ክርስቲያኖች ሃሎዊንን ማክበር ይኖርባቸዋል?

ይህ በአል በመላው ዩናይትድ ስቴትስና ካናዳ በየዓመቱ ጥቅምት 31 ቀን በስፋት የሚከበር በዓል ነው። ይህንን ባህል በርካታ አየርላንዳዊያን ወደ ዮናይትድ ስቴትስ ሲፈልሱ ይዘውት እንደመጡ ይነገራል። በአሁኑ ሰአት በአልም ዙሪያ በርካት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያሚያስገኝ ታዋቂ ክብረ በአል ለመሆንም ችሏል።

የሃሎዊን በአል በቀላል ቁጥር ያማይገመቱ ሰዎች ከመንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር ለመገናኘት አስበው የሚዘክሩት ክብረ በዓል ነው። እንደ ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ ገለጻ ሃሎዊን የመጣው፣ “ከ2,000 ዓመታት በፊት የኬልት ሕዝቦች ያከብሩት ከነበረው አረማዊ የሆነ ጥንታዊ ክብረ በዓል ነው።” እነዚህ ሕዝቦች በዚህ ቀን ሙታን በሕያዋን መካከል እንደሚንቀሳቀሱ ያምኑ ነበር። በሌላ አነጋገር ወቅቱ ሕያዋን ሙታንን ለማግኘት እድል ይሰጣቸዋል ብለው ያምናሉ። አልባሳቱም ቢሆን ከዚሁ አምልኮ ጋር የተያያዙና እምነቱ ለያዘው አስተምህሮ መገለጫዎች ናቸው። ለአብነት፣ የሚያስፈራ አልባሳትን የሚለብሱበት ምክንያት መናፍስቱ አልባሳቱን ያደረጉ ሰዎች ከነሱ አንዱ እንደሆኑ እንዲያስቡ በማድረግ ለማራቅ ሲሆን ጣፋጭ ምግቦች የሚያቀርቡበት ምክንያት ደግሞ መናፍስቱን ለመደለል እንደሆነ ይታመናል።  

ክርስቲያኖች የሃሎዊንን በአል ማክበር አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚለው ርዕስ በዚህ በዩናይትድ ስቴትስ አነታራኪ ከሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህ በአል ምንም ጉዳት እንደሌለው በመቁጠር ስርአቱ የሚጠይቀውን አልባሳት በማድረግ የበአሉ ተሳታፊ ይሆናሉ። ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ የሃሎዊን በአል የጨለማውን ስራ የሚያስፋፋ ባእድ አምልኮና የሰይጣን ከብረ በአል እንደሆነ በማመን በበአሉ አይሳተፉም፣ የሚሳተፉትንም ከተሳትፎ እንዲከለከሉ ይመክራሉ። የትኛው ጎራ ትክክል ነው? በውኑ ክርስቲያኖች የእምነታቸውን አስተምህሮ ሳያመቻምቹ የሃሎዊንን በአል ማክበር ይችሉ ይሆነ?

የሃሎዊን በአል ምንም ያህል ዘመናዊ ካባ ለብሶ የንግድ ማስታወቂያ ደርቦ በቴሌቪዥን መስኮት ሲቀርብ ስልጡን ዘመንኛ ባህል ቢምስልም አቀዳዱ እምነት የለሽ ከሆነ ሕዝብ ባሕር እንደሆነ ሁሉን ያሚያስማማ ሃቅ ነው። ሃሎዊን ለብዞዎች፣ ላይ ላዩን ንጹና ጉዳት አልባ ባህል ቢምስልም አባባሉ አጠቃላይ እውነታውን አያሳይም። ለአብነት፣ በክብረ በአሉ ወቅት አንዳንድ ሰዎች ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር ማለትም (ከሙታን መናፍስት፣ ከአድባር፣ ከጠንቋዮች፣ ከዲያብሎስ፣ ወዘተ) ጋር ለመገናኘት ጥረት ማድረጋቸው በአሉን ፍጹም ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን ያሳያል።   

ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ሃሎዊን በቀጥታ የሚናገሩን ነገር ባይኖርም ወሳኔዎችን ልናርግበት ያሚያስችሉንን መርህ ግን ያስጨብጡናል። በብሉይ ኪዳን በእስራኤል ዘንድ ጥንቆላ በሞት ያሚያስቀጣ ሃጢአት ነበር (ዘፀአት 22:18፤ ዘሌዋውያን 19:31፤ 20:6፣ 27)። በአዲስ ኪዳንም ቢሆን ከርኩሳን መናፍስ ጋር የሚደረግ ግንኙነት በክርስትና ትምሕርት የሚወገዝ እንደሆነ የሐዋርያት ሥራ 8:9-24 ላይ የሰፈረው የስምዖን ታሪክ በግልጽ ያስረዳናል። በሐዋርያት ሥራ 13:6-11 ላይ ሰፍሮ የምናነበው የጠንቋዩ ኤልማስ ታሪክ፣ አስማት እና ክርስትና ሊቀላቀሉ የማይገባቸው ሁለት የተለያዩ ተቃራኒ ትምሕርቶች መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል።  በዚህ ታሪክ ወስጥ እንደምናነበው ጳውሎስ ኤልማስን – የዲያብሎስ ልጅ፣ የጽድቅ ጠላት፣ የእግዚአብሔርን መንገድ የሚያጣምም፣ ሲል ጠርቶታል። በሐዋሪያት ሥራ 16 ላይ ደግሞ  የምዋርተኝነት መንፈስ ከነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ ከነበረች አንዲት ሴት ላይ ክፉውን መንፈስ ሴቲቱን ለቋት እንዲወጣ ጳውሎስ ሲያዘው እናነባለን። በዚህ ታሪክ ወስጥ ሌላው ትኩረታችንን የሚስበው ነገር ጳውሎስ ከሴትየዋ የሰማው ነገር ምንም እንኳን መልካም ንግግር ቢሆንም፣ የዜናው ምንጭ ዲያብሎስ ስለሆነ መቃወሙ ነው። በአንጻሩ፣ በሐዋሪያት ሥራ 19:19 ላይ ደግሞ በጌታ ኢያሱስ ያመኑ አዲስ አማኒያን ከቀድሞ ክፉ ስራቸውና አስማታቸው ተመልሰው የአስማት መጽሐፋቸውን ሰብስበው ሲያቃጥሉና ከቀድሞ ስራቸው ንስሃ ሲገቡ እናነባለን።

ክርስቲያኖች እምነታቸውን ሳያመቻምቹ ወይም ሳይሸቅጡ፣ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ በመኖር አንዳንድ የአሕዛብ በአላትን ሳይቀር በመጠቀም ወንጌልን መስበክ እንደሚጠበቅባቸው እምነቴ ነው። ሆኖም ግን እንደ እነዚህ አይነት ውሳኔዎች በታላቅ ጥንቃቄ ሊተገበሩ እንደሚገባቸውም መዘንጋት የለብንም። ይህ ክብረ በአል በሚዘወተርባቸው የምእራብ አገራት ለሚኖሩ ኢትዮጲያውያንና ኤርትራዊያን ወላጆች መልእክቴን ላስተላልፍና ጽሁፌን ልቋጭ። አለም በራሷ መንገድ ልጆቻችንን ከመቅረጿ በፊት ቀድመን ልጆቻችንን በእግዚአብሔር ቃል እውቀት የማስታጠቅ ሃላፊነታችንን ለአፍታ ልንዘነጋው አይገባም። በእኔ እምነት ልጆቻችን በእንደነዚህ አይነት ክብረበአላት ላይ እንዳይሳተፉ ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ይህን ማድረግ በማይቻልበት ጊዜ ድግሞ ተሳትፎአቸው ክርስቲያናዊ አስተምህሮንና ኑሮን በማይቃርን መልኩ መሆኑን ማረጋገጥ የእኛ የወላጆች ሃላፊነት ይሆናል። እግዚአብሔር ይርዳን!!!         

2 thoughts on “ክርስቲያኖች ሃሎዊንን ማክበር ይኖርባቸዋል?”

Leave a Reply

%d