ይህ ጥያቄ የዚህ ድረገጽ ተከታታይ በሆነ አንድ ግለሰብ ለዝግጅት ክፍላችን የቀረበ ቢሆንም ምላሹን ሁሉም አንባቢ ቢያገኘው ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘነው እነሆ፡
ውድ ወንድሜ፣ አስቀድሜ ጥያቄውን ለዝግጅት ክፍላችን ስለላክህ እናመሰግናለን፡፡ ከሃጢአት ጋር የሚደረግ ትግል የክርስቲያኖች ሁሉ ጤናማ ሕይወት መገለጫ ነው። ትግል የሚፈጠረው ጦረነት ሲኖር ነው። ጦርነት የሚኖረው ደግሞ ቢያንስ ሁለት ተቃራኒ ነገሮች ሲኖሩ ነው። ከሃጢአት ለመዳን የሚደረግ ትግል በአንድ ጎኑ እልህ አስጨራሽና አድካሚ፣ አንዳንዴም ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም በሌላ ጎኑ ደግሞ የመዳናችን አመላካች ጭምር መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ጌታን ያልተቀበሉ ሰዎች ሃጢአትን በተመለከት መጠነኛ የህሊና ትግል ቢኖርባቸውም ክርስቲያኖች እንዳላቸው አይነት የመረረ ጠብ ከሃጢአት ጋር ሊኖራቸው አይችልም።
ጌታን ስንቀበል ሃጢአትን እንቢ የሚል አዲስ ተፈጥሮን አብረን እንቀበላለን (2ቆሮ. 5:17)። ይሕ ተፈጥሮ ነው እንግዲህ ሃጢአትን ላለማድረግ እንቢ የሚለው። ሆኖም በውስጣችን የዚህ ተቃራኒ የሆነ ሌላ ተፈጥሮ ደግሞ ይገኛል (አሮጌው ሰው/ስጋ) እየተባለ የሚጠራው ማለት ነው (ሮሜ 8:8)። እስከ እለተ ሞታችን እነዚህ ሁለት ተቃራኒ ተፈጥሮዎች በውስጣችን ያለማያቋርጥ ጦርነት ያደርጋሉ (ገላቲያ 5:17)። በራሳችን የፈቃድ ሃይል ላይ በመመስረት በነዚህ ተፈጥሮዎች መካከል ያለውን ጦርነት ማሸነፍ አንችልም (ገላቲያ 5:17-18)። ጦርነቱ ከተፈጥሮ አቅማችን በላይ ነው (ሮሜ 7:15)። ነገር ግን ይህንን እውነት አምነን ለመቀበል ብዙ ጊዜ ይፈጅብናል። እናም በራሳችን ሃይል፣ በራሳችን ጸሎት፣ በራሳችን ጾም፣ ራሳችንን ከክፉ ቦታዎች በመጠበቅ፣ ቃሉን ይበልጥ በማንበብ፣ ቆራጥ ውሳኔ በመወሰን፣ል ጓዋደኞች በመቀየር፣ የተለያዩ ውጪያዊ ለውጦችን በማድረግ፣ ወዘተ…ሃጢአትን ለማሸነፍ እንሞክራለን። የጠቀስኳቸው ነገሮች ሁሉ ከሃጢአት ጋር ለምናደርገው ትግል ጠቃሚ መንፈሳዊ ነገሮች መሆናቸውን እየካድኩ ሳይሆን፣ እነዚህ ነገሮች በሃጢአት ላይ ድልን ከተቀዳጀን በኋላ ድሉን ለማስቀጠል ያሚረዱን እንጂ በራሳቸው ድሉን የምንቀዳጅባቸው መሳሪያዎች አለመሆናቸውን ለመግለጽ ነው። ቢሆኑ ኖሮ እነዚህን ሁሉ የሚያደርጉ የሃጢአት ትግል ጥያቄዎች ባልኖሩባቸው ነበር። እውነታው ግን ያ አይደለም። ከሃጢአት ትግልህ ለመውጣት እንደክርስቲያን እነዚህን ሁሉ ለማድረግ እንደምትጥር ተስፋ አደርጋለሁ። ጥረቱ በራሱ መልካም ቢሆንም ዋነኛ መፍትሄ ግን አይደለም።
ከሃጢአት ባርነት ነጻ የምንወጣው በጥረት ሳይሆን በክርስቶስ ስራ ላይ በማረፍ ብቻ ነው (ዮሐ. 8:36)። “በክርስቶስ ስራ ላይ ማረፍ ምን ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ ማንሳትህ አይቀርም። መልሴ ሁለት ዘርፍ ይኖረዋል። አንደኛው በክርስቶስ ስራ ከሃጢአት ባርነት ነጻ መሆንህን ማወቅ ሲሆን (ሮሜ 6:6) ሁለተኛውና ዋነኛው ደግሞ የዚህን እውቀት ልምምድ (experiential knowledge) መገለጥ ማግኘት ነው። ተግባራዊ እውቀት ጊዜ የሚጠይቅና እግዚአብሔር በወደደው ጊዜ የሚያበራልን አብርሆት ነው። የልብ አይኖች መብራት የምንለው ማለት ነው (ኤፌ. 1:18-19)። ይህ ጊዜ እስኪመጣ፣ የእኛ ድርሻ በተስፋና በእምነት እግዚአብሔርን መጠበቅ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህን ድል በማረፍና በመጠበቅ፣ በጸጥታና በመታመን የሚገኝ ድል ብለህ ልትጠራው ትችላለህ (ኢሳ. 30:15)።
እስራኤላውያን የፈርኦን ሰራዊት ሊያጠፋቸው የኤርትራን ባሕር በመሻገር ላይ ሳለ ሊያደርጉት የሚችሉት ምንም ነገር አልነበረም። የፈርኦን ሰራዊ ከአቅማቸው በላይ ነውና። ይህን ግዙፍ ጦር ተዋግተውም ሆነ ሸሸተውት ማምለጥ አይችሉም። ከሃጢአት ጋር የምናደርገው ውጊያም እንዲሁ አይነት ነው። ጦርነቱን በራሳችን ሸሽተነውም ሆነ ተጋፍጠነው ማሸነፍ አንችልም። የፈርኦን ሰራዊት ከእስራኤል አቅም በላይ እንደሆነ ሁሉ የሃጢአት ሃይልም ከእኛ አቅም በላይ ነው። ነገር ግን ይህን እውነት ማስተዋል ለብዙዎቻችን አዳጋች ነው። ከዚህ እውነታ ጋር በእውቀት ደረጃ እንስማማ ይሆናል። ነገር ግን ለልባችን የበራ የአብርሆት እውቀት ወይም ልምምድ ላይሆን ይችላል። እናም ከአይምሮአችን ወደ ልባችን ያልወረደው እውቀት ከሃጢአት ጋር ለሚኖረን ግብግብ መፍትሄ ሲሆነን አናገኘውም። በዚህም ምክንያት በሃጢአት ስንወድቅ፣ ተመልሰን ልንገጥመው እንነሳለን፣ ደግመን ስንወድቅ እንደገና በቆራጥ ውሳኔ ልንገጥመው እንነሳለን፣ ያም አልሆን ሲል ጾምና ጸሎት አክለንበት ልንገጥመው እንፎክራለን። እዚህ ላይ ያልተረዳነው ነገር ቢኖር፣ እኛ ልንገጥመው እስከወሰንን ድረስ ተሸናፊዎች መሆናችንን ነው። ይህን አስፈሪ ጦር ገጥሞ ሊያሸንፈው የሚችለው የጌታ መንፈስ ብቻ ነው (ሮሜ 8:13)። እስራኤላውያን ለገጠማቸው ችግር ሙሴ የሰጣቸውን መፍትሄ “…ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ”፣ የሚል ነበር ( ዘጸ.14፥13)። ድሉ የእግዚአብሔር ነው፣ የእኛ ድርሻ ከእርሱ ጋር መሰለፍ፣ በእርሱ ላይ መተማመን እና እርሱን ተስፋ ማድረግ ነው። እነዚህን ነገሮች ማድርግ በራሳችን እርምጃ ከመውሰድ አንጻር ሲቃኙ ለተፈጥሯችን እጅግ ከባዶች ናቸው። ጦርነቱን በራሳችን ለማሸነፍ ምን ያህል ተስፋ ቢሶች እንደሆንን ለማወቅ ዘመናት ይወስድብናል። ጦርነቱ መንፈሳዊ ስለሆነ ጎስቋሎች መሆናችንን ለመወቅና ለመቀበል ረጅም ጊዜ ይወስድብናል። ከሃጢአት ጋር የምናደርገውን ጦርነት በድል ለመወጣት ዋነኛውና ቁልፉ ጉዳይ ጦርነቱን በራሳችን ለመግጠም የማንችል፣ ተስፋ ቢሶችና ጎስቋሎች መሆናችንን ጠንቅቆ ማወቅ ነው (ሮሜ 7:24)። በራሱ ተስፋ የቆረጠ ክርስቲያን፣ ከሃጢአት ጋር ላለበት ጦረነት እግዚአብሔር ላይ መደገፍ ምርጫው ሳይሆን ግዴታው እንደሆነ የተረዳ ነው። እግዚአብሔር አጋዡ ሳይሆን ዋነኛው ተዋናይ እንደሆነ ያውቃል። ተዋጊውም እርሱ ሳይሆን እግዚአብሔር እንደሆነ ያምናል። በእርሱም ላይ ብቻ ተስፋ ያደርጋል። ይህም ድልን ያመጣለታል።
ያም ቢሆን ግን፣ አማኝ በዚህ ምድር ላይ ሲኖር ፍጹም ያለሃጢአት ሊኖር አይችልም (1ዮሐ 1፡8)። ያ የሚሆነው በክርስቶስ ዳግም ምጽአት አዲሱን ማንነታችንን ሙሉ በሙሉ በምንለብስበት ወቅት ነው። በዚህ ምድር ቆይታችን የተሰጠን ተስፋ በሃጢአት ጸንተን ላለመኖር እንቢ የምንልበት የመንፈስ አቅም እንደተሰጠን ነው። ሆኖም ግን አልፎ አልፎ ይህን የእግዚአብሔርን መንፈስ ምሪት መረዳት ስለሚያቅተን እና ተረድተነውም ሳለ ደግሞ በቸልተኝነት ወይም በእንቢተኘነት ስለምንተላለፍ በሃጢአት ወጥመድ ውስጥ እንገባለን። ይህ ሲሆን የእግዚአብሔር መንፈስ ወደንስሃ እንድንቀርብ ሲያበረታታን በተቃራኒው የሰይጣን መንፈስ ደግሞ በክስ ውስጥ በማድረግ ይበልጥ ከእግዚአብሔር እንድንርቅ፣ እግዚአብሔር እንደሰለቸን እንዲሰማን፣ ሃጢአታችን ከእግዚአብሔር ይቅርታ በላይ እንደሆነ እንድናምን፣ ሃጢአቱን ሆን ብለን እንደምናደርግ በመውቀስ፣ የእግዚአብሔርን እርዳታ ለመጠየቅ የማንበቃ፣ እግዚአብሔርም ይቅር እንደማይለን እንድናስብ አድርጎ ይዋጋናል። ከዚህ በታች የቀረቡት የእግዚአብሔር ቃል ግን ይህን ሃሳብ አይጋሩም፡
1ዮሐንስ 1፡8-10 ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።
1ዮሐንስ 2፡1-2 ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።
በመጨረሻም፣ ወንድሜ ሆይ፣ ሁላችን በሃጢአት ትግል ውስጥ እንደምንኖር አትዘንጋ። ይህ ትግል የማያቋርጥ ነው። ትግሉን የጨረሰ ሰው በምድር ላይ የለም። ስለዚህ አንተ ብቻህን ከሃጢአት ጋር የምትታገል ሌላው ግን ጨርሶ የተቀመጠ አድርገህ አታስብ። በዚህ ትግል ውስጥ በውደቅና መነሳት አለ። መጽሐፈ ምሳሌ 24፥16 “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፥ ይነሣማል” ተብሉ ነው የተጻፈው። በትግሉ ውስጥ አልፎ አልፎ መውደቅ ቢኖርም መነሳትም አለ። በእኔ እምነት በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት የሆነ አማኝ እያወቀም (በመሳብ) ሆነ ሳያውቅ (በመታለል) ሃጢአትን ሊያደርግ ይችላል (ያዕ 1፡14)። ሆኖም ግን በደስታ በአልጋው ላይ አይተኛም። አማኝ ሃጢአት ሊሰራ ይችላል፣ ሆኖም ግን ጸንቶ በሃጢአቱ አይኖርም። አማኝ በተደጋጋሚ በተመሳሳይ ሃጢአት ሊወድቅ ይችላል፣ ሆኖም ግን ከዚህ ወጥመድ ለመዳን ቀንና ለሊት ወደፈጣሪው ያለቅሳል። አምላኩን ተስፋ ያደርጋል፣ በሃጢአቱ ጊዚያዊ ደስታ ቢያገኝም ድርጊቱን ፈጥኖ ይጸየፋል፣ በመንፈሱም ሃዘን ይሞላል። እናም አድነኝ ብሎ አምርሮ ይጮሃል። እግዚአብሔርም፣ የእስራኤልን የባርነት እንባ እንዳበሰ ሁሉ፣ የአማኙንም ልቅሶ አንድ ቀን ይሰማል።
በእግዚአብሔር ተስፋ አትቁረጥ! እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም። (ዕን 2፡3)