ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ለማብራራት የተናገራቸው ምሳሌዎች (ሉቃስ 15፡1-32)

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ እግዚአብሔር ስታስብ በመጀመሪያ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምስል ምንድን ነው?

የሥነ ልቦና ምሑራን ስለ እግዚአብሔር ያለን አስተሳሰብ ስለ አባታችን ባለን ግንዛቤ እንደሚወሰን ይናገራሉ። አባታችን ኃይላኛ ከሆነ፣ እግዚአብሔርም ሩቅ ስፍራ እንደሚኖር ኃይለኛ አካል አድርገን እናስባለን። ነገር ግን አባታችን የፍቅር እንክብካቤ አድርጎልን ከሆነ፣ እግዚአብሔርን እንደ አፍቃሪ አባት እንረዳዋለን። እግዚአብሔርን የምናውቅባቸው ሁለት ምንጮች አሉ።

አንደኛው፥ ሰብአዊ ምንጭ ነው። ይህ የተለያዩ መልኮች ሊኖሩት ይችላል። አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔርን ከእንስሳት ጋር ስለሚያመሳስሉ፣ ሕንድን በመሳሰሉ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች እባብን ያመልካሉ። ሌሎች ደግሞ እግዚአብሔር ሰውን መሳይና ከሰው የሚበልጥ አካል እንደሆነ ያስባሉ። ሰዎች ደግሞ ወንድና ሴት ስለሆኑ፣ እግዚአብሔርም እንዲሁ ዐይነት ነው ብለው ያስባሉ። ሰዎች ወሲባዊ ፍቅርን ስለሚወዱ፤ እግዚአብሔርም ሚስቶች እንዳሉትና ከሌሎች አማልክት ጋር ወሲባዊ ግንኙነቶችን እንደሚያደርግ ይናገራሉ። ምንም እንኳ እነዚህ ነገሮች ለእኛ ምንም ችግር ባይፈጥሩብንም፣ ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች ስለ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ዕውቀት ሳይኖረን ሲቀር በራሳችን አምሳል የቀረጽነውን አምላክ ማምለክ እንጀምራለን። ለምሳሌ፥ እግዚአብሔር እንዴት ሦስት አካላት በአንድነት የሚገኙበት አምላክ ሊሆን እንደቻለ ባለመገንዘባችን ምክንያት፥ እንደ «ኢየሱስ ብቻ» (Only Jesus) አማኞች የሥላሴን አስተምህር ከካድን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ሳይሆን ራሳችን የፈለግነውን አምላክ ተክተናል ማለት ነው። ወይም ደግሞ እግዚአብሔርን በእንባችን ወይም በጸሎታችን በማታለል የምንፈልገውን እንዲያደርግልን ልናስገድደው እንችላለን ብለን ካሰብን፥ የምናመልከው እውነተኛውን አምላክ አይደለም ማለት ነው። ስለ እግዚአብሔር የሚኖረን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያልተገናዘበ አመለካከት አምልኮተ ጣዖት እንደሚባል ከመጽሐፍ ቅዱስ እንረዳለን።

ሁለተኛው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ስለ ራሱ የሚናገረውን አሳብ እናገኛለን። ከዚያም አሳባችንን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እናስተካክላለን።

እግዚአብሔር እኛ በግላችን የምንቀርፀው ዐይነት አምላክ ነው ብለን ካሰብን፥ ጣዖት ማዘጋጀታችን ነው። ስለ እግዚአብሔር ያለን ንዛቤ ከእርሱ ትክክለኛ ማንነት የተለየ በሚሆንበት ጊዜ፥ የአእምሮ ጣዖት አድርገናል ማለት ነው። እግዚአብሔር በትክክል ምን እንደሚመስል ለማወቅ ጊዜ የማይወሰዱ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው እውነት ከፊሉን ብቻ የሚያውቁ አንዳንድ ክርስቲያኖች፥ የሚያመልኩት እውነተኛውን አምላክ ላይሆን ጣዖትን ነው። ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ማጥናት የሚያስፈልገው። በአእምሯችን የፈጠርነውን ምናባዊ አምላክ ሳይሆን ራሱን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የገለጻውን እግዚአብሔርን በትክክል አውቀን የምናመልከው በዚህ ጊዜ ብቻ ነውና።

ኢየሱስ አይሁዶች ስለ እግዚአብሔር የነበራቸውን ግንዛቤ ለማረም ፈልጎ ነበር። እርሱ ስለ እግዚአብሔር የሰጠን ምስል ብዙውን ጊዜ እኛ ስለ እግዚአብሔር ከምናስበው የተለየ ነው።

ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ለማብራራት የተናገራቸው ምሳሌዎች (ሉቃስ 15፡1-32)

ኢየሱስ ከኖረው ሕይወት ርቀን ስለምንገኝ፣ በአብዛኛው ከኢየሱስ ይልቅ ፈሪሳውያንን እንመስላለን። ኢየሱስ ጊዜውን ከማን ጋር ነበር የሚያሳልፈው? ከሃይማኖት ሰዎችና መልካም ስም ካላቸው ጋር ነው ብለን ልናስብ እንችላለን። ነገር ግን ኢየሱስ ብዙ ጊዜውን ያሳለፈው የሃይማኖት ሰዎች ክፉዎች አድርገው ከሚቆጥሯቸው ቀራጮችና ኃጢአተኞች ጋር ነበር። በቡና ቤት ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር እየተነጋገርን ወይም ጫት ከሚቅሙ ጋር እየተጫወትን ብናሳልፍ ሰዎች መጥፎ ስም እንደሚሰጡን ሁሉ፤ ኢየሱስም ብዙውን ጊዜ ከእንደዚህ ዐይነት ሰዎች ጋር በማሳለፉ መጥፎ ስም አትርፎአል። ፈሪሳውያን እንደ ኢየሱስ ያለ ቅዱስ ሰው ለምን እግዚአብሔር በሚፈልጋቸው መንገድ ከማይኖሩ ሰዎች ጋር እንደሚተባበር ሊገባቸው አልቻለም። ኢየሱስ ከኃጢአተኞች ጋር ባለው ግንኙነት የእግዚአብሔርን ልብ ለማሳየት እነዚህን ምሳሌዎች ተጠቅሟል።

ሀ. የጠፋው በግ ምሳሌ (ሉቃስ 15፡1-7)። አንድ በግ ጠፍቶበት የሚችለውን ያህል አሰሳ ሳያደርግ ዝም ብሎ ወደ ቤቱ የሚሄድ እረኛ አይኖርም። በጉን ባገኘው ጊዜም ደስ ይለዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ እግዚአብሔር የሕዝቡ እረኛ ነው። ማኅበረሰቡ ያገለላቸውንና ኃጢአተኞችን ጨምሮ ሰዎች ሁሉ የእርሱ በጎች ናቸው። እግዚአብሔር ሁልጊዜም ወደ መንጋው አምጥቶ ሊንከባከባቸው ይፈልጋል። አንድ የጠፋ ኃጢአተኛ ተገኝቶ ወደ መንጋው በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ የእግዚአብሔር ልብ በደስታ ይሞላል። በመንሥተ ሰማይ ቅልጥ ያለ ድግስ ይደረጋል! (ማስታወሻ፡ ኢየሱስ 99ኙን ከጻድቃን ጋር ሊያመሳስል ምፀትን እየተጠቀመ ይሆናል። ፈሪሳውያንና አብዛኞቹ አይሁዶች ጻድቃን ነን ብለው ቢያስቡም፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ደኅንነት እንዳላገኙ እየተናገረ ነበር። እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አልተሰኘም። ደስ የሚሰኘው አንድ ኃጢአተኛ በእምነት ወደ እርሱ በተመለሰ ጊዜ ነው። ሁላችንም ደግሞ ኃጢአተኞች ነን።)

ለ. የጠፋው መሐለቅ ምሳሌ (ሉቃስ 15፡8-10)። ኢየሱስ አሥር መሐለቅ ብቻ ስለነበራት ድሀ ሴት ታሪክ በመናገር፥ አንዱን ምሳሌ በሌላ መንገድ ገልጾታል (አንድ መሐለቅ የአንድ ቀን ደመወዝ ያህል ነበር።) ይህች ሴት መሐለቋን ካጣች ሕይወቷ ለችግር እንደሚዳረግ ትገነዘባለች። ስለሆነም የጠፋውን መሐለቅ ባገኘች ጊዜ ደስታዋ ትልቅ ሆነ፡፡ ለእግዚአብሔር ትልቁ ሀብቱ ሕዝቡ ነው። ስለሆነም ዓለም ምንም ያህል ቢንቀውም አንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ጠፍቶ ከነበረበት ሁኔታ ተመልሶ ሲገኝ እግዚአብሔርና የሰማይ አካላት ሁሉ ደስ ይሰኛሉ። እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ጠልቶ በመጨረሻው ወደ ሲኦል ሊጥላቸው አያስብም። ስለዚህ ዐይኖቹ እንባ አቅርረው የጠፉትን በጎችና መሐለቆች መፈለጉን ይቀጥላል። በጎቹና መሐለቆቹ አንድ በአንድ በሚገኙበት ጊዜ ደግሞ እንባዎቹ ወደ ደስታ ይለወጣሉ፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ የእግዚአብሔር ምስል ብዙውን ጊዜ እኛ ከምናስበው የሚለየው እንዴት ነው? ለ) እግዚአብሔር እጅግ ኃጢአተኞች ለሆኑት ሰዎች ፍቅሩን ከገለጸላቸው፣ ሰዎች ለሚንቋቸው ኃጢአተኞች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ሐ) አንተ የምታውቀው ከሁሉም በላይ ኃጢአተኛ የሆነ ሰው ማን ነው? የእግዚአብሔር ልብ ደስ እንዲለው ይህንን ሰው ወደ እምነት ለማምጣት ምን ታደርጋለህ?

ሐ. የጠፋው ልጅ ምሳሌ (ሉቃስ 15፡11-32)። ኢየሱስ ከተናገራቸው ታላላቅ ምሳሌዎች አንዱ ስለ አንድ አባትና ሁለት ልጆቹ የሚተርክ ነው። የዚህ ምሳሌ እያንዳንዱ ክፍል ስለ እግዚአብሔርና እግዚአብሔር ከሰዎችሔር ጋር ስላለው የተለያዩ ግንኙነቶች ያብራራል።

  1. የልጆቹ አባት እግዚአብሔርን እንደሚወክል ግልጽ ነው። እግዚአብሔር ሰዎችን በቤቱ ውስጥ ለማቆየት ኃይል አይጠቀምም። ልጁን አይገርፈውም፡፡ ፍቅር እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው በነፃ ሲሰጥ ብቻ ነው። ኃይልን አይጠቀምም። ስለሆነም፣ አባቱ በትንሽ ልጁ ላይ ምን ሊደርስ እንደሚችል ቢያውቅም እሄዳለሁ ባለ ጊዜ አሰናበተው። እግዚአብሔርም እንዲሁ ታናሽ ልጁ እንዲመለስለት ይናፍቃል። ልጁ በሚመለስበት ጊዜ የፍርድ ቃላት አይጠብቁትም። አባቱ፤ «ብዬህ አልነበር» አይለውም። ይልቁንም ዐመፀኛ፣ ኃጢአተኛና ተቅበዝባዥ ልጁ ስለተመለሰለት ደስ ይለዋል። ለአባቱ አስፈላጊው ነገር የቁጣ ቃላትን መናገር ሳይሆን፣ የይቅርታና የእንኳና ደህና መጣህ ሰላምታ ማቅረብ ነበር።
  2. የአባቱን ቤት ጥሎ የሄደው ታናሹ ልጅ እያንዳንዱን ኃጢአተኛ ይወክላል። የኃጢአተኛ ሰው ልብ በራስ ወዳድነት መንፈስ የተተበተበ ነው። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ስንገኝ በረከቶቻችንንና ደስታዎቻችንን አሁኑኑ ለማግኘት እንፈልጋለን። ረጅም ጊዜ ለመጠበቅ አንፈልግም። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ የፈለግናቸው ነገሮች ሁሉ ይበላሻሉ። የዓለም ደስታ ወደ አሳማ ምግብነት ይለወጣል። ልጁ ለመመለስ ከፈለገ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስፍራ እንዳለው ማወቁ አስፈላጊ ነው። በሚመለስበት ጊዜ በባርነት ማገልገል የሚያስፈልገው ቢሆን እንኳ፥ በአባቱ ቤት መሆኑ ብቻ እንደሚበቃው እያሰበ በትሕትና ይመጣል። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ እንደ ልጅ እንዲመለስ ይደረጋል። የተሰጠው ልብስ የፍቅር ምልክት ነበር። ቀለበቱ ደግሞ የልጅነት ሥልጣኑን ያመለክታል። ጫማዎቹ ደግሞ ባሪያ እንዳልሆነ ያሳያሉ። ባሪያ ጫማ አያደርግም ነበርና። እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ምንም ያህል በከፋ ኃጢአት ውስጥ ቢወድቅም እንኳ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ አይቀርም። ስለዚህ እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ልጅ በትሕትና ወደ እርሱ ሊመለስ ይገባል። በዐመፀኛነትና በራስ ወዳድነት መንፈስ ወደ ቤቱ መመለስ አይችሉም። ንስሐ ገብተው ወደ እግዚአብሔር በሚመጡበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የወራሽነትን ስፍራ ይሰጣቸዋል። የሰማይ ሀብት ሁሉ የእነርሱ ይሆናል (ሮሜ 8፡17 አንብብ።)
  3. ከቤት ቀርቶ ለአባቱ ሲሠራ የነበረው ታላቁ ልጅ እንደ ፈሪሳውያን ዐይነቶቹን በራሳቸው የረኩ ሃይማኖተኞች ያመለክታል። እንደ መልካምና ታዛዥ ልጆች ይሠራሉ። የሃይማኖት ሰዎች የብሉይ ኪዳንን ሕግ ይጠብቃሉ። ውጭ ውጭውን የተነገራቸውን ሁሉ ተግባራዊ ቢያደርጉም፣ ልባቸው እግዚአብሔር ከሚፈልገው የራቀ ነው። እግዚአብሔርን የሚያገለግሉት በፍቅር ተነሣሥተው ሳይሆን በፍርሃት ወይም ውርስን ለማግኘት ከመፈለግ ነው። ለእነዚህ ሰዎች የቤተሰብ ግንኙነት ፋይዳ የለውም። የሚፈልጉት ውርሳቸውን ብቻ ነው። ኃጢአተኛ ልጆቹ በሚመለሱበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ለመደሰት ካልቻልን እንደ ፈሪሳውያን ሆነናል ማለት ነው። የእግዚአብሔርን ፍቅርና ምሕረት በራሳችን ጥረት ለማግኘት በምንፈልግበት ጊዜ እንደ ማንኛውም ኀጢአተኛ እግዚአብሔር ቢወደንም፥ በእግዚአብሔር ፍቅር ደስ ልንሰኝና የቤተሰቡም አባል በመሆናችን ርካታን ልናገኝ አንችልም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ጊዜ ለምን የታላቁን ወንድም ባሕርይ እንደምንይዝ በምሳሌ አብራራ። ለ) ከዚህ ምሳሌ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ምን እንማራለን? ሐ) የልጆቹን አባት ዐይነት ልብ ቢኖረን፣ ምንም የማይጠቅሙ ሰዎች ናቸው ብለን ለምናስባቸው ሰዎች ያለን አመለካከት እንዴት ሊለወጥ ይችላል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ለማብራራት የተናገራቸው ምሳሌዎች (ሉቃስ 15፡1-32)”

Leave a Reply

%d bloggers like this: