ኢየሱስ ኃይሉን ገለጠ (ሉቃስ 8፡22-56)

በዚህ የኢየሱስ የሕይወት ታሪክ ውስጥ፣ ሉቃስ አራት ተአምራትን መርጧል። ይህንንም ያደረገው ደቀ መዛሙርቱ በሕይወታቸው ውስጥ ለሚከሰት ማንኛውም ነገር በክርስቶስ ላይ ጽኑ እምነት ይኖራቸው ዘንድ የኢየሱስን ታላቅ ኃይል ለማሳየት ነው።

ሀ. ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ (ሉቃስ 8፡22-25)። ኢየሱስ ሥጋዊም ሆነ ግላዊ ሕይወታችንን የሚፈታተኑ ማዕበሎችን የመቆጣጠር ችሎታ አለው። ኢየሱስ የተኛ ወይም ግድ የሌለው ቢመስለንም እንኳ፣ በሁሉም ማዕበል ውስጥ አብሮን አለ። ከእርሱ ጋር በመሆናችን፣ ከየትኛውም ፍርሃት ነፃ ልንሆንና ለመልካም ውጤት በእርሱ ልንተማመን እንችላለን።

ለ. ኢየሱስ አጋንንትን አስወጣ (ሉቃስ 8፡26-38)። ኢየሱስ ከገሊላ ባሕር ማዶ ካገኘው ሰው ይልቅ ብዙ አጋንንት የሰፈሩበት እንዲህ ያለ ሰው ያለ አይመስልም። 6000 የአጋንንት ጭፍራ የሰፈረበት በመሆኑ፤ ሁኔታውን መርዳት የሚቻል አይመስልም። ነገር ግን እነዚህ አጋንንት ከኢየሱስ ጋር ሲተያዩ በፍርሃት ራዱ። ኢየሱስ ቃል በመናገር ብቻ እነዚህ አጋንንት ሰውዬውን ለቅቀው እንዲወጡ አዘዛቸው። ሰይጣን ኃይሉን ሁሉ አስተባብሮ ወደ ክርስቲያኖች ቢመጣ እንኳ፥ ከእኛ ጋር ያለው ከሰይጣን ኃይል እንደሚበልጥ እናውቃለን። በፍርሃት ተውጠን «በኢየሱስ ስም!» እያልን ልንፎክር አይገባንም። ኢየሱስ ሰይጣንን በአንዲት የትእዛዝ ቃል ብቻ ሊያሸንፈው እንደሚችል ማመኑ ይበቃል።

ሉቃስ ሰዎች ለኢየሱስ ሊሰጡ የሚችሉትን ሁለት ምላሾች ጠቅሷል። አብዛኞቹ ሕይወታቸውን ለእርሱ አሳልፈው ለመስጠት ስለማይፈልጉ ከእነርሱ እንዲርቅ ይፈልጋሉ። ነገር ግን በአጋንንት ተይዞ እንደነበረው ሰውዩ ያሉ ጥቂቶች ኢየሱስን ለመከተል ይሻሉ። ይህ ሰው ምን ማድረግ ነበረበት? ኢየሱስ ያደረገለትን ለሌሎች መመስከር ነበረበት። ምስክርነት እንደ ወንጌላውያን ያሉ አገልጋዮች ብቻ የሚፈጽሙት ተግባር አይደለም። ሁላችንም ኢየሱስ በሕይወታችን ውስጥ ያደረገውን ለሌሎች ልናካፍል እንችላለን።

ሐ. ለ12 ዓመት ደም ሲፈሳት የኖረችውን ሴት ፈወሰ (ሉቃስ 8፡43-48)። ሰዎች ከሚታገሏቸው ነገሮች አንዱ በሽታ ነው። እያንዳንዱ ክርስቲያን በወደቀው የኃጢአት ዓለም ውስጥ የሚኖር እንደ መሆኑ በአንድ ወይም በሌላ ወቅት መታመሙ አይቀርም። ነገር ግን በምንታመምበት ጊዜ ምን ዐይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? እምነታችንን ልንተው ይገባል? ልናጉረመርምስ? በፍጹም አይገባም! እንደዚያች ሴት ኢየሱስ በሕይወታችን ውስጥ ይሠራ ዘንድ ልናምን ይገባል። ሴቲቱ ኢየሱስን በመንካት እንደ ተፈወሰች ሁሉ፥ እኛም በእምነት ብንነካው ሊፈውሰን ይችላል።

ይሁንና ይህ ማለት በታመምን ጊዜ ሁሉ እንፈወሳለን ማለት ነው? ሉቃስ ለማስተላለፍ የፈለገው ትምህርት ይሄ ነውን? ሉቃስ በዋነኛነት ለማሳየት የፈለገው ኢየሱስ በበሽታዎች ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለው ነው። ይህንን ታሪክ የተጠቀመው ኢየሱስ ያለብንን በሽታ ሁሉ እንደሚፈውስ ለማብራራት አይደለም። ወደ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በምንሄድበት ጊዜ መንፈሳውያን ሰዎች ታምመው እንደ ነበር እንመለከታለን (ፊልጵ. 225-27፣ 2ኛ ጢሞ. 420 አንብብ።) ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ሕይወት ከበሽታዎች ሁሉ እንደምንፈወስ ዋስትና አይሰጠንም። ሕይወታችን በምድር ላይ የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ነው። ሌላ ሕይወት እየመጣልን ነው። በዚያ በሽታም ሆነ ሞት አይኖርም ራእይ 214፤ 22፡18 አንብብ።) ኢየሱስን የሚያምኑ ሰዎች ሙሉ በሙሉ የሚፈወሱት በዚያ ነው።

መ. የኢያኢሮስ ልጅ ከሞት መነሳት (ሉቃስ 8፡40-42፥ 49-56)። ሞት እጅግ የሚፈራ የሰው ልጆች ጠላት ነው። ነገር ግን በሞት ላይ ሥልጣን ያለው አዳኝ አለን። ኢየሱስ የኢያኢሮስን ልጅ ከሞት በማስነሣቱ፣ በሞት ላይ ሥልጣን እንዳለው አመልክቷል። ኢየሱስ በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ ከሞት ያነሣቸዋል። ደኅንነትን ባገኘን ጊዜ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ይህንን አድርጓል። በመጨረሻው ዘመን ደግሞ በትንሣኤ ሙታን አማኞችን ከሞት በማስነሣቱ ይህንኑ ተግባራዊ ያደርጋል።

የውይይት ጥያቄ፡- የኢየሱስ ተከታዮች ኢየሱስ በማዕበል፣ በአጋንንት፣ በበሽታና በሞት ላይ ሥልጣን እንዳለው ማወቃቸው ለምን ያስፈልጋል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: