የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት (ማቴ. 3፡1-12)

ማቴዎስ የክርስቶስን ታሪክ የቀጠለው ከሠላሳ ዓመት በኋላ ነበር። ማቴዎስ የክርስቶስን ይፋዊ አገልግሎት የጀመረው፥ ከክርስቶስ በፊት መጥቶ ሰዎችን ለእምነት ስለሚያዘጋጀው ነቢይ በአጭሩ በመግለጽ ነበር። ከዚያም ክርስቶስ የእግዚአብሔር አዳኝና ሊቀ ካህናት እንዲሆን ያዘጋጁትን ሁለት ክስተቶች ገልጾአል።

በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ከመሢሑ በፊት መንገድ ጠራጊ ነቢይ እንደሚላክ ለአይሁዶች ነግሯቸው ነበር። የብሉይ ኪዳን የመጨረሻው የእግዚአብሔር ነቢይ የሆነው ሚልክያስ ይህን ነቢይ «ኤልያስ» ብሎታል። ይህም ነቢዩ ከኤልያስ ጋር በሚመሳሰል መንገድ እንደሚመጣ ያሳያል። ከሚልክያስ እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ ለ400 ዓመት እግዚኣብሔር ለሕዝቡ አልተናገረም ነበር። እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ የተመራ ምንም ዓይነት ነቢይ አልላከም ነበር። ከረጅሙ ዝምታ በኋላ ግን አንድ ዐይን የማይገባ ልብስ የለበሰ ግለሰብ ከበረሃ ወደ ምሥራቅ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ዝምታው አበቃ [መጥምቁ ዮሐንስ ቆዳ የለበሰውና አንበጣ የበላው የአይሁዶች ነቢያት ምሳሌ የሆነውን ኤልያስን ለመምሰል ነበር (2ኛ ነገ. 1፡8)።] ስሙ ዮሐንስ ሲሆን፥ ልዩ ስሙ «መጥምቁ» የሚል ነበር። ይህም ሰዎች ሕይወታቸውን ለመለወጥና ለመሢሑ በተዘጋጀ ሁኔታ ለመኖር መወሰናቸውን ለማመልከት እንዲጠመቁ መጥራቱን ለማሳየት ነበር። እነዚህን ዐበይት እውነቶች ልብ አድርግ።

1. መጥምቁ ዮሐንስ ያስተላለፈው «የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» የሚል ቀላል መልእክት ነበር። ብዙውን ጊዜ ንስሐ መግባት ማለት ለፈጸምነው በደል መጸጸት ብቻ ይመስለናል። ነገር ግን የግሪኩ ቃል፥ ከዚያ የጠለቀና አያሌ ነጥቦችን ያካተተ ነው።

ሀ. የፈጸምናቸውን ዝርዝር ኃጢአቶችና እግዚአብሔርንም ያልታዘዝናቸውን ነገሮች አምነን እንቀበላለን። ኣብዛኛውን ጊዜ ይቅርታ ስንጠይቅ ኣንድን ሰው መበደላችንን እየገለጽን ነው። ኃጢኣታችን በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸም ዐመፅ መሆኑን እምብዛም ኣናጤንም። በዚህም ነው ብዙውን ጊዜ መጸጸታችንን ገልጸን ይቅርታ ብንጠይቅም፥ ተግባራችንን ግን የማንለውጠው።

የውይይት ጥያቄ፡- 1) ባለፈው ሳምንት የፈጸምኸውን ኃጢአት ጥቀስ። ይህ ኃጢአት የምትጸጸትበት ስሕተት ብቻ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ፊት የዐመፅ ተግባር የሚሆነው እንዴት ነው? 2) እያንዳንዱ ኃጢኣት በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸም ኃጢአት እንደሆነ ብንገነዘብ፥ ይህ በኃጢአት ላይ ያለንን አመለካከት እንዴት ይለውጠዋል?

ለ. እውነተኛ ንስሐ የፈጸምነውን ድርጊት ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ አኗኗራችንን የሚለውጥ ቁርጥ ውሳኔ የሚያካትት ነው። የግሪኩ ቃል ስለ ንስሐ የሚሰጠን አሳብ፥ ወደ አንድ አቅጣጫ ይሄድ የነበረ ሰው፥ ፊቱን አዙሮ በተቃራኒው አቅጣጫ መጓዙን ያሳያል። ጠቅላላ የተግባር ለውጥ የሌለበት ንስሐ ሊባል አይችልም። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ባሕርያቸውን ሳይለውጡ ውጫዊ የንስሐ ተግባር ለመፈጸም በመፈለጋቸው፥ መጥምቁ ዮሐንስ ወቅሷቸዋል። «የእፉኝት ልጆች» ብሎ በመጥራት፥ ሃይማኖታውያን ለመምሰል ቢሞክሩም፥ ጠቅላላ አኗኗራቸውን ሊለውጡና ፍጹም የተለየ አኗኗር ሊከተሉ እንደሚገባ ነግሯቸዋል። ሃይማኖተኛ መሆን ወይም ከትክክለኛው ነገድ ወገን (የአብርሃም ልጆች) መሆን ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንዲኖራቸው አላደረገም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ የንስሐ አሳብ ብዙውን ጊዜ ለማመን ወይም የቤተ ክርስቲያን ኣባል ለመሆን ለሚፈልጉ ሰዎች ከምንነግራቸው የሚለየው እንዴት ነው? ለ) የደኅንነት (የድነት) ወይም የይቅርታ ትምህርታችን፥ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ንስሐ የሚናገረውን ያንጸባርቅ ዘንድ እንዴት ሊለወጥ ይገባል?

ሐ ዮሐንስ ከልባቸው ለመለወጥና ለመሢሑ መምጣት የሚያዘጋጅ ሕይወት ለመኖር የወሰኑት ሰዎች እንዲጠመቁ ነገራቸው። ምሁራን የጥምቀትን አሳብ ከየት እንዳመጣ ይከራከራሉ። ጥምቀት በአይሁድ ታሪክ የተለመደ ነገር ነበር። በመጀመሪያ፥ አንድ አሕዛብ አይሁዳዊ ለመሆን በሚፈልግበት ጊዜ ይጠመቅ ነበር። ሁለተኛው፥ የኤሴናውያን ማኅበረሰብ አባል የሚሆን ሰው ሁሉ ይጠመቅ ነበር።

ጥምቀት ሁለት ዐበይት ዐላማዎች አሉት። በመጀመሪያ፥ አንድ ሰው አኗኗሩን ለመለወጥና እግዚአብሔርን ለመከተል የሚፈልግ ማኅበረሰብ አባል ለመሆን መፈለጉን ያሳያል። ግለሰቡ በውስጣዊ ሕይወቱ ለመለወጥ መፈለጉን የሚያሳይ ይፋዊ ምስክርነት ነበር። ሁለተኛው፥ የግለሰቡን ውስጣዊ ንጽሕና የሚያመለክት ውጫዊ ምሳሌ ነበር። ውኃ መንፈሳዊ ቆሻሻንና ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደማይችል አልጠፋቸውም ነበር። በብሉይ ኪዳን ካህናት እግዚአብሔርን ከማገልገላቸው በፊት በውኃ መታጠብ ያስፈልጋቸው ነበር። ይህም ኃጢአታቸውን በመናዘዝ መዘጋጀታቸውን የሚያመለክት ነበር። በተመሳሳይ መንገድ፥ ዮሐንስ የሚያጠምቃቸው ሰዎች ኃጢአታቸውን እንደ ተናዘዙና ሕይወታቸውን በእግዚአብሔር ፊት እንዳስተካከሉ ለማሳየት በውኃ ይታጠቡ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- የአይሁዶች የጥምቀት ግንዛቤ፥ ከክርስቲያኖች ጋር የሚመሳሰለው ወይም የሚለያየው እንዴት ነው?

ቤተ ክርስቲያን በተመሠረተችበት ወቅት፥ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ትእዛዝ ተከትለው ጥምቀትን ያካሂዱ ጀመር። በተጨማሪም ጥምቀት ክርስቲያኖች ክርስቶስን እንደ መሢሓቸው ለመከተል ሕይወታቸውን እንደ ሰውት የሚያመለክት ይፋዊ እርምጃ ነበር። ሕይወታቸው ከኃጢአት እንደ ነጻ ያሳዩ ነበር። እንዲሁም አማኞቹ የክርስቲያኖች ማኅበር አካል መሆናቸውንና የቤተ ክርስቲያን ሙሉ አባላት ለመሆን መፍቀዳቸውን እያሳዩ ነበር። ጥምቀት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር መተባበራቸውንም የሚያሳይ ተግባር ነበር። ለአርጌ ኃጢኣታቸው ሞተው፥ ለአዲሱ ሕይወት ተነሥተዋል።

2. መጥምቁ ዮሐንስ «መንግሥተ ሰማይ» እንደ ቀረበች አውጇል። ከማቴዎስ ቁልፍ ሐረጎች አንዱ «መንግሥተ ሰማይ» የሚለው ነው። በመጽሐፉ ውስጥ 33 ጊዜ ያህል ጠቅሶታል። ይህ ሐረግ ማቴዎስ መጽሐፉን ለኣይሁዶች እንደ ጻፈ ያመለክታል። ሌሎቹ ወንጌላት ትርጉሙን ለአሕዛብ ይበልጥ ግልጽ የሚያደርገውን «የእግዚአብሔር መንግሥት» የሚለውን ሐረግ ተጠቅመዋል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፥ «መንግሥት» በአይሁዶችና በክርስቲያኖች ግንዛቤ መልክአ ምድራዊ አካባቢን ኣያመለክትም። ነገር ግን በአንድ ነገር ላይ ኃይልና ሥልጣን መቀዳጀትን ያመለክታል። ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔር መንግሥት ነው። እግዚአብሔር በኣንድ ሰው ልብ ውስጥ የሚገዛ ከሆነ፥ ያ የእርሱ መንግሥት ነው። [ለዚህ ነው ክርስቶስ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ (በውስጣችሁ) ነች ያለው (ማቴ. 17፡21)።] ወይም ደግሞ ይህ ክርስቶስ በቤተ ክርስቲያን ላይ መግዛቱን ሊያመለክት ይችላል። መንግሥት የሚለው ቃል አካባቢን ሊያመለክት የሚችለው ክርስቶስ በምድር ላይ የሚመሠረተውን የመጨረሻ መንግሥት በሚጠቅስበት ጊዜ ብቻ ነው።

ማቴዎስ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰማይ የሚለውን ስም የተጠቀመው አይሁዶች «እግዚአብሔር» (ጀሆቫ) የሚለውን ስም በቀጥታ ለመጥራት ስለሚፈሩ ነበር። በዘጸ 20፡7 መሠረት፥ ስሙን መጥራት እግዚአብሔርን እንዳላከበሩ ወይም እንዳቀለሉ ይሰማቸው ነበር። በተለይ በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል በነበረው ጊዜ፥ አይሁዶች እግዚአብሔር ስሙን ካቃለልን ይፈርድብናል ብለው ስለሚፈሩ፥ ይህ እውነት በጣም አስፈላጊ ሊሆን በቅቷል። ስለሆነም የእግዚአብሔርን ስም ለመጥራት «የሰማይ አምላክ» የሚሉትን ዐይነት ሌሎች አገላለጾች ይጠቀሙ ነበር (ነህ. 1፡4)። ለአይሁዶች «ሰማይ» የሚለው ቃል የእግዚአብሔር ምትክ ነበር። ስለሆነም ማቴዎስ «ሰማይ» ሲል እግዚአብሔር ማለቱ ነበር። ይህም መንግሥተ ሰማይ እና የእግዚአብሔር መንግሥት አንድ ዐይነት መሆናቸውን ያመለክታል።

3. መጥምቁ ዮሐንስ ስለ እግዚአብሔር የጊዜ ሰሌዳ ሙሉ ግንዛቤ አልነበረውም። በኋላ ኢየሱስ ዮሐንስ ባልጠበቀው መንገድ በመሥራቱ፥ መሢሑ አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ? ብሎ ሲጠይቅ እንመለከታለን (ማቴ. 11፡2-6)። ዮሐንስ የጠበቀው መሢሑ የሚገዛበትን ምድራዊ መንግሥት ሲሆን፥ ክርስቶስ መጀመሪያ የመጣው እንደ መንፈሳዊ ንጉሥ ነበር፡፡ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ ሲመጣ ንጉሣዊ አገዛዙ ይጀመራል። የእግዚአብሔር የፍርድ ጊዜ መድረሱ የዮሐንስ መልእክት አካል ነበር። ከልባቸው ንስሐ ገብተው ሕይወታቸውን ለመለወጥ የማይፈልጉ ሰዎች ለእግዚአብሔር ፈጣን ፍርድ ይጋለጣሉ። ይህ በመጨረሻው ዘመን ይፈጸማል።

4. መጥምቁ ዮሐንስ ሰዎችን ለማዘጋጀት እንደ ተጠራና ይህንንም በትክክል እንደ ፈጸመ ተረድቷል። ሰዎችን ወደ ራሱ ለመሳብ በመሞከር ራሱንና ድርሻውን ከፍ ከፍ ከማድረግ ይልቅ፥ ዮሐንስ ከእርሱ ለሚበልጥ ሌላ አገልጋይ መንገድ እያዘጋጀ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። ስለሆነም መሢሑ ከእርሱ በኋላ እንደሚመጣ ለሕዝቡ አበሠረ። መጥምቁ ዮሐንስ ወደ መሢሑ በማመልከት ሁለት ዐበይት አገልግሎቶቹን ጠቅሷል።

በመጀመሪያ፥ መንፈስ ቅዱስን በመስጠት አገልግሎቱን እንደሚጀምር ገልጾአል። ኣይሁዶችና የጥንት ክርስቲያኖች ከመሢሕ መምጣት ዐበይት ምልክቶች አንዱ የመንፈስ ቅዱስ በሰዎች ሁሉ ላይ መውረድ እንደሆነ ያውቁ ነበር (ኢዩ. 28-29 አንብብ።) በብሉይ ኪዳን ዘመን መንፈስ ቅዱስ አገልግሎታቸውን ለማጽናት ሲል አንዳንድ ጊዜ ወደ ኣንዳንድ መሪዎች ይመጣ ነበር (መሳ. 6፡34)። አሁን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሙሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበላሉ። በሐዋ. 2 ላይ እንደምናነበው መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ሲወርድ፥ ይህ የኢዩኤል ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ ተገነዘቡ። ይህም የመጥምቁ ዮሐንስ የተስፋ ቃል ፍጻሜ ነበር።

ሁለተኛው፥ መሢሑ ተከታዮቹን በእሳት «ያጠምቃቸዋል»። አንዳንድ ክርስቲያኖች፥ ይህ በሐዋርያት ሥራ 2 ላይ በደቀ መዛሙርቱ ራሶች ላይ የተቀመጡትን የእሳት ልሳናት እንደሚያመለክት ያስባሉ። ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እሳት ከእግዚአብሔር ጋር ተያይዞ ስለተጠቀሰ (ለምሳሌ፥ ዘጸ. 3፡2-4)፥ እነዚህ ክርስቲያኖች እሳትን የእግዚአብሔር መገኘት ተምሳሌት አድርገው ይወስዱታል። ይሁንና የእሳት ጥምቀት መሢሑ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ በማይፈልጉ ሰዎች ላይ የሚያመጣውን የፍርድ ጥምቀት የሚያመለክት ይመስላል። መጥምቁ ዮሐንስ መሢሑ ንስሓ በማይገቡት ሰዎች ሁሉ ላይ ፍርድን እንደሚያመጣ እያስጠነቀቀ ነበር። ስንዴ ንስሐ ገብተው እግዚአብሔርን ለመታዘዝ የሚወስኑትን ሲያመለከት፥ የሚቃጠለው እንክርዳድ ደግሞ እግዚኣብሔር በሕይወታቸው ላይ እንዳይገዛ የሚያምፁትን ያመለክታል። መጥምቁ ዮሐንስ ይህ የእሳት ጥምቀት እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽኣት ድረስ እንደሚዘገይ አላወቀም ነበር (ራእይ 19፡11-21፤ 20፡7-8)።

የውይይት ጥያቄ፡- የመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎትና መልእክት ለዛሬው አገልግሎታችን ምሳሌ የሚሆነው በምን መንገድ ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

Leave a Reply

%d bloggers like this: