የግል ፀሎት ምንድን ነው?

አንተ ግን ስትጸልይ፣ ወደ እልፍኝህ ግባ፣ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፣ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሀል፡፡ ማቴዎስ 6፡6

ኢየሱስ ‹‹በስውር ላለው አባታችሁ ፀልዩ›› እንጂ ‹‹በስውር ስፍራ ወዳለው አባታችሁ ህልምን አልሙ፡፡›› አላለም፡፡ ፀሎት ፈቃድን ማስገዛት ይጠይቃል፡፡ ወደ እልፍኛችን ከገባንና በራችንን ከዘጋን በኋላ ልናደርግ የሚቸግረን ትልቁ ነገር ቢኖር መፀለይ ነው፡፡ አእምሮአችንን ለፀሎታችን ልንጠቀምበት በምንችለው ሁኔታ ማዘጋጀት አስቸጋሪው ሥራችን ይሆናል፡፡ የመጀመሪያ ውጊያችን የሚሆነው ሀሳባችንን ማሰባሰብና ለፀሎት ራሳችንን መግዛት ነው፡፡ በግል የፀሎት ጊዜ ያለው ታላቁ ጦርነት ሀሳባችንን ማሰባሰብና ለፀሎት ያልተዘጋጀውን አዕምሮአችንን ለዚሁ መንፈሳዊ ስራ እንዲነሳሳ ማድረግ ነው፡፡ በፈቃዳችን ላይ ለተመሠረተ እና ለታሰበበት ፀሎት አዕምሮአችንን በዲሲፕሊን መግዛት መማር ይኖርብናል፡፡

ለፀሎት የተለየ ስፍራ ሊኖረን ይገባል፡፡ ያም ሆኖ ግን ወደዚህ ስፍራችን ስንገባ ሀሳባችን መባከን ይጀምራል፣ ‹‹ይህ መሰራት አለበት››፤ ‹‹ያኛውን ደግሞ ዛሬ መጨረስ ይኖርብኛል፡፡›› የሚሉ ሀሳቦች በአዕምሮአችን መመላለስ ይጀምራሉ፡፡ ኢየሱስ ‹‹በራችሁን ዝጉ፡፡›› ነው ያለው፡፡ በፀሎት ወቅት የተረጋጋ የአዕምሮ ሁኔታን ለመፍጠር፣ የአዕምሮአችንን ደጆች ለሚያንኳኩ ስሜቶቻችን ሆን ብለን ደጃችንን በመዝጋት፣ እርሱን ብቻ ማሰብ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር በስውር አለ፡፡ ከ ‹‹ስውር ስፍራውም›› ይመለከተናል፡፡ እርሱ የሚመለከተን፣ ሰዎች እኛን ወይም ራሳችን ራሳችንን እንደ ምንመለከተው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር እኛን በሚያየን በዚህ ‹‹ስውር ስፍራ›› መኖር መለማመድ ስንጀምር እግዚአብሔርን መጠራጠር አይሆንልንም፡፡ ከማንም እና ከምንም ነገር በላይ ስለ እርሱ እርግጠኞች እንሆናለን፡፡ ወደዚህ ‹‹ስውር ስፍራ›› ስትገባ በእለት ተዕለት ሕይወትህ እግዚአብሔር በእርግጥ ትክክል እንደሆነ ታረጋግጣለህ፡፡ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ከእግዚአብሔር ጋር የማውጋት ልማድ ይኑርህ፡፡ የማለዳው ጎህ ሲቀድ የሕይወትህን ደጆች ወለል አድርገህ ከፍተህ እግዚአብሔርን ማስቀደም መማር ካልጀመርክ፣ የቀን ውሎህ ሁሉ በተሳሳተ መስመር ላይ መሆኑን እንዳትዘነጋ፡፡ ነገር ግን የሕይወትህን ደጆች ከፍተህ ‹‹በስውር ላለው አባትህ ፀሎት ካደረስክ››፣ በሕይወትህ የሚያለፉ ማህበራዊ ነገሮችህ ሁሉ የእግዚአብሔር የይሁንታ ማህተም ያረፈባቸው ይሆናሉ፡፡

በግለህ ወደ ፀሎት በገባህ ጊዜ የሚደርስብህን የትኩረት መበታተን ችግር ለመቀነስ፣ ወደ አይምሮህ እየመጡ የሚያስቸግሩህ እና ኋላ ላይ ልትሰራቸው የሚገቡህን ነገሮች የምታሰፍርበት ማስታወሻ ደብተር አዘጋጅ፡፡

 

Leave a Reply

%d bloggers like this: