ቤተ ክርስቲያን ከሚሄዱ ክርስቲያኖች መካከል ከ 80% በላይ የሚሆኑት መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በየቀኑ አያነቡም

የክርስቲያን አገር እየተባልች በምትጠራው ሰሜን አሜሪካ ውስጥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012ዓ.ም. በተደረገው ጥናት መሰረት ወደ ቤተ ክርስቲያን ከሚሄዱ ክርስቲያኖች መካከል ከ 80% በላይ የሚሆኑት መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በየቀኑ እንደማያነቡ ገልጿል። እንግዲህ በጥናቱ መሰረት አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን ከሚሄዱት 100 ክርስቲያኖች መካከል መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በየእለቱ የሚያነቡት ከ20 የሚያንሱ ናቸው። እርሶ ከየትኛው ጎራ ነዎት? ከሚያነቡቱ ከሆኑ እሰየሁ፣ በዚሁ ይቀጥሉ። ከማያነቡቱ ወገን ከሆኑ ከዚህ በታች ያሉትን ጥቂት ማነሳሻ ሃሳቦች ይመልከቱና የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቶን ይመዝኑ የሚለውን ሊንክ በመጫን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትዎን እንዲጀመሩ እናበረታታዎታለን።

  • እግዚአብሔር ስለ እርሱ ባለኝ እውቀት እንዳድግ እና የልቡን መሻት እንድገነዘብ ይፈልጋል፡፡ ኤር. 9፡23-24 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ጠቢብ በጥበቡ አይመካ ኃያልም በኃይሉ አይመካ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ ነገር ግን የሚመካ፡- ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፣ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና ይላል እግዚአብሔር፡፡
  • የእውነት ምንጭ እኔ ወይም ሌላ ሰው አይደለም፡፡ የእውነት ምንጭ ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹የምደርስባቸው እውነቶች›› ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል አንፃር (በመጽሐፍ ቅዱስ) መፈተሽና መረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡
  • እግዚአብሔር እኔን ከሚለውጥበት መሳሪያ አንዱ ቃሉ ነው፡፡ ቃሉ የታመነ ነው፡፡ 2ጢሞ. 3፡16-17 የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።
  • የእግዚአብሔር ቃል፣ በየዕለቱ እንደ ምመገበው ምግብ አስፈላጊዬ ሊሆን ይገባል፡፡ ኢዮብ 23፡12 ከአፉ ከወጣው ትእዛዝ አልራቅሁም፣ የአንደበቱን ቃል ከእለት እንጀራዬ አብልጬ ይዣለሁ፡፡ (አ.መ.ት.)
  • ለማደግ ቃሉን ማስታወስና ማሰላሰል ያስፈልገኛል፡፡ መዝ. 1፡1-3 ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፣ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል፡፡
  • የእግዚአብሔር ቃል በሕይወቴ ውስጥ እንደሚያበራ መብራት ነው፡፡ የልቤን ምስጢሮች ይገልጣል፤ እግዚአብሔር በሚያየኝ መንገድ ራሴን እንዳይ ይረዳኛል፡፡ መዝ. 119፡105 ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርኃን ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቃል የክርስቲያን ሁሉ ነገሩ ነው። የሰው ልጅ ያለምግብ ስጋው መኖር እንደማይችል ሁሉ መንፈሱ ደግሞ ያለ እግዚአብሔር ቃል ሕያው ሊሆን አይችልም። ለዚህ ነው ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ሲል የተናገረው (ማቴ. 4:4)። የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቶን ይመዝኑ የሚለውን ሊንክ በመጫን በጥያቄና መልስ እየታገዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትዎን እንዲጀመሩን መንፈስዎን ያለማቋረጥ እንዲመግቡ እናበረታታዎታለን።

 

Leave a Reply

%d bloggers like this: