ምዕራፍ 3 –የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት

ጸሎት

‹‹አባት ሆይ ከአንተ እርዳታ ውጪ አንተ የምትፈልገውን አይነት ሕይወት ለመኖር አልችልም፡፡ የአንተን መገለጥ፣ ምሪት እና ሃይል እሻለሁ! እባክህ የራስህን ሕይወት በእኔ ውስጥ እንድትኖር እንዴት ልፈቅድልህ እንደምችል አስተምረኝ፡፡ አሜን፡፡››

የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎትን ማወቅ ለምን ያስፈልጋል?

በቅርብ አንድ ጓደኛዬ ለእራት ጋብዞኝ ነበር፡፡ በምንመገብበት ጊዜ ሁሉ በጓደኛዬ ፊት ላይ የእርካታ ፈገግታ ይነበብ ነበር፡፡ አንድ ነገር እንደተፈጠረ ገምቻለሁ፡፡ ዋናውን ምግብ አጠናቀን የቀረበውን ጣፋጭ ነገር ከቀማመስን በኃላ ጓደኛዬ ለምን በኩራት ይፈግግ እንደነበር ለማወቅ ቻልኩ፡፡

‹‹አሁን በከተማው የተሳካለት የኮምፒውተር ባለሙያ ለመሆን በቅቻለሁ፣›› አለኝ በኩራት፡፡ ‹‹እውነትህን ነው?›› ስል መለስኩለት፡፡ ‹‹እንዴት ሊሆን ቻለ?›› አልኩት በመቀጠል፡፡ ከወንበሩ ተነሳና በመኖሪያው ወደሚገኘው ቢሮው ወሰደኝ፡፡ ‹‹ተከተለኝ፤ አሳይሃለው፡፡›› አለኝ፡፡

ቢሮው ስገባ የክፍሉን ግማሽ ቦታ ይዞ የተንሰራፋውን ዘመናዊና ድንቅ የኮምፒውተር ሲስተም ተመለከትኩ፡፡ ‹‹ይህን ምርጥ እቃ ባለፈው ሳምንት ነው ያስገባሁት፡፡ አምስት ቴራ ባይት ሃርድ ደራይቭ፣ 1.5 ጊጋ ባይት ቱርቦ ራም፣ በ2 ጊጋ ኸርዝ የሚሰራ 12 ፕሮሰሰር ፔንቲየም፣ 95× ዲቪዲ-ሲዲ ሮም ድራይቭ እና ግዙፍ ትሮን ቪዲዬ ሞኒተር አለው!›› አለ በኩራት፡፡

ከመደነቅ ሌላ ምንም ልለው የቻልኩት ነገር አልነበረኝም፡፡ እርግጥ ነው በዚህ እቃ ጓደኛዬ አስደናቂ ተግባር ሊፈፅም ይችላል፡፡ ‹‹ድንቅ ነገር!›› ስል አሞካሸሁለት፡፡ ‹‹ይህ አንድ ትልቅ ማሽን ነው! ለመሆኑ ምን ማድረግ ይችላል?›› ስል ጠየኩት፡፡

‹‹ምን ማድረግ የማይችለው ነገር አለ? ወርድ ፕሮሰሲንግ (የፅሁፍ ስራ)፣ ግራፊክስ (ንድፍ፣ ስዕል)፣ ስፕሬድሽት (ሂሳብ ነክ ስራዎች)፣ የኒውክለር ፋዚክስ፣ የልብ ቀዶ ጥገና፣ የስነልቦና የምክር አገልግሎት፣ የጥልፍ ጥበብ፣ ምን የማይሰራው ነገር አለ ብለህ ነው! ተአምራዊ ፍጥነቱ ሳይዘነጋ ማለት ነው፡፡›› ሲል መለሰልኝ፡፡

‹‹ግሩም ነው! ኮምፒውተሩን ቤትህ ካስገባህ በኋላ ምን እንደሰራህበት አሳየኝ?›› ስል ጠየኩት፡፡

ጓደኛዬም ለጥቂት ደቂቃ በዝምታ ከቆየ በኋላ፣ ‹‹እንግዳው ነገር ይህ ነው፡፡ እንዳመጣሁት ተቀምጦ ነው ያለው፡፡ ካስገባሁት ጊዜ አንስቶ ተጠቅሜበት አላውቅም፡፡” አለኝ።

‹‹እንግዳው እንዲህ እናድርግ፣ ከፍተን እንመልከተው፡፡›› ስል ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ የማብሪያ ማጥፊያውን ቁልፍ ተጫንኩት፤ የተፈጠረ ምንም ነገር ግን አልነበረም፡፡ ሦስት ጊዜ ለማብራት ሞከርኩ፤ የተለወጠ ነገር አልነበረም፡፡ ‹‹ሶኬቱን መሰካትህን እርግጠኛ ነህ?›› ስል ጠየኩት፡፡

‹‹መሰካትህን? ምን ማለትህ ነው?›› ሲል መልሶ ጠየቀኝ፡፡

ኮምፒውተሩ የቱንም ያህል አስደናቂ ይሁን፣ ሶኬቱ ካልተሳካ በቀር ውድ የአቧራ ማከማቻ እቃ ከመሆን የዘለለ አገልግሎት አይኖረውም፡፡ በተመሳሳይ መንገድ፣ ክርስቲያን ከመንፈስ ቅዱስ እቅድና ሃይል ጋር ካልተጣበቀ፣ ጌታ ኢየሱስ ከአማኙ ሊያየው የሚፈልገውን አይነት ሕይወት በሙላት ሊለማመድ አይችልም፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምታደርገው ቁርኝት ከእግዚአብሔር ጋር በጀመርከው አዲስ ሕይወት ውስጥ ልታደርገው የሚገባህ እጅግ በጣም ወሳኝና ጠቃሚ ቁርኝት ነው፡፡

ቆይ፣ቆይ፣ቆይ…

‹‹ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወደ ሕይወቴ የገባው ኢየሱስን እንደ ግል አዳኜና ጌታዬ የተቀበልኩ ጊዜ አይደለምን?›› በማለት እያሰብክ ይሆናል፡፡ ‹‹ይህ ማለት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ‹ከተቆራኘሁ› ሰነበትኩ ማለት አይደለምን? ክርስቲያን ሆኜ እንዴት ነው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሳልቆራኝ ልኖር የምችለው?››

የመንፈስ ቅዱስ ‹‹ማደሪያ›› መሆንና በመንፈስ ቅዱስ ‹‹መሞላት›› ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በርካታ ክርስቲያኖች አሁን ለሚኖሩት የሽንፈትና የእርካታ መጉደል ሕይወት ዋነኛ ምክንያት ይህንን ልዩነት አለማወቃቸውና በመንፈስ ቅዱስ ‹‹በመሞላት›› ሁኔታ ውስጥ አለመገኘታቸው ነው፡፡

የእነዚህን ሁለት ነገሮች ልዩነት ለማወቅ ንባብህን ቀጥል…

የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ መሆን

እያንዳንዱ ክርስቲያን በሕይወቱ ዘመን ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ አንድ ኀጢአተኛ ሰው አምኖ ንስሃ በገባና በዳነበት ሰአት መንፈስ ቅዱስ የዚህን ሰው ሕይወት ለዘላለም፣ መኖሪያው ያደርጋል (ዮሐንስ 14፡16፤ ሮሜ 8፡9)፡፡ ይህ ሁኔታ ‹‹የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት›› በመባልም ይታወቃል፡፡ በግሪክኛ (የአዲስ ኪዳን የፅሁፍ ቋንቋ) ‹‹ማጥመቅ›› ማለት ‹‹ማጥለቅ፣ መድፈቅ ወይም መዝፈቅ›› ማለት ሲሆን ይህም ትርጉም ‹‹በሌላ ከባቢ ውስጥ መስመጥን›› የሚያመለክት ሃሳብ ያስተላልፋል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ወይም በመንፈስ ቅዱስ ውስጥ ስንጠመቅ፣ ለዘላለም በመንፈስ ቅዱስ ተፅእኖ ውስጥ ወደምንወድቅበት አዲስ ከባቢ እንመጣለን (1ቆሮንቶ 12፡13)፡፡

በመንፈስ ቅዱስ መሞላት

ይህ ሁኔታ፣ መንፈስ ቅዱስ ሕይወቱን እንዲመራና በሃይል እንዲያስታጥቀው ፈቃዱን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ያስገዛ አማኝ ሕይወትን ያመለክታል፡፡ ይህ ሙላት አንዴ ከተደረገ በኋላ ዳግመኛ የማያስፈልግ ልምምድ አይደለም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት እንደ አማኙ መነሳሳት፣ መታዘዝና ዘላቂ ባሕሪ በየቀኑ ወይም በየሰአቱ የሚሆን ነገር ነው (ኤፌሶን 5፡18)፡፡ አማኝ በመንፈስ ቅዱስ ‹‹በማይሞላበትም›› ወቅት እንኳ መንፈስ ቅዱስ በአማኙ ውስጥ አድሮ ይገኛል፡፡ ነገር ግን በአማኙ ፍላጎት ማጣት ወይም የአመፅ ዝንባሌ ምክንያት ይገደባል፡፡ የዚህ ጥናት ትኩረት ይህንን ‹‹የአለመሞላት›› ሁኔታ መፍትሄ መስጠት ነው፡፡

መንፈስ ቅዱስ ማን ነው?

የስላሴ አንዱ አካል። …ምን? ይህ ማለት ሦስት አማልክት አሉ ማለት ነው ወይስ አንድ?

ስለ እግዚአብሔር ማንነት ኋላ ላይ በዚህ ጥናት ውስጥ እንመለከታለን፡፡ ሆኖም እዚህ ላይ ጥቂት ስለ መንፈስ ቅዱስ ማወቅ ስለ እርሱ አገልግሎት ለመረዳት ጠቃሚ ይሆናል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን ‹‹በስላሴ›› አንጻር ያብራራልናል፡፡ በሌላ መንገድ፣ ይህ ማለት እግዚአብሔር ራሱን በሦስት የተለያዩ ማንነቶች ገልጿል ማለት ነው፣ እነዚህም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡

አንድ ሰው ለእግዚአብሔር በመሸነፍና በእርሱ ሃይል ላይ ብቻ በመደገፍ ሰላም፣ ብርታትና በረከት ሲያገኝ፣ የዚህን ውጤት ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ሲያስቀምጥ፣ የዚህ ውጤት ምክንያት የመንፈስ ቅዱስ መገኘትና ሃይል፣ በላቀ ደረጃ የአማኙን ሕይወት የመውረስ ምክንያት ነው፡፡ ይህ ሰው ነው እንግዲህ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሕይወት ያለው! -ሌዊስ ስፔሪ ቻፈር

ዮሐንስ 6፡27 አንብብ፡፡ እዚህ ላይ ኢየሱስ እግዚአብሔርን፣ እግዚአብሔር ………… ሲል ገልፆታል ፡፡

ዮሐንስ 20፡26-28 አንብብ፡፡ እዚህ ላይ ደግሞ ቶማስ ኢየሱስን ‹‹ጌታዬ ………….›› ሲል ጠርቶታል፡፡

1ቆሮንቶስ 3፡16 አንብብ፡፡ ክርስቲያኖች የ………………….. መንፈስ መኖሪያ መቅደሶች ናቸው፡፡

አያዎ (እዉነትን ያዘለ ተፃራሪ የሚመስል ሃሳብ)! አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዳቸው እግዚአብሔር የተባሉ ቢሆንም እግዚአብሔር አንድ ነው፡-

‹‹…ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም።›› -ኢሳይያስ 43፡10

‹‹እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።›› -ዮሐንስ 17፡3

‹‹…ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን።›› -1ቆሮንቶስ 8፡4

‹‹እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤›› -ዘዳግም 6፡4

አያዎ የሚለው ቃል፣ እውነትን ያዘለ፣ ነገር ግን እርስ በእርሱ የሚፃረር ሃሳብን ይገልፃል፡፡ ለአብነት፣ የፊዚክስ ምሁራን ብርሃን፣ ፓርቲክልም (የመጨረሻ ትንሽ መጠን) ሞገድም ነው ሲሉ ሌሎች የቁስ አካላዊ ሕጎች ደግሞ ብርሃን ሁለቱንም ሊሆን አይችልም በማለት ያረጋግጣሉ፡፡ ሳይንቲስቶቹ ምንአልባት አንድ ቀን ይህን ጉዳይ አመክንዮአዊ በሆነ መንገድ ያብራሩልን ይሆናል፡፡ ነገር ግን እስከዛው ድረስ ከመረዳት አቅማችን በላይ ሆኖ ይሰነብታል – አያዎ ይሆናል፡፡

ስለ እግዚአብሔር ስናስብ፣ ከመረዳታችን በላይ የሚሆኑ በርካታ ነገሮች እናገኛለን፡፡ እርሱ የማይገደብ እኛ ደግሞ በአእምሮአችን ሃይል አንጻር ውሱን መሆናችን መዘንጋት የለበትም፡፡ በኤሌክትሪክ የሚሰራን ሞተር ለአንድ ጉንዳን ለማብራት የሚደረገውን ጥረት በአእምሮህ መገመት ትችላለህ? ጉንዳኗ የአንተን ማብራሪያ ለመረዳት የሚያስችላት ምንም አይነት የማገናዘቢያ መነሻ የላትም! በተመሳሳይ መልኩ በሙላት ስለ እግዚአብሔር ልንረዳቸው የማንችላቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ ነገሮች መካከል የስላሴ ትምህርት አንዱ ነው!

የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ እግዚአብሔር እንዳለና ራሱን በሦስት አካል እንደገለጸ አበክሮ ያስረዳል፡፡ እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ ግብር አላቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሦስቱም በአንድ ትዕይንት ውስጥ ሲገለጡ እንመለከታለን፡፡ የሚከተሉትን አራት ምንባቦች መርምር፡፡ በእያንዳንዱ ጥቅሶች ውስጥ የተገለጡትን የስላሴ አካላት በማክበብ ያከበብከውን ደግሞ መስመር በመጠቀም ከታች ከተቀመጠው አማራጭ ጋር አገናኝ፡፡

ኢየሱስ፣ የታላቁን ተልእኮ መመሪያ በሰጠበት ጊዜ፡-

‹‹እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤…›› -ማቴዎስ 28፡19-20            

 • አብ
 • ወልድ
 • መንፈስ ቅዱስ

ማርያም፣ ኢየሱስን እንደምትፀንስ በተነገራት ገዜ፡-  

‹‹መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።›› -ሉቃስ 1፡35            

 • አብ
 • ወልድ
 • መንፈስ ቅዱስ

ኢየሱስ፣ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በተጠመቀበት ጊዜ፡-

‹‹ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፣ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፣ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ።›› -ሉቃስ 3፡21-22            

 • አብ
 • ወልድ
 • መንፈስ ቅዱስ

‹‹የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፣ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው በመንፈስም እንደሚቀደሱ፣ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡት…›› -1ጴጥሮስ 1፡2           

 • አብ
 • ወልድ
 • መንፈስ ቅዱስ

መንፈስ ቅዱስ ለምን መጣ?

የሚከተሉትን ጥቅሶች ካጠናህ በኋላ እያንዳንዱ ጥቅሶች ለምን መንፈስ ቅዱስ መጣ፣ ተግባሩ ምንድን ነው? እቅዶቹ ምንድን ናቸው፣ ወዘተ ለሚሉት ጥያቄዎች የያዙትን ምላሽ ፃፍ፡፡ ጥቅሶቹ የሚገኙበትን አውድ ለማጥናት መጽሐፍ ቅዱስህን መመርመርም አትዘንጋ፡፡

መንፈስ ቅዱስ የሚከተሉትን ለማድረግ መጥቷል——

 • ኢየሱስ ስለመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፡- ‹‹እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤›› -ዮሐንስ 16፡8
 • ኢየሱስ ሲናገር፡- ‹‹ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።›› -ዮሐንስ 16፡13
 • ኢየሱስ ስለመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፡- ‹‹እርሱ ያከብረኛል፣ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና።›› -ዮሐንስ 16፡14
 • ኢየሱስ ሲናገር፡- ‹‹ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ። ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፣ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ።ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና።…›› ዮሐንስ 7፡37-40
 • ከትንሣኤ በኃላ ኢየሱስ ሲናገር፡- ‹‹ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።›› -የሐዋርያት ሥራ 1፡8

ክርስቲያን ስትሆን መንፈስ ቅዱስ በሕይወት ያደረጋቸው ነገሮች እነሆ…

በአንተ ውስጥ ገብቷል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕይወትህ እንዲገባ በጋበዝከው ሰአት፣ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ወዳንተ መጥቷል፡፡1ቆሮንቶስ 3፡16-17 ተመልከት፡፡

 • አጥምቆሃል፡፡ በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ጠልቀሃል፣ ወደ እግዚአብሔር መንፈስ አዲስ ከባቢ ውስጥ ተሰክተሃል፣ በክርስቶስ መንፈሳዊ አካል (ቤተክርስቲያን) ውስጥ ተካተሃል፡፡ 1ቆሮንቶስ 12፡13፡፡
 • አትሞሀል፡፡ እግዚአብሔር፣ አንተ ለዘላለም የእርሱ መሆንህን በመመስከር ዘላለማዊ ‹‹ፊርማውን›› በአንተ ላይ አኑሯል፡፡ በምድር ሕይወትህ ማክተማያ ወቅት በሰላም መንግስተ ሰማይ መድረስህንም ራሱ ያረጋግጣል፡፡ ኤፌሶን 1፡13-14 ተመልከት፡፡
 • ስጦታ ሰጥቶሃል፡፡ ክርስቲያን በሆኑም ሆነ ባልሆኑ ሰዎች መካከል ልዩና ውጤታማ አገልግሎት እንዲያበረክቱ መንፈስ ቅዱስ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን አንድና ከዛ በላይ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ሰጥቷል፡፡ 1ቆሮንቶስ 12፡4-11 ተመልከት፡፡
 • ሃይል ሰጥቶሃል፡፡ በአካበቢህና በመላው አለም ነፍሳትን ለእርሱ መንግስት በመናጠቅ፣ ወንጌልን በድፍረት ለመመስከር መለኮታዊ ችሎታን ሰጥቶሃል፡፡ የሐዋሪያት ሥራ 1፡8 እና 4፡31 ተመልከት፡፡
 • ለበረከት ወጥኖሃል፡፡ ዛሬም መንፈስ ቅዱስ በአንተ ፈንታ በእግዚአብሔር ፊት ይጸልያል፡፡ የማትጠራጠርበት አንድ ነገር ቢኖር መንፈስ ቅዱስ ሲፀልይ ውጤት አለው! ሮሜ 8፡26-27 ተመልከት፡፡

በቀጣይ መንፈስ ቅዱስ ሊያደርጋቸው የሚሻቸው ነገሮች እነሆ…

የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ካነበብክ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ያለማቋረጥ በአንተ ውስጥ ሊያደርጋቸው የሚሻቸውን ነገሮች ግለጽ፡፡

 • ዮሐንስ 14፡26 ___________________________________
 • 2ቆሮንቶስ 3፡18 __________________________________
 • ገላቲያ 5፡22-23 _________________________________

የመንፈስ ቅዱስ ሙላት

በመንፈስ ቅዱስ ‹‹ሙላት›› ውስጥ በምትገኝበት ወቅት፣ በአንተና በእግዚአብሔር መካከል ያለው የግንኙነት መስመር ጠንካራና ያልደፈረሰ ይሆናል፣ ይህም ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲመራህና በሃይል እንዲያስታጥቅህ መንገድ ይከፍታል፡፡ ‹‹ለምንድን ነው እግዚአብሔርን የበለጠ በሕይወቴ የምፈልገው? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል፡፡ እንደሚመስልህ አንተ አይደለህም ይበልጥ የምትፈልገው፣ እርሱ እንጂ! ሁለንተናህን የራሱ እስካላደረገና በእያንዳንዱ የሕይወትህ ክፍል ጌታ ካልሆነ አንተም ሆነ እርሱ አትረኩም፡፡

መቆጣጠር

በአንዲት ከተማ ውስጥ የተሰበሰበ የአገልጋዮች ኮሚቴ፣ በከተማው ሊደረግ በታቀደው ከተማ-አቀፍ የወንጌል ዘመቻ ዲ.ኤል. ሙዲ ይሳተፍ አይሳተፍ በሚለው ጉዳይ ላይ እየመከረ ነው፡፡ በመጨረሻ፣ አንድ ሙዲ እንዲጋበዝ ያልፈለገ ወጣት አገልጋይ ከመቀመጫው በመነሳት፣ ‹‹ለምን ሙዲ አስፈለገ? እርሱ መንፈስ ቅዱስን ተቆጣጥሯልን?›› ሲል ጠየቀ፡፡ ጥቂት ዝምታ ከሰፈነ በኃላ አንድ በእድሜ ገፋ ያሉና ፈርሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው አገልጋይ ከመቀመጫቸው በመነሳት፡፡ ‹‹ዲ.ኤል ሙዲ መንፈስ ቅዱስን አልተቆጣጠረም፣ መንፈስ ቅዱስ እርሱን ተቆጣጥሮታል እንጂ፡፡›› በማለት ለወጣቱ አገልጋይ ምላሽ ሰጡ፡፡

ምንም እንኳን እግዚአብሔር በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት በሕይወትህ ውስጥ ቢኖርም አሁንም ድረስ ‹‹ነፃ ፈቃድ›› አለህ፡፡ እግዚአብሔርን ለመታዘዝም ሆነ ላለመታዘዝ መምረጥ ትችላለህ፡፡ አለመታዘዝን በምትመርጥበት ጊዜ ተገቢ ባልሆነው ምርጫህ ምክንያት በሕይወትህ ሊደርስ የሚችለውን መከራ ከመፍቀድ በስተቀር በአምባገነንነት እንድትታዘዘው አያስገድድህም! የእግዚአብሔር አላማ የራሳቸው ፈቃድ የሌላቸው የሮቦት ሰራዊት ማፍራት ሳይሆን በጽድቅ የሚተገብሩ እና በመንግስቱ ውስጥ አብረው የሚሰሩ ወንድና ሴት ልጆችን ማፍራት ነው፡፡

እግዚአብሔር ቅዱስ መንፈሱን በውስጣችን ያደረገው እነዚህን ትክክለኛ ምርጫዎች እንድናደርግ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር የጉትጎታ ድምፅ ጀርባ ብንሰጥ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል መንፈስ ቅዱስን ‹‹እናጠፋለን›› (1ተሰሎንቄ 5፡19)፡፡

ባለመታዘዝ መንፈስ ቅዱስን ልናሳዝነው እንደምንችል መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል (ኤፌሶን 4፡30)፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ይመስልሃል?

ለራሳችን ጥቅም ስንል ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅር የተሞላና ፍሪያማ ግንኙነት ለመፍጠር እውነተኛ ፍላጎት ካለን ቸርነትና ርህራሄ ለተሞሉት መመሪያዎቹ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ይገባናል!

በመንፈስ ቅዱስ መሞላት እንዲያው ሳይሆን በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ውሳኔአችንን የሚጠይቅ እንደሆነ በምን እናውቃለን?

‹‹መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤›› -ኢፌሶን 5፡18

በኤፌሶን 5፡18 ላይ ሁለት ትዕዛዞች ተሰጥተውናል – አንደኛው አሉታዊ ሲሆን ሌላው ደግሞ አወንታዊ ነው፡፡ ምንድን ናቸው?

 1. ___________________________________________________
 2. ____________________________________________________
 3. አንድ ነገር እንዲያው የሚሆን ከሆነ፣ ይህ እንዲያው ሊሆን የሚችለው ነገር ተግባራዊ እንዲሆን ትእዛዝ ያስፈልጋልን?
 4. አንድ ነገር ከታዘዘ እና ትዕዛዙ ተፈፃሚነት ካላገኘ፣ በመታታዘዝ ምክኒያት ሊመጣ የነበረው ነገር እውን መሆን ይችላል?
 5. እንዳንሰክር የታዘዝነውን ትዕዛዝ ችላ ማለት እንችላለን?
 6. ‹‹በመንፈስ ቅዱስ እንድንሞላ›› የታዘዝነውን ትዕዛዝስ?
 7. በመንፈስ ቅዱስ ‹‹መሞላት›› ማለት ምን ማለት ነው? የአልኮል መጠጥ እንዴት ነው የሰውን ባህሪ የሚለውጠው?
 8. ይህንን፣ መንፈስ ቅዱስ የሰውን ባህሪ እንዴት መለወጥ እንደሚፈልግ በማብራራት አነፃፅር፡፡

‹‹ከመንፈስ ቅዱስ ውጪ፣ የክርስቲያን ሕይወት አስቸጋሪ ሳይሆን የማይቻል ነው፡፡ -ቢል ብራይት

“እያንዳንዱ ሰው ሊመልሰው የሚገባው ጥያቄ ቢኖር፣ ተጨማሪ ገንዘብ፣ ጊዜ ወይም ትምህርት ባገኝ ለጌታ ምን አደርጋለሁ የሚለውን ሳይሆን አሁን ባለኝ ነገር ለጌታ ምን አደርጋለሁ የሚለውን ነው፡፡ ዋናው ነገር፣ አንተነትህ ወይም ያለህ ነገር ሳይሆን ክርስቶስ አንተን መቆጣጠሩ ነው፡፡›› -ዳውሰን ትሮትማን

ሦስት አይነት ሰዎች

በ1ቆሮንቶስ 2፡14-15 እና 3፡1-3 ላይ የተገለፁትን ሦስቱን ሰዎች ለይተህ አክብባቸው፡፡

‹‹ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።…እኔም፣ ወንድሞች ሆይ፣ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፣ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም።  ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም። ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን?››

 1. ተፈጥራዊ ሰው – ‹‹የራሱ ነፍስ አዛዥ ነው››

እኔነቱ የሕይወቱን ማዕከላዊ ነገር ተቆጣጥሯል፡፡

ክርስቶስ ከሕይወቱ ውጪ ነው፡፡

ይህ ግለሰብ፣ ክርስቲያን ያልሆነ ሰውን ይወክላል፡፡ እግዚአብሔር ለእርሱ ካለው ፍፁም አላማ ጋር በመጋጨቱ ንዴት፣ ተስፋ መቁረጥና ግራመጋባትን የሕይወቱ መገለጫዎች ናቸው፡፡

 1. መንፈሳዊ ሰው – ‹‹በእምነት የሚጓዝ፡፡››

እኔነት ከሕይወቱ ዙፋኑ ላይ ወርዷል፣ ክርስቶስን በሕይወቱ ላይ አንግሷል፡፡

ክርስቶስ በዙፋኑ ላይ ነው፣ ኢየሱስ የክርስቲያኑን ሕይወት ይመራል ያስታጥቃል፡፡

ይህ ግለሰብ፣ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ክርስቲያንን ይወክላል፡፡ ክርስቶስ ሃያልና ሁሉን አዋቂ እንደመሆኑ መጠን በአማኙ ሕይወት ውስጥ ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግስትን፣ ቸርነትን፣ በጎነትን፣ ታማኝነትን፣ የውሃትን፣ እና ራስን መግዛትን ወዘተ በመፍጠር የአማኙ ሕይወት ከእግዚአብሔር አላማ አንፃር መዋሃዱን ያረጋግጣል!

 1. ሥጋዊ ሰው – ‹‹እስካሁን አንተ (ኢየሱስ) የሰራኸው ይበቃል። ከእንግዲህ ወዲህ እኔ እቀጥለዋለሁ፣ አመሰግናለሁ፣ የሚል ክርስቲያንን ይመስላል፡፡››

 ሥጋዊ ማለት ከእግዚአብሔር መንፈስ ይልቅ በሰው ተፈጥሮ የሚገዛ ማለት ነው፡፡

ሕይወቱን ራሱ መልሶ ለመምራት፣ እኔነት ተመልሶ ወደ ዙፋኑ መጥቷል፡፡

ክርስቶስ በሕይወቱ ውስጥ ነው፣ ነገር ግን ከዙፋኑ ተወግዶ ጌታ እንዳይሆን ተደርጓል፡፡

ይህ ግለሰብ፣ የእግዚአብሔርን ምሪት አሻፈረኝ ያለ ስለሆነ ሕይወቱ የተመሰቃቀለ ነው፡፡ በሥጋዊ ክርስቲያንና ክርስቲያን ባልሆነ ሰው ሕይወት መካከል ያለውን የንዴት፣ የተስፋ መቁረጥና ግራመጋባት መጠን ልዩነትን ማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው፡፡

በመንፈስ ቅዱስን ለመሞላት አምስት ደረጃዎች

 1. መሻት፡፡ማቴዎስ 5፡6 አንብብ፡፡ ‹‹ለመጥገብ (ለመሞላት)›› ኢየሱስ በቅድመ ሁኔታነት ያቀረበው ነገር ምንድን ነው?

ይህ ‹‹መሻት›› በሕይወትህ ውስጥ ምን ይመስላል?

ልብህን ፈትሽ፡፡ ‹‹ጽድቅን ትራባለህ፣ ትጠማለህ?›› በእርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወትህ ጌታ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ መሪህ እንዲሆን ትሻለህ? እግዚአብሔር እንድታደርግ ለሚነግርህ ነገር ትታዘዛለህ? በማስመሰል እየኖርክ የእርሱ ሃይል ያለመከልከል በአንተ ውስጥ እንዲፈስ አትጠብቅ፡፡ እግዚአብሔር ልብን ያያል፡፡

‹‹አሁን ሰውነትህ፣ የስላሴ አንዱ አካል የሆነው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ሆኗል፡፡ እንደ አገልጋይ እንዲረዳህ ብቻ አትጠይቀው፡፡ በሕይወትህ ሁሉን እንዲከውን ጠይቀው እንጂ፡፡ ሕይወትህን በሞላ እንዲቆጣጠር ጠይቀው፡፡ ምን ያህል ደካማ፣ እርዳታ የለሽ፣ ወላዋይ፣ እና ልትታመን የማትችል መሆንህን ንገረው፡፡ ገለል በልለትና በሕይወትህ ያሉትን ምርጫዎችና ውሳኔዎች ሁሉ እርሱ እንዲቆጣጠራቸው ፍቀድለት፡፡›› -ቢሊ ግርሃም

 1. መናዘዝ፡፡ 1ዮሐንስ 1፡9 አንብብ፡፡ ከአመፃ ሁሉ ለመንጻት በቅድመ ሁኔታነት የተቀመጠው ነገር ምንድን ነው?

መንፈስ ቅዱስ በሕይወትህ ውስጥ ‹‹የሚታቀበው›› በኃጢአት ምክንያት ሊሆን ይችላል፣ ይህም ለእግዚአብሔር ሃሳብ ‹‹እምቢ›› ብለህ ለራስህ ያልተቀደሱ ምኞቶች ‹‹እሺ›› ስትል ማለት ነው፡፡ በጸሎት ሆነህ አንተን ከእግዚአብሔር አላማና ሃይል ‹‹ያቆራረጠህን›› ነገር እግዚአብሔር እንዲገልጥልህ ጠይቀው፡፡ ሲገልጥልህ ደግሞ እነዚያ ምርጫዎችህ ስህተት እንደነበሩ በማመን ከእርሱ ጋር ተስማማ (ይህ ነው መናዘዝ ማለት)፡፡ እያንዳንዱን ስህተትህን ይቅር እንዲልህ ጠይቀው፡፡

 1. ራስን ማቅረብ፡፡ ሮሜ 6፡13፣19 አንብብ፡፡ በዚህ ጥቅስ ላይ የቀረበው ‹‹የእራስን ማቅረብ›› ሃሳብ፣ ግዴለሽ ወይስ ፍጹም መሰጠትን ነው የሚጠይቀው?

ቁጥር 19 ራስህን ለእግዚአብሔር ‹‹ስታቀርብ››፣ ለጽድቅ ‹‹ባሪያ›› ትሆናለህ ይላል፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ የሚመስልህን አብራራ፡፡

በርካታ ሰዎች ባርነትን ከአዋራጅ ጭቆና ጋር ያዛምዱታል – በእርግጥም ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ ቦታ ላይ የቀረበውን ባርነት ይህ ትርጉም አይወክለውም፡፡ በመንፈሳዊው አለም ሰይጣን አንተን ለፈቃዱ ባሪያ ለማድረግ ይሻል የዚህም ነገር መጨረሻው ጥፋት ነው፡፡ በአንፃሩ እግዚአብሔር ደግሞ ለፈቃዱ ባሪያ እንድትሆን ይሻል፡፡ ይህ ደግሞ ከሚያጠፋህ ነገሮች ነፃ አውጥቶ እርካታን፣ ሙላትና ደስታ ወደምታገኝበትና ወደምትታነፅበት ቁርኝት ይመራሃል፡፡

 1. መጠየቅ፡፡ ሉቃስ 11፡9-13 አንብብ፡፡ ይህ ጥቅስ፣ የምትሻውን ነገር እግዚአብሔር እንዲሰጥህ ‹‹ለማሳመን›› ምን አይነት አስደናቂ ልዕለ-ሰብአዊ ነገር እንድታደርግ ነው የሚያዝህ?

እግዚአብሔር መልካም ስጦታን ለእኛ ለመስጠት እንደሚወድ ግልጽ ነው፡፡ እና ለምን ይመስልሃል ‹‹እንድንጠይቅ፣ እንድንሻ እና እንድናንኳኳ›› የሚፈልገው? ስጦታውን ለምን ያለእነዚህ ነገሮች አልሰጠንም?

ከዚህ አስቀድም ስለ ነፃ ፈቃዳችን የተባለውን አስታወስክ? እግዚአብሔር በመምረጥ መብትህ ላይ አያመቻምችም፡፡ ከፈቃዱ ለመውጣት በፈቃድህ እንደመረጥክ ሁሉ ተመልሰህ ከእርሱ ጋር ‹‹ለመቆራኘትም›› በፈቃድህ መምረጥ አለብህ፡፡

ይህ አለም የሚለወጠው፣ በሚከራከሩ ወይም እጅ በሚሰጡ ሰዎች ሳይሆን ሕይወትን ልዩ በሚያደርገው በእግዚአብሔር መንፈስ በተቀጣጠሉ ነፍሶች ነው፡፡ -ቫንስ ሃቭነር

 1. በእምነት ማመስገን፡፡ ማርቆስ 11፡24 በማንበብ ሃላፊ ጊዜውን ልብ በል፡፡ ይህ ጥቅስ፣ የጸለያችሁትና የለመናችሁትን ሁሉ እንደተቀበላችሁ ብታምኑ ምን ይሆንላችኋል ነው የሚለው?

አንድ ነገር እንዲሆንልህ ጠይቀህ እንደተቀበልክ ካመንክ በቀጣይ ማድረግ የሚጠበቅብህ ትክክለኛ ነገር ማመስገን ነው! በመንፈስ ቅዱስ እየተሞላህ ስለመሆንህ ምን ያህል እርግጠኛ ነህ?

‹‹ምስጋና ‹በእግዚአብሔር ላይ የመታመንህ› ምልክት ነው፡፡›› -ቶሚ ደኪንስ

በ 1ዮሐንስ 5፡14-15 የሚገኘው ተስፋ ምንድን ነው? ‹‹በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን። ››

እግዚአብሔር ከፈቃዱ ውጪ የሆነን ነገር ያዝዝሀል? ፈፅሞ! በቃሉ እና በትዕዛዙ መሠረት መንፈሱን እንዲሞላህ ከልብህ ብትጠይቀው፣ እንደሞላህ፣ ሙሉ እምነት ልትይዝ ትችላለህ፡፡ ይህ እንዲሆን እርሱም ይሻል፣ አንተም ትሻለህ፣ እንዲያ ከሆነ ደግሞ ነገሩ ሰመረ ማለት ነው!

በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት መጠየቅ

በምትጸልይበት ጊዜ እግዚአብሔር ከቃልህ ይልቅ ለልብህ ዝንባሌ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ የልብህን ስሜት ለመግለጽ ይረዳህ ዘንድ ሌላ ሰው ቃላት መጠቀም የምትችልበትን ሁኔታ ቢጠቁምህ ክፋት የለውም፡፡ ስልሆነም፣ ልትጸልየው የምትችለው የጸሎት አማራጭ እነሆ፡-

የምወድህ አባት ሆይ፣ ታስፈልገኛለህ፡፡ ጽድቅህን ከዚህ አለም ምንም ነገር ይልቅ እራበዋልሁ፣ እጠማዋለውም፡፡ ገዢዬና መሪዬ እንድትሆን እፈልጋለሁ፡፡ የሕይወቴን ዙፋን ከአንተ ቁጥጥር ነጥቄ በመያዜ በድዬሃለው፡፡ በርካታ የተሳሳቱ ምርጫዎችን አድርጌአለሁ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ እባክህ ይቅር በለኝ፡፡ ራሴንና ጠላቴን፣ ዲያቢሎስን ከማገልገል ይልቅ አንተን ለማገልገል ሁለመናዬን በመታዘዝ አቀርብልሃለው፡፡ በቅዱስ መንፈስህ እንድትሞላኝ እለምንሃለው፡፡ ከሕይወቴ ዙፋን ላይ ወርጄ ቦታዉን ለአንተ አስረክባለሁ፡፡ በትእዛዝህ እና በተስፋህ መሠረት ጸሎቴን ሰምተህ በቅዱሱ መንፈስህ እንደሞላኸኝ አምናለሁ፡፡ አመሰግንሃለሁ! አሜን

ይህ ጸሎት፣ እግዚአብሔርን ልትጠይቀው የፈለከውን ነገር ይገልጽልሃል? ከሆነ አሁን ጊዜ ውሰድና ጸልየው፡፡

ትእዛዝ፡- ‹‹መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤›› -ኤፌሶን 5፡18

መሞላትህን በምን ታውቃለህ?

የእኛ ማረጋገጫህ በእምነት ላይ ሊመሠረት ይገባል፡፡ የእግዚአብሔር ፍላጎት፣ ሕይወታችን ሁልጊዜ በአምስቱ የስሜት ሕዋሶቻችን መረጃ ላይ እንዲመሠረት ሳይሆን በእምነት እንድንኖር ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ሙላትን በእርግጥ ሽተኸው ከሆነ፣ ኃጢአትህን ተናዘህ ከሆነ፣ ራስህን አቅርበህ ከሆነ፣ ለምነህና ከዛም አመስግነኸው ከሆነ፣ እንግዳው እርሱ ጸሎትህን እንደሰማህና የጠየከውን እንደሰጠህ ልትተማመንበት ትችላለህ፤ ምክንያቱም ይህ የእርሱ ፈቃድ ነውና፡፡

በመንፈሳዊው አለም ውስጥ የተካሄዱ በርካታ ለውጦች፣ በመቀጠል በግዑዙ አለም ላይ ለውጥ ያስከትላሉ ወይም ልዩነት ያመጣሉ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መሞላትህን የሚያረጋግጡ ምን አይነት ነገሮችን ማየት መጀመር አለብህ?

የሐዋሪያት ተግባራት (ሥራ)

ከክርስቶስ ትንሳኤ በኋላ አዲስ በተመሠረተችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በታላቅ ሁኔታ ይገለጥ ነበር፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት በብዛት ይታይ ነበር፡፡ በወቅቱ አስፈላጊ እንደሆነ መጠን እያንዳንዱ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት በተካሄደበት ጊዜ የተለያዩ የድርጊትና የዝንባሌ ለውጦች ይስተዋሉ ነበር፡፡ ከዚህ በታች ያሉትን ጥቅሶች ካነበብክ በኃላ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ከተሞሉ በኃላ ምን እንደተከሰተ ፃፍ፡፡

 1. የሐዋሪያት ሥራ 2፡1-11________________________________________
 2. የሐዋሪያት ሥራ 4፡8-13 (ፍንጭ፡- የጴጥሮስ ዝንባሌ)__________________
 3. የሐዋሪያት ሥራ 4፡31_________________________________________
 4. የሐዋሪያት ሥራ 7፡54-56_______________________________________
 5. የሐዋሪያት ሥራ 9፡17-18_______________________________________

ከላይ የቀረቡት ጥቅሶቹ ከመንፈስ ቅዱስ ሙላት በኋላ ስለተከሰቱት አስደናቂ ተአምራታዊ ውጤቶች ያወሳሉ። ነገር ግን ሁል ጊዜ በእኛ ላይ ልክ እንደዚሁ ይሆናል ማለት አይደለም!

ዘወትር በመንፈስ ቅዱስ በሚመራና ከእርሱ ሃይል በሚቀበል ሰው ሕይወት ውስጥ ምን እንደሚከሰት ነው ከዚህ በታች ያሉት ጥቅሶች የሚናገሩት?

 1. ሉቃስ 4፡1____________________________________________________
 2. ሉቃስ 4፡18-19________________________________________________
 3. ዮሐንስ 16፡13__________________________________________________________
 4. ገላቲያ 5፡22-23_________________________________________________________
 5. ሮሜ 8፡5-8_____________________________________________________

‹‹የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ታላቁ አላማ ለአገልግሎት የሚሆን ሃይል መቀበል ነው፡፡ እግዚአብሔር በይበልጥና ፍሪያማ በሆነ መንገድ ሲጠቀምባቸው ያየኋቸው አማኞች ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ጥልቅ ልምምድ የነበራቸው ነበሩ፡፡›› -ጄ. ኤድዊን ኦር

አንድ ጊዜ ከተሞላን ለሁል ጊዜ ተሞላን ማለት ነው?

የእግዚአብሔርን ፈቃድ ገሸሽ ማድረግና የሕይወታችንን ዙፋን መልሶ በመውሰድ የራሳችንን ፈቃድ ለማድረግ በውስጣችን ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ የአሮጌው ተፈጥሯችን ዝንባሌ ነው፡፡ በመንፈስ እያደግን ስንመጣ ግባችን የሚሆነው ይህንን ሁኔታ እየቀነሱ መሄድ ይሆናል! በመካከሉ አዳልጦን ‹‹በሥጋ›› ተፅዕኖ ውስጥ በምንወድቅበት ጊዜ ደግሞ በመንቃት መንፈስ ቅዱስን ዳግም ለመሞላት እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል፡፡ በኃጢአት በምንወድቅበት ጊዜ ጠፍተናል ወይም መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ተለይቶ ሄዷል ማለት እንዳልሆነ አስታውስ፡፡ በኃጢአት የምንወድቅበት ጊዜ ያሚያመለክተው፣ ኢየሱስን ከሕይወታችን ዙፋን ላይ አውርደን ነገሮችን በራሳችን መንገድ መምራት መጀመራችንን ነው፡፡

የኤፌሶን 5፡18 የግሪኩ ትርጉም ‹‹መንፈስ የሞላባችሁ ሁኑ፡፡›› ነው የሚለው፡፡ አንዴ እስከ ወዲያኛው የምናደርገው ድርጊት እንዳልሆነ አስተውል፡፡ ጥቅሱ የሚገልጸው፣ ይህን ሙላት በየዕለቱ መኖሩን የምናረጋግጠው እንደሆነ ነው፡፡ ‹‹ይህ ሻማ እየበራ ይቆይ!››  የሚለው ትዕዛዝ ይህን ሃሳብ ይገልጻ፡፡ ሲጠፋ፣ የምታደርገው ነገር ቢኖር ዳግም ማብራት ነው፡፡

መንፈሳዊ አተነፋፈስ

‹‹ዳግመኛ ለመሞላት›› ስትሻ ምን ማድረግ እንዳለብህ ለመረዳት የሚያግዝህ ገለጻ እነሆ፡፡ ጉዳዩን እንደመተንፈስ አስበው፡፡ ወደ ውጪ ስትተነፍስ ከሰውነትህ ውስጥ ጎጂ የሆነውን የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ አየር ታስወጣለህ። ወደ ውስጥ በምትተነፍስበት ጊዜ ደግሞ ሕይወትህ እንዲቀጥል የሚያደርገውን የኦክስጅን አየርን ታስገባለህ፡፡ መጥፎውን ታስወጣለህ፣ መልካሙን ታስገባለህ፡፡ በመንፈሳዊውም አለም የሚሆነው ነገር ይኸው ነው፡፡

ወደ ውጭ መተንፈስ፡፡ ኃጢአት በሕይወትህ እንዳለ በምትገነዘብበት ወቅት፣ ይህን መንፈሳዊ የአተነፋፈስ ስርአት ተግባራዊ ለማድረግ ሰአቱ መሆኑን ተገንዘብ፡፡ መጀመሪያ፣ ኃጢአትህን በመናዘዝ ወደ ውጪ ልትተነፍስ ይገባሀል፡፡ ‹‹መናዘዝ›› ለሚለው የግሪኩ አቻ ቃል ‹homologeo› ሲሆን ይህም ማለት ‹‹የተባለውን ያንኑ ማለት›› ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ፣ ድርጊትህ ስህተት እንደሆነ ይነግርሃል – አንተም ያንኑ ትላለህ – ይህ ነው መናዘዝ ማለት፡፡ በጉዳዩ ላይ በእርግጥ ከእርሱ ጋር ከተስማማህ፣ መስማማትህን መናገር ብቻ ሳይሆን የሚያሳዝነውን ይህን ነገር ለመተው ትቆርጣለህ፡፡ ‹‹ንስሃ መግባት›› ማለት ደግሞ ይህ ነው፡፡ ‹‹ማቆም፣ ፊትን መመለስና ከቀድሞ መንገድህ በተቃራኒው ጉዞ መቀጠል፡፡›› የ1ኛ ዮሐንስ 1፡9 ተስፋ ቃልን ታስታውሳለህ?

ወደ ውስጥ መተንፈስ፡፡ አሁን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ የሕይወትህን ዙፋን እንዲረከብ በመጠየቅ፣ የመንፈስ ቅዱስን ሕይወት ወደ ውስጥ ተንፍስ፡፡ እንዲቆጣጠርህ፣ በሃይል እንዲያስታጥቅህና እንዲመራህ በእምነት ፍቀድለት፡፡ ይህንን ጥያቄ ስታቀርብለት፣ እርሱ ደግሞ ኤፌሶን 5፡18 ላይ በተገለፀው ትዕዛዝና በ 1ዮሐንስ 5፡14-15 ላይ በሰፈረው የተስፋ ቃሉ መሠረት ወዲያዉኑ ለጥያቄህ ምላሽ ይሰጣል፡፡

ምን ያህል ጊዜ ይህን ማድረግ አለብኝ?

የሚያስፈልግህን ያህል፡፡ በሳምንት አንድ ጊዜ፣ በቀን አንዴ፣ በየሰአቱ አልያም በየተወሰኑ ደቂቃዎች ልታደርገው ትችላለህ! ዋናው ነገር ተስፋ አለመቁረጥና ለሽንፈት እጅ አለመስጠቱ ላይ ነው፡፡ በውሃ ውስጥ በመስመጥ ላይ ያለ ሰው ሳንባውን ከውሃ በመከላከል አየር ለማግኘት የሞት ሽረት ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ ኃጢአታችንን በመናዘዝና የእርሱን መንፈስ ሙላት በመጠማት መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ዙፋን ላይ የመቀመጡን ወሳኝ አስፈላጊነት መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

መንፈሳዊ የአተነፋፈስ ስርአታችን ልክ እንደ አካላዊ አተነፋፈሳችን ሁሉ ተፈጥሯዊ ሊሆን ይገባል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ወቀሳን በሰማህ በዛች ቅስበት፣ ቆም ብለህ ይህን መንፈሳዊውን አተነፋፈስ ተግባራዊ ልታደርግ ይገባል፡፡ አንዳንድ ክርስቲያኖች በእያንዳንዱ ቀን፣ ገና ከአልጋቸው ከመነሳታቸው በፊት እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኝ አንዳች ነገር በሕይወታቸው መኖሩን ጌታ እንዲጠቁማቸው የመጠየቅና፣ ሲገልጽላቸውም በመናዘዝ መንፈስ ቅዱስን እንዲሞላቸው የመለመን ልማድን አዳብረዋል፡፡

ከሕይወትህ ጋር ማዛመድ፡-

ሰሞኑን በመንፈስ የተሞላ የሕይወት ልምምድ ከሌለህ ይህ ለምን ሆነ? ይህን ለማድረግ ለምን አታቅድም?

ኃጢአት ሰርተህ፣ ተናዘህ፣ ንስሃ ገብተህ፣ በመንፈስ ቅዱስ እንዲሞላህ የጠየቅበትን የቅርብ ጊዜ ታስታውሰዋለህ? ይህን ካደረግህ ሰነባብተህ ከሆነ፣ ምናልባት አሁን በጸጋው ዙፋን ፊት ጊዜ ወስደህ ሙላቱን መናፈቅ ያለብህ ጊዜ ነው፡፡

የቃል ጥቅስ ጥናት፡-

‹‹መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤›› – ኤፌሶን 5፡18

ማጠቃለያ፡- ‹‹በአንተ ውስጥ የእኔን ኑሮ እንድኖር ትፈቅድልኛለህ?›› ሲል ኢየሱስ ይጠይቅሃል፡፡

ያሚቀጥለውን ምዕራፍ ከማጥናትዎ በፊት፣ በመንፈስ ቅዱስ ዙሪያ ሌላ ተጨማሪ ጽሁፍ ለማንበበ ከፈለጉ፣ መንፈስ ቅዱስ ማን ነው የሚለውን ሊንክ ይጫኑ። መንፈስ ቅዱስ ማን ነው?

ምዕራፍ 4ትን ያጥኑ

Leave a Reply

%d bloggers like this: