ማርቆስ ወንጌሉን ለማን ጻፈ?

ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው በቀዳሚነት ለአይሁዶች ሲሆን፥ ማርቆስ ስለ አሕዛብ አንባቢዎች ያሰበ ይመስላል። አንዳንድ ምሑራን ማርቆስ በዋናነት ያተኮረው በሮም ከተማ በሚኖሩት ሮማውያን ላይ እንደሆነ ያስባሉ። እርሱም በወንጌሉ አሕዛብ የማይረዷቸውን የአይሁድ ልማዶችን (ማር. 7፡2-4 አንብብ) እና የአረማይክ ቃላትን (ማር. 3፡17 አንብብ።) ያብራራል። በተጨማሪም፥ ከሌሎች መጻሕፍት በላይ ጥንታዊ የሮማውያን ቋንቋ የሆነውን የላቲን ቃላት ይጠቀማል። ማርቆስ ስለ ስደትና ሰማዕትነት ጭብጦች ልዩ ፍላጎት ያለው ይመስላል (ማር 8፡34-38፤ 13፡9-14)። ይህን ያደረገው ምናልባት፥ ብዙ ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ሲሞቱ በመመልከቱና ጴጥሮስና ጳውሎስም በእስር ላይ በመሆናቸው ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። ማርቆስ፥ ስምዖን የአሌክሳንድሮስ የሩፍስ አባት እንደነበር መግለጹ ለሮም መጻፉን ሊያመለክት ይችላል (ማር. 15፡21)። ምናልባትም ይህ ሩፎስ፥ ጳውሎስ በሮሜ 16፡13 የጠቀሰው ግለሰብ ሊሆን ይችላል። ብዙ ምሑራን የማርቆስ እጥር ምጥን ያለ አጻጻፍ፥ ለሮማውያን ተስማሚ እንደነበረ ይናገራሉ። በተጨማሪም፥ የማርቆስ ወንጌል በሮም ቤተ ክርስቲያን እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት በፍጥነት ተቀባይነትን ማግኘቱ መጻሕፉ በሮም በሚገባ ይታወቅ እንደነበር ያመለክታል።

የማርቆስ ወንጌል የተጻፈበትን ዘመንና ስፍራ፥ እንዲሁም ብዙ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉበትን ትክክለኛ ጊዜ ማወቅ፥ አስቸጋሪ መሆኑ ቀደም ሲል ተገልጾአል። አብዛኛዎቹ መጻሕፍት በተጻፉባቸው ጊዜያት ላይ ምሑራን በአሳብ ይለያያሉ። ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች፥ የማርቆስ ወንጌል ስለተጻፈበት ዘመን ሁለት የሚጋጩ መረጃዎችን ይሰጣሉ። አንዳንዶቹ ማርቆስ፥ ጴጥሮስ በ64 ዓ.ም. ሰማዕትነትን ከተቀበለ በኋላ እንደ ተጻፈ ሲናገሩ፥ ሌሎች ደግሞ ጴጥሮስ በሕይወት በነበረበት ጊዜ እንደ ተጻፈ ያስረዳሉ።

ምሑራን የማርቆስ ወንጌል እንደ ተጻፈ የሚናገሩበት ዘመን፥ ማቴዎስ ይህንኑ ወንጌል በምንጭነት ከመጠቀሙ ወይም ካለመጠቀሙ ላይ ይወሰናል። ማርቆስ ከማቴዎስ የሚቀድም ከሆነ፥ የተጻፈው በ50ዎቹ መጨረሻ ወይም በ60ዎቹ መጀመሪያ መሆን አለበት። አንዳንዶች ከ45-60 ዓ.ም. እንደ ተጻፈ ያስባሉ። ከማቴዎስ ካልቀደመ፥ ምናልባትም የተጻፈው ከ65-70 ዓ.ም. ነው ማለት ነው።

አብዛኞቹ ምሑራን ማርቆስ ወንጌሉን የጻፈው በሮም በነበረ ጊዜ እንደሆነ ያምናሉ። በ60 ዎቹ ዓመታት ውስጥ፥ ማርቆስ በአብዛኛው ሮም ውስጥ እንደነበረ እናውቃለን። መጀመሪያ ከጳውሎስ፥ ቀጥሎም ከጴጥሮስ፥ በመጨረሻም ከጳውሎስ ጋር እንደገና ኖሯል። የማርቆስ ወንጌል ለሮማውያን መጻፉ ደግሞ ይህን አሳብ ያጠናክረዋል። ማርቆስ ኔሮ ክርስቲያኖችን በሚያሳድድበት ጊዜ፥ ወንጌሉን እንደ ጻፈ የሚያመለክቱ መረጃ ዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፥ ብዙ ክርስቲያኖች በስታዲዮም ውስጥ ከዱር አራዊት ጋር እንዲታገሉ ይደረግ ነበር። (ክርስቲያኖቹ እርጥብ የዱር እንስሳት ቆዳ ለብሰው ከተኩላዎችና ከሌሎችም እንስሳት ጋር እንዲታገሉ ይደረግ ነበር)። ክርስቶስ በተፈተነ ጊዜ ከዱር አራዊት ጋር መሰንበቱን የሚገልጸው የማርቆስ ወንጌል ብቻ ነው (ማር. 1፡13)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading