ታላቁ የእግዚአብሔር የቁጣ ቀን መጥቶአል፤ ማንስ ሊቆም ይችላል? ራዕይ 6፡17

የሰው ልጅ የፈጣሪውን ትዕዛዝ በገዛ ፈቃዱ ከተላለፈባት እለት ጀምሮ ቅዱስ የሆነው ፈጣሪ፣ ከእርሱ ክብር በጎደለው (ሮሜ 3፡22-23) ፍጡሩ ላይ ተቆጥቷል። ይህ ቁጣ ሃጢአተኞችን ሁሉ ሊበላ ያለ ቁጣ ነው። እውነትን በዓመፃ በከለከሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ የሚገለጥበት ጊዜ ደርሷል (ሮሜ 1፥18)። ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ ላይ የእግዚአብሔር የቁጣ ጽዋዎች ሞልተው በምድር ላይ የሚፈሱበት ሰአት እንዳለ ገልጿል (ራእይ 16፥1፤ ራእይ 15፥7)።

ይህ የእግዚአብሔር ቁጣ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተጠበቀ አይደለም። ለተወሰነ የሃይማኖት ተከታዮች፣ ለተወሰኑ ዘሮች ወይም ነገዶች፣ ወይም ለተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ወይም የቆዳ ቀለም ላላቸው የተጠበቀም አይደለም። ለእርሱ በማይታዘዙ ሰዎች ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመጣል (ኤፌሶን 5፥6፤ ቆላስይስ 3፥6)።

የእግዚአብሔር ቁጣ ሕይወታችንን ለዘላለም ከእግዚአብሔር ቅድስና ለይቶ በዘላለም እሳት ውስጥ የሚያኖር ቁጣ ነው። ይህ ቁጣ ከምናስበው በላይ ብርቱ ነው (ራእይ 19፥15)።

ይህ ታላቅ የእግዚአብሔር ቁጣ ንስሃ በማይገቡ ሰዎች ላይ እንደነደደ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ እንደሚቆይ ጳውሎስ በ ሮሜ 2፥5 እንዲህ በማለት ያሳየናል፣ ‘‘ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።’’

‘‘ታዲያ፣ እንዴት ከዚህ የእግዚአብሔር ቁጣ ልተርፍ እችላለው?’’ መልሱን ሐዋሪያው ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ያሳውቀናል፣  ‘‘በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም’’ (ዮሐንስ  3፥36)።

ከአዳም ውድቀት ጀምሮ በሰው ላይ ተነጣጥራ ያለችው የእግዚአብሔር ቁጣ መብረጃዋ አንድ ነገር ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ቁጣ የእግዚአብሔርን ፍትህ ያሳያል። የእግዚአብሔር ፍትህ ደግሞ የእኛን ሞት ይጠይቃል (ሮሜ 6፡23)። የእግዚአብሔር ፍትህ የሃጢአተኛውን ሞት ይሻል (ዕብራውያን 9፡22)። ሁላችን ሃጢአትን ስላደረግን ለዚህ ሞት (የእግዚአብሔር ቁጣ ውጤት) ተዘጋጅቶልናል (ሮሜ 6፡23)። ሃጢአትን ያላደረገ በዚህ ምድር ላይ ስለሌለ (መክብብ 7፡20፤ 1ዮሐንስ 1፡8፤ ሮሜ 3፡10-18) ከዚህ ፍርድ ስር ያልሆነ ሰው በምድር ላይ የለም።

ሆኖም ግን፣ ከዚህ ፍርድ ስር መሆናችን ያሳዘነው እግዚአብሔር የራሱን ፍትሃዊ ፍርድ ራሱ ሊቀበልልን ወሰነ። በዚህም ምክንያት ሁላችን ከምንሞት አንድ ልጁ በእኛ ፈንታ እንዲሞት ፈቀደ (የሐንስ 11፡50-52)።  ይህ ቅዱስ ልጁ፣ ኢየሱስ ይባላል። ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ነው (ዮሐንስ 1፡29)። እግዚአብሔር በእኛ ላይ ሊያፈሰው የነበረውን ቁጣ በልጁ በኢያሱስ ላይ አፈሰሰው። ኢየሱስ በእኛ ሞት ፈንታ ሞተልን። በዚህ ምትክ ሞት ምክንያት በኢየሱስ ሞት እና ትንሳኤ የሚያምኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ቁጣ እንዲተርፉ ሆነ። እግዚአብሔር፣ በኢየሱስ ሞትና እና ትንሳኤ ያመኑትን ሁሉ፥ ከሞት ፍርድ ያድናቸዋል (1ተሰሎንቄ 4፡14)። ‘‘በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም’’ (ዮሐንስ  3፥36)።

በልጁ ሞት እና ትንሳኤ ማመን ማለት፣ የእርሱ ሞት እግዚአብሔር በእኔ ላይ የነበረውን ቁጣ እንዲያነሳና ከእኔ ጋር ሰላም እንዲያርግ (ሮሜ 5፡1) አድርጎታል ብሎ ማመን ነው። በልጁ የሚያምን ከእንግዲህ የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ የለበትም (ዮሐንስ  3፥36)። የእግዚአብሔር ጠላት (ሮሜ 5፡10) ሳይሆን ወዳጅ ሆኗል። የኢየሱስ የሚያምን ሰው የኢየሱስ ሞት ለእግዚአብሔር ቁጣ በቂ ምላሽ እንደሰጠ ያምናል። ተጨማሪ የማምለጫ ስልቶችንም አይቀየስም። የእግዚአብሔር የድነት መንገድ  (ዮሐንስ 14፡6) በቂ እና ፍጹም እንደሆነ ያምናልና።

ከእግዚአብሔር ቁጣ ለመትረፍ የሚበጁ ሌሎች አማራጮች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደሉም። በራስዎ ‘‘መልካም’’ ምግባር ወይም ስራ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተው ከእግዚአብሔር ቁጣ ለመትረፍ እንደሚችሉ ያስቡ ይሆን? ‘‘የተቀደሱ’’ ቦታዎች ላይ በመሄድ ከእግዚአብሔር ፍርድ የሚያመልጡ ይመስሎታል? ሃይማኖታዊ ክብረ በአላትን አዘውትረው በመጠበቅ ከቁጣው የሚሸሸጉ ይመስሎታል? የፓስተር ወይም የጳጳስ ልጅ ወይም ዘመድ በመሆንዎ የእግዚአብሔርን ፍረድ ሊያጣምምሙ የሚችሉ ይመስሎታል? ቁጣውን ለማፍሰስ በገዛ ፃድቅ ልጁ ላይ እንኳ ያልራራ (ሮሜ 8፡34)፣ ለእርሶ ጽድቅ ያውም ደግሞ የመርገም ጨርቅ ለሆነ ጽድቅዎ የሚራራ ይመስሎታል (ሮሜ 10፡2-3)? ገዳም በመግባትዎ፣ ለድሆች በመመጽወትዎ፣ ሳያጓድሉ በመጾምዎ እና በመፀለዮ፣ አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድዎ ምክንያት እግዚአብሔርን ከቁጣው የሚመልሱት ይመስሎታል? እንዲህ የሚያስቡ ከሆነ እንግዲያው ክርስቶስ በከንቱ ሞተ (ገላቲያ 2፡21)። እነዚህ መልካም ነገሮች ሁሉ ከዚህ ከእግዚአብሔር ቁጣ በክርስቶስ ሞት አማካኝነት ያመለጠ አማኝ ሁሉ ሊያፈራቸው የሚጠበቁ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ (ገላትያ 5፡20) ናቸው። እናም የሚናቁ አይደሉም። ነገር ግን፣ ከእግዚአብሔር ፍርድ የማምለጫ አቋራጮች አይደሉም። ከእግዚአብሔር ቁጣ እና ፍርድ ማምለጥ የሚቻልበት ሌላ አማራጭ ቢኖር ኖሮ እግዚአብሔር ፃድቅ እና አንድያ ልጁን ለሃጢአተኞች ሞት ተላልፎ እንዲሰጥ የሚፈቅድ የመስሎታል?ቅዱስ ጳውሎስ የሰው ልጅ እንዴት ከእግዚአብሔር ቁጣ ሊድን እንደሚችል የተናገረውን ተናግረን እናጠናቅ፣ ‘‘ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን (ሮሜ 5፡9)’’።

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

Leave a Reply

%d bloggers like this: