Site icon

የማርቆስ ወንጌል መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከወንጌላት ሁሉ የትኛውን ማንበብ የበለጠ ደስ ይልሃል? ለምን? ለ) ስለ ማርቆስ ወንጌል ከመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ እንብብ። ስለ ደራሲው ማንነት፥ ስለ እርሱ ስለምታውቀው ነገር፥ እንዲሁም ስለ ማርቆስ ወንጌል የሚያስረዱ ሌሎች ልዩ ነገሮችን ጠቅሰህ አንድ አጭር አንቀጽ ጻፍ።

የማቴዎስ ወንጌል የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን በጣም የተጠቀመችበት መጽሐፍ ሲሆን፥ ማርቆስ ግን ያንን ያህል ታዋቂ አልነበረም። ክርስቲያኖች የቅዱሳት መጻሕፍት አካል እንደሆነ ቢያውቁም። የማቴዎስና የሉቃስ ጥንቅር ነው ብለው ስላሰቡ፥ ከማርቆስ ይልቅ ማቴዎስንና ሉቃስን መጠቀምን መረጡ። ይህም ሆኖ፥ መንፈስ ቅዱስ ማርቆስ ይህን መጽሐፍ እንዲጽፍ እንዳነሣሣውና ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እንዳሰፈረው መዘንጋት የለብንም። ስለሆነም፣ ይህንንም ጠቃሚ መጽሐፍ ማንበብና ማጥናት ይኖርብናል።

ብርቱካን የታወቀች ክርስቲያን ልጅ ነበረች። አባቷ ለእምነታቸው ብዙ መከራ ተቀብለዋል። እርስዋም እግዚአብሔርን የምትወድና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በትጋት የምታገለግል ልጅ ነበረች። ከዘማሪ ቡድን ጋርም ሆነ ብቻዋን ትዘምር ነበር። በመንፈሳዊ ብስለቷ ምክንያት ሽማግሌዎች መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተምራ እንድትመለስና የሴቶችን አገልግሎት እንድትመራ መረጧት። ሥልጠናዋን ጨርሳ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ስትመለስ ከፍተኛ ስደት ተነሣ። ብርቱካን ከቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች አንዱ ስለነበረች ስደቱ ጸናባት፡ ፈተናው ስላስፈራት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን ትታ ለሌላ ድርጅት በጸሐፊነት ተቀጠረች። እምነቷን ባትተውም፥ ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመሄድና ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ከመተባበር ተቆጠበች። ስደቱ ካለፈ በኋላ ብርቱካን ወደ ቤተ ክርስቲያን ተመልሳ ለመሥራት ፈለገች።

የዉይይት ጥያቄ፡– ከዚያች ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች አንዱ ብትሆን ኖሮ ብርቱካን ወደ ቤተ ክርስቲያን ተመልሳ እንድትሠራ ልትፈቅድላት ይገባል ትላለህ? ለምን?

የማርቆስ ወንጌል ደራሲ

ከጥንት ጀምሮ፥ ዮሐንስ ማርቆስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያለውን ሁለተኛውን ወንጌል እንደ ጻፈ ይታመናል። የመጽሐፉ ርእስ «የማርቆስ ወንጌል» የሚል ሲሆን፥ ይህም ከመጀመሪያው ሰነድ ላይ የነበረ ወይም ከአጭር ጊዜ በኋላ የተጨመረበት ነው ተብሎ ይታመናል። ዮሐንስ ማርቆስ የዚህ ወንጌል ደራሲ በመሆኑ ላይ ሁሉም የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የታሪክ ምሑራንና ጸሐፊዎቹ ይስማማሉ። አንድ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ዮሐንስ ማርቆስ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ወይም የሕይወቱና የአገልግሎቱ የዓይን ምስክር ባይሆንም፥ ሁለተኛውን ወንጌል እንደ ጻፈ ገልጾአል። ቀዳሚ የመረጃ ምንጩ ጴጥሮስ እንደነበረ እናውቃለን። (1ኛ ጴጥ. 5፡13 አንብብ።) በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ የተናገረውን አሳብ በመስማት ማርቆስ ቅደም ተከተላዊ ባልሆነ መንገድ ትክክለኛ መልእክት አስፍሯል። ብዙ ዘመናዊ ምሑራን ማርቆስ ይህን ወንጌል እንዳልጻፈ ያስባሉ። ምክንያታቸውም መጽሐፉ የተጻፈው ስለ ክርስቶስ የሚነገሩ ታሪኮች የሚሰራጩበት ጊዜ ካለፈ በኋላ በመሆኑ ነው። ይሁንና ስለ ዮሐንስ ማርቆስ ደራሲነት የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን የታሪክ ጸሐፊዎች የሰጡትን ምስክርነት ለመጠራጠር የሚያስችል በቂ ምክንያት የለም።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዮሐንስ ማርቆስ ብዙ መረጃ አይሰጠንም። አይሁዳዊ ስሙ ዮሐንስ ሲሆን፥ የላቲን ቤተሰባዊ ስሙ ማርቆስ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስና በታሪክ በአጠቃላይ ማርቆስ ተብሎ ተጠርቷል። የእናቱ ስም «ማርያም» ይባላል (የሐዋ. 12፡12)። ስለ አባቱ የተጠቀሰ ነገር የለም። ይህም አባቱ ክርስቲያን እንዳልነበረ ወይም ቀደም ብሎ እንደ ሞተ ያመለክታል። በኢየሩሳሌም ሀብታም በሚባል ቤተሰብ ውስጥ አደገ። ይህም እናቱ ክርስቲያኖች ተሰባስበው የሚያመልኩበት ትልቅ ቤት የነበራቸውና ባሪያ አሳዳሪ እንደ ነበሩ ይታወቃል። በርናባስ የማርቆስ የአጎት ልጅ ነበር። ቢያንስ ክርስቶስ ሊሰቀል አቅራቢያ ማርቆስ ከክርስቶስ ጋር ሳይገናኝ እንዳልቀረ ይገመታል። ብዙ ምሑራን የክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ የመጨረሻው እራትና የበዓለ ኀምሳ ሥነ ሥርዓት በዮሐንስ ማርቆስ ቤት እንደ ተካሄደ ያስባሉ። ክርስቶስ እራቁቱን ተይዞ በተወሰደ ጊዜ፥ በጌቴሴማኒ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ስለነበረው «ወጣት» የጠቀሰው ማርቆስ ብቻ በመሆኑ (ማር.14፡51-52)፥ ምሑራን ይህ ወጣት ራሱ ዮሐንስ ማርቆስ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ።

ዮሐንስ ማርቆስ መጀመሪያ የተጠቀሰው ከያዕቆብ በኋላ በሐዋርያት ሥራ 12፡12-17 ነው። ጴጥርስ ከእስር ቤት በተፈታ ጊዜ፥ ክርስቲያኖች በማርቆስ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ሲጸልዩ እንደ ነበረ አይጠረጠርም። በርናባስና ጳውሎስ የመጀመሪያውን የወንጌላዊነት ጉዞ ሲጀምሩ፥ በርናባስ የአክስቱን ልጅ ይዞት መጣ። ይህንን ያደረገው ምናልባትም እንዲረዳቸው በማሰብ ሳይሆን አይቀርም (የሐዋ. 13፡4-5)። የበርናባስ የትውልድ ከተማ ወደሆነችው ቆጵሮስ ሲደርሱ፥ ማርቆስ አብሯቸው ነበር፡ ጵንፍልያ በደረሱ ጊዜ ግን ማርቆስ ከቡድኑ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ (የሐዋ. 13፡13)። ለምን ተመለሰ? ምክንያቱን በትክክል ባናውቅም፥ አያሌ ግምቶች አሉ።

በመጀመሪያ፥ አንዳንዶች መንፈስ ቅዱስ ለዚህ ጉዞ የጠራው በርናባስንና ጳውሎስን ብቻ ስለነበር (የሐዋ. 13፡2)፥ ማርቆስ የወንጌላዊነት ጥሪ አልነበረውም ይላሉ። ነገሮች አስቸጋሪ ሲሆኑበት፥ አገልግሎቱን ተወ።

ሁለተኛ፥ ሌሎች ደግሞ ጳውሎስ ቡድኑን መምራት ሲጀምር፥ ማርቆስ እንደ ተበሳጨ ያስባሉ። ከሐዋርያት ሥራ ጥናት እንደምንረዳው፥ ከታሪኩ መጀመሪያ አካባቢ የበርናባስ ስም ቀድሞ ይጠቀስ ነበር (የሐዋ. 13፡2)። ይህም በርናባስ የቡድኑ መሪ እንደ ነበረ ያሳያል። ከጵንፍልያ በኋላ ግን፥ ጳውሎስ የቡድኑ መሪ በመሆኑ በተቀዳሚነት ይጠቀስ ጀመር (የሐዋ.18፡9፣13 )።

ሦስተኛ፣ ሌላው ግምት፥ ጳውሎስ በጣም እንደ ታመመ የሚያመለክት ነው። (ገላ. 4፡14 አንብብ።) ማርቆስ የጳውሎስን ችግሮችና ሥቃይ በተመለከተ ጊዜ ፈርቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

አራተኛ፣ አንዳንዶች ማርቆስ ወንጌሉ ከአይሁዶች ይልቅ ወደ አሕዛብ እየተስፋፋ መሄዱን ሲያይ፥ ተበሳጭቶ እንደ ተመለሰ ያስባሉ። በአሕዛብ አገሮች ውስጥ ከማደጋቸው የተነሣ ከአሕዛብ ጋር ለመሥራት ከማይቸገሩት ጳውሎስና በርናባስ በተቃራኒ፥ ማርቆስ በኢየሩሳሌም ነበር ያደገው። ከዚህም የተነሣ፥ ጠባብ አመለካከት ይዞ በአይሁዶች ላይ ለማተኮር ፈለገ። ለአሕዛብ የሚሰጠው አገልግሎት ለእርሱ የሚስማማ አልሆነም።

ከአያሌ ዓመታት በኋላ፥ ጳውሎስና በርናባስ ለሁለተኛው የወንጌል ጉዞ ተሰናዱ (የሐዋ 15፡36፡41)። በርናባስ ለማርቆስ ሁለተኛ ዕድል ለመስጠት ፈለገ፡፡ በርናባስ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ማርቆስ ከመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ አቋርጦ በመመለሱ የተሰማውን ሐፍረት እንዲያስወግድና በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አገልግሎቱን ከግቡ ያላደረሰ ሰው ሆኖ እንዳይታወቅ ለማገዝ ስለፈለገ ይሆናል። ጳውሎስ ግን ቀደም ሲል ማርቆስ ቡድናቸውን ትቶ በመመለሱ በጥልቀት ቆስሎ ስለነበር፥ የበርናባስን አሳብ ለመቀበል ተቸገረ። ጳውሎስ፥ «ማርቆስ ቀደም ሲል አስቸጋሪውን የወንጌል ጉዞ ለመወጣት ስላልቻለ፥ አሁን አንፈልገውም» ሳይል አልቀረም። ይህ ጉዳይ በጳውሎስና በርናባስ መካከል ከባድ የአሳብ ልዩነት አስከተለ። ከሁለቱ አንዳቸውም አቋማቸውን ለማለዘብ ሳይፈቀዱ ቀሩ። በመጨረሻም፥ በተለያዩ አቅጣጫዎች ተሰማሩ። በርናባስ ማርቆስን ይዞ ወደ ቆጵሮስ ተመለሰ። ሉቃስ በጳውሎስ ላይ ስላተኮረ ስለነበርናባስ አገልግሎት ቀጣይ ውጤት የተጠቀሰ ነገር የለም። ጳውሎስ ሲላስን ይዞ ዛሬ ቱርክ ውስጥ ወደምትገኘው ገላትያ ተመለሰ። ይህ ሁኔታ በጳውሎስና በርናባስ ላይ ካስከተለው የልብ ኀዘን ባሻገር፥ እግዚአብሔር ሁኔታዎችን በመከታተል ላይ ነበር። በመሆኑም፥ ወንጌልን ለማሰራጨት የተሰማሩ ሁለት የወንጌል መልእክተኛ ቡድኖች ሊኖሩ ቻሉ።

ከ 10 ዓመታት በኋላ ጳውሎስ በሮም በታሰረበት ወቅት፥ ማርቆስ አብሮት እንደ ነበረ እንረዳለን። ማርቆስ ከጳውሎስ ጋር እንደገና አብሮ መሥራት ጀመረ። (ቆላ. 4፡10 አንብብ።) በዚህ ጊዜ ማርቆስ በእምነቱ የበሰለ ሆነ፥ ጳውሎስ ደግሞ ይቅር ማለትንና ለሰዎች ሁለተኛ ዕድል መስጠትን ተምሮ ነበር። ከዚያ በኋላ ማርቆስ ወደ ጴጥሮስ ዘንድም የሄደ ይመስላል። ይህንንም የምናውቀው ጴጥሮስ አንደኛ መልእክቱን በሚጽፍበት ወቅት አብሮት ስለነበረ ነው (1ኛ ጴጥ. 5፡13)። ጴጥሮስ ማርቆስን በጣም ስለ ወደደው እንደ ልጁ ቆጠረው። ከአያሌ ዓመታት በኋላ ጳውሎስ ለእምነቱ ሊሠዋ ሲቃረብ፥ ለሁለተኛ ጊዜ በሮም በታሰረበት ወቅት ማርቆስ እንዲጎበኘው ጠይቋል (2ኛ ጢሞ. 4፡11)። በዚህ ጊዜ ማርቆስና ጢሞቴዎስ የጳውሎስ የቅርብ ወዳጆች ነበሩ።

የዉይይት ጥያቄ፡- በአገልግሎታቸው ለሚሰናከሉ ሰዎች ሁለተኛ ዕድል ስለ መስጠት፥ የማርቆስ ታሪክ ምን ያስተምረናል?

እንደ ማርቆስ ሁሉ፥ ብርቱካንም ከአገልግሎቷ ተደናቅፋለች፥ ሁኔታዎች አስቸጋሪ በሆኑበት ወቅት አገልግሎቷን ትታለች። ነገር ግን በምንወድቅበት ጊዜ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ሁለተኛ ዕድል ለመስጠት ፈቃደኛ ነው። አለዚያ ማናችንም በአገልግሎት ውስጥ ልንሆን አንችልም። እኛም ሰዎችን ይቅር ልንልና፥ በእምነታቸው እንዲጠነክሩ ልንረዳቸው ይገባል። እየበሰሉ በሚሄዱበት ወቅት፥ የቀድሞዎቹን ስሕተቶች አልፈን ወደ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና ኅብረት ልንመልሳቸው ይገባል። ማርቆስ ለጴጥሮስና ጳውሎስ ታላቅ አጋዥ ከመሆኑም በላይ፥ መንፈስ ቅዱስ ሁለተኛውን ወንጌል እንዲጽፍ መርጦታል። እግዚአብሔር ሁልጊዜም ንስሐ የሚገቡትን ሰዎች ይቅር በማለት እንዲያገለግሉት ሁለተኛ ዕድል ይሰጣቸዋል።

ጳውሎስ ከሞተ በኋላ ማርቆስ ስለነበረበት ሁኔታ የተጠቀሰ ነገር የለም። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚለው ግን ወደ ግብጽ ሄዶ በአሌክሳንደሪያ ለቤተ ክርስቲያን ምሥረታ እገዛ አድርጓል። አሌክሳንደሪያ ከክርስትና ዐበይት ማዕከላት አንዱ ለመሆን በቅታ ነበር። ማርቆስ በኔሮ የአገዛዝ ዘመን ለእምነቱ እንደ ተሠዋ ይታሰባል። ማርቆስ ወጣት በነበረ ጊዜ ቢሸሽም፥ በኋላ ለክርስቶስ ለመሞት ፈቃደኛ ሆኗል።

ማርቆስ የክርስቶስን ታሪክ ለመሰብሰብ ብዙ ጊዜ ነበረው። ወጣት ሳለ ሐዋርያት ቤቱ ውስጥ ይሰባሰቡ ስለነበር፥ አብዛኛዎቹን ታሪኮች ለመስማት ሳይታደል አልቀረም። በኋላ ከጴጥሮስ ጋር ሲሠራ ተጨማሪ ታሪኮች ሊሰማ፥ እንዲሁም ግልጽ ያልሆኑለትን ጉዳዮች እየጠየቀ ማብራሪያ ሊያገኝ ችሏል። ማርቆስ ወንጌሉን የጻፈው ጳውሎስ በሕይወት እያለ ይሁን ከሞተ በኋላ የምናውቀው ነገር የለም። ይሁንና የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች፥ የማርቆስን ወንጌል መጻፍ ከጴጥሮስ ጋር በቅርብ ያዛምዱታል። ይህ ወንጌል ያለ ብዙ ውጣ ውረድ የአዲስ ኪዳን ክፍል ተደርጎ ከተወሰደባቸው ምክንያቶች አንዱ ይኼ ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version