የዳዊት ልጅ፥ የክርስቶስ የዘር ሐረግ (ማቴ. 1፡1-17)

የቅድመ አያቶችህን ስም ወደ ኋላ ተመልሰህ ምን ያህል ልትቆጥር ትችላለህ? አምስት ወይስ? ሰባት ትውልዶች? በኢትዮጵያ ብዙ ሰዎች የዘር ግንዳቸውን ቢያንስ እስከ ሰባት የዘር ሐረግ ይቆጥራሉ። ለኢትዮጵያውያን የዘር ሐረግ መቁጠር አስፈላጊ ቢሆንም፥ ለአይሁዶች ግን ከዚያ የበለጠ አስፈላጊ ነበር። አንድ አይሁዳዊ የዘር ሐረጉን የአይሁዶች ኣባት እስከሆነው አብርሃም ድረስ መቁጠር መቻል አለበት። በተለይም አንድ አይሁዳዊ የተስፋ ቃል የተገባለትን ነቢይ ያህል ታላቅ ሥልጣን ለመያዝ ከፈለገ፥ ይህንን ማድረጉ ወሳኝ ነው። በብሉይ ኪዳን በተለይም አስፈላጊ ግለሰቦችና የቤተሰብ መስመሮች በሚመሠረቱበት ጊዜ፥ የዘር ሐረጎችን በተደጋጋሚ እናገኛለን። በዘፍጥረት መጽሐፍ፥ ከአዳም እስከ ኖኅ ልጆች ድረስ የአይሁዶች የዘር ሐረግ በጥንቃቄ ተዘርዝሯል (ዘፍጥ. 5)። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ የሊቀ ካህናቱ የአሮን የዘር ሐረግ ተዘርዝሯል (ዘኁል. 3፡1-4)። በኋላም፥ የንጉሥ ዳዊት የዘር ሐረግ ተገልጾአል (ሩት 4፡13-2)።

ስለሆነም ማቴዎስ ክርስቶስ እውነተኛ አይሁዳዊ ብቻ ሳይሆን፥ የንጉሥ ዳዊት ሕጋዊ የዘር ሐረግ መሆኑንም ጭምር በመግለጽ ወንጌሉን ይጀምራል። ይህም ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን ትንቢት የተነገረለት መሢሕ ለመሆን ከሚያስፈልጉ ዐበይት መመዘኛዎች አንዱን እንዳሟላ ያሳያል። እርሱ የዳዊት የዘር ሐረግ የሆነ አይሁዳዊ ነበር። ከዚህ የዘር ሐረግ የሚከተሉትን ነጥቦች ልንመለከት እንችላለን።

1. ማቴዎስ የዘር ሐረጉን የጀመረው የአይሁዶች አባት ከሆነው ከአብርሃም ነው። ይህም ክርስቶስ ንጹሕ አይሁዳዊ እንደሆነ ያሳያል። ሉቃስ ፍጹም ሰው በሆነው ክርስቶስ ላይ በማተኮር፥ የዘር ሐረጉን ከአዳም ይጀምራል።

2. በመጀመሪያው ወንጌል ውስጥ የቀረቡት የዘር ሐረጎች በሦስት የ14 ትውልዶች ተመድበው ተከፍለዋል። ከንጉሥ ዳዊት በፊት 14 የዘር ሐረጎች ሲዘረዘሩ፥ ከዳዊት እስከ ባቢሎን ምርኮ 14፥ እንዲሁም ከምርኮው እስከ ክርስቶስ ድረስ 14 ትውልዶች ተዘርዝረዋል (ማቴ. 1፡17 አንብብ)። ማቴዎስ በመሢሕነቱ ላይ በማተኮር፥ ኢየሱስን ለማመልከት «ክርስቶስ» የሚለውን ስም ብቻ ይጠቀማል።)

3. «አባት» የሚለው ቃል ወሳኝ ባልሆነ መንገድ ገብቶአል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ቃሉ «የዘር ሐረግ» የሚል ፍች ነበረው። ምክንያቱም ማቴዎስ በዝርዝሩ ውስጥ አያሌ ትውልዶችን ዘሏል። ለምሳሌ፥ ማቴዎስ ኢዮራም ዖዝያን እንደ ወለደ ገልጾአል። በ2ኛ ዜና 21፡4-26፡23 ግን ከኢዮራም በኋላ ኣሃዚያ፥ ኢዮአስ፥ አሜስያስና ዖዝያን እንደሚመጡ እንመለከታለን።)

4. ማቴዎስ በዳዊት የዘር ሐረግ ውስጥ የገቡትን አራት የተለዩ ሴቶች ዘርዝሯል። የመጀመሪያዋ ይሁዳን የወለደችው ትዕማር የምትባል ከነዓናዊት ናት። ሁለተኛይቱ በኢያሪኮ ከተማ ውስጥ ሰላዮችን የሸሸገችው ረዓብ ናት። ሦስተኛዋ ቦዔዝን አግብታ የንጉሡ ዳዊት አያት ለመሆን የቻለችው ሞዓባዊቷ ሩት ናት። የመጨረሻዋ፥ ዳዊት ዝሙት የፈጸመባት የኦሪዮን ሚስት ናት። ማቴዎስ እነዚህን አራት ሴቶች ብቻ የጠቀሰው ለምንድን ነው? ማቴዎስ የእግዚአብሔር በረከት በጸጋ እንጂ፥ አንድ ሰው የትክክለኛ ቤተሰብ አባል ስለሆነ ብቻ የሚያገኘው ነገር እንዳልሆነ ለማመልከት ፈልጎ ይሆን? ምናልባትም ደግሞ ይህ እግዚአብሔር አሕዛብን ወደ ቤተሰቡ ለመቀላቀል ፈቃደኛ መሆኑን የሚያመለክት ይሆናል፡፡ ማቴዎስ ከሚያስተምረን ነገሮች አንዱ፥ እግዚአብሔር ለአሕዛብም ለአይሁዶችም እኩል ዕቅድ እንዳለው ነው።

5. የማቴዎስ የዘር ሐረግ የዮሴፍን አቅጣጫ ሲከተል፥ የሉቃስ ግን የማርያምን ይከተላል። ማቴዎስ ክርስቶስ ከዮሴፍ ጋር የነበረውን ግንኙነት የገለጸው በጥንቃቄ ነበር። ዮሴፍ የማርያም ባል ነበር። ነገር ግን የክርስቶስ አባት አልነበረም። ምንም እንኳ በሚገባ የማያውቁት ሰዎች እባቱ እንደሆነ ቢያስቡም። ዮሴፍ የክርስቶስ ሕጋዊ አባት እንጂ ሥጋዊ አባቱ አልነበረም። በአይሁድ ባህል፣ ሕጋዊ መብቶች የሚተላለፉት በወንዱ እንጂ በሴቷ የዘር ሐረግ አልነበረም። ይህ ግለሰቡ ሥጋዊ አባት ባይሆንም እውነት ነበር። ስለሆነም በሕጋዊ ገጽታው ዳዊታዊ መብቶች ወደ ክርስቶስ የሚተላለፉት በዮሴፍ እንጂ በማርያም በኩል አልነበረም። እንግዲህ ክርስቶስ የዮሴፍ ሕጋዊ ልጁ ባይሆን ወይም ዮሴፍ የዳዊት የዘር ሐረግ ባይሆን ኖሮ፥ እንደ ዳዊት ልጅ ወደ ዳዊት ዙፋን ለመውጣት መብት ኣይኖረውም፤ ደግሞም መሢሕ ለመሆን አይችልም ነበር። ማርያም ከዳዊት ወገን መሆኗ ብቻ በቂ ኣልነበረም።

6. የማቴዎስ ወንጌል የዳዊትን የዘር ሐረግ በሰሎሞንና በገዥ ነገሥታት በኩል ይዘረዝራል። ሉቃስ የዳዊትን የዘር ሐረግ የተከተለው ካልነገሡት የዳዊት ልጆች አንዱ በሆነው በናታን በኩል ነበር። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አንዳንድ ምሑራን ክርስቶስ ሁሉም የመሢሕነቱን መመዘኛዎች እንዳሟላ የሚያስረዱ በመሆናቸው፥ ሁለቱም የዘር ሐረጎች አስፈላጊዎች መሆናቸውን ይናገራሉ። በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር የኢዮአቄም ዘሮች በእስራኤል ላይ እንዳይነግሡ ረግሟቸው ነበር (ኤር. 22፡24-30)። ማቴዎስ የክርስቶስን የዘር ሐረግ በኢዮአቄም በኩል ዘርዝሯል (ኢኮንያን ማቴ. 1፡11)። ስለሆነም፥ ምንም እንኳ ክርስቶስ ከኢዮአቄም የሚወስደው ሕጋዊ የመግዛት መብት ቢኖረውም፥ የእግዚአብሔር ርግማን የኢዮአቄም ቀጥተኛ ትውልዶች በመሢሕነት እንዳይገዙ ይክለክል ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ ከኢዮአቄም የተቀበለው ሕጋዊ የመግዛት መብትን ብቻ ሲሆን፥ የኢዮአቄም ቀጥተኛ ትውልድ አልነበረም። ከድንግል በመወለዱ ምክንያት ክርስቶስ ከናታን ትውልድ ወገን ነበር። ይህም ክርስቶስ በእርግማኑ ሥር ሳይደመር በመሢሕነት የማገልገል መብት አግኝቷል።

1ኛ የውይይት ጥያቄ፡– ይህ እግዚአብሔር ለዳዊት ልጅ ለመሢሑ የወጠናቸው ዕቅዶች በሙሉ መሟላታቸውን እንዴት ያሳየናል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

2 thoughts on “የዳዊት ልጅ፥ የክርስቶስ የዘር ሐረግ (ማቴ. 1፡1-17)”

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading