ማቴዎስ 14፡1-36

ማቴዎስ  14፥ የክርስቶስ አገልግሎት ረዥሙ ዕለት በመባል ይታወቃል። በአንድ ቀን ክርስቶስ ታላላቅ ተቃውሞዎችና ፈተናዎች እጋጥመውታል። የአክስቱ ልጅና የመንሥቱ ኣገልጋይ የነበረው መጥምቁ ዮሐንስ ተገደለ። ክርስቶስ ምንም እንኳ ድካም ቢሰማውና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብቻ ለመሆን ቢፈልግም፥ ብዙ ሰዎች ስለሚከተሉት ለራሱ ጊዜ አላገኘም፤ አምስት ሺህ ሰው መገበ። ከዚያ በኋላ ግን ደቀ መዛሙርቱ ማዕበል በበረታባቸው ጊዜ በእርሱ አለማመናቸውን ታዘበ። ከዚያም አሳዛኝ ነገሮች ደረሱበት። ነገር ግን ክርስቶስ የአባቱን ድምፅ ይሰማ ስለነበር፥ እነዚህን ነገሮች የእግዚአብሔርን ፍላጎት ለማሟላቱ ተግባር እውሏቸዋል። ይህ ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ላይ ይደርሳል። ሰዎች ሲሞቱ፥ በኃጢአት ሲወድቁ ወይም እምነታቸውን ሊተዉ በከፍተኛ ደረጃ እንከፋለን። የራሳችን ዕቅዶች ቢኖሩንም፥ በጊዜ ሰሌዳቸው መሠረት አይከናወኑም። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በዚህ ምክንያት ሊቆጡ ወይም ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። ነገር ግን በእያንዳንዱ ተስፋ መቁረጥና ችግር ውስጥ የእግዚአብሔርን እጅ ማየቱ ከሁሉም የበለጠ ነው።

  1. የመጥምቁ ዮሐንስ አንገት በሰይፍ ተቀላ (ማቴ. 14፡1-12)

የብሉይ ኪዳን የመጨረሻው ታላቅ ነቢይ የነበረው መጥምቁ ዮሐንስ፥ ለረዥም ጊዜ ታስሮ ቆየ። ከዚያም በንጉሥ ሄሮድስ ቤተሰብ ተንኮል ምክንያት ሞት ተፈረደበት። ዮሐንስ የታሰረው የእግዚአብሔርን ቃል እየተናገረ የባለሥልጣናትን ሰላም እንዳይነሣ በማሰብ ነበር። ለእምነቱ መከራ ተቀብሎ ሞተ።

ይህ ሁኔታ ክርስቶስን በከፍተኛ ደረጃ ሳያሳዝነው አልቀረም። ይህ ድርጊት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢኣት ተቃውመው የተናገሩትን ነቢያት ከገደሉት የብሉይ ኪዳን አይሁዶች የተለየ አልነበረም። ይህንኑ የመሰለ የጭካኔ ተግባር ከኣንድ ዓመት በኋላ በክርስቶስ ላይ ሊደርስ ነው። ይህ ሁኔታ ክርስቶስን ለመከተል በሚመርጡ ሰዎች ላይም ስለሚደርሰው አደጋ የሚያስተላልፈው መልእክት አለው። እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ሕዝቡን ከሞት ቢያድንም (የሐዋ. 12፡6-11)፥ ስለዚህ በሌሎች ጊዜያት መከራ ተቀብለው እንዲሞቱ የሚፈቅድበት ጊዜ አለ (የሐዋ. 7፡54-60)።

  1. ክርስቶስ አምስት ሺህ ሰዎችን መገበ (ማቴ. 14፡13-21)

ክርስቶስ የአክስቱ ልጅ በሆነው መጥምቁ ዮሐንስ ላይ ስለደረሰው የሞት አደጋ ከሰማ በኋላ፥ ለመጸለይና ለማሰላሰል የተወሰነ ጊዜ ፈለገ። ነገር ግን በጀልባ ለጥ ወዳለ ስፍራ ለመሄድ በፈለገ ጊዜ፥ ከአምስት ሺህ በላይ የሆኑ ሰዎች (ማለትም ተጨማሪ አምስት ሺህ ሴቶችና ልጆች) ይከተሉት ጀመር። ክርስቶስ ለግል ጊዜው አክብሮት ባለመስጠታቸው ወይም ራስ ወዳድ በመሆናቸው ሊቆጣቸው ይችል ነበር። ማቴዎስ እንደሚነግረን ግን፥ ክርስቶስ የግል ሥቃይ ቢኖርበትም ለሕዝቡ ከመራራት አልታቀበም። ስለሆነም፥ ቃሉን በማስተማር፥ የታመሙትን በመፈወሰ፥ እንዲሁም ረሃብተኞችን በመመገብ ረዳቸው። (ክርስቶስ አምስት ሺህ ሕዝብ የመገበበት ተአምር በአራቱም ወንጌላት ውስጥ ከተመዘገቡት ጥቂት ተአምራቶች አንዱ ነው።)

ነገር ግን ክርስቶስ እንክብካቤውን ያሳየው ለሕዝቡ ብቻ አልነበረም። ለደቀ መዛሙርቱም እነርሱንና ያላቸውን ጥቂት ሀብት በመጠቀም፥ የሰዎችን ፍላጎት ሊያሟላ እንደሚችል አስተምሯቸዋል። ክርስቶስ ይህ በራሳቸው ሊወጡ የማይችሉት ተግባር መሆኑን እያወቀ ደቀ መዛሙርቱ ሕዝቡን እንዲመግቡ ነገራቸው። ይህን የተናገረው የማይቻል ነገር ሊያደርጉ እንደሚችሉ ለማስተማር ነበር። ወደ እርሱ ከተመለሱ እነርሱንና ሀብታቸውን በመጠቀም ከችሎታቸው የላቀ ተግባር ሊያከናውን ይችል ነበር። ከዚህ ክፍል የሚከተሉትን እውነቶች ልንመለከት እንችላለን።

ሀ. ደቀ መዛሙርቱ ሕዝቡን እንዲመግቡ የተናገረው ክርስቶስ ነበር። በዚህም ክርስቶስ ፍላጎታቸውን እንዲያሟላ እያስገደዱት አልነበሩም። ሰዎች የማይቻል ተግባር ለመፈጸም የሚሞክሩባቸው ሁለት አማራጮች አሉ። በመጀመሪያ፥ የእግዚአብሔር ልጆች አንድ ታላቅ ነገር (ለምሳሌ፥ አዲስ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ) የሚፈልጉባቸው ጊዜያት አሉ። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ እነሣሽ ምክንያታቸው በራስ ወዳድነት ስሜት የጎደፈ ነው። ለምሳሌ ያህል ትልቅ ቤተ ክርስቲያን በመገንባት ለራሳችንና ለቤተ ክርስቲያናችን የበለጠ ክብር እንደምናመጣ ልናስብ እንችላለን። እግዚኣብሔርን ሳይጠይቁ ወይም እምነታቸውን የሚፈትነው እግዚአብሔር መሆኑን ሳያረጋግጡ ክርስቲያኖች የሕንጻውን ሥራ ይጀምሩና እግዚአብሔር ፍላጎታቸውን እንዲያሟላላቸው ይጠይቃሉ። ብዙውን ጊዜ የዚህ ዓይነቱ እምነት ለሰዎቹም ሆነ ለእግዚአብሔር ስም ኃፍረትን ያስከትላል። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር ሰዎች አንድን የማይቻል ተግባር እንዲፈጽሙ በግልጽ የሚናገርባቸው ጊዜያት አሉ። ይህ በእግዚአብሔር ተማምነን እርሱ ሊሠራ የሚችለውን የምንመለከትበት መልካም አጋጣሚ ነው።

ለ. በማይቻሉ ሁኔታዎች ውስጥ እግዚአብሔር የራሱን ታላቅነት እንድንረዳ ለማገዝ ይፈልጋል። በራሳችን ሀብት የምንችለውን ብቻ የምናደርግ ከሆንን፥ የእግዚአብሔርን እገዛ እንፈልግም። እምነታችንም አይፈተንም። የእግዚአብሔርን እጅ በሥራ ላይ ልንመለከት የምንችለው እግዚአብሔር የማይቻለውን እንድናደርግ በሚጠይቀን ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ሰው እንደተናገረው፥ እግዚኣብሔር የማይቻል ነገር የሌለበትን ተግባር ለእርሱ እንድንፈጽም አይጠይቀንም። በዚህ ጊዜ ብቻ ነው ውጤቱ የእግዚአብሔር እንጂ የእኛ የማይሆነው።

ሐ. እግዚአብሔር አንድን ታላቅ ነገር እንድንሠራ በሚጠይቀን ጊዜ፥ ካለን ነገር ይጀምራል። እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ ከባዶ አይጀምርም። ክርስቶስ የማይቻለውን አምስት ሺህ ሰዎችን የመገበው በደቀ መዛሙርቱ እጅ በነበረው ጥቂት እንጀራና ዓሣ አማካኝነት ነበር፡፡ በመጀመሪያ ደቀ መዛሙርቱ ያላቸውን ለእርሱ መስጠት ነበረባቸው። እግዚአብሔር በራስ ወዳድነት ሀብታችንን የሙጥኝ ብለን፥ «እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተው አድርገው» በምንልበት ጊዜ ለመሥራት አይፈልግም። እግዚአብሔር ሕዝቡ ያለውን እንዲሠዋ ይሻል። ከዚያም የመፍትሔው አካል እንድንሆን ይፈቅድልናል። ነገር ግን፥ «ይህ የማይቻል ነገር መሆኑ ግልጽ ነው። ስለሆነም፥ የምችለውን አደርጋለሁ፥ ላደርገው የምችለውም ይህንኑ ብቻ ነው» ከሚል አመለካከት መቆጠብ አለብን። ያለንን ከሰጠን በኋላ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚሠራ መጠባበቅ አለብን።

መ. እግዚአብሔር የልጆቹን ፍላጎት የሚያሟላው በሚያገለግሉበት ወቅት ነው። ብዙውን ጊዜ ግን ሥራውን ከመጀመራቸው በፊት ፍላጎታቸውን አያሟላላቸውም። ደቀ መዛሙርቱም ተርበው ነበር። ምግብ ስጠንና ከበላን በኋላ የተረፈውን ለሰዎች እንሰጣለን ሊሉ ይችሉ ነበር። ክርስቶስ ግን ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ለሰዎች ከሰጡ በኋላ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ እያንዳንዳቸው አንድ ቅርጫት ምግብ ያገኙት (12 ቅርጫት ምግብ ስለ ተረፈ) የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት ከሰጡ በኋላ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፣ ሀ) ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሳይጠይቁ ወይም በራስ ወዳድነት ምክንያቶች አንድን ነገር ሊጀምሩ የሚችሉባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) እግዚአብሔር አንድ የማይቻል ተግባር እንድትፈጽም ከጠየቀህ በኋላ በታዘዝኸው ጊዜ እንዴት ፍላጎትህን እንዳሟላ የሚያስረዱትን ምሳሌዎች ዘርዝር። ሐ) ከዚህ ስለ መታዘዝና የእግዚአብሔር ቸርነት የምንማራቸው ሌሎች ትምህርቶች ምንድን ናቸው?

ማቴዎስ ክርስቶስ እንደ መሢሕና ፈጣሪ የሕዝቡን ሥጋዊ ፍላጎቶች እንዳሟላ ገልጾአል። እግዚአብሔር በምድረ በዳ ውስጥ በሙሴ አማካኝነት ለሕዝቡ ምግብን እንደ ሰጣቸው ሁሉ፥ ክርስቶስም በተአምር የሕዝቡን ፍላጎቶች ለማሟላት ችሏል። በተጨማሪም ማቴዎስ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ስለሚበሉት ምግብ መጨነቅ እንደሌለባቸው ተናግሯል። ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን ፍላጎት ያሟላል።

  1. ክርስቶስና ጴጥሮስ በውኃ ላይ ተራመዱ (ማቴ. 14፡22-36)

ክርስቶስ ኅዘን በደረሰበት ጊዜ ሳይቀር ተግባሩን ለመቀጠል ኃይልን ከየት አገኘ? ይህን ኃይል ያገኘው ከእግዚአብሔር ጋር ካሳለፈው የግል የጸሎት ጊዜ ነበር። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ይወዳቸው የነበረ ቢሆንም፥ በተለይም ብዙ ሠርቶ በደከመና ችግር በደረሰበት ወቅት ከእግዚአብሔር ጋር የግል ጊዜ የማሳለፉን ጠቀሜታ ተገንዝቦ ነበር። ስለሆነም፤ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን በጀልባ ከሰደዳቸው በኋላ፥ ለብቻው ወደሚጸልይበት ስፍራ ሄደ። ከሌሎች ሰዎች ጋር መጸለይ መልካም ነው። ነገር ግን የግል ጊዜ ወስደን እግዚአብሔር በቃሉ ሲናገር ካላዳመጥንና ወደ እርሱ ካልጸለይን፥ ፍሬያማ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ልንሆን እንደማንችል ከክርስቶስ ምሳሌነት እንማራለን፡፡

ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱን በጀልባ የላከበት ሌላም ምክንያት ነበር። ክርስቶስ በእርሱ ላይ የነበራቸውን እምነት ለመፈተን ፈልጎ ነው። ክርስቶስ ማዕበሉ እንደሚነሳ ቢያውቅም፣ ደቀ መዛሙርቱን ወደዚያው ላካቸው። ሕይወት ዘመናቸውን በሙሉ በውኃ ላይ ቢያሳልፉም፥ ክርስቶስ ዓሣ አጥማጆቹ ከማዕበሉ የማያመልጡበትን ሁኔታ አደረገ።

ቀደም ሲል እርሱ በማዕበል ውስጥ አብሯቸው ነበር። በዚህ ጊዜ በማዕበል ውልጥ ብቻችንን ነን ብለው ያስቡ ነበር። በማዕበሉ መካከል ክርስቶስ እየተራመደ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ። ጴጥሮስ ክርስቶስ በውኃ ላይ ሲራመድ ባየ ጊዜ፥ እንደ እርሱ ለማድረግ ፈለገ። ክርስቶስም ጴጥሮስ በውኃ ላይ እየተራመደ ወደ እርሱ እንዲመጣ ጠራው። ጴጥሮስ ክርስቶስን እየተመለከተ በውኃው ላይ ከተራመደ በኋላ፥ ማዕበሉንና ነፋሱን ሲያይ መስመጥ ጀመረ። ክርስቶስ ግን በፍጥነት ኣዳነው። ክርስቶስ ወደ ጀልባይቱም ሲገባ ማዕበሉ ጸጥ አለ።

ማቴዎስ ይህን ታሪክ የጨመረው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ፥ ታሪኩ የክርስቶስን ኃይል ያሳያል። ክርስቶስ በውኃ ላይ በመጓዙና ማዕበሉን ጸጥ በማሰኘቱ፥ በተፈጥሮ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው አሳይቷል። እንዲህ ዓይነት ኃይል ያለው እግዚአብሔር ብቻ በመሆኑ፥ ኣይሁዶች ስለ ክርስቶስ ኃይል ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር። ይህን የክርስቶስን ታላቅ ኃይል ካዩ በኋላ፥ ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ከሰው በላይ መሆኑን ተረድተዋል። ክርስቶስ አምላክ ስለሆነ (አንድን ሰው ወይም ጣዖት ማምለኩ የማይታሰብ ቢሆንም)፥ ራሶቻቸውን ዝቅ አድርገው «የእግዚአብሔር ልጅ» ለሆነው ክርስቶስ ሰግደዋል።

ሁለተኛ፥ ማቴዎስ በሕይወት ውስጥ የሚነሡ ማዕበሎች ከእግዚአብሔር ፈቃድ መውጣታችንን የሚጠቁሙ ሳይሆኑ፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ መሆናችንን የሚያሳዩ መሆናቸውን ያስተምረናል። ደቀ መዛሙርቱን ወደ ማዕበሉ የሰደዳቸው ራሱ ኢየሱስ ነበር። ኢየሱስ ስለምንጋፈጣቸው ማዕበሎች ያውቃል። ክርስቶስ ማዕበሉ እንዳይነሣ ማድረግ ይችል ነበር። ነገር ግን እምነታችን የሚያድግበት ብቸኛው መንገድ በፈተና አማካኝነት ስለሆነ ይህን አላደረገም። ማዕበል በሚያውከን ጊዜ ክርስቶስን በአዲስ መንገድ እናየዋለን። እጅግ በፈለጉት ጊዜ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ለመርዳት ከተፍ አለ። ማቴዎስ የእምነት ዓይኖቻችንን በክርስቶስ ላይ እስካደረግን ድረስ፥ ችግሮች በሚመጡበት ጊዜ በማዕበሉ ውስጥ እንድናልፍ ክርስቶስ እንደሚረዳን አሳይቷል። ነገር ግን በማዕበሉ ላይ ትኩረት አድርገን በምንፈራበት ጊዜ እንሸነፋለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በሕይወትህ ውስጥ ስለ ተከሰተ ስለ አንድ ማዕበል ግለጽ። ማዕበሉ አሸነፈህ ወይስ ስለ ክርስቶስ የበለጠ እንድትማር አደረገህ? እብራራ። ለ) እንድናድግና ማዕበሉን እንድናሸንፍ የሚረዱን ነገሮች ምንድን ናቸው? በማዕበል እንድንሸነፍ የሚያደርጉንስ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: