ከድረ-ገጽ ላይ ያገኘሁትን የሞት ስታስቲካዊ መረጃ ላስቀድም። ለመሆኑ በዚህ አለም ላይ በእያንዳንዷ ሰከንድ 1.78 ሰው፣ በአንድ ደቂቃ 107 ሰው፣ በአንድ ሰዓት 6390 ሰው፣ በአንድ ቀን 153000 ሰው፣ በአመት ደግሞ 56 ሚሊዮን ያህል ሰው እንደሚሞት ያውቃሉ? ይህ ሞት አካላዊ ሞት ነው። ከዚህ ሞት የሚቀር ከመካከላችን አንድም የለም። ከአዳም የተገኝ ሰው ሁሉ ይህን አካላዊ ሞት መቅመሱ አይቀሬ ነው።
ሞት አካላዊ ብቻ አለመሆኑ ደግሞ ይህን አስደንጋጭ ዜና አሰቃቂ እንዲሆን ያደርገዋል። በሕይወት እያሉ ስለሞቱ ሰዎች ሰምተው ያውቃሉ? ከሞት በኋላ ስላለው ሁለተኛው ሞትስ (የዮሐንስ ራእይ 21፡8)? ከዚህ በታች ባሉት ጥቂት አንቀጾች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህኛው የሞት አይነት ምን እንደሚል እናጠናለን።
ሞት መቼ መጣ?
የሰው ልጅ በፍጹም ተድላና ደስታ በዔድን ገነት ይኖር ነበር። ፈጣሪም ሰውን አንድ ነገር እንዲያደርግ አዘዘው፤ እንዲህ ሲል፣ ‘‘… መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ…’’ (ኦሪት ዘፍጥረት 2፥17)። ሌላው ባላንጣው ደግሞ እንዲህ ሲል ሃሳብ አቀረበለት፣ ‘‘…ሞትን አትሞቱም’’ (ኦሪት ዘፍጥረት 3፥4)። ባልዘራው፣ ባላጨደው እና ባልሰበሰበው ፍሬ ደስ እንዲሰኝ፣ ያማረ እና የተዋበ የአትክልት ስፍራ የሰጠውን ፈጣሪውን መስማት ያልወደደው የሰው ልጅ፣ ኋላ ረግጦ ለሚገዛው ሰይጣን ፈቃድ አደረ። ‘‘ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ’’ (ወደ ሮሜ ሰዎች 5፥12)። ሞት ሕግን በመተላለፋችን ምክንያት ወደ አለም ገባ (ሮሜ. 7፡9)። በአዳም መተላለፍ ምክንያት ሞት በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ሰለጠነ (ሮሜ 5፡7)። ሞት ለሃጢአታችን የተከፈለን ምንዳ (ደሞዝ) ነው (ሮሜ 6፡23)። በዚህም ምክንያት ሞት የሰው ልጅ ጠላት ሆነ (1ቆሮ. 15፡26)።
ወደ ሮሜ ሰዎች 7፥9 እኔም ዱሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣች ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ እኔም ሞትሁ፤
ወደ ሮሜ ሰዎች 5፥17 በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ።
ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥23 የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፥26 የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤
ቀዳሚ አባታችን አዳም በበደለው በደል እና እኛም ራሳችንን ካወቅንበት ደቂቃ ጀምሮ እግዚአብሔርን ስለበደልን የበደላችን ደሞዝ የሆነው ሞት ደጃችንን እያንኳኳ በሰረገላው ይዞን ሊነጉድ የመጨረሻዋን እስትንፋሳችንን እየጠበቀ ነው። ይህ ቅስበታዊ ስጋዊ ሞት ወደ ቀጣዩ እና ዘላለማዊ ሞት የሚያሻግረን ድልድይ ነው። ቅስበታዊው ሞት የሚያስፈራ ከሆነ፣ ዘላለማዊውማ እንዴት አብልጦ አያስፈራ!!! ‘‘ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው’’ (የዮሐንስ ራእይ 20፥14)።
እግዚአብሔርን ባለመታዘዛችን እና ፈቃዱን ባለማድረጋችን ምክንያት አሁን በሕይወት ሳለን እንኳ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን እያለ ይጠራናል። በሕይወት እያለን በሁለተኛው ሞት ፍርድ ስር መሆናችን የሚያሳዩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም አሉ። እስቲ ለአብነት የተወሰኑትን እንመልከት፡-
ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፥1-2 በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው።
ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፥5 ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥
ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፥14 ስለዚህ፦ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል።
ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2፥13 እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። (ይህ የስጋ ግርዘት ሳይሆን መንፈሳዊውን የልብ ግርዘት ነው ሮሜ 2፡29)
የሞት መፍትሄ ምንድን ነው?
ከአዳም ውድቀት ጀምሮ እስከ ኢየሱስ መምጣት፣ ሞት በሰው ልጆች ላይ ስልጣን ነበረው። ሞት ድል የተነሳበት ብስራት የተነገረው ኢየሱስ ይህችን ምድር ሲረግጥ ነው። የሞት መውጊያ የተወሰደው፣ ሙታኑን ሲቀበል የነበረው ሲኦል የደነገጠው፣ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሞትን፣ በሞቱ ሲቀጣ ነው። ‘‘ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?’’ (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፥55)። ከሞት ጋር ታግሎ ያሸነፈ የለም፣ ሞትን ገጥሞ ድል የነሳ የለም። የሲኦልን ድንፋታን ፀጥ ያሰኘ የለም። ኢየሱስ ብቻ ይህን አድርጓል። ‘‘ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና’’ (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፥21)። ያም ሰው ኢየሱስ ይባላል።
ቅዱሳን ብለን የምንጠራቸው አንዳቸው ሳይቀሩ በሞት የተሸነፉ ናቸው። ማንም ከማንም ሳይለይ ሰው የሆነ ሁሉ ከሞት በታች ነበር። ሞት ገዝቷቸው ነበር። ከአንዱ በቀር። ኢየሱስን ግን ሞት አልቻለውም። የመቃብር ደጅ አፍኖ ሊያስቀረው አልደፈረም። እርሱ ብቻ ከሙታን መካከል አልተገኘም፣ ሕያው ነውና። ‘‘…ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም’’ (የሉቃስ ወንጌል 24፥5)።
ከዚህ ሞት ማን ሊድን ይችላል?
እግዚአብሔር በሞት ጥላ የሚሄደውን ሰው ተመልክቶ ዝም የሚል ልብ ስለሌለው፣ አንድ ልጁን በመላክ በሞት የተገዛውን ፍጥረቱን ሊያድን ወደደ። እናም በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን ያይ ዘንድ፥ በሞት አገርና ጥላ የተቀመጡትም ብርሃንን ይመለከቱ ዘንድ (የማቴዎስ ወንጌል4፥14-16) ሙታን ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት መጣ (የዮሐንስ ወንጌል 5፥25)። ዘመኑ ሲደርስ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ምድር ላከ። የልጁም ብርሃን በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ለነበሩት ሁሉ አበራ (የሉቃስ ወንጌል 1፥7)።
የሚሰሙትም ሁሉ፣ ቃሉን የሚጠብቁቱ ከዚህ ሞት አምልጠው በሕይወት እንዲኖሩ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆነ (የዮሐንስ ወንጌል 5፥25)። ‘‘እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም’’ (የዮሐንስ ወንጌል 5፥24)። ‘‘እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ’’ (የዮሐንስ ወንጌል 5፥25)። ‘‘እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አያይም’’ (የዮሐንስ ወንጌል 8፥51)።
ኢየሱስ ሃጢአትን ስላላደረገ ሊሞት ባላተገባው ነበር። እኛ ግን፣ ሁላችን ሃጢአት ስላደረግን (ሮሜ 3፡23) በሞት ልንቀጣ ይገባናል (ሮሜ 6፡23)። ሆኖም፣ ሁላችን ይህን ሞት ከምንሞት (ዮሐንስ ወንጌል 11፡50-51) ኢየሱስ የእኛን ሞት ሊሞት ወደደ፣ ‘‘መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቶአልና፤ …’’ እናም የኢያሱስ ሞት ስለሃጢአታችን የተደረገ የእኛ ሞት ምትክ ነው (ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥10)። በእርሱ ሞት እኛ የእግዚአብሔርን ይቅርታ አግኝተናል፣ ‘‘ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን’’ (ወደ ሮሜ ሰዎች 5፥10)። የኢየሱስ ሞት ምትክ ሞት ብቻ ሳይሆን እኛ ሁላችን ከእርሱ ጋር ሆነን ለሃጢአት እንድንሞት ያደረገ ሞትም ጭምር ነው፡-
‘‘ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን (ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥7-8)።
‘‘ቃሉ የታመነ ነው እንዲህ የሚለው። ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን (2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፥11)።
‘‘ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ’’ (1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፥24)።
‘‘ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና።ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን፤ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ፊት እንዳይሞት ሞትም ወደ ፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና። መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቶአልና፤ በሕይወት መኖርን ግን ለእግዚአብሔር ይኖራል። እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቁጠሩ’’ (ሮሜ 6፡6-11)።
‘‘ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ’’ (ገላቲያ 6፡14)።
ኢየሱስ የሞት መፍትሄ ነው። ከሃጢአት እና ከሞት ፍርድ ነፃ እንድንሆን አድርጎናል፣ ‘‘በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና’’ (ወደ ሮሜ ሰዎች 8፥2)።
ከሞት ለመዳን የእኔስ ድርሻ ምንድን ነው?
ኢየሱስ ቅጣቴን ሁሉ ከተቀበለልኝ እና ሞቴን ከሞተልኝ፣ የእኔ ድራሻ ምን ሊሆን ነው? የሚል ጥያቄ ካለዎ፣ ምላሹ እነሆ ፡- ለበደላችን የእኛን ሞት በሞተውና እኛን ስለማጽደቅ በሶስተኛው ቀን ከሙታን መካከል በተነሳው በኢየሱስ የሚያምን ሰው ሁሉ ከአሰቃቂው ሁለተኛ ሞት ነፃ ነው። ከሞት ፍርሃት ድኗል። ከሞት ፍርድ በኢየሱስ አምልጧል። ማስረጃዎቹን ከዚህ በታች ይመልከቱ፡-
የዮሐንስ ወንጌል 11፥25 ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤
የዮሐንስ ወንጌል 11፥26 ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።
ወደ ሮሜ ሰዎች 8፥11 ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።
ወደ ሮሜ ሰዎች 10፥9 ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤
ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2፥13 እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ።
የዮሐንስ ራእይ 14፥13 ከሰማይም። ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። መንፈስ። አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ።
ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፥14 ስለዚህ፦ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል።
ማጠቃለያ
ከዘላለማዊው የሞት ፍርድ ለመዳን ልናደርግ የምንችለው አንድም ነገር የለም። ጾምና ፀሎታችን፣ ሃይማኖታዊ ስርአቶቻችን፣ ሞራላዊ ድርጊቶቻችን ሁሉ ከሞት አያስመልጡንም። በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ያለማቋረጥ ብንፀልይ፣ ያለመታከት ብንጾም፣ ሃብታችንን ሁሉ ሸጠን ለድሆች ብንመፀውት፣ ሞት አይፈራንም። ሞት የሚፈራው ኢየሱስን ብቻ ነው። ድል የነሳውም እሱ ብቻ ነው። እነዚህ መልካም ምግባራት ሁሉ በኢየሱስ በማመን ከሞት ያመለጡ አማኞች እንዲያደርጓቸው የሚጠበቁ ናቸው እንጂ የሞት ማምለጫዎች አይደሉም። ከሁለተኛው ሞት ለመዳን ይሻሉ? እንግዲያው ኢየሱስ ሞትዎን እንደሞተልዎት፣ ቅጣትዎን እንደተቀጣልዎት በልብዎ ይመኑ፤ ያመኑትን ያን እውነት በአፍዎ ይመስክሩ። አለቀ። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ከሆኑ የሚከተለውን አይነት ፀሎት ያድርጉ።
“ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንክ አምናለው። ስለሃጢአቴ በመስቀል ላይ በእኔ ፈንታ ስለሞትክልኝ አመሰግንሃለው። እባክህ፣ ሃጢአቶቼን ሁሉ ይቅር በለኝና የዘለዓለምን ሕይወት ስጠኝ። ወደ ሕይወቴ እና ወደ ልቤ አዳኜና ጌታዬ ሆነህ እንድትመጣ እለምንሃለው። በቀሪው ዘመኔ ሁሉ ላገለግልህ እወዳለሁ፤ አሜን።”