ኢየሱስ በሽተኞችን መፈወሱና ስለ ሥልጣኑ ከአይሁድ መሪዎች ጋር መከራከሩ (ዮሐ. 4፡43-5፡47)

፩. ሁለተኛው ምልክት፡ ኢየሱስ የሹሙን ልጅ ፈወሰ (ዮሐ 4:43-54)

አንዳንድ ጊዜ የፈውስ ስጦታ ያለው ሰው በመካከላችን ከሌለ እግዚአብሔር ሰዎችን የሚፈውስ አይመስለንም። ወይም ደግሞ ታማሚውን ሰው የፈውስ አገልግሎት ወደሚካሄድበት ቤተ ክርስቲያን እንወስዳለን። ልጁ እንዲፈወስለት ወደ ኢየሱስ የመጣው ሹምም እንዲህ ዓይነት አመለካከት ነበረው። ኢየሱስ ወደ ቤቱ መጥቶ ልጁን እንዲዳስስለት ፈለገ። ኢየሱስ ግን የሹሙን ሰው እምነት በአንድ ደረጃ አሳደገለት። ኢየሱስ ወደ ቤቱ መሄድ (መምጣት) እንደማያስፈልገው ነገረው። ሰውየው ማድረግ ያለበት ኢየሱስ የተናገረውን ቃል ማመን ብቻ ነው። ሰውየውም እንዲሁ አደረገ፤ ልጁም ዳነለት።

ይህ ሁለተኛው (ምልክት) ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ ኃይል እንዳለው አሳይቷል። ኢየሱስ መለኮታዊ ፈዋሽ ነው። ነገር ግን እንደ ሌሎች ሰዎች እርሱ ከበሽተኛው አጠገብ የግድ መገኘት አያስፈልገውም። ኢየሱስ ከየትም ስፍራ ሆኖ መፈወስ ይችላል። ይህ ኢየሱስ አሁን በመንግሥተ ሰማይ አለ። ከእኛ ርቆ እንደሚኖር ልናስብና ዳስሰው ሊፈውሱን ወደሚችሉ ሌሎች ሰዎች ለመሄድ እንፈልግ ይሆናል። እንዲህ በማድረጋችን ግን ኢየሱስ ስሰማይ ሆኖ ልክ በአጠገባችን እንዳለ ያህል ሊፈውሰን እንደሚችል እንዘነጋለን። ሹሙ ሰውዬ የነበረውን ዓይነት እምነት ሊኖረን ይገባል። ኢየሱስ ከፈቀደ ከየትኛውም ዓይነት በሽታ ሊፈውሰን እንደሚችል ማመን አለብን። እምነታችንን በሰው (የፈውስ አገልጋይ)፥ በቦታ (የተለየ ቤተ ክርስቲያን)፥ በተለየ ፕሮግራም ወይም ሥርዓት ላይ መመሥረት የለብንም። ኢየሱስ ብቸኛ የመለኮታዊ ፈውስ ምንጭ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ) ኢየሱስ ሰዎችን ሊፈውስ ያየህባቸውን አጋጣሚዎች ዘርዝር። ለ) በፈውስ ጊዜ በፈዋሹ፥ በስፍራው ወይም በሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ አጽንኦት ማድረጉ ትክክል ያልሆነው ለምንድን ነው?

፪. ኢየሱስ አንድ በሽተኛን በቤተ ሳይዳ ፈወሰ (ዮሐ 5፡1-15)

ዮሐንስ የጠቀሰው ሦስተኛው ምልክት ለ 38 ዓመት ታሞ የነበረውን (ምናልባትም ሽባ የነበረውን) ሰው ታሪክ ነው። ለጥቂት ጊዜ የታመመን ሰው መፈወስ ቀላል ይመስላል፤ ይሁንና ለረጅም ዘመን የታመመውን እንዲህ ያለውን ሰው ለመፈወስ ከቶ የማይሞከር ነው። ለመሢሑ ለኢየሱስ ግን ለአንድ ሳምንት የታመመን ሰው መፈወስ ቀላል እንደ ሆነ ሁሉ፥ ለ38 ዓመት የታመመውንም ሰው መፈወስ ቀላል ነው።

ዮሐንስ እንደገለጸው፥ ኢየሱስ ይህን ተአምር በፈጸመበት ጊዜ የአይሁድ በዓል እየተከበረ ነበር። በዚህ ክፍል የተጠቀሰው በዓል የትኛው በዓል እንደሆነ ሊቃውንት ከስምምነት ላይ አልደረሱም። በዓሉ ምናልባት የአይሁድ ወንዶች ሁሉ ሊያከብሩ ከሚገቧቸው ሦስት በዓላት፥ ማለትም ፋሲካ፥ በዓለ ኀምሳና የመገናኛ ድንኳን እንዱ ሳይሆን አይቀርም። ይህ በዓል የፋሲካ በዓል ከሆነ፥ የክርስቶስ ይፋዊ አገልግሎት ለምን ያህል ጊዜ እንደ ቆየ ለመወሰን ይረዳል። ዮሐንስ ሌሎች ሦስት የፋሲካ በዓሎችን ጠቅሷል (ዮሐ 2፡13፤ 6፡4፤ 11፡55)። ይህ የፋሲካ በዓል ከሆነ፥ የክርስቶስ አገልግሎት የቆየው ከሦስት እስከ አራት ዓመት ያህል ነበር ማለት ነው። በዓሉ ፋሲካ ካልሆነ ግን፥ የክርስቶስ አገልግሎት የቆየው ለሁለትና ሦስት ዓመት ብቻ ነበር ማለት ነው።

ዮሐንስ 5፡4 በመጀመሪያው ቅጂ ላይ ስለመኖሩ በሊቃውንት ዘንድ ክርክር አለ። አብዛኞቹ ሊቃውንት የውኃው «መናወጥ» ምን እንደሆነ ለማብራራት ሲባል ከጊዜ በኋላ የተጨመረ አሳብ ነው በሚለው ይስማማሉ።

ኢየሱስ የፈጸማቸው አብዛኞቹ ተአምራት የተከናወኑት በበሽተኞቹ ጥያቄ ሲሆን፥ በዚህ ስፍራ ግን ክርስቶስ ያለ ማንም ጥያቄ በሽተኛውን ሲፈውስ እንመለከታለን። ቤተሳይዳ በሚባል የውኃ ኩሬ አካባቢ ሲመላለስ ብዙ ሰዎች ተኝተው አገኛቸው። ክርስቶስ ሁሉንም ለመፈወስ አለመሞከሩ አስደናቂ ነገር ነው። ነገር ግን ለብዙ ዓመት በዚያ ተኝቶ ወደነበረው ሰው ሄደ። ውኃውን እግዚአብሔር በሚያናውጥበት ጊዜ መጀመሪያ የገባ ሰው ይፈወስ ነበር። ይህ ሰው ግን ወደ ውኃው የሚያስገባ ዘመድም ሆነ ጓደኛ አልነበረውም። አንድ ቀን እፈወሳለሁ የሚል ተስፋ ስለነበረው ብቻ ዘመኑን ሁሉ በዚያ ቆየ። በመሢሑ የማመን ምንም ምልክት ሳይታይበት ኢየሱስ ግን ፈወሰው።

ይህ ሦስተኛው ምልክት የሚያስተላልፍልን መልእክት ምንድን ነው? በመጀመሪያ፥ ኢየሱስ የትኛውንም ዓይነት በሽታ ለመፈወስ ኃይል እንዳለው ያሳያል። ለኢየሱስ የሚያቅተው ምንም ነገር የለም። ነገር ግን ይህ ሰው ኃጢአተኛነታችንን የሚወክል ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ድነት (ደኅንነት) የምናገኘው ከምንወስነው ውሳኔ ወይም ለራሳችን ከምንሰጠው መፍትሔ የተነሣ አይደለም። በመንፈሳዊ ሁኔታችን ክርስቶስ እንደ ፈወሰው ሰው ረዳት የለሾችና ተስፋ ቢሶች ነን። ነገር ግን ሕይወታችን ምንም ያህል ክፉ ቢሆንና ሁኔታችንም ምንም ያህል ምስኪን ሲሆን፥ ክርስቶስ ሲዳስሰን ሕይወታችንን ይለውጠዋል።

ከዚህ በኋላ ክርስቶስ ሰውየውን አገኘውና ዳግመኛ ኃጢአት እንዳይሠራ ነገረው። ክርስቶስ የሰውየውን ሥጋዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ሕይወትም ለመፈወስ ፈልጓል። መንፈሳዊ ፈውስ የሌለው ሥጋዊ ፈውስ ጊዜያዊ መፍትሔ ብቻ ነው። የዘላለም ሞት ከጊዜያዊ የሥጋ በሽታ የከፋ ነው። እንደዚሁም፥ ዘላለማዊ ሕይወት ከሥጋዊ ጤንነት የላቀ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስላየኸው አንድ ፈውስ ግለጽ። ለ) አብዛኛውን ክብር የሚወስደው የፈውስ አገልጋዩ ነው ወይስ ክርስቶስ? ሐ) ግለሰቡ ከመፈወሱ በፊትም ሆነ በኋላ የታየው መንፈሳዊ ጉዳይ ምንድን ነው? መ) አብዛኞቹ የፈውስ አገልጋዮች ትኩረት የሚሰጡት ለጊዜያዊ ነው ወይስ ለዘላለማዊ ፈውስ? መልስህን አብራራ።

፫. ክርስቶስ ስለ ሥልጣኑ ከአይሁድ መሪዎች ጋር ተከራከረ ( ዮሐ 5፡16-47)

ዮሐንስ በሃይማኖት መሪዎች አስተባባሪነት ኢየሱስን ለመቃወም የተነሡ ሰዎችን «አይሁድ» በማለት ነው የሚጠራቸው። ኢየሱስ በሽተኛውን ሰው ተአምራዊ በሆነ መንገድ በመፈወሱ ደስ ሊሰኙ ሲገባ፥ አይሁዶች የተፈወሰው ሰውዬ በሰንበት ቀን አልጋውን ተሸክሞ በመሄዱ ተቹት። ይህ ሥራ በብሉይ ኪዳን ሕግ ይከለከላሉ ከሚባሉት ነበር። ዮሐንስ እንደሚለው፥ አይሁዶች ኢየሱስን እንዲያሳድዱት ያደረገው የመጀመሪያው ምክንያት በሰንበት ቀን ሰዎችን ማገልገሉ ነበር።

ዮሐንስ፥ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ለማሳየት እርሱ የፈጸመውን ተአምር ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቅሷል። ክርስቶስ ከአይሁድ መሪዎች ጋር ያደረገው ክርክር የሚከተሉትን ነጥቦች ያጠቃልላል፡-

ሀ. እግዚአብሔር በሰንበትም ቀን ሆነ ሁልጊዜም ስለሚሠራ፥ ክርስቶስ በሰንበት ቀን መፈወሱ ስሕተት አልነበረም (ዮሐ 5፡17)። እግዚአብሔር በሰንበት ቀን ሕፃናትን ወደ ዓለም ያመጣል፥ ምግብን ይሰጣል፥ ከክፉ ይጠብቃል፥ ሕይወትን ይሰጣል፥ ሕይወትን ይጠብቃል። እግዚአብሔር ለአንዲት ሰከንድ መሥራቱን ቢያቆም የፈጠረው ዓለም ሁሉ ይናጋል። ኢየሱስ መለኮትና ልዩ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ስለሆነም፥ ሁልጊዜ በሰንበት ቀን ይሠራል። በሰንበትም ቀን መፈወሱ ከሥራዎቹ አንዱ ዓይነት ብቻ ነው። አይሁዶች እግዚአብሔርን «አባቴ» ብለው ለመጥራት አይችሉም። አንዳንድ ጊዜ «አባታችን» ሌላ ጊዜ ደግሞ «በሰማይ ያለህ አባታችን» ይሉ ነበር። ክርስቶስ እግዚአብሔርን «አባቴ» በሚልበት ጊዜ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር እኩል እንዳደረገ ተነዘቡ፤ ይህ ደግሞ ከቶ የማይታሰብ ነበር።

ለ. አይሁድ፥ ኢየሱስ «እግዚአብሔር አባቴ ነው» በማለቱ ራሱን «ከእግዚአብሔር ጋር እኩል» እንዳደረገ ተገነዘቡ (ዮሐ 5፡18-30)። ዮሐንስ የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስን ለመግደል የፈለጉበት ሁለተኛው ምክንያት ይሄ እንደነበር ገልጾአል። ይህ አሳብ እግዚአብሔርን መሳደብ ነው የሚል አመለካከት ነበራቸው። ክርስቶስ የራሱን መለኮትነት ከመደበቅ ይልቅ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ልዩ ግንኙነትና የዚህንም ግንኙነት ትርጉም በትክክል አብራራ።

  1. ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደመሆኑ፥ በባሕርይም ሆነ በችሎታ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ነው። በሥልጣን ግን ለእግዚአብሔር አብ ይታዘዛል። ስለሆነም፥ የራሱን ሥልጣን ከመጠቀም ይልቅ እግዚአብሔር አብ ያዘዘውን ያደርጋል። እግዚአብሔር አብም ለልዩ ልጁ ካለው ፍቅር የተነሣ ሊያደርግ የሚገባውን ሁሉ አሳይቶታል።
  2. እግዚአብሔር አብ ከሚያደርጋቸውና ልጁ እንዲፈጽም ሥልጣን ከሰጣቸው ነገሮች አንዱ፥ ሙታንን ማስነሣት ነው። ዮሐንስ በዚህ ስፍራ ለመግለጽ የፈለጋቸው ሁለት ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ፥ ሥጋዊ ሕይወትና የሙታን ትንሣኤ አለ። የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቶስ አልዓዛርን ከሞት እንዳስነሣው እኛንም ከሞት ያስነሣል (ዮሐ 11)፡፡ ክርስቶስ ሰዎችን ሁሉ ከሥጋዊ ሞት ያስነሣቸዋል። ከዚያም በእርሱ ለማመን ፈቃደኛ ያልሆኑ ሁሉ ይኮነናሉ። በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ ግን የዘላለም ሕይወትን ይቀበላሉ። ሁለተኛ፥ ዮሐንስ ክርስቶስ በእርሱ ለሚያምኑ ሰዎች ስለሚሰጣቸው መንፈሳዊ ሕይወት ይናገራል። ክርስቶስ በኃጢአታቸው ምክንያት በመንፈስ ሙት ለሆኑ ሰዎች መንፈሳዊ ሕይወትን ይሰጣል። ክርስቶስ ስለ ድነት (ደኅንነት) መንገድ የተናገረውን ቃል ሰምተው ክርስቶስን በላከው በእግዚአብሔር አብ የሚያምኑ ሰዎች ከማያምኑ ሰዎች ጋር ወደ ሲኦል አይወርዱም።
  3. ሌላው እግዚአብሔር ለልጁ የሰጠው ሥራ በመጨረሻው ቀን በሰዎች ላይ መፍረድ ነው። ሰዎች የሚፈርዱት ውጫዊ ነገርን ለምሳሌ ዘርን፥ ትምህርትን ወይም ሀብትን አይተው ነው፤ ኢየሱስ የሚፈርደው ግን ውስጣዊ ነገርን አይቶ ነው። ኢየሱስ አብን ለማስደሰት ካለው ፍላጎት የተነሣ ስለሚፈርድ ፍርዱ ሁሉ ትክክል ይሆናል።
  4. እግዚአብሔር አብ እርሱ እንዳከበረው ሁሉ ልጁም ይከብር ዘንድ ሥልጣንን ለልጁ ይሰጠዋል። እግዚአብሔር ክርስቶስን ወደ ዓለም ስለላከው ልጁን የማያከብር ሰው እግዚአብሔር አብን አከብራለሁ ሊል አይችልም። አይሁዶች ክርስቶስን ክደው የብሉይ ኪዳኑን ያህዌን ሊያከብሩና ከእርሱም ጋር ትክክለኛ ግንኙነት አለን ብለው ሊያስቡ አይችሉም። ሙስሊሞችና የሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮችም ክርስቶስን እንደ አምላክ ተቀብለው ካላከበሩት ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ሊኖራቸው አይችልም።

ሐ. ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚያሳዩ አራት ምስክሮችን አቀረበ (ዮሐ 5፡31-47)። በአይሁድ ችሎት አንድ ሰው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ካልመሰከሩበት በስተቀር እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ አይመረመርም ነበር (ዘዳግ 19፡15)። አንዱ ሌላውን መክሰሱ ብቻ በቂ አይደለም። በወንጀለኝነት በተከሰሰው ግለሰብ ላይ ሌላ አንድ ሰው መመስከሩም በቂ አልነበረም። አይሁዶች ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ሕጋዊ ተቀባይነት ባለው መንገድ እንዲያረጋግጥ ጠየቁት። እርሱም ምንም እንኳ ምስክርነቱ እውነት ቢሆንም፥ በቂ ማረጋገጫ እንደማይሆን አመልክቷል። ስለሆነም፥ ሌሎች አራት ምስክርነቶችን ጠቀሰላቸው፡፡

  1. መጥምቁ ዮሐንስ፡- ቀደም ሲል መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንደመሰከረ ተመልክተናል። አይሁዶች ዮሐንስን እንደገና ጠርተው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንዲያረጋግጥላቸው ጠየቁት። ክርስቶስ ይህንን በሚናገርበት ጊዜ ዮሐንስ ሳይሞት አልቀረም። ኢየሱስ ስለ እርሱ የገለጸው በኃላፊ ጊዜ ነበር።
  2. ክርስቶስ ባደረገው ሥራ፡- ክርስቶስ የፈጸማቸው ተአምራት እርሱ ሰው ብቻ ሳይሆን፥ አምላክም እንደሆነ የሚያመለክቱ «ምልክቶች» ነበሩ።
  3. እግዚአብሔር አብ፡- በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ክርስቶስ የሚወደውና በእርሱም ደስ የሚሰኝበት ልዩ ልጁ እንደሆነ ገልጾአል (ማቴ. 3፡17፤ 17፡5)። አንድ ጊዜ ክርስቶስ በዮሐንስ በሚጠመቅበት ጊዜ እግዚአብሔር ይህንኑ ምስክርነት ሰጥቷል። ሰዎች ድምፅ ቢሰሙም እግዚአብሔር የተናገረውን የተገነዘቡ አይመስልም። አለማመን የእግዚአብሔርን ድምፅ እንዳይሰሙ ጆሮዎቻቸውን ደፍኖት ነበር። ይህም ዛሬ ሰዎች በክርስቶስ አምነው እንዳይድኑ አለማመን እንደሚከላከላቸው ዓይነት ነው። እግዚአብሔር በሙሉ ልባቸው የሚፈልጉት ሁሉ እርሱን እንደሚያገኙት ተስፋ ሰጥቷል (ኤር. 29፡13)። ችግሩ በልባችን እግዚአብሔርን ላለመስማት ከወሰንን ጆሮዎቻችን ለድምፁ የተደፈኑ ይሆናሉ።
  4. ቅዱሳት መጻሕፍት፡- ከማቴዎስና ከሉቃስ ጥናታችን እንደምናስታውሰው፥ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ ወደ ኢየሱስ የሚያመለክቱ ናቸው። በብሉይ ኪዳን ሁሉም መጽሐፍ ማለት ይቻላል ስለ መሢሑ ክርስቶስ አንድ የሚናገሩት ነገር አለ። ነገር ግን ምንም እንኳ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ ቢያጠኑም፥ መጻሕፍቱ ስለ ክርስቶስ የሚሰጡትን ምስክርነት አልተረዱም። አይሁዶች በክርስቶስ ባለማመናቸው፥ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን በእርሱ በኩል ለመስጠት ቃል የገባውን የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት አልቻሉም።

አለማመን የሰው ልጆች ከሚጋፈጡት ብርቱ ትግል አንዱ ነው። ሰዎች ገና ከመጀመሪያው እግዚአብሔር የሚናገረውን ነገር ላለመስማትና ላለማየት፥ ልቦናቸውን ከዘጉ፥ እግዚአብሔር ተአምራትን ቢያደርግ ወይም ድምፁን ቢያሰማ እርሱን ሊሰሙትና በእርሱ ሊያምኑ አይችሉም። ክርስቶስ በግልጽ ተአምራት ቢያደርግም፥ ተአምራቱን ላለማመን የወሰኑትን ሰዎች ለመለወጥ አልቻሉም። ይህ ዛሬም እውነት ነው። እግዚአብሔር ዓለምን እንደ ፈጠረ፥ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ሰዎችን እየፈወሰ እንዳለ የማይቀበሉ ሰዎች ወይም እግዚአብሔርን ከሕይወታቸው ያስወጡ ሰዎች እርሱን አይተው ወንጌልን ሊቀበሉ አይችሉም።

አይሁዶች በጣም ሃይማኖተኛ ሰዎች ናቸው። ብሉይ ኪዳንን፥ በተለይም የሙሴን ሕግጋት ዘወትር ያነብባሉ። የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት መሪዎች የሰጧቸውን ሌሎች ሃይማኖታዊ ሕግጋትንም ለመጠበቅ ቀናተኛች ነበሩ። ነገር ግን በውጫዊ ሁኔታቸው እግዚአብሔርንና ሙሴን እንደሚያከብሩ ለማሳየት ቢሞክሩም፥ የአብዛኞቹ አይሁዶች ልብ ግን ባለማመን ተሞልቶ ነበር። ልባቸውን ከፍተው እግዚአብሔርን ለመስማት አለመፈለጋቸው ሁለት ነገሮችን አስከትሏል። አንደኛው፥ አይሁዶች ሙሴ የተናገረውን ነገር በትክክል አልተረዱም፤ ምክንያቱም ሙሴ የተናገረው ስለ ኢየሱስ ነው። ክርስቶስን ለማክበርና ለመቀበል ባለመፈለጋቸው አይሁዶች፥ ብሎም የሃይማኖት መሪዎች ሙሴን ከልባቸው እንደማያከብሩት አሳይተዋል። ከዚህ የሚከፋው ደግሞ ይህ ድርጊታቸው ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ማሳየቱ ነው። በልባቸው ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር ቢኖር ወይም ከእርሱ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ትክክል ቢሆን ኖሮ፤ የአይሁድ ሕዝብ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በመረዳት ያምኑበት ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የእግዚአብሔርን ቃል እናከብራለን የሚሉ የሃይማኖት ሰዎች፥ አንዳንድ ጊዜ እንዴት የእግዚአብሔርን ሥራ ለማየት እንደሚታወሩ ምሳሌዎችን ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር በዚህ መንገድ መሥራት አለበት በሚል አስተሳሰብ ሥራዎቹንና ድምፁን ከመቀበል እንዳንስት ይህ እንዴት ሊያስጠነቅቀን ይገባል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: