የእግዚአብሔር ቃል ፋይዳ ምንድን ነው?

የእውነት ምንጭ እኔ ወይም ሌላ ሰው አይደለም፡፡ የእውነት ምንጭ የመንግስትና የግል ዜና ማሰራጫዎች ወይም ሚዲያዎችም አይደሉም። የእውነት ምንጭ የታዋቂ ሰዎች አስተያየቶች አልያም የሳይንቲስቶች ላብራቶርም አይደለም። የእውነት ምንጭ ስሜት ሕዋሶቻችንም አይደሉም። እውነት ከራሱ ከእግዚአብሔር ብቻ ትፈልቃለች፡፡ እናም እውነት ብዬ የያዝኳቸውን እውቀቶች ሁሉ ወይም ደርሼባቸዋለው የምላቸውን ‘‘እውነቶች’’ ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል ፈትሼ በእርግጥም እውነት ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ይኖርብኛል።

ሀ. የእግዚአብሔር ቃል የታመነ ነው፡፡

መዝ. 119፡89 አቤቱ ቃልህ በሰማይ ለዘላለም ይኖራል፡፡ (1ጴጥ. 1፡25 በተጨማሪ ይመልከቱ)

ማቴ. 24፡35 ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም፡፡

ዮሐ. 14፡6 እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ …፡፡

ዮሐ. 17፡17 በእውነትህ ቀድሳቸው ቃልህ እውነት ነው፡፡

ኤፌ. 4፡21   …እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤…

1ዮሐ. 5፡6 (አ.መ.ት.) የሚመሰክረው መንፈስ ነው፤ መንፈስም እውነት ነውና ፡፡

ለ. የእግዚአብሔር ቃል፣ በየዕለቱ እንደ ምመገበው ምግብ አስፈላጊዬ ሊሆን ይገባል፡፡

ዘዳ. 6፡5-9 …እኔም ዛሬ አንተን የማዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ፡፡ ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሳም ተጫወተው፡፡ በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በአይኖችህም መካከል እንደ ክታብ ይሁንልህ፡፡ በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው፡፡

ኢዮብ 23፡12 ከአፉ ከወጣው ትእዛዝ አልራቅሁም፣ የአንደበቱን ቃል ከእለት እንጀራዬ አብልጬ ይዣለሁ፡፡ (አ.መ.ት.)

መዝ. 119፡16 በትዕዛዝህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም፡፡

መዝ. 119፡103 ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ፡፡

ማቴ. 4፡4 እርሱም መልሶ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፏል አለው፡፡

ሐ. ለማደግ የእግዚአብሔርን ቃል ማስታወስና ማሰላሰል ያስፈልገኛል፡፡

መዝ. 1፤1-3 ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፣ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል፡፡

መዝ. 119፡11 አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ ሰወረኩ፡፡

መዝ. 119፡97 አቤቱ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁት፤ ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው፡፡

መዝ. 145፡5 (አ.መ.ት.) ስለ ግርማህ ውበትና ስለ ክብርህ ይናገራሉ፤ እኔም ስለ ድንቅ ሥራህ አሰላስላለሁ፡፡

ቆላ. 3፡16 የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ . . .

የእግዚአብሔርን ቃል ለማስታወስ የሚረዱ ሁኔታዎች፡ ወደመስሪያ ቤትዎ ሲሄዱ አንድ ጥቅስ ለማስታወስ እየሞከሩ ይሂዱ፤ ካርድ ላይ ጥቅስ በመፃፍ በግልፅ የሚታይ ቦታ ላይ ይለጥፉ፣ ያንን ጥቅስ ቀኑን በሙሉ ያሰላስሉ፡፡

መ. የእግዚአብሔር ቃል በሕይወቴ ውስጥ እንደሚያበራ መብራት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የልቤን ምስጢሮች ይገልጣል፤ የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር እኔን እንደ ሚያየኝ ራሴን እንዳይ ይረዳኛል፡፡

መዝ. 119፡105 ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርኃን ነው፡፡

መዝ. 119፡130 የቃልህ ፍቺ ያበራል፣ ህፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል

ሮሜ. 10፡17 እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡

ዕብ. 4፡12-13 የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሰራም ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፤ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤

ሠ. እግዚአብሔር ራሱ የቃሉን መገለጥ ይሰጣል፡፡ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎችን ፍቼ ለመረዳት ቢያቅተኝም እንኳ፣ ለእርሱ ታማኝና ግልፅ በሆንኩ መጠን በሚያስፈልገኝ ደረጃ ቃሉን እንደሚገልፅልኝ ልታመነው እችላለው፡፡

ዘዳ. 29፡29 ምስጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው፡፡

ሉቃስ 24፡45 በዚያም ጊዜም መጽሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፡፡

1ቆሮ. 2፡12-14 እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የአለምን መንፈስ አልተቀበልንም መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም፡፡ ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም፡፡

2ጴጥ. 3፡15-16 እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፣ በመልዕክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ፡፡ በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፣ …

 

Leave a Reply

%d bloggers like this: