በአእምሮአችሁ (በልባችሁ) መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ (ሮሜ 12፡2)

በአእምሮ መታደስ መለወጥ ማለት በውጫዊ የባሕሪይ ለውጥ የክርስትና ሕይወታችንን መጀመር ማለት አይደለም፡፡ እውነተኛ ለውጥ ከውስጥ ይጀምራል፡፡ እውነተኛ የባሕሪይ ተሃድሶ፣ ከአእምሮ መለወጥ (መታደስ) ላይ በቅሉ ወደውጭ የሚንዝዥረግ ፍሬ ነው፡፡ ስሩ የአእምሮ መለወጥ ሲሆን ፍሬው ደግሞ ባሕሪይ ነው፡፡ የማንኛውም ተክል ፍሬ ከስሩ ቀድሞ እንደማይመጣ ሁሉ ሰናይ ባሕሪይም ከአእምሮ መታደስ (መለወጥ) ቀድሞ ሊመጣ አይችልም፡፡ ቢመጣም እርባና ቢስ የሆነ ግብዝነት ወይም አስመሳይነት የተሞላው ሃሰተኛ ፍሬ (artificial fruit) ነው፡፡ በዚህ “ፍሬ” እግዚአብሔር አይከብርም!

በርካታ ሰዎች ክርስቲያናዊ ሕይወት ስለ ውጪያዊ ክርስቲያናዊ ባሕሪ ብቻ እንደሚያወራ ያስባሉ፡፡ ነገር ግን፣ የአንድ ሰው ባሕሪ (characters) የአስተሳሰቡ (thought process) እና የፅኑ እምነቱ (convictions) ድምር ውጤት በመሆኑ ክርስቲያናዊ ሕይወት ሊመዘን የሚገባው ግለሰቡ በውጭ በሚገለጠው ባሕሪ ብቻ ሳይሆን በልቡ ዝንባሌም ጭምር መሆን ይኖርበታል፡፡

ከላይ እንደተገለጽው፣ ባሕሪ ውጫው ሲሆን የልብ ዝንባሌ ደግሞ ውስጣዊ ነው፡፡ ባሕሪ፣ የልብ ዝንባሌን ሊገልጥ የሚችል የሰው ውጫዊ መልክ ቢሆንም ሁል ጊዜ የሰውየውን እውነተኛ የልብ ዝንባሌ ላይወክል መቻሉን ልብ እንበል፡፡ ለአብነት፣ የትሁት ባህሪይ ውጪያዊ መገለጫዎችን ተላብሰን የልብ ዝንባሌያችን ትሁት ላይሆን ይችላል፡፡ ገንዘብ እየለገስን ቸርነት የተሞላው የልብ ዝንባሌ ላይኖረን ይችላል፡፡ መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችን ሞልቶ፣ በውጭ የሰላም ሰው መምሰል እንችላለን፡፡ ከአንዱ አፋችን በረከትና መርገም ማውጣት መቻላችን የእነዚህ አስመሳይ ችሎታዎቻችን ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ስለዚህ፣ በውጪ ተገልጦ የሚታየው ባሕሪያችን እውነተኛ የሆነው የልባችን ዝንባሌ ማሳያ ላይሆን ይችላል (ማቴ 23፡28፣ ሉቃ 11፡39)፡፡ የተገለጠው ባሕሪይ የልባችን ዝንባሌ እውነተኛ መገለጫ ሊሆንም ላይሆንም የሚችል መሆኑ እንደተሰመረበት ሆኖ የልባችን ዝንባሌ ማሳያ መስተዋት መሆኑ ግን ጥያቄ ውስጥ አይወድቅም፡፡

ዛፍ በፍሬው እንደሚታወቅ፣ ልባችን በባህሪያችን ተገልጦ ይታያል፡፡ከእሾህ በለስ፣ ከአጣጥ ቍጥቋጦም ወይን እንደማይቆረጥ ሁሉ ከትእቢት ልብ ትህትና፣ ከስስታም ዝንባሌም ቸርነት አይሸመጠጥም፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ በመልዕክቱ ይህን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን? ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም ጣፋጭ ውኃ አይወጣም” ያዕ 3፡-12፡፡ ጌታችን እና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ በወንጌሉ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል” ሉቃ 6፡45፡፡ እዚህ ላይ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባን ነገር ቢኖር፣ የልባችን ዝንባሌ ያለሆነውን ባሕሪ ማስመሰል የምንችል በመሆናችን፣ በላያችን ላይ ተገልጦ የሚታየው ባሕሪ በስውር ያለው የልባችን ዝንባሌ እውነተኛ መገለጫ መሆኑን ማጣራት ክርስቶስን ወደ መምሰል ለማደግ ለምናድረገው ደቀ መዝሙራዊ ጉዞ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም፡፡

ውጫችን የውስጣችን ነጸብራቅ ስለሆነ፣ ሕይወታችንን በውጫዊ ባህሪይ መመዘኛ ላይ ብቻ በመደገፍ መመዘን፣ ምዘናውን ሙሉ አያደርገውም፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ክርስቲያን ሁል ጊዜ ትኩረት ሊያደርግ የሚገባው ከውጭ በሚጀመር የባሕሪይ ለውጥ ላይ ሳይሆን ከውስጥ በአስተሳሰብ (በአእምሮ ዝንባሌ) ለውጥ ጀምሮ ወደውጪ በሚፈስ ለውጥ ላይ መሆን አለበት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ 12 ላይ የሚለውም ይህንኑ ነው፡፡

አእምሮ ለክርስትያን ሕይወት ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ በሰይጣን አይዞህ ባይነት፣ ከእግዚአብሔር ግብረገባዊ መርዎች በተቃራኒው በመሆን በእግዚአብሔር ሃሳብ ላይ በጠላትነት የተሰለፈውን የዓለም አስተሳስብ የመቃወሚያ ብቸኛው መንገድ ይህን አስተሳሰብ በእግዚአብሔር እውነት ማፍረስ ብቻ ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሔር እውነት ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጦ ያለው ፍጹም ፈቃዱ ነው፡፡ አማኞች በግል፣ በአነስተኛ ቡድንና በሕብረት በመሆን የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት ከመትጋት ውጪ ይህን ከአለም ያለማቋረጥ ወደአእምሮአቸው የሚትኮሱትን ተንበልባይ ፍላጻዎች ለመመከት ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቃሉን በመስበክ፣ ቃሉን በማጥናት፣ ቃሉን በመዘመር ልትተጋ ይገባታል፡፡ በአእምሮ ለመታደስ ሌላ ምንም አይነት አቋራጭ መንገድ የለም፡፡ መንገዱ አንድ ብቻ ነው፤ ያም ቃሉን ማጥናት፡፡ ቃሉ በሙላት ሊኖርብን ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን እውነት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ይቀድሰናል፣ ሰናይ ባህሪንም ያለብሰናል (ዮሐንስ 17፡17)፡፡

2 thoughts on “በአእምሮአችሁ (በልባችሁ) መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ (ሮሜ 12፡2)”

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading