ለምን በእግዚአብሔር ላይ እታመናለው?

ለምን በእግዚአብሔር ላይ እታመናለው? ለምንስ በእርሱ ላይ እደገፋለሁ? ለሚለው ጥያቄ የእግዚአብሔርን ባሕሪ ምክንያት ከማድረግ የተሻለ መከራከሪያ ያለ አይመስለኝም። አንድን ሰው ለማመንም ሆነ ላለማመን ባህሪውን በአስረጂነት መጥቀስ ተገቢም፣ አግባብም እንደሆነ ሁሉ በክርስትና ጉዞአችን ውስጥ ያለማቋረጥ ከነፍሳችን የሚወነጨፈውን የ “ለምን?” ነበልባላዊ ቀስት ለመመከት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ባሕሪ የገለጠው እውነታ ላይ እምነታችንን መመስረት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።

ከዚህ በታች የምናያቸው የእግዚአብሔር ባህሪያት የሰው አስተያየቶች አይደሉም፤ በቅዱሳኑ በኩል መንፈስ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር የገለጣቸው እውነቶች እንጂ። ገላጩን ካመንን የተገለጠውን ማመን ግድ ይሆናል። የተገለጠውን ካመንን ደግሞ በተገለጠው መደገፍ ግዴታ እንጂ አማራጭ አይሆንም። በተገለጠው ስንደገፍ፣ የተገለጠው ያለንን ሁሉ መሆን እንጀምራለን። የተገለጠው ያለንን መሆን ስንጀምር ደግሞ፣ ለእግዚአብሔር ክብር በጨለማው አለም ላይ የሚያበሩ ብርሃኖች እንሆናለን ማለት ነው (ማቴ. 5:16)።

በቃሉ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ባሕሪይ ጠንቅቆ ማወቅ፣ በዛም እውነት ላይ እምነታችንን መመስረት፣ ከመሰረታዊ የመታዘዝ ፈሬው ባሻገር፣ በእርሱ ላይ መታመናችን ምን ያህል ምክንያታዊና ተገቢ እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ባሕሪ በአመክኗዊ ሚዛን ላይ ስናስቀምጥ ደግሞ፣ እርሱን አለማመን ኢ-ምክንያታዊ፣ በእርሱ ላይ መታመን ደግሞ ምክንያታዊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እርሱን ለመቃወም ወይም ታቅበን ለመኖር ምንም አይነት አሳማኝ ምክንያት አይኖረንም፡፡ የወደቀው/የተበላሸው/አሮጌው የሰው ተፈጥሮ ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ያምፃል፡፡ እግዚአብሔርን የማናምንበት ዋና ምክንያትም እርሱ እንደኛ አይነት ባሕሪ ያለው ስለሚመስለን ነው፡፡ እርሱ እንደ እኛ አይነት ባሕሪ ቢኖረው እርሱን አለማመናችን ምክንያታዊ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን፣ እርሱ እንደ እኛ አይነት ባሕሪይ የለውም፣ አይኖረውምም። ሐሰትን ይናገር ዘንድ፣ ይጸጸትም ዘንድ፣ ይዋሽና ይበድል ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለምና።

“… እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው።” ዘዳ. 32፡3-4

“በእውነት እግዚአብሔር ክፉ አይሠራም፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ ፍርድን ጠማማ አያደርግም።” ኢዮብ 34፡12

“…እግዚአብሔር ከቶ ሊዋሽ አይችልም፤” ዕብ. 6፡18 (አ.መ.ት.)

“…እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥…” 1ዮሐ. 4፡16  

“እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤…” ሚል. 3፡6

ከላይ የቀረቡትን የእግዚአብሔር ባሕሪያት አንብቦና ተግንዝቦ፣ እግዚአብሔር በሕይወታችን ላይ ያለውን አላማ መልካምነት መጠርጠርም ሆነ አለማመን ሚዛናዊም ሆነ ፍትሃዊ ሊሆን አይችልም። እነዚህን ባሕሪያቶቹን ተረድቶ፣ “እግዚአብሄር ሆይ ለምን ተወከኝ? ለምን በእኔ ላይ ክፉ አደረክብኝ? ለምን ከአቅሜ በላይ ሸክም ታሸክመኛለህ? ይህን ሁሉ መከራና ጭንቀት ለምን አደረሰክብኝ? ለምን ርቀህ ቆምህ? በመከራዬ ጊዜ ለምን ትሰወርብኛለህ? እኔን ከማዳንና ከጩኸቴስ ስለምን ትርቃለህ? ጠላቶቼስ ሲያስጨንቁኝ ለምን ዝም ብለህ ታያለህ? አባት ሆይ ለምን ከልመናዬ ፊትህን ትሰውራለህ? መከራዬንና ችግሬንስ ለምን ትረሳለህ? አቤቱ፣ ለምን ጣልከኝ? አባት ሆይ፥ ከመንገድህ ለምን አሳትከኝ? እንዳልፈራህም ልቤን ለምን አጸናህብኝ? በደልንስ ለሚያደርጉ ሁሉ ስለምን ደኅንነት ታደርጋለህ? ብሎ ማጉረምረም ከእግዚአብሔር ባሕሪይ አንጻር ምክንያታዊ ሊሆን አይችልም።

እርሱ እንከን የሌለበት ፍጹም አምላክ ነው። መንገዱም ሁሉ የቀና ነው። ጠማምነት በእርሱ ዘንድ የለም። የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ እውነተኛና ቅን ነው። ፍርድን ጠማማ አያደርግም። ከቶም ሊዋሽ አይችልም። እነዚህ መለኮታዊ ባሕሪያቶች፣ ነፍሳችን በእግዚአብሔር ላይ ያላትን የጥርጣሬ ጥያቄ ፈጽማ እንድታነሳ ሊያደርጋት ባይችሉም፣ ነፍሳችን በእርሱ ላይ ላለመደግ የምታደርገው ጥረት ሁሉ መሰረት የለሽ ከንቱ ፍርሃት መሆኑን ግን በደማቁ ያሰምራሉ። በእርግጥም፣ እግዚአብሔር ልንታመነውና ልንደገፈው የሚገባን የፍቅር አምላክ ነው! 

“በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤” ምሳሌ 3:5

 

1 thought on “ለምን በእግዚአብሔር ላይ እታመናለው?”

Leave a Reply

%d bloggers like this: