ጴጥሮስ የገጠመው ተቃውሞ እና የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን (የሐዋ. 11፡1-30)

  1. የኢየሩሳሌም አይሁዶች ጴጥሮስ ከአሕዛብ ጋር ሲተባበር አይተው ተቃወሙት (የሐዋ. 11፡1-18)

ጴጥሮስ፥ እግዚአብሔር አድልዎን እንደማይፈቅድ ያቀረበለትን ፈተና አልፎአል። ሌሎች የአይሁድ ክርስቲያኖችስ? በሐዋርያት ሥራ 6 ላይ እንደተገለጸው የአይሁድ ክርስቲያኖች፥ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ በአሕዛብ ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ማስወገድ ነበረባቸው። ይህ ግን ለረጅም ጊዜ በመጥፎ ገጽታው ቀጥሎ ነበር። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ለእግዚአብሔር አልታዘዝም፥ ባሕሉንም አልተውም ብትል ኖሮ፥ አሕዛብ ወደ ኅብረትዋ መቀላቀል ከፈለጉ፥ በቅድሚያ አይሁድ ሁኑ በማለት ባስገደደቻቸው ነበር። አለበለዚያም ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተከፍላ አንዱ ወገን የአይሁድ፥ ሌላው ወገን የአሕዛብ ቤተ ክርስቲያን እየተባለ ይጠራ ነበር። አንድነት ካልኖራቸው ደግሞ ምስክርነታቸው እምብዛም ዓለምን የመለወጥ ኃይል ባልኖረውም ነበር።

የጥላቻን አመለካከት ማሸነፍ ቀላል አይደለም። ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም ወደነበረችው እናት ቤተ ክርስቲያኑ ሲመለስ፥ ከአሕዛብ ጋር እንዳይተባበሩ የሚያስጠነቅቀውን የአይሁድ ደንብ በመጣሱ ተከስሷል። ጴጥሮስ ስላየው ራእይና እግዚአብሔር ለአይሁድ እንዳደረገው ሁሉ ለአሕዛብም መንፈስ ቅዱስን እንደ ሰጠ፥ በዝርዝር ተናግሯል። አሕዛብ ወደ ይሁዲነት ሳይመጡ፥ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ሁሉም እኩል ናቸው፥ የሚለው አሳብ እጅግ ወሳኝ ነበር። በመሆኑም ሉቃስ፥ ጴጥሮስ ያየውን ራእይና መንፈስ ቅዱስ በአሕዛብ ላይ እንዴት እንደ ወረደ ያስተዋለውን ነገር በድጋሚ ጽፎታል። ጴጥሮስ እንዳለው «እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመንነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከላከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ?» ብሏል (ሐዋ.11፡17)፡፡ የሚያሳዝነው ዛሬም ብዙ ክርስቲያኖች ሌሎች ሰዎችን በእኩል ደረጃ ባለመቀበል እግዚአብሔርን ይቃወማሉ። በእኛና በሌሎች ሰዎች መካከል (በሸክላ ሠሪዎች፥ በቀጥቃጮች፥ ወዘተ) ወይም በጎሣዎች መካከል መከፋፈል እንዲከሰት ስናደርግ በድርጊታችን ለእግዚአብሔር እንዲህ እያልነው ነው። «አንተ ነገሮች እንዲሆኑ ከምትፈልግበት መንገድ ጋር አንስማማም» እኛ ከእነርሱ እንሻላለን ብለን ስለምናስብ፥ ባሕላችንን፥ ቋንቋችንን፥ የአምልኮ ስልታችንን፥ ዝማሬአችንን ካልተከተላችሁ እንቀበላችሁም እንላቸዋለን። እንዲህ ስንል ደግሞ ሁሉም ሰው እኛን ይምሰል ማለታችን ነው። ለዓለም ደግሞ፥ ወንጌሉ የጥላቻ አመለካከትን ሊያስወግድ አይችልም። በዓለም ውስጥ ያለው መከፋፈል እኛም ዘንድ አለ። ባሕላችንን መታዘዙ ክርስቶስን ከመታዘዝ የበለጠ ነው። አንድነት ለእኛ ብዙም አስፈላጊ አይደለም እያልን ነው። ሰዎች ወደ ክርስቶስ ከማይሳቡባቸው ምክንያቶች አንዱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ፍቅርና አንድነት አለመታየቱ ነው። እኛ ጎሣዊ ጥላቻን ለማስወገድ ካልቻልን፥ የአገራችንና የዓለም ጎሣዎች ተስማምተው ስለሚኖሩበት ሁኔታ እንዴት ልናስብ እንችላለን?

  1. የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን – የመጀመሪያይቱ የአይሁድና የአሕዛብ ጥምረት የታየባት ቤተ ክርስቲያን ሆነች (የሐዋ. 11፡19-30)

ምንም እንኳ በፍልስጥኤም ይኖር የነበረው ቆርኔሌዎስ በጌታ በማመን የመጀመሪያው ሰው ቢሆንም፥ ይህ ግን በቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽዕኖ አላደረገም ነበር። በፍልስጥኤም ቁጥራቸው ጥቂት የሆኑ የአሕዛብ አማኞች ነበሩ። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር አሕዛብን ወደ ቤተ ክርስቲያን ያመጣበት እውነት በአይሁድ ክርስቲያኖች ዘንድ ተፈትኖ ተቀባይነት ያገኘ ነገር አልነበረም። ነገር ግን ቀስ በቀስ ቤተ ክርስቲያን መስፋፋት ጀመረች። በኋላም በአሕዛብ አገሮች በቆጵሮስና በቀሬና ባደጉ አይሁዳውያን አገልግሎት ወደ ሰሜን እስከ ፊንቄ ሊባኖስ)፥ ከፊንቄ እስከ ቆጵሮስ፥ በመቀጠልም እስከ እንጾኪያ ከተማ ድረስ ተስፋፋች። አንጾኪያ በሮም ግዛት ውስጥ ከሚገኙት ከተሞች ሁሉ በትልቅነቷ የሦስተኛ ደረጃ ነበራት። ሁለቱ ታላላቅ ከተሞች ሮምና እስክንድርያ ነበሩ።) አንጾኪያ ለብዙ ዘመን የሶሉሲድ ግሪክ ግዛት መዲና ነበረች። በሮማውያን እጅ በነበረችበት ጊዜ፥ በመካከለኛው ምሥራቅ ዋነኛ የፖለቲካ ኃይል ማዕከል ሆና ቆይታለች። ቤተ ክርስቲያን ወደ አንጾኪያ መስፋፋቷ ጠቃሚ ነበር። በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ አሕዛብን በወንጌል ለመድረስ ያገለገለችው የኢየሩሳሌሟ ሳትሆን፥ የአንጾኪያዋ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በራሷ አሳብና በአይሁድ ባሕል ላይ ስላተኮረች፥ ለእግዚአብሔር ጠቃሚ መሣሪያ ለመሆን አልቻለችም። ነገር ግን የአሕዛብና የአይሁዶች ጥምር የሆነችው የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን፥ እግዚአብሔር ለሰዎች ሁሉ ያለውን ዕቅድ በተሻለ ሁኔታ ስለ ተገነዘበች፥ እግዚአብሔር አሕዛብን እንድትማርክ ተጠቅሞባታል።

የአንጾኪያ አይሁድ ክርስቲያኖች ተወልደው ያደጉት በአሕዛብ አገሮች በመሆኑ፥ በፍልስጥኤም ተወልደው ካደጉት አይሁዶች ይልቅ ከአሕዛብ ጋር በቀላሉ ለመግባባት ይችሉ ነበር። ብዙ አሕዛብ አመኑ። ለመጀመሪያ ጊዜ ከአባላት መካከል ብዙ የአሕዛብ አማኞችን ይዛ የተገኘችው ቤተ ክርስቲያን አንጾኪያ ናት። በኢየሩሳሌም የምትገኘው እናት ቤተ ክርስቲያን ከኢየሩሳሌም 500 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው አንጾኪያ፥ እግዚአብሔር እየሠራ ያለውን ትልቅ ሥራ ስትሰማ፥ በዚያ የሚደረገው ነገር እውነተኛና ከወንጌሉም ጋር የሚስማማ መሆኑን ለማረጋገጥ በርናባስን ላከችው። በአንጾኪያ የሚሠራው ሥራ በርናባስን እጅግ ደስ ስላሰኘው፥ ወደ ኢየሩሳሌም መመለሱን ትቶ በዚያ ለማገልገል ወሰነ። በርናባስ በአሕዛብ መካከል ተወልዶ ያደገ አይሁዳዊ በመሆኑ፥ እግዚአብሔር እያከናወነ ያለውን ልዩ ተግባር በአንክሮ ሊመለከት ችሏል። ከእርሱ በተጨማሪ በአገልግሎቱ እንዲያግዘው በአሕዛብ መካከል ተወልዶ ያደገ አይሁዳዊ መፈለግ ጀመረ። ስለዚህ 150 ኪሎ ሜትር ተጉዞ ወደ ተርሴስ በመሄድ ጳውሎስ አብሮት እንዲያገለግል አግባባው። ሉቃስ በአንጾኪያ ሁለት ዐበይት ነገሮች እንደተደረጉ ገልጾአል። አንደኛው፥ «ክርስቲያኖች» የሚለው ስም ለክርስቶስ ተከታዮች መስጠቱን ሲሆን፥ ይህ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ለክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ በማገልገል ላይ ይገኛል። ይህ ሌሎች ክርስቲያኖችን ለመስደብ (በደርግ ዘመን «ጴንጤ» ይባል እንደነበረው) ያወጡት ስም ይሁን ወይም ክርስቲያኖች ራሳቸው ያወጡት ስያሜ የሚታወቅ ነገር የለም። ነገር ግን የቃሉ ትርጉም «የክርስቶስ የሆነ» ስለሚል፥ ክርስቶስን ለሚከተሉ ሰዎች ተስማሚ መጠሪያ ሆኖ ቆይቷል።

ሁለተኛው የመጀመሪያው «የእርዳታ» ፕሮግራም በቤተ ክርስቲያን ተጀመረ። በኢየሩሳሌም ረሃብ መነሣቱን ቤተ ክርስቲያኒቱ ስትሰማ ብዙ ሀብት የነበራቸው የአንጾኪያ ክርስቲያን አባላት ለመርዳት ወሰኑ። ገንዘብ አሰባስበው በመሪዎቻቸው ማለትም በበርናባስና በጳውሎስ በኩል ወደ ኢየሩሳሌም ላኩ። ቀደም ሲል ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁት እርስ በርሳቸው በመዋደዳቸው እንደሆነ ክርስቶስ እንደ አስተማረ ተመልክተናል። ምንም እንኳ የአንጾኪያ ክርስቲያኖች ከእነርሱ 500 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው የነበሩትን የኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች በአካል ባያውቋቸውም፥ ለእግዚአብሔር ቤተሰብ ከነበራቸው ፍቅር የተነሣ የማያውቋቸውን ወገኖች ለመርዳት ፈቀዱ። ከራሷ ምእመናንና ግዛት አልፋ በሩቅ ስፍራ ያሉ ወንድሞችንና እኅቶችን ለመርዳት የተነሣች ቤተ ክርስቲያን፥ መንፈሳዊ መሆኗን አስመሰከረች።

የውይይት ጥያቄ:- ቤተ ክርስቲያንህ ለማታውቃቸው ሌሎች ክርስቲያኖች ፍቅሯን የምትገልጸው እንዴት ነው? ቤተ ክርስቲያንህ ይህንን የምታደርግ ከሆነ ምክንያቱ ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

3 thoughts on “ጴጥሮስ የገጠመው ተቃውሞ እና የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን (የሐዋ. 11፡1-30)”

  1. ahun yalechiw betekrstan wana yekrstna mahikel yehonewn fkrn yetwech
    ymeslegn fkr taft ersbers mebelalat betkrstan west gebtual fkr dgmo
    eg/br nw fkr kalele eg/ber yelem eg/br fkr nwna geta yrdan::

  2. እግዚአብሔር አገልግሎታቸHUን ይባርክ
    AMEN!!
    AM VERY HAPPY!

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading