ግሪክ ግዛተ ዐፄ (ክፍል 1)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የምዕራቡ ዓለም ባህል የኢትዮጵያን ባህል የለወጠባቸውን መንገዶች ግለጽ። መልካም የምትላቸው ለውጦች የትኞቹ ናቸው? መጥፎ የምትላቸውስ የትኞቹ ናቸው? ለ) ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት የተከሰቱ ነገሮች በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ተጽዕኖ የሚያደርሱት እንዴት ነው?

ሳይለወጥ እንዳለ የሚኖር ባህል የለም። የአንድ አገር ባህል በየጊዜው ይለወጣል። ለውጦች በአንድ ባህል ውስጥ ከሚገኙ እንቅስቃሴዎች ይመነጫሉ። ለአብነት ያህል ወጣቶች ከተለመደው ባሕል በተለየ መንገድ በማሰብ ለውጦችን ያመጣሉ። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ እነዚህ ለውጦች ከባህሉ ውጭ የሚመነጩ ናቸው። በተለይ ዛሬ ያለነው ብዙ ፈጣን ባህላዊ ለውጦች በሚካሄዱበት ዘመን ነው። ከእነዚህ ለውጦች አብዛኞቹ ከውጭ አገሮች ተጽዕኖ የሚመጡ ናቸው። ሰዎች የምዕራባውያኑን ባህል ለመከተል ሲሉ የእነርሱን አለባበስ፥ ሙዚቃና ቪዲዮ ይቀዳሉ። አንዳንዶቹ መልካም ቢሆኑ፥ ብዙዎቹ ግን መጥፎ ናቸው። በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ሁኔታው ተመሳሳይ እየሆነ ነው። ባለፉት 20 ዓመታት ኣምልኮንና መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ ያሉት አስተሳሰቦች በእጅጉ ተለውጠዋል። እነዚህም በዓለም አቀፍዋ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተከሰቱትን ለውጦች የሚያንጸባርቁ ናቸው።

በዓለም ታሪክ ውስጥ፥ የግሪክን ያህል በዓለም ላይ ብርቱ ተጽዕኖ ያስከተለ ባህል የለም። ዛሬ ስለ ሰዎች፥ ስለ ዲሞክራሲ፥ ስለ ስፖርት፥ ስለ መናገር ነጻነትና ስለ ትምህርት ያለን ግንዛቤ የመጣው በግሪክ ተወልዶ በዓለም ሁሉ ከተስፋፋው ባህል ነው። የታሪክ ምሑራን ይህንን ባህል «ሄለናዊነት» ብለው ይጠሩታል።

አይሁዶችን የተቆጣጠረውና ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ሦስተኛው መንግሥት የግሪክ ግዛተ ዐፄ ነበር። ታላቁ እስክንድር ትንሹን እስያና ፓለስቲናን ባሸነፈባት ወቅት የግሪክን ባህል ይዞ መጣ። ይህ ባህል በቀጣዩ 400 ዓመታት በመላው ዓለምና በአይሁዶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖን አስከትሏል። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፓና እስያ በኣንድ ግዛተ ዐፄ ሥር ሲዋሃዱ ሁለቱ በጣም የተለያዩ የአውሮፓና የእስያ ባህሎች እርስ በርስ ይታገሉ ጀመር፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- ዳንኤል ምዕራፍ 8ን አንብብ። የፋርስና የግሪክ መንግሥታት ግጭት የተገለጸው እንዴት ነው?

ለ150 ዓመታት ያህል የፋርስ መንግሥት የግሪክን መንግሥት ለማንበርከክ ቢሞክርም ሊሳካለት አልቻለም። ስለሆነም፥ የፋርስ መንግሥት መፈራረስ ሊጀምር፥ የታላቁ እስክንድር አባት በሆነው በፊሊፕ የሚመራው የግሪክ መንግሥት ማንሰራራት ጀመረ፡፡ በ338 ዓ.ዓ የተለያዩ የግሪክ ከተሞችና አውራጃዎች በሙሉ ተዋሃዱ። ፊሊፕ በ336 ዓ.ዓ ሲገደል፥ ልጁ ታላቁ እስክንድር ንጉሠ ነገሥት ሆነ። እርሱም ከሁለት ዓመት በኋላ የፋርስን መንግሥት መውጋት ጀመረ። በ331 ዓ.ዓ ትንሹ እስያን፥ ጳለስቲናንና ግብፅን ድል አድርጎ ያዘ።

ታላቁ እስክንድር ጳለስቲናን ድል ሊያደርግ አሳቡ የኢየሩሳሌምን ከተማ መደምሰስ ነበር። ነገር ግን የአይሁድ ትውፊት እንደሚለው በወቅቱ የአይሁድ ሊቀ ካህናት የነበረ አንድ ሰው ሃይማኖታዊ ልብሱን ተጎናጽፎ ወደ እስክንድር ዘንድ በመቅረብ፥ በዳንኤል 8 ላይ የተጻፈውንና ፋርስን እንደሚደመስስ የተነገረለትን ትንቢት አስነበበው። እስክንድር በሁኔታው እጅግ በመደነቁ ኢየሩሳሌምን እንደ ሌሎቹ ከተሞች ሳይደመስሳት ቀርቷል። እስክንድር የአይሁዶች አምላክ ሂድና አሸንፍ በማለት በራእይ እንደ ተገለጠለት ገልጾአል። ስለሆነም፥ ምንም እንኳ ጳለስቲናን የግሪክ መንግሥት አካል ቢያደርጋትም፥ አይሁዶች ከፊል ነጻነት ኖሯቸው የራሳቸውን ጉዳዮችና ሃይማኖታዊ ተግባሮች እንዲያካሂዱ ፈቀደላቸው።

ከዚያ በኋላ እክንድር ወደ ሰሜን ተመልሶ እስከ ሕንድ ድረስ የተለያዩ አገርችን ድል እየመታ ተጓዘ። እስክንድር ወደ ግሪክ በመመለስ ላይ ሳለ ብዙ አገሮችን ድል ካደረገ በኋላ በ323 ዓ.ዓ በሞት ተለየ። እርሱ ግን የገዛ ሕይወቱን ድል ማድረግ አልቻለም ነበር፡፡ ብዙ አልኮል ይጠጣ እንደ ነበር ይነገራል። የሞተው ገና በወጣትነቱ ስለ ነበር ታላቅ መንግሥቱን የሚረከብ የደረሰ ልጅ አልነበረውም። ነገር ግን የግሪክን ባህል ለማስተላለፍ ችሏል። ስለዚህ በመካከለኛው ምሥራቅ የመሠረተው ባህላዊ ጥምረት ለ1000 ዓመታት ሊቀጥል ችሏል።

ከእስክንድር ሞት በኋላ በግሪክ አመራር ውስጥ ቀውስ ተከሰተ። የእስክንድር ልጅ የተወለደው እርሱ ከሞተ በኋላ በመሆኑ ሥልጣን ለመጨበጥ ገና ብቁ አልነበረም። በመሆኑም አራት ጄኔራሎቹ የግሪክን መንግሥት ተከፋፈሉት። በመጀመሪያ ያሰቡት በእስክንድር ልጅ ሥልጣን ሥር ለመግዛት ነበር። ይሁንና የእስክንድር ዘሮች በሙሉ ስለ ተገደሉ፥ ሁሉም ጄኔራሎች በያዟቸው ግዛቶች ላይ ንጉሥ ሆኑ። የግሪክ መንግሥት መልክዐ ምድራዊ ውህደት አልነበረውም። ሆኖም ግዛተ ዐፄውን አንድ አድርጎ ያቆየው ባህላዊ ትስስሩና እነዚህ ጄኔራሎች ለሚገዛቸው አገሮች የግሪክን ባህል ለማስተላለፍ የነበራቸው ቁርጠኝነት ነበር።

በመጀመሪያ በአራቱ ጄኔራሎች መካከል ብርቱ የሥልጣን ትግል ተከስቶ ነበር፤ ይህም ሁሉም በግሪክ ግዛተ ዐፄ ላይ ታላቅ መሪ ለመሆን ይመኙ ነበር። በመጨረሻም፥ የግሪክ መንግሥት በሚከተለው ሁኔታ ተከፋፈለ። የመጀመሪያው ጄኔራል አንቲፓር ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ በግሪክና መቄዶኒያ ላይ ገዝቷል፡፡ ሁለተኛውና አንቲጎነስ የተሰኘው ጄነራል በትንሹ እስያ ላይ ነገሰ፡፡ ሲሉክስ የተባለው ሦስተኛው ጀኔራል በባቢሎንና በአካባቢዋ ላይ ነገሰ፡፡ አራተኛው ጀኔራል ፕቶሎሚ ሲሰኝ፥ ግብፅን ተቆጣጠረ። እነዚህ አራቱ ጀኔራሎች እያንዳንዳቸው የራሳቸውን ሥርወ መንግሥት መሥርተዋል። በመሆኑም የባቢሎንና ሰሜናዊ መካከለኛ ምሥራቅ ገዥዎች የሴሉሲጅ ገዥዎች ሲሰኙ፥ የግብፅና ደቡባዊ መካከለኛ ምሥራቅ ገዥዎች ፕቶሌሚክ ገዥዎች ተብለው ተጠርተዋል።

በአይሁዶች ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩት ሁለቱ ጄኔራሎች ፕቶሎሚና ሴሉከስ ነበሩ። ጳለስቲና ትገኝ የነበረችው ፕቶሎሚና ሴሉከስ በሚገዟቸው አገሮች መካከል ነበር። ውሾች አጥንት ሲያዩ እንደሚጣሉ ሁሉ፥ እስራኤል ብዙውን ጊዜ የእነዚህ ሁለት ጄኔራሎች መፋለሚያ ሜዳ ሆና ነበር። ከ331 እስከ 200 ዓ.ዓ ድረስ እስራኤል ግብፅን በሚገዙት ፕቶሎሚዎች ሥር ነበረች። ከ200 እስከ 64 ዓ.ዓ ድረስ ደግሞ ሴሉሲዶች አዲሷ መዲናቸው ከነበረችው ከአንጾኪያ ሆነው ጳለስቲናን ይቆጣጠሯት ነበር።

እግዚአብሔር በዚህ የግሪክ አገዛዝ ተጠቅሞበታል። የግሪክ መንግሥት በብዙ መንገድ ዓለምን ለመሢሑ ምጽአት አዘጋጅቷል።

1 በመላው የግሪክ ግዛት «ኮይኔ» በመባል የሚታወቀው ቀላል ቋንቋ ይነገር ነበር። እያንዳንዱ አገር የራሱ ቋንቋ ስለነበረው በቀላሉ ለመግባባትና አንድ ለመሆን አይችልም ነበር። ይህ ቀላል የግሪክ ቋንቋ በአገልግሎት ላይ በመዋሉ በግሪክና በሮም ግዛት ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ሰዎች በግሪክ ቋንቋ ይግባቡ ጀመር። ይህ በሁለት መንገድ ለወንጌል ጠቃሚ ሆኖ ነበር። በመጀመሪያ፥ ሐዋርያትና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወንጌልን ይዘው ከስፍራ ስፍራ በሚጓዙበት ጊዜ አዳዲስ ቋንቋዎችን መማር አያስፈልጋቸውም ነበር። ምክንያቱም በሚሄዱበት አገር ሁሉ የኮይኔ ግሪክ ይነገር ነበርና ነው። አዲስ ቋንቋ መማር ብዙ ጊዜ የማስተማርና የመስበክ አገልግሎቶችን እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንን ምሥረታ ያጓትታል። አስተርጓሚ መጠቀሙም ቢሆን የወንጌሉ መልእክት ግልጽ ሆኖ እንዳይተላለፍ ሊያደርግ ይችላል። እንደ ጳውሎስ ያሉ ሓዋርያት ከግብፅ እስከ ሮም፥ ከዚያም እስከ ሕንድ ድረስ በግሪክ ቋንቋ መጠቀም በመቻላቸው የወንጌሉን ምስክርነት ቀላል አድርጎታል።

ሁለተኛው፥ አዲስ ኪዳን ብዙ ሰዎች በሚያውቁት ኣንድ ቋንቋ ሊጻፍ ችሏል። ይህም የእግዚአብሔርን ቃል ወደ ተለያዩ ሰዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ ለመተርጎም የሚደረገውን አድካሚ ተግባር አስቀርቷል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሰዎች ሁሉ በአንድ ቋንቋ ለመግባባት ቢችሉ በኢትዮጵያ የወንጌል ስርጭት ቀላል የሚሆነው እንዴት ነው?

2 ግሪኮች ሰዎች ትምህርትና ሥልጣኔ በቀላሉ ለማግኘት በሚችሉባቸው ከተሞች እንዲቀመጡ ያበረታቱ ነበር። ታላቁ እስክንድር በሄደባቸው አገሮች የአካባቢውን ባህሎች በይፋ ባይደመስስም፥ የግሪክ ከተሞችን በመመሥረት የራሱን ባህል ያስፋፋ ነበር። ስለሆነም፥ ከግሪክ እስከ ሕንድና ግብጽ ድረስ፥ እስክንድርና ከእርሱ በኋላ የተነሡት የግሪክ መሪዎች የግሪክን ባህልና የአኗኗር ዘይቤ የሚያስተዋውቁ ቁልፍ ከተሞችን ይመሠርቱ ነበር። ምናልባትም በጥንቱ ዓለም ውስጥ ዐበይት የትምህርት ማዕከላት ከነበሩት የግሪክ ከተሞች እንዷ የግብፅ እስክንድርያ ሳትሆን አትቀርም። እነዚህ ከተሞች በራሳቸው ጉዳይ ላይ የመወሰን አካባቢያዊ ሥልጣን ነበራቸው። በሶርያ የምትገኘው አንጾኪያ ከእነዚህ ከተሞች አንዷ ስትሆን፥ በኋላም የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዐቢይ መዲና ሆናለች። ቤተ ክርስቲያን ጳውሎስና በርናባስ ወንጌልን ለተቀረው የዓለም ክፍል እንዲያደርሱ የላከቻቸው ከዚህች የግሪክ ከተማ ከሆነችው ከአንጾኪያ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በኢትዮጵያ የከተሞች ዕድገት የወንጌሉን ስርጭት ቀላል ያደረገው እንዴት ነው? ለ) በዚህ የከተሞች ዕድገት ምክንያት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተለወጠችው እንዴት ነው?

እግዚአብሔር የከተሞችን መስፋፋት ለወንጌሉ ስርጭት ተጠቅሞበታል። አንደኛው፥ ተራርቀው ከሚኖሩ ሰዎች ይልቅ በከተሞች ውስጥ ተቀራርበው የሚኖሩ ሰዎች ወንጌሉን ለመስማት የላቀ ዕድል አላቸው። ወደፊት እንደምንመለከተው፥ ጳውሎስ ወንጌሉን ይሰብክ የነበረው ከአንዱ ዐቢይ ከተማ ወደ ሌላው ዐቢይ ከተማ በመሄድ ነበር። ስለ ኢየሱስ የሚያወሳውን ወንጌል በከተሞች ሁሉ ለማሰራጨት የቻለው እነዚህን ከተሞች በመድረሱ ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ወንጌል ወደ ትንሹ እስያ በደረሰ በጥቂት ዓመት ውስጥ የአካባቢው ነዋሪዎች በሙሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ሰሙ ለመናገር ችሏል (የሐዋ. 9፡10)። ሁለተኛው፥ እነዚህ ከተሞች ከፍተኛ ሥልጣን ስላላቸው አዲስ በተመሠረተችው ቤተ ክርስቲያን ላይ የተቀናጀ ስደት እንዳይነሣ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል። የሮም መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ የተቀናጀ ስደት ለማድረስ የሞከረው ቤተ ክርስቲያን በሚገባ ከተመሠረተች በኋላ ነበር።

ጳለስቲና በፕቶሎሚዎች አገዛዝ ሥር (ከ323–198 ዓ.ዓ.)

በጥቅሉ ሲታይ የፕቶሎሚያውያን አገዛዝ ለአይሁዶች መልካም ጊዜ ነበር። ፕቶሎሚ በ331 ዓ.ዓ. ወደ ኢየሩሳሌም በመዝመት ብዙ አይሁዶችን በግብጽ ወደምትገኘው ርእሰ ከተማው ምርኮኛ አድርጎ ወሰደ። ወዲያውም ነፃ ሕዝቦች መሆናቸውን በመግለጽ እንዳሻቸው ለመኖርና ኣምላካቸውን ለማምለክ እንደሚችሉ ገለጸላቸው። በእስክንድርያ ሕይወት መልካም በመሆኑ ሌሎች አይሁዶችም ወደዚያው ይፈልሱ ጀመር። ከዚህም የተነሣ፥ የከተማዪቱ አንዱ ክፍል የራሳቸው ሕገ መንግሥትና አመራር ባላቸው አይሁዶች ሊሞላ ቻለ። ብዙም ሳይቆይ በእስክንድርያ የሚገኙ አይሁዶች በአረማይስጥ ቋንቋ መናገራቸውን አቁመው በግሪክ ቋንቋ ይግባቡ ጀመር። በኋላም እስክንድርያ ከተማ ለክርስትና መስፋፋት ቁልፍ ድርሻ ካበረከቱት ከተሞች መካከል አንዱ ለመሆን በቅታለች።

ከዳግማዊ ፕቶሎሚያ (285-246 ዓ.ዓ) በተደረገላቸው ድጋፍ መሠረት በእስክንድርያ የነበሩት አይሁዶች የመጀመሪያዎቹን አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ ቋንቋ ተረጎሙ። በ72 ምሁራን የተተረጎመ በመሆኑ ይህ መጽሐፍ “የሰብዐ ሊቃናት ትርጉም” (በግሪክ 70) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። በኋላም መላው ብሉይ ኪዳን ወደ ግሪክ ቋንቋ ተተረጎመ። ይህን የግሪክ ብሉይ ኪዳን ትርጉም በግሪክና በሮም የተበተኑ አይሁዶችና ክርስቲያኖች ይጠቀሙበት ነበር። እንዲያውም፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሱ በርካታ ምንባቦች የተወሰዱት ከዚሁ ከሰብዐ ሊቃናቱ ትርጉም ነው። ከብዙ ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው የግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ የተተረጎመው ከግሪኩ የሰብዐ ሊቃናት ትርጉም ነው፡፡ ለዚህም ነው የግእዙ (ኣማርኛው) መጽሐፍ ቅዱስ መዝሙረ ዳዊት ቁጥሮች አጠቃቀም ከዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ከተተረጎመው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለየው።

ቀጣዮቹ የፕቶሎሚ ነገሥታት ኢየሩሳሌም የተወሰነ ነጻነት ያላት ከተማ ሆና እንድትቀጥልና በሊቀ ካህናቱ እንድትመራ ፈቀዱ። አይሁዶች ከሴሉሲድ አገዛዝም ልዩ ድጋፍ ነበራቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ዳንኤል 11፡1-35 አንብቡ። ዳንኤል በፕቶሎሚና በሴሉሲድ(የሰሜን ነገሥታት) መንግሥታት መካከል እንደሚካሄድ ያመለከተውን ጦርነት ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

በ275 ዓ.ዓ. የግብፅ ፕቶሎሚዎች ከአንጾኪያ ሴሉሲዶች ጋር ጦርነት ገጠሙ። በመጀመሪያ ፕቶሎሚዎች ከዚያም ሴሉሲዶች ጦርነት ለመግጠም በጳለስቲና በኩል እያለፉ ሲሄዱ ጦርነቱ ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ ለ100 ዓመታት ቀጠለ። ምንም እንኳ ይሁዳ በእነዚህ ጠላቶች ባትጠቃም፣ አይሁዶች ከሁለቱ ቡድኖች አንዱን ለመምረጥ የተገደዱበት ጊዜ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ፥ ሠራዊቶቹ በጳለስቲን ምድር በኩል በሚያልፉበት ጊዜ ሕዝቡን መዝረፋቸውና መበዝበዛቸው እንዲሁም ግብር መጠየቃቸውና ወታደር መመልመላቸው አልቀረም። ይህም ለአይሁዶች የአሕዛብ ሠራዊት በምድራቸው ውስጥ እያቋረጡ ሲሄዱ መመልከት የሚያበላጭና ነፃ ሕዝብ ሳይሆኑ በአሕዛብ ቁጥጥር ሥር የሚኖሩ መሆናቸውን የሚያመለክታቸው ነበር። በዚህ ጊዜ በሚልክያስ ስለ መሢሑ መምጣት የተነገረው የተስፋ ቃል 200 ዓመት ያህል ሆኖት ነበር። ይህም አይሁዶችን ከአሕዛብ ኣገዛዝ ነፃ አውጥቶ እንደ ዳዊት ወይም ሰሎሞን ያለ ንጉሥ መጥቶ በእርሱ ሥር የከበረ ሕይወት እንዲኖሩ የሚያደርግ መሢሕ የሚመጣበትን ጊዜ እንዲናፍቁ ሳያደርጋቸው አልቀረም።

የውይይት ጥያቄ፡- አንድ ቀን ታላቅ እዳኝ መጥቶ ነፃ እንደሚያወጣህ የሚገልጽ የተስፋ ቃል ይዘህ በኢየሩሳሌም የምትኖር አይሁዳዊ ብትሆን፥ በዚህ የግሪክ አገዛዝ ዘመን ምን ዓይነት አስተሳሰብ ይኖርህ ነበር? ለ) የግሪክ መንግሥትና ባህል በኢየሩሳሌም ከተማ በነበሩት አይሁዶች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

1 thought on “ግሪክ ግዛተ ዐፄ (ክፍል 1)”

  1. Pingback: ክርስቶስን ለመከተል እምነት ወሳኝ ነው (ዕብ. 11፡1-39) – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d