ሉቃስ 13፡1-35

  1. ኢየሱስ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ፥ ካልሆነ ግን እንደሚጠፉ አስጠንቅቋል (ሉቃስ 13፡1-9)

ብዙውን ጊዜ በዓለም አንድ መጥፎ ነገር ከገጠመህ ይህ የሆነው አንተ ክፉ ሰው ስለሆንክ እንደሆነ፣ ጥሩ ነገር ካጋጠመህ ደግሞ ጥሩ ሰው እንደሆንህ ይነግሩሃል። አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ደግሞ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ክፉዎችን እንደሚቀጣ በመግለጽ ክፉ ነገር በተፈጸመ ቁጥር ይህ የኃጢአት ውጤት እንደሆነ ይናገራሉ። እግዚአብሔር የተቀደሰ ሕይወት እንደሆኑ የሚኖሩትን ሁልጊዜ ይባርካቸዋል ብለው ያስባሉ። ይህ ትክክለኛ ግንዛቤ ነውን? አይደለም! ብዙ ክርስቲያኖች የሚያስቡት እንደዚህ ነው። አንድ ክርስቲያን ክፉ ነገር ከገጠመው ፈጥኖ ወደ አእምሮአቸው የሚመጣው አሳብ፣ «ምን ኃጢአት ሠርቶ ይሆን?» የሚል ነው። አንድ ሰው ሀብት ሲያፈራና ኑሮ ሲመቸው ደግሞ፥ እግዚአብሔር እየባረከው ነው ብለው ያስባሉ። ምንም እንኳ እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ኃጢአተኞችን በፍጥነት እንደሚቀጣና ለእርሱ የሚኖሩትን ደግሞ እንደሚባርክ ቢታወቅም፣ ይህ ሁልጊዜ የሚሆን አይደለም። መጥፎ ነገሮች በጥሩ ሰዎች ላይ ይደርሳሉ፤ የዚህ ተቃራኒውም ይከሰታል።

ደቀ መዛሙርቱ ጲላጦስ በሆነ ምክንያት የገደላቸው የገሊላ ሰዎች ወይም የሰሊሆም ግንብ ተንዶ የገደላቸው ከሌሎች ሁሉ የከፉ ኃጢአተኞች እንደሆኑ ያስቡ ነበር። ኢየሱስ ግን ነገሩ እንደዚህ አለመሆኑን ገለጸላቸው። ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች ናቸው። ስለሆነም የሚደርስባቸው መልካምም ሆነ ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት በቀጥተኛ መልኩ አያሳይም። ንስሐ አንገባም የሚሉ ሰዎች ሁሉ የሚቀጡበት የፍርድ ቀን ስለ ደረሰ፣ ሁሉም ንስሐ መግባት ይኖርባቸዋል።

በበለሲቱ ምሳሌ፥ ኢየሱስ እንደ እስራኤል ሕዝብም ሆነ እንደ ግለሰብ ተከታዮቹ ለእግዚአብሔር የሚጠቅሙ መሆናቸውን ለማመልከት መንፈሳዊ ፍሬዎችን ማፍራት አለባቸው። ይህ ካልሆነ የፍርድ ቀን ይመጣል። ለበለሲቱ እንደተደረገው፣ እግዚአብሔር ጊዜ በመስጠት ሕዝቡን በትዕግሥት ይጠብቃል። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ነበር የሮም ሠራዊት ከተማይቱንና ቤተ መቅደሱን በመደምሰስ የእግዚአብሔርን ፍርድ በአይሁዶች ላይ የፈጸመው። በግለሰብ ደረጃም፣ ስዎች መልካም ፍሬ ካላሳዩ በሞት ተለይተው ወደ እሳት ፍርድ ይጣላሉ።

  1. ኢየሱስ በሰንበት ቀን አንዲት ጎባጣ ሴት ፈወሰ (ሉቃስ 18፡10-17)

እግዚአብሔር እንዴት መሥራት እንዳለበት የምናስባቸው ነገሮች ሙሉ በሙሉ ዐይናችንን የሚያሳውርበት ጊዜ አለ። የምኩራብ አለቃው ለአሥራ ስምንት ዓመታት ስትሠቃይ የነበረች ሴት ስትፈወስ ተመልክቷል። ነገር ግን እግዚአብሔርን ስለ ቸርነቱ ከማመስገን ይልቅ፣ ኢየሱስ በሰንበት ቀን ስለ ፈወሳት እጅግ ተቆጣ። የሃይማኖት መሪዎች እግዚአብሔር የምሕረት አምላክ እንደሆነና ሰዎችን ለማስጨነቅ እንደማይፈልግ አልተንዘቡም። የእግዚአብሔርን ዐይነት ርኅራኄ ባሕሪ የሌላቸው ሰዎች እንኳ በሰንበት ቀንም ጉድጓድ ውስጥ ቢገቡ ይረዳሉ።

የውይይት ጥያቄ:- በእግዚአብሔር ሥራ እንደ መደሰት እኛ ባልጠበቅናቸው መንገዶች ሲሠራ አይተን የምንከፋባቸውን መንገዶች ግለጽ።

የሚገርመው እግዚአብሔርን እናውቃለን ይሉ የነበሩ የሃይማኖት መሪዎች፥ ሥራውን ለማየት አይችሉም ነበር። እግዚአብሔር እነርሱ ከሚጠብቁት መንገድ በተለየ በሚሠራበት ጊዜ ለተቃውሞ ይነሣሉ። ነገር ግን ተራ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔርን እጅ አይተው ደስ ይሰኛሉ።

  1. ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተማረ (ሉቃስ 13፡18-30)

ሀ. የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እርሾና የሰናፍጭ ቅንጣት ከትንሽ ጀምሮ የሚያስደንቅ ዕድገት የሚያሳይ መሆኑ ግልጽ ነው። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከዓለም ጋር ሲነጻጸሩ ብዙም ትኩረት የሚሰጣቸው ላይመስሉ ይችላሉ። ነገር ግን ዛሬም እንኳ ጠቅላላውን ዓለም የሚለውጥ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

ለ. የእግዚአብሔር መንግሥት አካል መሆን ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። አይሁዶች ብዙ ጊዜ ስንት ሰው ወደ መንግሥተ ሰማይ ሊገባ እንደሚችል ይከራከሩ ስለ ነበር፥ ኢየሱስን ጠየቁት። ነገር ግን ኢየሱስ በነገረ መለኮታዊ ጥያቄዎች ላይ መከራከሩን ብዙም አይፈልገውም ነበርና፥ በአንጻሩም አሁን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ገለጸላቸው። (ማስታወሻ፡- ኢየሱስ የቤቱ ባለቤት ነው።) የዚህ መንግሥት በር የሚዘጋበት ጊዜ ይመጣል። ስለሆነም ስለ ኢየሱስ የሚያውቁት ነገር ቢኖርም፥ ከእርሱ ጋር ግላዊ ግንኙነት ስለሌላቸው ወደ ቤቱ እንዲገቡ አይፈቅድላቸውም።

ኢየሱስ፥ አይሁዶችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የመግባት ዕድላቸው እያበቃ መሆኑን በመግለጽ አስጠንቅቋቸዋል። እነዚህ ሰዎች ከአይሁድ ወገን መሆናቸው ብቻ በቂ እንደሆነ አስበው ሊሆን ይችላል። ይህ ግን ትክክል አልነበረም። እንደ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብን የመሳሰሉ አይሁዳውያን አባቶቻቸው፥ በእግዚአብሔር የዘላለም መንግሥት ደስ ላሰኙ፤ እነርሱ ግን ወደ ውጭ ይጣላሉ። አይሁዶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባሉ ብለው ያላሰቧቸው አሕዛብም እግዚአብሔር በሚገኝበት ስፍራ አብረው ደስ ይሰኛሉ። አይሁዶች መጀመሪያ ወንጌሉን እንዲሰሙ ቢደረግም፣ ለመቀበል ስላልፈለጉ ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጭ ይጣላሉ። በመጨረሻ ወንጌልን የሰሙት አሕዛብ የመጀመሪያዎቹ ሆነው የእግዚአብሔርን በረከት ይቀበላሉ።

  1. ኢየሱስ ኢየሩሳሌም እርሱን እንደ አዳኝና ጌታ ባለመቀበሏ አዘነ (ሉቃስ 18፡31-35)

ምናልባት ኢየሱስ የነበረው የአንቲጳስ ሄሮድስ ግዛት በነበረችው በጲሪያ ሳይሆን አይቀርም። ሄሮድስ ኢየሱስን ለማየትና ለማጥፋት ይፈልግ ነበር። ምናልባትም ፈሪሳውያን ስለ ሄሮድስ በማስጠንቀቅ ኢየሱስን ለማስፈራራት ፈልገው ይሆናል። ኢየሱስ ግን ምንም ሳይፈራ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ተናገረ።

ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም ሲያስብ አዘነ። ኢየሩሳሌም እግዚአብሔር በቤተ መቅደሱ ውስጥ ክብሩን ያሳረፈባት የዳዊት ከተማ ነበረች። ይሁንና በታሪክ ሁሉ ይህች ከተማ ለእግዚአብሔር አልታዘዝም ብላ መልእክተኞችን ስትገድል ኖራለች። ኢየሱስ ከተማይቱን ቢወዳትም፣ አይሁዶች እርሱ መሢሕ መሆኑን ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም። ስለሆነም ኢየሱስ ከተማይቱ ሙሉ በሙሉ እንደምትደመሰስ ትንቢት ተናገረ። አይሁዶች ከ500 ዓመታት በላይ የጠበቁት መሢሕ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ሰማይ የሚሄድ ሲሆን፣ ዳግመኛ እስኪመጣ ድረስ አያዩትም። በዚህም የበረከት መንገዳቸውን ዘግተው ነበር፡

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: