የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ልዩ ገጽታዎች

  1. ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የጴጥሮስና የጳውሎስ ስብከቶች አንድ አምስተኛውን ወይም ሃያ በመቶውን እጅ ይሸፍናሉ። በእነርሱ አማካይነት ስለ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና እምነት ጥሩ ማብራሪያዎችን አቅርቧል። በእነዚህ ስብከቶች አማካይነት አይሁዶችና አሕዛብ ክርስቶስ ለምን የተስፋቸው መልስ እንደሆነ ያውቁ ነበር።
  2. እንደ ወንጌላቱ ሁሉ የሐዋርያት ሥራም በጥንቃቄ የተመረጡ ታሪኮችን ይዟል። ይህ ግን ዐቢይ የትርጓሜ/ የአፈታት ጥያቄ እንድናነሳ ያደርጋል። በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ፥ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ የሚጽፈው ሰው የተፈጸመውን ነገር «እየገለጸ» ነው ወይስ ነገሮች እንደዚያ መሆን እንዳለባቸው «እያሳየ» ነው? ለምሳሌ፥ ክርስቶስ ምራቁን በጭቃ ለውሶ በመቀባት የሰውዩውን ዓይን ሲፈውስ፥ ይህ ክርስቶስ ካደረጋቸው ፈውሶች አንዱን ለመግለጽ የተጻፈ ነው ወይስ መንፈስ ቅዱስ ለዓይነ ስውሮች ለመጸለይ ስንፈልግ በምራቅ የተለወሰ ጭቃ መጠቀም እንዳለብን እያሳየን ነው? ስለ ሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ያለን ግንዛቤ፥ መጽሐፉ በወቅቱ የተፈጸሙ ድርጊቶችን እየገለጸ ነው ወይም ዛሬም ቢሆን በመጽሐፉ ውስጥ የተገለጹት ነገሮች በሙሉ በእኛም ዘመን መፈጸም አለባቸው በሚለው አሳብ ላይ የተመሠረተ ነው። ለምሳሌ፡- በሐዋርያት ሥራ 2 ላይ መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱ ሰው በመንፈስ ቅዱስ በሚሞላበት ጊዜ ነፋስ፥ እሳትና ልሳናት ይወርድበታል በማለት እያስተማረ ነው? ወይስ በዚያን ጊዜ የተደረገውን ልዩ ነገር መንፈስ ቅዱስ እየተረከ ነው? አንዳንድ ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ በልሳናት የተገለጸባቸው ምንባቦች ዛሬ መንፈስ ቅዱስ እንዴት ወደ ክርስቲያኖች እንደሚመጣ ያሳያሉ ይላሉ። የሐዋርያት ሥራ ዛሬም ይህ መሆን እንዳለበት እየነገረን ነው ይላሉ። ካሪዝማቲክ ያልሆኑ ክርስቲያኖች ግን የሐዋርያት ሥራ በመጀመሪያው ምእተ ዓመት ስለ ተከናወኑት ነገሮች የሚገልጽ ነው ይላሉ። በመሆኑም፥ አንድ ሰው ድነቱን (ደኅንነቱን) ካገኘ በኋላ በልሳን በመናገር የሚገለጽ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንደሚቀበል አድርገን ማሰብ የለብንም ባይ ናቸው። የሐናንያና ሰጲራ ታሪክ ዛሬም እግዚአብሔር ሌቦችን ወዲያውኑ እንደሚገድል የሚያስተምሩ አይደሉም። የጥንት ክርስቲያኖች ንብረታቸውን ሸጠው በአንድነት ማድረጋቸው፥ እኛም ልክ እንደ እነርሱ እንድናደርግ የሚያስተምረን አይደለም ይላሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ታሪኮች አንብብ። የሐዋ. 2፡45፤ 5፡19፤ 9፡1-6፤ 10፡1-8፤ 16፡26። መንፈስ ቅዱስ ዛሬም ተመሳሳይ ነገር እንደሚፈጽም መጠበቅ እንዳለብን የሚያስተምረን፥ ከእነዚህ ጥቅሶች የትኞቹ ይመስሉሃል? መንፈስ ቅዱስ ያለፈውን ታሪክ ብቻ የገለጸው በየትኞቹ ጥቅሶች ይመስልሃል?

እውነት ያለችው በሁለቱ አጽናፍ መካከል ይመስላል። የዚህ ጥናት መምሪያ ጸሐፊ፥ የሐዋርያት ሥራ የተፈጸሙ ድርጊቶችን ገላጭ መጽሐፍ አድርጎ ነው የሚመለከተው። በመሆኑም፥ መንፈስ ቅዱስ መጽሐፉ ውስጥ የተፈጸሙትን ድርጊቶች በሙሉ መቅዳት እንዳለብን አያስተምርም። እንደ ጳውሎስ እየተጓዝን ሳለ ኢየሱስን በራእይ ልናይ የምድር መንቀጥቀጥ ተከስቶ በመልአኩ አማካይነት የእስር ቤቱ በር ሲከፈት ልናይ ወይም ቁሳዊ ሀብቶቻችንን ሁሉ መስጠት አያስፈልገንም። እነዚህ ነገሮች እግዚአብሔር በዚያን ጊዜ በተለየ መንገዱ መሥራቱን ያመለክታሉ። በሌላ በኩል፥ መንፈስ ቅዱስ እነዚህን ታሪኮች ተጠቅም ነገሮችን እያብራራልን ነው። መንፈስ ቅዱስ ያን ጊዜ ሰዎችን ስለ ኃጢአታቸው በመውቀስና በመፈወስ በኃይል እንደ ሠራ ሁሉ፥ ዛሬም ይህንኑ ያደርጋል። በተለይ ወንጌል ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አንድ አካባቢ በሚገባበት ጊዜ ምንም እንኳ የጥንት ክርስቲያኖች ያላቸውን ሁሉ ሸጠው ድሆችን እንደ ረዱ ሁሉ እኛም ልክ እንደዚህ ማድረግ ባይኖርብንም፥ እንደ ቀድሞዎቹ ሁሉ እኛም ድሆችን በሚያስፈልጋቸው የመርዳትና የመደገፍ መንፈስ ሊኖረን ይገባል። በስደት ጊዜም እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ በተለየ መንገድ ሊያድነን ይችላል። ስለሆነም፥ ቀደም ሲል የተፈጸሙት ታሪኮች ዛሬ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚሠራ ትምህርቶችን ይሰጡናል። በ1ኛ ቆሮ. 10፡6 እና 11 ላይ ጳውሎስ የብሉይ ኪዳን ታሪኮች እንደ ምሳሌ የተሰጡን መሆናቸውን ተናግሯል። ይህን ሲል ጳውሎስ ለ40 ዓመታት በምድረ በጻ መቅበዝበዝ እንዳለብን ማመልከቱ አይደለም። ነገር ግን በእነዚያ ታሪኮች ውስጥ ከታዩት መልካምና ክፉ ምሳሌዎች እግዚአብሔር ዛሬ እንዴት እንደሚሠራ እንረዳለን፡፡ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የተፈጸሙትን ድርጊቶች እየገለጸ ሳለ እኛም በዚያው ዐይነት መኖር እንዳለብን የተናገረበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ፥ ሉቃስ እንደ ገለጻው ጴጥሮስ ክርስቶስ ብቸኛ የደኅንነት መንገድ መሆኑን ለአይሁዶች እንደ ተናገረ ሁሉ (የሐዋ. 4፡12) ዛሬም ክርስቶስ ብቸኛ የደኅንነት መንገድ ነው።

የሐዋርያት ሥራን ለመተርጎም መገንዘብ ያለብን ሌላም ነገር አለ። ደርግ ወድቆ የኢሕአዲግ መንግሥት ሥልጣን በያዘበት ጊዜ፥ የሕገ መንግሥት ለውጥና የሽግግር ጊዜ እንዳስፈለገ ሁሉ፥ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሽግግርን ጊዜ ያመላክታል። አሮጌው የብሉይ ኪዳን ዘመን በአዲሱ ኪዳን ዘመን በመተካት ላይ ነበር። ስለሆነም፥ በዚህ ጊዜ አንዳንድ ለውጦችን መጠበቅ አለብን። ሐዋርያት በቤተ መቅደስና ምኩራቦች ውስጥ በማምለክ ላይ ነበሩ። በኋላ ግን ቤተ ክርስቲያን አሕዛብን በመጨመር እየተስፋፋች ስትሄድ ይህ ሁኔታ ተቀይሯል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ከሕይወታችን ጋር ልናዛምዳቸው የሚገቡን አያሌ እውነቶች አሉ። ነገር ግን ሉቃስ የተፈጸመውን ታሪክ መግለጽ ብቻ ሳይሆን፥ እኛም ይህንኑ ማድረግ እንዳለብን እየነገረን መሆኑን ለማረጋገጥ በተለያዩ መልእክቶች ውስጥ የቀረበውን ትምህርት መመልከት አለብን። መልእክቶች በባሕርያቸው ክርስቲያኖች ምን ማመንና እንዴት መኖር እንዳለባቸው ያብራራሉ። በዚህም በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የምናነበውን አሳብ ተረድተን ተግባራዊ እንድናደርግ ይረዱናል።

  1. የሐዋርያት ሥራ በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ላይ ያተኩራል። መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ከ50 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። ይህም በየትኞቹም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ከምናገኘው የበለጠ ነው። የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ በጥንቃቄ በምናጠናበት ጊዜ፥ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ኃይል፥ የ«ኢየሱስ ብቻ» ተከታዮች እንደሚሉት የእግዚአብሔር አብ ወይም ወልድ ሌላ ስም እንዳልሆነ እንረዳለን። መንፈስ ቅዱስ ፍጹም አምላክ ሲሆን፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር አብ ወይም ከክርስቶስ ተለይቶ የራሱ አካልና ህልውና አለው።
  2. እንደ መጀመሪያው መጽሐፍ ሁሉ ሉቃስ በጸሎት ላይ ያተኩራል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እያንዳንዱ መጽሐፍ ማለት ይቻላል እግዚአብሔር ጸሎትን እንዴት እንደ ተጠቀመ ይገልጻል። ሉቃስ ስለ ጸሎት ለክርስቲያኖች ለማስተማር ከፈለጋቸው ነገሮች አንዱ፥ ለሕይወታችንና ለእግዚአብሔር ለምናከናውነው ተግባር ሁሉ መሠረት ነው።
  3. ሉቃስ ስለ ክርስቶስ መመስከር አስፈላጊ መሆኑንም አሳይቷል። ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር ለምናደርገው ኅብረት መሠረት እንደሆነ ሁሉ፥ ምስክርነት ለሌሎች እምነታችንን የምናሳውቅበት መንገድ መሆን አለበት። ምስክርነት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ተግባር ብቻ ሳይሆን፥ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ተግባር ነው። ስደት ቢያስከትልም በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ መመስከር አለባቸው። ሉቃስ እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ፍላጎቶችና ማኅበረሰብ ላይ ብቻ እንደምታተኩር ገልጾአል። እግዚአብሔር ወደ ሌሎች አካባቢዎች ወጥተው ይመሰክሩ ዘንድ በጥንት ክርስቲያኖች ላይ ስደት እንዲደርስ እንዴት እንዳደረገ ገልጾልናል። ስደቱ በሰማርያና አንጾኪያ እንዲመሰክሩ አስችሏቸዋል (የሐዋ. 8፡1-6)።
  4. የሐዋርያት ሥራ የተአምራት መጽሐፍ ነው። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ የበለጠ ተአምራት እንደሚያደርጉ ቀድሞ ገልጾ ነበር ( ዮሐ 14፡12)። በእርግጥም ሐዋርያቱ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት፥ በተለይም ጴጥሮስና ጳውሎስ ብዙ አስደናቂ ተአምራትን አድርገዋል። ተአምራቱ የሚመሰክሩት ወንጌል ከእግዚአብሔር የመጣ መሆኑን ነው። ምንም እንኳ በዚያን ጊዜ ተአምራት በመፈጸም ላይ የነበሩ ቢሆንም፥ ፈውስን ወይም ተአምራትን እንደ ዋንኛ አገልግሎቱ የተመለከተ ሐዋርያ አልነበረም። ዛሬ ከሚታየው ሁኔታ በተቃራኒ፥ «የፈውስ አገልጋዮች» ተብለው አይጠሩም ነበር። የፈውስ አገልግሎታቸው በቀዳሚነት በቤተ ክርስቲያን ላይ እንደ ተመሠረተ የሚያሳይ መረጃም አናገኝም። ይህ በይበልጥ ለማያምኑ ሰዎች የሚያበረክቱት አገልግሎት ነበር። ዛሬ በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚዘወተሩ ዓይነት የፈውስ አገልግሎቶች አልነበሩም። በዚህ ዘመን በየአብያተ ክርስቲያናቱ ለሚደረጉት ልምምዶች የሐዋርያት ሥራን ወይም አዲስ ኪዳንን እንደ ማስረጃ መጥቀስ አንችልም።
  5. መልእክቶችን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት የሐዋርያት ሥራን ማጥናት አለብን። የሐዋርያት ሥራ፥ ወንጌል ወደ ተለያዩ ስፍራዎች እንዴት እንደ ደረሰና የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ያጋጠሟትን ችግሮች ያብራራል።
  6. ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ አንድ አራተኛው ወይም ሃያ አምስት በመቶ የሚሆነው በጳውሎስ መታሰር፥ መመርመርና መከላከያ መስጠት ላይ ያተኩራል (የሐዋ. 22-28)። ምሑራን ሉቃስ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይፈጸሙ የነበሩትን አያሌ ነገሮች ማብራራት ሲችል፥ ለምን ይህን ያህል በጳውሎስ ሕይወት ላይ እንዳተኮረ ግራ ይጋባሉ። ለዚህ አንደኛው ምክንያት ሉቃስ ክርስትና ሕጋዊ ሃይማኖት መሆን አለበት ከሚል አሳብ ያመነጨው ሊሆን ይችላል። አብዛኛው ሃይማኖት ብዙውን ጊዜ የፖለቲካ ዐመፅ ምንጭ ተደርጎ ስለሚቆጠር ሮም በሃይማኖት ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ታደርግ ነበር። ሕጋዊነት የነበራቸው ሃይማኖቶች ጥቂቶች ነበሩ። ሉቃስ ከክርስትና ተከታዮች ጋር ለመገናኘት ዕድል ያገኙ የሮም ባለሥልጣናት ሁሉ እምነቱ እንዲቀጥል መፍቀዳቸውን ያሳያል። ሌሎች ምሑራን ሉቃስና ጳውሎስ በሚመረመርበት ችሎት ፊት ጳውሎስም ሆነ ክርስትና ከዐመፅ የነጹ መሆናቸውን የሚያሳይ ሰነድ እያዘጋጀ ነበረ ይላሉ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

2 thoughts on “የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ልዩ ገጽታዎች”

    1. ብርሃን፣

      በመልእክቶቹ እየተጠቀምክ መሆኑን በማወቄ ደስታዬ እጥፍ ድርብ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ጊዜ ወስደህ ደስታህን ልታጋራን ስለጽፍክልን ጌታ እግዚአብሔር ይባርክህ፡፡ በጸሎትህ አገልግሎቱን እንድትደግፍ እማጸንሃለሁ፡፡

      አዳነው ዲሮ
      የወንጌል በድረ ገጽ አገልግሎት አዘጋጅ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading