ሉቃስ 6፡1-16

«ጥሩ ክርስቲያን ከሆንህ፣ መጠጥ አትጠጣም፥ ፊልምም አታይም። ክርስቲያን ልጃገረዶች ደግሞ ጌጣጌጥ አያደርጉም ወይም ሱሪ አይለብሱም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችንና የጸሎት ስብሰባዎችን ሁሉ ትከታተላለህ። በሳምንት አንድ ጊዜ ትጾማለህ። አሥራትንና ምጽዋትን ትሰጣለህ። በእርግጥ ጥሩ ክርስቲያን ከሆንህ፣ በኳየር ወይም በወንጌላዊነት ታገለግላለህ።»

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እንዲህ ዐይነት ሥርዐቶች ለክርስቲያኖች ሲሰጡ የተመለከትህባቸውን ሁኔታዎች ግለጽ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ፣ ሌሎች ለክርስቲያኖች የሚሰጡ ሥርዐቶች ምንድን ናቸው? ለ) ክርስትናን ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚደረግ ግንኙነት ሳይሆን የትእዛዛት ዝርዝር አድርጎ መውሰዱ አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ከሰጣቸው ዐበይት ትምህርቶች መካከል አንዱ ብዙ የሰው ሕግ ከመጠበቅ ይልቅ፥ የልብ ንጹሕነት ዋጋ አለው። አንድ ሰው ሕጉን ሁሉ እየጠበቀ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ልብ ላይኖረው ይችላል። በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ያደረጉት ይህንኑ ነበር። ዛሬም ካሉብን ችግሮች መካከል አንዱ ይሄ ነው።

  1. ኢየሱስ የሰንበት ጌታ ነው (ሉቃስ 6፡1-11)

እንደ ሌሎቹ ወንጌሎች ሁሉ፣ ሉቃስም በኢየሱስና በሃይማኖት መሪዎች መካከል እየከረረ ስለመጣው ውጥረት ዘግቧል። እንደ ብዙዎቻችን፥ ፈሪሳውያንም ሃይማኖትን የሚመለከቱት የተወሰኑ ደንቦችን እንደ መጠበቅ አድርገው ነበር። ይህም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያስገኝልናል፣ ሰዎችም መንፈሳዊነታችንን ያውቁልናል ይሉ ነበር፡፡ መልካም የሃይማኖት ሰው ሕይወቱን የሚመረምረው በሚጠብቃቸው ደንቦች መሠረት ነው። ነገር ግን እንደ ብዙዎቻችን፥ ፈሪሳውያንም እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው ከእርሱና ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት እንደሆነ አልተገነዘቡም ነበር። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች በኢየሱስ ላይ እንዲነሡ ያደረገው ለሰው-ሠራሽ የሰንበት ደንቦች አለመገዛቱ እንደሆነ ከሉቃስ ዘገባ እንረዳለን።

ሉቃስ ሰንበትን አስመልክቶ ሁለት ግጭቶች መከሰታቸውን ገልጿል። አንደኛው፥ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በሰንበት እሸት ቀጥፈው ሲበሉ እየተመለከተ እንዳልገሠጻቸው የጠቀሰው ነው። ሉቃስ ይህንን ያደረገው እግዚአብሔር ከሰዎች ተግባር ይልቅ በልባቸው ደስ እንደሚሰኝና ልባቸው ትክክል እስከሆነ ድረስ ተግባሩን እንደሚፈቅድላቸው ለማመልከት ነው። ኢየሱስ የሰንበት ጌታ እንደ መሆኑ መጠን፣ የትኛው እግዚአብሔርን ደስ እንደሚያሰኝና የትኛው ደግሞ እንደሚያሳዝነው የመወሰን መብት አለው። ሁለተኛው እጁ የሰለለችውን ሰውዬ በሰንበት ቀን በመፈወሱ፣ ኢየሱስ እግዚአብሔር ሰው የፈጠራቸውን ሥርዐቶች ከመጠበቅ ሌሎችን በፍቅር መርዳት እንደሚበልጥ አሳይቷል። አይሁዶች በደንቦችና በባሕላዊ ድርጊቶች ላይ በማተኮር፣ ፍቅርና ርኅራኄ አስፈላጊ መሆናቸውን ዘንግተው ነበር።

  1. ኢየሱስ 12ቱን ሐዋርያት መረጠ (ሉቃስ 6፡12-16)

እንደ ሌሎቹ ተመሳሳይ ወንጌላት ሁሉ ሉቃስም ኢየሱስ ከተከታዮቹ መካከል 12ቱን መርጦ «ሐዋርያት» ወይም ዓላማዎቹን ለመፈጸም የተላኩ የኢየሱስ እንደራሴዎች ብሎ እንደ ሰየማቸው ያስረዳል። ሉቃስ ኢየሱስ እነዚህን ቁልፍ ሰዎች ለመሪነት ከመምረጡ በፊት፥ ሲጸልይ እንዳደረ ይነግረናል። ቤተ ክርስቲያን ከምታደርጋቸው ወሳኝ ውሳኔዎች መካከል ሰዎችን ለመሪነት ለማሠልጠንና መሪዎችን መምረጥ አንዱ ነው። ከዚህ በላይ የቤተ ክርስቲያንን የወደፊት ሕይወት የሚወስን ነገር የለም። አንዲት ቤተ ክርስቲያን ከመሪዎቿ መንፈሳዊ ሕይወት ወይም ራእይ በላይ ልታድግ አትችልም። ስለሆነም አንዲት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር የሚጠብቅባትን ሁሉ እንድትሆን ከተፈለገ መሪዎችን የመምረጥና የማሠልጠን ኃላፊነቷን በአግባቡ መወጣት ይኖርባታል። መሪዎችን በምንመርጥበት ጊዜ በትምህርት፣ በሥልጣን፣ ወይም በሀብት ላይ ከማተኮር ይልቅ፥ ለመንፈሳዊ ብቃቶች ከፍተኛውን ስፍራ መስጠት ይኖርብናል። ሰዎች መንፈሳዊ የአመራር ስጦታዎችና ባሕርያት እንዳሏቸው ለማረጋገጥ ውስጣቸውን ዘልቆ መመልከቱ ከባድ ነው። ስለሆነም ጸሎት እጅግ አስፈላጊ ነው። እውነተኞቹን መሪዎች ሊመርጥ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነውና። እግዚአብሔር ሳሙኤልን እንዳስተማረው፣ «ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል» ብሏል (1ኛ ሳሙ. 16፡7)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ቤተ ክርስቲያንህ መሪዎችን በመምረጡ ረገድ በጸሎት የተደገፈ ምርጫ የምታደርገው እንዴት ነው? ከዚህ የተሻለ ምን ልታደርግ ትችላለች? ለ) እግዚአብሔር በአመራር ብቃትና በመንፈሳዊ ባሕርይ አበልጽጓቸዋል ብለህ የምታስባቸውን አምስት ሰዎች ዘርዝር። የአምራር ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ ለማገዝ ምን ልታደርግላቸው ትችላለህ? ሐ) ለእነዚህ አምስት ሰዎች ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ጸልይላቸው። መ) እግዚአብሔር አሁን ያሉትን መሪዎች እንዲያበረታቸው በሳምንት ሁለት ጊዜ ጸልይላቸው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: