“ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለም…” ሮሜ 13፡1

ከምድራዊ ነገስታት ወይም ገዢዎች ጋር በተያያዘ ክርስቲያኖች በተደጋጋሚ ከሚጠይቋቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱና ዋነኛው፣ “እግዚአብሔር የአገር መሪዎችን ይሾማል ወይ?” የሚለው ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ 600 ዓመታት በፊት በባቢሎናውያን ግዛት ላይ ነግሶ የነበረው ናቡከደነፆር ከእግዚአብሔር ሕልምን አልሞ እንደነበር እና የሕልሙንም ፍቺ ነቢዩ ዳንኤል እንደሰጠው በትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ እናነባለን፡፡ ይህም የሆነው ደግሞ፣ “ልዑሉ (እግዚአብሔር) በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለወደደውም እንዲሰጠው፥ ከሰውም የተዋረደውን እንዲሾምበት ሕያዋን ያውቁ ዘንድ” እንደሆነም በትንቢቱ መጽሐፉ ላይ ተገልጿል (ዳን 4፡17)፡፡

በርካታ ቁጥር ባላቸው የአለማችን አገራት ውስጥ ያሉ ሕዝቦች የሕግ የበላይነትን በማይቀበሉ መሪዎች ምክንያት ስቃይና መከራ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ለማንም እንግዳ ጉዳይ አይደለም፡፡ ያም ሆኖ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ዘላለማዊ እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ እንደነዚህ አይነቶቹን ጨቃኝ ነገስታት ጭምር ሳይቀር ሊጠቀማቸው እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ምንም እንኳን፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በልቡ ያለው መልካም ፈቃድ፣ “ሰዎችን በጽድቅ የሚገዛ፣ በፈሪሀ እግዚአብሔርም የሚያስተዳድር” መሪ እንዲሆንላቸው ቢሆንም (2ሳሙ 23፡3)፣ አንዳንዳንዴ በራሱ ህዝብ ላይ ሳይቀር ጨቃኝ መሪዎች እንዲነግሱ ሊፈቅድ ይችላል፡፡ በእግዚአብሔር ስልጣን እንደተቀበለ የተነገረለትን ንጉስ ናቡከደነፆርን ብቻ እንኳን ለአብነት ብናነሳ የዚህ ዓረፍተ ነገር እውነትነት ግልጽ ይሆንልናል፡፡ ናቡከደነፆር ጥሩ ሰው አልነበረም፡፡ ላሰራው ምስል ሰዎች ካልሰገዱ ተቃዋሚዎቹን ወደ እቶን እሳት ለመጨመር የማያቅማማ ንጉስ ነበር፡፡ ያለመውን ሕልም ካልፈቱለት በቀር የራሱን ሹማምንት ሳይቀር በጅምላ ለመጨፍጨፍ የዛተ ሰውም ነበር፡፡ ሌላው ምሳሌያችን ደግሞ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተነሳው ፈርኦን ነው፡፡ “ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነሥቼሃለሁ” (ዘጸ 9፡16)፣ የተባለለት ይህ የግብጽ ንጉስ ጭምር ሳይቀር ከነዚህ ጨካኝ ነገስታት ጎራ እንደሚመደብ የእስራኤላውያንን የባርነት ታሪክ ያነበበ ሰው ሁሉ የሚስማማበት ጉዳይ ነው፡፡

እግዚአብሔር በንጉስ ቂሮስ ላይ እንዳደረገው፣ የእርሱን ዘላለማዊ እቅድ ለማስፈጽም ሰዎችን ወደ ከፍተኛ ስልጣን ከረጅም ዘመናት በፊት አስቀድሞ ሊጠራ ይችላል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ቂሮስ በፋርስ ግዛት ላይ መንገስ አስመልክቶ የተናገረው ይህ ትንቢት ፍጻሜ ያገኘው ከአንድ ምዕተ-አመት ተኩል በኋላ እንደነበር ያስተውሉ፡፡ የስልጣን ምንጭን በተመለከተ ነቢዩ ዳንኤል እና ሐዋሪያው ጳውሎስ የተናገሩትን እንመልከት፦ “ጥበብና ኀይል የእርሱ ነውና፣ የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ። ጊዜንና ወቅትን ይለውጣል፤ ነገሥታትን በዙፋን ያስቀምጣል፣ ደግሞም ያወርዳቸዋል” (ዳን 2፡20-21 አ.መ.ት.)፡፡ “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው” (ሮሜ 13፡1)፡፡ (ዮሐ 19፡10-11 ጨምረው ያንብቡ)፡፡

ይህ ማለት ግን፣ እግዚአብሔር የጨቃኝ እና ሕግ አልባ ሹማምንትን ክፉ ተግባራት ይደግፋል (ያጽድቃል) ማለት እንዳልሆነ ልብ ይበሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ስልጣን እንዲመጡ መፍቀድ እና ሹመታቸውን ወይም ተግባሮቻቸውን ማጽደቅ ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ የክፉዎቹም ይሁን የጽድቃን ነገስታት ንግስና ከእግዚአብሔር ዘንድ መሆኑ ግልጽ ነው “ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና” (ሮሜ 13፡1)፡፡ ክፉዎቹ ነገስታት በእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ ወደስልጣን ሲመጡ መልካሞቹ ነገስታት ግን በእግዚአብሔር ፈቃድና ባርኮት ጭምር ለሕዝብ ይሰጣሉ፡፡ “ጻድቃን ሥልጣን ሲይዙ ሕዝብ ሐሤት ያደርጋል፤ ክፉዎች ሲገዙ ግን ሕዝብ ያቃስታል” (ምሳሌ 29፡2 አ.መ.ት.)፡፡ ያለ እግዚአብሔር ባርኮት ወደ ስልጣን ሊመጡ ስለሚችሉ ነገስታት ሆሴዕ እንዲህ ሲል ተናግሯል፣ “ለራሳቸው ነገሥታትን አነገሡ፥ ከእኔም ዘንድ አይደለም፤ አለቆችንም አደረጉ፥ እኔም አላወቅሁም” (ሆሴ 8፡4)፡፡ ነገስታቱ ከእግዚአብሔር ዘንድ አለመሆናቸው የሚያሳየው ስልጣን ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ማግኘታቸውን ሳይሆን ተግባሮቻቸው በእግዚአብሔር ዘንድ አጸያፊ መሆናቸውን ነው፡፡ የመልካሞቹ ነገስታት ሹመት ለሕዝብ እረፍት የክፉዎቹ ደግሞ ሃዘንና ጭንቀት ቢሆንም ከእግዚአብሔር ዘላለማዊ እቅድ አንጽር ፈርኦንን “ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነሥቼሃለሁ” (ዘጸ 9፡16)” እንዳለው ሁሉ፣ እግዚአብሔር ሁለቱንም ጥቅም ላይ ሊያውል ይችላል፡፡

ሌላው ልብ ልንለው የሚገባው ነገር፣ ምንም እንኳ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን ዘላለማዊ ዕቅዱን ለመፈጸም፣ የክፉ ሰዎችን ሹመት ሳይቀር ቢፈቅድም በሕዝባቸው ላይ የሚፈጽሙትን ግፍና መከራ ግን ከቶ አያጽድቅም፡፡ የክፉ ተግባሮቻቸው ምክንያት ተደርጎ ሊታይም አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ናቡከደነጾር እና ፈርኦን የመሳሰሉ ጨካኝ መሪዎችን ወደ ስልጣን እንዲመጡ በመፍቀድ ዛላለማዊ እቅዱን ሊፈጽም የሚችል ሉአላዊ አምላክ ቢሆንም ለሚፈጽሟቸው ተግባራት ተጠያቂዎቹ ግን ራሳቸው ናቸው፡፡ እግዚአብሔር እነዚህ ክፉ መሪዎች ወደስልጣን እንዲመጡ መፍቀዱ የተግባሮቻቸው አንሳሽ ወይም ምክንያት እንዲሆን አያደርገውምና፡፡

ከዚሀ በተቃራኒው ደግሞ እግዚአብሔር መልካም የሆነውን የእርሱን ፈቃድ በማድረግ ለእርሱ ክብር እና ለሕዝባቸው ደግሞ ሰላምና ብልጽግን የሚያመጡ መሪዎችን ወደስልጣን እንዲመጡ ብቻ ሳይሆን የእርሱን ይሁንታም (ባርኮት) እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ ይህ አይነቱ ስልጣን፣ የእግዚአብሔርን ሉአላዊ ፈቃድ ባቻ ሳይሆን ሹመትንም ጭምር ያመለክታል፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድና ይሁንታ (ባርኮት) የመጡ መሪዎች ለእግዚአብሔር ክብር ለሰው ልጆችም ሰላም ናቸው፡፡ እንደነዚህ አይነት ሹማምንት በአገር ላይ እንዲነግሱ እና ሕዝብ ሁሉ “በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወትና በቅድስና ሁሉ፣ በሰላምና በጸጥታ እንዲኖር፣ ልመናና ጸሎት፣ ምልጃና ምስጋና ለሰዎች ሁሉ፣ ለነገሥታትና ለባለ ሥልጣናት ሁሉ እንዲደረግ” ጳውሎስ ያሳስባል (1ጢሞ 2፡1-2)፡፡

እግዚአብሔር መሪዎቻችንን ይባርክ!!!

Leave a Reply

%d