የሴሉሲድ አገዛዝ ዘመንና ነጻነት

«ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ» (ገላ. 4፡4)።

ከብሉይ ኪዳን መጨረሻ (ሚልክያስ) አንሥቶ እስከ መጥምቁ ዮሐንስ መምጣት ድረስ በነበረው 400 የዝምታ ዓመታት ውስጥ በመንፈስ ተመርቶ የእግዚአብሔርን ቃል የሚናገር ነቢይ አልተነሣም ነበር። በዚህ ወቅት በባቢሎናውያን፥ በፋርሳውያን፥ በግሪካውያንና በአይሁዳውያን አማካይነት የዓለም ሕዝብ ባህል መለወጥ ችሏል። በዚህም እግዚአብሔር ዓለምን ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት እያዘጋጀ ነበር።

ፖለቲካና ሃይማኖት ብዙም አይጣጣሙም። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በፖለቲካ ውስጥ እጃቸውን በሚያስገቡበት ጊዜ ለእግዚአብሔር መንግሥትና ለዚህ ዓለም መንግሥት በሚጠቅሙ ነገሮች መካከል ግጭት ይከሰታል። መገዛት ያለብን ለየትኛው መንግሥት ነው? ለምድራዊው መንግሥት ወይስ ለሰማያዊው መንግሥት? ለክርስቲያኖች በፖለቲካ ውስጥ መሳተፉ መልካም ቢሆንም፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ግን ሃይማኖትንና ፖለቲካን ከመቀላቀል መጠንቀቅ አለባቸው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የአንድን ፖለቲካ አጀንዳ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ደግፈው መታገል የለባቸውም። ነገር ግን ሰዎች በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመሥርተው መንፈሳዊ ውሳኔዎችን እንዲያስተላልፉ መርዳት አለባቸው። እንደ ብሉይ ኪዳን ነቢያት፥ የእግዚአብሔርን ቃል መርሆዎችን አለመከተል ስለሚያመጣው ጥፋት ማስጠንቀቅ አለባቸው። በፖለቲካ ተግባሮች ላይ የሚሳተፉ ክርስቲያኖች ከሁሉ በፊት ለእግዚአብሔር ታማኝ በመሆን በመጽሐፍ ቅዱስ መርሆዎች መሠረት መኖርና መተዳደር ይኖርባቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች በአገራቸው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት መሳተፍ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሃይማኖተኞችና ፖለቲከኞች በመሆናቸው ምክንያት ችግሮች ሲከሰቱ የተመለከትከው እንዴት ነው? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በፖለቲካና በአገራችን ጉዳዮች ላይ ምን ምን ኣስተዋጽኦዎችን ሊያበረክቱ ይችላሉ?

ጊዜው እየገፋ ሲሄድ፥ በኢየሩሳሌም ከተማ በተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች መካከል ዐቢይ ትግል ይካሄድ ጀመር። ካህናት የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎች ሲሆኑ፥ የፖለቲካ ሥልጣን ከተቀደሰ አኗኗር በላይ አስፈላጊ እየሆነ መጣ። ብዙም ሳይቆይ የሃይማኖት መሪዎች ልክ እንደ ዓለማውያን ዐይነት ፖለቲካዊ አቅጣጫ በመያዝ፥ እግዚአብሔር በማይፈልጋቸው መንገዶች ይጓዙ ጀመር። አይሁዶችን በመንፈሳዊ አምልኮ የመምራት ኃላፊነት ከተሰጣቸው ካህናት መካከል ሁለት ዐበይት የፖለቲካ ቡድኖች ብቅ አሉ። እነዚህ ሁለቱ ቡድኖች በአይሁድ ሕዝብ ላይ ለመንገሥ ይችሉ ዘንድ ከአሕዛብ ሞገስ ለማግኘት አጥብቀው ታገሉ። እነዚህ ሁለቱ ቡድኖች ወይም ቤተሰቦች ኦኒያዶችና ጦቢያቶች ይባላሉ። ኦኒያዶች አክራሪዎች ነበሩ። ኦኒያዶች የአይሁድን ባህል ጠብቆ ለማቆየት ባላቸው ጽኑ ፍላጎት መሠረት፥ ከግሪክ ባህል ጋር የሚደረገውን ውህደት በመጠኑ ብቻ ለማድረግ ፈለጉ። ጦቢያዶች የአሕዛብ ባህልን ለመከተል የተዘጋጁ በመሆናቸው፥ አይሁዶች አንዳንድ ጥብቅ ባህላዊ ልማዶቻቸውን ትተው የግሪኮችን የአኗኗር ስልት እንዲከተሉ ያበረታቷቸው ነበር። ጦቢያዶች መጀመሪያ ከፕቶሎሚዎች በኋላም ከሴሉሲዶች ግብር ለመሰብሰብ ውክልና በማግኘታቸው፥ በይሁዳ ሕዝብ ላይ ፖለቲካዊ ሥልጣንን ጨበጡ። እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው ስግብግቦች ነበሩ። ጦቢያዶች ግሪኮች የሚጠይቁትን ግብር ብቻ ሳይሆን ለራሳቸው ጭምር ሕዝቡን እያስገደዱ ግብር ይሰበስቡ ነበር። ይህም የኋላ ኋላ፥ ተራ ሕይወት በሚመሩት ሰዎች ዘንድ እንዲጠሉ አድርጓቸዋል። የሀብታም ነጋዴ ቤተሰቦች ግን የጥቅሙ ተካፋዮች ነበሩ።

ጦቢያዶችን የሚከተሉ ሀብታም ቤተሰቦች የአይሁድን ባህል ለመለወጥና ለአሕዛብ ተስማሚ ለማድረግ ፈለጉ። ስለሆነም፥ አይሁዶች ወደ «ዘመናዊነቱ» በማድላት ባህላቸውንና አምልኳቸውን ሳይቀር ከአሕዛብ ጋር እንዲያስማሙ አበረታቷቸው። በአዲስ ኪዳን ዘመን የጦቢያድ ቡድን ትውልዶች፥ ሰዱቃውያን ይባሉ ነበር። እነዚህ ገዥዎቻቸው ከነበሩት አሕዛብ (ማለትም፥ ግሪካውያንና ሮማውያን) ጋር ለመስማማት የሚችሉትን ሁሉ ከማድረግ የማይመለሱና የፖለቲካ ሥልጣን የነበራቸው ቡድኖች ነበሩ።

የውይይት ጥያቄ፡- የዓለም ባህል በክርስቲያኖች በተለይም በወጣቶች ላይ ተጽዕኖ በማድረስ፥ እንዴት ከንጹሕ አኗኗር እንደሚመልሳቸው አንዳንድ ምሳሌዎችን ስጥ።

ለብሉይ ኪዳን ታማኝ ሆነው ልዩ ባህላቸውንና እምነታቸውን ጠብቀው ለመኖር የፈለጉ ብዙ አይሁዶች ነበሩ። እነዚህ ኣይሁዶች ጦቢያዶችን በመቃወም ሃሲዲያን የተባለ ሌላ ቡድን መሠረቱ። በይሁዳ ይህ ቡድን በአሕዛብና የአሕዛብን ባህል በመደገፍ አይሁዶች የግሪኮችን ባህል ይበልጥ እንዲቀበሉ ባደረጉት ሀብታም የአይሁድ መሪዎች ላይ ዐመፅ እንዲቀሰቀስ ኣደረጉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ዳን. 11፡36-45 አንብብ። ሀ) በዚህ ክፍል የታየው ባህላዊ ትግል ምንድን ነው? ለ) ከሰሜን ንጉሥ ትውልዶች አንደኛው በኢየሩሳሌም ላይ ምን ያደርጋል? ሐ) ዳንኤል ይህ ዘመን ለአይሁዶች ምን ዓይነት ዘመን እንደሚሆን ገለጸ?

በዚህ ጊዜ ሴሉሲዶች ፕቶሎሚዎችን አሸንፈው ጳለስቲናን ተቆጣጠሩ። የሴሉሲድ መሪ የነበረው አንቲዮክስ ግልላዊ መንግሥቱን ለማስፋፋት አሰበ። ነገር ግን አዲሱ የሮም መንግሥት በዚህ ጊዜ በመስፋፋት ላይ ነበር። አንቲዮክስ ግሪክን ለመቆጣጠር በሞከረ ጊዜ ሮማውያን አሸነፉት። ከዚያም ለጦር ጉዳት ካሳ እንዲከፍል አስገደዱት። አንቲዮከስ እየተዳከመ ሲሄድ በመንግሥቱ ውስጥ የነበሩ ጠንካራ ፓርቲዎች ዐመፁበት። እርሱ ከሞተ በኋላ በእግሩ የተተካው የሴሉሲድ ንጉሥ ለሮም የሚከፍለውን ገንዘብ የግድ ማግኘት ነበረበት። ስለሆነም፥ አይሁዶች ቀደም ሲል ይከፍሉት ከነበረው ግብር በተጨማሪ እጥፍ እንዲከፍሉ መጣሉ ብቻ ሳይሆን፥ ወደ የቤተ መቅደሱ የሚመጣውንም ገንዘብ በሙሉ እንዲሰጡት ጠየቀ። አይሁዶች በዚህ ፖሊሲ ላይ ከማመፃቸው በፊት ተገደለ።

ይህ መሪ በሞተበት ወቅት ልጆቹ ገና ሕፃናት በመሆናቸው፥ አንቲዮከስ ኤፕፋነስ (ትርጉሙ የእግዚአብሔር መገለጥ) የተባለ ወንድሙ ዙፋኑን ያዘ። ይህኛው አንቲዮከስ የአይሁዶች ብርቱ ጠላት ሆነ። እንደ ታላቁ እስክንድር ድል ነሺ በመሆን፥ የግሪክን (ሴሉሲድ) መንግሥት ክብር ለመመለስና ሰዎች ሁሉ የግሪክን ባህል እንዲከተሉ ለማስገደድ ጣረ። ይህ ሰው ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ፥ ሁለት አይሁዶች ከአንቲዮከስ ጋር ለመነጋገር ወደ አንጾኪያ ሄዱ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ስለ ግብሩ መጨመርና ከቤተ መቅደሱ ስለሚወሰደው ገንዘብ በማማረር የገለጸው የአይሁድ ሊቀ ካህናት ነበር። ሌላው ደግሞ የሊቀ ካህናቱን ወንበር ለመውሰድ የፈለገው ጄሰን የተባለ የገዛ ወንድሙ ነበር። ጄሰን የሊቀ ካህንነቱን ወንበር ከያዘ የግሪክን ባህል እንደሚያስፋፋና ለአንቲዮከስም ጠቀም ያለ ገንዘብ ከቤተ መቅደሱ ካዝና ለመስጠት እንደሚችል ገልጾ ኣግባባው። አንቲዮከስ የግሪክን ባህል ለማስፋፋት ፍላጎት ስለ ነበረው፥ ጄሰንን ሊቀ ካህናት አደረገው። (ከዚህ ጊዜ ጀምሮ፥ ግሪኮች የእነርሱን ፖሊሲ የሚደግፍ ሊቀ ካህናት ሲሾሙ ኖረዋል።)

ጄሰን ወደ አገሩ እንደተመለሰ የግሪክን ባህል ለማስተዋወቅ ደፋ ቀና ይል ጀመር። የአይሁድ ወጣቶች የግሪኮችን ባህልና ስፖርት የሚለማመዱበትን ጂምናዚየም ገነባ። አይሁዶች ግሪኮች እንዳለመሠልጠን አድርገው የሚመለከቱትን ወንድ ልጆችን የመግረዝ ባህላቸውን እንዲያቆሙ አዘዘ።

የሊቀ ካህናቱን መንበር ለመጨበጥ ግን ፖለቲካዊ ትግሉ ተጧጡፎ ቀጠለ። መነሊስ የተባለ አንድ የቤተ መቅደስ ወታደር ዓመታዊ ግብሩን እንዲያስረክብ ወደ አንጾኪያ ተልኮ ነበር። ምንም እንኳ ይህ ሰው በብሉይ ኪዳን ሕግ መሠረት ከኣሮን የትውልድ ሐረግ ወገን ባለመሆኑ ሊቀ ካህን መሆን ባይችልም፥ መነሊስ ለአነቲዮከስ ጉቦ በመስጠት ይህን ሥልጣን እንዲሰጠው ጠየቀ። መነሊስ የሊቀ ካህንነቱን ሥልጣን ከመያዝም አልፎ፥ ትክክለኛ ሊቀ ካህን ሊሆን የሚገባውን የጄሰንን ወንድም መግደሉ አይሁዶችን ይበልጥ አስቆጣ።

በተከታዩ ዓመት ማለትም በ168 ዓ.ዓ. አንቲዮከስ ግብፅን በመውጋት ዋና ከተማዋን ለመያዝና ራሱንም ንጉሥ አድርጎ ለመሾም አሰበ። ነገር ግን ሮማውያን ኣንድ የልዑካን ቡድን ልከው አንቲዮከስ የግብፅ ንጉሥ ለመሆን የነበረውን ምኞት እንዲሰርዝ አስገደዱት። ከዚህ ጊዜ ኣንሥቶ ሮም ለቀጣይ 100 ዓመት የዓለም ኃያል አገር ሆነች። ነገር ግን እንቅስቃሴአቸው በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይም በኢየሩሳሌም ጎልቶ አይታይም ነበር።

አንቲዮከስ በሮማውያን ተገድሏል የሚል አንድ የሐሰት ወሬ ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ፥ የቀድሞው ሊቀ ካህናት ጄሰን 1000 ወታደሮችን ኣስከትሎ በመምጣት መነሊስን ሽሮ ቤተ መቅደሱን ተቆጣጠረ። አንቲዮከስ ይህን ዐመፅ ሲሰማ፥ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ በዐመፁ ተግባር ላይ እንደ ተሳተፉና ከእርሱ ይልቅ ፕቶሎሚዎችን የደገፉ መሰለው። ስለሆነም፥ ሠራዊቱን ወደ ኢየሩሳሌም ላከ። ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ተገደሉ፤ በባርነትም ተወሰዱ። መነሊስም ተመልሶ በሥልጣኑ ላይ ተቀመጠ። በተጨማሪም፥ አንቲዮከስ ብዙ ወታደሮችን በኢየሩሳሌም አሰፈረ። በዚህ ጊዜ አንቲዮከስ ኢየሩሳሌምን ከሃይማኖታዊ መንበርነት ወደ ግሪክ ከተማነት ለመለወጥ ቆርጦ ተነሣ። በመሆኑም፥ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ማፈራረስ ጀመረ። በተጨማሪም፥ የኣይሁድን ሃይማኖት ለማዳከም ሲል አይሁዶች የግሪክ ጣዖትን እንዲያመልኩ አስገደደ። የሃይማኖቷ ኃይል እስካልተደመሰሰ ድረስ ይሁዳ የግሪክን ባህል እንደማትቀበል ተገነዘበ። ስለሆነም፥ ባለፉት 300 ዓመታት ሲደረጉ የነበሩት የቤተ መቅደስ መሥዋዕቶች እንዲቀሩና ብሉይ ኪዳንም እንዲወገድ አዘዘ። ሰዎች የሰንበትን ኣምልኮና ወንድ ልጆችን የመግረዝ ሥርዐታቸውን እንዲያቆሙ አስጠነቀቀ። በ197 ዓ.ዓ. በቤተ መቅደሱ አካባቢ ሌላ መሠዊያ ሠርቶ ዜውስ ለተባለ የግሪክ ጣዖት መሥዋዕት አቀረበ። ይህ ዳንኤል ስለ “ጥፋት ርኩሰት” የተናገረውን ትንቢት በከፊል ይፈጽመዋል (ዳን. 9፡27፤ 11፡31)። [ክርስቶስ ወደፊት ሌላ የጥፋት ርኩሰት እንደሚነሣ ተንብዮአል (ማቴ. 24፡5)።] በአይሁድ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ፥ በሃይማኖታቸው ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ተሰነዘረ። አንቲዮክስ የአይሁዶችን ሃይማኖት ለመቆጣጠር የፈለገው በሕይወታቸው ላይ የነበረውን ቁጥጥር አሜን ብላው በተገዥነት መንፈስ እንዲቀበሉ ለማድረግ መሆኑ አይጠረጠርም። ነገር ግን ለ300 ዓመታት ያህል በራሳቸው መንገድ እንዲያመልኩ በተፈቀደላቸው አይሁዶች ላይ ይህን የፖሊሲ ለውጥ ማምጣቱ አይሁዶችን ለቁጣ ቀስቅሷል።

በይሁዳ ውስጥ በምትገኝ አነስተኛ ከተማ ማታቲያ የሚባል አንድ ካህን ነበር። ከአንቲዮከስ የተላከ አንድ ሰው ወደ እርሱ መጥቶ በኢየሩሳሌም በተሠራው መሠዊያ ላይ ለዜውስ እንዲሰግድ ሲጠይቀው ፈቃደኛ ሆኖ አልተገኘም። ማታቲያ ለዜውስ ጣዖት ለመሠዋት የተስማሙትን አንዳንድ አይሁዶችና ተልከው የመጡትን ሰዎች ከገደለ በኋላ፥ ለእግዚአብሔር ለመቆም የፈለጉ ሰዎች እንዲከተሉት ጠየቀ። አንቲዮከስንም ለመውጋትና ለመቋቋም ወሰኑ። ወዲያውም በእግዚአብሔር ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመቋቋም የፈለጉ ሰዎች ሁሉ ተባበሯቸው። እነዚህ ዐማፅያን የጣዖት ኣምልኮን በመደምሰስ፥ የግሪክን አምልኮና ባህል የተቀበሉትን አይሁዶች በመግደልና የኣይሁድ ወንድ ልጆችን በመግረዝ ተቃውሟቸውን አቀጣጠሉ። ይህም በአይሁድ ታሪክ የመቃብያን ዘመን የሚባለውን ጊዜ አበሰረ። በኋላ የመቃብያን ትውልዶች ሃስሞኒያን ተብለዋል። የሃስሞኒያን ሥርወ መንግሥት በዚያች አጭር የነጻነት ጊዜ (ከ142-63 ዓ.ዓ) በይሁዳ የሊቀ ካህንነቱን አገዛዝ የተቆጣጠሩ የማታቲያ ትውልዶች ናቸው። ሥርወ መንግሥታቸው ከፍጻሜ የደረሰው ሮማውያን ኢየሩሳሌምን በወረሩና ታላቁ ሄሮድስ የይሁዳ ንጉሥ በሆነ ጊዜ ነበር።

ማታቲያ ከሞተ በኋላ፥ ከአምስት ልጆቹ አንዱ የነበረው ይሁዳ መቃቢ (ትርጉሙ «መዶሻ » ማለት ነው) የዐማፅያኑን ቡድን መምራት ጀመረ። ከ400 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አይሁዶች ጦርነት አካሄዱ። ዐማፂ ተዋጊ በመሆኑ፥ አንዳንድ የሴሉሲድ ሠራዊቶችን ሊያሸንፍ ቻለ። ይህን ድል ሲያዩ ሌሎችም ጦሮች ተቀላቀሉ። ሁኔታው ያበሳጨው አንቲዮከስ ዐመፁን እንዲያስቆምና አይሁዶችን ከይሁዳ እንዲያግዙ ብዙ ወታደሮችን ወደ ኢየሩሳሌም ሰደደ። በቁጥር ባይመጣጠኑም እንኳ አይሁዶች ለጊዜው የሴሉሲድን ጦር ለማሸነፍ ችለው ነበር። በመጨረሻም፥ አንቲዮክስ ከአይሁዶች ጋር በመደራደር እንደ ቀድሞው አምላካቸውን እያመለኩ በሰላም መኖር እንደሚችሉ አስታወቀ። ይሁዳና ሠራዊቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ከተማይቱን ተቆጣጠሩ። የዜውስን የጣዖት መሠዊያዎችን አፈራርሰው በብሉይ ኪዳን እንደተደነገገው የእግዚአብሔርን የቤተ መቅደስ አምልኮ ጀመሩ።

ይሁዳና ሌሎችም አይሁዳውያን ለሃይማኖታቸው ነጻነት ታግለው ባገኙት ድልና ሞራል ለፖለቲካ ድል ይታገሉ ጀመር። ስለሆነም ከሴሉሲድ ጋር ጦርነት ገጠሙ። በመጀመሪያ ትንሽ ድል የቀናው የይሁዳ ጦር ተሸነፈ። ሴሉሲዶች አይሁዶች በጥንታዊ መንገዳቸው እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ቢፈቅዱላቸውም ፖለቲካዊ ነጻነት ሊሰጧቸው አልፈቀዱም። ይሁዳ በዚህ ሁኔታ ስላልረካ በሴሉሲድ አገዛዝ ላይ ማመፁን ቀጠለ። በኋላም ይሁዳ በጦርነት ላይ ሲሞት፥ ዮናታን የተባለ ወንድሙ ተካው።

በዚህ ጊዜ፥ በአንጾኪያ በሴሉሲድ መንግሥት ዙሪያ ለመግዛት መብት ያለው ማን ነው በሚለው ላይ ትግል ይካሄድ ነበር። ትክክለኛው ንጉሥ እኔ ነኝ እያሉ ከሚፋለሙት ሰዎች መካከል አንዱ ወደ ዮናታን መጥቶ ድጋፍ ከሰጠው የሊቀ ካህንነቱን ሥልጣን እንደሚሰጠው ነገረው። ዮናታን ፈተናውን ለመቋቋም ስላልቻለ ከሰውየው ጋር ተስማምቶ የሊቀ ካህንነቱን ሹመት ተቀበለ። ይህም ዮናታን ሃይማኖታዊና ወታደራዊ ሥልጣንን አጣምሮ መያዙ በወጥመድ እንዲያዝ አደረገው። ዮናታን ድጋፉን የሰጠው ባላስ የንግሥናውን መንበር ሲይዝ፥ ዮናታን የይሁዳ ገዥ በመሆን የፖለቲካውንም ሥልጣን ጨበጠ። በአንጾኪያ የሚካሄደው የዙፋን ትግል ለብዙ ዓመታት ቀጠለ። ዮናታና አታላይ መሪ በመሆኑ በይሁዳ ላይ የበለጠ ሥልጣን ያስገኛል ብሎ ያሰበውን ቡድን ሲደግፍ ቆየ። ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የጳለስቲናን አገዛዝ እያሰፋ እንዲሄድ ረዳው። ይሁንና አንድ የሴሉሲድ መሪ ዮናታንን አታሎ ከማረከው በኋላ ገደለው። ይህም በይሁዳ የነጻነት ትግሉ አመራር ከማታቲያ ልጆች መካከል በሕይወት በነበረው በስምዖን ጫንቃ ላይ እንዲወድቅ አደረገ።

በ142 ዓ.ዓ. ስምዖን ለይሁዳ መሠረታዊ ነጻነት የሚያስገኝ ድርድር ከሴሉሊድ መንግሥት ጋር ለማድረግ ችሎ ነበር። የሌሉሲድን ኃይል ለማዳከም ይፈልግ በነበረው በሮም መንግሥት ድጋፍ፥ ይሁዳ ለ80 ዓመታት ነፃ ሆና ቆይታለች። በዚህ ነጻነት የተደሰቱት አይሁዶች ለስምዖን የሊቀ ካህንነቱን ሹመት ሰጡት። ምንም እንኳ ስምዖን ብሉይ ኪዳን ከሚደነግገው የሊቀ ካህናት ዘር ሐረግ ወገን ባይሆንም፥ ዘሩ ለዘላለም የሊቀ ካህንነት መብት እንዲኖረው ወሰኑ። ነገር ግን ስምዖን በልጁ ባል ስለተገደለ በሊቀ ካህንነት መሪነቱ ብዙም አልቆየም። ዮሐንስ ሂርካነስ የተባለው የስምዖን ልጅ የሃይማኖቱንና የፖለቲካ ሥልጣኑን ተረከበ።

የሚያሳዝነው የውጭ ወራሪን ለመቋቋም የሚተባበሩ ሰዎች በሰላም ጊዜ እርስ በርሳቸው ይዋጋሉ። በመሆኑም፥ በዚህ የሰላም ጊዜ አይሁዶች እርስ በርሳቸው መዋጋት ጀመሩ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ውስጣዊ ትግል ሲካሄድ ያየህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ይህ ለምን የሚሆን ይመስልሃል?

ዮሐንስ ሂርካነስ ንጉሥ ሲሆን፥ ሶርያውያን ምንም እንኳ ኢየሩሳሌምን ድል ማድረግ ቢችሉም ረዥም ጊዜ የሚወስድ ጦርነት ለማካሄድ ስላልፈለጉ ከእርሱ ጋር ስምምነት አደረጉ። የበላይነታቸውን እስካከበረላቸው ድረስ ነጻነት ሊሰጡት ተስማሙ። በዚህ ጊዜ የተነሣው ኣዲስ ትውልድ ምንም እንኳ በወታደራዊ ድሎቹ ደስ ቢሰኝም፥ ሰላምን ይናፍቅ ነበር። የሚዋጉትም ለሃይማኖት ነጻነት ባለመሆኑ፥ ብዙም የመዋጋት ፍላጎት አልነበራቸውም። ከሶርያውያን ጋር ስምምነት የተፈራረመው ዮሐንስ እንደ አባቱ የግሪክን ባህል አይቃወምም ነበር። ይህም የግሪክን ባህል የሚከተሉትን የአይሁድ ሀብታሞች ደስ አሰኛቸው። ስለሆነም፥ ከሶርያ ጋር ተስማምቶ አገሪቱን ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ ጀመሩ። እነዚህ ዮሐንስን የደገፉትና የግሪክን ባህል የተከተሉት ሀብታም ኣይሁዶች በኋላ የሰዱቃውያንን ቡድን መሥርተዋል።

ኣንዳንድ አጥባቂ አይሁዶች ዮሐንስ ከትክክለኛው የካህናት ዘር ሐረግ ወገን ሳይሆን የሊቀ ካህንነቱን ስፍራ በመያዙ ቅር ተሰኙ። ስለሆነም ዮሐንስ ይህን ሥልጣን እንዲለቅ ጠየቁት። ፈቃደኛ ኣለመሆኑን ሲገነዘቡ እነርሱም ለእርሱ ድጋፍ ከመስጠት ተቆጠቡ። ብዙ ምሁራን የፈሪሳውያን ቡድን በዚህ ጊዜ እንደተጀመረ ይናገራሉ፡፡ (ፈሪሳዊ ማለት የተለየ ማለት ሲሆን፥ የዮሐንስን አገዛዝ ከመደገፍ መለየታቸውን ያሳያል። እነዚህ ሰዎች ሃይማኖታዊ ኣጥባቂነትን ይከተሉ የነበሩ ሲሆን፥ በኋላም የክርስቶስ ጠላቶች ሆነው ተገኝተዋል።) ፈሪሳውያን የገዥው ቡድንና የሰዱቃውያን ፖለቲካ ቡድን አባላት የሆኑት የነጋዴ ቤተሰቦች ጠላቶች ሆኑ። በታሪክ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሱት በዚህ ጊዜ ነበር። በ70 ዓም. ሮማውያን ሰዱቃውያንን እስከደመሰሱበት ጊዜ ድረስ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ትግል ሲካሄድ ቆይቷል። እነዚህ ሁለቱ ቡድኖች ተባብረው የሠሩበት ጊዜ ቢኖር የሁለታችንም ጠላት ነው ብለው ያሰቡትን ክርስቶስን ለመስቀል በተነሡበት ወቅት ብቻ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋ. 23፡6-10 አንብብ። ይህ ክፍል በእነዚህ ሁለት ቡድኖች መካከል የነበረውን ጥላቻ የሚያሳየው እንዴት ነው?

ዮሐንስ ሂርካነስ የጥንቱን የአይሁድ ሕዝብ ክብር ለመመለስ ቆርጦ ተነሥቶ ነበር። በዚህ ጊዜ የሴሉሲድ ግዛት ተዳክሞ ስለ ነበር አዳዲስ ግዛቶችን መውረር ያዘ። በደቡብ የኢዱሚያን ሕዝብ በመውረር ተገርዘው አይሁዳውያን እንዲሆኑ አደረገ። ይህን በሚያደርግበት ጊዜ ከኢዱሚያን ተወላጆች አንዱ የሆነው ታላቁ ሄሮድስ ዙፋኑን ከትውልዶቹ እንደሚወስድ አላወቀም ነበር። ከዚያም ዮሐንስ ወደ ሰሜን ገስግሶ ሰማርያን ያዘ፡፡ ዮሐንስ ሳምራውያንን ከሚገባው በላይ ይጠላቸው ስለ ነበር፥ ቤተ መቅደሳቸውን አፍርሶ ብዙ ሳምራውያንን ገደለ። ይህም ተግባር በአይሁዶችና በሳምራውያን መካከል የነበረውን ጥላቻ አባባሰው።

የዮሐንስ ዘሮችም እርሱ የጀመራቸውን ተግባሮች መፈጸም ቀጠሉ። ከሰማርያ በስተሰሜን የምትገኘው ገሊላ አይሁዶች የሰፈሩባት ኣካባቢ ብትሆንም ብዙ ኣሕዛብ ነበሩባት። የዮሐንስ ልጅ የሆነው አሪስቶሉሉስ ገሊላን ለመቆጣጠር ቻለ። ይህ ሰው ብዙ አይሁዶችን ወደ ገሊላ ከመላኩም በላይ፥ በዚያ የነበሩትንም ሰዎች ወደ ይሁዲነት እንዲለወጡ አድርጓል። ምናልባት የዮሴፍና የማርያም ቅድመ ኣያቶች ከቤተልሔም ወደ ገሊላ የሄዱት በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ የተወለደው በገሊላ ሲሆን፥ አብዛኛውን አገልግሎቱንም ያደረገው በዚያ ነው። አብዛኞቹ ደቀ መዛሙርትም የገሊላ ሰዎች ናቸው። ሁልጊዜ በይሁዳ አገዛዝ ላይ ጥላቻዋን ከምታሳየው ከሰማርያ በተቃራኒ፥ ገሊላ በከፍተኛ ደረጃ ኣይሁዶችን ትደግፍ ነበር። እንዲያውም፥ በአዲስ ኪዳን ዘመን ከሮማውያን ነፃ ለመውጣት ከፍተኛ ትግል ያካሄዱት የገሊላ ኣይሁዶች ነበሩ።

ጊዜው እየገፋ ሲሄድ፥ የሃስሞኒያን መሪዎች አንድ ጊዜ በወረራ ሌላ ጊዜ ድግሞ በስምምነት ግዛታቸውን ለማስፋፋት ፈለጉ። ከዚህም በተጨማሪ፥ የአይሁድን ሃይማኖት በማጣጣል አይሁዶች እንደ ኣሕዛብ እንዲኖሩ አደረጉ። ይህም አይሁዶች በፈሪሳውያን እየተመሩ በጨቋኝ አገዛዛቸው ላይ እንዲነሡ አደረገ። ይህም በሃስሞኒያን ዘሮች መካከል ወደ ተደረገው የጦርነት ዘመን መራቸው፡፡ ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን በሁለት ተቃራኒ ጎራዎች ተሰልፈው እንዲዋጉ ያደረገው ይኸው ጦርነት፥ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊም ነበር። ነገሮች እየከረሩ በመሄዳቸው ፈሪሳውያን ሴሉሲዶች መጥተው ኢየሩሳሌምን እንዲያጠቋትና እንዲቆጣጠሯት ጋበዟቸው። የሶርያ ሠራዊት ሲሸነፍ፥ ከ800 ፈሪሳውያን በላይ ተገደሉ።

በሃስሞኒያን ዘመን የሮም ግዛት እየተስፋፋ በመሄዱ በጥንቱ ዓለም እጅግ ታላቅ ስፍራ ለመያዝ በቃ። በመጀመሪያ ሮማውያን የሴሉሲድን መንግሥት ለማዳከም ሲሉ ብዙም አቅም ያልነበራት ይሁዳ ነፃ እንድትሆን ፈቅደው ነበር። ነገር ግን ሮማውያን በ66 ዓ.ዓ የሴሉሲድን አዛዝ ገርስሶ የአይሁዶችን ነጻነት ማከበሩ አስፈላጊ ሆኖ አላገኙትም። በይሁዳ የሮም አገዛዝ ተቃውሞ ሲገጥመው በ64 ዓ.ዓ. ፖምፔ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ።

ለተወሰነ ጊዜ ውጊያ ከተካሄደ በኋላ ብዙ ሰዎች ተገደሉ፤ የኢየሩሳሌምም ከተማ ተሸነፈች። የነጻነት ዘመኗም አበቃ። ፖምፔ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ አንድ የተለየ ነገር ይኖራል ብሎ ስላሰበ ወደዚያው ለመግባት ፈለገ። ይህም ነጻነታቸውን በመገፈፋቸው ብቻ ሳይሆን በሃይማኖታቸውም ላይ አስከፊ ተግባር እንደ ተፈጸመ በሚቆጥሩ ኣይሁዶች ጥላቻን አተረፈ።

ምንም እንኳ ይሁዳ ነጻነቷን ብታጣም፥ የሃስሞኒያን ገዥዎች የሊቀ ካህንነቱንና የገዥነቱን ሥልጣን ለመያዝ ይሻኮቱ ጀመር። በተጨማሪም፥ አይሁዶች በሮም አገዛዝ ላይ የማያቋርጥ ተቃውሞ ያካሄዱ ነበር። በዚህ ጊዜ አንቲፓር የተባለ ኢዱሚን ወደ ሥልጣን የሚወጣበትን መሰላል ተመለከተ። ይህ ሰው ከሃስሞኒያን ገዥዎች የአንዱ ዋንኛ ደጋፊ በመሆን ሮማውያን የአንቲፓርን ጓደኛ ሊቀ ካህናት አድርገው እንዲሾሙት ተጽዕኖ አሳደረ። የሮም ጀኔራሎች በሚቸገሩበት ጊዜ አንቲፓር እነርሱን ለመርዳት የሚችለውን ሁሉ አደረገ። ለዚህ ተግባሩ ብድር ለመመለስ ሮማውያን ልጆቹን በቀድሞው የሃስሞኒያን ግዛት ውስጥ ሾሟቸው። ከልጆቹ አንዱ የሆነው ሄሮድስ ገሊላን እንዲገዛ ተደረገ።

በዚህ ጊዜ ሁለት ጄኔራሎች እርስ በርሳቸው በመዋጋታቸው በሮማውያን መካከል ውስጣዊ ትግል ይካሄድ ጀመር። ሄሮድስ ከአንደኛው ጄኔራል ጎን ሲሰለፍ፥ ይህ ሰው የኋላ ኋላ የንጉሠ ነገሥትነቱን አክሊል ሊደፋ ቻለ። በዚህ ጊዜ ሄሮድስ ለፈጸመው ተግባር የንግሥና ሹመት ተሰጠው። አሁንም የሊቀ ክህነትና የፖለቲካ መሪነት ሥልጣን ተነጣጠሉ፤ ሊቀ ካህናቱ ከፖለቲካ መሪ ሥር እንዲሆን ተደረገ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በዚያን ዘመን የምትኖር ኣይሁዳዊ ብትሆን ኖሮ፥ ትልቁ ናፍቆትህ ምን ይሆን ነበር? የሰላም ንጉሥ የሆነው መሢሕ እንዲመጣ ምን ያህል ትፈልግ ነበር? ለ) እግዚአብሔር አይሁዶችን ለመሢሑ መምጣት ለማዘጋጀት ይህንን የነጻነትና የብጥብጥ ጊዜ የተጠቀመው እንዴት ነው? ሐ) ከአይሁድ መሪዎች አሉታዊ ምሳሌነት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ስለ ኣመራር ምን ሊማሩ ይችላሉ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

2 thoughts on “የሴሉሲድ አገዛዝ ዘመንና ነጻነት”

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading