ምዕራፍ 9 – ምስክርነት

ጸሎት

‹‹አባት ሆይ፣ ይህችን ምድር ዳግመኛ ለመግዛት በምታደርገው ሂደት ውስጥ እንደ እኔ አይነቱን ሰው ለመጠቀም ስላሳየኸው ፍላጎት አመሰግንሃለው፡፡ የሚጠቅም እቃ ሆኜ እንዳገለግልህ ፍቅር፣ እውቀት እና ከቅዱስ መንፈስህ ጋር ጤናማ ሕብረት ስጠኝ፡፡ አሜን፡፡››

ስለምስክርነት ማወቅ ለምን ያስፈልጋል?

ሉጊ ታሪሶ የታሪክ ማህደር ከሚያስታውሳቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በ1792 በጣሊያን ሚላን የተወለደ ሲሆን በመጀመሪያ የአናፂነት ሙያ ሰልጣኝ ተማሪ ነበር፡፡ ታሪሶ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለየት ያሉ ቫዮሊኖችን ለመሰብሰብ ሲል ያላካለለው አገር አልነበረም፡፡ በምርጥ ሞያተኞች የተሰሩ ልዩ ቮዮሊኖችን በማደን ልዩ ተሰጥኦ ነበረው፡፡ እነዚህን ቫዮሊኖች ገዝቶ በጥንቃቄ በመኪናው ጭኖ ካመጣቸው በኃላ በትንሿ መኖርያ ቤቱ ውስጥ ያስቀምጣቸዋል፡፡ የእለት ችግሩን ለመፍታት ከሸጣቸው ጥቂት ቫዮሊኖች በስተቀር የገዛቸው በርካታዎቹ ቫዮሊኖች በመኖሪያ ቤቱ ደብቆ አስቀምጡአቸዋል፡፡ አንዳንድ የአለማችን ታዋቂ ሙዚቀኞች እነዚህን ቫዮሊኖች ለመጎብኘት ወደ ታሪሶ ይመጡ ነበር፡፡ እንዲጫወቱ ግን ፈፅሞ አይፈቅድላቸውም ነበር፡፡

ከቫዮሊኖቹ ሀሉ ለእርሱ ልዩ የነበረው በአንቶኒዮ ስትራዲቫሪ የተበጀው ቫዮሊን ነበር፡፡ ታሪሶ በዚህ ቫዮሊን ውበት በጣም ቢኩራራም በግላጭ አውጥቶ ለማሳየት ግን አይፈቅድም ነበር፡፡ አንድም ጊዜ አውጥቶ አሳይቶት አያውቅም፡፡ ስሙን ‹‹መሲህ›› ብሎ ሰይሞታል ምክንያቱንም ሲገልጽ ‹‹ቫዮሊኑ፣ እንደምንጠብቀው ግን እንደማናየው መሲህ ስለሆነ ነው›› ይላል፡፡

ታሪሶ በ1854 ከዚህ አለም በሞት ሲለይ በቆሻሻ መኖሪያው መሲሁን ጨምሮ 246 የሚደርሱ ውብ ቫዮሊኖች ተቀምጠው ተገኙ፡፡ ለቫዮሊን ካለው ልዩ ፍቅር የተነሳ እነዚህን ውብ የሙዚቃ መሳሪያዎች ከአለም ሸሽጎ ኖረ፣ ባይቆልፍባቸው ኖሮ ሊሰጡ የሚችሉትንም ጥቅም አስቀረ፡፡

በውስጣችን ያለውን መሲህ (ኢየሱስ) ለሌሎች ሳንገልጠው ይህን ታልቅ የምስራች ዜና በእኛ ውስጥ ቆልፈን እንድንኖር እግዚአብሔር አይፈልግም፡፡ ጌታ ኢያሱስ በእኛ ውስጥ ከመኖሩ የተነሳ ሕይወታችን በሚያስደንቅ ሁኔታ ተባርኳል፣ ነገር ግን የእርሱ ምኞት አለሙ ሁሉ ይህን በርከት እንዲካፈል ጭምር ነው፡፡ ይህንን የምስራች ማንም ሊደርስበት በማይችለው የሕይወታችን አፓርትመንት ውስጥ ሸሽገነው እስከመቼ በስስት እንኖራለን?

የካምፓስ ክሩሴድ ለክርስቶስ መስራች የሆነው ቢልብራይት ብዙ ጊዜ እንደሚጠይቀው፣ ‹‹በሕይወትህ ላይ የሆነልህ ታላቅ ነገር ምንድን ነው?›› ተብለን ብንጠየቅ፣ የብዙዎቻችን መልስ፣ ‹‹ክርስቶስን እንደ ግል አዳኜ ማወቄ፣›› ብለን ምላሽ እንሰጥ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የተቀበልነው ሕይወት ዘላለማዊ ነውና፡፡ የዚህ ሰው የሁል ጊዜ ቀጣይ ጥያቄ፣ ‹‹እናስ፣ ለሌላው ሰው ልታደርግ የምትችለው ታላቅ ነገር ምንድን ነው?›› የሚል ሲሆን፣ ጥያቄው ለአንተ ቀርቦ ቢሆን ምላሽህ ምንድን ነው?

በክርስቶስ ላይ ያለህን እምነት ለሌሎች በማካፈል ሃሳብ ላይ ያለህ ስሜትና አስተሳሰብ ምን ይመስላል? ጉዳዩ በውስጥህ ደስታን ይጭራል ወይስ ፍርሃትን? ድፍረት ይሰማሀል ወይስ አንድ አንድ ጊዜ ሊደርስብህ የሚችለው ተቀባይነት የማጣት ስሜት ያስፈራሃል? በራስ የመተማመን ስሜት ይሰማሀል ወይስ ግር ትሰኛለህ? የግዴታ ስሜት ይሰማሃል ወይስ የፈቃደኝነት?

‹‹በእኔ እምነት በዘመናት ሁሉ የክርስቲያኖች መካከል በስፋት ተሰራጭቶ የሚገኘው የተሳሳተ ግምት፣ ሰዎች እግዚአብሔርን አይሹም – የሚለው ነው፡፡ በተለያዩ አገሮች ስጓዝ ያገኘሁት በቂ ማስረጃ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በበርካቶች ልብ ውስጥ እግዚአብሔርን የመፈለግ ረሀብን ፈጥሮ ተመልክቻለሁ፡፡›› ቢል ብራይት

ወንጌል ምንድን ነው?

ከዚህ በታች ወንጌልን በአጭሩ የሚገለጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ቀርበዋል፡፡ ካነበብካቸው በኃላ በውስጣቸው ስለ ወንጌል የያዙትን ፍሬ ሃሳብ ፃፍ፡፡

  1. ዮሐንስ 3፡16
  2. ሉቃስ 24፡46-48
  3. 1ቆሮንቶስ 15፡3-4

ተጨማሪ ምልከታ፡- ‹‹ወንጌል የሚለው ቃል የግሪክ አቻ ቃሉ evangelion ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹የምስራች›› ወይም ‹‹አስደሳች ዜና›› ማለት ነው፡፡ ይህ ቃል ‹‹evangelism›› ለሚለው ቃል ስርወ ቃልም ጭምር ነው፡፡

የወንጌል በአጭሩ፡- ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በኃጢአት ምክንያት በደለኛ ነው፡፡ የኃጢአት ደምዎዝ ሞት (ለዘላለም ከእግዚአብሔር ተለይቶ መኖር) ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ታላቅ ፍቅር የተነሳ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአታችንን ቅጣት ይቀበልልን ዘንድ በመስቀል ላይ ስለኛ እንዲሞት ላከው፡፡ ከሦስት ቀን በኋላ ከሙታን መካከል ተለይቶ ተነሳ፣ ሕያው ሆኖ ለዘላለም ይኖራል፡፡ አንድ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እና ከዘላለም ሞት ሊያድነው እንደሚችል ቢያምን ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ተደርጎ ይቆጠራል፣ የዘላለም ሕይወትን ይወርሳል፡፡

ምስክርነት ምንድን ነው?

‹‹ምስክርነት፣ የኢየሱስን ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ለሌሎች ለማካፈል መነሳሳት እና ውጤቱን ለእግአዚብሔር መተው ነው፡፡›› ቢል ብራይት

በግርድፉ፣ ምስክርነት የምታውቀውን ነገር መናገር ማለት ነው፡፡ ልክ ጴጥሮስና ዮሐንስ የአይሁድ ባለስልጣናት ስለ ኢየሱስ እንዳይመሰክሩ ባስጠነቀቋቸው ጊዜ እንደመለሱላቸው ማለት ነው – ‹‹እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም፡፡›› (የሐዋርያት ሥራ 4፡20) ፡፡ ስለ ኢየሱስ ምን ሰምተሀል፣ ምንስ አይተሃል? ይህንን እርሱን ለማያውቁ ሌሎች ሰዎች ስታካፍል እየመሰከርክ ነው፡፡

እስቲ በችሎት ውስጥ ያለውን ትእይንት እንመልከት፡፡ በችሎት ያሉ ሰዎች ሁሉ የራሳቸው የሆነ ሚና እና ሃላፊነት አላቸው፡፡ እንደ ‹‹መስካሪ›› የምትጫወታቸው ሚና ምንድን ናቸው?

የከሳሹን ጥፋተኛነት የሚወስኑትን ሰዎች ማሳመን ያንተ (የምስክሩ) ድርሻ ነው? የአንተ ዋነኛ የቤት ስራ እሱ አይደለም፡፡ እንደ አቃቤ – ሕግ መሆን ይኖርብሃል? እንደ ተከላካይ ጠበቃስ? እንደ ዳኛስ? ለሶስቱም ጥያቄዎች መልሱ ፈፅሞ ነው፡፡ እንደ ምስክር ከአንተ የሚጠበቀው ነገር ‹‹ያየኸውንና የሰማኸውን መናገር›› ሲሆን እግዚአብሔር ደግሞ የቀረውን ያከናውናል፡፡

በችሎት ፊት የቀረበ ምስክር የሚጠበቅበት ነገር ‹‹እውነቱን፣ ሁሉንም እውነት፣ እና እውነቱን ብቻ›› መናገር ነው፡፡ እንደ ክርስቶስ ምስክር፣ በሕይወትህ የሆነልህን ነገር አጋነህ ወይም አኮስሰህ በተሳሳተ መንገድ ብትገልጥ ይህ ታማኝነትህን አያሳይም፡፡ እውነትንም መሸሸግ ከዚህ የተለየ ትርጉም አይኖውም፡፡ ማድረግ ያለብህ ነገር የሚሹ ሁሉ ያነቡት ዘንድ ሕይወትህን እንደተገለጠ መጽሐፍ ለሌሎች ማሳየት ነው፡፡ ይህን ካደረግህ በእርግጥ የክርስቶስ ጠቃሚና ውጤታማ ምስክር መሆን ትችላለህ!

በምስክርነት ውስጥ የእግዚአብሔር ድርሻ

‹‹ያየኸውንና የሰማኸውን›› ነገር ለአንድ ሰው ለመመስከር በምትጥርበት ጊዜ እግዚአብሔር ደግሞ ምናልባት አንተም ሆነ የምትመሰክርለት ሰው በማትረዱበት መንገድ ታላቅ ስራን ይሰራል፡፡

ዮሐንስ 16፡7-11 አንብብ፡፡ [በዚህ ክፍል ውስጥ የተገለጸው ‹‹ረዳት›› ወይም ‹‹አጽናኝ›› እግዚአብሔር ከክርስቶስ ትንሳኤ በኋላ የላከው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡] ክፍሉ፣ መንፈስ ቅዱስ ምን እንደሚያደርግ ነው የሚያወራው?

በውጤታማ ምስክርነት ውስጥ የእግዚአብሔር ድርሻ ወሳኝ በመሆኑ፣ በምስክርነት ስልትህ ውስጥ ለጸሎት ቅድሚያ ልትሰጥ ይገባል።

‹‹በወንጌል ስርጭት ወቅት ሁለት ሰአት ከሚፈጅ ንግግር ይልቅ የጥቂት ደቂቃ ጸሎት የበለጠ ስራ ይሰራል፡፡›› ዲ.ኤል.ሙዲ

‹‹ለሰዎች ስለ እግዚአብሔር ከመናገርህ በፊት ስለ ሰዎቹ ለእግዚአብሔር መናገርህን እርግጠኛ ሁን፡፡›› ጆ አልድሪክ

ለምን እመሰክራለሁ?

ከዚህ በታች ለጥያቄው ምላሽ የሚሰጡ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ቀርበውልሃል፡፡ ጥቅሶቹን ካነበብክ በኋላ ያስተዋልከውን ነገር በማስታወሻህ ላይ አስፍር፡፡

  1. ማርቆስ 16፡15
  2. ሉቃስ 19፡10 እና 2ጴጥሮስ 3፡9
  3. ሮሜ 10፡13-14
  4. ዮሐንስ 10፡10
  5. ሉቃስ 9፡26

እንዴት ልመስክር?

ምስክርነት ሁለት በጣም ጠቃሚ ነገሮችን ያካትታል፡፡ በምንኖረው የሕይወት አይነት እንመሰክራለን፤ በተጨማሪም በቃላቶቻችን – በንግግር እንመሰክራለን፡፡ አንዱ ከአንዱ ውጪ ሲሆን በራሱ ሙሉ አይደለም፡፡ ሕይወታችን ክርስቲያን ላልሆኑ ሰዎች የሚናገረው ነገር ይኖረዋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ሕይወታችን በቃላችን የምናካፍለው መልዕክት አውድና ማረጋገጫ ነው፡፡ ቃላችን ደግሞ የመልዕክታችንን ይዘት ይናገራል። የመልዕክታችንን ሕይወት እየኖርነው በቃላችን ባንናገረው ተመልካቹ ምን ማድረግ እንዳለበት ስለማያውቅ ውሳኔ ማድረግ እንዲቸገር እናደርገዋለን፡፡ የምንናገረውን መልዕክት በአኗኗራችን እየተቃረነው ቃሉን ብቻ ብንናገር ደግሞ ሰሚው በምንናገረው ሕይወት አልባ ቃላት ፍላጎት እንዲያጣ እናደርገዋለን፡፡

በሕይወታችን መመስከር

በርካታ ሰዎች ከሚሰሙት ይልቅ ለሚያዩት ነገር ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ አንድ ምሽት ወንጀለኞች በሚበዙበት ሰፈር ስታልፍ አንድ ወንበዴ የሚመስል ሰው በከፊል የተጠጣ የአረቄ ጠርሙስ እና ቅቤ የጠገበ ዱላ በእጁ ጨብጦ በአንድ ጠባብ መተላለፊያ ጠርዝ ላይ ቆሞ ብትመለከት ምን ልታስብ ትችላለህ? ‹‹ይቅርታ አድርግልኝ፣ ለአንድ ደቂቃ ወደ እኔ ቀርበህ ልትረዳኝ ትችላለህ? መነፅሬ ወድቆ ጥፍቶብኝ ነው፣›› ቢልህስ፣ ቀድሞ ስለ ሰውየው ታስብ የነበረውን ሃሳብ እንድትለውጥ ያደርግሃል? ሰውየው እንድትረዳው የቀረበበት መንገድ ስነስርአት የሞላው ቢሆንም ከሰውየው የምትመለከተው ነገር ግን አስደሳች ነገር አይደለም፡፡ በመሆኑም፣ ሰውየውን ቀርቦ ለማውራት አትፈቅድም፡፡

በተመሳሳይ መንገድ፣ ክርስቶስን የማያውቁ ሰዎች ሕይወታችንን በወጉ ያጤናሉ። እናም ድርጊቶቻችን ከምናወራው ነገር ጋር አብረው የሚሄዱ ወይም የማይሄዱ ስለመሆን አለመሆናቸው የራሳቸውን ግምገማ ያደርጋሉ።

ድርጊቶቻችን በምስክርነታችን ወቅት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ስንዘነጋ የእግዚአብሔር መንግስት መስፋፋትን እናውካለን፡፡ 1ቆሮንቶስ 15፡34 አንብብ፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ጳውሎስ፣ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የኃጢአት ድርጊቶቻቸውን ችላ በማለታቸው ምክንያት በአካባቢያቸው በሚኖሩ ኢ -አማኞች ላይ ያሳደሩትን አሉታዊ ተፅእኖ በመጠቆም ይወቅሳቸዋል፡፡ ይህ መልዕክት ዛሬ ላለችው ቤተ ክርስቲያን ምን የሚያስተላልፍ ይመስልሃል?

‹‹ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደቀረበው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጸንተው ቢሮሩ ኖሮ፣ በአሁኑ ሰአት መላዋ ሕንድ ክርስቲያን በሆነች ነበር፡፡›› -ሞሀንዳስ ኬ. ጋንዲ

በቃላችን መመስከር

የማያምኑ ሰዎች እግዚአብሔር በሕይወታችን ደምቆ ማየታቸው እጅግ መልካም ነገር ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ቢቀር ሕይወታችንን ምን እንደዚህ ሊያደርገው እንደቻለ የማወቅ ጉጉት እንዲያድርባቸው ያደርጋልና፡፡ በዚህ ምክንያት ልንነግራቸው ያለውን ነገር ለማድመጥ በሚሹ ግዜ ምን እንበላቸው?

ከዚህ በታች የቀረቡ አራት ቁልፍ ፍሬ ሃሳቦች አንድ አድማጭ በሚገባው መንገድ ከቀረቡ ግለሰቡ ወንጌልን እንዲገነዘብና ክርስቶስን ለመቀበል ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ይረዳዋል፡፡

  1. እግዚአብሔር እያንዳንዱን ሰው ያፈቅራል፡፡ እያንዳንዳችን ከእርሱ ጋር ዘላለማዊ ሕብረት እንዲኖረን አድርጎ ነው የፈጠረን።

‘በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና’ ዮሐንስ 3፡16። በጥቅሱ መሠረት፣ እግዚአብሔር ልጁን ለሰው ልጆች ኃጢአት እንዲሞት የላከበት ዋነና አነሳሽ ምክንያት ምንድን ነው?

  1. ሁሉ ኃጢአትን ሰርቷል፣ ይህም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረንን ሕብረት አውኳል፣ ችግሩ ካልተፈታ የዚህ ነገር መጨረሻው ለዘላለም ከእርሱ ተለይቶ መኖር ነው፡፡ ‘ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤’ሮሜ 3፡23
  • በጥቅሱ መሠረት ምን ያህሉ ሰዎች ናቸው ኃጢአትን የሠሩት?
  • እግዚአብሔር በክርስቶስ ያዘጋጀው ድነት የሚያስፈልጋቸው ምን ያህሉ ናቸው?
  1. ከእግዚአብሔር ጋር የነበረን ሕብረት ዳግም ይታደስ ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአታችንን ዋጋ እንዲከፍል፣ እግዚአብሔር ልጁን ላከ፡፡

በ1ጴጥሮስ 3፡18 መሠረት እግዚአብሔር ክርስቶስ ለሰው ልጆች እንዲሞት ወደ ምድር የላከበት ምክንያት ምንድን ነው? ኢየሱስ ከሞተ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ዳግመኛ ሕያው ሆኗል፡፡ ትንሳኤው ሲከተሉት ለነበሩትና የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ለነገራቸው ምን የሚያስረዳው ነገር አለ?

  1. ክርስቶስን በገዛ ፈቃዳችን በእምነት ስንቀበል የኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕትነት ለእያንዳንዳችን ይቆጠርልናል፡፡
  •  ከዚህ በፊት የተገለጹትን ሦስቱን ነጥቦች ብቻ ማወቅ በቂ ነው ወይስ በዮሐንስ 1፡12 ላይ እንደተገለጸው መውሰድ የሚገባን አስፈላጊ እርምጃ ይኖር ይሆን?
  • ካለ ይህ አስፈላጊ የሆነ ድርጊት ምንድን ነው?
  • አንድ ሰው ከክርስቲያን ቤተሰብ በመወለዱ ክርስቲያን ሊሆን ይችላል?

ተጨማሪ ምልከታ፡- በምትመሰክርበት ጊዜ አመቺ በሆነ ጊዜ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቀም፡፡ ለአብነት ያህል የምታስታውሰውን ጥቅስ አካፍል፤ አልያም መጽሐፍ ቅዱስህን በመግለጥ ግለሰቡ ክፍሉን በቃሉ እንዲያነብ ጋብዝ፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ተመስርቶ ወንጌልን ለሌሎች ማካፈል ወንጌልን የመመስከር አንዱ አካሄድ ሲሆን ስለራስህ መንፈሳዊ ሕይወት ምስክርነት በማቅረብ ወንጌልን መመስከርም በአግባቡ ከተተገበረ ሌላው ውጤታማ አካሄድ ነው።

ከ 3 ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የራስህን ምስክርነት ለማካፈል ዝግጅት አድርግ፡፡ ስለ ራስህ የምትመሰክረው ምስክርነት ብዙውን ጊዜ ሦስት ክፍሎች ይኖሩት፡-

  1. አስቀድሞ – ክርስቶስን ከመቀበልህ በፊት ሕይወትህ ምን እንደሚመስል
  2. እንዴት – እንዴት ክርስቶን ለመቀበል እንደወሰንክ
  3. በኃላ – ክርስቶስን ከተቀበልክ በኃላ ሕይወትህ ምን እንደሚመስል

ስለ ራስህ ሕይወት በምትመሰክርበት ጊዜ የወንጌሉን መልዕክት ማካተትህ በጣም ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ምስክርነትህን በምታጠናቅቅበት ጊዜ አድማጩ ክርስቶስ እንደሚያስፈልገውና እንዴት ክርስቲያን መሆን እንደሚችል መረጃ ይሰጠዋልና፡፡

የሐዋሪያት ሥራ 26፡1-23 አንብብ፡፡ ጳውሎስ በአይሁድ ቁጥጥር በመሆን እስር ቤት ከገባ በኃላ በንጉሥ አግሪጳ ፊት እንዲቀርብ ተደረገ፡፡ ለጳውሎስ የራሱን ምስክርነት ለማካፈል ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነበር! የጳውሎስን ምስክርነት ከዚህ በታች በቀረቡት አራት ክፍሎች ስር መድበህ አስፍር፡-

  1. የጳውሎ ሕይወት አስቀድሞ ቁጥር 1-11
  2. ጳውሎስ እንዴት እንደ ዳነ ቁጥር 12-18
  3. የጳዉሎስ ሕይወት ከዳነ በኃላ  ቁጥር 19-23
  4. ስለ ወንጌል የሚናገሩ ጥቅሶች

ሰዎች ምስክርነቴን ቢቃወሙስ?

አንዳንድ ሰዎች ወንጌልን መስማት ላይፈልጉ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የሚቃወሙት አንተን እንዳልሆነ ልታስታውስ ይገባሃል፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚቃወሙት ወይም የማይቀበሉት አዳኝ እንደሚያስፈልጋቸው የሚሞግታቸውን መንፈስ ቅዱስን ነው፡፡ ስለዚህ አንተን እንደተቃወሙህ አድርገህ አትቁጠር፡፡

ሌላው ልታስታውሰው የሚገባህ ነጥብ – ከምስክርነት በኋላ ሁል ጊዜ የሚታይ ውጤት መጠበቅ የለብህም፡፡ በመሠከርከው መጠን የሚለወጡ ሰዎች አሉ ብለህ አትደምድም! በእርግጥ ምስክርነት በሂደት ውጤትን ሊወልድ ይችላል፡፡ በርካቶቹ ክርስቲያኖች (በተለይም ጎልማሶች) ጌታን ለመቀበል ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ሰይጣን ለዘመናት በሕይወታቸው ውስጥ የዘራውን ለመንቀልና ጥራጣሬያቸውን ለማጥፋት ጊዜ ያስፈልጋቸው ይሆናል፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ ሰው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ከአምስት ወይም አስር የተለያዩ ምንጮች የምስራቹን ዜና እየሰማ ጥቂት በጥቂት ወደ ወንጌሉ መቅረብ ያስፈልገው ይሆናል፡፡ ወንጌል ለአንድ ሰው በነገርህ ቁጥር ይህን ሰው ለጌታ ይበልጥ ቅርብ እያደረከው ነው፡፡

  1. 1ቆሮንቶስ 3፡5-10 አንብብ፡፡ በመስካሪዎች መካከል ያለውን የጋራ ሥራ አስተዋልክ? (አጵሎስ እንደ ጳውሎስ ያለ ወንጌላዊ ነበር) ፡፡ ‹‹እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስም አጠጣ—›› (ቁጥር 9 ) የሚለው አረፍተ ነገር ምን ማለት ይመስልሃል?
  2. ጳውሎስ፣ በቁጥር 7 ላይ ‹‹—የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም፡፡›› ሲል ምን ማስተላለፍ ፈልጎ ይመስልሃል?

ጥያቄአቸውን መመለስ ቢያቅተኝስ?

ሰዎች ስለ ክርስትና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጥያቄዎችን ያነሱ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ጥያቄዎች በእምነታቸው ፊት የተጋረጡ እንቅፋቶች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሌላ ጊዜ ግን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛቸው ላለመቀበል የሚደነቅሯቸው ሰበቦች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የገጠመህ ሰው የትኛው እንደሆነ እንዲገልጽልህ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ታመን፡፡

ወንጌልን በምትመሠክርበት ጊዜ የምስክርነትህን መስመር የሚያስለቅቅ ጥያቄ ቢነሳብህ፣ ‹‹ጥሩ ጥያቄ ነው፤ ትያቄው ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን አሁን ወደ ጀመርነው ነጥብ እንመለስና በዚህ ሂደት ውስጥ ጥያቄው ካልተመለሰ፣ በኃላ እንደገና ጥያቄውን ልታነሳ ትችላለህ፡፡›› በማለት አላማህ ግቡን እንዲመታ ጣር፡፡

ተገቢ ጥያቄ ተጠይቀህ መልሱን የማታውቀው ከሆነ ደግሞ፣ ‹‹መልሱን አላውቅም፤ ነገር ግን በሌላ ጊዜ ለጥያቄው ምላሽ እንድታገኝ አደርጋለው፡፡›› በማለት መልስ፡፡ ከዛ በኃላ ምላሹን ለማግኘት ጥረት አድርግ!

  • በ 2ጢሞቴዎስ 2፡16፣ 2-26 ላይ ጳውሎስ ለወጣት ደቀመዝሙሩ፣ ጢሞቴዎስ ምን አይነት ምክር መከረው?

የምስክርነት ውይይት እንዴት አድርጌ ልጀምር?

ውይይትን በጥያቄ መጀመር የተሻለ መንገድ ነው፡፡ የሐዋሪያት ሥራ 8፡26 አንብብ፡፡ ፊሊጶስ ለኢትዮጵያዊው ሰው በሚመሰክርበት ጊዜ እንዴት አድርጎ ጀመረ?

ውይይት ለመጀመር የሚረዱ ጥቂት ነጥቦች እነሆ፡-

  • ስለ መንፈሳዊ ነገሮች (ወይም ስለ እግዚአብሔር፣ ከሞት በኃላ ስላለ ሕይወት) አስበህ ታውቃለህ?
  • መንፈሳዊ ሕይወትህ ምን ይመስላል?
  • ወደ ቤተ ክርስቲያን ትሄዳለህ? ለምን? በቤተ ክርስቲያናችሁ ስለ ምንድን ነው የምትማሩት?
  • ከእግዚአብሔር ጋር ባለህ ሕብረት ረክተሃል ወይስ አንድ የሚጎድል ነገር እንዳለ ይሰማሃል?
  • ያደረከውን መስቀል ተመልክቼዋለሁ፣ ክርስቲያን ነህ? [ካለሆነ፡-] ይህ መስቀል የሚወክለውን ነገር ለማወቅ ፈቃደኛ ነህ?
  • ስለ አራቱ መንፈሳዊ ሕጎች ሰምተህ ታውቃለህ?
  • ስለ ክርስቲያናዊ ሥነ ስርአት አንስተህ፡- ስለዚህ ነገር ምን ታስባለህ? ትርጉም ይሰጥሃል? ተጨማሪ ነገር መስማት ትፈልጋለህ?
  • ለምታውቀው ሰው፡- ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት ሕብረት እንደጀመርኩ ነግሬህ አውቃለሁ?

ከሕይወትህ ጋር ማዛመድ

ልትጸልይላቸው የሚገባህን የ 10 ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎችን ስም ዝርዝር ፃፍ፡-

  • ለእነዚህ ሰዎች ያለማቋረጥ ለመጸለይ ቁርጠኛ ውሳኔ አድርግ፡፡
  • ከእነዚህ ሰዎች ጋር እንድታሳልፍ እግዚአብሔር የሚያዘጋጅልህን ‹‹መለኮታዊ ቀጠሮ›› ንቁ ሆነህ ተጠባበቅ፡፡

ለተጨማሪ ምልከታ፡- ለማያምኑ ወዳጆችህ ልትጸልይላቸው የምትችለው የጸሎት አይነት በኤፌሶን 1፡17-19 ላይ ሰፍሮ ታገኛለህ፡፡

ማጠቃለያ

‹‹ስለ እኔ ለሌሎች ሰዎች ልትነግር ትፈቅዳለህ?›› ሲል ኢየሱስ ጥያቄ ያቀርብልሃል፡፡

የቃል ጥናት ጥቅስ

‹‹በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና።›› ሮሜ 1፡16

ምዕራፍ 10ን ያጥኑ

Leave a Reply

%d bloggers like this: