የሰይጣን ዋነኛ የጦር ስልት ምንድን ነው?

የሰይጣን ዋነኛ የጦር ስልት የእግዚአብሔር ባህሪ አጣሞ፣ ቀይሮ እና አወናብዶ በማስቀመጥ ለሚሰሙት ሁሉ መስበክ ነው። ያለው ትልቁ የውጊያ መሳሪያ ማታለል፣ የተዘራውን እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል መንጠቅ፣ መዋሸት እና የመሳሰሉትን የማወናበድ ስራዎች መስራት ነው። ውሸትን እውነት አስመስሎ ማቅረብ የተዋጣለት ብልሃቱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለሰይጣን የጦር ስልቶች የሚለውን የተወሰኑ አብነቶች እንመልከት፡-

የማቴዎስ ወንጌል 4፥15 በሰሙት ጊዜም ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል ይወስዳል

2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2፥11 በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና።

2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፥14 ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና

2ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 2፥9-10 ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው።

የዮሐንስ ራዕይ 3፥9 እነሆ፥ አይሁድ ሳይሆኑ። አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ እነሆ፥ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ።

የዮሐንስ ራእይ 12፥9 ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።

የሰይጣንን ውሸት ለመቃወም አቅም የምናገኘው የእግዚአብሔርን ባሕሪ በአግባቡ ያወቅን እንደሆነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ባሕሪ የገለጠውን እውነታ ማወቅ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል የገለጠውን የእግዚአብሔርን ባሕሪ በውል መገንዘብ በእርሱ ላይ መታመናችን ምን ያህል ምክንያታዊና ተገቢ እንደሆነ ለማወቅ ይረዳናል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ባሕሪ በአመክኗዊ ሚዛን ላይ ስናስቀምጥ፣ እርሱን አለማመን ኢ-ምክንያታዊ፣ በእርሱ ላይ መታመን ደግሞ ምክንያታዊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እርሱን ለመቃወም ወይም ታቅበን ለመኖር ምንም አይነት አሳማኝ ምክንያት የለንም፡፡ የወደቀው/የተበላሸው/አሮጌው የሰው ተፈጥሮ ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ያምፃል፡፡ እግዚአብሔርን የማናምንበት ዋና ምክንያት እርሱ እንደኛ አይነት ባሕሪ ያለው ስለሚመስለን ነው፡፡ እርሱ እንደ እኛ አይነት ባሕሪ ቢኖረው እርሱን አለማመናችን ምክንያታዊ ይሆን ነበር፡፡ ሆኑም ግን ያ እውነት አይደለም።

ዘዳግም 32፡3-4 የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁና፤ ለአምላካችን ታላቅነትን ስጡ። እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው።

ኢዮብ 34፡10 ስለዚህ አእምሮ ያላችሁ ሰዎች ስሙኝ ክፋትን ያደርግ ዘንድ ከእግዚያብሔር በደልንም ይሰራ ዘንድ ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ፡፡

ዕብራዊያን 6፡18 (አ.መ.ት.) እግዚአብሔር ከቶ ሊዋሽ አይችልም፤…

1ዮሐንስ መልዕክት 4፡16 … እግዚያብሔር ፍቅር ነው፤…

ሚኪያስ 3፡6 እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ …

የሰይጣን የጦር ታክቲክ

የሰይጣን ዋና የጦር ታክቲክ፣ ሰዎች በእግዚአብሔር ባሕሪ ላይ ያላቸውን እምነት በመሸርሸር እግዚአብሔር ሊታመን የማይችል አምላክ እንደሆነ ማሳመን ነው፡፡ ለአብነት- በዘፍጥረት 3፡1-5 ሰይጣን፣ እግዚአብሔር ከአዳምና ሔዋን አንዳች የሚጠቅም ነገር እንደ ደበቀባቸው፣ የእነርሱንም መልካም ነገር የማይሻ እንደሆነ በእጅ አዙር በመንገር፣ በውስጣቸው ጥርጥርን በመዝራት እግዚአብሔርን ውሸታም ለማድረግ ያደረገውን ሴራ ያስተዉሉዋል፡፡

ዘፍጥረት 3፡1-5 እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ ነበረ፡፡ ሴቲቱንም፡- በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዟልን? አላት፡፡ ሴቲቱም ለእባቡ አለችው፡- በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ እግዚአብሔር አለ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም፡፡ እባብም ለሴቲቱ አላት ሞትን አትሞቱም ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካሙን እና ክፉውን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ፡፡

አዳምና ሔዋን በተፈጠሩ ጊዜ እንደሌሎቹ የእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ፣ እንከን የለሽ (perfect) ነበሩ፡፡ ሙሉ እና ምንም ሳይጎድላቸው ፍፁም የረኩ (complete and totally satisfied) ነበሩ፡፡ ያደርጉት የነበረው ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር ባሕሪ አንፃር የተጣጣመና የተዋሀደም ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ሞት አልነበረም፡፡

ሮሜ 5፡12 ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ አለም ገባ፣ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ …

1ቆሮንቶስ 15፡21-22 ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ … ሁሉ በአዳም እንደ ሚሞቱ …

አዳምና ሔዋን በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን መደገፍ ወደጎን በመተው፣ በራሳቸው ላይ በመተማመን፣ ሰይጣን በእግዚብሔር ባሕሪ ላይ የተናገረውን የውሸት ቃል አደመጡ፡፡ ከእግዚአብሔር ውጪም በራሳቸው አይን እርካታን ለማግኘት ተራመዱ፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ካላቸው መታመን ለመውጣት መወሰናቸውን የሚያመላክቱ ሦስት ማሳያዎች አሉ፡፡

(1) የሰው ማስተዋል/human understanding (ለጥበብ መልካም እንደሆነ አዩ)፣

(2) የሰውነት ፍላጎት/appetites of the body (ለመብላት ያማረ እንደሆነ አዩ)፣ እና

(3) ሐብት/possessions (ለዓይን እንደ ሚያስጎመጅ አዩ)፡፡

ዛሬም የዘወትር ፈተናዎቻችን ከነዚህ በአንዱ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ‹‹በራስ የመተማመን ዝንባሌ›› የሰው ልጆች ችግር ‹‹ሥር›› እንዲሁም እኛና አለሙ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ለምናደርገው አመፅ ዋነኛ አነሳሽ ምክንያት መሆኑን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡

ዘፍጥረት 3፡6 ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደሆነ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ ለጥበብም መልካም እንደሆነ አየች ከፍሬውም ወሰደችና በላች ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ፡፡

ልክ አዳም እንደ ተፈተነ ኢየሱስም በተመሳሳይ ሦስት አቅጣጫዎች ላይ ተፈተነ፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ሰይጣን ያቀረበለትን በራስ የመታመን ግብዣ ወደጎን በመተው ራሱን በእግዚአብሔር ጥበቃ ስር አሳልፎ በመስጠት ለመኖር ወሰነ፡፡

የማቴዎስ ወንጌል 4፡1-10 ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፥ አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ። ፈታኝም ቀርቦ። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው። እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ። መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው። ኢየሱስም፦ ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው። ደግሞ ዲያብሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ። ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው። ያን ጊዜ ኢየሱስ፦ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው።

ኢየሱስ በአባቱ ቃል ላይ በመደገፍ የሰይጣንን የፈተና ጥበብ እንዳዋረደ፣ እኛም መንፈስ ቅዱስ በገለጠው እግዚአብሔር ቃል እውነትነት ላይ እና በማይለወጠው የእግዚአብሔር ባሕሪይ ላይ በመደገፍ የሰይጣንን የውሸት ታክቲክ እንቃወም።

 

Leave a Reply

%d bloggers like this: