ክርስቶስ የመጣው የብሉይ ኪዳንን ሕግ ለመሻር ሳይሆን ለመፈጻም ነው (ማቴ. 5፡16-48)

የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 5፡16-48 ኣንብብና ክርስቶስ ከብሉይ ኪዳን ሕግ ጋር ምን ዐይነት ግንኙነት እንደ ነበረው ግለጽ።

የክርስቶስ ቀንደኛ ጠላቶች ፈሪሳውያን ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ከክርስቶስ ጋር የሚጋጩት እርሱ የብሉይ ኪዳን ሕግን ባለመፈጸሙ ምክንያት ሳይሆን፥ እነርሱ የጨመሯቸውንና ከብሉይ ኪዳን ሕግ እኩል እንደሆኑ የሚያስተምሯቸውን ሕግጋት ለመፈጸም ባለመፈለጉ ነበር። ይህም ክርስቶስ ሕግን አያከብርም የሚል ወሬ እንዲዛመት አደረገ። ማቴዎስ ግን ክርስቶስ የብሉይ ኪዳንን ሕግ እንደማይቃወም አመልክቷል። ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ሕግ አንዲት ነቁጥ እንኳ እንደማትወድቅ አስተምሯል። ሰዎች የእርሱ ተከታዮችና የመንግሥቱ አካል ለመሆን ከፈለጉ፥ የእግዚአብሔርን ሕግ በሙሉ መጠበቅ እንዳለባቸውም ኣስተምሯል።

ምሑራን ክርስቶስ «ልፈጽም» ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ይከራከራሉ። ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን የሕግ ዓይነቶች በሙሉ በሁሉም ዘመን ለሚኖሩ ክርስቲያኖች አሁንም ይሠራሉ ማለቱ ይሆን? ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የሥነ ምግባር ሕግን (ለምሳሌ፥ «አታመንዝር»)፣ ሥርዐታዊ ሕግን (ለምሳሌ፥ ለእግዚአብሔር በመሠዊያ ላይ መሥዋዕቶችን ማቅረብ)፥ እና ማኅበራዊ ሕግን (ለምሳሌ፥ የአንድ ሰው በሬ ወደ ሌላው ግለሰብ እርሻ ዛሬ በሚገባበት ጊዜ ምን እንደሚደረግ) መጠበቅ አለበት? ይህ የዕብራውያን መጽሐፍ ከክርስቶስ መሥዋዕት የተነሣ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች እንደተሻሩ ከሚናገረው ወይም የምግብ ሥርዓቶች ከእንግዲህ እንደማይጠቅሙ ከሚያስረዳው ከሐዋርያት ሥራ 10 ጋር እንዴት ይዛመዳል? ስለሆነም ኢየሱስ ሕግን ስለመፈጸሙ ሲናገር ምን ማለቱ እንደሆነ የሚያስረዱ የተለያዩ አሳቦች አሉ።

  1. ኢየሱስ የብሉይ ኪዳን ሕግን ሙሉ በሙሉ ፈጽሟል፤ ለሕጉ ታዟልም።
  2. ብሉይ ኪዳን በሙሉ ወደ ክርስቶስ ያመለክታል። ዘጸኣት ክርስቶስ ከባርነት እንደሚያወጣን ያሳያል። መሥዋዕቶችና ሃይማኖታዊ በዓላት ሁሉ ወደ ክርስቶስና አገልግሎቶቹ ያመለክታሉ። ነቢያት ሁሉ በክርስቶስና በተግባሩ ላይ ያተኩራሉ። ስለሆነም የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎች በሙሉ በኢየሱስ ተፈጻሚነትን አግኝተዋል። እርሱ እውነተኛ የአምልኮ መንገድ ነው። እርሱ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋርና እርስ በርሳቸው የሚዛመዱበትን መንገድ ያስተምራል። ሰዎች እንዴት በፍቅር አብረው እንደሚኖሩ ያሳያል። ክርስቶስ የኢሳይያስን ትንቢቶች እንደፈጸመ ሁሉ፥ በብሉይ ኪዳንም የእግዚአብሔርን ተምሳሌቶች ሁሉ ፈጽሟል። የብሉይ ኪዳን ሥርዐታዊ ሕግና ማኅበራዊ ሕግ መሢሑ ከመጣ በኋላ አስፈላጊዎች አልነበሩም።
  3. በኢየሱስ መምጣት፥ የብሉይ ኪዳን ሕግና የተስፋ ቃሎች፥ እግዚአብሔር ለእነርሱ የነበረው ዓላማ ከፍጻሜ ደረሰ።

ኢየሱስ ብሉይ ኪዳን ከእንግዲህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዳልሆነ ኣልተናገረም። ይህ ከእግዚአብሔር የመነጨ በመሆኑ፥ ሁልጊዜም የመጽሐፍ ቅዱስ አካል ነው። ነገር ግን በክርስቶስ መምጣት ብሉይ ኪዳንን የምንረዳበት መንገድ የተለወጠበት ሁኔታ አለ። አሁን እግዚአብሔር ብሉይ ኪዳንን የሰጠባቸውን ዐላማዎች ከኣዲስ ኪዳንና ከክርስቶስ ትምህርቶች እንረዳለን።

ከዚያ በኋላ ግን ክርስቶስ የዘላለምን ሕይወት የሚቀበሉት፥ ከፈሪሳውያንና ከሕግ መምህራን የበለጠ ጽድቅ ያላቸው ብቻ እንደሚሆኑ ገልጾአል። ይህ አባባሉ አይሁዶችን አስደነገጠ። የፈሪሳውያንን ያህል መንፈሳዊ የሚመስል ሰው አልነበረም። የሕይወታቸውን ክፍሎች የሚገዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕግጋት ይከተሉ ነበር። አይሁዶች እንዴት ከፈሪሳውያን በላይ መንፈሳዊ መሆን ይቻላል? ብለው ማሰባቸው አልቀረም። ክርስቶስ ምክንያቱ የፈሪሳውያን በውጫዊ ነገሮች ላይ ማተኮር እንደሆነ ገለጸ። የእግዚአብሔርን ሕግጋት ከመጠበቅ ኋላ ስለነበሩት መርሖዎች አይጨነቁም ነበር። እግዚአብሔርን የሚያሳስበው ከውጫዊ ሥርዐት ይልቅ የልባችን ነገር ነው። እግዚአብሔር ልባችን ትክክል ከሆነ ትክክለኛ ተግባር እንደምናከናውን ያውቃል። ፈሪሳውያን የተለወጠ ልብና ትክክለኛ ምኞት ስላልነበራቸው በእግዚአብሔር ፊት ከንቱዎች ነበሩ።

የውይይት ጥያቄ፡- ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች ከተግባሩ ባሻገር ያሉትን አነሣሽ ምክንያቶችና አመለካከቶች ሲያጤኑ በውጫዊ ተግባራት ላይ እንዴት እንደሚያተኩሩ ኣብራራ።

ኢየሱስ ሕግን እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ከልብ መታዘዝ ከውጫዊ ተግባራት እንዴት እንደሚለይ ለማሳየት ስድስት ምሳሌዎችን ሰጥቷል። እነዚህም እግዚአብሔር ሕግን ስለመጠበቅ ያለው አመለካከት ከፈሪሳውያን የላቀ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው። (ማቴዎስ በዚህ ክፍል ውስጥ ከሚያሳያቸው ነገሮች መካከል አንዱ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ልብ ለመተርጎም እንደሚችል ነው። የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መሆኑ መጠን፥ ክርስቶስ የተጻፉትን የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ብቻ ሳይሆን ከ1400 ዓመታት በፊት የሙሴን ሕግ ሲሰጥ ከሕዝቡ ምን እንደፈለገም ያውቅ ነበር። ክርስቶስ «ሙሴ ተብሏል እኔ ግን እላለሁ» ሲል ሕግን ከሰጠው እግዚአብሔር ጋር ራሱን እኩል እያደረገ ነበር።)

ሀ. ስለ መግደል የተነገረ ምሳሌ (ማቴ. 5፡12-26)። ብሉይ ኪዳን ሰው መግደል የተከለከለ መሆኑን በግልጽ አስተምሯል። ፈሪሳዊ ሰው ገድሎ ስለማያውቅ፥ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንዳለው ያስብ ነበር። ይህ ሕግ ትዕቢቱንና ቁጣውን እንዲያስወግድ፣ ወይም የተበላሸውን ግንኙነት እንዲያስተካክል አላስገደደውም ነበር። ክርስቶስ ግን የግድያ ሁሉ ሥር በሆነው ጥላቻ ላይ አተኮረ። በእግዚአብሔር ዐይን፥ አንድን ሰው መጥላት ኃጢአት ነው። የቁጣ ውጤት በመጀመሪያ ደረጃ የግድያን ያህል አስከፊ ላይሆን ቢችልም፥ የግድያ ሁሉ ሥር ቁጣ ነው። ስለሆነም ከሕይወታችን ውስጥ ቁጣን እስካላስወገድን ድረስ እግዚአብሔር የሚፈልገውን የፍቅር ግንኙነት፥ ከሌሎች ጋር የማድረግ ሕይወት ልንመራ ኣንችልም። (‹ደንቆሮ› የሚለው አንድ ሰው በሌላው ላይ የሚሰነዝረው የንቀት ስድብ ነው። የአይሁድ ሸንጎ የግድያ ጉዳዮችን የሚመረምር የአይሁዶች የሕግ ምክር ቤት ነበራቸው።) ትዕቢተኛ፥ ሌሎችን የሚንቅ፥ በጥላቻና በክፋት የተሞላ ልብ ለእግዚአብሔር የነፍሰ ገዳይን ያህል የከፋ ነው። ሁለቱም ግለሰቡ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት እንደማያደርግና የተለወጠ ሕይወት እንደሌለው ያሳያሉ።

ክርስቶስ የሕግ ዋንኛ መልእክት ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት ማድረግ መሆኑን ለማሳየት ሁለት ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። የመጀመሪያው ምሳሌ በመሠዊያው ላይ እንስሳትን በመሠዋት እግዚአብሔርን የሚያመልከውን ሰው ይመለከታል። እየሰገደ ሳለ አንድ የተጣላው ሰው እንዳለ ትዝ አለው። ምንም እንኳ ሰጋጁ ከራሱ ልብ ጉዳዩን ያወጣው ቢሆንም፥ ግለሰቡ ግን አሁንም እንደተናደደ ያውቅ ነበር። በሰዎች መካከል ጥል እያለ እግዚአብሔርን ማምለክ አይቻልም። ስለሆነም ኢየሱስ፥ መሥዋዕትን የሚሠዋው አማኝ፥ አስቀድሞ የተቀየመውን ግለሰብ መታረቅ እንዳለበት ገልጾአል። ከዚያ በኋላ ተመልሶ መሥዋዕት በማቅረብ እግዚአብሔርን ሊያመልክ እንደሚቻል አስረድቷል።

ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ መከፋፈል ይታያል። ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር እንደሚደሰትብን እያሰብን በመዘመር፥ ስብከቶችን በመስማት፥ በመጸለይና በመጾም እናመልከዋለን። ክርስቶስ ግን ግንኙነቶች ከተበላሹ ማንም ይበድል ማን ሁለቱም ወገኖች ግንኙነቱን ለማስተካከል መጣር እንዳለባቸው ገልጾአል። እግዚአብሔር በአምልኳችን ደስ የሚሰኘው በዚህ ጊዜ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በብዙ የተበላሹ ግንኙነቶች ውስጥ እግዚአብሔርን ለማምለክ ብንሞክር፥ ዛሬ ለእኛ የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው? ለ) የተቀያየምኸው ሰው አለ? እግዚአብሔር ብርታትና ምሪት እንዲሰጥህ ጠይቅና ግንኙነቱን ለማስተካከል ትችል ዘንድ ወደ ግለሰቡ ሄደህ ተነጋገር።

በክርስቶስ ዘመን ሰዎች ገንዘብ የመበደር ልማድ ነበራቸው። የተበደሩትን ገንዘብ ለመክፈል ካልቻሉ፥ እነርሱ ወይም ቤተሰቦቻቸው ለባርነት ይሸጡ ነበር። ወይም ደግሞ ገንዘቡን እስኪከፍሉ ድረስ ወኅኒ ቤት ይወርዳሉ። ክርስቶስ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ችሎት ከመድረሱ በፊት ተበዳሪው ከአበዳሪው ጋር ሆኖ መፍትሔ መፈለግ እንዳለበት ተናግሯል።

ክርስቶስ ይህንን በመጠቀም አለመስማማትና ክርክሮችን እንዴት ማስተናገድ እንደሚገባ አስተምሯል። በክርክር ውስጥ አቋምህን በልበ ደንዳናነት ይዘህ በቀጠልህ ቁጥር፥ ክርክሩ እየከፋ ሄዶ በአንተና በተሟጋችህ ላይ ጉዳት ማድረሱ የማይቀር ነው። ስለሆነም ቁጣና ትዕቢት የፍትሕን በር ከመዝጋታቸው በፊት፥ ችግሩን ለመፍታት መሞከሩ መልካም ነው (ምሳሌ 25፡8-10 አንብብ።) አለመስማማትን በጊዜ ውስጥ ለመፍታት መሞከራችን ክብደቱን ከማቃለሉም በላይ በእኛና በቤተሰባችን ፥ በቤተ ክርስቲያናችንና ከሁሉም በላይ በጌታ ስም ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በእጅጉ ይቀንሳል።

ስለ ዝሙት የተነገረ ምላሌ (ማቴ. 5፡27-30)። የሙሴ ሕግ ሰዎች ዝሙትን መፈጸም እንደሌለባቸው በግልጽ አመልክቷል። ያገባ ሰው ከሚስቱ ውጭ ወሲባዊ ግንኙነት እንዳያደርግ ተከልክሎአል። ያላገባ ሰው ደግሞ ከማግባቱ በፊት ምንም ዓይነት ወሲባዊ ግንኙነት ማድረግ አይችልም ነበር። አሁንም ለክርስቲያኖች ዝሙት አልፈጸምሁም ብሎ መኩራራቱ ቀላል ነው። ነገር ግን ክርስቶስ ዋናው ጉዳይ ውጫዊው የወሲብ ተግባር እንዳልሆነ ገልጾአል። ዋናው ጉዳይ ከልብ ጋር ሲሆን፥ አንድ ሰው በተግባር ዝሙት ባይፈጽምም ይህንኑ ለማድረግ ሊመኝ ይችላል። የዝሙት ሥር ምኞት ስለሆነ፥ እግዚአብሔርንና ሌላውን ሰው የሚያስከብር ውስጣዊ ሕይወት ለመምራት ከምኞት መራቅ እንዳለበት ኢየሱስ አስተምሯል። ብዙ ጊዜ ኃጢአትን ቀላል አድርገን እንመለከታለን። ኃጢአት ከፈጸምን በኋላ ይቅርታ ለመጠየቅ እንደምንችል እናስባለን። «ሌላውን ሰው እስካልጎዳሁ ድረስ ምን ችግር አለው?» ብለን ራሳችንን እንጠይቃለን። ክርስቶስ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብና እግዚአብሔር ኃጢአትን እንዴት አጥብቆ እንደሚጠላ ለማሳየት ፈለገ። ሰዎችን ለማስደንገጥ የሚያስችል የንግግር ዓይነት በመጠቀም፥ ክርስቶስ ወደ አንድ ኃጢኣት የሚመራ ዝንባሌ ያለው ሰው ፈጣን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ተናግሯል። ክርስቶስ አንድ ሰው ዓይኖቹ ዝሙትን ከተመኙ፥ እንዲያወጣቸው ወይም እጆቹ ለመስረቅ ከፈለጉ እንዲቆርጣቸው ያዘዘው በቀጥተኛ አገላለጽ አልነበረም። ይህ በትክክል ተግባራዊ ቢደረግ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዓይን ወይም እጅ ያለው ሰው ሊገኝ አይችልም። ክርስቶስ ይህን ሲል እግዚአብሔር ኃጢአትን ምን ያህል እንደሚጠላ ማመልከቱ ነበር። ኃጢኣታችን ክርስቶስን ለመስቀል ሞት እንዳበቃው መዘንጋት የለብንም! ትንሿ ውሸት ክርስቶስን መስቀል ላይ ለማውጣት በቂ ነበረች። ክርስቶስ የኃጢአትን ክፋት ስለሚያውቅ፥ የኃጢአትን ፈተና ለመቋቋም ጥብቅ እርምጃ መውሰድ እንዳለብን አስረድቷል። በሥራ ቦታ አንድ የምንመኘው ሰው ካለ፥ ሥራውን ማቆም አለብን። ለመጠጣት የምንፈተን ከሆነ፥ ከመጠጥ ቤት አካባቢ መራቅ ኣለብን። ቪዲዮ ከክርስቶስ እያራቀህ ከሆነ ቪዲዮህን ሽጥና እንደገናም ቪዲዮ አትመልከት። ብዙ ገንዘብ በማግበስበስ ላይ ካተኮርን፥ ከሕይወታችን ውስጥ የገንዘብን ፍቅር ለማስወገድ ብርቱ ጥረት ማድረግ አለብን፥ ያለንንም ገንዘብ ለሌሎች ማካፈል ይገባል። ሕይወታችንን የተቀደሰ ለማድረግ ጥብቅ እርምጃ ዎችን መውሰድ አለብን። በኃጢአት ላይ ልል አቋም መያዝ በሕይወታችንና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ትልቅ መዘዝ ያስከትላል። ለኃጢአት ያለን አመለካከት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ስለሚያሳይ፥ በዘላለም ዕጣ ፈንታችን ላይ አደጋ ሊጥል ይችላል። ስለሆነም በኃጢኣት ላይ ጥብቅ አቋም በመውሰድ፥ አሁንም ሆነ በዘላለማዊው መንገድ ከክርስቶስ ጋር መልካም ግንኙነት ልናደርግ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ክርስቲያኖች ለኃጢአት ጠንካራ አቋም ያላቸው ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ለ) ክርስቲያኖች ከሕይወታቸው ውስጥ የኃጢአትን ኃይልና ፈተና ለመቀነስ ሊያደርጓቸው የሚችሏቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

ሐ) ስለ መፋታት የተነገረ ምሳሌ (ማቴ. 5፥1-32)። ጋብቻ የሁሉም ማኅበረሰብ ዋነኛ መሠረት ነው። የአንድ ቤተ ክርስቲያን ወይም ማኅበረሰብ ጥንካሬ የሚለካው በጋብቻ ጥንካሬ ነው። የጋብቻን መፍረስን ያህል የግለሰቦችን ሕይወት የሚያናጋ ነገር የለም። ለዚህም ነው ክርስቶስ ይህን አስፈላጊ ነገር ያነሣው። ከሰዎች ኃጢአተኝነት የተነሣ፥ እግዚአብሔር ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዲፈቱ ፈቀደ። ለምትፈታው ሚስት የፍችው የምስክር ወረቀት እንዲሰጣት የታዘዘው በገዛ ፈቃዷ እንዳልኮበለለች ማረጋገጫ ነበር። የሚያሳዝነው ብዙ አይሁዶች ይህን ቀዳዳ ተጠቅመው ደስ ባላቸው ቁጥር ሚስቶቻቸውን ያባርሩ ጀመር። ጋብቻ ባልና ሚስት እስኪሞቱ ድረስ ለዘለቄታው አብረው የሚኖሩበት ቃል ኪዳን ነው። ዳሩ ግን አይሁዳውያን ይህን ሕግ ይጥሱ ነበር (ዘፍጥ. 2፡24 አንብብ።)

ኢየሱስ ጋብቻ በእግዚአብሔር ዘንድ የተከበረ መሆኑን አመልክቷል። ለፍች አንድ ምክንያት ብቻ ነበር። ይህም ፍቺ ሊፈጸም የሚችለው የባል ወይም የሚስት ዝሙት አድርጎ መገኘት ነው። ይህ እግዚአብሔር ፍቺን የሚፈቅድበትን ሁኔታ ገለጸ እንጂ፥ ኢየሱስ ዝሙት ከተፈጸመ ተጋቢዎቹ መፋታት አለባቸው አላለም። ሚስቱን ፈትቶ ሌላ እንድታገባ የሚያደርግ ሰው ሁሉ ለዝሙት ይዳርጋታል። በዚህ ጉዳይ ላይ ክርስቶስ ባል ሚስቱን ወደ ዝሙት እንደ መራ አመልክቷል። በሰው ዐይን ብትፋታም፥ በእግዚአብሔር ዐይን አሁንም በጋብቻ ትኖራለች። ይህም ሴትዮዋ ከጋብቻ ውጭ ወሲብ የምትፈጽምበት ዐይነት ነው። ስለሆነም ክርስቶስ በባሏ ዘማዊነት ካልሆነ በቀር የተፋታችውን ሴት የሚያገባ ሰው ዝሙት እንደሚፈጽም ገልጾአል። [ክርስቶስ ስለዚህ የጋብቻ ጉዳይ በማቴ. 19፡3-21 ተጨማሪ ትምህርት ይሰጣል።]

ችግሩ ሰዎች ይህን ትእዛዝ ችላ በማለት ለፍቺ የተለያዩ ምክንያቶችን ያቀርባሉ። በምዕራቡ ዓለም የክርስቲያኖች ፍች ቁጥር እንደ ዓለማውያን የበዛ ነው። ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ተግተው በመሥራት ችግሮቻቸውን እንደ መፍታት፥ ከችግሮቻቸው ለመሸሽ ሲሉ ይፋታሉ።

ነገር ግን ክርስቲያኖች ሳይፋቱ ይህን ትእዛዝ በውጫዊ ገጽታው ሊጠብቁትና እግዚአብሔር ለጋብቻ የወጠነውን ዓላማ ላያሟሉ ይችላሉ። እግዚአብሔር በጋብቻ ሁለቱ ሰዎች አንድ እንደሚሆኑ ተናግሯል። ይህ በወሲብ ብቻ ሳይሆን፥ የቅርብ ጓደኝነትን፥ እውነተኛ ወዳጅነትን፥ እግዚአብሔርን ለማስደሰት አብሮ መሥራትን የሚገልጽ ነው። ምንም እንኳ ብዙ ክርስቲያን ባለትዳሮች ባይፋቱም፥ የሚጣሉ ከሆነ ወይም ባል ሚስቱን እንደ ዕቃ የሚቆጥራትና የማያከብራት ከሆነ፥ ትዳራቸው እግዚአብሔር የሚፈልገው ትዳር አይደለም።

መ. ስለ መሐላ የተነገረ ምሳሌ (ማቴ. 5፥3-37። በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሰዎች የሚናገሩትን አሳብ እውነተኛነት ለማጽናት ሲፈልጉ፥ «ኃይለ ሥላሴ ይሙት» ይሉ ነበር። አይሁዶችም ንግግራቸው እውነት መሆኑን ለማሳየት በመሐላ ያጻኑት ነበር። ብሉይ ኪዳን ስለ መሐላ ግልጽ አሳቦችን ይሰጣል። አንድ ሰው ለእግዚኣብሔር ወይም ለሌላ ሰው ከማለ ወይም ቃል ከገባ፥ ቃሉን የመጠበቅ ግዴታ ነበረበት (ዘጸኣት 20፡7፤ ዘሌዋ. 19፡12፤ ዘኁል. 30፡2፤ ዘዳግ. 5፡1፤ 6፡18፤ 23፡21-23)። መሐላ ጥብቅ በመሆኑ ዮፍታሔ መሐላውን ለመጠበቅ ሲል ሴት ልጁን ሠውቷል (መሳ. 1፡29-39)። ነገር ግን አይሁዶች በመሐላ ለመታሰር ስለማይፈልጉ፥ ብዙውን ጊዜ መሐላን በመጠቀም ሰዎች እንዲያምኗቸው ያታልላሉ። ስለሆነም መፈጸም ያለባቸውና የሌለባቸው ብለው መሐላዎችን በሁለት ይከፍላሉ። አንድ ሰው በእግዚአብሔር ስም ከማለ ሊያፈርሰው አይችልም። ነገር ግን በሰማይ፥ በምድር ወይም በኢየሩሳሌም ከማለ፥ መሐላው ሊፈርስ ይችላል።

ይህ ቃልን ስለ መጠበቅ እግዚአብሔር ደንቡን የሰጠበትን ምክንያት ሙሉ ለሙሉ አጥፍቶታል። ከእግዚአብሔር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስለሌለው ቃሉን ለመጠበቅ አልገደድም ማለቱ የእግዚአብሔርን ማንነት አለማወቅ ነው። እግዚአብሔር በሰማይ፥ በምድርም ሆነ በኢየሩሳሌም፥ በሁሉም ስፍራ ስለሚገኝ ከእነዚህ በአንዱ ስም መማሉ በእግዚአብሔር ስም የመማል ያህል ከባድ ነበር።

ምንም ይሁን ምን ሰው ቃሉን መጠበቅ አለበት። የክርስቶስ ተከታይ የሆነ ሰው መሐላውን ማፍረስ የለበትም። «አዎን» ካለ ከልቡ ማለት አለበት። «አይደለም» ካለም እንደዚሁ። ሰውን ለማታለል መማሉም ሆነ የገቡትን ቃል አለመጠበቁ የክፉ ነው። የክርስቶስ ዋነኛ ጉዳይ የመሐላ አጠቃቀም ሳይሆን፥ የግለሰቡ እውነተኛነት ነው። ቃላችን ሙሉ በሙሉ እንዲታመን ለማድረግ፥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን ሰዎች የሚምሉት ስለማይታመኑ ብቻ ነው! (የማይተማመኑ ባልንጀራሞች በየወንዙ ዳር ይማማላሉ) ሁላችንም እውነተኞች ብንሆን ኖሮ መሐላው በጭራሽ አያስፈልግም ነበር። ክርስቶስ አንድ ቀን ከአፋችን በሚመጣው ቃል ሁሉ እንደሚፈርድብን አስጠንቅቆናል (ማቴ 12፡36-3)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች የተስፋ ቃል ከሰጡ በኋላ የሚያፈርሱባቸውን ነገሮች በምሳሌ ጥቀስ። ለ) ሰዎች ተስፋ ሰጥተው ሳያከብሩት ሲቀሩ፥ ከዚያ በኋላ እነርሱን ለማመን የሚከብደን እንዴት ነው?

ለብዙዎቻችን ተስፋ መስጠት ቀላል ነው። ጠዋት በ 3 ሰዓት እመጣለሁ» እንልና እስከ 6 ሰዓት ወይም ቀኑን ሙሉ አንመጣም። የዚህ ውጤት ሌላ ጊዜ ስንቀጣጠር እምነት ያሳጣናል። «ለቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ 100 ብር እከፍላለሁ» እንልና የተናገርነውን መልሰን ኣናስታውስም። «በስድስት ወራት ውስጥ ብድሩን እንከፍላለን» እንልና ዕዳውን ለመክፈል ከማቀድ እንቆጠባለን ወይም ወደፊት ከረዥም ጊዜ በኋላ ለመክፈል እናስባለን። ቃላችንን ባጠፍን ቁጥር፥ ሰዎች እኛን የማመን አቅም አይኖራቸውም። የማይተማመኑን ደግሞ ቃላችንን ባልጠበቅንበት ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን፥ በሌሎችም ጭምር ነው። ቃላችንን ከጠበቅን ሰዎች ለአመራርም ሆነ ለገንዘብ ጉዳዮች ያምኑናል። ቃላችንን ከተጠራጠሩ ደግሞ በሌሎች ጉዳዮችም ላይ ይጠራጠሩናል።

ሠ. ስለ በቀል የተነገረ ምሳሌ (ማቴ. 5፡38-42)። በብሉይ ኪዳን ሕግ መሠረት፥ ቅጣቱ ከጥፋቱ ጋር መመጣጠን ነበረበት። ይህም መርሕ፥ «ጥርስ ለጥርስ፤ ዓይን ለዓይን» ይባል ነበር (ዘዳግ. 21፡23-25፤ ዘሌዋ. 24፡19-20)። በዓለም የተለመደው ብቀላ አንድ ሰው ከጎዳኝ የበለጠ እጎዳዋለሁ የሚል ነው። እግዚአብሔር ተጨማሪ ብቀላን ለመከላከል ሲል፥ ለበቀል ወሰን አበጅቷል። አንድ ሰው ሆን ብሎ ዓይኔን ቢያጠፋ፥ መልሼ ላደርግበት የምችለው ነገር ዓይኖቹን ማጥፋት ብቻ ነው። በቁጣ ተነሥቼ እጆቹን ልቆርጥ ወይም ልገድለው አልችልም። እግዚአብሔር ይህን ሲል በቀልን ማደፋፈሩ ሳይሆን፥ ድንበር መወሰኑ ነበር። አይሁዶች ግን በበቀል ኣስፈላጊነት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ ነበር።

ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ፍጹም በተለየ መርሕ እንዲመላለሱ ኣዝዟል። ለስምምነትና ለሰላም ስንል ብቀላን መተው ይኖርብናል። ብዙዎቹ ጦርነቶች የተቀሰቀሱት በድንገት አይደለም። ነገር ግን ጦርነት አንዱ አገር በሌላው ላይ የሚፈጽማቸው የበቀል ድርጊት ውጤት ነው። አንዱ አገር ለፈጸመበት አነስተኛ በደል ሌላው አገር እንዳይፈጸምበት ጌታ አስጠንቅቋል። ስለዚህ ኢየሱስ በእነዚህ አራት ምሳሌዎች አማካይነት ለተጨማሪ ወቀሳና በቀል ከመጋበዝ ይልቅ ፍቅርን ማሳየት እንዳለብን አስተምሯል። እነዚህ አራቱም ምሳሌዎች በቀዳሚነት የክርስቶስ ተከታዮች ለገዛ መብቶቻቸው ፍጹም የተለየ ዕድል ለመስጠት ኢየሱስ እነዚህን አራት መርሖዎች ኣራት ኣዳዲስ ትእዛዛት ለማድረግ አልሞከረም። ዓላማው በልጆቹ ውስጥ ለማየት የሚፈልገውን የልብ ዝንባሌ ለማሳየት ነበር። በዚህም (ኢየሱስ የሚናገረው ስለ ማኅበራዊ ፍትሕ ሳይሆን፥ ስለ ግለሰባዊ ጠቦችና ስደት ነው።)

  1. ስለ ኣካላዊ ጥቃት የተነገረ ምሳሌ። ብዙውን ጊዜ በጠብ ወቅት፥ አንዱ ሌላውን በጥፊ ሲመታው እርሱም የበኩሉን ምላሽ ይሰጣል። አይሁዶች በጥፊ መመታትን እንደ ትልቅ ስድብ ስለሚቆጥሩ፥ ይህን ያደረገውን ሰው ያስቀጡ ነበር። ምናልባትም ክርስቶስ ይህን የተናገረው ተከታዮቹ ብዙውን ጊዜ በሌሎች ስለሚበደሉ ይሆናል። የክርስቶስ መልእክት፥ «ሲበድሏችሁ ምላሽ ለመስጠት አትሞክሩ» የሚል ነበር። ደቀ መዛሙርት የበደሏቸውን ሰዎች ወደ ፍርድ ቤት ወስደው ከማስቀጣት ይልቅ፥ በቀልን በመተው ውስጣዊ ጥንካሬያቸውን እንዲያሳዩ አሳስቧቸዋል። ለበደል ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አለመስጠት የበለጠ የሥነ ምግባር ጥንካሬን ይጠይቃል። ለአካላዊ ጥቃት ኣለመበቀል በተበደለ ጊዜ ምንም ያልተናገረውን የክርስቶስን ምሳሌ መከተል ነው (ማቴ. 26፡67፤ ኢሳ. 50፡67፤ 1ኛ ጴጥ. 2፡23 እንብብ።)
  1. ስለ ፍርድ ቤት የተነገረ ምሳሌ። ክስ፥ በብሉይ ኪዳን ዘመን ገንዘብ የተበደረ ሰው መያዣ ያቀርብ ነበር። ለዋስትና በመያዣነት ከሚጠቀሙባቸው ነገሮች አንዱ ኮት (መጎናጸፊያ) ነበር። ኮት የድሃ ንብረት ከሆኑት ውድ ነገሮች አንዱ ነበር። ነገር ግን አንድ ሰው ሌላውን ሰው በፍርድ ቤት ከሶ እጀ ጠባቡን ሊወስድ ሲፈልግ፥ ክርስቶስ ተከሳሹ ኣንድ ተጨማሪ ምዕራፍ ተጉዞ ጠቡን ለማብረድ ይበልጥ ውድ የሆነውን ኮቱን እንዲሰጠው አስገነዘበ። የዓለም ሀብት ከግንኙነቶቻችን አንጻር ሲታይ ከንቱ መሆኑን ያሳያል።
  1. አስገድዶ ስለ ማሠራት የተነገረ ምሳሌ። በሮም ሕግ ወታደሮች በመንገድ ላይ ያገኙትን ማንኛውንም ሰው አስገድደው ሻንጣዎቻቸውን አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ለሚሆን ርቀት ለማሸከም መብት ነበራቸው፡፡ አንድን ሰው ከዚህ በላይ የሚያስገድዱበት ሕጋዊ ድጋፍ አልነበራቸውም። አይሁዶች ይህንን የአሕዛብ ጭቆና በመጥላታቸው ከሮማውያን ጋር የመዋጋት ፍላጎት ነበራቸው። ኢየሱስ ግን በጥላቻ የሕጉን ፊደል ከመከተል ይልቅ አንድ ምዕራፍ፥ በሕግ ከሚፈለገው በላይ በመሥራት ፍቅራቸውን እንዲያሳዩ አስገነዘባቸው። በዚህም ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ሌሎችን የማገልገል አመለካከት እንዲያዳብሩ ጥሪ ማድረጉ ነበር። የግዴታ ወይም የሚጠበቅብንን ብቻ የምናደርግ ከሆነ፥ ሁሉም ሰው ከሚያከናውነው የተሻለ ተግባር ልንፈጽም አንችልም። ነገር ግን ሌሎች ከሚሠሩት የበለጠ የመሥዋዕትነት ተግባር ብናከናውን፥ የተለየን ሰዎች መሆናችንን እናሳያለን። ሌሎችን ማገልገል ከመብታችንና ከምቾታችን ይበልጣል።
  1. ለሚጠይቅ ሁሉ ስለ መስጠት የተነገረ ምሳሌ። የክርስቶስ ተከታዮች በልግስናቸው መታወቅ አለባቸው። እግዚአብሔር የሰጠንን በረከቶች በነፃ በማካፈል በችግር ላይ ያሉትን ወገኖች መርዳት ይኖርብናል። የሌሎችን ፍላጎቶች ከራሳችን ማስቀደም አለብን። ይህንን ከሌሎች ሁለት አሳቦች ጋር ሚዛናዊ ማድረግ አለብን። በመጀመሪያ፥ ይህ ለመተዳደሪያነት የማያስፈልገንን ነገር በራስ ወዳድነት ለመጠየቅ ማመኻኛ ሊሆንን አይገባም። ይህ ለሌላው ሰው ፍቅርን ሳያሳይ የራስ ወዳድነትን ተግባር መፈጸም ይሆናል። ሁለተኛው፥ ይህ ማለት አንድ ነገር ለሚጠይቀን ሰው ሁሉ የመስጠት ግዴታ አለብን ማለትም አይደለም። በምሳሌ 11፡5፤ 17፡18፤ 22፡26 ላይ የተሳሳተ ልግስና አሰጣጥ ተገቢ አለመሆኑ ተገልጾአል። ነገር ግን ነገሮችን በማገናዘብ እውነተኛ ችግር ላይ ላሉትና በማስተዋል ሊጠቀሙ ለሚችሉ ሰዎች መስጠት አለብን። ተግባርቅብንንንቋያዳብሩክርስቶስ ስቃይ ባሕጉን ማውያልነበራችው።

ረ. ጠላትን ስለ መውደድ የተነገረ ምሳሌ (ማቴ. 5፡43-48)። ብሉይ ኪዳን አንድ አይሁዳዊ ባልንጀራውን (ሌላውን አይሁዳዊ) እንዲወድ ያዝዛል (ዘሌዋ. 19፡18)። ኣይሁዶች ያልሆኑትን ሰዎች እንዲወዱ የሚጠይቅ ትእዛዝ እልነበረም። ምናልባትም «ጠላትን መጥላት» የሚለው ሐረግ የመጣው ከሁለት ምንጮች ሳይሆን አይቀርም። በመጀመሪያ፥ አሴናውያን በማኅበረሰባቸው ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ እንደሚወዱና ከዚያ ውጭ ያሉትን ሁሉ እንደሚጠሉ ኣስተምረው ነበር። ሁለተኛው፥ አብዛኞቹ ኣይሁዶች አሕዛብንና የአገራቸው ከዳተኞች የሆኑትን ሁሉ መጥላት እንዳለባቸው ያምኑ ነበር። ስለሆነም በብሉይ ኪዳን ውስጥ በግልጽ ባይጠቀስም፥ ጠላትን መጥላት በክርስቶስ ዘመን በነበሩ አይሁዶች ዘንድ የተለመደ ግንዛቤ ነበር።

ክርስቶስ ግን ደቀ መዛሙርቱ የተለየ አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልጾኣል። የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን የተለየ መርሕ መከተል አለብን። እግዚአብሔር ዓለምን በሚወዳቸውና በሚጠላቸው ሕዝቦች አልከፈለም። እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ ይወድዳል። ለሰዎች ሁሉ ማለትም በእርሱ ላይ ለሚያምፁ ሁሉ እንደ ዝናብ ዓይነቱን በረከት በመስጠት ፍቅሩን ይገልጻል። በተጠሉት ቀራጮች ምሳሌነት የተገለጹት እጅግ ክፉ ኃጢአተኞች እንኳን ለተወሰኑ ሰዎች ፍቅራቸውን ያሳዩ ነበር። የክርስቶስ ተከታዮች በተግባራዊ መንገዶች ፍቅራቸውን በማሳየት፥ ጠላቶቻቸውን እንደሚወዱና የተለዩ ሕዝቦች እንደሆኑ ማረጋገጥ ያስፈልጋቸው ነበር። የሚጠሉንን ከመጥላትና ልባችን በመራርነት እንዲሞላ ከማድረግ ይልቅ፥ እግዚአብሔር እንዲባርካቸውና እንዲለውጣቸው መጸለይ ይኖርብናል። (ክርስቶስ ለተሰቀሉት ሰዎች ይቅርታን በመጸለዩ ይህንን ተግባራዊ አድርጓል።) እግዚአብሔር በልባችንና በአመለካከታችን ላይ እንዲገዛ መፍቀዳችን ከሚረጋገጥባቸው ዐበይት መንገዶች አንዱ፥ ሊጎዱን የሚፈልጉንን ሰዎች የምናስተናግድበት መንገድ ነው። (በዚህ ስፍራ ‹መውደድ› የሚያመለክተው ስሜታዊ ፍቅርን የሚያሳይ አይደለም። ነገር ግን የጎዳንን ሰው ላለመበቀል ወይም ላለመጥላት የምንወስደው ተግባራዊ እርምጃ ነው።)

ክርስቶስ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ባሕርይ ያቀረበውን ትምህርት፥ «የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ» በማለት ኣጠቃሏል። ‹ፍጹም› የሚለው ቃል ‹በሳል› ወይም ‹እንከን የለሽ› ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። በብሉይ ኪዳን ምንም ዓይነት ጉድለት የሌለባቸው ለመሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሳት ፍጹም ይባሉ ነበር። ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብን ያህል ከኃጢአት የጸዳን እንድንሆን እየጠየቀን አይደለም። ያ የማይቻል ነገር ነው። ነገር ግን ክርስቲያኖች በተግባራችን ሁሉ በእግዚአብሔርና በሰዎች ፊት እንከን የለሽ መሆን እንዳለብን መግለጹ ነው። እንከን የለሽ ለመሆን ውጫዊ ሕግን በመጠበቁ ላይ ማተኮር የለብንም። የተለመዱትን የኩራት፥ የበቀል፥ የኃጢአተኝነት፥ የቁጣ አመለካከቶቻችንን ማሸነፍ አለብን። ባሕርያችንን ለማሻሻል ተግተን መሥራት አለብን። እንደ ክርስቲያኖች፥ ራሳችንን ለመጠበቅና ለመጥቀም ያለንን መብት መተው አለብን። ለቁሳዊ ሀብት ያለንን ፍቅርና በሚጎዱን ሰዎች ላይ ያለንን የጥላቻ ስሜት ማስወገድ አለብን። ክርስቶስ መመዘኛውን መሥርቷል። እኛስ ከሕይወታችን ጋር እያዛመድነው ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስ መለወጥ እንዳለብን የተናገራቸውን ሁለት የውስጣዊ አመለካከቶች ምሳሌ ዘርዝር። ለ) በሥጋ ሕጉን እየጠበቅን እንዴት ክርስቶስ ከተከታዮቹ የሚፈልጋቸውን አመለካከቶች ልንጥስ እንደምንችል፥ ለእያንዳንዱ ማብራሪያ ሁለት ምሳሌዎችን በመስጠት አስረዳ። ሐ) ዛሬ ክርስቲያኖች በእነዚህ ስድስት ምሳሌዎች የክርስቶስን ትምህርት እንዴት ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ለእያንዳንዱ ምሳሌ ሁለት ምሳሌዎችን ስጥ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: