ለምን??? እንቢልታ ሲነፋ ለቅሶ፣ ሙሾ ሲወጣ ዘፈን

ግራ በተጋባ አለም፣ ግራ የገባው ነፍስ ይዞ፣ “ለምን?” የሚል ጥያቄ ሳያነሳ ቀኑ መሽቶለት ወደ አልጋው የሚሄድ ሰው አለ ብዬ አላምንም። በሰው ነፍስ ውስጥ ብዙ መልስ አልባ ጥያቄዎች አሉ። ያም ሆኖ ግን ነፍስ ከመጠየቅ አትደክምም። ለማወቅ መሻት፣ የተደበቀውን መፈለግ፣ የእውቀትን ደጆች ማንኳኳት፣ ያለተደረሰበትን ለመድረስ መንጠራራት፣ ስውሩን ለመግለጥ ጠልቆ መቆፈር፣ ወዘት፣ የነፍስ ባህሪዋ ነውና “ለምን ጠየቀች?”፣ የሚል ሙግት ልንይዝ አንችልም። እንኳን በውድቀት ሜዳ ላይ (በምድራችን ላይ) የሚጋልበው አሮጌው ሰው ቀርቶ፣ ከውድቀት በስቲያ በነበረው አለም (በዔድን ገነት) ውስጥ የነበረው አባታችን አዳም፣ እድፍ ያላጠላበትን፣ ያለድንግዝግዝ የነበረውን የዋህ ነፍስ ይዞ፣ ፈጣሪው ካዛዘዘው ትእዛዝ ጀርባ፣ “ምን ይኖር?”፣ የሚለውን ለማወቅ ነፍሱ ጓጓች፤ እናም ሞት ሊያስከትል ወደሚችለው የውርርድ ሜዳ ያልፍርሃት ወረደ። ለማወቅ ሲል ሞተ! ያኔ… ገና በየዋህነታችን ዘመን ነፍሳችን ከመጋረጃው ጀርባ ያለውን፣ ከእርሷ የተሰወረ የመሰላትን እውቀት አጮልቃ ለማየት ለሞት እንኳን ካልተመለሰች፣ ዛሬማ እንዴት አብዝታ?!

የነፍስ ጥያቄ ሁሉ የሞትን አፍንጫ የሚያሸት ጥያቄ ብቻ ነው የሚል ድምዳሜ አልያዝኩም። እንዳውም አብዛኛው ጥያቄያችን ከፍትህ ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑ አስገርሞኝ እንጂ። በዚህ ማለዳ ነፍሴ “ለምን?” እያለች ከምትጠይቀኝ የሙግት ማማ ላይ ለአፍታ ወርጄ፣ እንደኔ፣ “ለምን?” እያሉ ፈጣሪያቸውን የሚሞግቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች እንዳሉ አይ ዘንድ ቅዱሱን መጽሐፍ ከፈትኩ። በጥያቄያቸውና በጥያቄዬ መካከል ያለው የይዘት መመሳሰል ቢያስገርመኝ፣ ለራሴ፣ “ለካ ሰው ሁል ጊዜ፣ ሰው ነው አልኩ”።

ከሰው ተሰውረን፣ በልባችን በለሆሳስ፣ ለራሳችን፣ በውስጣችን፣ እግዚአብሔርን የጠየቅናቸው ስንት ጥያቄዎች ይኖሩ ይሆን? ለምን በእኔ ላይ ክፉ አደረግህብኝ? ለምንስ በፊትህ ሞገስ አላገኘሁም? ለምን ይህን ሁሉ ሸክም በእኔ ላይ አደረግህ? ጌታ ሆይ፣ አንተ ከእኔ ጋር ከሆንህ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብኝ? ተአምራትህ ወዴት አለ? አባት ሆይ፥ ለምን ርቀህ ቆምህ? በመከራዬ ጊዜ ለምን ትሰወርብኛለህ? አባ፣ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳንና ከጩኸቴስ ስለምን ትርቃለህ? እግዚአብሔር ሆይ ለምን ረሳኸኝ? ጠላቶቼስ ሲያስጨንቁኝ ለምን ዝም ትላለህ? አባት ሆይ ለምን ከልመናዬ ፊትህን ትሰውራለህ? መከራዬንና ችግሬንስ ለምን ትረሳለህ? አቤቱ፣ ለምን ጣልከኝ? ፊትህንስ ከእኔ ለምን ትሰውራለህ? እንዲህ አድርገህ የምትከራከረኝ ለምን እንደ ሆነ ንገረኝ? አባት ሆይ፥ ከመንገድህ ለምን አሳትከኝ? እንዳልፈራህም ልቤን ለምን አጸናህብኝ? አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? የኃጢአተኞች መንገድ ስለምን ይቃናል? በደልንስ ለሚያደርጉ ሁሉ ስለምን ደኅንነት ይሆናል?

ከላይ የተዘረዘሩት ጥያቄዎች ሁሉ እኔ ያልፈጠርኳቸውም። እነዚህ ሁሉ፣ “ለምኖች” እጅግ ከምንወዳቸውና ከምናከብራቸው መልካሚቱንም የሕይወት መንገድ ከምንማርባቸው የእምነት አባቶች፣ ነቢያቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ታላላቅ ሰዎች አንደበት የወጡ መቃተቶች መሆናቸውን ቢያውቁ ምን ይሰማዎት ይሆን? ሙሴ፣ ጌዴዎን፣ ዳዊት፣ ኢዮብ፣ ኢሳይያስ፣ ዕንባቆም፣ እንዲሁም ጌታ ኢየሱስ ሳይቀር “ለምን?” ሲሉ ወደ ፈጣሪ እንደጮሁ ቢያውቁ ለእርስዎ እና ለእኔ የልብ ጩኸት ምን ፋይዳ ይኖረው ይሆን? እኔ የተማርኩትን እንዳካፍልዎ ይፍቀዱልኝ።

ለካ፣ “ለምን?” ተፈጥሯዊ የነፍስ ጩኸት ነው። ለካ፣ “ለምን?” ፍትህ በተጓደለበት አለም ለምትሰቃየዋ ነፍሳችን የሲቃ ድምጿ ነው። ለካ፣ “ለምን?” ሊሆን የተገባው ሳይሆን ሲቀርና ሊሆን ያልተገባው ደግሞ ሲሆን ስታይ ለምትተክዘዋ ነፍሳችን የእሪታ ዋሽንቷ ነው። ለካ፣ “ለምን?” በጭንቀትና በፍርሃት፣ በሃዘንና በትካዜ ወገቧ ለጎበጠው ነፍሳችን የምጥ ድምጿ ነው። ለካ፣ “ለምን?” በሆነውና እየሆነ ባለው ግፍ ለተሰበረችው ነፍሳችን የሃዘን እንጉርጉሮዋ ነው። በአጭሩ፣ ለካ “ለምን?” ሰው የመሆናችን፣ በውድቀት አለም፣ በወድቀ ሰውነት ውስጥ ሆነን፣ ካለብን ከበባ ለማምለጥ የምናሰማው ሰዋዊና ተፈጥሯዊ ጥያቄያችን ነው።

የ “ለምን?” ጩኸት በነፍሳችን ውስጥ ከቶ እንደሌለ ከማስመሰልና ያልሆነውን ሆነን ከመኖር ይልቅ የምራችንን በቅን ልብ አብዝተን ፈጣሪያችንን፣ “ለምን?” ብንል፣ ባለመዳኒቱ ጌታ በሽተኛ መሆናችንን ላወቅነው ለእንደኛ አይነቶቹ ጯሂዎች በጊዜው ይደርስልናል። ነፍስ በውስጥ “ለምን?” እያለች በምትሰቃይበት ዘመን አታሞ ማስመታት ማለት እንቢልታ ሲነፋ ለቅሶ፣ ሙሾ ሲወጣ ዘፈን አይነት አይመስላችሁም? ነፍሳችን በውስጧ ለምን ማለት ስትፈልግ፣ አንደበታችንም አብሮ ለምን ሊል ይገባዋል ባይ ነኝ። ውስጥ ሳይስቅ ጥርስ ቢያገጥ ምን ዋጋ አለው? ነፍስ ደስ ሳትሰኝ ቆዳ በዘይት ቢረሰርስስ ምን ይፈይድልናል? ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፡ – ለሃዘንም ቢሆን ጊዜ አለው፣ ለጥያቄም ቢሆን ጊዜ አለው፣ ለጩኸትም ቢሆን ጊዜ አለው። እናም፣ ነፍሴ ለምን ማለት ስትመኝ፣ አንደበቴን ላልከለክላት ወሰንሁ።

ዘኍ. 11፥1፣ መሣ. 6፥13፣ መዝ.10፥1፣ መዝ. 22፥1፣ መዝ. 42፥9፣ መዝ. 43፥2፣ መዝ. 44፥23፣ መዝ. 44፥24፣ መዝ. 74፥11፣ መዝ. 88፥14፣ ኢዮብ 10፥2፣ ኢዮብ 24፥1፣ ኢሳ. 40፥27፣ ኢሳ. 63፥17፣ ኢሳ. 12፥1፣ ኢሳ. 5፥19፣ ዕን. 1፥13፣ ዕን. 1፥14፣ ማር. 15፥34

ጌታ ጸሎታችንን ይስማ!

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading