ጸሎት
አባት ሆይ፣ በሕይወቴ ስላደረካቸው አስደናቂ ነገሮች አመሰግንሃለው! ሆኖም ካደረክልኝ ከእነዚህ በርካታ ነገሮች መካከል እጅግ ጥቂቷን ብቻ እንደማውቅ ይሰማኛል፡፡ እባክህ አይኖቼን አብራ! ወደ ሕይወቴ መጥተህ ለዘላለም የሚኖር ሰው እንድሆን ባደረከኝ ጊዜ ምን እንደሆነልኝ እንዳውቅ እርዳኝ! አሜን፡፡
የሆነልኝን ማወቅ ለምን ያስፈልገኛል?
ፒር ቻነል በፈረንሳይ ላርክ በሚገኘው የአሮጌ እቃዎች መሽጫ መደብሩ ውስጥ ሆኖ ለሦስት ወራት ያህል አንድ በአቧራ የጠገበ የቆየ ስዕል ለመሸጥ እየጣረ ነው፡፡ ሸራው 12 ኢንች በ22 ኢንች የሆነና ድንግል ማርያም በጭኖቿ ላይ ሁለት ሕፃናትን አስቀምጣ የሚያሳይ ነው፡፡ እነዚህ ሕፃናት ኢየሱስና መጥምቁ ዮሐንስ መሆናቸው ነው፡፡ በመጨረሻ እ.ኤ.አ. በሰኔ ወር 1999ዓ.ም. ጃኩወስ ፕራውስት የተባለ አንድ መምህር በዚህ ሱቅ እንደ አጋጣሚ ያልፍና ስዕሉን በ 70 ዶላር ይገዛል፡፡ ቻነልም ይህንን ስዕል በማስወገዱና ትርፍ በማግኘቱ ይደሰታል፡፡
ፕራውስትም ስዕሉን በወፍራም መጠቅለያ ጠቅልሎ በጭነት መኪናው ኃላ በማስቀመጥ በአካባቢው ለሚገኝ የስነጥበብ ነጋዴ የስእሉን ዋጋ ለማስገመት አቅዶ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ፡፡ ነጋዴውም ባየው ነገር በመደነቅ ለስዕሉ የተሻለ የባለሙያ የዋጋ ግምት ለማግኘት ወደ ፓሪስ እንዲሄድ ፕራውስትን መከረው፡፡ ስዕሉ በዚህ ሁኔታ ከአንዱ የዋጋ ገማች ወደ ሌላው በመሸጋገር በመጨረሻ ጂዮቫኒ ፎርቲኒ የተሰኘ ታላቅ የስእል ባለሟያ እጅ ላይ ይደርሳል፡፡ ይህም ሰው ይህን ስዕል ካየ በኋላ ቢያንስ 50 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያለው የሊዮናርዶ ዳ ፒንቺ የጠፋ የጥበብ ስራ መሆኑን ይፋ ያደርጋል፡፡
ቻነል የዚህችን ትንሽ ስዕል ዋጋ ተገንዝቦ ቢሆን ኖሮ እንዲህ አይነቱን (ምናልባትም በስነጥበብ ታሪክ ውስጥ ውድ) ስህተት ይፈፅም ይመስልሃል? ይህን ባያደርግ ኖሮ አሁን በአሮጌ እቃዎች መደብር ውስጥ ስዕል እየቸረቸረ የሚኖር ይመስልሃል?
ጃኩወስ ፕራውስትስ፣ 70 ዶላሩ በሸመተችለት የማይታሰብ ሃብት ሕይወቱ እንዴት ባለ ሁኔታ እንደተለወጠስ በአይነ ሕሊናህ መሳል ትችላልህ?
ምንም እንኳን እንደ ሸመታ ባይቆጠርም አንተም ቢሆን ውድ የሆነ ነገር ‹‹ገብይተሃል››፡፡ በእርግጥ ይህንን ነገር ገዝተኸው ሳይሆን በስጦታ ነው ያገኘኸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኝህ በተቀበልክ ጊዜ ያገኘኸውን ነገር መጠንና ዋጋ ተረድተኸው ቢሆን ኖሮ፣ ሕይወትህ እንደ ጃኩወስ ፕራውስ እንዳውም ከዚያ በላይ በሚያስደንቅ ሁኔታ በተለወጠ ነበር! የዚህ ጥናት አላማ ክርስቲያን ስትሆን ምን እንደሆነልህ በጉልህ ማሳየት ነው፡፡ ምን ተለወጠ? ምን አገኘህ? ምን አጣህ? ምንህ ልዩ ነገር ሆነልህ?
ያገኘኸውን ነገር በሙላት ትጠቀምበት ዘንድ ጌታን በመቀበልህ የአንተ የሆነውን ሃብት ሁሉ እንድትረዳ እንፈልጋለን! ራስህን በርካሽ ሸጠህ በሕይወትህ ዘመን መጨረሻ ላይ ‹‹ስለ ጉዳዩ ሳስብ ሕመም ይሰማኛል…›› ብሎ የተናገረውን የፒር ቻነል ዐረፍተ ነገር ለመድገም አትፍቀድ፡፡
በመጀመሪያ ከመጥፎ ዜናዎች እንጀምር። ይህ ክርስቶስን ከመቀበልህ በፊት የነበርክበት ን ሁኔታ ያመለክታል፡፡
የሚከተሉት ጥቅሶች ክርስቶስን ከመቀበልህ በፊት የነበርክባቸውን አሉታዊ ሁኔታዎች ያስረዳሉ…
‹‹ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤›› -ሮሜ 3፡23
- በሮሜ 3፡23 መሠረት፣ እኔ ———————- ነበርኩ፡፡
- ‹‹የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል›› ማለት ምን ማለት ይመስልሃል?
- ‹‹ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፣ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል።›› -ኢሳይያስ 59፡2።
- በኢሳይያስ 59፡2 መሠረት፣ በደሌ ከእግዚአብሔር ምን አድርጎኝ ነበር? ——————-ፀሎቴስ ምን ሆኖ ነበር? ————————-
“ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፥ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ ስፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ። ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፥ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፥ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው። በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።” -ራዕይ 20፡11-15
ክርስቶስን የግል አዳኛቸው አድርገው ያልተቀበሉ ሰዎች ስለሚጠብቃቸው የመጨረሻ ፍርድ ያብራራል፡፡ እነዚህ ሰዎች ‹‹እንደስራቸው መጠን›› እንደተከፈላቸው ልብ በል፡፡ ሁላችን ኃጢአትን የሰራን ስለሆነ ማናችንም ብንሆን ይህን ፍርድ ልናመልጥ አንችልም ነበር፡፡ ሆኖም ጥቅሱ ከዚህ ሃሳብ በተጨማሪ፣ የአንዳንዶች ስም ‹‹በሕይወት መጽሐፍ›› ተፅፎ ነበር ይላል፡፡ ኢየሱስን በተቀበልክ ጊዜ ስምህ በዚህ መጽሐፍ ላይ ተፅፏል፤ የእርሱም ጽድቅ ወደ አንተ ‹‹የባንክ ተቀማጭ ሂሳብ›› ተዘዋውሮልሃል፡፡ አሁን ዳኛው፣ እግዚአብሔር አንተ በምድር ሳለህ በሰራኸው ኃጢአት ፈንታ ስለ አንተ የኢየሱስን ፍፁም መዝገብ ስለሚመለከት፣ የኃጢአትህ መዝገብ በእርሱ ፊት እንደ ባዶ ሆኗል፡፡ –ራዕይ 20፡11-15
ነገር ግን ይህ ‹‹በእግዚአብሔር ጸጋ የሆነ የሂሳብ ልውውጥ›› ሳይሆንልህ ማለትም ጌታን ሳትቀበል ነፍስህ ከሥጋህ ተለይታ በእግዚአብሔር ‹‹የነጩ ዙፋን›› ፊት ብትቀርብ ምን የምትሆን ይመስልሃል?
‹‹ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፣ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፣ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል።›› -ኢሳይያስ 64፡6
- በኢሳይያስ 64፡6 መሠረት፣ በራሴ ብርታት ‹‹ጻድቅ›› ለመሆንና በእግዚአብሔር ፊትም ተቀባይነት ለማገኘት ስሞክር፣ ምን ይሆናል?
የሚከተለው ሃሳብ በቀና መንፈስ የቀረበ ነው… ክርስቶስን ከመቀበልህ በፊት ያለው ሕይወት፣ የተሰራህበትን አፈር ግምት ያህል የማያወጣ – በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የሌለው እንደነበረ ማወቅ ይኖርብሃል፡፡ ከሌሎች ሰዎች አንጻር ጥሩ ሰው ልትሆን ትችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ወደ መንግስተ ሰማይ ለመግባት መመዘኛውን ሞራላዊ ፍፅምና (perfection) ባደረገው በእግዚአብሔር ፊት ግን ምንም ነህ፡፡ ሁላችን በአንድ ወቅት እንደዚህ ነበርን፡፡
በመቀጠል፣ መልካም ዜናዎችን እናቅርብ፡፡ ይህ ክርስቶስን ከተቀበልክ በኋላ ያለውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡
‹‹እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፣ ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪደረጉ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል። አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና። ›› -ዕብራዊያን 10፡12-14
የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች፣ ስለ ‹‹አዲሱ አንተነትህ›› አዎንታዊ እውነታዎችን ያቀርባሉ…
- ዕብራዊያን 10፡12-14 ስለየትኛው መስዋዕት ነው የሚያወራው?
- ይህ መስዋዕት ምን እንድትሆን አደረገህ?
- ‹‹ኃጢአታቸውንና ዓመጻቸውንም ደግሜ አላስብም…።›› -ዕብራዊያን 10፡17
- በዕብራዊያን 10፡17 መሠረት፣ እግዚአብሔር ስለአለፈው ኃጢአትህ አሁን ምን ይላል?
ተጨማሪ ምልከታ፡- እንደ አንድ ኢ-አማኝ፣ ኃጢአትህ ከእግዚአብሔር ለይቶ ወደ ገሃነም እሳት ይስብህ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ትክክል የሆነውንና ያልሆነውን ሁሉ ነግሮናል፡፡ ያለመታዘዝ መዘዙንም ገልጦልናል፡፡ ያም ሆኖ ሁላችንም ባለመታዘዝ አምጸንበታል፡፡ ቅዱሱ እግዚአብሔር አመጻችንን አይቶ፣ ‹‹አበጃችሁ፣ ተከድኖ ይብሰል!›› ሊለን አይችልም፡፡ ይህ ኃጢአት አንድ ነገር መሆን ነበረበት፡፡ ዋጋ ሊከፈልበት ግድ ነበር፡፡ ያንንም ክርስትቶስ በእኛ ፈንታ አድርጎታል፡፡ እናም በክርስቶስ መስዋዕትነት ዋጋችን ተከፍሎ፣ ኃጢአታችን ከመዝገቡ ላይ በተደመሰሰ ጊዜ፣ አሁን እግዚአብሔር ራሱን ከኛ ለመለየት ምንም ምክንያት አይኖረውም፡፡ አሁን እግዚአብሔር አንተን ሲያይ የሚመለከተው ነገር የኢየሱስ ክርስቶስን ከበደል የነፃ ጽድቅ ብቻ ነው፡፡
‹‹ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፣ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።›› -ሮሜ 8፡11
- በሮሜ 8፡11 መሠረት፣ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ አሁን የት ነው የሚኖረው?
ማስታወሻ፡- ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ይህን አዲስ ቁረኝት ስለጀመርኩ በሕይወቴ ውስጥ ከእንግዲህ ወዲያ ምንም አይነት ችግር አያጋጥመኝም ብለህ እንዳታስብ፡፡ እንዲህ ልታስብ ባይገባም፣ የአጽናፈ አለሙ ታላቁ ችግር ፈቺ፣ እንደ ልብህና ሳንባዎችህ ቅርብህ መሆኑን በማወቅ ግን ልትበረታታ ይገባል፡፡
- ዮሐንስ 3፡1-10 አንብብ፡፡ እዚህ ስፍራ ላይ፣ ኢየሱስ፣ አንድ ሰው የእግዚአብሔርን መንግስት ለማየት ምን ማድረግ አለበት አለ? (ቁጥር 3)
- ኢየሱስ፣ ‹‹ከውሃ መወለድ›› (ቁጥር 5) ሲል እና ‹‹ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው›› (ቁጥር 6) ሲል ስለምን አይነቱ ልደት እያወራ ነው?
- የሰው ዘር ሁሉ ይህን ልደት አግኝቷልን?
- ‹‹ከመንፈስ መወለድ›› (ቁጥር 5 እና 8) የሚለውስ ስለየትኛው አይነት ልደት ነው የሚያወራው?
- ኒቆዲሞስ ‹‹ሃይማኖተኛ›› ሰው ነበር፣ ይህን ልደት አስቀድሞ ተለማምዶ የነበር ይመስልሃል?
- ክርስቶስን በመቀበልህ በእርግጠኝነት ‹‹ከመንፈስ ተወልጃለሁ!›› ማለት ትችላለህ?
- ‹‹እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም። የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ።›› 1ዮሐንስ 5፡11-13
- ከላይ ያለው ጥቅስ ‹‹የዘላለም ሕይወት›› የት ነው ይለናል?
- ከአንተ አንጻር ኢየሱስ ክርስቶስ የት ነው ያለው?
- የእግዚአብሔርን ልጅ በሕይወትህ በመቀበልህ ምክንያት ይህ ጥቅስ በተጨማሪ ምን አለህ ይላል?
ኢየሱስ ‹‹የዘላለምን›› ሕይወት እሰጣችኋለሁ ብሎ በተናገረበት ክፍል ውስጥ ያለው ‹ዘላለም› የሚለው የግሪክ አቻ ቃል aionios ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹ያልተወሰነ ጊዜ፣ ማብቂያ የሌለው፣ ያለማቋረጥ›› ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት በክርስቶስ ያገኘኸው ሕይወት ምን ያህል ጊዜ ይዘልቃል? ያልቅ ይሆን? ይጠፋ ይሆን? ከአንተ ይለይ ይሆን ? ፈጽሞ፣ አለበለዚያማ aionios ተብሎ ሊሰየም ባልተገባው ነበር፡፡ ወይም ‹‹ጊዜያዊ ዘላለማዊ ሕይወት›› ተብሎ መሰየም ነበረበት፡፡ የዚህ ነገር ጭብጡ ምንድን ነው? ጭብጡ፣ ክርስቶስ የሚሰጠው ‹‹የዘላለም ሕይወት›.፣ የዘላለም ሕይወት ነው!
“ዘላለማዊ ሕይወታችን አስተማማኝ ባይሆን ኖሮ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት የሰጣቸውን እነዚያን እንዴት ‹ለዘላለምም አይጠፉም፣› (ዮሐንስ 10፡28) ሊላቸው ይችላል? አንድ ሰው የዘላለምን ሕይወት ካገኘ በኃላ በኃጢአት ምክንያት ቢጠፋ፣ ይህ ኢየሱስን፣ ቃል አባይ አያደርገውምን?›” -ቻርለስ ስታን
- ‹‹ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፣ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።›› -2ቆሮንቶስ 5፡17
ክርስቶስን በመቀበልህ ምክንያት በሰውነትህ (በአካልህ) ላይ አንዳች ለውጥ የተከሰተ ይመስልሃል?
ከአምስቱ የስሜት ህዋሶችህ ጋር በማይደመረው በመንፈሳዊው ማንነትህ በኩል በሚያስደንቅ ሁኔታ ልዩ ሰው ሆነሃል! መጽሐፍ ቅዱስም ‹‹አዲስ ፍጥረት!›› ብሎ ይጠራሃል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ክርስቲያን ከሆኑ ጊዜ አንስቶ በሰውነታቸው ላይ ጭምር ለውጥ አስተውለዋል፡፡ ይህ፣ በውስጥ የተካሄደው ለውጥ ውጫዊ መገለጫ ነው፡፡ በመንፈስ አዲስ ፍጥረት በሆነ ሰው ላይ ሊከሰቱ ከሚችሉ ውጫዊ አካላዊ ለውጦች መካከል ጥቂቱን ግልጽ፡፡
- ከሕይወትህ የተወገዱት ‹‹አሮጌ›› ነገሮች ምንድን ናቸው?
- ወደ ሕይወትህ የመጡት ‹‹አዲስ›› ነገሮችስ?
- ‹‹ነገር ግን የሆነው ሁሉ፣ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፣ ከእግዚአብሔር ነው፤›› -2ቆሮንቶስ 5፡18
‹‹እርቅ›› የሚለው ቃል ፍቺ ምን ማለት ይመስልሃል?
የፍቺ ዜና ሲሰማ ‹‹እርቅ›› የሚለው ቃል ዜናውን ለመቀልበስ ወዲያውኑ የሚሰማ ቃል ነው፡፡ አንዳንዴ በፍቺ ጥያቄ መካከል እርቅን እውን ማድረግ ሲቻል ሌላ ጊዜ ግን ‹‹እርቅ ሊደረግበት የማይቻል ልዩነት›› ይኖራል፡፡ ይህ የሚከሰተው አንዱ ወይም ሁለቱም አብረው ለመኖር ሳይፈልጉ ሲቀሩ ሲሆን በዚህ ሁኔታ ላይ ያሉ ጥንዶች ሕብረታቸውን ማከም ሳይሆን አንዳቸው ከአንዳቸው መለየትን ብቻ ነው የሚፈልጉት፡፡ በተወሰነ መልክ በአንተና በእግዚአብሔር መካከል የሆነው ይኸው ነበር። ሃጢአተ በአንተ እና በእግዚአብሔር መካከል ፍቺን አይቀሬ አድርጎት ነበር። ነገር ግን አብ ይህ እንዳይሆን ሁሉን አደረገ። ከታላቅ ፍቅሩም የተነሳ በክርስቶስ የመስቀል ሞትና በመንፈስ ቅዱስ ስራ ያቀደውን ማድረግ ቻለ፡፡ ፍቺው ፈረሰ። አሁን አብረኸው ሆነሀል፣ የፍቺውም ወረቀት ለዘላለም ተቀዷል!
- ‹‹እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ፤›› -ሮሜ 5፡1
- የ ‹‹ሰላም›› ተቃራኒ ምንድን ነው?
‹‹ሰዋች ከእግዚአብሔር ጋር በጦርነት ላይ መሆናቸውን አይገነዘቡም፡፡ ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ ክርስቶን እንደ ግል አዳኛቸው ካላወቁና ለጌትነቱ ራሳቸውን ካላስገዙ በስተቀር ፣ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በጦርነት ላይ እንደሆኑ አድርጎ ነው የሚቆጥራቸው፡፡›› -ቢሊ ግርሃም
- ክርስቶስ በመቀበላችን ምክንያት ከ ‹‹እግዚአብሔር ጋር ሰላም›› ካለን፣ ክርስቲያን ከመሆናችን በፊት ከእርሱ ጋር የነበረንን ግንኙነት ምን ሊገልጸው ይችላል?
እንዴት ነው ከእግዚአብሔር ጋር በጦርነት ውስጥ የገባነው? ሰውን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ከሺህ አመታት በፊት እግዚአብሔር እልፍ አእላፍ መላእክትን እንደፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ውብና ጠቢብ የነበረውና ቁጥር አንድ የነበረው መልአኩ ሉሲፈር የእግዚአብሔርን የአምላክነት ስፍራ ለመውሰድ ወሰነ፡፡
ሲሶ የሚሆኑትን መላእክት በመንግስት ግልበጣው አመጽ አብረውት እንዲከቱ አደረገ፡፡ ጦርነቱም ተከፈተ፡፡ በውጊያውም፣ የእግዚአብሔር ጦር አሸነፈ፤ አሁን ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው ሉሲፈር እና በአሁኑ ሰአት ዲያብሎስ እየተባሉ የሚጠሩት ተከታዮቹ ከእግዚአብሔር መንግስት ተጣሉ፡፡ ይህም ሆኖ ሰይጣን ሃሳቡን አልቀየረም፡፡ በመቀጠል ደግሞ እግዚአብሔር በሰው ሕይወት ውስጥ የነበረውን ስፍራ መውሰድ ፈለገ፤ በእነርሱ ሕይወት ውስጥ አለቃ መሆንና መመለክ ተመኘ፡፡ በመሆኑም አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ፣ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝ ከእርሱ አመጻ ጋር እንዲተባበሩ አሳመናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ዘራቸው በሞላ በእግዚአብሔር ስልጣን ላይ የማመጽ ተፈጥሯዊ ዝንባሌ በመያዝ መወለድ ጀመሩ (ዘፍ. 6:5)፡፡
- ስለ ሰይጣን አመጽ ለተጨማሪ መረጃ ኢሳይያስ 14፡12-17፣ ሕዝቅኤል 28፡11-19፣ ራዕይ 12፡3-6 ያንብቡ
- ጠላታችን ማን እንደሆነ ኤፌሶን 6፡10-12 ጨምረው ያንብቡ
በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከሰይጣን አመጻ ጋር ለመተባበር ወስነናል፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብን እግዚአብሔር እንዲነግረን አንፈልግም፡፡ በዚህ ግትር ፈቃዳችን ምክንያት የሰይጣን አጋሮችና የእግዚአብሔር ጠላቶች ሆነናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ጠላቶቹን ይወዳል፡፡ የጦርነት ስልቱ ደግሞ ጠላቶቹ የሆኑትን በፍቅር በመሳብና ወዳጅ በማድረግ ከእርሱ ጎን ለጦርነት ማሰለፍ ነው፡፡ አሁን ከእርሱ ጋር የወገኑቱ ከእርሱ ጋር ሰላም አውርደዋል፣ የእርሱ ወዳጆችና አጋሮችም ሆነዋል፡፡
አሁንም ድረስ ጦርነት ካለና እኛ ደግሞ ከእንግዲህ የእርሱ አጋሮችና ወታደሮች መሆናችን ከተረጋገጠ፣ ማንን ነው ታዲያ እየተዋጋን ያለነው? እንዴትስ ነው እየተዋጋን ያለነው? (ይህ ጉዳይ በስፋት በምዕራፍ 10 ውስጥ ተዳሷል፡፡)
- ‹‹ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፣ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ።›› -ገላቲያ 4፡4-5
- ከላይ በቀረበው ጥቅስ ውስጥ ‹‹መዋጀት›› የሚለው ቃል ትርጓሜ ‹‹አንድን ባርያ ነፃ ለማውጣት መግዛትን›› ያመለክታል፡፡ ራሳችንን ለሰይጣን ‹‹ሸጠን›› የእርሱ ባሪያዎች ሆነን ነበር፡፡
- በየትኞቹ የሕይወትህ ክፍሎች ነበር የሰይጣን ‹‹ባሪያ›› የነበርከው (ማለትም ለእርሱ እሺ ብለህ ለእግዚአብሔር እምቢ የምትለው)?
- ከዚህ የባርነት ገበያ እኛን ለመግዛት ኢየሱስ ምን ተጠቀመ?
- አሁን የሰይጣን ባሪያዎች አይደለንም፡፡ ከሙሉ መብትና ጥቅማችን ጋር የእግዚአብሔር ወንድና ሴት ልጆቹ ሆነናል፡፡ ከእነዚህ ‹‹መብቶች›› መካከል አሁን አንተ ያሉህ ምን ይመስሉሃል?
‹‹እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፣ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።›› -ቆላሲያስ 1፡13-14
ቆላሲያስ 1፡13 ከሰይጣን መንግስት እንደዳንን ይናገራል፡፡ ለራሳችን ማንነት ተላልፈን ተሰጥተን በስደት አለም ተጥለን የምንኖር ነበርን ወይስ ከዚህ የተለየ እጣ ፈንታ ነበረን? ከነበረ ምን?
‹‹እምነት ማለት በማናየው በእግዚአብሔር ቃል ተስፋ ላይ መታመን ማለት ነው፤ የዚህ ሽልማት ደግሞ ሳናይ ያመነውን ነገር በአይናችን በማየት መደሰት ነው፡፡›› -ቅዱስ ኦግስቲን
የሚከተለውን አሰላስል፡- እንደ አዲስ የእግዚአብሔር መንግስት ዜጋ አካበቢህ ክርስቶስን ከማወቅህ በፊት ከነበረው በተለየ ሁኔታ ይታይሃል? ምናልባት የተለየ ሆኖ ላይታይህ ይችላል፡፡ የክርስትና ሕይወት ዋነኛ ነገር በማታያቸው ነገሮች ማመን ነው፡፡ ይህም እምነት ይባላል፡፡ ምንም እንኳን በግዑዙ አለም ውስጥ የሚታይ የተለየ ነገር ባይኖርም በማይታየው መንፈሳዊ አለም ውስጥ ግን ከጨለማ መንግስት ወደ ብርሃን መንግስት ፈልሰናል፡፡ ሰይጣን ንጉሳችን መሆኑ አክትሟል፣ እኛም ከእንግዲህ ወዲያ አንገዛለትም፡፡ አሁን አምልኳችንን ለኢየሱስ ክርስቶስ እናመጣለን፡፡ በዚህ አዲስ መንግስት ውስጥ ሰፊ ሰአት ባጠፋን ቁጥር፣ በዝንባሊያችን፣ በድርጊታችን፣ ቅድሚያ በምንሰጣቸው ነገሮች ውስጥ ይህንን መንግስት ከጊዜ ወደ ጊዜ በግልጥ እየተመለከትነው እንሄዳለን፡፡
ሮሜ 8፡15-17 አንብብ፡፡
- አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል።
- ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾችሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።
- በጥቅሱ መሠረት፣ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህ ያስገኘልህ ነገር ምንድን ነው?
ቁጥር 17 ላይ የሰፈረውን ሃሳብ ልብ በል፣ ‹‹…አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።›› ከእግዚአብሔር ጋር በተፈጠረላቸው አዲስ ቁርኝት አማካኝነት ሕይወት ‹‹አልጋ በአልጋ›› እንደሆነ ለሚያስቡ ክርስቲያኖች ይህ ጥቅስ ምን መልዕክት ያስተላልፋል?
- ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት (እግዚአብሔርን በሚፈሩት) ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፣ ያድናቸውማል።›› -መዝሙር 34፡7
- እግዚአብሔርን ‹‹መፍራት›› ማለት ምን ማለት ይመስልሃል?
- ምንም እንኳን ጦርነት በዙሪያህ ቢሆንና እንደ ክርስቲያን ከችግር የጸዳ ሕይወት መጠበቅ ባትችልም፣ ይህ ጥቅስ ምን ተስፋ ይሰጥሃል?
በልጅነትህ ስለ ‹‹ጠባቂ መላእክቶች›› ታሪክ ሰምተህ ይሆናል፡፡ ይህ ነገር እውነታ እንጂ ቅዠት አይደለም! እግዚአብሔር አንድ ወይም ከዛ በላይ መላእክቶች እንዲጠብቁህ አዞልሃል፡፡ ሊተናኮልህ የሚቀርብ ማንኛውም ነገር በመጀመሪያ ይህን ጠንካራ ድንበር ማለፍ ይኖርበታል! መጽሐፍ ቅዱስ መላእክቶች ብርቱ መንፈሳዊያን አካላት መሆናቸውን ይናገራል፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ የቀረበውን ቅድመ ሁኔታ (እግዚአብሔርን መፍራት) እስካሟላህ ድረስ እግዚአብሔር እነዚህን መላእክቶች ይጠብቁህ ዘንድ ይልክልሃል!
ለብዙዎቻችን ‹‹ፍርሃት›› ማለት ጭንቀት ወይም ህመም ሊያስከትልብን የሚችል ክፉ ነገር ከመፍራት ጋር ይያያዛል፡፡ ቃሉ፣ በአወንታዊ ጎኑ አማኝ ለዋጃው ጌታ ከሚያሳየው ስሜት አንፃር በመጽሐፍ ቅዱስ ሲቃኝ ግን ከዚህ የተለየ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ በዚህ አንጻር የቃሉ ትርጉም ለእግዚአብሔር ክብር አምልኮ የሚያመጣ የመታዘዝ ዝንባሌ ማለት ይሆናል፡፡ ልጆቹ ስለሆንን፣ እግዚአብሔር አንዳች ክፉ ነገር ወይም ጉዳት እንደሚያመጣብን በማሰብ መንገድ ልንፈራው አይገባም፡፡ አስፈሪ ሃይልና አስደናቂ ደግነት ስላለው ለእርሱ አምልኳዊ ፍርሃት ሊኖረን ግን ይገባል፡፡ ‹‹እግዚአብሔርን ስለመፍራት›› እላይ የፃፍከው መልስ ላይ አሁን ለውጥ ማድረግ ያስፈልግህ ይሆን?
ከእንግዲህ ወዲያ አንተን የማይመለከቱት የአራቱ አሉታዊ ሃሳቦች ማጠቃለያ ከዚህ በታች ቀርቧል፡-
- የተኮነንክ ኃጢአተኛ ነበርክ –ሮሜ 3፡23
- ከእግዚአብሔር የተለየህ ነበርክ –ኢሳይያስ 59፡2
- ወደ ገሃነም እሳት የምታመራ ነበርክ –ራዕይ 20፡11-15
- እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት የማትችል ነበርክ-ኢሳይያስ 64፡6
በአሁኑ ሰአት ስለ አንተ እውነት የሆኑት የአስራ ሁለቱ ሃሳቦች ማጠቃለያ ከዚህ በታች ቀርቧል፡-
- እግዚአብሔር በአይኖቹ ፊት ፍፁም እንደሆንክ ተናግሮልሃል – ዕብራዊያን 10፡12-14
- ኃጢአትህ ይቅር ተብሏል፣ ዳግሞም አይታሰብምም – ዕብራዊያን 10፡17
- መንፈስ ቅዱስ አሁን በአንተ ውስጥ ይኖራል – ሮሜ 8፡11
- በመንፈስ ዳግም ተወልደሃል – ዮሐንስ 3፡1-8
- የዘላለም ሕይወት ተሰጥቶሃል – 1ዮሐንስ 5፡11-13
- አዲስ ፍጥረት ሆነሃል – 2ቆሮንቶስ 5፡17
- ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀሃል – 2ቆሮንቶ 5፡18
- ከእግዚአብሔር ጋር ጦርነት ውስጥ አይደለህም – ሮሜ 5፡1
- ከሰይጣን ባርነት ተዋጅተሃል – ገላቲያ 4፡4-5
- አሁን የእግዚአብሔ መንግስት ዜጋ ነህ – ቆላሲያስ 1፡13
- አሁን የእግዚአብሔር ልጅ ነህ – ሮሜ 8፡15-17
- አሁን በመለኮታዊ አጥር ጥበቃ ውስጥ ነህ – መዝሙር 34፡7
ከሕይወትህ ጋር ማዛመድ፡-
እነዚህን ሁለት ዝርዝሮች፣ በቀን አንዴ ለሦስት ሳምንታት (ማለትም ለ 21 ቀናት!) ድምፅህን ከፍ አድርገህ እያነበብክ በራስህ ላይ አውጃቸው፡፡ አራቱን አሉታዊ ነጥቦች ስታውጅ ‹‹ነበርክ›› የሚለውን ‹‹ነበርኩ›› እያልክ አንብብ፡፡ ለተቀሩት አስራ ሁለት አዎንታዊ ነጥቦች ደግሞ ዐረፍተ ነገሩን ለራስህ እየለወጥክ አንብብ፡፡ ሃይማኖታዊ ስርአት ወይም ግዴለሽ ድግግሞሽ እንዳይሆንብህ ጥንቃቄ አድርግ፡፡ እያንዳንዱን አረፍተ ነገር ስትናገር በፍጹም ትኩረት ይሆን፣ በዐረፍተ ነገሩ ውስጥ ያለውም ቁም ነገር ወደ ነፍስህ ዘልቆ እንዲገባ ፍቀድ፡፡ በእንደዚህ አይነቶቹ የቃል እወጃዎች ውስጥ አንዳች ታላቅ ነገር አለ፡፡ እወጃው፣ በሕይወትህ ውስጥ በተካሄዱት ለውጦች ላይ መተማመን እንድትጨምር ከማድረጉ ባሻገር የተረዳኸውን ነገር እውነታነት ለእግዚአብሔርና ለሰይጣን በየዕለቱ የምታረጋግጥበት መንገድም ነው!
ማጠቃለያ፡- ‹‹ምን እንድትሆን እንደሰራውህ ተረድተሃል?››፣ በማለት ኢየሱስ ይጠይቅሃል፡፡
የቃል ጥናት ጥቅስ፡-
‹‹ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፣ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።›› -2ቆሮንቶስ 5፡17
Thanks