እንዴት መጽሐፍ ቅዱስም ጌታ ኢየሱስም የእግዚአብሔር ቃል ሊባሉ ይችላሉ?

“የእግዚአብሔር ቃል” የሚለው ሐረግ በተደጋጋሚ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጾ የሚገኝ ሐረግ ሲሆን በአገባቡ እና በዕብራይስጥ ወይም በግሪክ ቃላት አጠቃቀም አንጻር ጥቅም ላይ እንደዋለበት አውድ መጠነኛ የትርጉም ልዩነቶች ሊያሳይ ይችላል። ዮሐንስ 1:1 እንዲህ ይላል፣ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።” በዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጸው “ቃል”፣ ያገለገለው የጌታ ኢየሱስ መጠሪያ (title) በመሆን ነው። ቃሉ፣ ሎጎስ ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም “የሃሳብ መግለጫ” (the expression of thoughts) ማለት ነው። ሎጎስ የሚለው ቃል እግዚአብሔር ለሰው ያለውን አጠቃላይ መልዕክት ሊያመለክት ይችላል (ሐዋ 11:1፣ 1ተሰ 2፡13)። ኢየሱስ የዚህ ጠቅላላ መልዕክት (ማለትም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለው ምሉዕ መልዕክት) አካላዊ መገለጫ በመሆኑ ምክንያት ነው “ሎጎስ” ወይም “ቃል” ተብሎ የሚጠራው (ቆላስያስ 1፡19፣ 2፡9)።

ሎጎስ፣ በጽሑፍ የተቀመጡትን ቅዱሳት መጻሕፍት (መጽሐፍ ቅዱስን) ለማመልከትም በርካታ ጊዜ ጥቅም ላይ ውሏል (ዮሐ 17:17፣ 1ኛ ጢሞ. 4:5፣ ራዕይ 1፡2፣ ቆላ.1፡25)። የዕብራውያን መልዕክት 4:12 እንዲህ ይላል፣ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤” ኢየሱስ በእርሱና በተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል መካከል ስላለው ግንኙነት ሲያወራ፣ እርሱ (ማለትም ኢየሱስ) በጽሑፍ የተገለጸው የእግዚአብሔር ቃል ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ (subject) እንደሆነ ገልጿል። “እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤” ዮሐ. 5:39።

የእግዚአብሔር ቃል (መጽሐፍ ቅዱስ)፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለው አጠቃላይ መልዕክት ሲሆን ኢየሱስ (ቃል) ደግሞ የዚያ መልዕክት አካላዊ መገለጫ ነው።

Leave a Reply

%d bloggers like this: