ኢየሱስ ድነትን (ደኅንነትን) ለሳምራዊቷ ሴት አብራራ (ዮሐ. 4፡1-42)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የጾታ፥ የጎሣና የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ በሚገኙ ሰዎች መካከል የምታያቸውን የመናናቅ ሁኔታ ዘርዝር። እነዚህ አሉታዊ የመናናቅ ሁኔታዎች አንዳንድ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚንጸባረቁት እንዴት ነው? ለ) እነዚህ የመናናቅ ሁኔታዎች አንዳንድ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከሰቱት እንዴት ነው? ሐ) ክርስቶስ በእነዚህ ሁለት የተለያዩ ቡድኖች መካከል ያለው ግንኙነት ምን ዓይነት መልክ እንዲኖረው ነው የሚፈልገው?

በማኅበረሰቡ ውስጥ ሥር የሰደደ መናናቅ አብዛኛውን ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ መርዝ ነው። ወንዶች ሴቶችን ይንቃሉ። አንዱ ጎሳ ከሌላው እበልጣለሁ ብሎ ያስባል። የተማሩት ያልተማሩትን ይንቃሉ። የከተማ ሰዎች ከገጠር ሰዎች እንሻላለን ብለው ያስባሉ። ነጋዴዎች ወይም ገበሬዎች ደግሞ ከሸክላ ሠሪዎችና ከቀጥቃጮች እንሻላለን ብለው ያስባሉ። መናናቅ ሌላው የትዕቢት ገጽታ ነው፤ እግዚአብሔር ደግሞ ትዕቢትን ይጠላል። (ያዕ. 4፡6፤ 2፡1-7 አንብብ።)

አይሁዶች ሌሎች ሕዝቦችን ክፉኛ ይንቃሉ። አሕዛብን እጅግ ስለሚጠሉ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ፍቅርም ሆነ ዕቅድ የለውም ብለው ያስቡ ነበር። አሕዛብ ልክ እንደ አረም ተነቅለው መጣል አለባቸው ይሉ ነበር። ግማሽ ጎናቸው አይሁድ ግማሽ ጎናቸው ደግሞ አሕዛብ የነበሩትንና ከይሁዳ በስተ ሰሜን በገሊላና በይሁዳ መካከል ይኖሩ በነበሩት ሳምራውያን ላይ የነበራቸው ጥላቻ የከፋ ነበር። በ722 ዓ.ዓ እስራኤል ወደ አሦር በምርኮ ከሄደችና ከየቦታው ተግዘው የመጡ አሕዛብ በሰማርያ እንዲሰፍሩ ከተደረገ በኋላ፥ በሳምራውያንና በአይሁዳውያን መካክል የከረረ ጠላትነት ሰፍኖ ቆይቷል። በመቃቢያን ዘመን ይህ ጠላትነት እጅግ ከማየሉ የተነሣ፥ አይሁዶች በሺህ የሚቆጠሩ ሳምራውያንን ገድለዋል። ይህ ጥላቻ እጅግ እየከፋ በመምጣቱ ማንኛውም አይሁዳዊ በሰማርያ በኩል አያልፍም ነበር። አይሁዶች ሰማርያን አልፈው ወደ ገሊላ ለመሄድ ተጨማሪ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ለመጓዝ ተገድደዋል።

ኢየሱስ ይጠላው የነበረ ሌላም መናናቅ ነበር። ይህም በወንዶችና በሴቶች መካከል የነበረው መናናቅ ነው። ከአይሁድ ወገን የሆኑ ወንዶች ብዙውን ጊዜ፥ «እግዚአብሔር ሆይ፥ ሴት አድርገህ ስላልፈጠርኸኝ አመሰግንሃለሁ» በማለት ይጸልዩ ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ለሴቶች የነበረው አመለካከት በዚያን ዘመን ከነበሩት አይሁዳዊ ወንዶችና ዛሬም በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ከሚገኙ ምእመናን የተለየ ነበር።

ኢየሱስ የመናናቅ ሕይወትን አውግዟል። እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ እንደሚወድ ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል። በኢየሱስና በሳምራዊቷ ሴት ታሪክ ውስጥ የኢየሱስን ልብ በግልጽ ማየት ይቻላል፤ ኢየሱስ የጥላቻን ግድግዳ አፍርሶ አንዲት የተናቀች ሴት በእርሱ እንድታምን አደረገ። ይህ የክርስቶስና የሳምራዊቷ ሴት ታሪክ፥ ለሰዎች እንዴት መመስከር እንደምንችል የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው። ከዚህ ታሪክ ብዙ እውነቶችን መማር ቢቻልም፤ ከዚህ በታች ስድስት ዐበይት እውነቶች ቀርበዋል፡-

  1. ኢየሱስ ከሌሎች ጋር ለመወዳደር አልፈለገም። የእርሱ እውቅና ማግኘት ከመጥምቁ ዮሐንስ ጋር የውድድር መንፈስ እንዳስከተለ ሲያውቅ፥ ይሁዳን ትቶ ወደ ገሊላ ተመለሰ። ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ወይም ቤተ እምነቶች ጋር ለመወዳደር (ለመፎካከር) እንዳልተጠራን ሁልጊዜ ልብ ማለት ይኖርብናል። በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ እውነተኛ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ናቸው። ስለሆነም፥ ልንወዳቸውና ልንቀበላቸው ይገባል። እግዚአብሔር ሌላውን ግለሰብ ወይም ቤተ ክርስቲያን ከእኛ በላይ ቢጠቀም፥ ከእነርሱ ጋር ከመፎካከር ይልቅ በእግዚአብሔር መንግሥት መስፋፋት ደስ ልንሰኝ ይገባል።
  2. ኢየሱስ በሰማርያ በኩል ማለፍ ነበረበት። በዚያን ዘመን አንድ ሰው ከይሁዳ ወደ ሰማርያ ለመሄድ የሚያስችሉት ሦስት ሁኔታዎች ነበሩ። ከእነዚህ ሁሉ ቀጥተኛው በሰማርያ በኩል ማለፍ ነው፤ ይሁን እንጂ አይሁዶች ሳምራውያንን በብርቱ ስለሚጠሏቸው ይህን መንገድ እምብዛም አይጠቀሙም ነበር። ወይም ደግሞ ከሰማርያ በስተ ምዕራብ በኩል ከተጓዙ በኋላ ወደ ገሊላ መመለስም ይቻል ነበር። ሦስተኛው መንገድ ደግሞ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ከሰማርያ በስተ ምሥራቅ ከሄዱ በኋላ እንደገና የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ገሊላ መመለስም ይቻላል። ብዙውን ጊዜ አይሁዶች በቀጥታ በሰማርያ በኩል ከማለፍ ይልቅ ሁለተኛውንና ሦስተኛውን መንገድ ይመርጡ ነበር። እንግዲህ ኢየሱስ በሰማርያ በኩል ለማለፍ የተገደደው መንገዱ ይሄ ብቻ ስለሆነ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ሳምራዊቷን ሴት እንዲያገኝ ስለነገረው ነው።
  3. ኢየሱስ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር በተነጋገረበት ጊዜ ሁለት የምስክርነት መርሖዎችን ተጠቅሟል። አንደኛው፥ ንግግሩን የጀመረው ሴቲቱ ከምትፈልገው ነገር በመነሣት ነበር። ሴቲቱ ውኃ መቅዳት ሰልችቷት ነበር፤ እርሱ ግን መንፈሳዊ ውኃ አቀረበላት። ሁለተኛው፥ ከምታውቀው ተነሥቶ ወደማታውቀው ወሰዳት። የውኃ ጥማቷን መንፈሳዊ ጥማቷን ለመግለጽ ተጠቀመበት።

አንዲት ሴት ውኃ ለመቅዳት እኩለ ቀን ላይ መሄድ እንግዳ ነገር ነው ምክንያቱም ይህ ሰዓት ሙቀቱ እጅግ የሚበረታበት ሰዓት ስለሆነ ነው። ሌቶች ውኃ ለመቅዳት የሚሄዱት ጠዋት ወይም ማታ ነው። ነገር ግን ይህች ሳምራዊት ሴት በማኅበረሰቡ የተጠላችና ሌሎችም ሰዎች የሚያውቋት ዘማዊ በመሆኗ ማንም ሰው በሌለበት ሰዓት ውኃ ለመቅዳት ወረደች። ምናልባትም ስላሳለፈችው ሕይወት ነፍስና ሥጋዋን የሚለያይ ሐሜት ሰምታ ይሆናል። በውኃው ጉድጓድ አካባቢ የሚሰበሰቡ ሌሎች ሴቶች አግልለዋትም ሊሆን ይችላል።

ኢየሱስ ለዚህች ሴት ስለ ወንጌል ሊነግራት አስቦ፤ ንግግሩንም ጥያቄ በማንሣት ጀመረ። ይህ በአይሁዳውያን ዘንድ እጅግ እንግዳ ተግባር ነበር። በተለይም አንድ አይሁዳዊ ወንድ አንዲትን ሴት ይህን አድርጊልኝ ሊላት አይችልም። ኢየሱስ ይህን ጊዜ የተጠቀመው እርሱ ብቻ ሊሰጣት ስለሚችለው «ሕያው ውኃ» ማለትም ዘላለማዊ ሕይወት ሊነግራት ነው። (ማስታወሻ፡- በአይሁድ አፈ-ታሪክ መሠረት መሢሑ በመጣ ጊዜ ይሰጠናል ብለው ከሚያስቡት ነገሮች መካከል አንዱ ሙሴ እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩ ጊዜ ከዓለት ውኃ እንዳፈለቀላቸው ሁሉ መሢሑም የማያቋርጥ ውኃ እንደሚሰጣቸው ነበር።) ሴቲቱ ኢየሱስ የሚናገረው ስለ ምድራዊ ውኃ መሰላት። ስለዚህ ሊሰጣት ያሰበው ውኃ የዘላለምን ሕይወት ውኃ እንደሆነ አብራራላት።

ነገር ግን ለሰው ኢየሱስ የሚሰጠውን በረከት ብቻ ማወቅ በቂ አይደለም፤ እያንዳንዱ ሰው በኃጢአቱ መገሠጽ አለበት። ስለሆነም ኢየሱስ አምስት ባሎችን ያገባችና በወቅቱ ባሏ ካልሆነ ሰው ጋር የምትኖር ኃጢአተኛ መሆኗን ገለጸላት። ክርስቶስ ይህን ያደረገው የእግዚአብሔር ጸጋ እንደሚያስፈልጋት ለማመልከት ነበር።

በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ኃጢአት ለመቀበል እጅግ አስቸጋሪ ነው። የምንመሰክርላቸው ስዎችም ሆኑ እኛ አብዛኛውን ጊዜ ርእሰ ጉዳዩን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለማዞር እንጥራለን። ስለዚህ ሴቲቱ ትክክለኛው የአምልኮ ስፍራ ሳምራውያኑ የሚያመልኩበት የገሪዛን ተራራ ነው ወይስ አይሁዳውያኑ የሚያመልኩባት ኢየሩሳሌም ስትል አንድ ነገረ መለኮታዊ ጥያቄ አነሣች። ኢየሱስ ግን ውይይቱ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳያመራ አደረገ። ይልቁንም፥ ወደ አምልኮ ዋነኛ አሳብ በማምራት የሚከተለውን አስተማራት።

ሀ. አምልኮ በእውነት ላይ መመሥረት አለበት። ይህ እውነት በሁለት መንገዶች ተመልክቷል። አንደኛው፥ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ከተመሠረተ አምልኮ የሚመጣ እውነት አለ። ክርስቶስ የአይሁዶች አምልኮ የተመሠረተው በብሉይ ኪዳን ላይ በመሆኑ፥ የትክክለኛ አምልኮ ምንጭ እንደሆነ ገልጾላታል። መሢሑ ከመጣ በኋላ ግን ዐቢዩ ጥያቄ የሰዎች ልብ እንጂ  የአምልኮ ስፍራ አይደለም። ሁለተኛው፥ እውነት ከምናምነውና የእግዚአብሔርም ቃል ከሚናገረው እንጻር የምንኖረውን ሕይወት ያመለክታል። ብዙ ክርስቲያኖች ክርስቶስ ብቸኛ የድነት (የደኅንነት) መንገድ እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁንና ወደ ጠንቋዮች ይሄዳሉ፤ መልካም ሥራ በመሥራት ወደ መንግሥተ ሰማይ ለመግባት ይጥራሉ፤ ወይም ደግሞ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ በመወለዳቸው ድነትን (ደኅንነትን) እንደሚያገኙ ይናገራሉ። አንዳንድ ሰዎች የክርስቶስ ተከታይ እንደ ሆኑ ይናገራሉ። ይሁንና በቤት ወይም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ የሚያደርጉት ነገር ከእግዚአብሔር ቃል ጋር አይስማማም። የብዙ ክርስቲያኖች ሕይወት በመንፈሳዊ ግብዝነት የተሞላ ነው። ስለዚህ ክርስትናቸው ከልብ በሆነ እውነት ላይ የተመሠረተ አይደለም። በእውነት ማምለክ የግብዝነት ተቃራኒ ነው፤ ግብዝነት መንፈሳዊነታችንን ለማሳየት የምንጣጣርበት መንገድ ነው።

ለ. አምልኮ በመንፈስ ላይ መመሥረት አለበት። ይህም ሁለት መሠረታዊ አሳቦችን ይዟል። አንደኛው፥ አምልኮ በመንፈስ ቅዱስ ላይ መመሥረት አለበት። መንፈስ ቅዱስ ወደ ግለሰቡ ልብ ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወትን ከማምጣቱም በላይ ግለሰቡ እግዚአብሔርን እንዲያመልክ ያነሣሣዋል። እግዚአብሔርን በንጽሕና ልናመልክ የምንችለው መንፈስ ቅዱስ ልባችንን በሚያንቀሳቅስበት ጊዜ ብቻ ነው። ሁለተኛው፥ አምልኮ በመንፈስ ከተዘጋጀ ልብ መፍለቅ አለበት። ዳግም መወለዱ ብቻ ሳይሆን፥ የምንዘምራቸው መዝሙሮች፥ የምንጸልያቸው ጸሎቶችና የምንሰማቸው ስብከቶች ሁሉ፥ አክብሮታችንንና ፍቅራችንን ለእግዚአብሔር ለመግለጽ ከሚሻ ልብ ሊመነጩ ይገባል። አምልኮ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንመጣ ብቻ የሚፈጸም ተግባር ሊሆን አይገባም። ነገር ግን ሳምንቱን ሁሉ የምንመላለስበት የታዛዥነትና የፍቅር ሕይወት ሊሆን ይገባል።

አምልኮ ሁለት ነገርችን ያካትታል። አምልኮ በልማድ ወይም በስሜት ላይ መመሥረት የለበትም። ነገር ግን አምልኮ ሕይወት ያለው እውነተኛ ድርጊት መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም፥ አምልኮ ለእግዚአብሔር ካለን የትሕትና መገዛት የሚመነጭና በእግዚአብሔር ቃል ላይ መመሥረት አለበት። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምናካሂደው አምልኮ ስሜት የሞላበት ነው። ይህ አብ ደስ የሚሰኝበት አምልኮ ነውን? በልማድ የምናከናውነው ተግባር ምን ያህል ነው? ወይም ሳናስብ በስሜት የምንፈጽመውስ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያልተመሠረተ መሆኑ እየታወቀ፥ ሰዎች በመንፈሳዊነታቸው ሌሎችን ለማስደሰት ብለው የሚያደርጓቸው ነገሮችስ ምን ያህል በርክተዋል?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያንህን አምልኮ ሥርዓት ገምግም። መንፈስና እውነት የዚህ አምልኮ መገለጫዎች ናቸው ብለህ ታስባለህ? ለ) ካልሆነ፥ አምልኮአችሁ እግዚአብሔርን የሚያስደስት ይሆን ዘንድ ሊለውጥ የሚገባው ምንድን ነው?

  1. ከዚህ ምንባብ የምንማረው አራተኛው መርሕ ብርቱ ምስክርነት መስጠት የሚችሉት የተለየ ጸጋ አላቸው ብለን የምናስባቸው ሰዎች ሳይሆኑ፥ እግዚአብሔር በሕይወታቸው ውስጥ ያደረገውን ነገር የሚናገሩ አዳዲስ ክርስቲያኖች ናቸው። ሳምራዊቷ ሴት ስለ ኢየሱስ በከተማይቱ ውስጥ ለነበሩት ሰዎች በመናገሯ ብዙዎች በእርሱ ሊያምኑ ችለዋል።
  2. እግዚአብሔር የሚጠይቀንን ከማድረግ የበለጠ ምንም የሚያስደስት ነገር የለም። ኢየሱስ ለሳምራዊቷ ሴት ወንጌልን በማካፈሉ ምግብ ከመብላት የበለጠ ደስ አሰኝቶታል።
  3. የኢየሱስ ተከታዮች አጋጣሚዎችን ሁሉ ለምስክርነት መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ወደፊት ለምስክርነት አመቺ ዘመን ይመጣል ብለን የምንጠብቀው ጊዜ አይኖርም። ይልቁንም እንደ ሳምራዊቷ ሴት «ለመሰብሰብ የደረሱ ብዙ መከሮች» አሉ። ስንዴ ከዘራን በኋላ መከሩን ለመሰብሰብ አራት ወር መጠበቅ ይኖርብን ይሆናል። በእግዚአብሔር መንፈሳዊ መከር ግን እንዲህ አይደለም፥ መከሩ የሚደርስበትና የሚሰበሰብበት ጊዜ አንድ ነው። ብዙውን ጊዜ ግን እነዚህ ሁለቱ በአንድ ሰው አይካሄዱም። አንድ ሰው ወንጌሉን ይመሰክራል። ይህም ዘሩን መዝራት ነው። በዚህ ጊዜ የተመሰከረለት ግለሰብ በክርስቶስ ላያምን ይችላል። በኋላ ግን ሌላ ሰው ሊመሰክርለትና ሊያምን ይችላል፤ ይህ መከሩን መሰብሰብ ነው። በእግዚአብሔር ሥራ ደስ መሰኘት እንጂ እርስ በርሳችን መቀናናት የለብንም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከዚህ ታሪክ ላላመኑ ሰዎች እምነታችንን ስለማካፈል የምንማራቸው መርሖዎች ምንድን ናቸው? ለ) በቅርቡ ለአንድ ሰው ስለ ክርስቶስ የመሰከርኸው መቼ ነው? ምላሻቸውስ ምን ነበር? ሐ) ኢየሱስ የተጠቀመባቸውን ሁለት መርሖዎች በመጠቀም የተሻለ ምስክርነት ልትሰጥ የምትችለው እንዴት ነበር? (ከላይ ቁጥር 3ን ተመልከት)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ኢየሱስ ድነትን (ደኅንነትን) ለሳምራዊቷ ሴት አብራራ (ዮሐ. 4፡1-42)”

  1. Asiretu samuel

    silezi agelgilot geta abzito yibariki. eyesus kirstos ke samarawitua set gar yasalefew gize ejig betam dink gize new. degmen degagmen binanebina binimar yemianetsan new. ene echi set madenkat binor misikirinetua kirstosin meseret yaderege mehonuna yetederegelatin sayhon ketema woxita yetederegewn neger yaderegelatin kirstosin le sewoch meterekua ejig betam yemiasdenik. new. ahunu sat yalut misikirinetoch yetederegelinin neger meterek enji yaderegelinin meterekina madnek aydelem. lemisale and ke HIV yetefewese sew misikirinet binsema endet be HIV endeteyaze, endet sitamem endeneber, keza endet endetefewese sinager ye egzr sew ketseleyelign buhala hejie simeremer yelem yilal. ayek? yezi sew misikirinet eyesus ke HIV yadinal yifewusal yemil bihon endet des bale!! <> yemilew misikirinet yaderegelinin sinmesekir bicha new.
    Brother Asiratu
    thank you so much!

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading