ኢየሱስ የአይሁዶችንና የሃይማኖት መሪዎችን እምነት ቢስነትን ፊት ለፊት ተቋቋመ (ሉቃስ 11፡14-54)

ሀ. ኢየሱስ ኃይሉን ከሰይጣን እንዳገኘ ለቀረበበት ክስ መልስ ሰጠ (ሉቃስ 11፡14-26)። ኢየሱስ አጋንንትን በቀላሉ ከሰዎች የማስወጣት ኃይሉን ከየት እንዳገኘ አይሁዶች እንዲያስቡ አደረጋቸው። መሢሕ መሆኑን ለማመን ያልፈለጉ ሰዎች ኃይሉን ያገኘው ከብዔል ዜቡል (ሰይጣን) እንደሆነ ተናገሩ። ኢየሱስ ግን ሰዎች እርሱንና በሰይጣን ላይ ያለውን ኃይል እንዴት መመልከት እንዳለባቸው የሚያስገንዝቡ ጠቃሚ እውነቶችን አስተማረ።

  1. የውስጥ ቅራኔ ያለበት መንግሥት ሊጸና ስለማይችል፣ ኢየሱስ አጋንንትን ያስወጣው ከአጋንንት ጋር በመተባበር አልነበረም። ኢየሱስ ከሰማይ መንግሥት የመጣ ንጉሥ ነው። ይህ ንጉሥ ኢየሱስም በመካከላቸው ተገኝቶ ነበር።
  2. ሰይጣን ከኢየሱስ ኃይል ጋር ለመታገል ብርቱና ኃይለኛ ቢመስልም፥ የኢየሱስ መለኮታዊ ኃይል ግን ከእርሱ ይበልጣል። እርሱም ሰዎችን ከሰይጣን መንግሥት አውጥቶ ወደ ራሱ መንግሥት ይወስዳል።
  3. ሁለት መንግሥታት ብቻ አሉ፣ አንዱ የሰይጣን ሌላው የኢየሱስ መንግሥት። ስለሆነም ለሰው ያለው ዕድል ወይ የሰይጣን ወይም የኢየሱስ መንግሥት አባል መሆን ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው የየትኛው መንግሥት አባል ሊሆን እንደሚፈልግ መምረጥ አለበት። ከዚህ ገለልተኛ እንሆናለን የሚሉ ሰዎች ካሉ የሰይጣን መንግሥት አባል ናቸው።
  4. አጋንንት የወጣለት ሰው ራሱን ለኢየሱስ ካላስገዛ፣ ከድሮው የከፋ ሁኔታ ይገጥመዋል።

ለ. እግዚአብሔርን መስማትና መታዘዝ በረከትን ያመጣል (ሉቃስ 11፡27-28)። አንድ ሰው ዝነኛ በሚሆንበት ጊዜ፥ ቤተሰቡም ዝነኛ ይሆናል። ስለሆነም አንዲት ሴት የኢየሱስ እናት ብፅዕት እንደሆነች ተናገረች። ኢየሱስ ግን በረከት የቤተሰብ ውርስ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት የማድረግ ጉዳይ እንደሆነ ገልጾአል። በእግዚአብሔር የሚባረኩት ቃሉን የሚሰሙና በሕይወታቸው ተግባራዊ የሚያደርጉት ብቻ ናቸው።

ሐ. ኢየሱስንና ተአምራቱን መመልከት ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ያስከትላል (ሉቃስ 11፡29-32)። አይሁዶች ተአምራት በመሥራቱ ምክንያት ኢየሱስን ይወዱት ነበር፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ ሌላ የተሻለ ተአምር እንዲሠራ ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስም ይህ ፍላጎታቸው በእርሱ ያለማመን ምልክት እንደሆነ አስተዋለ። የኢየሱስ ተከታዮች ወደ እርሱ የሚመጡት ተአምራትን ፍለጋ መሆን የለበትም። የእምነታችን መሠረቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ መሆን አለበት። ሰዎች ሁሉ በኢየሱስ እንዲያምኑ ለማድረግ «የዮናስ ምልክት» በቂ ነው። ተአምራቱ እስካለ ድረስ በኢየሱስ ለማመን የሚፈቅዱ ብዙ ሰዎች አሉ። ነገር ግን ተአምራቱ ሊቋረጥ እምነታቸውም ያበቃል። ይህም እነዚህ ሰዎች እንደ አይሁዶች የማያምን ልብ እንዳላቸውና ምልክትን ብቻ ፈላጊዎች እንደሆኑ ያመለክታል። ኢየሱስንና ተአምራቱን ማስተዋል በረከቶችን ሳይሆን ኃላፊነቶችን ይጨምራል። ስለሆነም የአይሁዶቹ ፍርድ በነነዌ ዘመን ከነበሩት ሰዎች የከፋ ይሆናል። የደቡብ ንግሥት የተባለችው ንግሥት ሳባና የነነዌ ከተማ፥ ሰሎሞንንና ዮናስን ባገኙ ጊዜ አሳባቸውን ለውጠው ንስሐ ገብተዋል። አይሁዶች ግን ኢየሱስን የመሰለ የእግዚአብሔር ልጅ በመካከላቸው እያለ፥ ንስሐ ገብተው ለማመን ፈቃደኞች አልነበሩም።

መ. ለመንፈሳዊ ብርሃን የሰዎች መልስ (ሉቃስ 11፡33-36)። በዚህ ምንባብ ውስጥ፣ ኢየሱስ ብርሃን መሆኑን እንዳስተማረ የሚገልጽ ነገር ያለ ይመስላል። ተአምራቱን በግልጽ በማሳየት የእግዚአብሔርን እውነት አስተምሯቸዋል። እንግዲህ ሰዎቹ ይህንን ብርሃን ምን እንደሚያደርጉት መወሰን የእነርሱ ኃላፊነት ነው። የእምነት ዐይኖቻቸው የወንጌሉን ብርሃን ለማየት ካልቻሉ፣ ልባቸው ይጨልማል። የእምነት ዐይኖቻቸው የወንጌሉን ብርሃን ካዩ፣ እውነቱ ወደ ሕይወታቸው ዘልቆ ነገሮችን ሁሉ ይለውጣል። ክፋትንም ከልባቸው ያስወግዳል።

ሠ. ኢየሱስ ግብዝ የሃይማኖት መሪዎችን በመቃወም ያቀረበው ትምህርት (ሉቃስ 11፡37-54)። በክርስቲያን መሪዎች ላይ ከሚከሰቱ አደጋዎች አንዱ በአነስተኛ ነገርች ላይ በማተኮር እጅግ የሚያስፈልገውን ነገር ችላ ማለት ነው። ሴቶች ሊፕስቲክ መቀባታቸውን ወይም ሱሪ መልስሳቸውን እየተቆጣጠርን ቅንዓትን ወይም ሐሜትን እንዘነጋለን። በዚህ ክፍል ኢየሱስ እንደዚህ ስላለው የግብዝነት ሕይወት ጠንከር ያለ ተግሣጽ ሰጥቷል። ኢየሱስ በሃይማኖት መሪዎች ላይ ያቀረባቸውን ዎች ቀጥለን እንመለከታለን።

  1. የሃይማኖት መሪዎች (የመንጻት ሥርዓትን በመሳሰሉት) ውጫዊ ነገሮች ላይ በማተኮር፥ የሰውዬውን ውስጣዊ ማንነት ይዘነጉ ነበር። ከመታጠብ ወይም ከየትኛውም ባህል በላይ የልብ ንጽሕና ወሳኝ ነው። መሪዎቹ ለድሆች በልባቸው ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን ፍቅር ቢገልጹ፣ ልባቸው ብቻ ሳይሆን ተግባራቸውም ትክክል ይሆናል።
  2. መሪዎቹ እግዚአብሔር (ከጓሮ ቅመማ ቅመሞች አሥራት ማውጣትን ጨምሮ) ሕግን ከመጠበቁ ዝርዝር ጉዳይ አንሥቶ ከሰዎችና ከእግዚአብሔር ለሚደረጉ ግንኙነቶች ትኩረት እንደሚሰጥ መገንዘብ ነበረባቸው። ነገር ግን መሪዎቹ በትናንሽ ነገሮች ላይ እያተኮሩ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ቢዘነጉ ተሳስተዋል ማለት ነው። ይልቁንም ፍቅርና ፍትሕ ማሳየትን ለመሳሰሉት የሕጉ ቁም ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋቸዋል።
  3. ፈሪሳውያን በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ ልብ ከመያዝ ይልቅ ከሰዎች ክብር ለማግኘት ይፈልጉ ነበር። ስለሆነም ሰዎች ሊያዩዋቸው በሚችሏቸው ስፍራዎች ላይ ለመቀመጥና ለመመላለስ ይፈልጉ ነበር።
  4. የሃይማኖት መሪዎቹ ሰዎች የሚከተሏቸውን ሕጎች መደንገግ ይወዱ ነበር። አንድ ሰው እነዚያን ሁሉ ሕግጋት ሳይፈጽም በሚቀርበት ጊዜ እንደ ዳኞች ይቀጧቸው ነበር። ሰዎቹ ሕግጋቱን እንዲገነዘቡና እንዲታዘዙ የመርዳት ፈቃደኝነት አልነበራቸውም። ብዙውን ጊዜ በመሪዎቹና በሕዝቡ መካከል ብዙ ርቀት ይታያል። መሪዎች (ሰባኪዎች) ስለ ሕዝቡ ኃጢአት የከፋ ነቀፋ ይሰነዝራሉ። ይሁን እንጂ እምብዛም ወደ ሰዎቹ ሕይወት ጠልቀው በመግባት የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲጠብቁ አይረዷቸውም።
  5. የሃይማኖት መሪዎች ነቢያትን በማክበርና በመቃብራቸው ላይ ታላላቅ ኀውልቶች በማሠራት ከእነርሱ ጋር እኩል እንደሆኑ አድርገው ያስቡ ነበር። ዋናው ቁም ነገር ግን እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች የሚናገሩት ሳይሆን የሚያከናውኑት ተግባር ነበር። ታላቁ ነቢይ ኢየሱስ በመካከላቸው እያለ ሊሰሙት አልፈለጉም። በኋላ ኢየሱስን የገደሉት እነዚሁ መሪዎች ነበር። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች በኢየሱስና በደቀ መዛሙርቱ ላይ በፈጸሙት በደል፥ ልባቸው ነቢያትን ከገደሉት አባቶቻቸው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ አሳይተዋል። ስለሆነም እነዚህ ሰዎች በብሉይ ኪዳን ዘመን በመጀመሪያ ከተገደለው ከአቤል ጀምሮ በመጨረሻው ላይ ከተገደለው እስከ ዘካርያስ ድረስ ለፈሰሰው የእግዚአብሔር ሕዝቦች ደም ተጠያቂዎች ይሆናሉ። በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌም የፈራረሰችበት ወረራ ኢየሱስ በአይሁዶች ላይ ይደርሳል ያለው ፍርድ ከፊል ፍጻሜ ነበር።
  6. ብሉይ ኪዳንን የሚያውቁ የሃይማኖት መሪዎች እንደ መሆናቸው፣ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ምን እንደሚፈልግና እንዴት ከእርሱ ጋር መገናኘት እንደሚችሉ በሚገባ ያውቁ ነበር። ነገር ግን ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለማስገዛትና እርሱ በፈለገው መንገድ ለመመላለስ ስላልፈለጉ፤ እነዚህ መሪዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገቡ አልቻሉም። ይህም ብቻ አይደለም። የሃይማኖት መሪዎቹ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት የእነርሱን ምሪት የጠየቁትንም ሰዎች አሰናክለዋል። የቤተ ክርስቲያን መሪ ብዙ ኃላፊነቶች አሉት። ሰዎች እግዚአብሔር ከእነርሱ ምን እንደሚፈልግ ለማወቅ የመሪውን ቃልና ሕይወት ይከታተላሉ። ምእመናን መጽሐፍ ቅዱስን አንብበው የራሳቸውን ውሳኔ ከማድረግ ይልቅ የመሪዎቻቸውን ሕይወት መመልከት ይቀልላቸዋል። እርምጃችንን ከእግዚአብሔር ጋር ሳናስተካከል ስንቀር ቃላችን ከሕይወታችን ጋር ሳይስማማ ይቀራል፤ በዚህም ሰዎች ወደ ኢየሱስ እንዳይመጡ ጋሬጣ እንሆንባቸዋለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በዚህ ዘመን የሚኖሩ መሪዎች ኢየሱስ ፈሪሳውያንን የወቀሳቸውን ተግባራት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ለማሳየት፥ ከላይ ለተመለከትናቸው ስድስት ነጥቦች ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ምሳሌዎችን ስጥ። ለ) ይህንን መንፈሳዊ መሪዎች እግዚአብሔርን በሚያስደስት መንገድ ሊኖሩ ይገባል ከምትልበት መንገድ ጋር አነጻጽር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: