የኢየሱስ የመጀመሪያ አገልግሎት ማጠቃለያ (ማር. 1:14-39)

እንደ ማቴዎስ ሁሉ፥ ማርቆስ ስለ ኢየሱስ የመጀመሪያ ክፍል ይፋዊ አገልግሎት አልዘገበም። ይህም ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስ እስከታሰረበት ጊዜ ድረስ በግልጽ አለመሥራቱን የሚያመለክት ይመስላል። ከመጥምቁ ዮሐንስ ጋር እየተፎካከረ አልነበረም።

ሀ. የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት መጠራት (ማር. 1፡14-20)። ኢየሱስ ይፋዊ አገልግሎቱን በጀመረ ጊዜ፥ መልእክቱ ከዮሐንስ ጋር ተመሳሳይና የተለየም ነበር። ዮሐንስ ወደፊት እያመለከተ ሰዎችን ሲያዘጋጅ፡ ኢየሱስ ግን፥ «ጊዜው ደርሷል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች» ብሏል። ኢየሱስ አሁን ስለ ነገሠ፥ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ሊገባ ተቃርቦ ነበር፡፡ አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚገባው እንዴት ነው? እንደ ዮሐንስ ሁሉ፥ ክርስቶስም ንስሐ በመግባትና የምሥራቹን ቃል በማመን መሆኑን ተናግሯል።

ክርስቶስን መከተል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማርቆስ ለመጀመሪያ ጊዜ ይነግረናል። ስምዖን፥ እንድርያስና ዮሐንስ በእግዚአብሔር እንደ ተጠሩ ሁሉ ክርስቶስ እያንዳንዳችንን እየጠራ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የዓሣ ማጥመጃ መረቦቻቸውንና የቤተሰቦቻቸውን የአኗኗር ዘይቤ ትተው፥ ክርስቶስን እንደ ተከተሉ ሁሉ፥ እኛም ክርስቶስን ለመከተል አሮጌውን አኗኗራችንን መተው አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡- የክርስቶስ ተከታይ ለመሆን ስትወስን ሕይወትህ እንዴት እንደ ተለወጠ ግለጽ።

ለ. ኢየሱስ በአጋንንት ላይ የነበረው ኀይል የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ያሳያል (ማር. 1፡21-28)። ለማርቆስ፥ የክርስቶስን መለኮታዊ ባሕርይ ጥርት አድርገው የሚያሳዩት ነገሮች አንዱ፥ በአጋንንት ላይ የነበረው ኃይል ነበር። በአጋንንት የተያዘ ሰው ክርስቶስን እንዳየ ወዲያውኑ “ቅዱስ-የእግዚአብሔር ልጅ” እንደሆነ ይናገር ነበር። ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፥ አጋንንት የክርስቶስን አምላክነት ያውቁ ነበር፡ ስለዚህ የትእዛዝ ቃል ታዝዘውት ከያዟቸው ሰዎች ስለሚወጡ፥ ክርስቶስ በእነርሱ ላይ ሙሉ ሥልጣን ነበረው።

ነገር ግን ሰዎችን ያስደነቀው ክርስቶስ በአጋንንት ላይ የነበረው ኀይል ብቻ አልነበረም። የክርስቶስ ትምህርት በጣም የተለየ መሆኑንም ተገንዝበው ነበር። ማርቆስ በዚህ የክርስቶስ የመጀመሪያው ክፍል አገልግሎት ሰዎች መደነቃቸውን በአጽንኦት ጠቅሷል። ክርስቶስ በሙሉ ሥልጣን አዲስ ትምህርት ያስተምር ነበር (ማር. 1፡27)። ክርስቶስ ፈሪሳውያን እንደሚያደርጉት ሁሉ፥ ትምህርቱን ከታወቁ የሃይማኖት መሪዎች እንዳገኘ ሰው፥ በእግዚአብሔር ሥልጣን አስተምሯል።

ሐ. ኢየሱስ በበሽታ ላይ የነበረው ሥልጣን የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን መስክሯል (ማር. 1፡29-39)። ማርቆስ ከጴጥሮስ አማት ጀምሮ፥ የትኛውንም በሽታ የመፈወስ ኃይል እንደነበረው አመልክቷል። ማርቆስ ክርስቶስ በአጋንንት ላይ የነበረውን ኀይል እንደገና ገልጾአል። በዚህ ጊዜ ግን ክርስቶስ ከአጋንንት ጋር ስለነበረው ግንኙነት አንድ ነገር ጨምር ጠቅሷል። ይህም ክርስቶስ አጋንንትን በሚያስወጣበት ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በይፋ እንዳይናገሩ ከልክሏቸዋል። ይህ ማርቆስ ካተኮረባቸውና ለየት ካሉ የክርስቶስ ባሕርያት አንዱ ነበር። ክርስቶስ ስለ ማንነቱ ለሰዎች እንዳይናገሩ አጋንንትን የከለከላቸው ለምንድን ነው? ምናልባትም ሁለት ምክንያቶች ነበሩት። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ ዝናንና ክብርን አልፈለገም። እርሱ የፈለገው ሰዎች ትምህርቱን ሰምተው ሕይወታቸውን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲያስተካክሉ ነበር። እርሱ ዛሬ ብዙ ሰው ለመሳብ ተአምራትን እንደሚያደርጉና አጋንንትን እንደሚያስወጡ አገልጋዮች አልነበረም። ሁለተኛ፣ ክርስቶስ ከትክክለኛ ምንጭ የመጣ ምስክርነት ነበር የፈለገው፡፡ አጋንንት ስለ ማንነቱ እንዲመሰክሩለት አልፈለገም ነበር።

ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን ታዋቂነት በመደገፍ ተአምራቱንና ፈውሱን ሲያደንቁ ሳሉ፥ ክርስቶስ አጽንኦት የሚሰጠው ለስብከት መሆኑን ገልጾላቸዋል። በአንድ ስፍራ ተወስኖ የሰዎችን ፍላጎት ከማሟላት ይልቅ፥ ብዙ ሰዎች ቃሉን ሰምተው የሚያምኑበትን ዕድል ለመስጠትና ለመንግሥቱ እንዲዘጋጁ ለማድረግ ፈለገ፡፡ ክርስቶስ «እኔ የመጣሁት ለዚሁ ነው» ሲል ተናገረ። ምንም እንኳ ለማኅበረ ምእመኖቻችን እንክብካቤ ማድረግ ቢኖርብንም፥ በማኅበረ ምእመናኑ ላይ ብቻ ማተኮሩ በቂ አይደለም። የቤተ ክርስቲያን ጥሪ ወደ ጠፉት መድረስ ስለሆነ፥ እያንዳንዷ ቤተ ክርስቲያን፥ «ወንጌሉን ላልሰሙት ለማዳረስ ምን እያደረግን ነው?» እያለች ራሷን መጠየቅ አለባት።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) የክርስቶስ የፈውስ አገልግሎትና፥ ስለ ታዋቂነት የነበረው አመለካከት ዛሬ ከሚታየው የብዙ ሰዎች ሁኔታ የሚለየው እንዴት ነው? ለ) ክርስቶስ ይህንን አመለካከት ያሳየው ለምን ይመስልሃል? ሐ) ተደናቂ ስም ለማግኘትና በተአምራት አማካኝነት የሰዎችን ልብ ወደ ራሳችን ወይም ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ከመሳብ እንድንቆጠብ ሊያስጠነቅቀን የሚገባው እንዴት ነው? መ) ቤተ ክርስቲያንህ የምእመኖቿን ፍላጎቶች በማሟላት ብቻ ሳትወሰን ወንጌሉን ለሌሎች ለማዳረስ ምን እያደረገች ነው?

ክርስቶስ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው ነበረ። እንደ ሰው፥ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት መጠበቅ ያስፈልገው ነበር። ብቻውን የሚሆነው ጠዋት በማለዳ ብቻ በመሆኑ፥ ከሌሎች ሰዎች ተለይቶ ከእግዚአብሔር ጋር ይገናኝ ነበር። ማርቆስ፥ ክርስቶስ ይህንን ማድረግ ካስፈለገው፥ እኛም በበለጠ ማድረግ እንዳለብን ያስተምረናል። ይህንኑ አሳብ የገለጸው ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ ጊዜ ማሳለፍ የመንፈሳዊ ሕይወትና አገልግሎት ኃይል ምንጭ ነው ለማለት ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: