የኢየሱስ አገልግሎት ከይሁዳ ወደ ገሊላ ተሸጋገረ። ዮሐንስ ኢየሱስ በገሊላ ሳለ ስላጋጠመው ሁኔታ ብዙም የነገረን ነገር የለም። ሌሎች ተመሳሳይ ወንጌላት በገሊላ ላይ ሲያተኩሩ፣ ዮሐንስ ግን በይሁዳ ላይ ትኩረት አድርጓል።
ኢየሱስ በገሊላ ሳለ ቤተሰቡና ደቀ መዛሙርቱ ለሰርግ ታድመው ነበር። እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በአይሁዳውያንም ዘንድ ጋብቻ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ ለአያሌ ቀናት የሚሰነብት ሥርዐት ነበር። ለእንግዳው ሁሉ የሚበቃ ምግብና መጠጥ አለማቅረቡ ደግሞ እንደ እኛው ሁሉ በአይሁድ ባሕልም አስነዋሪ ተግባር ነበር። እንዲህ ዐይነት ችግር የተከሰተበት ሰርግ ከዚያ በኋላ በቂ የወይን ጠጅ ባለማቅረቡ ሲፌዝበት ይሰነብት ነበር። ምናልባትም የኢየሱስ እናት የሆነችው ቅድስት ማርያም የሰርገኞቹ ዘመድ ወይም የቅርብ ወዳጅ ሳትሆን አትቀርም። ስለሆነም ወይኑ እንዳለቀ ስትሰማ ወደ ልጇ ዘወር ብላ ችግሩን ያስወግድላቸው ዘንድ አንድ ተአምር እንዲያደርግ ጠየቀችው። ለዚህ ጥያቄ ኢየሱስ የሰጠው ምላሽ ለእኛ ከረር ያለ ይመስላል። ነገር ግን ኢየሱስ ለእናቱ አክብሮት የጎደለው ምላሽ ሰጥቷል ማለቱ የማይመስል ነው። «አንቺ ሴት» የሚለው አገላለጽ ለድብ ሳይሆን፣ ሴቶችን መጥራት የሚቻልበት ሌላው መንገድ ነበር። ኢየሱስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው? ለሚለው ጥያቄ የሚቀርቡ ሁለት መልሶች አሉ። አንደኛው፥ የወይኑ አለመኖር እኔንና አንቺን ለምን ያሳስበናል? ወይም ደግሞ በእኔና በአገልግሎቱ ላይ ምን ሥልጣን አለሽ? ማለቱ ነው። በዚህም ኢየሱስ በሁለት እውነቶች ላይ እያተኮር ሊሆን ይችላል።
ሀ. የኃላፊነቱ ሥልጣን የኢየሱስ እንጂ የእናቱ አልነበረም። ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር የተለየ ግንኙነት ስለነበረው፥ ሊያደርግ የሚገባውን የሚነግረው እግዚአብሔር ነበር (ዮሐ 5፡36)። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ኢየሱስ ውኃን ወደ ወይን ጠጅ በመለወጡ የተአምር ተግባሩን እንዲጀምር አልነገረውም፡፡ ይህ ኢየሱስ ለእናቱ የተናገረው ቃል በሉቃስ 2፡49 ላይ ለወላጆቹ የአባቱ የሥራ ተካፋይ መሆን እንዳለበት ከተናገረው ጋር ተመሳሳይ ነበር።
ለ. በሁለተኛ ደረጃ ፥ ኢየሱስ በጊዜው ላይ ትኩረት እያደረገ ነበር። ዮሐንስ በወንጌሉ ኢየሱስ፥ ውስን የጊዜ ሰሌዳ እንዳለውና አገልግሎቱም በመስቀል እንደሚደመደም ገልጾአል። በይፋዊ አገልግሎቱ ሁሉ ወደዚያው መስቀል እያመራ ነበር (ዮሐ 7፡6፣ 8፣ 30፤ 8፡20 እና 12፡23፣ 27፤ 13፡1፤ 16፡32፤ 17፡1።)
ማርያም በመጠኑም ቢሆን ኢየሱስ ተአምር ሊሠራ እንዳለው አውቃለች፤ ምክንያቱም፣ ለአገልጋዮቹ ኢየሱስ የሚላቸውን እንዲያደርጉ ነግራቸዋለች። ኢየሱስም ለማንጻት ሥርዓት የሚሆን ውኃ የሚያጠራቅሙባቸውን ስድስት የድንጋይ ጋኖች ውኃ እንዲሞሏቸው አላቸው። ከዚያም ውኃው ወደ ወይን ጠጅ ተቀየረ።
ዮሐንስ ይህንን የኢየሱስ የመጀመሪያ ተአምር «ምልክት» ይለዋል። ለመሆኑ ኢየሱስ በተአምሩ አማካይነት ሊያሳይ የፈለገው ምልክት ምንድን ነበር፥ ዮሐንስስ ይህንን ተአምር መጽሐፉ ውስጥ ለምን አካተተው? ብዙ አማራጮች አሉ። መጀመሪያ፣ አይሁዶች ስለ መሲሑ መምጣት ካሏቸው ትውፊቶች ውስጥ አንዱ ያ ጊዜ የመብልና ወይን የመጠጥ ወቅት ይሆናል የሚል ነው። አንዳንድ ምሑራን የውኃው ወደ ወይን ጠጅ መለወጥ መሲሑ ኢየሱስ አሁን በመካከላቸው እንዳለ የሚያሳይ ምልክት ነው ብለው ያስባሉ። ሁለተኛ፣ ምናልባትም የውኃው ወደ ወይን ጠጅ መቀየር የመለወጥ ምልክት ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ተራውን ውኃ ወደ ልዩ ወይን ጠጅ እንደለወጠው ሁሉ፥ እንዲሁ የተራ ሰዎችን ሕይወት ልዩ ሰዎች እንዲሆኑ፥ ባዶ ሕይወቶችን ወደ ሙሉ ሕይወቶች፥ እና ደስታ የለሽ ሕይወቶችን ወደ ደስተኛ ሕይወቶች ሊለውጥ ይችላል።
ሐዋርያው ዮሐንስ ተአምሩ በተከናወነበት ስፍራ ሆኖ ይመለከት እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱም ስለ ተአምሩ ብዙ ዝርዝር ጉዳዮችን ያውቃል፥ ይኸውም ምን ያህል ጋኖች እንደ ነበሩ፥ ጋኖቹ ምን ያህል ትልቅ እንደ ነበሩ፥ እና የድግሱ ኃላፊ ምላሽ ምን እንደ ነበረ። ዮሐንስ እንደሚነግረን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህንን ተአምር በተመለከቱ ጊዜ ሁለት ነገሮች ሆኑ። አንደኛ፥ ተአምሩ የኢየሱስ ማንነት እና የክብሩ መገለጸ ነበር። ሁለተኛ፥ ደቀ መዛሙርቱ በኢየሱስ ላይ ያላቸውን እምነት የመጨመሩን ሂደት ጀመሩ፡፡ ስለ ኢየሱስ ብዙ ባወቁ ቀጥር፥ እምነታቸውም እያደገ ይመጣ ነበር። የምናምነውን የበለጠ ባወቅነው መጠን፣ እምነታችን ያድጋል። እምነታችን ደካማ ከሆነ፥ ይሄ የሚያመለክተው ስለ ኢየሱስና ስለ እግዚአብሔር አብ ያለን እውቀት ደካማ መሆኑን ነው።
የውይይት ጥያቄ- ሀ) ኢየሱስን የበለጠ ባወቅኸው ጊዜ እምነትህ እንዴት አደገ? ለ) ይሄ አዳዲስ ክርስቲያኖች እምነታቸው እንዲያድግ ስለ ኢየሱስ በደንብ ማስተማር እንደሚያስፈልገን ምን ያስገነዝበናል?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)