ክፉ የሆነውን የሥጋ ስራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን በሕይወት ትኖራላችሁ። (አ.መ.ት. ሮሜ 8:13)

ይህን ያህል ዘመን በክርስትና ሕይወት ቆይቼም እንኳ ይህ እና ያ ሃጢአት ዛሬም ያስቸግሩኛል። አሁንም ድረስ በዚህኛው ሃጢአት ባርነት ውስጥ ነኝ። እከሌ ከሚባለው ሃጢአት መላቀቅ አልቻልኩም። መልካም ሰው ለመሆን ዘወትር እጥራለሁ፤ ነገር ግን ስኬት ከኔ እጅግ ርቋል። ምኞቴና ምግባሬ የሰማይና የምድር ያህል ተራርቀዋል። ጥረቴና ውሎዬ ፊትና ጀርባ ከሆኑብኝ አመታት ቆጠርኩ። አሁንማ በራሴ ከማፈሬ የተነሳ ክርስቲያን ነኝ ብዬ ራሴን ማስተዋወቅ አንገቴን ያስደፋኝ ጀምሯል። የምወደውን ሳይሆን የማልወደውን አደርጋለሁና። ኸረ ለመሆኑ ከዚህ ባርነት ማን ነው የሚታደገኝ? – የሚል ጩኸት ላለው ሰው የቅዱስ ጳውሎስ ምክር፣ – ክፉ ከሆነው የሥጋችን ስራ ነጻነት የምንወጣው በእግዚአብሔር መንፈስ ቁጥጥር ውስጥ በመሆን ብቻ ነው ይለና (ሮሜ 8:1-39)።

ክፉ የሆነው የሥጋችን ስራ ወይም ሃጢአታዊ ዝንባሌአችን፣ በራሳችን አቅም አይመከትም። መንፈሳዊ ጥረቶቻችን፣ ክርስቲያናዊ ምኞቶቻችን፣ የፈቃድ ጉልበታችን (will power)፣ መራር ውሳኔዎቻችን፣ ጥንቃቄዎቻችን፣ ትምህርቶቻችን፣ ስልቶችና እቅዶቻችን፣ ሃይማኖታዊ ምግባሮቻችን ሳይቀሩ በሥጋችን (በአሮጌው ሰዋችን) ውስጥ ያለውን የሃጢአት ዝንባሌ ወይም የሃጢአት ሃይል (the power of sin) ማስገበር አይችሉም፡፡ እውነታው ይህ ቢሆንም፣ ስለራሳችን ያለን ግምት እጅግ የተዛባና አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ለመቀበል ቀላል አይሆንልንም። በአይምሯችን ሳይሆን በልባችን ይህን እውነት አምኖ ለመቀበልና ውስጣዊ ሳይሆን ውጫዊ እርዳታ ለመጠየቅ ለብዙዎቻችን ረጅም አመታት ይፈጅብን ይሆናል።

በእለት ተዕለት ሕይወታችን ከሃጢአት ሃይል ባርነት ነጻ የሆነ የድል ሕይወትን እያጣጣምን ለመኖር በናፈቅን ቁጥር፣ መፍትሄው በእኛ ውስጥ ያለ ይመስል ፈልጎ ለማግኘት የምናረገው እርባና ቢስ ጥረት ዋነኛ ችግራችን ነው። ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ማወቅ ያለብን አንድ ትልቅ ቁም ነገር አለ፤ ይኸውም እኛ ውስጥ ያለው ችግሩ እና ከችግሩ የመውጣት ፍላጎት ብቻ እንጂ መፍትሄው አለመሆኑን። መፍትሄው ከላይ ነው። እኛ የችግሩ እንጂ የመፍትሄው አካል አይደለንም። ይህን የተረዳው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም” ሮሜ 7:18። ቅዱስ ጳውሎስ እያለን ያለው – “በእኔ፣ ማለትም ኀጢአተኛ በሆነው ተፈጥሮዬ ወይም ሥጋዬ ውስጥ ምንም በጎ ነገር እንደማይኖር ዐውቃለሁ፤ በጎ የሆነውን የማድረግ ምኞት አለኝ፤ ነገር ግን ልፈጽመው አልችልም” ነው። “ታዲያ ይህን ማመን ቀላል አይደል እንዴ?” የሚል አንባቢ ካለኝ፣ መልሴ ይህን ታላቅ መገለጥ መረዳት እንደምናስበው ቀላል አለመሆኑን ማሳወቅ ነው። አባታችን አዳም የወደቀበት ፈተና እና እኛም ዛሬ ድረስ የምንፍገመገምበት ወጥመዳችን ይኸው በራሳችን ላይ የመደገፍ አባዜ ነው። በቅድመ-ውድቀት ዘመን የሰው ልጅ ጥፋት ማማለያ የነበረው በእግዚአብሔር ላይ ከመደግፍ ይልቅ በራስ ላይ የመታመን ፈተና (ዘፍ. 3:5)፣ በድኀረ-ውድቀት ዘመንማ እንዴት አብዝቶ ዋንኛ ወጥመዳችን አይሆን? ቀድሞም ገደል የከተተን ምኞታችን እንደ እግዚአብሔር መሆን ነበር ዛሬም በድብቅ የሚያጠምደን አምሮት ይኸው ነው (ዘፍ. 3:22)።

ሰው እግዚአብሔርን ከማመን ይልቅ ራሱን ማመን ይቀለዋል። በፈጣሪው ከመታመን ይልቅ በራሱ መታመንን ምርጫው ያደርጋል። መፍትሄን ከአምላኩ ከመሻት ይልቅ መፍትሄውን በራሱ ውስጥ መፈለግ ይቀርበዋል። ፈጣሪዉን አማራጭ (alternative) ወይም ሁለተኛ (second option) ማድረግ ተፈጥሯዊ ዝንባሌው ነው። እናም በፈተና፣ በችግሮች እና በትግሎች ውስጥ ሲያልፍ መፍትሄውን በቀዳሚነት የሚፈልገው በራሱ ውስጥ ካለ ጥበብ፣ ስልት፣ ተሞክሮ፣ ግብአት፣ ወዘተ መዝገብ ውስጥ ነው። ከሃጢአት ሃይል ጋር ለሚያደርገውን ግብግብ መፍትሄው ጾሙ፣ ጸሎቱ፣ ምጽዋቱ፣ አገልግሎቱ፣ እና መሰል ሃይማኖታዊ ስርዓቶቹ እንደሆኑ ያስባል፤ ይሞክራልም። እነዚህ ሃይማኖታዊ ጥረቶች በዝተው፣ የአማኙ መታወቂ እስኪሆኑ ድረስ በሕይወቱ ላይ ቢትረፈረፉ ባልከፉ። ነገር ግን ችግሩ ያለው እነዚህን ጥረቶች በራሳቸው የችግሩ መፍትሄ አድርጎ መውሰዱ ላይ ነው። እነዚህ ጥረቶች፣ በራሳቸው መፍትሄዎች ሳይሆኑ ወደ መፍትሄው የሚያመለክቱ የመንገድ ላይ ጠቋሚዎች ናቸው።

ሆኖም ግን፣ ከነዚህ ጥረቶች በተጓዳኝ አልፍ አልፎ የሚከሰቱ ዘላቂ ያለሆኑ “መንፈሳዊ ድሎች” ስለሚታዩ ጥረቶቹን በመፍትሄነት የመከተል ፈተና ቀላል አይሆንም፡፡ ከዚህ የተነሳ፣ ያደረግነው ውሳኔ ትክክል እየመሰለን አንጻራዊ ድል ስናገኝ ጥረቶቻችንን እያደነቅን፣ ስንሸነፍ ደግሞ ይበልጥ እየጣርን መውጫ በሌለው አዙሪት ውስጥ ለረጅም ዘመን ስንዳክር እንኖራል። እስራኤላውያን አንዱን ተራራ ለ40 አመት ያለፍሬ ደግመው ደጋግመው ሲዞሩት እንደነበር የእኛም በራሳችን ውስጥ ለሃጢአት መፍትሄ የመፈለግ ጥረት እንዲሁ ነው። “ይህን ተራራ መዞር ይበቃችኋል” የሚል ሰማያዊ አዋጅ ውስጥ መፍትሄያቸው እንደነበረ ሁሉ የእኛም የሃጢአት መፍትሄ ያለው ይህን ሃጢአታዊ የስበት ሃይል “በቃ!” በሚለው በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ላይ በማረፍ ብቻ ነው። ይህ ክፉ የሥጋ ሥራ መፍትሄ የሚያገኘው በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ሙላት ብቻ ነው። በመንፈስ ቅዱስ ሙላት ውስጥ በምንገኝበት ወቅት፣ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ያለው የግንኙነት መስመር ጠንካራና ያልደፈረሰ ይሆናል፣ ይህም መንፈስ ቅዱስ በድል ሕይወት ጎዳና ላይ እንዲመራንና በሃይል እንዲያስታጥቀን መንገድ ይከፍታል፡፡  

በአንዲት ከተማ ውስጥ የተሰበሰበ የአገልጋዮች ኮሚቴ፣ በከተማው ሊደረግ በታቀደው ከተማ-አቀፍ የወንጌል ዘመቻ ዲ.ኤል. ሙዲ ይሳተፍ አይሳተፍ በሚለው ጉዳይ ላይ እየመከረ ነው፡፡ (ዲ.ኤል. ሙዲ፣ እግዚአብሔር በታላቅ ሃይል በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለክብሩ ከተጠቀመባቸው ስመጥር ወንጌላዊያን መካከል አንዱ ናቸው።) በመጨረሻ፣ አንድ ሙዲ እንዲጋበዝ ያልፈለገ ወጣት አገልጋይ ከመቀመጫው በመነሳት፣ ‹‹ለምን ሙዲ አስፈለገ? እርሱ መንፈስ ቅዱስን ተቆጣጥሯል እንዴ?›› ሲል ጠየቀ፡፡ “በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን?” (ዘኍ. 12:2) ብለው እንዳጉረመረሙት አሮንና ማርያም አይነቷ ቅናት ቢጤ አስተያየት መሆንዋን አንባቢ ልብ ይሉዋል። ጥቂት ዝምታ ከሰፈነ በኃላ አንድ በእድሜ ገፋ ያሉና ፈርሃ እግዚአብሔር ያደረባቸው አገልጋይ ከመቀመጫቸው በመነሳት፡፡ ‹‹እርግጥ ነው፣ ዲ.ኤል ሙዲ መንፈስ ቅዱስን አልተቆጣጠረም፤ ሆኖም ግን መንፈስ ቅዱስ እርሱን ተቆጣጥሮታል፡፡›› በማለት ለወጣቱ አገልጋይ ጥበብ የተሞላው ምላሽ ሰጡ፡፡

ምንም እንኳን እግዚአብሔር በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት በሕይወታችን ውስጥ ቢኖርም፣ ሙሉ በሙሉ ፈቃዳችንን ስሜታችንን እውቀታችንን፣ ሰውነታችንን፣ መንፈሳችንን እና መላ ማንነታችንን እንዲቆጣጠር ለመፍቀድና ለመንፈግ ‹‹ነፃ ፈቃድ›› አለን፡፡ እግዚአብሔርን ለመታዘዝም ሆነ ላለመታዘዝ መምረጥ እንችላለን፡፡ አለመታዘዝን በምንመርጥበት ጊዜ ተገቢ ባልሆነው ምርጫችን ምክንያት በሕይወታችን ሊመጣ የሚችለው መከራ እንዲያገኝን ከመፍቀድ አልፎ በአምባገነንነት እንድትታዘዘው አያስገድደንም! የእግዚአብሔር አላማ የራሳቸው የሆነ ፈቃድ የሌላቸው የሮቦት ሰራዊት በምድር ላይ ማፍራት ሳይሆን በጽድቅ የሚኖሩ እና በመንግስቱ ውስጥ አብረውት የሚሰሩ ወንድና ሴት ልጆችን ማፍራት ነው፡፡

ወንጌልን ባመንን ቅስበት፣ እግዚአብሔር ቅዱስ መንፈሱን በውስጣችን አድርጓል። ይህ ክንውን ከእግዚአብሔር ጋር የጀመርነውን የማይቋረጥና ዘላለማዊ ዝምድና (relationship) ያመለክታል። ይህ ዝምድና በየእለቱ እየታደሰ በሚሄድ ሕብረት (fellowship) ሊጎለብት ይገባል። በመንፈስ ቅዱስ ላይ ለመደገፍ በማንመርጥበት ጊዜ ሁሉ ዝምድናችን (ማለትም ልጅነታችን) እንዳለ ቢሆንም ሕብረታችን ግን ይታወቃል።  ይህ በሚሆንበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ ሕብረታችንን በንስሃ አድሰን ከእርሱ ጋር የጀመርነውን ሕብረት እንድንቀጥል በፍቅር ይጠራናል። ለዚህ የፍቅር ጉትጎታ ጀርባ ብንሰጥ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል በውስጣችን ያለውን የመንፈስ ቅዱስ እሳት እናዳፍናለን (1ተሰሎንቄ 5፡19)፡፡ ይህ ማለት የሕይወታችን ዋነኛ ሰራተኛ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ያለስራ በማስቀመጥ መስራት የማንችለውን ስራ በራሳችን ተፈጥሯዊ ሃይል ለመስራት ደፋ ቀና ማለት ጀመርን ማለት ነው። ውጤቱም ፈሬቢስነት፣ ሃዘንና የሃጢአት ባርነት ብቻ ነው። ባለመታዘዛችን መንፈስ ቅዱስን ልናሳዝነው እንደምንችል መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፦ “ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ።”(ኤፌሶን 4፡30)፡፡ በእለት ተዕለት ሕይወታችን  ከሃጢአት ባርነት ነጻ ወጥተን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተሳካ የሕብረት ጉዞ ለመጓዝና ፍሪያማ ኑሮ ለመኖር ከፈለግን ቸርነትና ርህራሄ ለተሞሉት ጥያቄዎቹ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ይገባናል!

በመንፈስ ቅዱስ መሞላት (በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ውስጥ መሆን) እንዲያው በዘፈቀደ የሚመጣ ሳይሆን  በፈቃደኝነታችን ላይ የተመሠረተ እና ውሳኔአችንን የሚጠይቅ እንደሆነ ‹‹መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤›› ኢፌሶን 5፡18 የሚለው ቃል በትዛዝ አንቀጽ መጻፉ መረጋገጫችን ነው። የእርሱ ድርሻ እኛን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር (መሙላት) እና ለአብ ክብር ፍሪያማ ማድረግ ነው። የእኛ ድርሻ ደግሞ እንዲቆጣጠረን መፈለግና መፍቀድ ነው። ያለ እርሱ ምንም ልናደርግ የማንችል መሆናችንን ስናውቅ እና የድል ሕይወት ለመኖር በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ውስጥ መሆን ግዴታችን እንጂ አማራጫችን እንዳልሆነ ስንረዳ በጥም የምታለከልክ ዋላ ወደ ውሃ ምንጭ እንደምትናፍቅ ነፍሳችንም እርሱን እና እርሱን ብቻ ማለቷ አይቀሬ ይሆናል። ያን ጊዜ ነው እንግዲህ ከሃጢአት ባርነት ነጻ የመሆን ቅኔና ዜማ ከአፋችን መፍለቅ የሚጀምረው። አምላካችን የልቦናችንን አይኖች ያብራ፣ አሜን!

3 thoughts on “ክፉ የሆነውን የሥጋ ስራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን በሕይወት ትኖራላችሁ። (አ.መ.ት. ሮሜ 8:13)”

 1. Rahel Yeshitila

  ተባረክ: ፀጋውን አብዝቶ ይጨምርልህ:: ትክክል ነው:: ብዙ ግዜ ግን ከእኔ ጀምሮ ፍፁም ለመሆን እንጥራለን:: አንዲት መተላለፍን በራሳችን ላይ ስናይ የረከስን: ቅድስናችንን ያጣን: እግዚያብሄር የሚያዝንብን ሆኖ ይሰማናል:: ብዙ ግዜ ይህ ሲሰማኝ በራሴ አይቸዋለህ:: ሲጀመር ንፁህ ፍፁም ሆነን ጌታ አላገኘንም:: ከነሀጥያታችን ነው: የወደደን:: አሁንም ቢሆን ሀጥያተኛውን የሚወድ ሀጥያትን የሚጠላ አምላክ ነው ያለን ::ሀጥያትን መጥላት የኛም ተግባር መሆን አለበት:: ነገር ግን እንደጌታ ፍፁም ለመሆን አንችልም :: የምንችልበት ግዜ ግን ይመጣል:: አሁን ግን ተላልፈን ብንገኝ ይቅር ሊለን ባባቱ ቀኝ ተቀምጧል: ስለዚህ ለሰራነው ሀጥያት ሁልግዜ በንሰሀ ዉስጥ መሆን አለብን:: ሀጥያት አይመጥነንም : ብሳሳት ግን አሁንም ይቅር እባላለህ:: ይህ ለኔ በፅድቅ መኖር ነው:: አሁንም ተባረክ እንዲያው ፍፁም ለመሆን ስንጥር እንዳንሰናከል ብዬ ነው ::

 2. አሜን፣ ራሄል።

  የአዲስ ኪዳን የሕይወት ስርዓት እኛ ለእግዚአብሔር በምንሰጠው ነገር ሳይሆን ከእግዚአብሔር በምንቀበለውን ነገር ይጀመራል፣ በእርሱ ስራ ላይ በማረፍ ይቀጥላል በመጨረሻም በድል ብስራት ዜማ ይጠናቀቃል። “እርሱ (ኢየሱስ) ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበባችን፣ ጽድቃችንና ቅድስናችን፣ ቤዛችንም ሆኖአል።” 1ቆሮ 1:30-31 ጽድቅ ከእኛ እንዳልሆነ ሁሉ ቅድስናም ከእኛ አይደልም። ጽድቅ የስራ ውጤት ሳይሆን በእምነት የሚወረስ ነጻ ስጦታ እንደሆነ ሁሉ ቅድስናም እንዲሁ የእኛ ጥረትና ላብ ውጤት ሳይሆን በተጠናቀቀው የክርስቶስ ሥራ ላይ በማረፍ የሚገኝ የእምነት ፍሬ ነው።

  የጌታ ፍቅር ይብዛልሽ!!!
  አዘጋጁ

 3. Pingback: “…የምጠላውን ያን አደርጋለሁ…የምወደውን እርሱን አላደርገውም።” ሮሜ 7:15 – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d bloggers like this: