አቋማዊ (positional) ቅድስና ምን ማለት ነው?

መቀደስ ማለት ለንጽህና መለየት ማለት ነው። ሃጢአተኞች በእግዚአብሔር ጸጋ አማካኝነት በተሰጣቸው እምነት በጸጋው በኩል ከሃጢአት ሲድኑ ይቀደሳሉ (ኢፌ. 2:8-9)፤ ማለትም ለንጽህና ይለያሉ። የመዳን (የድነት) ሦስት “ደረጃዎች” አቋማዊ መቀደስ (positional sanctification)፣  ቀጣይነት ያለው መቀደስ (progressive sanctification)፣ እና የመጨረሻው መቀደስ (final sanctification) በመባል ይጠራሉ። በሌላ አነጋገር፣ አቋማዊ ቅድስናችን በክርስቶስ አማካኝነት በእግዚአብሔር ፊት ስላልን ጽድቅ (justification) ሲያውራ፣  ቀጣይነት ያለው ቅድስናችን ደግሞ በምድር ላይ ስለሚኖርን መንፈሳዊ ብስለት (spiritual maturity) ያወራል።  የመጨረሻው መቀደስ የሚያወራው ደግሞ በትንሳኤ ስለምንቅበለው ክብራችን (glorification) ነው።

ጌታ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛችን በተቀበልን ቅስበት አቋማዊ ቅድስናን አግኝተናል፤ ወይም ጸድቀናል። ይህም ማለት በኃጢአታችን ምክንያት ሊደርስብን ይችል ከነበረው ቅጣት ሙሉ በሙሉ ድነናል ማለት ነው። ይህ ቅድስና የአንድ ጊዜ ክንውን እንጂ ሂደት አይደልም። ይህ ቅድስና እየተሻሻለ ወይም እያደገ የሚሄድ አይደልም፤ ፍጹምና የመጨረሻ እንጂ። አቋማዊ ቅድስናችን ማለት በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ምክንያት ያገኝነው ቅድስና ማለት ነው። ስለዚህ ቅድስና ስናወራ እያወራን ያለው ስለ ሰማያዊው ቅድስናችን፣ አሁን ሰለ ማይታየው ነገር ግን ወደፊት ሊገለጥ ስላለው ቅድስናችን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ስለ ተሰወረው ቅድስናችን፣ ወይም በክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ሊገለጥ ስላለው ቅድስናችን ነው። ባጭሩ፣ ይህ ቅድስና ክርስቶስ ስለ እኛ በአብ ፊት የሚታየው መታየት ማለት ነው። ስለ አቋማዊ ቅድስናችን ስናወራ የምናወራው በእግዚአበሔር ፊት ተቀባይነት ስላገኘውና ፍጹም ስለሆነው ቅድስናችን ነው። አቋማዊ ቅድስናችን በክርስቶስ ለእግዚአበሔር የተለየን ሕዝቦች መሆናችንን ያሚያበስር እንጂ አሁን በምድር ላይ ስላለን መልካም ባሕሪይ አያወራም። ጉዳዩ ሰለ ስፍራችን እንጂ ስለ ባሕሪያችን አይደለም። አቋማዊ ቅድስና የሚያወሳው እኛን አስመልክቶ በሰማይ ስለተከናወነው ለውጥ እንጂ በምድር ስላልን ስነ-ምግባራዊ ለውጥ አይደልም።

በምድር ስላለን ስነ-ምግባራዊ ቅድስና ስናወራ ደግሞ እያወራን ያለንው ‘’ቀጣይነት ስላለው መቀደስ (progressive sanctification)” ነው። ይህ ቀጣይነት ያለው ቅድስና፣ ከኃጢአት ልምምድ (practice of sins) እና ከኃጢአት ኃይል (the power of sin) የመዳን ሂደትን ያመለክታል። ይህ የቅድስና ደረጃ አንደ አቋማዊ ቅድስና የአንድ ጊዜ ክንውን ሳይሆን በምድር በሕይወት እስካለን ድረስ ያሚቆይ የቅድስና ጉዞ ወይም ሂደት ነው። ቀጣይነት ያለው ቅድስና ያሚያወራው ስለ ተግባራዊ ቅድስና ወይም ስለ ምግባራዊ ቅድስና ነው። በሌላ አነጋገር ይህ ቅድስና የሚያወራው በምድር ላይ ስላለን የኑሮ ቅድስና ወይም ተጨባጭ ቅድስና ነው።

በዚህ ምድር ላይ ያለን የቆይታ ጊዜ ሲያበቃ ማለትም ነፍሳችን ከስጋችን ሲለይ በመጨረሻው መቀደስ (final sanctification) እንቀደሳለን። በዚህኛው የቅድስና ደረጃ ደግሞ ፈፅሞ ከኃጢአት መገኘት (presence of sin) እንድናለን ማለት ነው። በዚህ ቅድስና ውስጥ ስንገባ የመጨረሻውን ክብራችንን እንቀበላለን።    

ቀጣይነት ስላልውና ስለ መጨረሻው የቅድስና አይነት እዚህ ላይ ገታ እናድርግና የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ጉዳይ ስለሆነ ስለ አቋማዊ ቅድስና ተጨማሪ ጉዳዮች እናውራ። ከላይ እንደተገለጸው ይህ አይነቱ ቅድስና መንፈስ ቅዱስ በአማኙ ልብ ውስጥ የሚያከናውነው የአንድ ጊዜ ድርጊት ነው። በድነት ወቅት፣ አማኞች ኃጢአተኛ መሆናቸውን ተረድተው ይናዘዛሉ፤ በራሳቸው ማንኛውም ሥራ ራሳቸውን ለማዳን እንደማይችሉ ይገነዘባሉ፤ አዳኝ እንደሚያስፈለጋቸው ይረዳሉ፤ ክርስቶስ ለኃጢአት ክፍያ በመስቀል ላይ የከፈለውን መሥዋዕት ይቀበላሉ፤ እንዲሁም በኢየሱስን ትንሣኤም ያምናሉ።  በዚያ ቅጽበት፣ አማኞች ከድቅድቅ ጨለም ወደሚያስደንቅ ብርሃን ይሻገራሉ። “በእምነት ይጸድቃሉ” ( ሮሜ 5:1 ) ከእግዚአብሔር አንጻር ስፍራቸው (አቋማቸው) ለዘላለም ይቀየራል። የአዲስ መንግስት ዜጎች ይሆናሉ። “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን” (ቆላ. 1:13 )።

አቋማዊ ቅድስና የመንፈሳዊ አድራሻ ለውጥ ማድረግ ማለት ነው። ቀድሞ የእግዚአብሔር ቁጣ የሚጠብቀን ሃጢአተኞች ነበርን። ስፍራችን፣ መለዮአችን ወይም አቋማችን ይህ ነበር። በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ባመንን ወቅት ግን ባገኘነው አቋማዊ ቅድስና ምክንያት አድራሻችን፣ መለዮአችን ለአንዴና ለመጨረሻው ተቀይሯል፡፡ አሁን የቁጣ ለጆች ሳንሆን የተወደድን የእግዚአብሔር ልጆች ነን። ሃጢአተኞች ሳንሆን በአግዚአብሔር ፊት ፍጹማን ነን። ይህ የአቋማዊ ቅድስና ውጤት ነው፤ ማለትም የኢየሱስ የመስቀል ስራ ውጤት። የመንፈሳዊ አድራሻ ለውጣችን የክርስቶስ አካል ብልቶች እንድንሆን (1ቆሮ. 12:27 )፤ የርስቱ ወራሾች አንድንሆን (1ጴጥ. 2:9 )፤ አዲስ ፍጥረት አንድንሆን (2 ቆሮ. 5:17 )፤ ለኃጢአት አንድንሞት (ሮሜ 6:2 )፤ እና የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች አንድንሆን (2 ጴጥ. 1:4) አድርጎናል። ድነት የመንፈስ ቅዱስ ፍጹም ስራ ስለሆነ በመንፈሳዊው ስፍራ የተደረገው መነፈሳዊ የአድራሻ ለውጥ በአማኙ ምግባር ምክንያት ዳግመኛ ያማይቀለበስ ለውጥ ነው። የአማኙ መንፈሳዊ አድራሻ ፈጽሞ አይቀየርም ወይም አይለወጥም ወይም አይጠፋም ወይም ቀድሞ ወደነበረበት አይመለስም። ይህን አቋማዊ ቅድስና በገዛ እጃችን መለወጥ አንችልም። በተለወጠው አዲስ አድራሻችን ለዘላለም እንንኖራለን።  አቋማዊ ቅድስና የእግዚአብሔር ስራ ነው። እግዚአብሔር “ከእርሱ (ከክርስቶስ) ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን” (ኤፌ. 2:6 ) የሚለው አረፍተ ነገር በሃላፊ ጊዜ መቀመጡን እናስተውል። ስፍራችን ተቀይሯል። አቋማዊ ቅድስና ማለትም ይህነኑ ማለት ነው። እርሱ ማለትም እግዚአብሔር አስቀምጦታልና አማኝ በዚህ ስፍራ ለዘላለም ይኖራል። አቋማዊ ቅድስና በእኛ ስሜት ላይ የተመሰረት ባለመሆኑ በሰማያዊ ስፍራ ያለነው ስለተሰማን ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል የሚያረጋግጠው የድነት እውነታ ስለሆነ ብቻ ነው።  ይህንንም በእምነት እንቀበላልን።  ዛሬ በምድር ላይ ያለን ተግባራዊ ልምምድ ከመንፈሳዊ አድራሻችን አንጻር ያማይጣጣም መስሎ በሚሰማን ወቅትም ቢሆን እንኳ ስፍራችን (አቋማዊ ቅድስናችን) አይቀየርም፤ ስሜታችን የእግዚአብሔር ቃል ያወጀውን መንፈሳዊ እውነታ አይቀይረውም።

አቋማዊ ቅድስና ያሚያስተላልፈውን መንፈሳዊ እውነታ በአግባቡ ላልተረዳ ሰው አማኙን መረን የሚለቅ ትምሕርት ሊመስል ይችላል። በመሰረቱ፣ አቋማዊ ቅድስና አማኙን ቀጣይነት ወዳለው ቅድስና የሚመራ የአዲስ ሕይወት መነሻ እንጂ የአሮጌው ሕይወት ልምምድ ላይሰንስ (ፈቃድ) አይደለም። ይህም በአማኙ ሕይወት ውስጥ በየጊዜው እያደገ የሚሄድ የመልካም ምግባር ፍሬን ያፈራል ማለት ነው። ዳግም ልደት ያገኙ አማኞች አዲሱ ተፈጥሯቸው ግድ ያሚላቸውን የአዲሱን ተፈጥሮ ባሕሪይ መለማምድ ይጀምራሉ። የመንፈሳዊ አድራሻ ለውጣቸው በምድር ላይ በሚኖሩት የእለት ተእለት ሕይወታቸው ላይ አወንታዊ ለውጥ ማሳደር ይጀምራል። ይህም በየእለቱ እያደገ በሚሔድ የባሕሪይ/የስነ-ምግባር ለውጥ እየታየ ይሄዳል (1ጴጥ.1:15-16)። ይህንንም ቅድስና ቢሆን፣ አቋማዊ ቅድስናን በኛ የሰራው መንፈስ ቅዱስ በታዘዝነው መጠን በእኛ ውስጥ የሚያደርገው ይሆናል።

ለማጠቃለል ያህል፣ አቋማዊ ቅድስናችንን ስናገኝ፣ ቀጣይነት ያለው የመቀደስ ሂደት በሕይወታችን ተግባራዊ መሆን ይጀምራል። ቀጣይነት ያለው መቀደስ ክርስቶስን እየመሰሉ የማድግ የሕይወት ዘመን ሂደት ነው። መንፈስ ቅዱስን በታዘዝነው መጠን እና ሕይወታችንን እንዲቆጣጠር በፈቀድንለት መጠን ክርስቶስን በመምሰል እናድጋለን (ሮሜ. 8:29፤ 2ቆሮ. 3:18)። አቋማዊ ቅድስናችንን ስናገኝ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል እንደመሳሪያነት በመጠቀም ይህንን ቀጣይነት ያለውን የመቀደስ ሂደት በሕይወታችን እውን ያደርጋል (ዮሐ. 17:17)። ምግባራዊ ቅድስናችን የሰማያዊ ቅድስናችን ነጸብራቅ እስኪምስል ድርስ እለት ተእለት ክርስቶስን እየመሰልን እናድጋልን (1ዮሐ. 3:2)።

ምንጭ፣ https://www.gotquestions.org/

ትርጉም፣ አዳነው ዲሮ ዳባ

2 thoughts on “አቋማዊ (positional) ቅድስና ምን ማለት ነው?”

  1. Pingback: ጌታን ከተቀበልኩ በኋላ ኃጢአት ሰርቼ ንስሃ ሳልገባ ብሞት ወዴት ነው የምሄደው? – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply to tsegaewnetCancel reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading