እግዚአብሔር በኃጢአት ልምምድ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖችን ጸሎት ይሰማል?

ዛሬ ማለዳ ወደ መስሪያ ቤቴ እየሄድኩ በአይምሮዬ አንድ ሃሳብ ይዤ ከራሴ ጋር እሟገት ነበር። በልቤ ወደ እግዚአብሔር አንድ ጸሎት ጸለይኩ። በጸሎቴ ማብቂያ ላይ “እግዚአብሔር ጸሎቴን የሚሰማበት ምክንያት ምንድን ነው?” ብዬ ራሴን ጠየኩ። ሁላችን በክርስቶስ ስራ በአብ ፊት የመታየት ድፍረትና መብት እንዳለን ባውቅም፤ ጸሎታችንም ስለስሙ በአብ ዘንድ እንደሚሰማልን ብረዳም፤ ጉዳዩ እዚህ ላይ ብቻ እንደማያበቃና የኔ ድርሻ እንደሚቀር ያወቀችው ነፍሴ ነች እንግዲህ ይህን ጥያቄ እንዳነሳ የሞገተችኝ።

እግዚአብሔር ሁሉን ያውቃል፤ የማንኛውንም ሰው ጸሎት ይሰማልም። መስማት ባይችል፣ ሁሉን አዋቂ አያደርገውምና (1ዮሐ. 3:20፤ መዝ. 139:1-4)። ሆኖም እዚህ ቦታ ላይ የተነሳው ጥያቄ እንድምታ እግዚአብሔር ያደምጣል/አያድምጥም ሳይሆን፣ በኃጢአት ልምምድ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖችን ጸሎት ሰምቶ ምላሽ ይሰጣል ወይ ነው።

ስለ ጸሎት አንስተን ስናወራ ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ጤናማ ሕብረት ማንሳታችን የግድ ነው። ጸሎት እና ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ጤናማ ሕብረት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸውና። ይህ ሕብረት ጤናማና ጠንካራ ሲሆን በእግዚአብሔር ፊት ጸሎታችን ሞገስ ይኖረዋል። ሲታመም ወይም ሲታወክ ደግሞ እግዚአብሔር ለጸሎቶቻችን ጀርባውን ይሰጣል።

ለመሆኑ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ጤናማ ሕብረት ማለት ምን ማለት ነው? ጤናማ ሕብረት ማለት ያለሃጢአት መኖር ማለት አይደለም። እንዲህ አይነቱ ሕይወት በምድር ላይ የለምና። የጤናማ ሕብረት መለኪያዎች መንፈስ ቅዱስና ሕሊናችን ናቸው። በአሁኑ ሰአት ነፍሳችን ከመንፈስ ቅዱስና ከሕሊናችን ወቀሳዎች ነጻ ከሆነች፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሕብረት ጤናማ ነው ማለት ነው። ነፍሳችን ከመንፈስ ቅዱስና ከሕሊናችን ወቀሳዎች ነጻ ናት ማለት ግን ፈጽሞ ሃጢአት የለብንም ማለት እንዳልሆነ ልብ ይበሉ።

«ሕሊናዬ ንፁሕ ነው፤ ይህ ግን ጥፋት አልባ መሆኔን አያረጋግጥም፤ በእኔ ላይ የሚፈርድ ጌታ ነው።» (1ቆሮ 4፣4 አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

ከሕሊና ክስ ነጻ መሆናችን የሚያረጋግጠው ከበደል ነጻ መሆናችንን ሳይሆን ዛሬ ላይ (አሁን) ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሕብረት ጤናማ መሆኑን ብቻ ነው። በተጓዳኝ፣ በመንፈስ ቅዱስ አልተወቀሰንም ማለት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሕብረት ጤናማ መሆኑን ያሳያል እንጂ ፍጹም (ከበደል የነጻን) መሆናችንን ከቶ አይናገርም። ይህንን ጉዳይ ይበልጥ ለመረዳት ከዚህ በታች የቀረበውን ምሳሌ አብረን እንመልከት።

በሃሳባችን ወደ አንድ የቤታችን ክፍል ውስጥ እንግባ። በክፍሉ ያለውን አየር ስንቃኝ ሁል ጊዜ በአግባቡ የምንይዘው ክፍል ስለሆነ ንጹህ መስሎ ሊታየን ይችላል። ይህ ንጽህና ከእኛ እይታ አንጻር ነው። በክፍሉ አሁን ካለው ብርሃን የበለጠና የደመቀ የብርኃን ጨረር ቢያበራ ግን በቅፅበት በአየሩ ላይ ቀድሞ ያላስተዋልነውን ቁጥር ስፍር የሌለውን አቧራ ማየት እንጀምራለን። ይሄ እይታ ደግሞ የእግዚአብሔር እይታን ይወክላል፡፡ በዚህ መሳሌ ውስጥ አይናችን ሕሊናችንን፣ ደማቁ የብርሃን ጨረር ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ይወክላሉ። በልባችን ያለውን ቆሻሻ አላየንም ማለት ቆሻሻው በልባችን ውስጥ ፈጽሞ የለም ማለት አይደለም። ከሕሊናችን ለጊዜ ተሰውሯል ማለት እንጂ። በልባችን ውስጥ ያለውን ቁጥር ስፍር የሌለው ሃጢአት አልተገነዘብንም ማለት የሃጢአቱን አለመኖር አያረጋግጥም። እግዚአብሔር ለጊዜው በእነዚህ ሃጢአቶች ተጠያቂ ሊያደርገን አልፈቀደም ማለት እንጂ። እግዚአብሔር ሁሉንም ሃጢአቶቻችንን በአንድ ጊዜ ወደ ግንዛቢያችን በማምጣት (ብርሃኑን በማብራት) ተገቢውን ምላሽ እንድንሰጥ አያደርግም። ይህ ሂደት የሕይወት ዘመን ነው። እንደደረስንበት መንፈሳዊ አቅም፣ በጊዜው የእኛን ትኩረት ሊያገኝ በፈለገው ጉዳይ (አቧራ) ላይ ብቻ ተጠያቂ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚሰራው አንደ እንደ ደረስንበት የብስለት ደረጃ እና ከእርሱ ለመማር እንደምናሳየው ፈቃድ መጠን መሆኑን አንዘንጋ፡፡ መኖራቸውን ባላወቅን ወቅትም ቢሆን እንኳ የአቧራ ብናኞቹ በቦታቸው መኖራቸውን መዘንጋት የሌለብን ነጥብ ነው፡፡ ይህ ማለት ሃጢአተኝነት በማይሰማንም ወቅት ቢሆን እንኳ ሃጢአተኞች ነን ማለት ነው። ነገር ግን ይህ አይነቱ ሃጢአተኝነት አይደልም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ሕብረት የሚያውከው። በመንፈስ ቅዱስ ብርሃን ለሕሊናችን አይን የተገለጡትና ዛሬ ላይ የምንወቀስበት ሃጢአቶች እንጂ። እዚህ ላይ የእኛ ሃላፊነት ሊሆን የሚገባው፣ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የነቃ ሕብረት በማድረግ የትኞቹን መረዳቶቻችንን እና የትኞቹን ባሕሪያቶቻችንን ሊለውጥ እንደፈለገ ማወቅና የንስሃ ምላሽ መስጠት ነው፡፡

ከላይ እንደተገለጠው ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሕብረት ያሚታወከው ወይም ጸሎታችን ምላሽ ያሚያጣው መንፈስ ቅዱስ ወይም ሕሊናችን ዛሬ ተጠያቂ በሚያደርገን ማለትም በሚወቅሰንና ባልተናዘዝነው ሃጢአት ምክንያት ብቻ ነው። በልባችን ክፋትን ይዘን (መዝ. 66:18)፣ በአመጻችን ለመኖር ወስነን፣ ያለ እግዚአብሔር ፍርሃት ለመኖር መርጠን (ምሳሌ 1:28-30) እግዚአብሔር ጸሎታችንን ሰምቶ ምላሽ እንደሚሰጠን ብንጠብቅ ተሳስተናል።

“በልቤስ በደልን አይቼ ብሆን ጌታ አይሰማኝም ነበር።” መዝ. 66:18
“ሃጢአትን በልቤ አስተናግጄ ቢሆን ኖሮ፣ ጌታ ባልሰማኝ ነበር።” መዝ. 66:18 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

“የዚያን ጊዜ ይጠሩኛል፥ እኔ ግን አልመልስም፤ ተግተው ይሹኛል፥ ነገር ግን አያገኙኝም። እውቀትን ጠልተዋልና፥ እግዚአብሔርንም መፍራት አልመረጡምና፤ ምክሬን አልፈቀዱምና፥ ዘለፋዬንም ሁሉ ንቀዋልና፤” ምሳሌ 1:28-30

“እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል።” ኢሳ. 1:15

“ሕግን ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ጸሎቱ አስጸያፊ ናት።” ምሳሌ 28:9

“ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም፤ ለራሳችሁ ስጋዊ ደስታ በማሰብ በክፉ ምኞት ትልምናላችሁና።” ያእቆብ 4:3 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

ለታወከው ሕብረታችን ብቸኛው መፍትሄው ንስሃ መግባትና ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ሕብረት ማደስ ነው። ጸሎት ከዚህ ይጀምራል። ሕብረታችን ታሞ ልናደርግ የምንችለው የሚሰማ ጸሎት ቢኖር አንድ ብቻ ነው። እርሱም የንስሃ ጸሎት ይባላል (1ዮሐ. 1:9)። ከዛ በተረፈ ሕብረታችን ታውኮ ማለትም መንፍስ ቅዱስና ሕሊናችን ተጠያቂ በሚያደርገን ሃጢአት ላይ ጀርባ ሰጥተን የምንጸልየው ጸሎት የእግዚአብሔርን ፊት አያይም። ከንቱ ድክም ብቻ ይሆናል። ከዚህ የፍቅር አምላክ ጋር ጤናማ ሕብረት ፈጥረን ያምንኖርበትን ጸጋ እንያዝ። ጸሎታችንም በፊቱ ሞገስ ያግኝ። አሜን!!!

4 thoughts on “እግዚአብሔር በኃጢአት ልምምድ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖችን ጸሎት ይሰማል?”

 1. Rahel Yeshitila

  በጣም ትክክለኛ መለስ ነው የመለስከው ለጥያቄህ:: የንሰሀ ፀሎት: ተደርጎልህ የምስጋና ፀሎት: ስለእግዚአብሄር እግዚአብሄርነቱ እያወደሱ ፀሎት: በጣም ቀላል ነው ፀሎትን ለተለማመደ ሰው:: ነገር ግን የጥያቄ : የልመና: ፀሎት ልበለው ቃሉ ስለሚል ( ጠይቁ ለምኑ ፈልጉ) ስለሚል በጣም አስቸናቂ ነው:: ለምሳሌ የትዳር :የልጅ: የጤነት: የስራ …ጥያቄ ይኖረንና ባይመለስልን: ያልተመለሰልን ከኔ ችግር ነው ? ወይስ እግዚአብሄር ሊያደርግልኝ ስላልፈለገ ነው:? ብለን ጥያቄ ይኖርብናል:: እህቴ ለባል ትፀልያለች: ጎደኛዬ ለልጅ እና አመታት አፉ:: የፀለይነውን ሁሉ እንደማንቀበል ነገርግን ለኛ የሚያስፈልገንን የሚሰጠን አባት እንዳለን ቢገባኝም: የአንዳንድ ጥያቄዎች አለመመለስ ግን ሚስጢሩ ለእግዚአብሄር ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ: ተባረክ: በፁሁፎችህ በጣም ነው የምባረክባቸው: ፀጋውን አብዝቶ ይጨምርልህ::

 2. Gezahagne Gebermichael

  በጣም ጠቃሚ ትምህርት ነው፡፡ አማኝ ሁል ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነተ በመፈተሽ ግንኙነቱን ጤናማ ማድረግ ይገባዋል፡፡ በትምህርቱ ላይ እንደተገለፀው መንገዱ ደግሞ ዘወትር በፊቱ በንስሀ መሆን ነው፡፡ በተጨማሪ መጠየቅ የምፈልገው ይህን ትምህርት በቀጣይነት ለመማር ስለምፈልግ ትምህርቱ በወቅቱ እንዲደርሰኝ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ብትገልፁልኝ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ጌታ አብዝቶ ይባርካችሁ!!

  1. ወንድሜ ገዛኀኝ፣
   ለዝግጅት ክፍላችን ምስጋናህን እና ጥያቄህን ስላደረስከን ምስጋናዬን አቀርባለው፡፡  
   ለዝግጅት ክፍላችን መልዕክትህን ስላደረስከን ምስጋናዬን አቀርባለው፡፡  
   የወንጌል በድረ ገጽ አገልግሎት ዌብ ሳይት (https://ethiopiansite.com/) በርካታ መንፈሳዊ ጽሑፎችን የያዘ ሳይት ነው፡፡ በዌብ ሳይቱ ለአዳዲስ አማኞች የሚሆን የድነት (የደኅንነት) ትምሕርቶች፣ ለሰነበቱ አማኞች የሚሆን የደቀ መዝሙር ማሰልጠኛዎች፣ ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጽሐፎችን ያካተተ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማቴሪያሎችን፣ ለተለያዩ መንፈሳዊ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ አጫጭር የጥናት ጽሑፎች፣ ወዘተ ተካተዋል፡፡ እንግዲህ እንደ ምርህ ሊንኮቹን በመጫን ጥናትህን ማካሄድ ትችላለህ፡፡      
   የወንጌል በድረገጽ ዌብ ሳይት ተከታታይ (follower) ለመሆን የምትሻ ከሆነ የወንጌል በድረ-ገጽ አገልግሎት ዌብ ሣይት (https://ethiopiansite.com/) የፊት ገጽ ግርጌ ላይ በመሄድ፣ በስተቀኝ ባልው ክፍት ሣጥን ውስጥ የኢ-ሜይል አድራሻህን በመጻፍና “ድረ-ገጹን ይከታተሉ” የሚለውን ቁልፍ በመጫን የዌብ ሣይቱ ተከታይ (follower) መሆን ትችላለህ፡፡ ይህን ስታደርግ በዌብ ሣይቱ ላይ አዳዲስ ጽሑፎች ሲጫኑ፣ በኢ-ሜይል አድራሻህ የማንቂያ መልእክት (notification) የምታገኝ ይሆናል፡፡ 
   ከዚህ በተጨማሪ የግል ጥያቄዎች ቢኖርህ በሚከተለው ኢሜይል ልትልክልኝ ትችላለህ፣ በደስታ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ (tsegaewnet@gmail.com)፡፡
   የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከአንተና ቤተሰብህ ጋር ይሁን። አሜን።

Leave a Reply

%d bloggers like this: