ክርስቶስ በዳስ በዓል ላይ ተገኘ (ዮሐ. 7፡1-53)

ዮሐንስ ከሚናገራቸው ነገሮች አንዱ የክርስቶስ ሕይወት በእግዚአብሔር አብ እጅ ውስጥ ባለው «ጊዜ» የተገዛ ነው። ቀደም ሲል ለክርስቶስ ተአምራትን ለማድረግ «ጊዜው» እንዳልነበር ተመልክተናል (ዮሐ 2፡4)። አሁን ኢየሱስ ሰዎችን ስለ መሢሕነቱ ለማሳመን ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ጊዜው እንዳልሆነ ተናግሯል። የክርስቶስ መንገድና ጊዜ ከሌሎች ሰዎች የተለየ ነው። ዮሐንስ እንደሚናገረው የኢየሱስ «ወንድሞች» ማለትም የዮሴፍና የማርያም ልጆች ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን አልተቀበሉም። ክርስቶስ መሢሕነቱን እንዲያረጋግጥ ይገፋፉት ነበር። ክርስቶስ መሢሕ ከሆነ፥ መሢሕነቱን ለማረጋገጥ በኢየሩሳሌም ከሚደረገው የዳስ በዓል የተሻለ ስፍራ እንደማይኖር ገለጹለት። ይህ የአይሁድ ወንዶች ሁሉ ከሚሳተፉባቸው ዐበይት በዓላት አንዱ ነበር።

ክርስቶስ ጊዜውን የሚጠቀመው በሰዎች አሳብ አይደለም። የሚያደምጠው እግዚአብሔር አብን ብቻ ነው። ስለዚህም ክርስቶስ ፈጥኖ ወደ ኢየሩሳሌም አልሄደም። ነገር ግን ዝናው የገነነ በመሆኑ፥ አይሁዶች ስለ እርሱ ይነጋገሩ ነበር። አንዳንዶች ጥሩ ሰው እንደሆነ ሲናገሩ፥ ሌሎች ደግሞ መጥፎ ሰው ነው ይሉ ነበር።

የዳስ በዓል የሚቆየው ለስምንት ቀን ነው። በዚያን ጊዜ ክርስቶስ ወደ በዓሉ መጥቶ ሕዝቡን ማስተማር ጀመረ። ዮሐንስ በቀጥታ ባይናገርም ኢየሱስ በሰንበት ቀን አንድ ሰው ሳይፈውስ አልቀረም። አሁንም ሰዎች ኢየሱስን በተመለከተ ሁለት ምላሽ ሰጥተዋል። አንዳንድ ሰዎች በትምህርቱ ተደንቀው ነበር። ክርስቶስ ትምህርቱ ከእግዚአብሔር እንደ መጣና እውነተኛ የእግዚአብሔር ተከታዮች ሁሉ የተናገረው እውነት እንደሆነ እንደሚያምኑ ገለጸ። ነገር ግን የሰንበት ሕጎቻቸውን ባለማክበሩ ምክንያት እንደ ሃይማኖት መሪዎች ያሉ ሰዎች እንደሚጠሉትና ሊገድሉትም እንደሚፈልጉ ያውቅ ነበር። ክርስቶስ ከምሕረት ይልቅ ሥርዓቶችን ማክበር የራስ ወዳድነት ተግባር መሆኑን ገለጸላቸው። ምክንያቱም በስምንተኛው ቀን ወንድ ልጆቻቸውን በሚገርዙበት ጊዜ አንዱን ሥርዓት ለማክበር ሲሉ ሌላውን (ሰንበት) ያፈርሱ ነበር።

የበዓሉ ቀን እያለፈ ሲሄድ የክርስቶስ ትምህርት ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጣ። በእግዚአብሔር ተልእኮ ከሰማይ እንደ መጣ በግልጽ በመናገሩ አይሁዶች ተሳድቧል ብለው ሊገድሉት ፈለጉ። ከዚያም ክርስቶስ ወደ ሰማይ የሚመለስበት ጊዜ መቃረቡን ነገራቸው።

የዳስ በዓል የሚከበርበት የመጨረሻው ቀን በዓሉ ይበልጥ የሚደምቅበት ዕለት ነው። በዚያን ዕለት ከሚካሄዱት የአምልኮ ሥርዓቶች አንዱ ልዩ የውኃ መቅጃ ይዞ ወደ ምንጭ መሄድ ነበር። ካህናት ከምንጩ ውኃ ቀድተው በመምጣት በቤተ መቅደሱ መሠዊያ ላይ ያፈስሱታል። ይህም መንፈሳዊ በረከት በሕዝቦች ሁሉ ላይ መፍሰሱን ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ የሚያመለክት ነው። ይህ በተጨማሪም፥ መሢሑ በሕዝቡ ላይ የሚያወርደውን በረከት የሚያመለክት ነበር። ምናልባትም በበዓሉ መጨረሻ ላይ፥ ክርስቶስ ለሕዝቡ የሕይወት ውኃን የሚሰጠው መሢሕ ራሱ እንደሆነ ሳይገልጽ አልቀረም። እርሱ ለሕዝቡ መንፈሳዊ የድነት (የደኅንነት) ውኃ ይሰጣቸው ነበር። በተጨማሪም፥ የማያልቀውን መንፈሳዊ የውኃ ምንጭ በልባቸው ውስጥ ያፈስ ነበር። ዮሐንስ እንደሚለው ይህ ሕያው ውኃ መንፈስ ቅዱስ ነው።

በክርስቶስና በሃይማኖት መሪዎች መካከል የተነሣው ጠላትነት እየከረረ ሄደ። ወታደሮቹ ሊያስሩት ቢፈልጉም በትምህርቱ በመደነቃቸው ይህን ለማድረግ አልፈለጉም። አስፈላጊው ምርመራ ሳይደረግ በማንም ሰው ላይ መፍረድ ተገቢ እንዳልሆነ ያሳሰበው ኒቆዲሞስ ብቻ ነበር። የአይሁድ መሪዎች ከገሊላ አንድም የእግዚአብሔር ነቢይ መጥቶ አያውቅም በማለታቸው ጥላቻቸውንና የእግዚአብሔርን ቃል አለማወቃቸውን አሳዩ። ዮናስ የመጣው ከገሊላ እንደ ሆነ ረስተው ነበር። በተጨማሪም፥ እግዚአብሔር ሥራውን ለማከናወን ሲፈልግ ደስ ካለው ስፍራ የማስነሣት መብት እንዳለው ዘንግተው ነበር። እግዚአብሔር በተወሰኑ ዘሮች ወይም መሪዎች አማካይነት ብቻ ነው የሚሠራው ብለን እንድናስብ የሚያደርገን ትምክህታችንና ትዕቢታችን ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡– ትምክህታችንና ትዕቢታችን እግዚአብሔር በመካከላችን የሚሠራውን ሥራ እንዳናስተውል የሚያደርግበትን መንገድ በምሳሌ ግለጽ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: