አማኞች ወደ እሳት ባህር ሊጣሉ ይችላሉ ወይ? 2 ጴጥሮስ 2:18-22

ክርስቲያኖች በክርቶስ አምነው ከዳኑ በኋላ ድነታቸውን ያጣሉ ወይ? የዳነ ሰው ወደ ቀድሞው የሃጢአት ኑሮው ቢመልስ ድነቱ ወይም ደኅንነቱ ከእርሱ ይወሰዳል ወይ? የሚለው ጥያቄ የብዙ አማኞች ጥያቄ ነው፡፡ በተለይ፣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ለትርጉም አስቸጋሪ መሆናቸው ጥያቄው ይበልጥ ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ፣ ለትርጉም አስቸጋሪ ከሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል አንዱ የሆነውን ሁለተኛ የጴጥሮስ መልዕክት 2:18-22 በማብራራት ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት እንሞክራለን፡፡

የጴጥሮስ መልዕክት 2:18-22 የሚያነቡ አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ ጴጥሮስ በዚህ መልዕክቱ ላይ የሚያወራው መጀመሪያ አማኝ ሆነው ኋላ ላይ ይህን እምነታቸውን ስለለወጡ ሰዎች ሳይሆን ቀድሞውኑም ቢሆን በክርስቶስ ላይ እምነታቸውን ስላልጣሉ ኢ-አማኒያን ሰዎች ነው ብለው ያምናሉ፡፡ እስቲ ክፍሉን ረጋ ብለን እንመርምር፡፡

“ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፥ በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ። ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው፦ አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና። በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ፦ የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።” 2 ጴጥሮስ 2:18-22

ከቁጥር 17 ከፍ ብሎ ያለው ክፍል ስለ ሃሰተኛ አስተማሪዎች የሚያወራ ሲሆን ከቁጥር 18 ጀምሮ እስከ 22 ያለው ክፍል ደግሞ በነዚህ ሃሰተኛ አስተማሪዎች ሴሰኛ ትምሕርት ስለተታለሉ ሰዎች ይናገራል፡፡ በሃሰተኛ አስተማሪዎች ሴሰኛና ሥጋዊ ምኞት ትምህርት የሳቱት እነዚህ ሰዎች በስሕተት ከሚኖሩት መካከል አምልጠው የመጡ ሰለመሆናቸው ክፍሉ ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም፣ እነዚህ ሰዎች ጌታችንንና አዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ እንደ ገና ተጠላልፈው የተሸነፉ ስለመሆናቸውም ይተርካል፡፡ ጴጥሮስ በ 2 ጴጥሮስ 1:2-6 ላይ የተጠቀመው “እውቀት” የሚለው ቃል እና በዚህ ክፍል ወስጥ የተጠቀሰው “እውቀት” የሚለው ቃል ተመሳሳይ ቃሎች ናቸው፡፡ ይህ ቃል በ 2 ጴጥሮስ መልዕክት ውስጥ ከአማኞች ጋር በተያያዘ ብቻ ጥቅም ላይ የዋለ ነው፡፡ ከነዚህ ማብራሪያዎች በመነሳት ልንደርስበት የምንችለው ትክክለኛ መደምደሚያ፣ ጴጥሮስ በ 2 ጴጥሮስ 2:18-22 ላይ እያወራ ያለው ስለአማኞች መሆኑን ነው፡፡ 2 ጴጥሮስ አማኞችን የሚመለከት መልዕክት መሆኑን ለማረጋገጥ በተጨማሪ የሚከተሉትን ጥቅሶች ይመልከቱ (1፡1፣ 1፡9፣ 3፡1፣ 8፣14፣17-18)፡፡ በ 2 ጴጥሮስ ሦስቱም ምዕራፎች ውስጥ፣ ጴጥሮስ አማኞች በሃሰተኛ አስተማሪዎች ትምሕርት ምክንያት ትተውት ወደመጡት የሃጢአት ኑሮ እንዳይመለሱ ያለውን ስጋት ይገልጻል፤ በዚህ ወጥመድ ተሰናክለው ከመውደቅ እንዲጠበቁም ያሳስባል (1:5፣ 1:10,፣ 2፡18-22፣ 3፡14፣ 3፡17)፡፡

እዚህ ላይ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ዋነኛው ጥያቄ የሚከተለው ነው – ለመሆኑ ጴጥሮስ አማኞች በዚህ ወጥመድ ተይዘው ቢወድቁ ምን እንደሚከተላቸው ነው ያስጠነቀቃቸው? በቁጥር ቀላል የማይባሉ ተንታኞች ቁጥር 21 እና 22ትን በማስረጃነት በመጥቀስ የሚሰጡት መልስ “ዘላለማዊ ፍርድ ወይም – ሲዖል” የሚል ነው፡፡ እነዚያን ጥቅሶች በጥንቃቄ ካነበብን ግን ጴጥሮስ የሚያወራው ዘላለማዊ ፍርድ ስለሆነው ገሃነመ እሳት ሳይሆን ጊዜአዊ ስለሆነው ምድራዊ ፍርድ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ጴጥሮስ በዚህ ክፍል ውስጥ የዘላለምን ፍርድ ለመግለጽ ጥቅም ላይ የሚውሉ  እንደ ገሃነም፣ የእሳት ባህር፣ የማያቋርጥ መከራ፣ ወዘተ አይነት ቃላት ወይም ሐረጋት አለመጠቀሙን ልብ ይበሉ፡፡ ጴጥሮስ አማኞች የመዳንን እውቀት ከተቀበሉ በኋላ እና ከጥፋት ከዳኑ በኋላ ወደ ቀድሞ መንገዳቸው ቢሄዱ ወይም በሃጢአት ቢወድቁ ሊገጥማቸው ያለውን ፍርድ የገለጸው – የጽድቅን መንገድ ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ኋላ ከሚመለሱ፣ ቀድሞውኑ የጽድቅን መንገድ ባላወቁዋት ይሻላቸው ነበር – በማለት ነው።

እነዚህን ሃረጋት አሳጥሮ የዘላለም ፍርድ ወይም ሲዖል በማለት መተርጎሙ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ይህ አተረጓጎም ጴጥሮስ አማኞች መዳናቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ አድርጎ እንዳስተማረ ከማሳየቱ በተጨማሪ ከሌሎች ትምሕርቶቹ ጋር የተቃረነም እንዲመስል ያደርገዋል (ሉቃስ 10:20፣ ዮሐንስ 13:10፣ ሐዋ 10:43-48፣ 11:16-18፣ 15:7-11፣ 1 ጴጥሮስ 1:23-25፣ 2 ጴጥሮስ 1:9፣ 2 ጴጥሮስ 3:8-13)፡፡ ጴጥሮስ በዚህ ክፍል ውስጥ እያለ ያለው፣ አንድ አማኝ በኃጢአት ሕይወት ለመኖር ከመረጠ፣ በምድር ላይ የሚኖረው ኑሮ ክርስቲያን ባይሆን ኖሮ ሊኖረው ከሚችለው ኑሮ ይልቅ የከፋ መሆኑን ነው፡፡

ክርስትያኖችም ሆኑ ክርስቲያን ያልሆኑ ሁሉ በዚህ ምድር ላይ የሃጢአቶቻቸው አስከፊ ውጤቶች ገፈት ቀማሽ መሆናቸው እሙን ቢሆንም ቅጣቱ በክርስቲያኖቹ ላይ እጅግ የከፋ ነው፡፡ ከክፉው አለም መካከል ለቅድስና የተጠራን የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን በአመጻ በውስጣችን ያለውን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ ባሳዘንን (ኤፌ 4:30) ጊዜ፣ የእግዚአብሔር የመጨረሻው ፍርድ በሚገለጽበት በመጨረሻው ዘመን ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን (1ቆሮ 11፡32፣ ዕብ 12፡5-6)፡፡ የሚፈረድብን ወይም የምንገሰጸው ወይም የምንቀጣው ከአለም ጋር እንዳንኮነን ነው፡፡ ኩነኔ የዘላለም ፍርድን የሚያሳይ ቃል ነው፡፡ ክርስቲያኖች ከዚህ ነጻ ናቸው (ሮሜ 8፡1)፡፡ አመጻችን ወይም ኃጢአቶቻችን የሚያስከትሉብንን ጊዚያዊ መዘዞች መቀበላችን ግን አይቀሬ ነው፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትምና (ገላ 6፡7)፡፡ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች በዚህ ደረጃ በምድር ላይ በእግዚአብሔር ላይቀጡ ይችላሉ (ዕብ 12፡8)፤ ፍርዳቸው በሰማይ ቀርቷልና፡፡ አማኝ ግን መንፈሱ (ነፍሱ) በጌታ ቀን እንድትድን በምድር ላይ ለሚያሳየው አመጻ ሁሉ እዚሁ ምድር ላይ ጊዚያዊና ከባድ ፍርድ ይቀበላል (1ቆሮ. 5:1-5፣ 1ቆሮ. 3:15)፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: