስትን ወይም ባልን ለመምረጥ ዋናው መመዘኛ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ነው። ሥጋዊ የሆነ ክርስቲያን ብናገባ የሚያጋጥመን ችግር የማያምን ሰው በማግባት ከሚገጥመን ችግር የተለየ አይደለም። ዳሩ ግን እንደ እኛው እግዚአብሔርን ለማገልገልና ለመታዘዝ ጥማት ያለውን ሰው ካገባን፥ የቤተሰቡ ውርስ ወይም ውበት ወይም ሀብት ምንም ዓይነት ቢሆን በትዳራችን ውስጥ ስምምነት፥ ሰላምና ፍቅር ይኖራል።

ለ. አንድ ሰው ያገባውን ሰው መፍታት የለበትም። የሚያሳዝነው ነገር አይሁዶች ፍቺ ምንም ችግር የሚያስከትል አይመስላቸውም ነበር። እንዲያውም ኢየሱስ በኖረበት ዘመን አንዲት ሴት እንጀራ ወይም ወጥ ብታሳርር ወይም ጥሩ ምግብ ለማዘጋጀት ባትችል፥ ባሏ ሊፈታት ይችል ነበር። ፍቺ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ በዘዳግም 24፡1-4 የሚገኘውን ጥቅስ እንደ ይለፍ ፈቃድ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር። ለእስራኤላውያን ፍቺ የሚፈቀደው በሕይወታቸው ውስጥ ባለ ኃጢአት ምክንያት ብቻ ነበር (ማቴዎስ 19፡8)። እግዚአብሔር የደገፈው አማራጭ አልነበረም። ጋብቻ ሴትና ወንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገቡት የተቀደሰ ቃል ኪዳን ነው። ይህም እግዚአብሔር የሚያከብረውና የሚባርከው ነው። ጋብቻ ማለት ፍጹም መጣመርና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ልጆችን ማፍራት ማለት ነው። ሚልክያስ ሚስትን «ባልንጀራ» ብሎ ይጠራታል (ሚልክያስ 2፡14)። ይህንን አሳብ የሚገልጠው የዕብራይስጡ ቃል ሁለት እንጨቶች ሊለያዩ በማይችሉበት መንገድ በምስማር ማጣበቅን የሚያመለክት ነው። የእግዚአብሔር ፍላጎት ጋብቻን በምንመሠርትበት ጊዜ ከትዳር ጓደኛችን ጋር በአካል፥ በስሜትና በመንፈስ አንድ እንድንሆን ነው። ፍላጎቶቻችን አንድ ይሆናሉ። ዕቅዶቻችን አንድ ይሆናሉ። ኑሮአችን ፍጹም በሆነ መግባባት፥ በስምምነትና በፍቅር የተመሠረተ ይሆናል። ባል ለሚስቱ ምን ማድረግ፥ ምን ማመን ወይም ምን ማቀድ እንዳለባት ያዛታል ማለት አይደለም። በአንድነትና በኅብረት ይሠራሉ። የእስራኤልና የቤተ ክርስቲያን ባል በሆነው በእግዚአብሔርና ሚስት በሆነችው በእስራኤል ወይም በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ በሙላት ሊፈጸም የሚችለው የዚህ ዓይነቱ ኅብረትና ግንኙነት በተገቢው ሁኔታ ሲኖር ብቻ ነው (ኤርምያስ 2፡1-3፤ 31፡32፤ ሕዝቅኤል 16፤ ሆሴዕ 2፡1-9። እስራኤልና እግዚአብሔር የሚስትና የባል ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ጥቅሶች ስለሆኑ ተመልከታቸው)። አዲስ ኪዳን ፍቺ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳልሆነ ያስተምረናል (ማቴዎስ 5፡31-32፤ 19፡1-10፤ ማርቆስ 10፡1-10፤ ሮሜ 7፡13፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡10-16፥ 39)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ሚስት ወይም ባል በሚመርጡበት ጊዜ የተሳሳተ መመዘኛ የሚጠቀሙት እንዴት ነው? ለ) ወንድ ወይም ሴት የትዳር ጓደኛ በሚመርጡበት ጊዜ ሊጠቀሙበት የሚገባ አንዳንድ መመዘኛዎችን ዘርዝር። ሐ) ከላይ የጠቀስነው እግዚአብሔር ለጋብቻ ያለው ዓላማ የሚፈጸመው በጥቂት ክርስቲያናዊ ጋብቻዎች ብቻ የሚሆነው ለምን ይመስልሃል?

3. ነቢዩ ኤልያስ (ሚልክያስ 4፡5-6)፡- ትንቢተ ሚልክያስ የሚጠቃለለው የነቢዩ ኤልያስን መምጣት እንዲጠባበቁ ለእስራኤል ሕዝብ በመንገር ነው። የዚህ ነቢይ መምጣት «የጌታን ቀን» የሚቀድም ሲሆን፥ የልጆችን ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኤልያስ የእግዚአብሔር ነቢይ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚገልጽና ከሌሉች ነቢያት መካከል አብዛኛዎቹ የተከተሉት ዐቢይ ምሳሌ ነበር። ምክንያቱም፡-

ሀ) ኤልያስ የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎችን በድፍረት በመቃወም፥ ከአባቶቻቸው እምነት ዞር በማለታቸው፥ በሥነ ምግባር ጉድለታቸውና ማኅበራዊ ፍትሕን በማዛባት ኃጢአታቸው ወቅሶአቸዋል። 

ለ) ኤልያስ ንስሐ የመግባትን አስፈላጊነት፥ ይህ ካልሆነ ግን ሰው የእግዚአብሔር ፍርድ እንደሚጠብቀው በግልጽ አስተምሯል። 

ሐ) የኤልያስ መልእክቶች እውነትነት በተአምራት የተረጋገጠ ነበር።

መ) ኤልያስ ከሃይማኖት መሪዎች አንዱ አልነበረም፤ ዳሩ ግን ከተመሠረተው ሃይማኖታዊ መዋቅር ውጭ ሆኖ ሕዝቡ ወደ እውነተኛ ሃይማኖት እንዲመለሱ ለማድረግ ሠራ። ኢየሱስ በተራራ ላይ በተለወጠ ጊዜ ከሙሴና ከኤልያስ ጋር ተገናኝቶ ነበር (ማቴዎስ 17፡1-8)። ሙሴ ሕግን፥ ኤልያስ ደግሞ ነቢያትን የሚወክሉ ሲሆን፥ ሁለቱም የመሢሑን መምጣት የሚያመለክቱ ነበሩ። የእነርሱ መገለጥ ኢየሱስ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የነበሩት የሕግና የነቢያት ፍጻሜ መሆኑን ማሳየት ነበር።

ሚልክያስ በዚህ ስፍራ የተናገረው፥ አንድ ቀን ኤልያስን የሚመስል ሰው እንደሚመጣ ነው። የእርሱ መምጣት ከመጨረሻዎቹ ቀናትና ከመሢሑ መምጣት በፊት ይሆናል።

ሚልክያስ ይኖር በነበረበትና መጥምቁ ዮሐንስ በተነሣበት ዘመን መካከል በነበሩት 400 ዓመታት ውስጥ አይሁድ ስለዚህ ኤልያስ የነበራቸው ወግ ዕድገት እያሳየ መጥቶ ነበር። ይህ የኤልያስ ተምሳሌት ይሁን ወይም የኤልያስ ከሞት ተነሥቶ መምጣት የሚያውቁት ነገር አልነበረም። መጥምቁ ዮሐንስ በመጣ ጊዜ በአለባበስና በመልእክቱ እነርሱ የሚጠብቁትን ኤልያስ ይመስል ነበር። ብዙ ሕዝብ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ የመጡበትና በእርሱ ያመኑበት አንዱ ምክንያት ይህ ነበር። በኋላ ጌታ ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስ ይህን ትንቢት እንደፈጸመ ተናገረ (ማቴዎስ 11፡7-15)።

ብዙ ምሁራን ከዘመናት መጨረሻ ጥቂት ቀደም ብሎ የሚመጣ ሌላ “ኤልያስ” አለ ብለው ያስባሉ። ይህ ሰው ከዘመኑ ፍጻሜ በፊት ሕዝቡን ለንስሐ የሚጋብዝ የመጨረሻ መልእክተኛ ይሆናል። በራእይ 11፡1-12 ከምናያቸው ሁለት ነቢያት አንዱ ኤልያስን የሚመስል ነቢይ ነው ብለው ያስባሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ክርስቲያኖች እነዚህን እውነቶች ሊያውቋቸውና ሊታዘዟቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

የውይይት ጥያቄ፥ ሚልክያስ 1-4 አንብብ። ሀ) አይሁድ ለእግዚአብሔር ያቀረቧቸውን የተለያዩ ጥያቄዎች ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር እነዚህን ጥያቄዎች የመለሰላቸው እንዴት ነበር? ሐ) ከእነዚህ ጥያቄዎችና ትምህርቶች አብዛኛዎቹ በዚህ ዘመን ላሉ ክርስቲያኖች ጠቃሚ የሚሆኑት እንዴት ነው?

እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሰጣቸው ኃላፊነቶች አንዱ፥ ለእግዚአብሔር ሕዝብ «ነቢይ» የመሆን ኃላፊነት ነው። ይህን ስል የእግዚአብሔር ሕዝብ ኃጢአታቸውን እንዲያዩ ማድረግና የተሳሳተ ዝንባሌያቸውን ሁሉ በግልጽ መቃወም አለባቸው ማለቴ ነው። እግዚአብሔር በረከቱን ያለማቋረጥ እንዲሰጥ የእግዚአብሔር ሕዝብ ንጹሕ አምልኮና ኑሮ እንዲኖሩ የማስተማርና የማበረታታት ኃላፊነት አለባቸው። እግዚአብሔር የሕዝቡን ንጽሕና ጠብቆ ለማቆየት በቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንዴት እንደሚጠቀም የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ሚልክያስ ነው።

ሚልክያስ በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ ያሉትን ችግሮች የሚጠቁሙ አጫጭር መልእክቶችን በመጽሐፉ ውስጥ አቅርቧል። ብዙ ጊዜ የሚጀምረው እውነታን ወይም ጭብጥን የያዙ አጫጭር ዐረፍተ ነገሮችን በማቅረብ ሲሆን፥ ሕዝቡ ከእነዚህ ዐረፍተ ነገሮች በመነሣት እግዚአብሔርን ይጠይቃሉ። 

1.1ኛ ጥያቄ፥ እግዚአብሔር እኛን የወደደን እንዴት ነው? (ሚልክያስ 1፡1-5) 

ሰዎች ሁሉ የኢኮኖሚ ችግር ወይም በሥጋቸው ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነገር ሲገጥማቸው የሚሰጡት ምላሽ ከሚከተሉት ሁለት ነገሮች አንዱን ነው:- አንዳንዶች ትከሻቸውን በመስበቅ ይህንን ችግር በሕይወቴ ላይ ያመጣ እግዚአብሔር ስለሆነ ምንም ማድረግ አልችልም ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ወደ አለማመንና የተጣመመ ትርጉም ወደ መስጠቱ በመቻኰል የእግዚአብሔርን ፍቅር በጥያቄ ምልክት ያስቀምጡታል። አይሁድ ተጠራጣሪና ጠማማ በሆን ልባቸው ወደ እግዚአብሔር በመመልከት፥ እርሱ በእርግጥ ይወዳቸው እንደሆነ መጠየቅ ጀምረው ነበር።

እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ፍቅር ለማረጋገጥ ለአይሁድ ታሪካዊ የሆነው የእስራኤልን ጥሪ ያስታውሳቸዋል። የያዕቆብ ዝርያዎች የሆኑትን እስራኤላውያንን የዔሳው ዝርያዎች ከሆኑት ከኤዶማውያን ጋር ያወዳድራቸዋል። ያዕቆብና ዔሳው ወንድማማቾች ቢሆኑም እንኳ እግዚአብሔር የጠራውና ቃል ኪዳን ያደረገው ከያዕቆብ (እስራኤል) ጋር ብቻ ነበር። የአይሁድ ታሪካዊ ጠላቶች የሆኑት ኤዶማውያን እንደሚበለጽጉ ቢያስቡም እንኳ እግዚአብሔር እንደሚፈርድባቸው ተናገረ። በሌላም በኩል እግዚአብሔር እስራኤልን እንደሚባርክ ተናገረ።

ክርስቲያኖችም የተጠሩት በእግዚአብሔር ነው (ሮሜ 8፡28-30)። እግዚአብሒር በዓለም ከሚኖሩ ሕዝቦች መካከል መረጣቸው። ይህ የእግዚአብሔር ፍቅር ልዩ ምልክት ነው። 

2.2ኛ ጥያቄ፥ ካህናት የሆንን እኛ የእግዚአብሔርን ስም ያቃለልነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 1፡6-2፡9)

ከእንስሳት ወገን የሚመደቡት በሬ፥ አህያ ወይም ፍየል ባለቤታቸው ማን እንደሆነ በመረዳት ይታዘዙታል። ከእንስሳት ይልቅ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ሰው ግን ፈጣሪው የሆነውን እግዚአብሔርን አላከበረም፤ አላወቀውምም። እስራኤላውያን ይህንን በተጠራጠሩ ጊዜ እግዚአብሔር ለእርሱ ያሳዩትን አክብሮት የጎደለው ሁኔታ ለካህናትና ለእስራኤላውያን አሳያቸው። ይህንን በተለያዩ መንገዶች ያደርጉ ነበር። በመጀመሪያ፥ ሕዝቡ በካህናት ትእዛዝ ለእግዚአብሔር ተገቢ ያልሆነ መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። ይኸውም ዕውርና ሽባ የሆኑ እንስሳትን ለመሥዋዕት በማቅረብ ነው። ለምድራዊ መሪዎች እንኳ የማይቀርበውን ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ነበር። እግዚአብሔር ይህን የመሰለ እርሱ የማይከበርበት ሥርዓታዊ አምልኮ ከሚፈጸም ከቶውኑ ባይቀርብ መረጠ።

ሁለተኛ፣ ካህናት እግዚአብሔርን ለማገልገል በነበራቸው ዝንባሌ ውስጥ እርሱን አያከብሩም ነበር። ካህናት በቤተ መቅደስ ውስጥ ባለማቋረጥ የሚበራውን መብራት መለኮስ፥ በወርቅ መሠዊያው ላይ ዕጣን ማጠን ወይም እንስሳትን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ታክቶአቸው ነበር።

በሦስተኛ ደረጃ፥ ካህናት ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን መንገዶች ለማስተማር ፈቃደኞች ባለመሆን እርሱን አያከብሩም ነበር።

የእስራኤል መንፈሳዊ መሪዎች የነበሩት ካህናት፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የክህነት ቃል ኪዳን እንዳደረገው እንደ አሮን የልጅ ልጅ እንደ ፊንሐስ አልነበሩም (ዘኁልቁ 25፡10-13)። ስለዚህ እግዚአብሔር የእስራኤልን አምልኮ የመምራት መብት ከእነርሱ በመውሰድ ሊፈርድባቸው ግድ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ ክርስቲያኖችና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ዝንባሌ ሊኖራቸው የሚችለው እንዴት ነው? ምሳሌዎችን ዘርዝር። 

3. 3ኛ ጥያቄ፥ እኛ ሕዝቡ ለቃል ኪዳኑ ታማኞች ያልሆንነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 2፡10-16)

የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ሕዝብ መሆናችንን የምናረጋግጠው በምናምነው ወይም በምንናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን፥ በምንኖረው ኑሮ ጭምር ነው። የክርስቶስ አካል የሆነው የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ አካል ክፍል በምንሆንበት ጊዜ እርስ በርሳችን የምናደርገውን ግንኙነት ለመለወጥ መቻል አለብን። ሁላችንም አንድ ቤተሰብ ነን። የመንፈሳዊ ቃል ኪዳን ሕዝብ ቤተሰብ ደግሞ በሥጋ ከተወለድንበት ቤተሰብ ይበልጥ የላቀና አስፈላጊ ነው።

አይሁድ እግዚአብሔርንና ቃል ኪዳኑን ያቃልሉ ነበር። ይህን ነገር በጋብቻ ሕይወታቸው ውስጥ እንዴት እንደፈጸሙት ለማስረዳት ሚልክያስ ሁለት ምሳሌዎችን ይጠቅሳል፡፡

ሀ) ሕዝቡ ጣዖታትን ከሚያመልኩ አሕዛብ መካከል ሚስቶችን አግብተው ነበር፤ 

ለ) ሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን የገቡላቸውን ሚስቶቻቸውን ፈትተው ነበር። 

የሚልክያስ የመጨረሻ ክፍል በይበልጥ የሚያተኩረው በመጪው ጊዜ ላይ ነው። የእግዚአብሔርን ሕዝብ ክፋትና ኃጢአት የሚናገር ቢሆንም እንኳ መሚሑ ወይም ኤልያስ» በሚመጣበት ጊዜ ስለሚፈጸሙ ነገሮች ይናገራል። 

4. 4ኛ ጥያቄ፥ እግዚአብሔርን ያሰለቸነው በምንድን ነው? (ሚል. 2፡17-3፡6)

ክፉ የሚያደርጉ ሰዎች በጥፋታቸው ላይያዙና ሳይቀጡ ሲቀሩ፥ የእግዚአብሔር ሰዎች የዓለምን ድርጊት መከተልና ተመሳሳይ ክፋት መፈጸም ይጀምራሉ። ጉቦ በመቀበልና በፈተና ጊዜ ከሌሎች መኮረጅ መልካም እንደሆነ በአፋቸው ባይናገሩም እንኳ እግዚአብሔር ክፉ ነው ያለውን ይህን ነገር በተግባር መልካም እንደሆነ ያህል ይለማመዱታል። «ይህን ነገር ሌሎች አድርገው ከተሳካላቸው እኔም ማድረግ አለብኝ። ስለዚህ ጉዳይ እግዚአብሐር ቢገደው ኖሮ ሊቀጣቸው ይገባ ነበር» ብለው ማሰብ ይጀምራሉ። ከዚህም የተነሣ የሥነ-ምግባር መመዘኛቸው የረከሰ ይሆናል።

እግዚአብሔር የዚህን ችግር መፍትሔ ለማግኘት «መልእክተኛውን» እንደሚልክ ይናገራል። መልእክተኛ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በፍርድ ሲመጣ ክፉ የሚያደርጉትን ሁሉ ይቀጣል። የገዝ ሕዝቡ ከዚህ ዓይነት አስተሳሰብና ተግባር ይነጹ ዘንድ በስደት ውስጥ በማሳለፍ ያጠራቸዋል። ከዚያም ሕዝቡ በቃልና በተግባር በመንጻት፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት ያቀርባሉ።

ማስታወሻ፡- ሚልክያስ በንግግርና በማኅበራዊ ፍትሕ ኃጢአት ላይ ያተኮረበትን መንገድ ልብ ብለህ ተመልከት። 

5. 5ኛ ጥያቄ፥ ወደ እግዚአብሔር እንዴት ልንመለስ እንችላለን? (ሚልክያስ 3፡7-12)

እግዚአብሔር ባሕርዩን ለሙሴ በገለጸበት ጊዜ መሐሪና ለቁጣ የዘገየ እንደሆነ ነግሮት ነበር (ዘጸአት 34፡6)። የእግዚአብሔር ባሕርይ ከቶውኑም ሊለወጥ አይችልም። እግዚአብሔር በሙሴ ጊዜ እንደነበረ፥ በሚልክያስም ጊዜ ነበር፤ በእኛ ጊዜም አለ። ስለዚህ እግዚአብሔር ከኃጢአታቸው ይመለሱ ዘንድ ሕዝቡን ጋበዛቸው። 

ንስሐ በተለወጠ አካሂድ ራሱን መግለጥ አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ንስሐ ያለው አመለካከት የአስተሳሰብ ለውጥን ብቻ ሳይሆን፥ የተግባር ወይም የኑሮ ለውጥን ጭምር የሚመለከት ነው። ሚልክያስ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ እንዴት መለወጥ እንዳለባቸው ለእስራኤላውያን ለማሳየት በሕይወታቸው ሊያከናውኑአቸው ከሚገባ ተግባራት አንዱን ጉዳይ ያነሣል፤ ይህም:- አሥራታቸውን ለእግዚአብሔር የመስጠት ጉዳይ ነበር። ሚልክያስ ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን በክበር፥ ከሚያገኙት ነገር ሁሉ ከምርቱና ከገንዘቡ አንድ አሥረኛውን ለእግዚአብሔር እንዲሰጡ ጠየቃቸው። ይህንን ካደረጉ እግዚአብሔር በሥጋ ሊባርካቸውና እነርሱም በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተባረኩ እንደሚባሉ ቃል ገባላቸው። 

6. 6ኛ ጥያቄ፥ በእግዚአብሔር ላይ ደፍረን የተናገርነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 3፡13-4፡3)

በሚልክያስ 2፡17-3፡6 እንዳየነው፥ እስራኤላውያን ክፉ የሚሠሩ እየበለጸጉ ሲሄዱ ጻድቅ መሆን የተሻለ ዋጋ አለውን? ብለው የጥርጥር ጥያቄ መጠየቅ ጀምረው ነበር። ስለዚህ ከጽድቅ አኗኗር ይልቅ በክፋት መኖር እንደሚሻል በመገመት ኃጢአተኞች ሆነው መኖር እንደሚገባቸው ማሰብ ጀመሩ። 

እግዚአብሔር የሚያደርጉትን ሁሉ እንደሚያስታውስ በመንገር እስራኤላውያንን ያስጠነቅቃቸዋል። በቅድስና በመኖር እግዚአብሔርን ያከበሩ ሰዎች ያደረጉትን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር በመዝገብ ጽፎታል፤ በጊዜውም ይሸልማቸዋል። እግዚአብሔርን አናከብርም ብለው ዓለምን የተከተሉትን ሁሉ እንደሚቀጣቸው ተናግሮአል።

«የጽድቅ ፀሐይ» የሆነው መሢሑ ሲመጣ፥ ክፉ ሰዎች ሁሉ በእሳት ውስጥ እንዳለ ገለባ ይቃጠሉና ጻድቃን ፈውስ አግኝተው ደስታና ሐሤትን ያደርጋሉ። 

7. ለሕዝቡ የተሰጠ የመጨረሻ ምክር (ሚልክያስ 4፡4-6)

የብሉይ ኪዳን የሚጠቃለለው ሰዎች ለእግዚአብሔር ሕግጋት እየታዘዙ እንዲጓዙ በመምከር ነው። ከሙሢሑ አስቀድሞ የሚመጣውን ኤልያስን መጠባበቅ ነበረባቸው። ኤልያስ የሕዝቡን ልብ ወደ ቀደምት አባቶቻቸው በመመለስ የምድሪቱን መንፈሳዊ ሁኔታ ለመለወጥ ይፈልግ ነበር። በቤተሰብ መካከል አንድነትን ያመጣ ነበር። ዳሩ ግን ይህንን የማይቀበሉ ሁሉ ከባድ ፍርድ ያገኛቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በትንቢተ ሚልክያስ ውስጥ የሚገኙትን ዐበይት እውነቶች ዘርዝር። ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ለሚገኙ ምእመናን መንፈሳዊ ትምህርት ለማስተማር፥ የትንቢተ ሚልክያስ ሰባት ክፍሎች እያንዳንዳቸው ሊጠቅሙ የሚችሉባቸውን ግልጽ መንገዶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሚልክያስ አስተዋጽኦ እና ዓላማ

የትንቢተ ሚልክያስ አስተዋጽኦ

የውይይት ጥያቄ፥ ) ስለሚልክያስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ለ) በዚህ ስፍራ ስለ ሚልክያስ የተጠቀሱትን ዐበይት እውነቶችን ዘርዝር።

ሚልክያስ የተጻፈው እጅግ ልዩ በሆነ መንገድ ነበር። በመጀመሪያ አብዛኛው የመጽሐፉ ክፍል የተጻፈው ሚልክያስ እግዚአብሔርን ወክሎ እንደሚናገር ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ራሱ ለእስራኤላውያን በቀጥታ እንደሚናገር ሆኖ ነው። በመጽሐፉ አብዛኛ ክፍል ውስጥ እግዚአብሔር ለአይሁድ የሚናገረው «እኔ» የሚለውን ተውላጠ ስም በመጠቀም ነው።

በሁለተኛ ደረጃ፣ ሚልክያስ በጽሑፉ የተጠቀመው ልዩ የሆነ የአጻጻፍ ሥልትን ነው። አብዛኛዎቹ መልእክቶቹ የሚከተለውን አደረጃጀት የተከተሉ ናቸው፡-

ሀ. እግዚአብሔር ስለ ራሱ ወይም ስለ እስራኤላውያን መንፈሳዊ እውነትን ይናገራል።

ለ. ቀጥሉ እስራኤላውያን በዚህ የእግዚአብሔር ንግግር ላይ ተመሥርተው የሚያነሡት ጥያቄ በመላ ምት ይቀርባል። 

ሐ. እግዚአብሔር፥ ጥያቄአቸው ትክክል አለመሆኑን በሚያስረዳ መንገድ ለእስራኤላውያን ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

መ. እግዚአብሔር ለተናገረው ቃል ማረጋገጫ ያቀርባል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሚልክያስ 1፡2-5 አንብብ። በዚህ ክፍል ውስጥ እነዚህ አራት ደረጃዎች የሚታዩት እንዴት ነው?

ትንቢተ ሚልክያስ መልእክቱን የመሠረተባቸውን ስድስት ስብከቶች ይዟል። እነዚህ ስድስት መልእክቶች መልሶችን የያዙ ጥያቄዎች ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ። 

እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ያቀረበው ክስ

1ኛ ጥያቄ፡- እግዚአብሔር እኛን የወደደን እንዴት ነው? (ሚልክያስ 1፡1-5)።

መልስ፡- ሀ) እግዚአብሔርን እስራኤልን የራሱ አድርጎ መርጧታል፤ ለ) እግዚአብሔር እስራኤልን ይጠብቃታል። 

2ኛ ጥያቄ፡- እኛ ካህናት የእግዚአብሔርን ስም የናቅነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 1፡6-2፡9)።

መልስ፡- ሀ) ካህናቱ እግዚአብሔርን አያከብሩም፤ ለ) ካህናቱ ለእግዚአብሔር ተገቢ ያልሆነ መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ሐ) ካህናቱ ለእግዚአብሔር ስም ክብር አይሰጡም፤ መ) ካህናቱ ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ አያስተምሩም። 

3ኛ ጥያቄ፡- እኛ እስራኤላውያን ለቃል ኪዳኑ ታማኞች ያልሆንነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 2፡10-16)። 

መልስ፡- ሀ) ሕዝቡ ሌሎች አማልክትን ከሚያመልኩ አሕዛብ መካከል ሚስቶችን አግብተዋል፤ ለ) ሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት በቃል ኪዳን ያገቧቸውን ሚስቶቻቸውን ፈትተዋል። 

እግዚአብሔር በፍርድና በመቤዥት ወደ ሕዝቡ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል 

4ኛ ጥያቄ፡- እግዚአብሔርን ያሰለቸነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 2፡17-3፡6)።

መልስ፡- ሀ) ሕዝቡ እግዚአብሔር ጻድቅ አይደለህም ብለው ይከሱት ነበር፤ ለ) እግዚአብሔር በቃላቸውና በተግባራቸው ታማኝ ባልሆኑት ሕዝቡ ላይ ፍርድን ያመጣና ይቀጣቸዋል፤ ያነጻቸዋልም። 

5ኛ ጥያቄ፡- ወደ እግዚአብሔር መመለስ የምንችለው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 3፡7-12)።

መልስ፡- ሀ) ከእግዚአብሔር መስረቅን በማቆምና ለእግዚአብሔር መክፈል የሚገባውን አሥራትና መባ በመስጠት። ለ) ለእግዚአብሔር በሚሰጡበት ጊዜ እርሱ በረከቱን ያፈስላቸዋል። 

6ኛ ጥያቄ፡- በእግዚአብሔር ላይ በድፍረት የተናገርነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 3፡13-4፡3)።

መልስ፡– ሀ) እግዚአብሔርን ማገልገል ምንም ጥቅም የለውም ብላችኋል፤ ለ) የሚያከብሩኝንና የሚታዘዙኝን አስባቸዋለሁ፤ ደግሞም እሸልማቸዋለሁ፤ ሐ) እኔን ባለመታዘዝ የማያከብሩኝን እቀጣቸዋለሁ፤ መ) «የጽድቅ ፀሐይ» በምትወጣበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር በረከትና ፍርድን ያመጣል። 

7. ለሕዝቡ የተሰጠ የመጨረሻ ግሣጹ (ሚልክያስ 4፡4-6)

ሀ) የእግዚአብሔርን ሕግጋት መጠበቅን አስታውሱ፤ ለ) ሕዝቡን ለመሢሑ ለማዘጋጀት ከመሢሑ በፊት የሚመጣውን ኤልያስን ጠብቁ። 

የትንቢተ ሚልክያስ ዓላማ

የብሉይ ኪዳን ትምህርቶች እምብርት ቃል ኪዳንን የሚመለከት አሳብ ያዘለ ነው። እግዚአብሔር በጸጋውና በፍቅሩ የቃል ኪዳኑ ሕዝብ እንዲሆኑ እስራኤላውያንን መረጣቸው። ይህም የተጀመረው እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን ነበር። ይህ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ለአይሁድ በሲና ተራራ ቃል ኪዳን በሰጣቸው ጊዜ ሊስፋፋ ችሏል። ይህም ከካህናት፥ በኋላም ከዳዊት ጋር የተደረገውን ቃል ኪዳን ይጨምር ነበር። ቃል ኪዳኖቹ የእግዚአብሔርን ፍቅርና ጸጋ የሚያስረዱ ናቸው። የቃል ኪዳኑ ጀማሪ እርሱ ሲሆን፥ ሕዝቡ በቃል ኪዳኑ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ነገር ባላደረጉ ጊዜ እንኳ ሊለውጠው አልፈለገም። ይሁን እንጂ ብሉይ ኪዳን የሚያስተምረን በቃል ኪዳኑ ውስጥ የተጠቀሱትን በረከቶች ለመቀበል ለቃል ኪዳኑ ታዛዥ መሆናቸው አስፈላጊ እንደ ነበር ነው። ይህ መታዘዝ በውጫዊ ሥርዓት ብቻ የሚሆን ሳይሆን፥ ከሕዝቡ ልብ የሚመነጭ መሆን ነበረበት።

እግዚአብሔር ሚልክያስን በጠራው ጊዜ ሕዝቡ በቃል ኪዳኑ ውስጥ የታዘዙትን አብዛኛዎቹን ሥርዓቶች እየተከተሉ ነበር። ዳሩ ግን እግዚአብሔርን ከልባቸው አያመልኩትም ነበር። መሥዋዕቶችንም ያቀርቡ ነበር፤ ነገር ግን ለእነርሱ የማይጠቅሙትን ሽባ ወይም ዕውር እንስሳት በመስጠት እግዚአብሔርን ያቃልሉት ነበር። እንደ ቀደምት አባቶቻቸው ጣዖትን አያመልኩም ነበር፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ የመሆናቸውን እውነታ ለመቀበልና ልባቸውን ለመለወጥ አይፈቅዱም ነበር።

ስለዚህ እግዚአብሔር ነቢዩን ሚልክያስን ማስጠንቀቂያ የሚሰጣቸው የመጨረሻ መልእክተኛ አድርጎ ላከው። ሚልክያስ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር በገባው ቃል ኪዳን ላይ ያተኵር ነበር። ይህ ለእስራኤላውያን የእግዚአብሔር ፍቅር ማረጋገጫ ነበር። ካህናቱ በእግዚአብሔር ፊት አገልግሎታቸውን የሚፈጽሙበት መሠረት ነበር። ሚልክያስ የቃል ኪዳኑ ውጤት በእስራኤላውያን ሕይወት ምን መሆን እንዳለበት ተመለከተ። የቃል ኪዳኑ እምብርት ወደ እግዚአብሔር የሚመለከት ትክክለኛ ዝንባሌ ነበር። ቃል ኪዳኑ እግዚአብሔርን እንደ ቅዱስነቱ በክበርና በሙሉ ሕይወታቸው እርሱን ለማክበር ባላቸው ፍላጎት ላይ መመሥረት ነበረበት። ያ አክብሮት ለእግዚአብሔር ወደሚቀርብ እውነተኛ አምልኮ ሊመራቸውና ለእግዚአብሔር የማይረባውን ሳይሆን ከሁሉም የተሻለውን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ሊያደርጋቸው ይገባ ነበር። መሪዎችና ሕዝቡ እርስ በርስ በመከባበር እንዲነጋገሩና በተለይም ለሚስቶቻቸው የገቡትን ቃል ኪዳን በመጠበቅ ከመፋታት እንዲታቀቡ ሊያደርጋቸው ይገባ ነበር። በእግዚአብሔር የማያምኑትን እንዳያገቡ እምነታቸውን በንጽሕና የመጠበቅ ፍላጎት ሊያሳድርባቸው ይገባ ነበር። ይህንንም እግዚአብሔር ከሰጣቸው ነገር አሥራታቸውን በታማኝነት በመስጠት ማረጋገጥ ነበረባቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአዲስ ኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ቃል ኪዳን ከዚህ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ በመሆናችን ምክንያት በሕይወታችን ሊለወጡ የሚገባቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ሐ) ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ እንደሆኑ የሚናገሩባቸው፥ ዳሩ ግን ለዚህ ቃል ኪዳን ባለመታዘዝ እግዚአብሔርን የማያስከብሩባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

ነቢዩ ሚልክያስ በእግዚአብሔር የተጠራው አይሁድ ለቃል ኪዳኑ ታዛዦች ይሆኑ ዘንድ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ነበር። እግዚአብሔር በሚልክያስ በኩል አይሁድን ስለ ኃጢአታቸው ሊወቅሳቸውና ወደ እርሱ እንዲመለሱ ሊጠራቸው ፈልጎ ነበር። ሚልክያስ ሕዝቡን፥ በተለይም የሃይማኖት መሪዎችን መሢሑ በሚመጣበት ጊዜ ስለ ኃጢአታቸው እንደሚፈርድባቸውና ለእግዚአብሔር ታማኞች የሆኑትን ደግሞ እንደሚሸልማቸው ያስታውሳቸዋል።

ልዑል አባት፥ የፍጥረታት ሁሉ ጌታና የቃል ኪዳኑ መሥራች የሆነው እግዚአብሔር ሊከበር፥ ከእርሱ ጋር ግንኙነት የሚያደርጉ ሰዎች ደግሞ በቃል ኪዳኑ ውስጥ በተመለከተው መንገድ በተገቢ ሁኔታ ግንኙነት ሊያደርጉ ይገባል (ዘጸአት 20፡12፤ ዘዳግም 31፡1-10)። እግዚአብሔር ሕዝቡ ንስሐ እንዲገባና ከእርሱ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን እንዲያድሱ ጥሪ ያደርጋል። በዚህ መሠረት፡-

ሀ) የተበላሽውን የክህነት አገልግሎት ማንጻት ነበረባቸው፤ 

ለ) ሥርዓታዊውን አምልኮ ሐሤትና ደስታ ወደሞላበት አምልኮ መለወጥ ነበረባቸው፤ 

ሐ) አሥራት በመክፈልና መሥዋዕት በማቅረብ በኩል የሚታዩትን ድክመቶች ማስተካከል ነበረባቸው፤ 

መ) ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ተገቢ የሆነ ግንኙነት ሊያደርጉ ይገባቸው ነበር፤ 

ሠ) ከጎረቤቶቻቸው ጋር በማኅበራዊ ፍትሕ መኖር ነበረባቸው።

የትንቢተ ሚልክያስ መልእክት ውጤት ምን እንደነበር አልተነገረንም። በቅድሚያ ሕዝቡ መጠነኛ የሆነ ምላሽ ሳይሰጡና ንስሐ ሳይገቡ አልቀሩም። ዳሩ ግን አይሁድ ብዙም ሳይቆዩ ወደ ቀድምው ዝንባሌያቸው ተመለሱ። ኢየሱስ በምድር ላይ ይመላለስ በነበረ ጊዜ ሕዝቡ በተለይም ፈሪሳውያን የዚህ ዓይነት ዝንባሌ ነበራቸው። የልባቸው ዝንባሌ ትክክል ባይሆንም እንኳ ይከተሉት የነበረው ሥርዓታዊ አምልኮ እግዚአብሔርን ደስ እንደሚያሰኝ አስበው ነበር። ኢየሱስ ስለነበራቸው ዝንባሌ በግልጽ እየወቀሳቸው፥ በልባቸው ተለውጠው እግዚአብሔርን በተገቢው ሁኔታ እንዲያመልኩ በነገራቸው ጊዜ ተቃወሙት፤ በመጨረሻም ሰቅለው ገደሉት። ይህ ብዙ ጊዜ በግልጽ የሚታይ እውነታ ነው። ለትምህርቶቻቸውና ለሥርዓተቸው ጥብቅና ለመቆም የሚፈልጉ የሃይማኖት መሪዎች ሁልጊዜ እውነትን ይቃወማሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በሚልክያስ ዘመን የነበሩት ካህናትና በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ፈሪሳውያን ያደርጉት እንደነበረው በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ዝንባሌ ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚወቀሱበትን ማንኛውንም ስሕተት ላለመቀበል የሚቃወሙትና ከዚህ ቀደም የለመዷቸውን ሥርዓቶች ለመጠበቅ የሚጥሩት ለምን ይመስልሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሚልክያስ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት

ትንቢተ ሚልክያስ በዕዝራና በነህምያ ታሪክ ዘመን አካባቢ የተጻፈ ነው። ከትንቢተ ሐጌና ዘካርያስ ጥናታችን እንደሚታወሰው እነዚህ ሁለቱ፥ ነቢያት አይሁዶች ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ ያበረታቱ ነቢያት ነበሩ። በመጨረሻ በ516 ዓ.ዓ. የቤተ መቅደሱ ሥራ ተጠናቀቀ። አይሁድ የተሰጧቸውን የተስፋ ቃላት ፍጻሜ ይጠባበቁ ነበር። መሢሑ እንደሚመጣ ቢጠባበቁም፥ መምጣቱን በሚመለከት አንዳችም ምልክት አልታየም ነበር። ከእግዚአብሔር በረከትን በመቀበል በቁሳዊ ነገሮች እንደሚበለጽጉ አስበው ነበር፤ ዳሩ ግን እስካሁን ድረስ ድሆች ነበሩ። ከአሕዛብ መንግሥታት ነፃ ለመሆንና ራሳቸውን ለመቻል ፈልገው ይጠባበቁ ነበር፤ ነገር ግን እስካሁን ድረስ በፋርስ መንግሥት ውስጥ እጅግ አነስተኛና ከቁጥር የማይገባ አንድ ክፍለ ሀገር ነበሩ፡፡ ታላቅ ሕዝብ እንደሚሆን አስበው ነበር፤ ነገር ግን ብዙ አይሁድ ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ። የቤተ መቅደሱን ሥራ ለመጨረስ ከነበራቸው የስሜት ምጥቀት በፍጥነት በመውረድ፣ ተስፋቸው ተሟጥጦ ቅንነት በራቀው የአሳብ ማዕበል ውስጥ ተዘፈቁ። ለእግዚአብሔር የነበራቸውን መንፈሳዊ ግለት አጡ። እግዚአብሔር እንደሚወዳቸው ማሳብ ተሳናቸው።

በ458 ዓ.ዓ. በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ችሮታ ካህኑ ዕዝራ ከብዙ ሺህ አይሁድ ጋር ወደ አገሩ ተመለሰ። በእርሱ መንፈሳዊ አመራር የእግዚአብሔር ሕዝብ ንስሐ ለመግባትና ለሕጉ በመታዘዝ ለመኖር ተነቃቁ።

ከአሥራ ሦስት ዓመታት በኋላ፥ ማለትም በ445 ዓ.ዓ. ነህምያ ከብዙ አይሁዶች ጋር ተመለሰና የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ሠራ። ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን ይሠሩ ዘንድ እንዳስቻሉት እንደ ሐና ዘካርያስ፥ ነህምያ ሕዝቡን ሁሉ ለማሳመንና የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እንዲሠሩ ለማድረግ ችሎ ነበር። ከዚህም በላይ ነህምያ በይሁዳ አንዳንድ ተሐድሶዎችን ለማምጣት ችሎ ነበር። ከእነዚህም መካከል ድሆችን መርዳት (ነህምያ 5፡2-13)፥ ድብልቅ ጋብቻዎችን ማስቆም፥ ሰንበትን መጠበቅ (ነህምያ 10፡30-31) መባቸውንና አሥራታቸውን ወደ ቤተ መቅደስ ማምጣት (ነህምያ 10፡37-39) ይገኙባቸዋል። በዚህ ጊዜ ሚልክያስ ከነህምያ ጋር እየሠራ ነበር ለማለት ይቻላል።

በ433 ዓ.ዓ. ነህምያ ከንጉሥ አርጤክስስ ጋር ለመሥራት ወደ ፋርስ ተመለሰ። እርሱ በሌለበት ሕዝቡ እንደገና በኃጢአት ወደቁ። ነህምያ ከብዙ ዓመታት በኋላ በተመለሰ ጊዜ ሕዝቡ አሥራታቸውን እንደማይከፍሉ፥ ሰንበትን እንደማያከብሩ፥ ከአሕዛብ ጋር እንደሚጋቡና ካህናቱም ምግባረ ብልሹዎች እንደሆኑ ደረሰበት (ነህምያ 13፡7-31)። በትንቢተ ሚልክያስ ከተጠቀሱት አንዳንድ ተመሳሳይ ኃጢአቶች መካከል እነዚህ ይገኙባቸዋል (ሚልክያስ 1፡6-14፤ 2፡14-16፤ 3፡8-11)። ስለዚህ ሚልክያስ ያገለገለው ነህምያ ወደ ፋርስ ሄዶ ሳለ ወይም በዚሁ ጊዜ ከነህምያ ጋር ሳይሆን አይቀርም።

ኃጢአት እንደ ማግኔት በመሆኑ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያለማቋረጥ ይስባል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች መንፈሳዊ ግዴለሽነትንና በኃጢአት የመውደቅ ዝንባሌን ያለማቋረጥ ካልተዋጉ በስተቀር፥ አያሌ ጊዜ ሳይፈጅ መንፈሳዊ ግለታቸውንና ቅድስናቸውን ይጥላሉ። በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ራስ ላይ ከተጣሉት ብዙ ዐበይት ኃላፊነቶች አንዱ የእዚአብሔር ሕዝብ ለኢየሱስ የነበራቸውን የመጀመሪያ ፍቅር እንዲጠብቁና ዓለምን ከመምሰል ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት የንጽሕና ሕይወት እንዲኖሩ ማበረታታት ነው። ነህምያና በሚልክያስ ጊዜ በእስራኤላውያን የተፈጸመው ነገር ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ደግሞ ሊፈጸም ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በኃጢአት የመውደቅ ዝንባሌ በምታውቃቸው ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው? ለ) ይህን ዝንባሌ በራስህ ሕይወት ውስጥ ያየኸው እንዴት ነው? ሐ) ይህን ነገር ለማሸነፍ ምን እያደረግህ ነው? መ) የቤተ ክርስቲያን መሪ እንደ መሆንህ ሰዎች ለእግዚአብሔር ያላቸው መንፈሳዊ ግለት ከፍተኛ እንዲሆንና የቤተ ክርስቲያን አባሎች በኃጢአት እንዳይወድቁ ምን ማድረግ ትችላለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ትንቢተ ሚልክያስ መግቢያ

የብሉይ ኪዳንን የትንቢት መጻሕፍት በምናጠናበት ጊዜ ሁሉ ሕዝቡ የወደፊቱን ነገር በተስፋና በጉጉት ይጠብቁ እንደነበር ተመልክተናል። ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ሕዝብ በስደትና በመከራ ውስጥ ቢሆኑ ወይም አይሁድ በምድር ዙሪያ ሁሉ ተበትነው የሚኖሩ ቢሆኑም የእግዚአብሔር ቃል የወደፊቱን ነገር እንዲመለከቱ ያበረታታቸው ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ የወደፊት ተስፋዎች መካከል አይሁድ ይጠብቁት የነበረው ዋና ተስፋ የመሢሑን መምጣት ነበር። የእስራኤል ንጉሥና የምድር ሁሉ ገዥ እንደመሆኑ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉንም ነገር ያስተካክላል። ይህ ቃል ኪዳን በጨለማ ውስጥ እንደሚበራ ብርሃንና በትልቅ ችግር ውስጥ እንደሚሰማ አበረታች የተስፋ ቃል ነበር።

የመጨረሻው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ትንቢተ ሚልክያስ ስለ መሢሑ መምጣትና ከእርሱ በፊት ስለሚመጣው ኤልያስ የተስፋ ቃል በማስተላለፍ ይጠቃለላል። እግዚአብሔር ከሚልክያስ በኋላ አዳዲስ ትንቢቶቹን የሚናገሩ ነቢያት አልላከም። እነዚህም ዓመታት 400 የጸጥታ ዓመታት በመባል ይታወቃሉ። በእነዚህ 400 ዓመታት አይሁዶች የተሰጣቸውን ተስፋ ፍጻሜ ሲጠባበቁ ኖረዋል። ከ400 ዓመታት በኋላ ግን በሚልክያስ እንደተተነበየው በድንገት በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ የተባለለት መጥምቁ ዮሐንስ የነቢያት መልእክት ይፈጸም ዘንድ የጊዜውን መድረስ በሚመለከት አዋጅ መናገር ጀመረ። መሢሑ መጣ። በብሉይ ኪዳን ሲጠበቁ የነበሩ ነገሮች በሙሉ መፈጸም ነበረባቸው። የሚያሳዝነው ነገር፥ መሢሑ፥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ሕዝቡ ሊቀበሉት አልተዘጋጁም ነበር፤ ስለዚህ ሳይቀበሉት ቀሩ።

አዲስ ኪዳን ይህንን የተስፋ ላይ ሐረግ ከብሉይ ኪዳን ቀጥሎአል። ዳሩ ግን የመጀመሪያ አመጣጡን ከልብ በማመን ምትክ ኢየሱስ ዳግም በሚመለስበት ጊዜ ያተኩራሉ። በዚያን ጊዜ በፍጥረታት ሁሉ ላይ በመግዛት፥ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተጻፉትን የበረከት ተስፋዎች በሙሉ ይፈጽማል። የኢየሱስ ክርስቶስን መመለስ የሚመለከተው ተስፋ ለእኛ ለክርስቲያኖች በስደት ጨለማ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ ብርሃን የሚሆነን «ተስፋ» ነው። ክርስቲያኖች በኢየሱስ ዳግመኛ መምጣት ቃል እርስ በእርስ እንድንጽናና ታዘናል (1ኛ ተሰሎንቄ 4፡13-18)። ክርስቲያኖች በዚህ በሚያልፍ የዓለም ነገር ላይ እምነታቸውንና ተስፋቸውን መጣል ጨርሶ የለባቸውም። ዜግነታቸው ሰማያዊ መሆኑን፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት በመጓዝ ላይ ያሉ መናንያን መሆናቸውን፥ የእግዚአብሔር በረከት በሙላት የሚፈጸመው በሰማይ እንደሆነ ዘወትር ሊያስታውሱ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች በከባድ ችግርና መከራ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ኢየሱስ ሲመለስ የሚያገኙትን ብሩህ ፍጻሜ፥ ተስፋ ማድረግ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ለ) ኢየሱስ ሲመለስ የሚፈጸሙልንን አንዳንድ የተስፋ ቃሎች ዘርዝር? ሐ) ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ አገራቸው በሚደርሱበት ጊዜ ሊፈጸምላቸው ከተገባላቸው ተስፋ ይልቅ በዚህ ምድር ሊቀበሏቸው ባሉት በረከተች ላይ ብዙ ጊዜ የሚያተኩሩባቸውን አንዳንድ መንገዶች ዘርዝር። 

የትንቢተ ሚልክያስ ጸሐፊ

ምንም እንኳ መጽሐፈ ዜና መዋዕል፥ ዕዝራና ነህምያ ከሚልክያስ በኋላ ሊጻፉ ቢችሉም፥ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል የጻፈ የመጨረሻ ነቢይ ሚልክያስ ነበር። በመጽሐፉ ጸሐፊ ማንነት ላይ ምሁራን የተለያዩ አሳቦች አሏቸው። ስለዚህ ጉዳይ ሁለት ዐበይት አመለካከቶች አሉ፡-

1. በዕብራይስጥ «ሚልክያስ» የሚለው ስም ትርጉም «መልእክተኛዬ» ማለት ነው። ይህ ቃል አንዳንድ ጊዜ ነቢያትን፥ ካህናትንና መላእክትንም እንኳ ለመግለጥ የሚጠቅም ነበር። ስለዚህ ብዙ ምሁራን ሚልክያስ 1፡1 «የእግዚአብሔር ቃል ለእስራኤል በመልእክተኛው በኩል መጣ» ተብሎ መተርጐም አለበት ይላሉ። ይህ መልእክተኛ (ነቢይ) ማን እንደሆነ አይታወቅም። በአብዛኛዎቹ የነቢያት መጻሕፍት በተለየ ሁኔታ፥ ነቢዩ መቼ እንደኖረና የእግዚአብሔርን ቃል እንደተናገረ ወይም የማን ልጅ እንደሆነ የሚገልጹ የተለመዱ እውነቶች አልተሰጡም። ይህም ትንቢተ ሚልክያስ የተጻፈው በአንድ ባልታወቀ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነው የሚለውን አሳብ ይደግፋል። የሴፕቱዋጀንት ትርጉም የሚልክያስን ስም ሳይጠቅስ የእግዚአብሔር ቃል በመልእክተኛው በኩል እንደተላለፈ አድርጎ ይህን ጥቅስ ይተረጉማል።

2. ሌሎች ምሁራን ደግሞ ጸሐፊው “ሚልክያስ” ተብሎ ከመጠራቱም፥ መልእክቶቹን ያሰፈረው ራሱ ሚልክያስ ወይም ሌላ አንድ ጸሐፊ ነው ይላሉ። ከዚህ ሌላ ስለሚልክያስ የምናውቀው ምንም ነገር የለም። የአይሁድ ትውፊት ሚልክያስ የኖረው በሐጌና በዘካርያስ ዘመን እንደነበር ይናገራል። ሚልክያስ የታላቁ ምኩራብ የጸሐፍት ጉባኤ አባላትና ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ለአይሁድ የሃይማኖት ሕይወት እውቅና ለመስጠት እገዛ ካደረጉት የአይሁድ መሪዎች አንዱ ነበር ይላሉ። 

ትንቢተ ሚልክያስ የተጻፈበት ጊዜ

ሚልክያስ ይህን መጽሐፍ መቼ እንደጻፈው ስለማይናገር በይሁዳ ያገለገለው መቼ እንደሆነ መጽሐፉን በመመርመር መረጃ ማግኘት አለብን። አሁንም ምሁራን በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸው አሳብ የተለያየ ነው። አንዳንዶች ሚልክያስ የኖረውና ያገለገለው ዕዝራና ነህምያ በኖሩበት ዘመን ነው ይላሉ (450-430 ዓ.ዓ.)። በሚልክያስና በነህምያ ዘመን የነበረውን የአይሁዶች መንፈሳዊ ሁኔታ ብንመረምር ተመሳሳይ ነበረ። ለምሳሌ በሦስቱም መጻሕፍት ማለት በዕዝራ፥ በነህምያና በሚልክያስ ከአሕዛብ ጋር የተደረጉ ጋብቻዎች ችግር፥ ድሆችን ያለ አግባብ መበደል፥ ሰንበትን ባለማክበር ለሕግ ተገዥ አለመሆንና የቤተ መቅደሱ አገልግሎት ችላ መባል በጋራ ከተጠቀሱ ነገሮች ጥቂቶቹ ነበሩ።

ሌሎች ምሁራን ግን የዕብራይስጡን የአጻጻፍ ስልትና ሌሎች የቋንቋ ጉዳዮችን በመመልከት ሚልክያስ የተጻፈው ቀደም ሲል ዕዝራ ወደ ይሁዳ ከመምጣቱ በፊት ነው ይላሉ፤ የተጻፈውም ከ500-475 ዓ.ዓ. ነው ብለው ያስባሉ። 

ትንቢተ ሚልክያስ የተጻፈው ከ475-425 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ነው ማለት ከሁሉም የተሻለ አሳብ ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ዘካርያስ 1-14

ብዙ ሰዎች እግዚአብሔር ትንቢትን የሰጠው ወደፊት ምን እንደሚሆን እንድናውቅ ነው ብለው ያስባሉ። ስለዚህ የትንቢትን መጻሕፍት የሚያጠኑት በከፍተኛ ጉጉት ነው። ወደፊት በመካከለኛው ምሥራቅ ምን እንደሚሆን ለማወቅ፥ ወይም ሩስያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሳ እንደሆነ ወይም በመጨረሻዎቹ ቀናት ከእስራኤል ጋር የሚዋጉት አገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ በመጓጓት ያጠናሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ አንዳንድ ክርስቲያኖች ትንቢትን በተመለከተ የዚህ ዓይነት አመለካከት ሲጠቀሙ ያየኸው እንዴት ነው?

እግዚአብሔር የትንቢት መጻሕፍትን መልእክት የሰጠን ወደፊት ምን እንደሚሆን የማወቅ ፍላጎታችንን ለማርካት አይደለም። ትንቢት የተሰጠው የእግዚአብሔርን ሕዝቦች በተለይም ደግሞ በስደት ውስጥ የሚኖሩትን እግዚአብሔር የበላይ ተቆጣጣሪ መሆኑን በማስተማር ለማበረታታት ነው። እግዚአብሔር ስለመጪው ጊዜ ዕቅድ አለው። ይህ ዕቅድ ጦርነቶችንና ፍርድን የሚጨምር ነው። ይህም ቢሆን በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር የሚፈጸም ነው። ይህ ዕቅድ በሚጠቃለልበት ጊዜ እግዚአብሔር ፍጹም በሆነው ምድር ይነግሣል። ኃጢአትና ሞት ይደመሰሳሉ። ክርስቲያኖች በእምነታችን ምክንያት በምንሰደድበት ጊዜ ወይም ብዙ ችግሮች ሲያጋጥሙን ፍጻሜያችን መልካም መሆኑን በማስታወስ ልብ ገዝተን ልንኖርና በእምነታችን ልንጸና እንችላለን። ወደፊት እግዚአብሔር ምን ሊያደርግ እንዳለው በእምነት መመልከት እንችላለን።

በትንቢተ ዘካርያስ ውስጥ ዘካርያስ ተስፋ የቆረጡትን አይሁድ የሚያበረታታበት ዋና መንገድ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መምጣትና እርሱም የሚያመጣውን በረከት በማሳየት እግዚአብሔር የሁሉ ነገር የበላይ ተቆጣጣሪ መሆንን በማረጋገጥ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘካርያስ 1-14 አንብብ። ሀ) ዘካርያስ ያያቸውን የተለያዩ ራእዮች ዘርዝር። የእነዚህ ራእዮች ትርጉም ምን ይመስልሃል? ለ) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች የተጠቀሱትን የተለያዩ ትንቢቶች ዘርዝር። ሐ) ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠቀሱትን የተለያዩ ትንቢቶች ዘርዝር።

ክፍል 1፥ አይሁድ ቤተ መቅደሱን በመሥራት ላይ ሳሉ የመጡላቸው መልእክቶች (ዘካርያስ 1-8)

1. ዘካርያስ ንስሐ እንዲገቡ ለሕዝቡ ጥሪ አደረገ (ዘካርያስ 1፡1-6)

አይሁድ ለእግዚአብሔር ታዝዘው ቤተ መቅደሱን እየሠሩ ቢሆኑም እንኳ በሕይወታቸው አሁንም ኃጢአት ነበር። ስለዚህ ትንቢተ ዘካርያስ የሚጀምረው አይሁድን ስለ ኃጢአታቸው በመውቀስና ንስሐ እንዲገቡ ጥሪ በማድረግ ነው። ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ከምናደርግለት ይልቅ ብንቀደስለት ይመረጣል። እግዚአብሔር የምናደርግለትን ነገር የሚቀበለው ከኃጢአታችን ንስሐ ስንገባ ብቻ ነው። አይሁድ የዘካርያስን መልእክት ከሰሙ በኋላ ንስሐ ገቡ። እግዚአብሔርም ይባርካቸው ዘንድ ከሚችልበት ሁኔታ ላይ ደረሱ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዚህ ዘመን ብዙ ክርስቲያኖች ቅዱሳን ከመሆን ይልቅ የእግዚአብሔርን ነገር ማከናወን የሚቀላቸው ለምንድን ነው? ለ) ይህ ነገር ሲፈጸም እንዴት እንደተመለከትህ የሚያስረዱ ሥዕላዊ መግለጫዎችን ዘርዝር። ሐ) እግዚአብሔር ለእርሱ ምንም ነገር ከማድረጋችን በፊት እንቀደስ ዘንድ በእጅጉ አበክሮ የሚናገረው ለምን ይመስልሃል? 

2. ዘካርያስ በሌሊት ያያቸው ስምንት ራእዮች (ዘካርያስ 1፡7-6፡8)

ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንዲኖራቸው ካደረገው መልእክቱ ቀጥሎ፥ ዘካርያስ በአንድ ሌሊት ያያቸውን ስምንት ራእዮች ያቀርባል። እነዚህ ራእዮች በአሕዛብ እንደተጨቆኑ በመቁጠር ኃዘን የተሰማቸውንና ለእግዚአብሔር በሚሠሩት ሥራ ተስፋ ቆርጠው የነበሩትን አይሁዶች የሚያበረታቱ ነበሩ፤ እያንዳንዳቸው እግዚአብሔር ለአይሁዶች የሰጠውን ግልጽ የሆነ ልዩ የማበረታቻ መልእክት የያዙ ነበሩ።

ሀ. የመጀመሪያው ራእይ – በዛፎች መካከል ቆሞ የነበረው ፈረሰኛ (ዘካርያስ 1፡7-17) 

አይሁድ ወደ አገራቸው ቢመለሱም፥ ገና በአሕዛብ ቁጥጥር ሥር ነበሩ። አሕዛብ በምቾት ሲዝናኑ እነርሱ ግን በመከራ ውስጥ ነበሩ። ነገር ግን እግዚአብሔር ነገሮችን ተቀጣጥሮ ነበር። ፈረሰኛው በዓለም ሁሉ ተዘዋውሮ ሰላምን እንዳገኘ ሁሉ እግዚአብሔርም ቤተ መቅደሱ እንደሚሠራና የእስራኤል ሕዝብ በሰላም እንደሚኖር ለአይሁድ ተስፋ ሰጠ። ሰላም እየመጣ ነበር፤ ዳሩ ግን እግዚአብሔር በእነርሱ ምትክ ሆኖ እስኪሠራና የይሁዳን ምድር እስኪያድስ ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው።

ለ. ሁለተኛው ራእይ – አራት ቀንዶችና አራት ጠራቢዎች (ዘካርያስ 1፡18-21) 

ለአይሁድ ቀንድ የብርታትና የኃይል ምልክት ነበር። እነዚህ ቀንዶች እስራኤልን የበተኑትን መንግሥታት ወይም በአሕዛብ ላይ የነገሡትን ነገሥታት ሊያመለክቱ ይችላሉ። ቀንዶቹ እስራኤልን የበተኑና አይሁድን ወደ ምርኮ የወሰዱትን መንግሥታት የሚወክሉ ነበሩ። በዚህ ስፍራ የቀንዶቹ አራት መሆን አራት የተለያዩ መንግሥታትን የሚወክል ይሆናል የሚለው አሳብ ምሁራንን ያከራክራቸዋል። አንዳንዶች እነዚህ አራት መንግሥታት ባቢሎን፥ ሜዶንና ፋርስ፥ ግሪክና ሮም ናቸው ሲሉ፥ ሌሎች ደግሞ አሦር፥ ግብፅ፥ ባቢሎንና እንዲሁም ሜዶንና ፋርስ ናቸው ይላሉ።

አራቱ ጠራቢዎች የሚወክሉት ደግሞ ለአይሁድ መበተን ምክንያት የሆኑት የአሕዛብ መንግሥታት የሚቀጡባቸውን የእግዚአብሔርን የፍርድ መሣሪያዎች ነው። እስራኤልን የወጉ ሁሉ በተራቸው ይደመሰሳሉ። አንዳንድ ምሁራን እነዚህ አራት ጠራቢዎች ባቢሎንን የደመሰሰው ሜዶንና ፋርስ፥ ሜዶንና ፋርስን የደመሰሰው ግሪክ፣ ግሪክን የደመሰሰው ሮም፥ በመጨረሻ ላይ የሮምን መንግሥት የሚደመስሰው መሢሑ ነው ብለው ያምናሉ።

ዋናው ትምህርት የእስራኤልን ጠላቶች እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ ይደመስሳቸዋል የሚለው ነው። እግዚአብሔር ጠላቶቹን የሚደመስስባቸው የተለያዩ ዓይነት ጠራቢዎች አሉት።

ሐ. ሦስተኛው ራእይ – የመለኪያ ገመድ የያዘው ሰው (ዘካርያስ 2)

በዘካርያስ ዘመን የኢየሩሳሌም ቅጥሮችና የከተማው አብዛኛው ክፍል ተደምስሶ ነበር። ነህምያ ከአይሁድ ጋር ቅጥሩን ለመሥራት የሚመጣው ገና ከብዙ ዓመታት በኋላ ነበር። በጥንት ጊዜያት አንድ ከተማ ቅጥር ከሌለው፥ የማይረባና ጥቃት መፈጸም ለሚፈልግ ጠላት ሁሉ የተጋለጠ ነበር።

በዚህ ራእይ ዘካርያስ የኢየሩሳሌምን ከተማ ለመለካት የመለኪያ ገመድ የያዘ ሰው ይመለከታል። ዳሩ ግን በኢየሩሳሌም ከተማ የሚኖረው ሕዝብ እጅግ ብዙ ስለነበር ለመለካት ጨርሶ የማይቻል ነበር። እግዚአብሔር አንድ ቀን የኢየሩሳሌም ከተማ ቅጥር ሊኖራት እስከማይችል ድረስ እጅግ ታላቅ ትሆናለች የሚል ተስፋ ሰጠ። እግዚአብሔር ራሱ በከተማዋ ውስጥ ስለሚኖርና የእሳት ቅጥር ስለሚሆናት ለጥበቃ የሚሆን ምንም ዓይነት ቅጥር የማያስፈልግበት ጊዜ ይመጣል።

ከአይሁድ መካከል ከምርኮ የተመለሱት ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። ብዙዎቹ በባቢሎንና በሌሎች አሕዛብ መካከል በምቾት መኖርን መረጡ። ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ጥሪ አደረገላቸው። አንድ ቀን አይሁድን ሁሉ ከዓለም ዙሪያ በመሰብሰብ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚያመጣቸው ተናገረ። በዚያም ከእነርሱ ጋር ከሚተባበሩ ሌሎች ሕዝቦች ጋር እግዚአብሔር አብሮአቸው ይሆንና ይባርካቸዋል።

መ. አራተኛ ራእይ – ለታላቁ ካህን ለኢያሱ የተሰጡ ንጹሕ አልባሳት (ዘካርያስ 3) 

ኢያሱ የእስራኤል ሊቀ ካህን ነበር። ይሁን እንጂ የሚሠራበት ቤተ መቅደስና ከእርሱ አስቀድሞ የነበሩ ካህናት ይለብሱአቸው የነበሩት ዓይነት ንጹሕና ጌጠኛ አልባሳት አልነበሩትም። ታዲያ እርሱ በእርግጥ የሕዝቡ መንፈሳዊ መሪ ነበርን? እግዚአብሔር አገልግሎቱን ተቀብሏልን? ኢያሱ በእግዚአብሔር የተመረጠ መሣሪያ መሆኑን ለሕዝቡ ለማሳየት እግዚአብሔር ለዘካርያስ ራእይ ሰጠው። በዚያ ራእይ ሰይጣን ንጹሕ አይደለም በማለት ኢያሱን በእግዚአብሔር ፊት ሲከሰው እንመለከታለን። (እድፋም ልብስ የመንፈሳዊ ንጽሕና ጉድለት ምልክት ነበር።) እግዚአብሔር ግን ኢያሱን የመረጠው እርሱ እንደሆነና በፊቱ ንጹሕ እንደሆነ ለሰይጣን ያረጋግጥለታል። (ጥሩ ልብስና ንጹሕ ጥምጥም ተደረገለት።) ሊቀ ካህን መሆን እንደሚገባው ለማረጋገጥ እግዚአብሔር ለኢያሱ የሊቀ ካህን ልብስ ሰጠው።

ካህን እንዲሆን የተጠራው ኢያሱ የእስራኤል ሕዝብ ተምሳሌትም ነበር (ዘጸአት 19፡5-6)። ሰይጣን ኢያሱን እንደከሰሰ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ የሆኑትን እስራኤልንም ንጹሕ አይደላችሁም በማለት ከሰሳቸው። ዳሩ ግን እግዚአብሔር አንጽቶ እንደገና የእርሱ ካህናት ይሆኑ ዘንድ ጠራቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰይጣን ኃጢአተኛ ነህ በማለት ለሚከሰው ክርስቲያን እግዚአብሔር ስለሚሰጠው መልስ ይህ ራእይ ጥሩ መግለጫ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ኃጢአታችን የተሸፈነው በምንድን ነው?

በዚህ ራእይ ስለ ኢየሱስ የሚናገር አሳብ እናገኛለን፤ እርሱም ቅርንጫፍ ተብሏል። ይህም በኢሳይያስ 4፡2 እና በሌሎችም የብሉይ ኪዳን ክፍሎች ከዳዊት ሥር የሚመጣውን መሢሕ ለማመልከት የተጠቀሰ ተምሳሌታዊ አገላለጽ ነው። ይህ ትንቢት ሙሉ በሙሉ የሚፈጸመው በእርሱ ብቻ ነው። የሰዎችን ኃጢአት ለመሸፈንና አይሁድን ለማዳን በመስቀል ላይ በተፈጸመው የክርስቶስ የሞቱ ሥራ አንድ ቀን ኃጢአት ከምድሪቱ ፍጹም ይወገዳል፤ ሰላምም ይኖራል።

ሠ. አምስተኛ ራእይ – የወርቅ መቅረዝና ሁለት የወይራ ዛፎች (ዘካርያስ 4) 

የቤተ መቅደሱ ሥራ መጓተት ብዙዎቹን አይሁድ ተስፋ አስቆርጦ ነበር። የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ ያህል ትልቅ እንዳልነበር አወቁ። ስለሆነም ምናልባት በዘሩባቤልና በኢያሱ ላይ ማጉረምረም ሳይጀምሩ አልቀሩም።

እግዚአብሔር የእስራኤል ሕዝብ የፖለቲካ መሪ የነበረውን ዘሩባቤልንና መንፈሳዊ መሪ የነበረውን ኢያሱን በመንፈሱ እንዳበረታቸው ለሕዝቡ የሚያስረዳ አምስተኛ ራእይ ለዘካርያስ ሰጠው። በዚህ ራእይ ዘካርያስ ሰባት መብራቶች የነበሩበትን አንድ የወርቅ መቅረዝ አየ። በወርቅ መቅረዙ ላይ የዘይት ማሰሮ ነበር። በወርቅ መቅረዙ አጠገብ በማሰሮው ግራና ቀኝ አይሁድ ለመቅረዙ ብርሃን ዘይት የሚያወጡባቸው ሁለት የወይራ ዛፎች ነበሩ። ከማሰሮው ወደ ሰባቱ መብራቶች ያለማቋረጥ ዘይት የሚያስተላልፉ ሰባት ቧንቧዎች ነበሩ። ዘሩባቤልና ኢያሱ ሁለቱ የወይራ ዛፎች ነበሩ። እግዚአብሔር እነዚህን ሁለት ሰዎች ሕዝቡን እንዲያገለግሉ መርጦአቸው ነበር። በመንፈስ ቅዱስ ምልቷቸው ነበር። እነዚህ መሪዎች የጌታን ሥራ የሚያከናውኑትና ቤተ መቅደሱን የሚሠሩት በኃይል ወይም በራሳቸው ብርታት እንዳልሆነ ማስታወስ አስፈላጊያቸው ነበር። ነገር ግን ኃይልን በሚያስታጥቃቸው፥ በእነርሱ በኩል በሚሠራውና ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ይሠሩ ዘንድ በሚያበረታቸው በእግዚአብሔር መንፈስ ላይ መደገፍ ነበረባቸው። የወርቅ መቅረዙና መብራቶቹ ደግሞ የሚያመለክቱት፥ እግዚአብሔር እስራኤልን ለአሕዛብ ብርሃን እንድትሆን እንደመረጣት ሳይሆን አይቀርም (ኢሳይያስ 42፡6፤ 49፡6)። ቤተ መቅደሱን በመሥራት እግዚአብሔርን የሚያገለግሉበትን ችሎታ እግዚአብሔር ከሚሰጣቸው ከመንፈስ ቅዱስ ማግኘት አስፈላጊያቸው ነበር። እስራኤላውያንም ልክ እንደ ዘሩባቤል መታመን ያለባቸው በራሳቸው ችሎታ ብቻ ሳይሆን፥ የሁሉ ነገር ምንጭ የሆነውን እግዚአብሔርን በመፈለግ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዚህ ዘመን ያሉ ክርስቲያን መሪዎች የእግዚአብሔርን ሥራ በራሳቸው ብርታት ለመሥራት የሚሞክሩባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? ለ) እግዚአብሔር ለዘሩባቤልና ለኢያሱ የሰጣቸው የተስፋ ቃሎች ዛሬ ለእኛ ከሰጠን ጋር ተመሳሳይ የሚሆኑት እንዴት ነው?

ረ. ስድስተኛው ራእይ – በራሪው የመጽሐፍ ጥቅልል (ዘካርያስ 5፡1-4) 

ዘካርያስ በስድስተኛው ራእይ 9 ሜትር ርዝመትና 4.5 ሜትር ወርድ የነበረውን አንድ የመጽሐፍ ጥቅልል ተመለከተ። በመጽሐፉ ሁለት ጐን እርግማን ተጽፎ ነበር። የመጽሐፉ ጥቅልል በአየር ላይ ይበርር ነበር።

ይህ ራእይ እግዚአብሔር የሕዝቡን ኃጢአት ሳይቀጣ እንደማይተው የሚያሳስብ ነበር። ንስሐ ገብተው ካልተመለሱና ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕይወትን ካልኖሩ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር በገባው ቃል ኪዳን ውስጥ ያሉትን እርግማኖች በሙሉ ሊያመጣባቸው ወስኖ ነበር (ዘዳግም 28፡5-68)። ይህ ክፍል የሚያተኩረው ግለሰቦች በሚሠሩት ኃጢአት ላይ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡ በማኅበር ደረጃ እንዲቀደሱ ይፈልግ ነበር። ነገር ግን እያንዳንዱ ግለሰብም በግሉ ደግሞ እንዲቀደስ ይፈልግ ነበር። የሚሰርቁ ወይም የሚዋሹ ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርድ ይደርስባቸው ነበር።

ሰ. ሰባተኛው ራእይ – በኢፍ መስፈሪያ ውስጥ ተቀምጣ የነበረችው ክፉ ሴት (ዘካርያስ 5፡5-11)

ስድስተኛው ራእይ በተለይ የሚናገረው ስለ ግለሰቦች ክፋትና ኃጢአት ሲሆን፥ ሰባተኛው ደግሞ እስራኤላውያን በሕዝብነታቸው የሠሩትን ኃጢአት ይገልጣል። ዘካርያስ በእርሳስ መክሊት የተከደነ አንድ የኢፍ መስፈሪያ አየ። በውስጡ አንዲት ሴት ነበረች። ሌሎች ሴቶች የኢፍ መስፈሪያውን አንሥተው በመብረር ወደ ሰናዖር ወሰዱት። (ሰናዖር የባቢሎን ሌላው ስም ነው።)

ይህ ራእይ እግዚአብሔር ክፋትን መታገሥ እንደማይችል ያሳያል። በክፋታቸው የሚቀጥሉ ሰዎች ከምድሪቱ መወገድ ነበረባቸው። ይህ ነገር በተለይ አንድ ቀን እግዚአብሔር ክፋትን ሁሉ ከሕዝቡ እንደሚያስወግድ የሚያመለክት ነበር። የክፋት ስፍራ ተምሳሌት ወደሆነችው ወደ ባቢሎን ይወሰዳል። በዚያ የእግዚአብሔርን ሕዝብ እንደገና ጨርሶ ሊያውክ በማይችልበት ሁኔታ ይጠበቃል።

የእስራኤልን ሕዝብና የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በምንመለከትበት ጊዜ፥ ዋናው ችግር ስደት አልነበረም። ይልቁንም ቀስ በቀስ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሰርጎ የሚገባው ክፋትና ኃጢአት ነው። ይህ ክፋትና ኃጢአት ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር እርስ በርስና ከዓለም ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሁሉ ያበላሻል። ዛሬም ቢሆን ቅድስናችንን ለመጠበቅ መታገል አለብን። አለበለዚያ ከእግዚአብሔር የበረከት ስፍራ እንወገዳለን። ለሁላችንም ማበረታቻ የሚሆነን ተስፋ ግን አንድ ቀን እግዚአብሔር ክፋትን ሁሉ ከምድር የሚያስወግድ መሆኑ ነው። ያኔ በእውነት እንቀደሳለን። 

ሸ. ስምንተኛው ራእይ – አራቱ ሰረገሎች (ዘካርያስ 6፡1-8)

ዘካርያስ በመጨረሻው ሌሊት በተሰጠው ራእይ አራት ሰረገሎችን አየ። አራቱ ሰረገሎች በቡድን በተጣመሩ ፈረሶች የሚጎተቱ ነበሩ። የመጀመሪያው ሰረገላ በመጋላ፥ ሁለተኛው በዱሪ፥ ሦስተኛው በአምባላይ አራተኛው ደግሞ በቅጠልማ ፈረሶች የሚመሩ ነበሩ። እነዚህ አራት ሰረገሎች እንደ መጀመሪያው ራእይ እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ የበላይ ተቆጣጣሪ እንደሆነ ያሳዩ ነበር። እርሱ የታሪክና የሕዝቦች ሁሉ የበላይ ተቆጣጣሪ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑትን እስራኤልን በሚወጉ ሁሉ ላይ ይፈርዳል። እነዚህ ሰረገሎች ታሪክን በመቆጣጠር ሂደት ውስጥ የእግዚአብሔርን መላእክት ሥራ የሚያሳዩ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የስምንቱን ራእዮች ዐበይት ትምህርቶች በአጭሩ አቅርብ። ለ) እነዚህን ትምህርቶች ከሕይወታችን ጋር የምናዛምደው እንዴት ነው?

3. የሊቀ ካህኑ የኢያሱ ተምሳሌታዊ አክሊል መጫን (ዘካርያስ 6፡9-15) 

እግዚአብሔር በሕዝቡ በእስራኤል መካከል ባዋቀረው መዋቅር ውስጥ ሦስት የተለያዩ ዓይነት መሪዎች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው፥ የፖለቲካ አመራሩን የሚይዘው ንጉሥ ነው። እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ የፖለቲካ መሪነት ሥልጣን እንዲይዝ ያደረገው ከይሁዳ ነገድ የዳዊትን ዘር ነበር። ሁለተኛው፥ የሃይማኖት መሪዎች የሆኑት ካህናት ነበሩ። ይኸኛው ደግሞ ከሌዊ ነገድ ለአሮን ዘር የተሰጠ ኃላፊነት ነበር። ሦስተኛው፥ እግዚአብሔር ከየትኛውም ነገድ የሚመርጣቸውና የእርሱን መልእክት ወደ ሕዝቡ የሚያመጡ ነቢያት ነበሩ። እነዚህ ሦስት ዓይነት መሪዎች ብዙ ጊዜ ለብቻ ተለይተው ያሉ ነበሩ። እግዚአብሔር ይህንን ያደረገው የመሪነትን ሚዛናዊነት ለመጠበቅ ነበር።

ዳሩ ግን ኣንድ ቀን እግዚአብሔር ለዘካርያስ አክሊል ሠርቶ በሊቀ ካህኑ በኢያሱ ላይ እንዲጭን ነገረው። እግዚአብሔር በዚህ ተምሳሌት የተናገረው አንድ ቀን የካህንና የንጉሥ ሥልጣን እንደሚዋሐዱ ነበር። ኢያሱ የኢየሱስ ክርስቶስ ተምሳሌት ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሌዊ ነገድ ሳይሆን ከመልከ ጼዴቅ ወገን የነበረ ካህን ነው። ደግሞም ከዳዊት ነገድ የሆነ ንጉሥ ነው። በዚህ ስፍራ ይህንን የሚያመለክት ነገር ባይኖርም እንኳ ኢየሱስ ነቢይ እንደ ነበረ እናውቃለን። ስለዚህ ሦስቱንም ዓይነት አመራር በአንድ ላይ የያዘ ነበር።

ዘካርያስ አንድ ቀን «ቁጥቋጦ» እንደሚመጣ ተነበየ። ይህም የመሢሑ ሌላው ስሙ ነው። በንጉሣዊ ማዕረግ ልብሱን ለብሶ ዙፋን ላይ ይቀመጣል። ቤተ መቅደሱንም ደግሞ ይሠራል። ሁለቱን የንጉሥና የካህንን ሥልጣን ያጣምራል።

4. ጾምን ስለሚመለከት ችግርና ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች የተነገሩ ታላላቅ ተስፋዎች (ዘካርያስ 7-8) 

ሰዎች ለተለያዩ ምክንያቶች ይጾማሉ። አንዳንዶች በቋሚነት የሚጾሙት የቤተ ክርስቲያናቸው ልማድ ስለሆነ ነው። ጾም በእነዚህ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ያለው ስፍራ እጅግ አነስተኛ ነው። ሌሎች ደግሞ የሚጾሙት ሊጸልዩበት የሚፈልጉት እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ሲኖራቸው ነው። ሁሉን ነገር መብላትንም ቢሆን እንኳ ትተው ከልባቸው በመጸለይ በእግዚአብሔር ፊት ይቆያሉ። በብሉይ ኪዳን ሕግጋት እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የሚጾሙባቸውን የተለዩ ቀናት ደንግጎላቸው ነበር። ራሳቸውን የሚመረምሩበትና ከኃጢአታቸው የሚነጹበት ጊዜ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን አይሁድ እግዚአብሔር በሰጣቸው የጾም ቀናት ላይ ሌሎች ቀናትን ጨመሩ። ከምርኮ በኋላ አይሁድ ኢየሩሳሌም በተደመሰሰችበት ጊዜ፥ ቤተ መቅደሱ በፈራረሰበትና ጎቶልያ በተገደለችበት ቀን ይጾሙ ነበር። የምርኮው ዘመን አብቅቶ አይሁድ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ በተመለሱ ጊዜ እነዚህን ሦስት የጾም ቀናት ማክበር እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው ማወቅ ፈለጉ።

እግዚአብሔር በዘካርያስ በኩል ለዚህ ጥያቄአቸው መልስ ሰጣቸው። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡ በተለይም የሃይማኖት መሪዎች በሚጾሙበት ወይም የሃይማኖት በዓላትን በሚያከብሩበት ጊዜ ትክክለኛ ዝንባሌ የሌላቸው መሆኑን በመጥቀስ ወቀሳቸው። ጾምና በዓል እውነተኛ የሆነውን የመጀመሪያ ትርጉማቸውን እየሳቱ ሥርዓት ብቻ ሆነው ይፈጸማሉ። የሃይማኖት ሥርዓቶች ተገቢውን ትርጉም ይዘው ትክክለኛ በሆነ ግንዛቤ እንዲሁም ትክክለኛ በሆነ ልብ ካልተፈጸሙ ዋጋ የሌላቸው ተግባራት መሆናቸውን እግዚአብሔር ለአይሁዶች ኣስተማራቸው።

በሁለተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር፥ እርሱን ደስ የሚያሰኙ የሚያደርጓቸውን እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የሕይወት ቁም-ነገሮችን ለአይሁዶች ያስታውሳቸዋል። እግዚአብሔርን ማክበር ከፈለጉ፥ በእርስ በርስ ግንኙነታቸው ትክክለኛ ፍርድን በማድረግ በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች በመርዳትና አንዳቸው ለሌላቸው መልካምን እንጂ ክፉን ባለማሰብ መኖር ነበረባቸው። እግዚአብሔር አባቶቻቸውን በምርኮ የቀጣው ሃይማኖታቸውን በተግባር ባለሙግለጻቸውና ፍቅርን ለሰዎች ሁሉ ባለማሳየታቸው ነበር።

በሦስተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር ወደ ፊት ለሕዝቡ ለእስራኤልና ለኢየሩሳሌም የሚሰጣቸውን በረከቶች አመለከተ። ኢየሩሳሌም ትባረካለች፤ እግዚአብሔር በውስጧ ያድራል፥ እርስዋም በእውነት ትሞላለች። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከተበተኑበት ስፍራ ሁሉ ተመልሰው እርሱን በጽድቅ እንዲያመልኩት ጥሪ ያቀርብላቸዋል። አሕዛብም የጌታን በረከት ለመቀበል ከእስራኤላውያን ጋር ይተባበራሉ። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በዚህ መንገድ ከባረከ የመታሰቢያ ጾማቸው ወደ ደስታ ይለወጣል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ የምንፈጽማቸውን የሃይማኖት ሥርዓቶች ከልብ እንጂ ከልማዳዊ ሥርዓት አንጻር ብቻ እንዳናደርጋቸው ይህ ክፍል የሚያስታውሰን እንዴት ነው? ለ) ከልብ ካልሆኑና በትክክለኛ ዝንባሌ ካልተደረጉ በስተቀር መልካም ቢሆኑም እንኳ ዋጋ የሌላቸውን አንዳንድ ተግባራት ጥቀስ።

ክፍል 2፥ ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች ለአይሁድ የተነገሩ ሁለት መልእክቶች (ዘካርያስ 9-12)

የትንቢተ ዘካርያስ የመጨረሻ ክፍል በተለይ ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች የተነገሩ ትንቢቶችን የያዘ ነው። የሚከተሉትን ትንቢቶች ልብ ብለህ ተመልከት፡-

1. እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በከበቡት አሕዛብ ሁሉ ላይ ይፈርዳል (ዘካርያስ 9፡1-8) 

2. የእስራኤል ንጉሥ መሢሑ በውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣል። በጥንት ዘመን የነበሩ ነገሥታት የሚመጡት ለሰላም እንጂ ለጦርነት አለመሆኑን ለመግለጽ በአህያ ላይ ይቀመጡ ነበር (መሳፍንት 10፡4፤ 2ኛ ሳሙኤል 16፡2 ተመልከት)። መሢሑ የሰላም ንጉሥ በመሆኑ፥ የጦር መሣሪያዎችን ሁሉ በመደምሰስ ለሕዝቡ ደኅንነትን ያመጣል፤ የታሰሩትን ነፃ ያወጣል። እግዚአብሔር ሕዝቡን በሚያድንበት ጊዜ፥ ሕዝቡ ለአክሊል እንደሚሆኑ እንደ ከበሩ ድንጋዮች ይሆናሉ። የእግዚአብሔር ጸጋ ጽዋዎች ይሆናሉ (ዘካርያስ 9፡9-17)። 

3. እግዚአብሔር ይሁዳን ይንከባከባል። ምድሪቱን ይባርካል። እስራኤልን ያስኮበለሉትን እረኞች (ክፉ መሪዎች) ይቀጣል። እግዚአብሔር የተበተኑትን እስራኤላውያን በሙሉ ወደ እስራኤል መልሶ ይሰበስባቸዋል (ዘካርያስ 10)።

4. እግዚአብሔር በዘካርያስ ሕይወት አማካይነት መልካምና ክፉ እረኞችን በማነጻጸር አቅርቦአል። በዚህ ረገድ ዘካርያስ የመልካሙ እረኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ ታይቷል (ዮሐንስ 10)። አንዳንድ ምሁራን፥ ዘካርያስ የሚያመለክተው መሢሑን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመቀበላቸው በአይሁድ ላይ የሚመጣውን ፍርድ ነው ይላሉ። ኢየሱስ በአብዛኛው ያገለገለው ተጨቁነው የነበሩትን ሰዎች እንደሆነ ሁሉ፥ ዘካርያስም በሌሉች የተጨቆኑ የበጎች መንጋ እረኛ ሆነ። የዘካርያስ ሁለት በትሮች፡- ውበት (ሞገስ) እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጣትን ውበት (ሞገስ) ሲያመለክት፥ ማሰሪያ ደግሞ ከሮብዓም ዘመን ጀምሮ ተከፋፍለው የነበሩት አይሁዳውያንና እስራኤላውያን አንድ እንደሚሆኑ የሚያመለክት ነበር (ዘካ. 11፡7)። ዘካርያስ በእስራኤል ክፉ እረኞችን ወይም የእስራኤልን ገዥዎች ለማጥፋት ጥረት አድርጎ ነበር። ነገር ግን በጎቹ (እስራኤላውያን) እንኳ ዘካርያስን ወይም መሢሑን አልሰሙም። ዘካርያስ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ የነበረው ውበት (ሞገስ) መቋረጡን ለማሳየት ሁለቱን በትሮች ሰበራቸው። እንደ አንድ ባሪያ ለሥራው የተከፈለው ዋጋ ሠላሳ ብር ብቻ ሲሆን፥ ገንዘቡን በእግዚአብሔር ቤት ባለው በግምጃ ቤቱ አኖረው። ይህም ይሁዳ ኢየሱስን እንዴት በሠላሳ ብር እንደ ሸጠውና የተቀበለውንም ገንዘብ እንዳልተጠቀመበት የሚያሳይ መሆኑ የተረጋገጠ ነው። በዚህ ዘመን ያሉ አይሁዶች በዓለም ዙሪያ ተበትነው በግዞት እንዳሉ ሁሉ በጎቹ ወይም አይሁዶች በእግዚአብሔር ፍርድ ይበተናሉ። እረኛቸው የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ስላልተቀበሉ በላያቸው ክፉ እረኞች ይሠለጥኑባቸዋል።

በኋላም ዘካርያስ እረኛው ሲመታ በጎቹ እንዴት እንደሚበተኑ በመናገር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ይተነብያል (ዘካርያስ 11፤ 13፡7-9)። 

5. እግዚአብሔር እስራኤልን ከጠላቶችዋ ይጠብቃታል። የኢየሩሳለምንም ጠላተት ይደመስሳል ዘካርያስ (12፡1-9)።

6. አይሁድ፥ በመስቀል ላይ የወጉትን ሚሑን ያዩታል። በዘመናት ሁሉ ስለፈጸሙት ድርጊትና ስለ አለማመናቸው በማዘን ንስሓ ይገባሉ። መሢሑ ምድሪቱን ፍጹም ያድሳታል፥ ያነጻታልም። የሐሰት አምልኮና ሐሰተኞች ነቢያት ይደመሰሳሉ (ዘካርያስ 12፡10-13፡6)። 

7. ጌታ ኢየሱስ ዳግም ሲመለስ ሁሉም ነገር ይለወጣል። መንግሥታት ኢየሩሳሌምን ለመደምሰስ ቢፈልጉም እንኳ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስለሚዋጋ ይደመስሳቸዋል። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ዘላለማዊ ብርሃን ይሆናል። በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ከኢየሱስ ክርስቶስ ዙፋን መንፈሳዊ በረከትን የሚያስገኝ የሕይወት ውኃ ምንጭ ይፈልቃል። በሕይወት የሚቀሩ አሕዛብም እግዚአብሔርን በመፍራት በኢየሩሳሌም ያመልኩታል። በምድር ላይ አንዳችም ክፋትና ኃጢአት አይኖርም። ነገር ግን ሁሉም ነገር “ለእግዚአብሔር የተቀደሰ” ይሆናል (ዘካርያስ 14)። 

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) ከትንቢተ ዘካርያስ የተማርካቸውን መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) የቤተ ክርስቲያን አባሎች እነዚህን ትምህርቶች ሊማሯቸው የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

በትንቢተ ዘካርያስ ውስጥ የሚገኙ ዐበይት ትምህርቶች

1. የመጨረሻዎቹ ዘመን 

ከሥነ መለኮት ትምህርት ዐበይት ክፍሎች አንዱ «ኤስካቶሎጂ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፥ ይህም በመጨረሻው ዘመን ስለሚሆኑት ነገሮች የሚመለከት ጥናት ነው። እስካሁን ድረስ የተመለከትናቸውን የነቢያትን መጻሕፍት ስናጠና ሁሉም በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በመጨረሻው ዘመን ስለሚሆኑ ነገሮች እንደሚናገሩ አስተውለናል። በሩቁ መጪ ጊዜ ስለሚፈጸሙት ተናጠል ክስተቶች ለመናገር «የጌታ ቀን» ወይም «በዚያ ቀን» የሚሉ ሐረጎችን ይጠቀማሉ። ዳሩ ግን በመጨረሻው ዘመን ስለሚሆነው ነገር በጊዜ ቅደም ተከተል የሰፈረ ዝርዝር መግለጫ ያቀረበ አንድም ነቢይ የለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን በዘመን መጨረሻ በሚሆኑ ነገሮች የአፈጻጸም ቅደም ተከተል ላይ የማይስማሙበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። ስለዚህ በተለያዩ ስፍራዎች የተሰጡትን መረጃዎች ማጠናቀርና ስለ መጨረሻው ዘመን ወደ አንድ አሳብ መድረስ የራሳችን ኃላፊነት ነው።

በብሉይ ኪዳን ከሚገኙት መጻሕፍት ሁሉ በተሻለ ሁኔታ በመጨረሻው ዘመን ስለሚፈጸሙት ነገሮች ግልጽ መረጃ የሚሰጡን ሁለት የትንቢት መጻሕፍት አሉ። እነርሱም ትንቢተ ዳንኤልና ዘካርያስ ናቸው። ትንቢተ ዳንኤል የሚያተኩረው በመጨረሻ ዘመን በአሕዛብ መንግሥታት ዘንድ ምን እንደሚሆን በመናገር ላይ ነው። ዳንኤል ስለ አይሁድ ቢናገርም እንኳ፥ ታሪካቸውን አስቀድሞ የሚናገረው ከአሕዛብ መንግሥታት ጋር ካላቸው ግንኙነት አንጻር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ዘካርያስ የሚያተኩረው የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ የሆኑትን የእስራኤልን ሕዝብ በሚመለከት ጉዳይ ላይ ነው። ዘካርያስ በተጨማሪ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት በግልጽ ከተነገሩ መረጃዎች አንዳንዶቹን ይሰጠናል።

ቀጥሎ ዘካርያስ የጠቀሳቸውን የመጨረሻውን ዘመን ክስተቶች ልብ ብለህ ተመልከት፡-

ሀ. እስራኤል በመጨረሻው ዘመን እንደገና ትሰበሰባለች፣ ትታደላለችም (ዘካርያስ 10፡9-12) 

ለ. ኢየሩሳሌም በመጨረሻው ዘመን ትከበባለች (ዘካርያስ 12፡1-3፤ 14፡1-2)፣ 

ሐ. በመጀመሪያ አሕዛብ እስራኤልን ያሸንፋሉ (ዘካርያስ 14፡2)፤

መ. እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይታደጋል (ዘካርያስ 14፡3-4)፤ 

ሠ. እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል (ዘካርያስ 12፡9)፤ 

ረ. ይሁዳና እስራኤል እንደገና አንድ ሕዝብ ይሆናሉ (ዘካርያስ 10፡9-12) 

ሰ. አይሁድ የገደሉትን መሢሑን በሚያዩበት ጊዜ ይለወጣሉ፤ ከኃጢአትም ይነጻሉ (ዘካርያስ 12፡10-13፡9)፤ 

ሸ. የደብረ ዘይት ተራራ ለሁለት ይሰነጠቃል። ከኢየሩሳሌም የሚፈስስ ወንዝ ይወጣል (ዘካርያስ 14፡4-6) 

ቀ. አዲስ ፍጥረት፥ አዲሲቷ ኢየሩሳሌም፥ እንዲሁም አዲስ ቤተ መቅደስ ይሠራል፥ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ይገዛል (ዘካርያስ 14፡6-2) 

በ. አሕዛብ በኢየሩሳሌም ያመልካሉ (ዘካርያስ 14፡16)። 

2. መሢሑ ኢየሱስ ክርስቶስ

ትንቢተ ዘካርያስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ አስደናቂ ትንቢቶችን የያዘ መጽሐፍ ነው። ትንቢቶቹ ዛሬ የኢየሱስን ታሪክ ለምናውቅ ለእኛ አስደናቂ ላይሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ትንቢቶች ከመፈጸማቸው ከአራት መቶ ዓመታት በፊት መሰጠታቸውንና ያለ አንዳች ስሕተት በትክክል መፈጸማቸውን ስናስብ እንደነቃለን። ከአራት መቶ ዓመታት በኋላ የሚፈጸመውን ነገር ቀርቶ ከአሥር ዓመት በኋላ የሚሆኑትን ነገሮች እንኳ ማን አስቀድሞ ሊናገር ይችላል? ዳሩ ግን እግዚአብሔር ያለፈውን እንደሚያውቅ ሁሉ የወደፊቱንም ያውቃል። ለእርሱ በመቶ ወይም ከሺህ ከሚጠሩ ዓመታት በፊት እንኳ የሚሆኑትን ነገሮች አስቀድሞ መናገር እጅግ ቀላል ነው። ቀጥሎ የቀረበው ሰንጠረዥ ስለ መሢሑ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጡ ትንቢቶች እንዴት እንደተፈጸሙና የወደፊቶቹ ደግሞ እንዴት እንደሚፈጸሙ ያሳየናል።

ትንቢት

ኢየሱስ ትሁት ይሆናል

የተነገረበት ክፍል 

ዘካርያስ 6፡12፤ 13:7

የትንቢቱ ፍጻሜ 

ማቴዎስ 26፡31 56

ትንቢት

ኢየሱስ ሰው ይሆናል

የተነገረበት ክፍል 

ዘካርያስ 6፡12፤ 13፡7

የትንቢቱ ፍጻሜ 

ሉቃስ 2

ትንቢት

ኢየሱስ ተቀባይነት አይኖረውም፤ በሠላሳ ብርም ይሸጣል

የተነገረበት ክፍል 

ዘካርያስ 11፡12-13

የትንቢቱ ፍጻሜ 

ማቴዎስ 26፡15፤ 27፡9-10

ትንቢት

ኢየሱስ በጦር ይወጋል፤ ይገደላል

የተነገረበት ክፍል 

ዘካርያስ 12፡10፣ 13፡7

የትንቢቱ ፍጻሜ 

ማቴዎስ 26፡31፣ ዮሐ. 19:37 

ትንቢት

ኢየሱስ ካህን ይሆናል

የተነገረበት ክፍል 

ዘካርያስ 6፡13

የትንቢቱ ፍጻሜ 

ዕብራውያን 6፡20 

ትንቢት

ኢየሱስ የሰላምና የጽድቅ ንጉሥ በመሆን በኢየሩሳሌም ይነግሣል

የተነገረበት ክፍል 

ዘካርያስ 6፡13፤ 9፡9፤ 14፡9፡16

የትንቢቱ ፍጻሜ 

ማቴዎስ 21፡5፤ ራዕይ 11፡15፤ ራእይ 19፡6 

ትንቢት

ኢየሱስ በክብር በመመለስ ሕዝቡን እስራኤልን ነጻ ያወጣል

የተነገረበት ክፍል 

ዘካርያስ 14፡1-6

የትንቢቱ ፍጻሜ 

ማቴዎስ 25፡31

ትንቢት

ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይሠራል

የተነገረበት ክፍል 

ዘካርያስ 6፡12-13

ትንቢት

ኢየሱስ አዲስ የዓለም ሥርዓት ይመሠርታል

የተነገረበት ክፍል 

ዘካርያስ14፡6-19

የትንቢቱ ፍጻሜ 

ራእይ 21፡22-27፡ 22:1፣ 5

ትንቢት

ኢየሱስ በቃል ኪዳኑ ደም እስራኤልን ያድሳል

የተነገረበት ክፍል 

ዘካርያስ 9፡11

የትንቢቱ ፍጻሜ 

ማርቆስ 14፡24

ትንቢት

ኢየሱስ ለተበተኑና እንደ በጎች ለሚቅበዘበዙት ሕዝቡ እረኛ ይሆናል

የተነገረበት ክፍል 

 ዘካርያስ 10፡2

የትንቢቱ ፍጻሜ 

 ማቴዎስ 9፡36

** የትንቢት መጻሕፍት የኢየሱስን የመጀመሪያና ዳግመኛ ምጽአት በግልጽ ለይተው እንደማያመለክቱ ልብ በል። አንድ ጊዜ ተቀባይነት ስለማይኖረውና ተሰቅሎ ስለሚገደለው ስለ ትሑቱ ኢየሱስ ይናገራሉ። በሚቀጥለው ቁጥር ደግሞ አይሁዳውያን ስለሚቀበሉት እንዲሁም በጽድቅና በሰላም ስለሚገዛው ንጉሥ ይናገራሉ። በሸለቆ ሥር ቆሞ አሻግሮ የሚመለከት አንድ ሰው እጅግ የተቀራረቡ በሚመስሉ ተራሮች መካከል ያለውን ርቀት በትክክል መናገር እንደማይችል፥ የወደፊቱን ብዙ መቶ ዓመታት አሻግረው የተመለከቱት ነቢያት በኢየሱስ የመጀመሪያና ዳግም ምጽአት መካከል ያለውን ልዩነት ለመመልከት አልቻሉም። ነቢያቱ የሚናገሩት ስለ ሁለት የተለያዩ ጊዜያት መሆኑ የታወቀው ከኢየሱስ የመጀመሪያ አመጣጥ በኋላ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዘመን መጨረሻ የሚፈጸመውን ነገር ማወቅ ዛሬ በክርስቲያናዊ ጉዞአችን የሚያበረታታን እንዴት ነው? ለ) የዘካርያስ ትንቢቶች የሚያበረታቱን እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ዘካርያስ አስተዋጽኦ እና አላማ

የትንቢተ ዘካርያስ አስተዋጽኦ

ክፍል 1፥ አይሁድ ቤተ መቅደሱን በመሥራት ላይ እያሉ የተነገሯቸው መልእክቶቹ (ዘካርያስ 1-8) 

1. ሕዝቡ ንስሐ እንዲቡ ዘካርያስ ጥሪ ማድረጉ (ዘካርያስ 1፡1-6)፣ 

2. ዘካርያስ በሌሊት ያያቸው ስምንት ራእዮች (ዘካርያስ 1፡7-6፡8)፣ 

ሀ. የመጀመሪያው ራእይ – በዛፎች መካከል የቆመው ፈረሰኛ (ዘካርያስ 1፡7-17)። 

ለ. ሁለተኛው ራእይ – አራቱ ቀንዶችና አራት ጠራቢዎች (ዘካርያስ 1፡18-21)፥ 

ሐ. ሦስተኛው ራእይ – የመለኪያ ገመድ የያዘ ሰው (ዘካርያስ 2)፥

መ. አራተኛው ራእይ – ለታላቁ ካህን ለኢያሱ የተሰጡት ንጹሕ አልባሳት (ዘካርያስ 3)፥ 

ሠ. አምስተኛው ራእይ – የወርቁ መቅረዝና ሁለት የወይራ ዛፎች (ዘካርያስ 4)፥ 

ረ. ስድስተኛው ራእይ – በራሪ የመጽሐፍ ጥቅልል (ዘካርያስ 5፡1-4)፥ 

ሰ. ሰባተኛው ራእይ – በኢፍ መስፈሪያ ውስጥ ተቀምጣ የነበረችው ክፉ ሴት (ዘካርያስ 5፡5-11)፥ 

ሸ. ስምንተኛው ራእይ – አራቱ ሰረገሎች (ዘካርያስ 6፡1-8)። 

3. የታላቁ ካህን የኢያሱ ተምሳሌታዊ አክሊል መጫን (ዘካርያስ 6፡9-15)፥ 

4. ጾምን የሚመለከት ችግርና የወደፊት ታላላቅ ተስፋዎች (ዘካርያስ 7-8)፡ 

ክፍል 2፥ መጪውን ጊዜ የሚመለከቱ ለአይሁድ የተሰጡ ሁለት መልእክቶች (ዘካርያስ 9-12)። 

1. የመጀመሪያው መልእክት – የመሢሑ መምጣትና ተቀባይነት ማጣት (ዘካርያስ 9-11)፥ 

2. ሁለተኛው መልእክት – የመሢሑ መምጣትና ተቀባይነት ማግኘት (ዘካርያስ 12-14)።

** የትንቢተ ዘካርያስ ሁለተኛ ክፍል የተጻፈው የመጀመሪያው ክፍል ከተጻፈ ከብዙ ዓመታት በኋላ ሳይሆን አይቀርም። ብዙ ምሁራን ሁለተኛው ክፍል የተጻፈው የቤተ መቅደሱ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው ብለው ያስባሉ።

የትንቢተ ዘካርያስ ዓላማ

ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን መሪ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመምራት የሚያስችሉ ስጦታዎች ሁሉ ለብቻው ሊኖሩት አይችሉም። ዳሩ ግን እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ያዋቀረው እንደ አንድ አካል በመሆኑ፥ እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን አባል የተለዩ ስጦታዎችና ችሎታዎች ይኖሩታል፡፡ እነዚህም በኅብረት በመሥራት ጠንካራ ቤተ ክርስቲያንን ያስገኛሉ።

እግዚአብሔር ሐጌን የጠራው ከምርኮ የተመለሱ አይሁዳውያን ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ ለማነሣት ነበር። ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ፍላጎት ከቤተ መቅደስ ሕንጻ ሥራ የላቀ ነበር። የቤተ መቅደሱ ሕንጻ ሥራ እንደተጠናቀቀ ሕዝቡ ያመልኩት ዘንድ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲዘጋጁ ይፈልግ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ነቢዩ ዘካርያስን በመጥራት፥ በሕዝቡ መካከል መንፈሳዊ መነቃቃትን ለማምጣት ተጠቀመበት። ሐጌና ዘካርያስ በአንድነት በመሆን ቤተ መቅደሱ እንዲሠራና በሕዝቡ መካከል መንፈሳዊ ተሐድሶ እንዲካሄድ ለማድረግ ቻሉ።

ዘካርያስ እግዚአብሔር ዛሬም ከአንድ የቤተ ክርስቲያን መጋቢ ወይም መሪ የሚፈልገው ዓይነት ሰው ምሳሌ ነው። ዘካርያስ አንድ የቤተ ክርስቲያን መጋቢ ለሕዝቡ መንፈሳዊ ዕድገትና ተሐድሶ ለማምጣት ከፈለገ ማድረግ ያለበትን ብዙ ተግባራት አሟልቶአል። ትንቢተ ዘካርያስ የተጻፈው በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፡-

1. ዘካርያስ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር የገቡትን ቃል ኪዳን በመተላለፋቸው ሕዝቡን ይወቅሳቸዋል። እግዚአብሔር በፍርድ እንዳስማረካቸው እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው ሆነው ነበር (ዘካርያስ 1፡3-5፤ 7፡8-14)። ዘካርያስ መልካም መጋቢዎች ሁሉ እንደሚያደርጉት፥ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ጋር ያፋጥጣቸዋል፤ ንስሐ እንዲገቡ አለበለዚያ ግን ስለ ኃጢአታቸው የእግዚአብሔር ፍርድ እንደሚጠብቃቸው በመንገር ያስጠነቀቃቸዋል።

2. ዘካርያስ ሕዝቡን መውቀስ ብቻ ሳይሆን፥ ለችግራቸው የሚሆን መፍትሔም ይሰጣቸዋል። ንስሐ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ይነግራቸዋል (ዘካርያስ 1፡3-5)። እግዚአብሔር በቤተ መቅደስ የሚያቀርቡትን አምልኮ የሚቀበለው ንስሐ ገብተው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ላደረገው ቃል ኪዳን ሲታዘዙ ብቻ እንደሆነ ይገልጥላቸዋል። እግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ለሚታዘዙ ሊሰጥ ቃል የገባው በረከት ወደ ሕዝቡ የሚመጣው ይህን ካደረጉ በኋላ ብቻ ነበር (ዘካርያስ 6፡9-15፤ 8፡13)። 

3. ዘካርያስ እውነተኛ ንስሐ የሰዎችን ባሕርይ እንደሚለውጥ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ሕዝቡ እንዴት መለወጥ እንዳለባቸው ይናገራል። ለእግዚአብሔር ያላቸው መታዘዝ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በሚኖሩት ኑሮና በማኅበራዊ ፍትሕ መገለጥ አለበት (ዘካርያስ 7፡9-10)። 

4. ዘካርያስ በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው እምነት ተስፋ ቈርጠው የነበሩትን አይሁድ ለማጽናናትና ለማበረታታት ፈልጎ ነበር። ይህንንም በሁለት ዐበይት መንገዶች አደረገው፤ በመጀመሪያ፥ ሌሊት ባያቸው ራእዮች እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንደሆነና ለሕዝቡ እንደሚጠነቀቅ አስተማራቸው። አሁንም አሕዛብን እየተቆጣጠረ ነበር። እግዚአብሔር መሪዎቻቸው ከሆኑት ከዘሩባቤልና ከኢያሱ ጋር ነበር። (በዘካርያስ ዘመን ለአይሁድ የተሰጠው የማበረታቻ መልእክት በዘካርያስ 1-8 ይገኛል።) 

ሁለተኛ፥ የሩቁን መጪ ጊዜ በማሳየት አበረታታቸው። ስለሚመጣው መሢሕና እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ የገባላቸውን ቃል ኪዳን ሁሉ ይህ መሢሕ እንዴት እንደሚፈጽምላቸው ነገራቸው። (ስለ መጪው ጊዜ በመናገር አይሁድን ያበረታታበት መልእክት በዘካርያስ 8-14 ይገኛል፡፡)

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አራቱ የዘካርያስ ዓላማዎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከምእመኖቻቸው ጋር ሊኖሯቸው ከሚገቡ ዓላማዎች ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ያሉ መሪዎች እነዚህን አራት ዓላማዎች በሙሉ ያሟሉባቸውን መንገዶች የሚገልጹ ምሳሌዎችን ስጥ። ሐ) እነዚህን ዓላማዎች በተሻለ መንገድ እንዴት ሊያሟሏቸው ይችላሉ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ዘካርያስ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት

አይሁድ በ539 ዓ.ዓ. ከምርኮ በተመለሱ ጊዜ ከፍተኛ መነቃቃትና ደስታ ተሰማቸው። ከሰባ ዓመታት በኋላ ከምርኮ እንደሚመለሱ እግዚአብሔር ለኤርምያስ የሰጣቸው ትንቢቶች እየተፈጸሙ ነበር። እግዚአብሔር በኢሳይያስ፥ በኤርምያስና በሕዝቅኤል የሰጣቸው ሌሎች ትንቢቶችም በቶሎ እንደሚፈጸሙ ያምኑ ነበር (ለምሳሌ፡- ኤርምያስ 30-33፤ ሕዝቅኤል 36-39)። እነዚህ ትንቢተች አይሁድ ወደገዛ ምድራቸው እንደሚመለሱ፥ መሢሑ እንደሚመጣ፥ በአሕዛብ አገዛዝ ሥር መኖራቸው እንደሚያከትም፥ ታላቁ ቤተ መቅደስ እንደገና እንደሚሠራ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደሚጀምርና ስራቸው እንደሚያበቃ የሚናገሩ ነበሩ። ስለዚህ በታላቅ ደስታ የሚመጣውን በረከት በሚጠባበቅ ልብ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው፥ እግዚአብሔርን ለማምለክ መሠዊያ ከማቆማቸውም የቤተ መቅደሱን ሥራ ጀመሩ።

ነገር ግን እነዚህ ተስፋዎች አለመፈጸማቸውን ለማወቅ ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። የቤተ መቅደሱን ሥራ እንደጀመሩ በተለይ ከሳምራውያን በኩል ተቃውሞ ገጠማቸው። ሳምራውያን ከፊል አይሁዳውያን ከፊል አሕዛብ የሆኑ በጥንታዊቷ የእስራኤል ምድር ይኖሩ የነበሩ ናቸው። አይሁድ የቤተ መቅደሱን ሥራ ወዲያውኑ ለማቆም ተገደዱ። ይህም አይሁድ ከአሕዛብ ተጽዕኖ ነጻ እንዳልሆኑና አገራቸው ከቁጥር የማትገባ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ግዛት ክፍለ ሀገር እንደነበረች አረጋገጠላቸው።

አይሁድ በየስፍራው የሚመለከቱት ከ50 ዓመታት በፊት ባቢሎን ኢየሩሳሌምን በደመሰሰች ጊዜ የተረፉትን ፍርስራሾች ነበር። የቤተ መቅደሱ፥ የኢየሩሳሌም ቅጥርና በውስጧ የሚገኙ ቤቶች ፍርስራሽ በአካባቢው ነበር። አይሁድ የቤተ መቅደሱን ሥራ ለማቆም ስለተገደሉ የየራሳቸውን ቤቶች መሥራት ጀመሩ። የእግዚአብሔርን ነገሮች ረስተው፥ ለራሳቸው ፍላጎት ብቻ የሚጠነቀቁ ራስ ወዳዶች ሆኑ። ወዲያውኑ ሁሉን ነገር የሚያጥላሉ ሆኑና እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ይፈጽም ይሆንን? የሚል ጥያቄ አቀረቡ። ሌሎች ደግሞ ተስፋ መቁረጥ ጀመሩ። ደግሞም የተመለሱት አይሁድ ቁጥር ጥቂት ስለነበረ ብዙ ሕዝብ አልነበረም፡፡ ድርቅና ራብ አከታትሉ ያጠቃቸው ነበር። የእግዚአብሔር ተስፋዎች የታሉ? እግዚአብሔር በተስፋዪቱ ምድር እንደሚባርካቸው አምነው መመለሳቸው ስሕተት ነበርን? በዚህ ሁኔታ ዓመታት እየተቀጠሩ ሲሄዱ ሕዝቡ የበለጠ ተስፋ እየቆረጡና ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸው ፍላጎት እየቀነሰ ይሄድ ነበር።

በመካከሉ እግዚአብሔር ሁለት ነቢያትን ጠራ፡፡ በመጀመሪያ ሐጌ እግዚአብሔር ሕዝቡን ያልባረከው በራስ ወዳድነት ተይዘው የየራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ለማሟላት ይጥሩ ስለነበር እንደሆነ ነገራቸው። ንስሐ በመግባትና ቤተ መቅደሱን በመሥራት ለእግዚአብሔር መታዘዝ ነበረባቸው። ሁለተኛ፥ ከሁለት ወራት በኋላ እግዚአብሔር ዘካርያስ የተባለ ሌላ ነቢይ ጠራ። አይሁድ ቤተ መቅደሱን መሥራት ከጀመሩ አምስት ወር አልፏቸው ነበር። በዚያኑ ወቅት ተንትናይ የተባለና ሌሎች የፋርስ ባለ ሥልጣናት አይሁድ ቤተ መቅደሱን በመሥራታቸው በፋርስ መንግሥት ላይ በእርግጥ ዓምፀው እንደሆነ ለመመርመር መጡ። እነርሱም የመሪዎችን ስም ጻፉና ወደ ዳርዮስ ደብዳቤ ላኩ። አይሁድ የግንባታውን ሥራ የቀጠሉ ቢሆንም ሥራውን መቀጠል የሚችሉት እስከመቼ እንደሆነ በማሰብ ሳይደነቁ አልቀሩም። ከዚህ ቀደም እንደሆነው ጠላታችን ያስቆሙን ይሆን? ብለው መሥጋታቸው አልቀረም። ስለዚህ ተስፋ መቁረጥ ጀመሩ። እግዚአብሔር ዘካርያስን የጠራው እዚህን ተስፋ የቆረጡ ሕዝብ እንዲያገለግል ነበር። አገልግሎቱ የሕዝቡን መንፈሳዊ ሕይወት እንደገና ማደስ ነበር። ዘካርያስ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን በማፍረሳቸው ተጠያቂዎች እንደሆኑ በመንገር ሕዝቡን ያስጠነቅቃቸዋል። ሕዝቡ ንስሐ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ይነግራቸዋል። እግዚአብሔር የሚባርካቸው ይህ ሲሆን ብቻ ነበር። እግዚአብሔር ከእነርሱና ከመሪዎቻቸው ከዘሩባቤልና ከኢያሱ ጋር እንደሆነ የሰጣቸውም ተስፋ እንደሚፈጸም በመናገር ሕዝቡን ያበረታታል። የቤተ መቅደሱ ሥራ ይጠናቀቃል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይጠብቃል፡፡ በመሲሁም መምጣት የእግዚአብሔር ተስፋዎች ይፈጸማሉ፡፡

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዚያን ዘመን አይሁድ የነበራቸው ዝንባሌ ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ካላቸው ዝንባሌ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) በዘካርያስ ዘመን የእግዚአብሔርን በረከት ለማግኘት የሚያስችሉት ቅድመ-ሁኔታዎች ከዛሬዎቹ ጋር አንድ ዓይነት የሚሆኑት በምን መንገድ ነው? ሐ) እግዚአብሔር ወደፊት ስለሚያደርገው ነገር እኛም እንደ ዘካርያስ በመናገር ክርስቲያኖችን እንዴት ማበረታታት እንችላለን?

ዘካርያስ አገልግሎቱን ለብዙ ዓመታት ቀጥሉ ነበር። ዘካርያስ የአይሁድ ሕዝብ መንፈሳዊ ተሐድሶ በተካሄደና ቤተ መቅደሱ እንደገና በተሠራ ጊዜ ታላቅ ድርሻ እንዳበረከተ ከመጽሐፈ ዕዝራ እናነባለን (ዕዝራ 5፡2)። የቤተ መቅደሱ ሥራ በ516 ዓ.ዓ. ሊጠናቀቅ ዘካርያስ ምስክር እንደነበር አንጠራጠርም። አገልግሎቱን በሚጀምርበት ጊዜ ወጣት የነበረ ይመስላል (ዘካርያስ 2፡4)። ስለዚህ አስቴርን እስካገባው ንጉሥ እስከ ቀዳማዊ አርጤክስስ ዘመነ መንግሥት ድረስ ሳይኖር አልቀረም (465-424 ዓ.ዓ.)።

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ዘካርያስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በመዝገበ ቃላት ውስጥ የምታገኛቸውን ጠቃሚ ትምህርቶች ዘርዝር፡

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡