ያለ መንፈስ ሰይፍ፣ እጅግ አደገኛ ወደሆነው መንፈሳዊ ጦርነት እግርዎን አያንሱ!!!

“…የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።” ኤፌ. 6:17

“የመንፈስ ሰይፍ” የሚለው ሐረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን የሚገኘውም በኤፌሶን ምዕራፍ 6 ቁጥር 17 ላይ ነው። የመንፈስ ሰይፍ፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ አማኞች የዲያብሎስን ሽንገላ ለመቃወም ይችሉ ዘንድ እንዲለብሱት ከመከራቸው መንፈሳዊ የጦር መሳሪያዎች (እቃዎች) መካከል አንዱ ነው።

ሰይፍ፣ በጦር ሜዳ ላይ ወታደሮች ጠላቶቻቸውን ለማጥቃትና ራሳቸውን ከጠላት ጥቃት ለመከላከል የሚጠቀሙበት የማጥቂያና መከላከያ መሳሪያ ነው። ሰይፍ፣ ለጦርነት በስፋት ይውል በነበረበት በጳውሎስ ዘመን፣ ወታደሮች ለጦርነት ከመክተታቸው አስቀድሞ መሳሪያውን በአግባቡ መጠቀም ይችሉ ዘንድ ከፍተኛ ስልጠና ይወስዱ ነበር። ስልጠናውን እንደሚገባቸው የፈጸሙ ወታደሮች በወሳኙ ሰአት ማለትም በጦር ሜዳ ላይ ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከልም ሆነ ውጤታማ በሆነ መንገድ ጠላቶቻቸውን ለማጥቃት ይችላሉ።

የአማኝ ጦርነት መንፈሳዊ ነው። “…መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለም…(ኤፌ. 6:12)። ጦርነቱ መንፈሳዊ ስለሆነ ስጋዊ ጥበብ፣ ሃይል፣ ስትራቴጂ በዚህ ስፍራ ላይ ቦታ የላቸውም። ይህን ጦርነት ስብሰባ አይፈታውም፤ ምክክር አያስደነግጠውም፤ እቅድ አይበግረውም። መንፈሳዊውን ጦርነት ለመመከትም ሆነ ለመግጠም መንፈሳዊ የጦር እቃ (መሳሪያ) ያስፈልጋል። ከነዚህ መሳሪያዎች መካከል አንዱ የመንፈስ ሰይፍ ነው። ለመንፈሳዊው አለም ጦርነት ልናውለው የምንችለው ይህ የመንፈስ ሰይፍ፣ የእግዚአብሔር ቃል ነው (ኤፌ. 6:17)። ይህ መሳሪያ ከክፉው አለም ገዢ (ከዲያብሎስ) የሚሰነዘርብንን መንፈሳዊ ጦርነት ለመቋቋም (ለመመከት) ብቻ ሳይሆን መልሰን ለማጥቃትም ተግባር ላይ ሊውል ይችላል። በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሳሳውን ክፉውን እውቀት ለማጥቃት የምንችለውም (2ቆሮ. 10:5) ሆነ በቀጥታ ከዲያብሎስ የሚገጥመንን ሽንገላ (ፈተና) ለመቋቋም የምንችለው በመንፈስ ሰይፍ ማለትም በእግዚአብሔር ቃል ነው (ሉቃስ 4:1-12)።

በዕብራውያን መልክት ላይ ደግሞ፣ የእግዚአብሔር ቃል በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ሰይፍ እንደሆነ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም፣ ሕያውና የሚሰራ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ የሚወጋ ፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት የሚመረምር እንደሆነ ተብራርቷል (ዕብ 4:12)። የእግዚአብሔር ቃል መንፈሳዊ ከሆነው ጠላታችን ጥቃት የምንድንበትና መልሰንም የምናጠቃበት የመንፈስ ሰይፋችን ብቻ ሳይሆን በውስጣችን ያለውን ሌላውን ዋነኛ ጠላታችንን ማለትም በብልቶቻችን ውስጥ ያሚሰራውን ስጋዊ ምኞቶቻችንን ዝም ለማሰኘትም የሚረዳን ዋነኛ መዋጊያችን መሆኑን ልብ ይሉዋል።

በእግዚአብሔር ቃል ይበልጥ በታጠቅን መጠን፣ ይበልጥ እግዚአብሔርን እንፈራለን እንታዘዛለንም (መዝ. 119:11)። በእግዚአብሔር ቃል ይበልጥ በሰለጠንን መጠን፣ በመንፈሳዊው ጦርነት የማያሳፍሩ ወታደሮች፣ የማያፈገፍጉ ደፋሮች፣ እጅ የማይሰጡ ብርቱዎች፣ መልካሙን ገድል ለመጋደል የሚበቁ የክርስቶስ ወታደሮች ለመሆን እንችላለን።

ከዚህ በታች በቀረበው የእግዚአብሔር ቃል ጥናት ላይ በመሳተፍ፣ የመንፈስ ሰይፍ አጠቃቀም ስልጠና በነጻ ይውሰዱ!!! ወደ መንፈሳዊው አለም ጦርነት እግርዎን ከማንሳትዎ በፊት የመንፈስ ሰይፍ የሆነውን ሊንኩን በመጫን የእግዚአብሔርን ቃል አብረውን እንዲያጠኑ ተጋብዘዋል። መልካም ጥናት

 

Leave a Reply

%d bloggers like this: