እንዴት ነው ሃሰተኛ ተአምራትን ከእውነተኞቹ ተአምራት መለየት የምንችለው?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ 24:24 ላይ በመጨረሻው ዘመን “ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ።”  ሲል አስጠንቅቋል።  በ 2ኛ ተሰሎንቄ 2:9-10 (አ.መ.ት.) ላይ ደግሞ “የዐመፀኛው አመጣጥ በሰይጣን አሠራር ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ይህም በሐሰተኛ ታምራት በምልክቶችና በድንቅ ነገሮች ሁሉ ይሆናል፤ እንዲሁም ይድኑ ዘንድ እውነትን ባለመውደድ የሚጠፉትን ሰዎች በሚያታልል በተለያየ የክፋት ሥራ ይመጣል” ሲል ቅዱስ ጳውሎስ አማኞችን ያስጠነቅቃል።

እግዚአብሔር ከግብፅ ባርነት እስራኤላውያንን ለማዳን ሙሴን በላከው ጊዜ ሙሴ የእርሱ እውነተኛ መልእክተኛ እንደሆነ ለሕዝቡ ለማረጋገጥ በሙሴ በኩል ተአምራዊ ምልክቶችን ፈጽሟል። ይሁን እንጂ፣ የግብፅ ጠንቋዮችም ሳይቀር በአስማታዊ ጥበባቸው ተመሳሳይ ተአምራትን እንዳደረጉ የታሪኩ ቀሪ ክፍል ያስነበበናል (ዘፀአት 7:22)። በመጨረሻም ድግምተኞቹና አስማተኞቹ አስመስለው ሊያደርጉት የማይችሉትን ተአምራት በማድረግ እግዚአብሔር የእርሱን የበላይነት እንደገለጸ ከታሪኩ እናነባለን (ዘጸአት 8:18፤ 9:11)። ሆኖም ግን የፈርዖን ድግምተኞችም ሳይቀር በዚህ ታሪክ ውስጥ ተአምራት መፈጸም መቻላቸውንም መዘንጋት የለብንም። እንግዳው፣ የተአምራት ምንጫቸው እግዚአብሔር ወይም አጋንንታዊው ዓለም ሊሆን የሚችል ከሆነ እውነተኞቹን ማለትም ከአምላካችን የሆኑትን ካልሆኑት በምን መለየት እንችላለን ያሚለው ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ይገባዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ የሐሰት ተአምራትን መለየት የምንችልበትን ዝርዝር መመሪያ አይሰጥም። ይሁን እንጂ የሐሰት መልእክተኞችን ማንነት መገንዘብ እንድንችል የሚረዳንን ዝርዝር መመሪያ ሰጥቶናል። ሰራተኛው ከእግዚአብሔር ከሆነ ስራውም እንዲሁ ከእርሱ እንደሆነ እናውቃለን። እናም፣ ሰራተኛው ከእግዚአብሔር ዘንድ መሆኑነ የምንለይበትን መመሪያ በመጽሐፍ ቅዱሳችን በማያሻማ መልኩ ተቀምጦ እናያለን። አንደኛው መመሪያ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” (ማቴዎስ 7:16፣20) ያሚለው ሲሆን ሁለተኛውን መመሪያ ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል፣ “የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤…እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ ዓለሙም ይሰማቸዋል። እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን።” (1ኛ ዮሓንስ 4:2-6)።

የመጀመሪያው መመሪያ ክርስቲያናዊ ወይም የየአገልጋይ ሕይወትን (1ኛ ጢሞቴዎስ 3:1-13) መሰረት ያደረገ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አስተምህሮን (2ኛ ጢሞቴዎስ 2:15፤ 3:16-17፤ ዕብራውያን 4:12) መሰረት ያደረገ ነው። አስተማሪው ወይም ተአምር አድራጊው በእነዚህ ሁለት መመዘኛዎች ተፈትሾ ውድቆ ከተገኘ፣ የቱንም ያህል ተአምራት ይከተሉት እንጂ ከእግዚአብሔር የመጣ መልዕክተኛ ሊሆን አይችልም። እግዚአብሔር ቃሉን ሊቃረን አይችልምና።

እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ጉዳይ አለ። የክርስቲያን ሕይወት በእድገት ላይ ያለ ነው። ማንም የተፈጸም የለም። በስራ ላይ ነን። ስለ እውቀትም ስናወራ ዛሬ ላይ ቆመን በትናንት እውቀቶቻችን ላይ የሳቅንበትን ጊዚያት መዘንጋት የለብንም። በእውቀትም ቢሆን መውደቅ መነሳት አይቀሬ ነው። እንግዲያው በሕይወትም ሆነ በእውቀት በመዘኛዎች በዚህ ምድር ላይ ሳለን ከሰው ፍጽምናን አንጠብቅም። እናም የክርስቲያናዊ (የአገልጋይ) ሕይወትን እንደመመዘኛ አድርገን እንዚህን ሰዎች ስንመዝን ክፍተኛ ጥንቃቄ ልናድርግ ይገባል። ደካማ ክርስቲያንን (ሮሜ 15:1) ከአውቆ አጥፊው (ፊልጵስዩስ 3:2)፣ የሚንገዳገድውን አማኝ (1ኛ ተሰሎንቄ 5:14) ከልበ ደንዳናው (ዕብራውያን 3:8፣ 9፣ 15) ሲሮጥ እገረመንገዱን ከሚደነቃቀፈው ወንድም ሆን ብሎ ከሚያስተው አሳች (2ኛ የዮሐንስ 1:7) ለይተን የምናውቅበትን ጥበብ ልንይዝ ይገባል። ለዚህ ነው የእግዚአብሔር ቃል ለፍርድ እንዳንቸኩል ያሚያዘን (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ 4:5)። የሕይወት ድካም ባየንበት ቅስበት ሁል፣ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” የሚለውን ጥቅስ እየሳብን በሰው ላይ ፈጥነን እንዳንፈርድ ልንጠነቀቅ ይገባል። እኛም ከዚያ የጸዳን አይደለንምና። ይህ መመዘኛ የሚያወራው አልፎ አልፎ በክርስቲያኖች ሕይወት ስለሚታዩ ውድቀቶች ወይም ስህተቶች አይደልም። ይህ መመዘኛ ያሚያወራው ውድቀቶቹ ስህተቶች የማንነቱ መገለጫዎች ስለሆነና  ከተገለጠው አመጻውም ንስሃ ለመገባት ፈቃድ ስለሌለው ሰው ነው። እንዲህ አይነቱ ግለስብ እንዚህን ሁለት መመዘኛዎች ጥሶ አገር ጉድ ያሚያሰኝ ተአምራት በማንም ስም ቢያደርግ፣ ክርስቲያኖች ይህ ከአምላካቸው እንዳልሆነ ሊረዱ ይገባል።

በመጨረሻም፣ ድንቅና ተአምራት እንዲሁም ምልክቶች ዛሬም ድረስ ጌታ ወንጌልን ለማስፋትና ቃሉን ለማጽናት ሊጠቀምባቸው እንደሚችል ስናምን፣  እነዚህን ምልክቶች ብቻ መከተል ግን ወደ ተሳሳተ መንገድ ሊመራን እንደሚችልም በማስመር ነው። የእግዚአብሔር ቃል ግን ሁል ጊዜም ቢሆን የእግራችን መብራት፥ የመንገዳችንም ብርሃን ነው (መዝሙር 105፡119)።

2 thoughts on “እንዴት ነው ሃሰተኛ ተአምራትን ከእውነተኞቹ ተአምራት መለየት የምንችለው?”

  1. This is so wonderful and seasonal ade God bless you more in wisdom and deasernment of his will .This is what we need the basic knowledge that shows us to choose our spritual father.

    1. Meri, Thank you for reading the article and for your encouraging comment. I am glad to hear that the article helped you to grow one step further in your spiritual growth. If you go to the bottom right corner of the website and sign up, you will be notified every time I upload a new article. Once again thank you and God bless.

      Adanew Diro Daba

Leave a Reply to tsegaewnetCancel reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading