ማቴዎስ 18፡1-14

እጅጉ በጣም የተከበረ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባል ነበረ። ሁልጊዜም ችግር የሚገጥማቸውን ሰዎች ከመርዳት አይቆጠብም ነበር። በጽጻት፥ ወንበሮችን በማስተካከል፥ በሌላም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተግቶ ያገለግል ነበር። በዚህ አገልግሎቱ ምክንያት ለሽምግልና አገልግሎት ተመረጠ። ከዚያ በኋላ ግን ባሕርዩ ተቀየረ፡፡ እንደ በፊቱ ሰዎችን በመርዳት ፈንታ ማዘዝ ጀመረ። አሳቡን የሚቀናቀን ሰው ሁሉ ያበሳጨው ጀመር፡፡ የሽምግልና ሥልጣኑን የሚያጠናክርባቸውን መንገዶችና፥ በሥልጣኑ ራሱንና ቤተሰቡን የሚረዳባቸውን ስልቶች መወጠን ጀመረ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሥልጣን ካገኙ በኋላ፥ ባሕሪያቸው የሚቀየረው በምን መንገዶች ነው? ለ) ይህ የሚሆነው ለምን ይመስልሃል?

ቀደም ብለን ማቴዎስ በአምስት የማስተማሪያ ክፍሎች ላይ እንደሚያተኩር ገልጾልናል። የመጀመሪያው ማቴዎስ 5-7 ነው። ቀጣዩ በምዕራፍ 3 የቀረቡትን ብዙ ምሳሌዎች ይይዛል። ሦስተኛው ማቴዎስ 18 ሲሆን፥ በደቀ መዝሙርነት ላይ ያተኩራል።

  1. ኢየሱስ ስለ መሪነትና በእግዚአብሔር መንግሥት ታላቅ ስለ መሆን አስተማረ (ማቴ. 18፡1-9)።

ደቀ መዛሙርቱ ባለማቋረጥ ከሚነጋገሩባቸው ጉዳዮች ኣንዱ፥ በክርስቶስ መንግሥት ታላቅ መሪ ስለ መሆን ነበር። ክርስቶስ አልፎ በተሰጠባት ምሽት እንኳ፥ ስለዚህ ጉዳይ ይነጋገሩ ነበር። (ሉቃስ 22፡24-30 ኣንብብ።) ማቴዎስ የተሳሳተ የመሪነት ግንዛቤ ለቤተ ክርስቲያን እጅግ አደገኛ ከሆኑት ነገርች አንዱ መሆኑን በመገንዘብ፥ ክርስቶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አመራር የገለጻቸው የተለያዩ ታሪኮችን በወንጌሉ ውስጥ አካትቷል። በኣይሁድ ባሕል የአንድን ሰው የሥልጣን ደረጃ ማወቁ አስፈላጊ ነበር፡፡ አይሁዶች ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ከእነርሱ በላይ የተከበረ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ይፈልጉ ነበር፡፡ ስለሆነም ደቀ መዛሙርት፥ ክርስቶስ በመንግሥቱ ውስጥ ያላቸውን ደረጃ ከታላቁ እስከ ታናሹ በመግለጽ፥ ማንን እንደሚያከብሩና ማን እንዲያከብራቸው ለማወቅ ጠየቁት።

ኢየሱስ የእርሱ የአመራር መንገድ ሙሉ በሙሉ ከዓለም የተለየ እንደሆነ ገለጸላቸው። የእርሱ አመራር ኃይልና ሥልጣን የሚንጸባረቅበት ሳይሆን፥ ትሕትና ራስ ወዳድ አለመሆንና ፍጹም መተማመን የሚሰፍንበት እንደሆነ አብራራላቸው። ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዴት መግባት እንዳለብን ለማሳየት፣ ልጆችን እንደ ምሳሌ አድርጎ አቅርቦላቸዋል። የክርስቶስ መንሥት አባል ለመሆን የሚፈለግ ሰው፣ መሠረታዊ እሴቶቹን መቀየር አለበት። ዛሪ በብዙ አገሮች እንደሚታየው በአይሁድ ኅበረሰብ፥ ልጆች ብዙም ትኩረት አይሰጣቸውም ሰዎች ልጆችን ቢወዱም፥ ከእነርሱ ጋር በመነጋገር፣ በማስተማር ወይም አሳባቸውን በመስማት ብዙ ጊዜ አያጠፉም «ልጅ ምን ሊያስተምረኝ ይችላል?» ብለው ያስባሉ።

ነገር ግን ልጆች በእግዚአብሔር መንግሥት መሠረታዊ የሆኑ ሁለት ብቃቶች አሏቸው። በመጀመሪያ፣ ሙሉ በሙሉ በሰዎች ይተማመናሉ። አንድ ልጅ አንድን ሰው ካወቀና ካመነ፥ ሁልጊዜም ከልቡ ያምነዋል። ትንሽ ልጅ የሚያምነው ሰው እንደሚይዘው ካወቀ ከዛፍ ላይ እንኳ ያለፍርሃት ሊዘልል ይችላል። የእግዚአብሔር ልጆችም በክርስቶስና በሰማያዊ አባታችን ላይ ፍጹማዊ እምነት ሊኖራቸው ይገባል። ሁለተኛ፥ ትንሽ ልጅ ለማኅበራዊ ሥልጣን ግድ የለውም ትንሽ ልጅ ታላቅ ወይም ታናሽ መሆኑ፥ ማን ትልቅ ወይም ትንሽ መሆኑ፣ የየትኛው ጎሳ አባል መሆኑ እያስጨንቀውም። በትንሽ ልጅ አመለካከት አስፈላጊው ነገር የፍቅር ግንኙነት መኖሩ ብቻ ነው። በእግዚአብሔር መንግሥትም፣ አስፈላጊው ጉዳይ ብዙ ሥልጣን ወይም የሌሎችን እክብሮት መሻት ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን መውደድና እርስ በርስ መዋደድ ነው። ማኅበራዊ የሥልጣን ደረጃ በዓለም አስፈላጊ ቢሆንም፥ በቤተ ክርስቲያን ስፍራ የለውም፡፡ እግዚአብሔር መማር አለመማራችንን ነጋዴ ወይ ገበሬ መሆናችንን፥ የተራ ወይም የንጉሥ ቤተሰብ መሆናችንን፥ አይጠይቅም። እነዚህ ሁሉ አስፈላጊዎች አይደሉም። አስፈላጊው የእዚአብሔር ቤተሰብ አካል መሆናችን ነው፡፡

ኢየሱስ ልጆችን በምሳሌነት በመጠቀም በሁለት ደረጃዎች አማካይነት ተናሯል። በመጀመሪያ፣ ስለ ሥጋዊ ልጆች ተናገሯል። በቤተ ክርስቲያን ወላጆችና አዋቂ ሰዎች ልጆችን ችላ ማለት የለባቸውም። ልጆች በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው። ስለሆነም በአንድ ሰው መጥፎ ቃላት፥ ተግባራት ወይም የማስተማር ጉድለት ትንሽ ልጅ ከእግዚአብሔር ከራቀ፥ እግዚአብሔር አሰናካዩን ሰው በኃላፊነት በመጠየቅ ይፈርድበታል። ኢየሱስ ስለዚህ ጠንካራ አገላለጽ ተጠቅሟል። ይህ ኃጢአት በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት በጣም ከባድ ነው፥ ይህን ኃጢአት በልጆች ላይ የሚፈጽሙ ወፍጮ በአንገቱ ላይ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ወይም ሰውነትን ከመቆረጥ የከፋ ቅጣት እንደሚያስከትል ገልጾአል።

በዓለም ሁሉ ከሚገኙ ክርስቲያኖች ከ80 እጅ በላይ የሚበዙት በክርስቶስ ያመኑት፣ ከ15 ዓመት ዕድሜያቸው በፊት ነው። ይህም ሆኖ በአብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ለዚህ የዕድሜ ክልል ትኩረት ሲሰጥ አይታይም፡፡ ትናንሽ ልጆች ገና በስሜት የሰከኑ አይደሉም። ስለሆኑም፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር ካላሳየናቸውና የማመን ዕድል ከነፈግናቸው ወይም አዋቂዎች ለእግዚአብሔር እንዴት እንደሚኖሩ ካላሳዩዋቸው፥ በቀላሉ ከእግዚአብሔር ፊታቸውን ሊያዞሩ ይችላሉ። ነገር ግን በአዋቂዎች ላይ ጥሩ ምሳሌዎችን ከተመለከቱ፥ በፍጥነት ሊያምኑና እንደ ሳሙኤል ከልጅነታቸው ጀምር እግዚአብሔርን ሊያገለግሉ ይችላሉ (1ኛ ሳሙ. 2-3)።

ሁለተኛ፥ ይህ በቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ምእመናን (እነርሱም ለእግዚአብሔር እንደ ትናንሽ ልጆች በመሆናቸው) መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት ጠቃሚ ትምህርት ይሰጣል። መሪዎች ምእመናንን የሚያስተናግዱበት ሁኔታ በጣም አስፈላጊ ነው። መሪዎች በቃላቸው፥ በተግባራቸው ወይም በአመለካከታቸው፥ እነዚህ መንፈሳዊ ልጆች ከእምነት እንዲመለሱና በኃጢአት እንዲወድቁ ካደረጓቸው፥ የእግዚአብሔር ቅጣት ያይልባቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች (በቤተ ክርስቲያን ሳይቀር) ብዙ ኣዋቂዎች ለልጆች ካላቸው አመለካከት፣ የኢየሱስ የሚለየው እንዴት ነው? ለ) እግዚአብሔር ለልጆች ያለው ፍቅር ተግባራዊ ይሆን ዘንድ፤ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ሊካሄዱ የሚገባቸው ለውጦች ምንድን ናቸው? ሐ) የኢየሱስ አመለካከት ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መንፈሳዊ ልጆችን (ምእመናን) ከሚያስተናግዱበት ሁኔታ የሚለየው እንዴት ነው? መ) ኢየሱስ ከቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ከአመለካከቶቻቸው ምን ዓይነት ለውጥ የሚፈልግ ይመስልሃል?

  1. እግዚአብሔር ለአንድ የጠፋ በግ ላይቀር ይገደዋል (ማቴ.18፡10-14)

የአንድ ልጅ ወይም የኣንድ አዲስ ክርስቲያን ከእምነቱ ወደ ኋላ መመለስ፥ ክርስቶስን ምን ያህል ያሳስበው ይሆን? በቤተ ክርስቲያናችን ሌሎች ብዙ ሰዎች ካሉ መጨነቅ አለብን? ብዙውን ጊዜ ዓለማዊ የቤተ ክርስቲያን መሪና፥ መንፈሳዊ የቤተ ክርስቲያን መሪ፥ በዚህ ጉዳይ ላይ ይለያያሉ። «ወደ ዓለም ለመመለስ ከፈለገ የራሱ ጉዳይ። ሁሉንም ሰው ለመከተል የሚበቃ ጊዜ የለንም፤ ቤተ ክርስቲያን ሰው አላነሣትም፤ የራሱ ችግር ነው፤ በቂ እምነት የለውም።» ይሉ ይሆናል። በቃላት ባይገለጽም እንኳ፥ እነዚህ ሁሉ ማመኻኛዎች በልባችን ውስጥ የሚጉላሉ ወይም በተግባራችን የሚገለጹ ከሆነ፥ የክርስቶስ ልብ ያለን መሪዎች አይደለንም ማለት ነው። ምክንያቱም ክርስቶስ ዘጠና ዘጠኝ በጎችን ትቶ አንድ ትንሽ ጠቦት ፍለጋ የሚሄድ አምላክ ነው። እንደ ክርስቶስ መልካም እረኞች የመሆናችን ምልክቱ ለእያንዳንዱ ትንሽ ልጅና በኃላፊነታችን ሥር ላለው የእግዚአብሔር መንጋ መንፈሳዊ ሁኔታ ሁሉ የምናስብ መሆናችን ነው፡፡ ስለሆነም የመሪነት ጥያቄ፥ «መንጋውን እንዴት ልቆጣጠረው እችላለሁ? ወይም «ከአገልግሎቱ እንዴት ልጠቀም እችላለሁ?» የሚል ሳይሆን፥ «እያንዳንዱ የእግዚአብሔር በግ ጤናማ ሆኖ በመንጋው ውስጥ እንዲኖር ራሴን እንዴት ልሰጥ እችላለሁ?» የሚል መሆን አለበት።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: