የሰው ማንነት

ሰው መንፈስ፣ ነፍስና ስጋ (አካል) እንዲኖረው ሆኖ በእግዚአብሔር የተፈጠረ ልይ ፍጡር ነው፡፡ (ዘፍጥረት 1፡27፣ 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡23)፡፡ ስጋችን ማለትም “የውጭው ሰው”፣ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ አካላዊ መኖሪያችን ነው፡፡ ስጋችን ለመብላት፣ ለመጠጣትና ለመተኛት የሚያስችሉ ውስጣዊ ፍላጎቶችን በማሟላት በዋናነት በአምስቱ የስሜት ሕዋሳት አማካኝነት ይሰራል፡፡ ስጋችን በራሱ ክፉ አይደለም፤ ከእግዚአብሔር በስጦታ የተቀበልነው መልካም ስጦታ እንጂ፡፡ ይህን ስጋችንን (ብልቶቻችንን) ለእግዚአብሔር ሕያው መስዋዕት አድርገን እንድናቀርብ መጽሐፍ ቅዱስ ይመክረናል (ሮሜ 12፡1-2)፡፡ በክርስቶስ በኩል የእግዚአብሔርን የድነት ስጦታ ስንቀበል፣ አካላቻችን (ስጋችን) የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ይሆናል (1ኛ ቆሮንቶስ 6:19-20፣ 3:16)፡፡.

ነፍሳችን ደግሞ አእምሯችን (ዕውቀታችን)፣ ፈቃዳችን እና ስሜታችን የሚገለጡበት የስብዕናችን ማዕከል ነው፡፡. የራሳችንን ሥጋዊ ፍላጎቶች ወይም የመንፈስ ቅዱስን ምኞቶች ለማዳመጥ እና ለመታዘዝ ምርጫችንን የምናደርገው በነፍሳችን አማካኝነት ነው (ገላ 5:16-17፣ ሮሜ 8 9፣ ማርቆስ 14፡38)፡፡ ነፍሳችን የሕይወታችን ውሳኔዎች የሚደረጉበት የፍርድ ቤት ነው፡፡ ነፍሳችን የማንነታችን (የእኔነታችን) መቀመጫ ስፍራ እና የተለያዩ ባሕሪያቶቻችን ምንጭም ነው፡፡

መንፈሳችን፣ የውስጡ ሰውነታችን ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ የሚናገረውም ለውስጡ ሰውነታችን ነው፡፡ እኛም ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ትክክለኛ እና እውነተኛ አምልኮ የሚመነጨውም ከዚሁ ማንነታችን ውስጥ ነው፡፡ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” (ዮሐንስ 4፡24)፡፡ ጳውሎስ በመልዕክቶቹ “የውስጥ ሰውነት” የሚለውን ሃረግ በተደጋጋሚ ተጠቅሟል (2ኛ ቆሮንቶስ 4፡6፣ ኤፌሶን 3:16)፡፡ ሮሜ 7 22-23 እንዲህ ይላል፣ “በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፥ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ”፡፡ “ውስጣዊው ሰው” የሚለው ሃረግ መንፈሳዊውን የሰው ገጽታ የሚገልጽ ሲሆን “ውጫዊው ሰው” የሚለው ደግሞ በገሃድ የሚታየውን የሰው ገጽታ ያመለክታል፡፡

ዳግም ልደት ያገኘነው በመንፈሳችን ነው (ዮሐንስ 3፡3-6)፡፡ ይህ “ውስጣዊው ሰው”፣ መንፈስ ቅዱስ ስለ ኃጢአት ሊወቅሰው የሚያስችለውን ሕሊና ይዟል (ዮሐ 16:8፣ ሐዋርያት ሥራ 24:16)፡፡ መንፈሳችን፣ መልካምንና ክፉን የመለየት ማንነት ያለው እና እግዚአብሔርን የምንመስልበት መልካችን ነው (ሮሜ 2፡14-15)፡፡ 1ኛ ቆሮንቶስ 2:11 እንዲህ ይላል፣ “በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም”፡፡

2 thoughts on “የሰው ማንነት”

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading