ዮሐ. 16:1-33

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የመንፈስ ቅዱስ ትልቁ አገልግሎት ምን እንደ ሆነ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ፣ የሙሉ ወንጌል፥ የመካነ ኢየሱስና የቃለ ሕይወት ክርስቲያኖችን ጠይቅ። መልሶቻቸውን በወረቀት ላይ ጻፍ። ለ) የመንፈስ ቅዱስ ትልቁ አገልግሎት ምን ይመስልሃል? ሐ) ዮሐ 16፡5-16 አንብብ። በዚህ ክፍል ክርስቶስ የመንፈስ ቅዱለ ትልቁ አገልግሎት ምንድን ነው አለ? መ) አብዛኛቹ ክርስቲያኖች የመንፈስ ቅዱስ ትልቁ አገልግሎት እንደ ሆነ የሚያስቡት ክርስቶስ የተናገረውን ነው ወይስ ሌላ ነገር? መልስህን አብራራ። አንዳንድ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ክርስቶስ ከተናገረው ውጭ እንደ ሆነ የሚያስቡት ለምንድን ነው?

እስካሁን ድረስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠውን የመጨረሻውን ዐቢይ ትምህርት ስናጠና ቆይተናል። በሞት ሊለይ ጥቂት ጊዜ ብቻ የቀረው አባት፥ ለልጆቹ ጠቃሚ ምክሮችን ለመስጠት እንደሚፈልግ ሁሉ፥ ኢየሱስ ክርስቶስም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ከመሞቱ በፊት እጅግ ዐበይት ከሆኑ እውነቶቹ መካከል፥ አንዳንዶቹን ለደቀ መዛሙርት አስተምሯል። ክርስቶስ ካስተማራቸው ዐበይት ጉዳዮች አንዱ የመንፈስ ቅዱስ ትምህርት ነው። ስለ መንፈስ ቅዱስ ግልጽና ሚዛናዊ ግንዛቤ ለመጨበጥ ከፈለግን፤ ክርስቶስ በዚህ ጊዜ ስለ መንፈስ ቅዱስ መሠረታዊ ዓላማ ያሰማውን ትምህርት መረዳት አለብን።

  1. ክርስቶስ እርሱን የሚከተሉ ሰዎች ስደትና ሞት እንደሚደርስባቸው ለደቀ መዛሙርቱ አስጠነቀቀ (ዮሐ 16፡1-4)።

አብዛኛውን ጊዜ ለአዲስ አማኞች የወንጌልን አዎንታዊ ጎኖች ብቻ ስለምንነግራቸው እንሳሳታለን። ስለ ድነት (ደኅንነት)፥ የዘላለም ሕይወት፣ ክርስቶስ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚሰጣቸው፥ ከበሽታም እንደሚፈውሳቸው እንነግራቸዋለን። ይህ የበረከት ገጽታው ነው። ወንጌሉ ሌላም ገጽታ አለው፥ ፈተና፥ ቅጣትና ስደት በአማኞች ላይ ሊደርስ ይችላል። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሁለቱንም የወንጌል ገጽታዎች ነበር የገለጸላቸው። ክርስቶስ በእርሱ ለሚያምኑ የዘላለም ሕይወትን፥ ሰላምንና ደስታን እንደሚሰጣቸው ተናግሯል። በተጨማሪም፥ ስደት እንደሚያጋጥማቸው ከመግለጽ አልተቆጠበም። ክርስቶስ እንደ ተጠላ ሁሉ እነርሱም ይጠላሉ።

ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ከአይሁድ ምኩራብ እንደሚባረሩ ገልጾላቸዋል። አይሁዶች የክርስቶስን ተከታዮች በመግደላቸው፥ እግዚአብሔርን ያገለገሉ እየመሰላቸው ደቀ መዛሙርቱን በመግደልና በመጥላት አሳድደዋቸዋል። (እስጢፋኖስ እና ያዕቆብ ለዚህ ተስማሚ ምሳሌዎች ናቸው። የሐዋ. 7፡54-60፤ 12፡2-3)። አይሁዶች በዚህ ድርጊታቸው እግዚአብሔርን እያስደሰቱ ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ ኅብረት እንዳልነበራቸው የሚያመለክት ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለአንድ ሰው በምንመሰክርበት ጊዜ ክርስቶስን መከተል የሚያስከፍለውን ዋጋ ጨምረን ብንገልጽለት፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የወንጌል ምስክርነት የሚለወጠው እንዴት ነው? ለ) ብዙውን ጊዜ ለአዳዲስ ክርስቲያኖች ክርስቶስን መከተል ስለሚጠይቀው ኃላፊነት የማንናገረው ለምንድን ነው?

  1. ክርስቶስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ስለሚመጣው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ አስተማረ (ዮሐ 16፡5-16)

ክርስቶስ ለተከታዩቹ ሁሉ ስለሚሰጣቸው ስለ መንፈስ ቅዱስ ተጨማሪ ገለጻ ይሰጣል። ኢየሱስ በምድር ላይ ከሚቆይ ይልቅ ቢሄድ እንደሚሻል፥ ለደቀ መዛሙርቱ ገልጾአል። ለተከታዮቹ በሙሉ መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው እርሱ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ ብቻ ስለሆነ ነው። የመንፈስ ቅዱስ ዐቢይ አገልግሎት ምን እንደሆነ ክርስቶስ የተናገረውን ልብ ብለህ አስብ።

ሀ. መንፈስ ቅዱስ ላላመኑ ሰዎች የሚሰጠው አገልግሎት አለው። አገልግሎቱም ኃጢአተኞች መሆናቸውን ማስገንዘብና አዳኝም እንደሚያስፈልጋቸው መግለጽ ነው። የማያምኑ ሰዎች የሚገሠጹበት ትልቁ ኃጢአት ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ መንገድ መሆኑን አለማመናቸው ነው። በክርስቶስ በሚያምኑበት ጊዜ እንደማይኮንናቸው ያሳውቃቸዋል፥ ይህም ጻድቃን እንደሚሆኑ ያሳያል። በክርስቶስ ባለማመናቸው እግዚአብሔር ስለሚያወጣባቸው ፍርድ ያስጠነቅቃቸዋል። በተጨማሪም፥ የዓለም ገዥ የሆነው ሰይጣን እንደተሸነፈና ከእንግዲህ እርሱን መፍራትም ሆነ የሐሰት ትምህርቱን መከተል እንደሌለባቸው ያረጋግጥላቸዋል።

ምስክርነት የሁለት ወገኖች ተግባር ነው። በሰዎች ዘንድ እግዚአብሔር ለሚያምኑ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ፥ እንዲሁም በዚህም ስለሚሰጣቸው የዘላለም ሕይወት፥ ለማያምኑ ሰዎች ደግሞ ስለሚጠብቃቸው የዘላለም ሞት እንድንናገር አዝዞናል። ይሁንና ይህን ተግባር ሰዎች ብቻ የሚያከናውኑት ከሆነ ማንም ሰው ወደ እምነት አይመጣም። ሰዎች በመንፈሳቸው ሙት ናቸው። ሰይጣንም ሊበጥሱት በማይችሉት ሰንሰለት ተብትቦ አለሯቸዋል። ስለዚህ በሥራው ላይ እግዚአብሔርም መሳተፍ አለበት። መንፈስ ቅዱስ ለሰዎች በምናካፍላቸው ቃል አማካይነት መንፈሳዊ ዓይኖቻቸውንና አእምሯቸውን ይከፈታል። ይህም የተመሰከረላቸው ሰዎች ወንጌሉን እንዲረዱት ያደርጋል። በዚህ ጊዜ ዓለማዊው ሰው በክርስቶስ ያምናል።

ለ. መንፈስ ቅዱስ በአማኞችም መካከል ያገለግላል። ክርስቲያኖችን ያስተምራል፣ ወደ እውነትም ይመራቸዋል። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ የሚያስተምረውን እውነት የሚያገኘው ከየት ነው? መንፈስ ቅዱስ የሚያስተምረው ከኢየሱስ የተቀበለውን ብቻ እንደ ሆነ ራሱ ገልጾአል።

ሐ. መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስን ያስከብራል። ይህ የመንፈስ ቅዱስ ተቀዳሚ ተግባር ነው። በሌላ አገላለጽ፥ መንፈስ ቅዱስ ዓለምን በኃጢአቱ በመውቀስ ሰዎች በክርስቶስ እንዲያምኑ ሲያደርግና ክርስቲያኖች እውነትን እውቀው እንዲኖሩበት ሲመራቸው፥ በዚያን ጊዜ ክርስቶስ ከፍ ከፍ ይላል።

የውይይት ጥያቄ፡– እነዚህ ሦስት የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች ተግባራዊ ሲሆኑ ያየህባቸውን የተለያዩ መንገዶች ዘርዝር።

ክርስቶስ በብዙ የተለያዩ መንገዶች ይከብራል። በዕለተ ሰንበት ብቻ ሳይሆን በየቀኑ ለእርሱ እየተገዛን ስሙን ከፍ ስናደርግ፥ ትእዛዛቱን ስንጠብቅ፥ እርሱን ስንመስልና ለሌሎች ስለ እርሱ ስንመሰክር ይከብራል።

  1. ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱ ኀዘን ወደ ደስታ እንደሚለወጥ ተነበየ (ዮሐ. 16፡17-33)።

ዓላማ እንዳለንና የደስታም ቀን እንደሚመጣልን ስናውቅ፥ ይህ ችግሮችን ለመታገሥ ይረዳል። ነገር ግን ችግሮች ለምን እንደ ደረሱብን ካላወቅን ወይም የደስታ ቀን እንደሚመጣ እርግጠኞች ካልሆንን፥ በቀላሉ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። እርጉዝ የሆነች ሴት የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስ የሚያጋጥማትን የምጥ ችግር ታግሣ መቋቋም ይኖርባታል። ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ስለሚመጣው «ኅዘን»፥ እንዲሁም ስለሚያጋጥማቸው «ደስታ» አብራርቶ አስተምሯቸዋል።

ሀ. ኀዘን፡- በደቀ መዛሙርቱ ላይ የሚመጣው ኀዘን ሁለት ደረጃዎች ይኖሩታል። አንደኛው፥ ደቀ መዛሙርቱ ከፍተኛ ኀዘን የሚደርስባቸው ጌታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ወንጀለኛ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሲሞት ነው። በዚህ ጊዜ ተስፋቸው ሁሉ ይመነምናል። በአንጻሩ የክርስቶስ ጠላቶች እርሱ ለችግራቸው መፍትሔ ሆኖ ሲሞት በሚመለከቱበት ጊዜ እጅግ ደስ ይሰኛሉ። ሁለተኛው፥ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ወደ እግዚአብሔር አብ በሚመለስበት ጊዜ በመጠኑ ያዝናሉ። ይህን ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ከሚወዱት ከኢየሱስ በአካል ይለያሉ።

ለ ደስታ፡– ይህ ሦስት ደረጃዎች ይኖሩታል። አንደኛው፥ ክርስቶስ ከሞት ተነሥቶ በሕይወት ሲያገኙት ደስ ይላቸዋል። ሁለተኛው፥ በክርስቶስ አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር አዲስ ግንኙነት ስለሚኖራቸው ደስ ይላቸዋል። የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናችን፥ ጸሎታችንን ሰምቶ እንደሚመልስልን በመገንዘብ ወደ እርሱ የምንቀርብበት በር ተከፍቶልናል። ሦስተኛው፥ ክርስቶስ ዳግም በሚመለስበት ጊዜ ዘላቂ ደስታ ይኖረናል። ከክርስቶስ በአካል መለያየታችን ያበቃል። ችግሮቻችንና ስደቶቻችን አክትመው በታላቁ መንግሥት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር እንኖራለን። ጳውሎስ እንዳለው፥ «ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፥ የሚታየው የጊዜው ነውና የማይታየው ግን የዘላለም ነው» (2ኛ ቆሮ. 4፡16-18)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በሕይወትህ ያጋጠሙህን አንዳንድ ኅዘኖች ዘርዝር። ለ) በኀዘንህ ወቅት እግዚአብሔር ምን አስተማረህ? ሐ) በኀዘንህ ጊዜ ተስፋ ሳትቆርጥ እንድትኖር ያደረገህ ነገር ምንድን ነው? መ) በመከራ ጊዜ ዓይኖቻችንን በዘላለሙ ተስፋችን ላይ ማሳረፉ ለምን ይጠቅማል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: