Site icon

የሉቃስ ወንጌል ዐላማ እና የመጥምቁ ዮሐንስ በተአምር መፀነስ (ሉቃስ 1:1-25)

ደመራዝ የአንድ ዕውቅ ወንጌላዊ ልጅ ነበረች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ የጸሐፊነት ሥልጠና እንድታገኝ እግዚአብሔር ረዳት። ከዚያም ለአንድ ነጋዴ ተቀጥራ ለመሥራት አሰበች። አንድ ቀን አንድ ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ የመጣ ወንጌላዊ ለጋብቻ ጠየቃት። የወንጌላዊው ጥያቄ ደመራዝን አስከፋት። ሰውዬው የገጠር ወንጌላዊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፥ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ያጠናቀቀው በቅርቡ ነበር፡ ደመወዙ ትንሽ ስለሆነ ይጠቅሙኛል ብላ የምታስባቸውና የወርቅና የብር ስጦታዎች ሊያቀርብላት እንደማይችል ተገንዝባለች። ብሔሩም ቢሆን እርሷ ከምታከብራቸው ብሔሮች መካከል አልነበረም። ከሰውዬው ሁኔታ የሚስባት ምንም ነገር ስላልነበረ በፍጥነት አሉታዊ ምላሿን ሰጠችው። ውሎ ሲያድር ግን እግዚአብሔር በልቧ ውስጥ መሥራት ጀመረ። «ከእኔ በላይ ምቹ ሕይወት ትፈልጊያለሽ? ከትምህርትሽ በላይ እኔን ትወጅኛለሽ? ከክብርሽ በላይ እኔን ትወጅኛለሽ? ይህን ወንጌላዊ እንድታገቢው እፈልጋለሁ። ፈቃደኛ ነሽ?» ሲል እግዚአብሔር አፋጠጣት። ጓደኞቿን ስታማክር፣ «ድሃ ወንጌላዊ ለማግባት ማሰብሽ ራሱ ዕብደት ነው» ሲሉ መለሱላት። መጫወቻም አደረጓት። ወላጆቿም የማይመጥናትን ሰው ልታገባ ነው ብለው ስለተበሳጩ፥ ሁኔታው በጣም አናጋት፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ደመራዝ ምን ማድረግ ያለባት ይመስልሃል? ለ) ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር እንድናደርግ የሚፈልጋቸው ነገሮች የተሻለ ደረጃ፣ ክብርና የተሻለ የሕይወት መንገድ ያመጡልናል ብለን የምናስበው እንዴት ነው?

አብዛኛውን ጊዜ ለራሳችንና ለልጆቻችን ውሳኔ የምንሰጠው ራስ ወዳድና ዓለማዊ መመዘኛዎችን መሠረት አድርገን ነው። ስለዚህ የልባችንን መሻት ለመግለጽ ለልጆቻችን መልካሙን ሁሉ እንመኛለን። ስለዚህ ልጆቻችን ጥሩ ትምህርትና ጥሩ ሥራ እንዲያገኙ፣ ከሀብታም ወይም ከዝነኛ ቤተሰብ ጋር እንዲጋቡ እንፈልጋለን? ወይስ ትልቁ ፍላጎታችን ልጆቻችን በጌታ መንገድ ሲመላለሱ፣ ሲታዘዙትና የዓለምን ምቾት መጣል በሚያስፈልግበት ሁኔታ እንኳን እግዚአብሔርን ሲያገለግሉ ማየት ነው? የቤተ ክርስቲያን መሪ ልጆች አነስተኛ ደመወዝ በሚያስገኝ የወንጌላዊነት ሥራ ላይ ተሰማርተው እግዚአብሔርን የማያገለግሉት ለምንድን ነው?

ዛሬ እግዚአብሔር አንዲት ወጣት እጅግ ከባድ ውሳኔ እንድታደርግ እንዴት እንዳደረገ እንመለከታለን። ይኸውም በሰብአዊ ባሕል ባል ሳታገባ የእርሱን ልጅ በማሕፀኗ ውስጥ እንድትሸከም አድርጓል። ይህች ወጣት የጓደኞቿን ሽሙጥ ታግሣ ፅንሱን በማሕፀንዋ ውስጥ ትሸከማለች? የወላጆቿን ቁጣም ለመታገሥ ፈቃደኛ ነበረች? እጮኛዋ መተጫጨታቸውን እንዲያፈርስ ፈቅዳለች? ከአምልኮ ቦታዋ ለመባረር ፈቃደኛ ሆናለች? ማርያም እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ስለ መረጠችና የዓለምን ውርደት ለመቀበል ስለ ፈቀደች እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። ይህች ወጣት በዓለም ሁሉ የታወቀች ለመሆን በቅታለች። እግዚአብሔርን ለመታዘዝና እርሱ በሚፈልገው መንገድ ለመኖር ስንወስን፣ ዓለም ልትስቅብን፣ ወላጆቻችን አሳባችንን ላይረዱት፣ እኛም መልካሙን ስማችንንና ሕይወታችንን ልናጣ ብንችልም፣ በሰማይ ስማችን የከበረ ይሆናል። እግዚአብሔርም የሚገባንን ዋጋ ይሰጠናል።

  1. ሉቃስ መጽሐፉን የጻፈበት ዐላማ (ሉቃስ 1፡1-4)

ሉቃስ የኢየሱስን ሕይወትና ሞት በዐይኑ አልተመለከተም። ነገር ቀን ከኢየሱስ ጋር የነበሩ ሰዎች የነገሩትን ታሪክ ከመስማቱም በላይ፣ ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚገልጹ መጻሕፍትም አንብቧል። ሉቃስ የተማረ ሰው በመሆኑ እምነቱን በሌሎች እምነት ወይም ታሪክ ላይ ብቻ ሳይሆን፥ በእውነት ላይ እንዲመሠረት ይፈልግ ነበር። ለእምነቱ መሞት ካለበት ያመነው ነገር እውነት እስከ ሆነ ድረስ ሕይወቱን ቢያጣ ግድ አልነበረውም። ሉቃስ የኢየሱስን እውነት አምኖ ከተቀበለ በኋላ፥ ኢየሱስን አይተው ለማያውቁ ሌሎች ሰዎች ማሰብ ጀመረ። ስለሆነም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ መጽሐፉን ጻፈ።

በጥንት ሥነ ጽሑፍ እንደተለመደው፣ ሉቃስ መጽሐፉን የጻፈው ለሚያሳትምለት ሰው ነው። ስለሆነም በጊዜው ሀብታም ክርስቲያን ለነበረው ቴዎፍሎስ ጻፈ። ሉቃስ መጽሐፉን የጻፈበትን ዓላማ ሲገልጽ ክርስቲያኖች እምነታቸው በእውነተኛ ታሪክ፣ ተአምራትን ባደረገው፣ ባስተማረውና ለዓለሙ ሁሉ በሞተው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንዲያውቁ ነበር። እንደ አስተዋይ ሳይንቲስት ሉቃስ ስለ ኢየሱስ የተጻፉትን መጻሕፍትና ታሪኮች በጥንቃቄ መርምሯል። የታሪኮቹን እውነተኝነት ካረጋገጠ በኋላም ሉቃስ ለዘመናት ሁሉ በታላቅነታቸው ከሚዘከሩ ታሪኮች አንዱን ሊጽፍ በቅቷል።

  1. የመጥምቁ ዮሐንስ በተአምር መፀነስ (ሉቃስ 1፡5-25)

ሉቃስ የታሪክ ምሑር እንደ መሆኑ መጠን፣ ሁኔታዎቹ የተፈጸሙበትን ጊዜ ጠቅሷል። እነዚህ ሁኔታዎች የተፈጸሙት የይሁዳ ንጉሥ በሆነው በሄሮድስ ዘመን ነበር። ሄሮድስ ከፊል አይሁዳዊና ከፊል አሕዛብ የነበረ ሲሆን ጳለስቲናን ከ37 እስከ 4 ዓ.ዓ. ድረስ ያስተዳድር የነበረው ታላቁ ሄሮድስ ነው። ከሌሎቹ ወንጌላት ጸሐፊዎች ይልቅ ሉቃስ፥ የመጥምቁ ዮሐንስንና የኢየሱስን ልደት ጨምሮ በነገሮች አጀማመር እጅግ የሚደነቅ ጸሐፊ ነው። በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር አዲስ የዘመን ምዕራፍ የሚከፍተውና መሪ የሚመርጠው፥ አንድ የተለየ ሰው ሲወለድ ነው (ለምሳሌ፣ ሳምሶን፣ ሳሙኤል)። እግዚአብሔር ለመጥምቁ ዮሐንስና ለኢየሱስም ተመሳሳይ ነገርን አድርጓል። ሉቃስ ታሪኩን የጀመረው ከኢየሱስ የስድስት ወራት ቅድሚያ በነበረው በመጥምቁ ዮሐንስ ታሪክ ነው።

ሉቃስ የእነዚህን ታሪኮች ዝርዝር ከየት አገኘ? ስለዚህ በእርግጥ የምናውቀው ነገር የለም። በዚህ ጊዜ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ በሕይወት ያሉ አይመስልም። ሆኖም ስለ ዮሐንስ ልደትና የኢየሱስ የልጅነት ጊዜ ካቀረበው ዝርዝር መረጃ በመነሣት ሉቃስ የኢየሱስ እናት ከሆነችው ከቅድስት ማርያም ጋር ሳይነጋገር እንዳልቀረ እንገምታለን። ቅድስት ማርያም የኢየሱስን የልጅነት ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ ከዘመዷ ኤልሳቤጥ የሰማችውን የዮሐንስንም ልደት ታሪክ በሚገባ ታስታውሳለች።

የመጥምቁ ዮሐንስ ወላጆች የነበሩት ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ሁለቱም ከአሮን የክህነት ሐረግ ወገን ሲሆኑ፤ ኑሯቸውን የመሠረቱት በይሁዳ ነበር። በዘመኑ ከነበሩት ብዙ ካህናት በተለየ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ትእዛዛቱን በመጠበቅ ይገልጹ ነበር። ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር ሕይወታቸውን ባርኮ ነበር ማለት አይደለም። ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ ለመውለድ የማይችሉ መካኖች ነበሩ። ስለ እነዚህ ሰዎች በምናስብበት ጊዜ ለእግዚአብሔር በመኖራችን ብቻ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ እናገኛለን ማለት አይደለም።

በጊዜው ካህናት ሁሉ በ24 መደብ የተከፈሉ ነበር። እያንዳንዱ የካህናት ቡድን በየተራ በቤተ መቅደሱ ውስጥ መሥዋዕቶችን በማቅረብና ሌሎች ተግባራትን በማከናወን ያገለግል ነበር። እነዚህ የአንድ ቡድን አባላት ዕጣዎችን በመጣል አንዱን ካህን ይመርጡና፥ የተመረጠው ካህን ወደ ቅድስቱ ይገባል። ይህ ካህን ዘይት በመቅረዙ ውስጥ በመጨመር፣ ልዩውን ቅዱስ ኅብስት በሳምንት አንድ ጊዜ በአዲስ ኅብስት በመተካትና ዕጣኑን በተገቢው ጊዜ በማጥንቱ ውስጥ በመጨመር ያገለግላል።

ይህ የአገልግሎት ዕጣም አንድ ቀን ለዘካርያስ ደረሰ። እርሱም በቅድስቱ ሙሉ ዕጣኑን እያጠነ ሳለ፥ የጌታ መልአክ ተገልጦለት እርሱና ባለቤቱ ኤልሳቤጥ ልጅ እንደሚወልዱ አበሰረው። መልአኩ ስለዚህ ልጅ በጣም ግልጽ የሆኑ መመሪያዎችን ጨምሮ ሰጠው። ልጁ «ዮሐንስ» ተብሎ እንደሚጠራም ነገረው። ትርጉሙም «እግዚአብሔር ቸር ነው» የሚል ነው። በዚህ አኳኋን እግዚአብሔር ለዘካርያስና ለኤልሳቤጥ ልጅ በመስጠት ቸርነቱን ገለጠላቸው።

ከሁሉም በላይ ግን እግዚአብሔር የዓለም አዳኝ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲወለድ ስማድረግ ለዓለም ሁሉ ቸርነቱን አሳየ።

ዮሐንስም እንደ ሳምሶን ሁሉ በናዝራውያን የአስተዳደግ ሥርዓትና ሕግ መሠረት ሳያድግ አልቀረም (ዘኁልቁ 6፡1-4 አንብብ)። ለምሳሌ፥ አልኮል እንዲጠጣ አልተፈቀደለትም ነበር። መልአኩ ዮሐንስ ለወላጆቹም ሆነ ለአይሁዶች በረከትን እንደሚያመጣ ገልጾአል። በእግዚአብሔርም ፊት ታላቅ ሰው ይሆናል ተብሏል። እግዚአብሔር የአይሁዶችን ልብ ወደ ራሱ ለመመለስ ይጠቀምበታል ብሏል። እርሱም በሚል. 4፡5-6 ላይ በተነገረው ትንቢት መሠረት ለመሢሑ መንገድ ጠራጊ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በተለየ መንገድ ከመወለዱ ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ እንደሚሆንም ተመስክሮለታል።

ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ለብዙ ዓመታት ልጅ ለማግኘት ያቀርቡት የነበረ ጸሎት ባለመሳካቱ ያዝኑ ነበር። ምናልባትም አንዳንድ መልካም ወዳጆቻቸው፣ «አይዟችሁ፣ እግዚአብሔር ጸሎታችሁን በመመለስ ልጅ ይሰጣችኋል» ሳይሏቸው አልቀሩም። ሆኖም ወዳጆቻቸው በየቀኑ በልጆቻቸው ተከብበው ሲሄዱ በሚያዩበት ጊዜ ልባቸው የበለጠ በሐዘን ሳይሞላ አልቀረም። ስለሆነም፣ መልአኩ ዘካርያስ ልጅ እንደሚያገኝ በነገረው ጊዜ በቃሉ ወዲያውኑ አላመነም። ምናልባትም የመልአኩን ቃል የተጠራጠረው፣ «እኔም ባለቤቴም አርጅተናልና ልጅ የመውለድ ተስፋ የለንም» በሚል ይሆናል። ምንም እንኳ ዘካርያስ እግዚአብሔርን የሚወድና በታዛዥነት የሚመላለስ ሰው ቢሆንም፣ እግዚአብሔር በአብርሃም ሕይወት ውስጥ ያደረገውን ተአምር አላስታወሰም።

የመልአኩ ምላሽ ግን በጣም ፈጣን ነበር። የዘካርያስን አፍ በመዝጋት፥ ኤልሳቤጥ ልጁን እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ ድዳ እንደሚሆን ነገረው። ሁኔታው በዚህ አብቅቶ ዘካርያስ ወደ ቤቱ እንደ ተመለሰ እግዚአብሔር ቃሉን አከበረ። ኤልሳቤጥም አረገዘች። ሆኖም ልብዋ በተለያዩ አሳቦች እንደ ተሞላ ምንም አያጠራጥርም። ምናልባት ፅንስዋ ቀኑን ጠብቆ በደህና ስለ መወለዱ ላትሰጋ አትቀርም። ያም ሆኖ የኋላ ኋላ ለማርገዝ በመቻሏም ደስ ብሏታል። ሉቃስ ለአምስት ወራት ያህል የትም ሳትሄድ ራሷን ደብቃ እንደቆየች ይነግረናል።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር እኛ በምንፈልገው መንገድ ጸሎታችንን ባለመመለሱ፥ ተስፋንና እምነትን ስለ ማጣት ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version