መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን!!!

ቀጥተኛ የአማርኛ ትርጉሙ፣ “የሰማይን መንግስት ያውርስዎ”፣ የሚለው ይሕ አረፍተ ነገር በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለመደና ብዙውንም ጊዜ ሃይማኖታዊ በሆኑ አውዶች ውስጥ አዘውትረን የምንጠቀመው አባባል ነው። የሰው ልጅ በሕይወቱ ሊመኛቸው ከሚገባው ትልልቅ ምኞቶች ተርታ ግንባር ቀደሙ ሊሆን እንደሚገባ አስተውለን ምንያህሎቻችን ይህን አባባል እንደምንጠቀመው ፍርዱን ለእናንተው ልተውና ወደተነሳሁበት ዋነኛ አጀንዳ ልሂድ።

የሰማይን መንግስት ለመውረስ መመኘቱም ሆነ ሌላውን ግለሰብ በዚህ መልካም ንግግር መመረቁ ባልከፋ። ዋናው ቁም ነገር ግን፣ “የሰው ልጅ እንዴት ነው ይህን የሰማይ መንግስት ሊወርስ የሚችለው?” የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ መቻላችን ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ማንኳኳት ያለብንን በር መጠቆም የሚያስፈልገኝ አይመስለኘም። ካስፈለገም፣ መጽሐፍ ቅዱስ በቻ ነው።

ይህ ቅዱስ መጽሐፍ፣ መንግስተ ሰማይን ለመውረስ፣ መጀመሪያ የዚህ መንግስት አምላክ ልጅ መሆን የግድ ነው ይለናል።
“ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥…” ሮሜ 8:17
“…ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ።” ገላቲያ 4:7

ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ጥቅሶች መሰረት፣ የመውረስ ቅድመ ሁኔታ ልጅ መሆነ ነው። የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች ነን። የእግዚአብሔር መንግስት (መንግስተ ሰማይ) የምትሰጠው፣ ለእግዚአብሔር ልጆች ብቻ ነው። ይህችን መንግስት ሊወርሱ የሚችሉ፣ የእርሱ ልጆች ብቻ ናቸው። የመንግስተ ሰማይ መታወቂያ፣ የእግዚአብሔር ልጅነት ነው። ይህ መታወቂያ (ልጅነት) ያላቸው ሁሉ፣ የዚህ መንግስት ወራሾች ናቸው። ይህ መታወቂያ የሌላቸው ማለትም የእግዚአብሔር ልጆች ያልሆኑ ሁሉ በዚህ መንግስት ውስጥ ስፍራ (ውርስ) የላቸውም።

ቀጣዩ ጥያቄ ሊሆን የሚገባው ደግሞ፣ “እንዴት ነው የእግዚአብሔር ልጅ መሆን የምችለው?” የሚለው ነው። ለዚህም ጥያቄ ቢሆን ልናንኳኳ የሚገባው በር የመጽሐፍ ቅዱስን በር ነው። የሰው ልጅ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም። የሰው ልጅ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆን ኖሮ፣ የሰው ዘር ሁሉ (የክርስቶስ ጠላትም ሆነ ወዳጅ ባጠቃላይ) የመንግስተ ሰማይ ወራሽ በሆኑ ነበር። ሆኖም ግን ይህ ሃሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም። በዚህ ምድር ላይ የእግዚአብሔር ልጆች እንዳሉ ሁሉ የዲያብሎስ ልጆችም መኖራቸውን መጽሐፍ ቅዱሳችን ይነግረናል (1ኛ ዮሐንስ መልእክት 3:10፣ የዮሐንስ ወንጌል 8:44)። የሰው ልጅ ከሁለቱ የአንዱ ልጅ ነው። ሌላ ምርጫ የለውም። ወይ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ አልያም የዲያብሎስ ልጅ ነው።

የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን የምንችልበትን አንድና ብቸኛ መንገድ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 1:12-13 በግልጽ ያሳየናል። “…ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።” በዚህ ቅዱስ ቃል መሰረት፣ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ የሚሆነው ከእግዚአብሔር በመወለድ ነው። ከእግዚአብሔር የሚወለደው ደግሞ አብ የላከውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በመቀበል ነው። ኢየሱስን መቀበል ማለት በምትክ ሞቱና ትንሳኤው እንዲሁም በአጠቃላይ ትምሕርቱ ማመን ማለት ነው። ይህም ማለት ኢየሱስ እኔን ሃጢአተኛውን ስለማጽደቅ የእኔን ሞት ሞቶልኛል፤ ከእንግዲህ ወዲህም ለእርሱ እንድኖር ስለኔ ተነስቷል፣ ዳግመኛም ለፍርድ ይመጣል ብሎ ማመን ነው። ይህ እምነት ያለው ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዷል፤ የእግዚአብሔር ልጅነት ስልጣንንም ተቀብሏል። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ ደግሞ፣ የመንግስተ ሰማይ ወራሽ ነው ማለት ነው።

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

ሌሎች ተዛማጅ የሆኑ ጽሁፎችን ሊያነቡ የሚሹ ከሆነ፣ እነሆ፦

  1. ከዘላለም ሞት ፍርድ ለመዳን ምን ማድረግ አለብኝ?
  2. ዳግም ልደት ማለት ምን ማለት ነው?
  3. የዘላለም ሕይወት፣ የእግዚአብሔር ታላቁ ስጦታ
  4. ኢየሱስን መቀበል – መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይስ መናፍቃዊ?

መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን!!!

Leave a Reply

%d bloggers like this: