በእኔ እምነት፣ በዚህ ምድር ላይ የነበረውና አሁንም ድረስ ፍልሚያው ያልቀዘቀዘው አስጨናቂውና ረጅም ዘመን ያስቆጠረው ጦርነት በሁለት ሃያላን አገራት መካከል የተደረገው ወይም ይደረጋል ተብሎ የሚሰጋው ጦርነት ሳይሆን በአማኞች ሕይወት ውስጥ በአሮጌውና በአዲሱ ተፈጥሮዎች መካከል የሚካሄደው ድምጽ አልባ ጦርነት ነው። የተኩስ እሩምታ የማይሰማበት፣ ሰይፍ የማይመዘዝበት፣ መድፉ የማይደፈይበት፣ ነገር ግን ከሞት ያለተናነሰ የሲቃ ድምጽና የጣር ጩኸት የሚሰማበትን ይህን ጦርንት የሚያውቁ በውስጡ እያለፉ ያሉ አማኞች ብቻ ናቸው። ጦርነት ሊፈጠር የሚችለው ጎራ ለይተው የሚፋለሙ ቢያንስ ሁለት ባላንጣዎች ሲኖሩ ብቻ እንደሆነ እሙን ነው። ያለ ባላንጣ ጦርነትም ሆነ የጦር ዜና የለምና። አማኞች በአንዱ ሰውነታቸው ውስጥ ሁለት ተቃራኒ ተፈጥሮዎችን ይዘው የሚኖሩ ስለሆነ በባላንጣዎቹ መካከል ያለውን አስከፊ ፍልሚያ በሕይወታቸው ያስተናግዳሉ፡፡ የምታወራው ጦርነት በሕይወቴ ፈጽሞ የለም የሚል አንባቢ ካለኝ፣ በትህትና የምጠይቀው ነገር በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት እንዲሆን መጋበዝ ብቻ ነው።
በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ያለሆነ ሰው (ኢ-አማኝ)፣ ያለው ተፈጥሮ አንድ ብቻ ነው። በእንዲህ አይነቱ ሰው ሕይወት ውስጥ ልቡ ወደ ፈጣሪው እንዲያቀናና ንስሃ እንዲገባ ከደካማ ሕሊናው የሚመነጭ መጠነኛ ግጭት ቢገጥመውም፣ ከላይ የገለጽኩትን አይነት መራር ጦርነት ሕይወቱ ሊያስተናግድ አይችልም። ይህን መራርና እልህ አስጨራሽ ጦርነት የሚያውቁትም ሆነ የሚረዱት በክርስቶስ በማመን አዲስ ፍጥረት የሆኑ ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። በክርስቲያኖችም መካከል ቢሆን የጦርነቱ አስከፊነት እነደደረሱበት መንፈሳዊ ብስለት ይለያያል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወንጌልን የሰማና ገና የጦርነቱን መኖር በውል ያላስተዋለ አማኝ ሊኖር እንደሚችል ሁሉ በመንፈሳዊ ጉዞው ከጌታ ጋር ብዙ ርቀት ከመሄዱ የተነሳ ጦርነቱ መኖሩን መገንዘብ ብቻ ሳይሆን በጦርነቱ አስከፊነት ምክንያት እንደ ጳውሎስ፣ “ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?” (ሮሜ 7:24) ያለም ይኖራል።
ለመሆኑ በአማኝ ሕይወት ውስጥ ጦርነት የገጠሙትና እየገጠሙ ያሉት እነዚህ ሁለት ባላንጣዎች እነማን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱሳችን እነዚህን ተፈጥሮዎች – አሮጌው እና አዲሱ ሰው (ኤፌ. 4:22-24፣ ቆላ. 3:9-10፣ ሮሜ 6:6) ወይም ስጋና መንፈስ (ገላ. 5:17-24፣ ሮሜ 8:5፣ ሮሜ 8:3-13፣ ሮሜ 6:6፣ ሮሜ 7:18፣ ሮሜ 9:27፣ 1ጴጥ 2:11፣ ) በማለት ይሰይማቸዋል። አሮጌው ሰው ወይም ስጋ፣ የወንጌልን ዜና ወይም በክርስቶስ አዳኝነትና ጌትነት ያላመነ ሰውን ተፈጥሮ የሚወክል ነው። አዲሱ ሰው ወይም መንፈስ ደግሞ በክርስቶስ የቤዛነት ስራ ያመነና ከዘላለም ፍርድ በእግዚአብሔር ጸጋ ያመለጠ ሰው የተቀበለውን አዲስ ተፈጥሮ ያመለክታል፤ ፡…ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤” (1ቆሮ. 5:17)። አማኝ ይህን አዲስ ተፈጥሮ ሲቀበል አስቀድሞ የነበረው አሮጌው ሰው (ተፈጥሮ) ከውስጡ አይጠፋም። ለዚህ ነው ባመነበት ቅስበት የሁለት ተቃራኒ ተፈጥሮዎች ባለቤት የሚሆነው።
ተረዳውም አልተረዳውም፣ አማኙ የእነዚህ ሁለት ተፈጥሮዎች ባለቤት በሆነ ቅስበት ወደለየለት የጦር ሜዳ ዘምቷል፡፡ ይህ ሕይወት ታዲያ ብዙዎች እንደሚያወሩለት፣ እንደሚዘምሩለትና እንደሚቀኙለት ያለ ዙሪያውን በአበባ የተሞላ የአበባ እርሻ ሳይሆን ቅልጥ ያለ የጦርነት ሜዳ ነው። ይህ ጉዞ የሞት ዜና ያንጃበበበት፣ ብዙ መከራ፥ ችግር፥ ጭንቀት፥ መገረፍ፥ ወኅኒ፥ ሁከት፥ ድካም፥ እንቅልፍ ማጣት፣ ወዘተ የሞላበት መሆኑን ብዙ ክርስቲያኖች ሲናገሩ አልሰማም (2ቆሮ 6፡5፣ 2ቆሮ 11፡27፣ ሮሜ 9፡1-2፣ ፊል 2፡30)። በቤተ ክርስቲያን መድረክም ሆነ በመጽሐቅ ቅዱስ ጥናት ቡድን ውስጥ “…የምጠላውን ያን አደርጋለሁ…የምወደውን እርሱን አላደርገውም።” (ሮሜ 7:15) ከዚህም የተነሳ ነፍሴ በትልቅ ትግል ውስጥ ነች የሚል ሰባኪ የሰማሁበትን አጋጣሚ አላስታውስም። ዘንግቼውም ከሆነ እጅግ በጣም ጥቂቶች መሆናቸውን ብቻ ነው የሚያረጋግጠው፡፡ ታዲያ፣ ይህ ሁሉ “መንፈሳዊ ጀግና” በተሰበሰበበት እነደ እኔ አይነቱ ምስኪን፣ ያለበትን አሰቃቂ የውስጥ ጦርነት እንዴት አድርጎ ይናገር? እንዴትስ እውነተኛውን የአድነኝ ጩኸት ይጩህ? የዚህ ጽሁፍ ጠቀሜታ፣ እውነተኛውን የውስጥ ጩኸት ለመተንፈስ መድርክ ላጥችሁ እነደ እኔ ላላችሁት ምስኪኖች እንጂ ጦርነቱ ለማይሰማችሁ ወይም ተሰምቷችሁ እንዳልተሰማችሁ ለመሆን ለመረጣችሁት አይደለም። ይህን ማሳሰቢያ ከሰጠው ዘንዳ፣ ወደ ሮሜ 7፡14-24 ልመልሳችሁና በጳውሎስ የሕይወት ልምምድ ላይ በመንተራስ በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ያለውን ድምጽ አልባ ግን ህያው ጦርነት ለማስረዳት ልሞክር።
ቅዱስ ጳውሎስ ታሪኩን የሚጀምረው በሙሴ እጅ ሕግ ያልተሰጠበትን ዘመን እንደመግቢያ በመጠቀም ነው። ጳውሎስ ለሚያስነብበን ታሪክ መንደርደሪያነት የመረጠው ዘመን ሙሴ ከእግዚአብሔር ሕግ ያልተቀበለበትን ዘመን ቢሆንም ዘመኑ ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ መሆኑን ግን ልብ ይሏል። ያኔ፣ በሙሴ በኩል በሰው ልጅ ሕግ ባልተሰጠበት ዘመን ሃጢአት፣ ሃጢአት መሆኑ አይታወቅምና እኔም ህያው ሆኜ እኖር ነበር ይለናል (ሮሜ 7፡9)። ከዛም የሰውን ልጅ ታሪክ የሚለውጠው ሕግ ወደ ሰው ልጅ ታሪክ ገባ። ከሕጉም መሰጠት ጋር ተያይዞ የሃጢአት እውቀቶች በሩልኝ (ሮሜ 7፡13)። ከዚህ በፊት ሃጢአት መሆናቸውን እንኳ የማላውቃቸው ጉዳዮች ከሕጉ መሰጠት በኋላ ሃጢአት መሆናቸውን ተገነዘብኩ። ለምሳሌ ሕጉ አትመኝ ስላለ መመኘት ሃጢአት ሆነ። እኔንም ስመኝ በሃጢአተኝነት ኮነነኝ። ከሕጉ መሰጠት በፊት ግን መመኘትን የሚከለከል ሕግ አልነበረምና ተከሳሽ አልነበርኩም። ከዚህ በተጨማሪ፣ ከሕጉ መሰጠት በፊት የመመኘት ተፈጥሯዊ ዝንባሌም እንዳለኝ አላውቅም ነበር። የሕጉ መሰጠት ግን በውስጤ ቀድሞውኑም ቢሆን ተሸሽጎ ይኖር የነበረውን የሃጢአት መሻት ቀሰቀሰው (ሮሜ 7፡5)። ቢሆንም ይህን በውስጤ የተቀሰቀሰውን መሻት በመቃወም የሕጉን ትዕዛዝ ልፈጽም ሞከርኩ፤ ግን አልሆነም። ይበልጥ ጣርኩ፤ ግን አለተሳካም። አሁንም ያለኝን የፈቃድ ሃይል ሁሉ አሰባስቤ ልፈጽመውና እግዚአብሔርን ደስ ላሰኘው ጣርኩ፤ ሆኖም የማልወጣው ተራራ ሆነብኝ። አድርግ የሚለውን ለማድረግ፣ አታድርግ የሚለውን ደግሞ ላለማድረግ ሃይሌን ጥበቤን እውቄቴንና ፍላጎቴን አሟጥጬ ደግሜ ደጋግሜ ሞከርኩ፣ ውጤቱ ግን ተስፋ አስቆራጭ ነበር። እናም አንድ ነገር ተረዳሁ፣ ቀድሞ ያለ ሕግ ህያው የነበርኩትን ሕጉ ሃጢአተኛ አድርጎ በመክሰስ ሙት እንዳደረገኝ (ሮሜ 7፡9)።
ሕግ በስጋዬ ተሸሸጎ የነበረውን የሃጢአት መሻት ለመቀስቀስ አላማ ከተሰጠ ለእኔ ሞትን እንጂ ሕይወትን አልሰራም። እርግጥ ነው፣ ሕግ በራሱ ሞት አይደለም። ነገር ግን ሞትን በእኔ ሰርቷል። ለሕይወት የተሰጠችው ሕግ በእኔ ሞትን ሰርታለችና (7:10) የሕግ ፍሬ ሞት ነው። ሕግ በእኔ ውስጥ አለዝቦ የተኛውን አመጸኛ ማንነቴን ከእንቅልፉ ቀስቀሰ። በዚህም ምክንያት፣ ሕግ የሃጢአት መሻቴ ቀስቃሽ ደወል ሆነ። እንግዲያስ፣ ሕግ ሃጢአት ነውን? አይደለም። ነገር ግን ኀጢአት በኀጢአትነቱ ይታወቅ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር በኩል ሞትን አመጣብኝ (7:13)። ሃጢአት፣ ሃጢአት እንደሆነ ያወኩት በሕግ በኩል ነው። በሕግ ባይሆን ኖሮ የሃጢአት መሻቴን ሃጢአትነት ባላውቅሁም ነበር። በዚህ አለማወቄም በሃጢአተኝነት ባልተከሰስሁ ነበር። አሁን ግን ሕጉ የሃጢአት መሻቴን ህያው አደረግ፤ እኔንም በሃጢአተኝነት በመክሰስ እና በፍርድ ስር እንድሆን በማድረግ ሙት አደረገኝ።
ሃጢአት ያለ ሕግ ምውት ነው። ሃጢአትን ህያው የሚያደርገው ሕግ ነው። ሕጉ አትመኝ ባይል ኖሮ መመኘት ምን እንደሆነ ባላወቅሁም ነበር። ባለማወቄም ሃጢአት ባልሆነብኝ ነበር። ነገር ግን አሁን አትመኝ የሚለው ሕግ የምኞት ሃጢአትን በእኔ ውስጥ ሕያው አድርጎ ይህን ትዕዛዝ ለመፈጸም በማልችለው በእኔ ውስጥ የሞትን ፍሬ ሰራብኝ። ሕጉ ሳይኖር እኔ ሕያው ነበርኩ። ነገር ግን፣ ሕጉ ሕያው ሲሆን ሃጢአት ሕያው ሆነ፤ እኔም ሞትኩ።
ሃጢአት ያለ ሕግ ምውት ነው። ሃጢአት ያለ ሕግ ሃጢአት ሊባል አይችልም። ሃጢአት ከሌለ ሞት የለም። ሃጢአትን ህያው የሚያደርገው ሕግ ነው። ሃጢአት ደግሞ ሞትን ይሰራል። ሕግ ሃጢአትን፣ ሃጢአት ደግሞ ሞትን ሕያው ያደርጋል። ሕግ፣ የሃጢአት አባት የሞት ደግሞ አያትነው ብል አልተሳሳትኩም። ሕግ ለሃጢአት ሃይል ይሰጣል፤ ሃጢአትም ሞትን ይወልዳል። “የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤” (1ቆሮ. 15:56)። ያለ ሕግ፣ ሃጢአት ሃይል የለውም፤ ያለ ሃጢአት ደግሞ ሞት መውጊያ አይኖረውም። የሃጢአትም ሆነ ሞት እስትንፋስ ሕግ ነው። የሕግ እስትንፋስ በሌለበት ሃጢአትም ሆነ ሞት ህያዋን አይደሉምና። እናም ለሕይወት እንዲሆን የታሰበው ሕግ ሞትን አመጣብኝ።
ለምን በራሱ ሃጢአት ያልሆነው ሕግ ሃጢአትን ሰራብኝ፣ ለምንስ ቅዱስና ጻድቅ በጎም የሆነው ሕግ ለሞት ሆነብኝ? የሚለው ጥያቄ እዚህ ቦታ ላይ ሊነሳ የሚገባ ተገቢ ጥያቄ ነው። ታዲያ በጎ የሆነው ሕግ ሞት ሆነብኝን? ለሚለው ጥያቄ መልሱ “ከቶ አይደለም” የሚል ነው። ነገር ግን ኀጢአት በኀጢአትነቱ ይታወቅ ዘንድ በጎ በሆነው በሕጉ በኩል ሞትን አመጣብኝ። ቢሆንም ይህ ለመልካም ሆነልኝ ምክንያቱም ኀጢአት በትእዛዝ በኩል ይብሱን ኀጢአት መሆኑ የታወቅ ዘንድና በእኔ ውስጥ በስውር የሚሰራው የሃጢአት ስጋ ባህሪይ ትክክለኛ ማንነት ይታወቅ ዘንድ ጠቅሞኛል። ሕግ በትዕዛዝ በኩል ሞትን ቢያመጣብኝም፣ በውስጤ ተሸሽጎ የሞትን ፍሬ የሚያፈራውን የሃጢአት ስጋ ማንነት በማጋለጥ ረገድ ግን ጠቅሞኛል። ሕግ ይህንን ማንነቴን እንዳውቅ በመርዳቱም ይህን ሃጢአት “የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚያድር ኃጢአት ነው እንጂ”፣ እንድል እውቀትን ሰጥቶኛል። ሕግ በእኔ ውስጥ ሁለት ተቃራኒ ተፈጥሮዎች እንዳሉና አንዱ በሌላው ላይ እንደሚመኝ እኔም ምንም ላደርግ የማልችል አቅም ቢስ ፍጥረት እንደሆንኩ እውቀት ሰጥቶኛል። ይህ እውቀት በእርግጥ ታላቅ እውቀት ነው! ይህ ምን ማለት እንደሆነ አብረን እንመልከት።
በሮሜ 7 ላይ የተጠቀሱ ሁለት እኔዎች በአንድ ሰው ውስጥ የሚኖሩ ጽንፈኞች ናቸው (ሮሜ 7፡20)። አንደኛው “እኔ” ስጋችን (አሮጌው ተፈጥሯችን) ሲሆን ሌላኛው “እኔ” ደግሞ በክርስቶስ ዳግመኛ የተፈጠረው አዲሱ ሰው ነው። በሮሜ 7:14-20 የሚጮኸው ጩኸት፣ የሚጠላውን የሚያደርግ፣ ማድረግ የሚፈልገውን ደግሞ ለማድረግ አቅም የሌለው ሰው የጣር ጩኸት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ልምምድ ውስጥ ሲያልፍ የተማረውን ድንቅ መገለጥ አካፍሎናል። የማይፈልገውን የሚያደርገውና የሚፈልገውን ለማድረግ የማይችለው እርሱ ሳይሆን በእርሱ ውስጥ ያለው አሮጌ ተፈጥሮ እንደሆነ ነግሮናል። ይህ ተፈጥሮ የሃጢአት ባሪያ ስለሆነ የሕግን ፍላጎት ሊያሟል አይችልም። በዚህ ተፈጥሮ ውስጥ ምንም መልካም ነገር የለም (ሮሜ 7፡18)። ቢኖርም እንኳ መልካሙን የማድረግ ፈቃድ ብቻ ነው። በአሮጌው ተፈጥሮ ውስጥ ያለው ይህ ፈቃድ የማድረግ ነጻነት የሌለው የሃጢአት ባሪያ ነው። እናም መልካሙን ማድረግ አይችልም (ሮሜ 7፡18)። ይህ ተፈጥሮ (ስጋዬ) የማልወደውን ክፉ ነገር በእኔ ውስጥ ሆኖ ያደርጋል፤ ተምወደውን በጎ ነግር ግን አያደርግም (ሮሜ 7፡19)። እንግዳውስ፣ “ላደርገው የማልፈልገውን ነገር የማደርገው ከሆነ፣ ያን የማደርገው እኔ ራሴ ሳልሆን፣ የሚያደርገው በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኀጢአት ነው” (7፡20)። ከአዲሱ ልደቴ በኋላ፣ እኔ እያልኩ የምጠራው ዋነኛ ማንነቴ አዲሱ ሰውን (መንፈሴን) ነው። ይህ እኔ (መንፈሴ) የሚፈልገውን፣ ያኛው እኔ (ስጋዬ) አይፈልገውም። መንፈሴ ያማይፈልገውን ደግሞ ስጋዬ ይፈልገዋል። በውስጡ ሰውነቴ (በመንፈሴ) በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛል። ነገር ግን ከዚህ ፍላጎቴ ጋር የሚዋጋ ሌላ ሕግ (የሃጢአት ሕግ) በብልቶቼ ውስጥ ሲሠራ አያለሁ (ስጋዬ)። በመንፈሴ በጎ ነገር ለመሥራት ስፈልግ፣ በስጋዬ ክፋት ከእኔ ጋር ይኖራል። አንዱ እኔነቴ (መንፈሴ) በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ሲሰኝ ሌላው እኔነቴ (ስጋዬ) ደግሞ በሃጢአት ሕግ ደስ ይሰኛል፡፡ በአንዱ ሰውነቴ ውስጥ ለሁለት ባላንጣ ሕጎች (ለእግዚአብሔር ሕግ እና ለሃጢአት ሕግ) የምገዛ ምስኪን ሰው ነኝ። አሮጌው ማንነቴ (ስጋዬ) የሃጢአት ባሪያ ሲያደርገኝ፣ መንፈሴ (አይምሮዬ) ደግሞ የእግዚአብሔር ሕግ ባሪያ አድርጎኛል (7:25)። ለሁለት ብርቱ ጌቶች የምገዛ ምስኪን ባሪያ ነኝ። ምንኛ በስቃይ የምንገላታ ሰው ነኝ! ምንኛስ ጎስቋል ሰው ነኝ! ማን ከዚህ ሰውነት (ስጋ) ሊለየኝ ይችላል?
ይህ ጦርነት አማኝ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ የሚያስተናግደው እውን ጦርነት ቢሆንም የቅርብና የሩቅ የድል ብስራቶች የተበጀለት ጦርነትም መሆኑን አሳስቤ ጽሁፌን ልደምድም። ጳውሎስ ይህን አስመራሪ ጦረነት የዘጋበት ጥቅስ እንዲህ ይላል፦ “በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እንግዲያስ እኔ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ፥ በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ እገዛለሁ።” ይህ ጥቅስ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም የሚለውን የኢየሱስን ትምህርት ያስታውሰኛል (ዮሐ. 15:5፤ ገላ 5፡17)። በመንፈሳችን በኩል ባሪያ የሆንለትን የእግዚአብሔር ፈቃድ (ሕግ) ልንፈጽም የምንችለው እንደ መንፈስ ፈቃድ ስንመላለስ ብቻ እነደሆነ ቃሉ ይነግረናል (ገላ 5፡16)። ጳውሎስ አያይዞም “እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕዳ አለብን፥ እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም። እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ” (ሮሜ 8፡13) ብሎ ይመክረናል። የዚህ ጦርነት ድል መንሻችን መንፈስ ቅዱስ ብቻ እንደሆነ ከነዚህ ጥቅሶች መረዳት እንችላለን። ጥረታችን፣ የጥቅስ ብዛት እውቀታችን፣ ጥበባችን፣ ጥንቃቄያችን፣ ሃይማኖታዊ ስርዓቶቻችን፣ ውሳኔዎቻችን፣ የፈቃድ ጉልበታችን፣ ወዘተ፣ በመንፈሳዊ ጉዞአችን የራሳቸው የሆነ ፋይዳ ሊኖራቸው ቢችልም በዚህ ጦርነት ውስጥ ግን ቅንጣት ያህል አይጠቅሙንም። ይህ ጦርነት ከእኛ አቅም በላይ ነው። ጦርነቱ ረቂቅና መንፈሳዊ ብሎም የሁለት ሃያላን ሕጎች ጦርነት ነው። በዚህ ጦርነት ውስጥ ብቸኛው ፍቱን መሳሪያችን በመንፈስ ቅዱስ ላይ ሙሉ በሙሉ ማረፋችን (መታመናችን) ብቻ ነው። በእርሱ ላይ ለማረፍ መጀመሪያ የእኛን ጥይት መጨረስ ይኖርብናል። በእግዚአብሔር መንፈስ ላይ ማረፍ እንደምናወራው ለተፈጥሯችን ቀላል ጉዳይ አይደለም። በእግዚአብሔር መንፈስ ላይ ለማረፍ የሚችል በራሱ አቅም ላይ ተስፋ የቆረጠና ምስኪን ፍጥረት መሆኑን የተገነዘበ ሰው ብቻ ነው (ሮሜ 7፡18)። ለእግዚአብሔር መንፈስ የሚማረክ ሰው በጦር ሜዳው ላይ የራሱን አቅም አሟጦ የሞከረና ሙከራው እንዳልተሳካለት የተገነዘበ ሰው ብቻ ነው። እንደ መንፈስ ቅዱስ ሃሳብና ፈቃድ ለመሄድ የወሰነ ሰው መጀመሪያ የዚህ ጦርነት ቁስለኛና የጦርነቱ አስከፊ ከጽታ ገፈት ቀማሽ የሆነ ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ያለው በመንፈስ ቅዱስ ላይ የመደገፍ እውቀት የአይምሮ ጉዳይ እንጂ የልምምድ ወይም የአብርሆት ጉዳይ አይደለም።
ጸሃፊ፣ አዳነው ዲሮ ዳባ