አንድ ጊዜ አንድ ታላቅ ወንጌላዊ፥ «ዓለም እግዚአብሔር ሙሉ ለሙሉ ራሱን ለእርሱ በሰጠ አንድ ሰው አማካኝነት የሚሠራውን ተአምር ገና ታያለች» ብለው ነበር። እግዚአብሔር በእያንዳንዳችን ተጠቅሞ የምንኖርባትን ዓለም ለመለወጥ ይፈልጋል። የሁላችንም ችግር ሙሉ ለሙሉ ራሳችንን ለእርሱ አለመስጠት ነው። አንድ ሰው ራሱን ለእርሱ ከሰጠ እግዚአብሔር እንዴት በከፍተኛ ደረጃ ሊጠቀምበት እንደሚችል ከጳውሎስ ሕይወት ልንማር እንችላለን። ጳውሎስ በሕይወቱና በአገልግሎቱ እግዚአብሔርን ለማስደሰት ከልቡ ስለፈለገ፥ «እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ» (1ኛ ቆሮ. 11፡1፤ ፊልጵ. 3፡17) እስከ ማለት ደርሷል። ብዙዎቻችን ይህን ልንል አንችልም። ምክንያቱም በብዙ የሕይወት ክፍሎቻችን ራሳችንን ሙሉ ለሙሉ ለእርሱ አሳልፈን እንዳልሰጠንና እርሱ የሚፈልገውን ዓይነት ሕይወት እንደማንኖር እናውቃለን። ነገር ግን ብናስተውልም ባናስተውልም ሰዎች እየተመለከቱን ናቸው። በተለይም መሪዎች ከሆንን ብዙዎች የእኛን ምሳሌነት ይከተላሉ። ለብዙ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ብቻ እግዚአብሔርን የሚያስከብር ሕይወት መምራት አስቸጋሪ ነው። ብዙ ሰዎች እግዚአብሔርን ስለመከተል የሚማሩት ሌሎችን፥ በተለይም የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን በመመልከት ነው። ዛሬ እጅግ አስፈላጊው ነገር ለምእመኖቻቸው እንዴት ለጌታቸው ለኢየሱስ የተሰጠ ብርሃን ያለው ሕይወት ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ብዙ መሪዎችን ማግኘት ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች ከእግዚአብሔር ቃል በላይ መሪዎቻቸውን ሲከተሉ የተመለከትህበትን ሁኔታ ለሌሎች አካፍል። ለ) መሪዎች ከርስቶስን ስለ መከተል መልካም ምሳሌነትን ያሳዩበትን ሁኔታ ግለጽ። ይህ በሌሎች ሰዎች ሕይወት ውስጥ ያስከተለው ተጽዕኖ ምን ነበር? ሐ) መሪዎች ክርስቶስን ስለ መከተል መጥፎ ምሳሌነት ያሳዩበትን ሁኔታ ግለጽ። ይህ በሌሎች ሰዎች ሕይወት ውስጥ ያስከተለው አሉታዊ ለውጥ ምን ነበር? መ) ምሳሌነትህን ለመከተል የሚፈልጉትን ሰዎች ስም ዘርዝር። እነዚህን ሰዎች ወደ ክርስቶስ ይበልጥ እያቀረብህ ወይም እያራቅህ መሆንህን መንፈስ ቅዱስ እንዲያሳይህ በጸሎት ጠይቅ። ሙሉ ለሙሉ ለክርስቶስ ተሰጥቶ ለእርሱ የመኖር መልካም ምሳሌ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር ምንን እንድትለውጥ የሚፈልግ ይመስልሃል?
የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ጳውሎስ የሚናገር አሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንብብ። ስለ ሕይወቱና ስላስተማራቸው እውነቶች የምታውቀውን ጻፍ። በተለይም ካስተማራቸው እውነቶች መካከል ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን እጅግ ጠቃሚዎች ናቸው በምትላቸው ላይ ትኩረት አድርግ።
የጳውሎስ ሕይወት
በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ፥ የጳውሎስን ያህል ዓለምን የለወጡ ሰዎች ጥቂቶች ናቸው። በመጀመሪያው ምእተ ዓመት ወንጌልን ለሮም ግዛቶች ለማዳረስ የእግዚአብሔር መሣሪያ ሆኖ ከማገልገሉም በላይ፥ መልእክቶቹ ዛሬም የሰዎችን ሕይወት ይለውጣሉ። ለዚህም ነው ሉቃስ ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ግማሹን ያህል የጳውሎስን አገልግሎት ለማብራራት ተግባር ያዋለው።
ጳውሎስ የተወለደበትን ጊዜ በትክክል አናውቅም። አብዛኞቹ ምሁራን ግን ከክርስቶስ አሥር ዓመት ያህል ዘግይቶ እንደተወለደ ያስባሉ። በ5 ዓም. አካባቢ መሆኑ ነው። የጳውሎስ ወላጆች ከቢንያም ነገድ የተወለዱ አይሁዶች ነበሩ። ሮማዊ ስሙ ጳውሎስ ሲሆን፥ አይሁዳዊ ስሙ ሳውል ነበር። አይሁዶች ሳውል ብለው ሲጠሩት፥ ከአሕዛብ ጋር በሚሠራበት ጊዜ ጳውሎስ እየተባለ ይጠራ ነበር። ሌሎች ሐዋርያት ሁሉ በፓለስታይን ክልል የተወለዱ ሲሆን፥ ጳውሎስ ግን በትንሹ እስያ ውስጥ በምትገኘው ጠርሴስ ነበር የተወለደው። ጠርሴስ በሮም ግዛት ውስጥ ከሚገኙ ታላላቅ ከተሞች አንዷ ስትሆን፥ ወደ 500,000 ሰዎች ይኖሩባት ነበር። ጠርሴስ የሮም ግዛት የሆነችው ሶርያ ኪልቂያ መዲና ስትሆን፥ በዩኒቨርስቲዎቿ ትታወቅ ነበር። ጳውሎስ «የከተማዪቱ ዜጋ» ነበር (የሐዋ. 21፡39)። ይህም ለታደሉ ቤተሰቦች ብቻ የሚሰጥ በረከት ነበር። ከዚያም በላይ፥ ጳውሎስ የሮም ዜግነት ነበረው (የሐዋ. 22፡28)። በሆነ ምክንያት የሮም መንግሥት ለጳውሎስ ወላጆች ወይም አያት ቅድመ-አያቶች የሮም ዜግነትን ዕድል ሰጥቷቸው ነበር። ይህም ዜግነት ከወላጆቹ በመወለዱ ምክንያት ወደ ጳውሎስ ተላለፈ። ጳውሎስ ከታደሉት ሰዎች መካከል አንዱ እንደ መሆኑ መጠን፥ የግሪክን ፍልስፍና ሳይማር እንዳልቀረ ለማመን የሚያስደፍር ምክንያት አለ። ( በአቴንስ ለፈላስፎች ባስተማረበት ወቅት፥ የታወቁትን ፈላስፎች ትምህርት እየጠቀሰ አሳቡን አብራርቷል (ሐዋ. 17፡28)።
ጳውሎስ የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው ከአሕዛብ ጋር ቢሆንም፥ ገና ወጣት ሳለ ወደ ኢየሩሳሌም ተልኮ ነበር። ሀብታምና ወግ አጥባቂ አይሁዶች የነበሩት ወላጆቹ ልጃቸው የጥንት አይሁዶችን ትውፊት ተምሮ የሃይማኖት መሪ እንዲሆን ፈለጉ። ስለዚህም ከዝነኛ የሃይማኖት መምህራን ትምህርት እንዲቀስም ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱት። ለዚህም ነው ጳውሎስ «ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ» የሚለው (ፊልጵ. 3፡5)። ይህም የአሕዛብን አኗኗር ለመቀላቀል ያልፈለገ ንጹሕ አይሁዳዊ መሆኑን የገለጸበት ነው። በኢየሩሳሌም፥ ጳውሎስ ከታዋቂው የሃይማኖት መምህር ከገማልያል እግር ሥር ቁጭ ብሎ ተምሯል። የአይሁድ ታሪክ እንደሚነግረን፥ ገማልያል በመጀመሪያው ምእተ ዓመት እጅግ ከተከበሩ የሃይማኖት መምህራን አንዱ ነበር። በገማልያል ሥር፥ ጳውሎስ የፈሪሳዊነትን ትምህርት ተከታተለ። ፈሪሳውያን የብሉይ ኪዳን ሕግጋትንና በዘመናት ሁሉ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ያስተላለፉላቸውን ትውፊቶች በጥንቃቄ ይከተሉ ነበር።
ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ያለውን ጥልቅ ፍቅር፥ በቅንዓት ሕግጋቱንና ትውፊቱን በመጠበቅ ደስ ሊያሰኘው መሻቱን በፍጥነት አስመሰከረ። የአይሁዶች ሸንጎ (sanhedrin) አባል እስከ መሆንም ደረሰ።
ሁለቱም በተመሳሳይ ጊዜ በኢየሩሳሌም ይኖሩ እንደነበር በማመልከት፥ ምሁራን ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር ስለመገናኘቱ የተለያየ አቋም ይይዛሉ። ጳውሎስ በመልእክቶቹ ውስጥ ከክርስቶስ ጋር ስለመገናኘቱ ስላልጠቀሰ ተገናኝተው የሚያውቁ አይመስልም። ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በኋላ ጥቂት ዓመታት ቆይቶ ጳውሎስ የክርስቶስ ተከታዮች ቀንደኛ ጠላት ሆነ። ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ መጀመሪያ የተጠቀሰው እስጢፋኖስ በተወገረበት ወቅት ነበር። ምናልባትም ሸንጎው እስጢፋኖስን ወስዶ እንዲያስወግር ኃላፊነት ሰጥቶት ይሆናል። ጳውሎስ በክርስቲያኖች ላይ የመረረ ጥላቻ ስለነበረው በተቻለ አቅም ብዙ ክርስቲያኖች እንዲታሰሩ ጥረት አደረገ። በኋላ እንደመሰከረው፥ ብዙ ክርስቲያኖችን እያሰረ ወኅኒ ቤቶች ውስጥ ይጥልና ሲገደሉም ደስ ይሰኝ ነበር (የሐዋ. 22፡4)። ይህም ለቀሪ ዘመኑ ጸጸት ሆኖበታል። ጳውሎስ ክርስቲያኖችን የማሳደድ ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረው፥ ክርስቲያኖችን ከደማስቆ አስሮ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት ከ200 ኪሎ ሜትሮች በላይ ይጓዝ ነበር።
እግዚአብሔር ግን ለጳውሎስ ሌላ ዕቅድ ነበረው። እግዚአብሔር የክርስቲያኖች አሳዳጅ የነበረው ሳውልን የአሕዛብ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ አድርጎ ሊለውጠው ፈለገ። ክርስቶስ ከሞተ ከሦስት ዓመታት ያህል ጊዜ በኋላ፥ ክርስቶስ በደማስቆ መንገድ ከጳውሎስ ጋር በመገናኘት ሕይወቱን ለወጠው፡፡ ከዚያ በኋላ ጳውሎስ በችሎታው፥ በውርሱ፥ በትምህርቱ ወይም ለሕጉ በመቅናቱ አልተመካም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጳውሎስ አስፈላጊው ነገር ክርስቶስና ሰው ከክርስቶስ ጋር ያለው ዝምድና ብቻ መሆኑን ተረዳ፡፡ ክርስቶስ ብቸኛ የድነት (የደኅንነት) መንገድ ሲሆን፥ ሰውን የእግዚአብሔር ልጅ የሚያደርገው በእርሱ ማመን ብቻ ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስለ እግዚአብሔር አስደናቂ ጸጋና እርሱ እንደ ሰው ስላለመሥራቱ ምን እንማራለን? ለ) እግዚአብሔር በሕይወትህ ጸጋውን ያሳየው እንዴት ነው?
ለቀጣይ አያሌ ዓመታት የጳውሎስ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበረ በዝርዝር ማወቁ አስቸጋሪ ነው። ጳውሎስ በደማስቆ ከተማ ለአጭር ጊዜ ካገለገለ በኋላ ወደ ዓረቢያ የሄደ ይመስላል። በዚያም ስለ ክርስቶስ ማንነትና የእግዚአብሔርን ዕቅድ ስለፈጸመበት ሁኔታ እያጠና፥ እያሰላሰለና ግንዛቤውን እያጤነ ለሦስት ዓመታት ቆየ። ከዚያም አገልግሎቱን ለመጀመር ወደ ደማስቆ ተመለሰ። ጳውሎስ በብሉይ ኪዳን የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ዕቅድ በትክክል ከተገነዘበ በኋላ ከአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ጋር በአጥጋቢ ሁኔታ ሊከራከር ቻለ። አይሁዶች ሊገድሉት በመሞከራቸው ደማስቆን ለቅቆ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። ጳውሎስ ለክርስቲያኖች በነበረው ጥላቻ ይታወቅ ስለነበር አማኞች ሊጠጉት ፈሩ። በርናባስ ግን ጳውሎስ የተናገረውን ታሪክ አምኖ ከአያሌ ሐዋርያት ጋር አገናኘው። በጳውሎስ ላይ የሚሰነዘረው ስደት እየጠነከረ ሲመጣ ሐዋርያት ወደ ትውልድ አገሩ ጠርሴስ ላኩት። ለቀጣይ 11 ዓመታት ጳውሎስ ያካሄደው አገልግሎት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም።
የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት እያደገች ስትመጣ፥ በርናባስ ጳውሎስን ከጠርሴስ አስመጥቶ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን እንዲያገለግል አደረገ። ከሁለት ዓመታት በላይ አብረው ከሠሩ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርናባስና ጳውሎስ የመጀመሪያውን የሚሲዮናዊነት ጉዞ እንዲያካሂዱ አደረገ። ለቀጣዮቹ ሃያ ዓመታት ጳውሎስ ለአሕዛብ ወንጌልን በማድረሱ በኩል ዋነኛ ተዋናይ ሆነ። ብዙ ጊዜ ሰዎች አገልግሎቱን ለማደናቀፍ ጥረዋል። ጳውሎስ አስከፊ ስደትና ተቃውሞ ቢገጥመውም፥ አገልግሎቱን አልተወም። በመጨረሻም፥ በንጉሥ ኔሮ ዘመን ታስሮ ከቆየ በኋላ በ67 ዓ.ም. አካባቢ ተገደለ።
የጳውሎስ ትምህርቶች
ነገረ መለኮት የመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ገለጻ ነው። ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ፥ ድነት፥ የመጨረሻው ዘመን፥ ቤተ ክርስቲያን፥ መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ ወዘተ.. በመልእክቶቹ ውስጥ ገልጾአል። የጳውሎስ መልእክቶች ሰፊ ረእሰ ጉዳዮችን ስለሚሸፍኑ፥ ጠቅለል አድርጎ ለማቅረብ አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን በአብዛኞቹ መልእክቶቹ ውስጥ የሚከተሉት ጭብጦች ተንጸባርቀዋል።
- የእግዚአብሔር ታላቅነት፡- ሰዎች ስለ እግዚአብሔር የራሳቸውን ግንዛቤ ያንጸባርቃሉ ይባላል። ስለሆነም፥ ሰዎች እግዚአብሔር ምሕረትንና ፍቅርን የማያሳይ ጨካኝ አምላክ ነው ብለው ካሰቡ፥ እነርሱም እንደዚያ ይሆናሉ። በመሆኑም፥ ለክርስቲያኖች ስለ እግዚአብሔር ትክክለኛ ግንዛቤ መጨበጡ በጣም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ እግዚአብሔር ታላቅና ግርማ ሞገስ ያለው አምላክ እንደሆነ ያምናል። ጳውሎስ እግዚአብሔር የሕይወት ፈጣሪና ምንጭ የሆነ ዘላለማዊ አምላክ መሆኑን ገልጿል። እግዚአብሔር ሙሉ ጥበብ፥ እውቀትና ኃይል ያለው አምላክ ሲሆን፥ የነገሮች ሁሉ ሉዓላዊ ገዥ ነው። እንደ ሰይጣን ዓይነት መንፈሳዊ ኃይል ወይም ምድራዊ ንጉሥ ከእርሱ ኃይልና ቁጥጥር በላይ አይደለም። እግዚአብሔር በየዕለቱ ስለሚፈጽሙት ተግባራቸውና ከእርሱ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ሰዎችን በኃላፊነት የሚጠይቅ አምላክ ነው። እርሱ ሰዎች ሁሉ ሊያመልኩትና ሊያወድሱት የሚገባው አምላክ ነው። እርሱ ሰዎችን ሁሉ ለማዳን የሚፈልግ የፍቅርና የምሕረት አምላክ ነው። ለዚህም ነው ክርስቶስ የሰዎች ሁሉ አዳኝ ሆኖ ወደ ዓለም እንዲመጣ ያደረገው። እግዚአብሔር በልጁ ከሚያምኑ ሰዎች ጋር የሚያደርገው ግንኙነት በፍቅርና በእንክብካቤ የተሞላ ነው። ለእርሱ የምንኖርበትን ኃይል እናገኝ ዘንድ መንፈስ ቅዱስን የሰጠን እግዚአብሔር ነው። ወደ ዘላለማዊ ቤታችን እስክንደርስም ድረስ መንፈሳዊ ልጆቹን ይጠብቀናል። እንዲሁም አኗኗራችንን፥ ከእርሱ ጋር የምናደርገውን ግንኙነትና የሰጠንን ስጦታዎችና ችሎታዎች በመጠቀም እርሱንና አካሉ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ማገልገል አለማገልገላችንን ይቆጣጠራል፤ ይጠይቀናል፤ ይሸልመናልም።
- ክርስቲያን ከሕግ ጋር ያለው ግንኙነት፡- ጳውሎስ ያደገው የብሉይ ኪዳንን ሕግና የሃይማኖት መሪዎች ትውፊቶችን እጅግ አስፈላጊ ናቸው በሚል አስተሳሰብ ነበር። መንፈሳዊነትና አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት ውጫዊ ደንቦችን በመጠበቅ እንደሚለካ ያምን ነበር። ጳውሎስ ክርስቲያን በሆነ ጊዜ ግን ይህ አመለካከቱ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። ይህ ለውጥ ደግሞ ከክርስቲያኖችም ጋር ሆነ ክርስቲያን ካልሆኑት አይሁዶች ጋር ወደ ግጭት አመራው። በአዲስ ኪዳን ዘመን የሕግ ሚና ምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ ጳውሎስ ስለ «ሕግ» የሚሰጠውን ትምህርት መረዳቱ አስቸጋሪ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ጳውሎስ ቃሉን በተለያዩ መንገዶች መጠቀሙ ነው። በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ «ሕግ» የሚለውን ቃል ከዘፍጥረት እስክ ሚልክያስ ያለውን የብሉይ ኪዳን ክፍል ለማመልከት ይጠቀምበታል (ሮሜ 3፡19)። ሁለተኛ፥ ሙሴ የጻፋቸውን አምስት መጻሕፍት (ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም) ያመለክታል (ሮሜ 3፡21)። ሦስተኛ፥ ጳውሎስ ፍጹም ያልተለወጡትን፥ ለሰዎች ሁሉ አስፈላጊ የሆኑትንና ከእግዚአብሔር የተሰጡትን ሥነ ምግባራዊ ትእዛዛት ለማመልከት ሕግን ይጠቅሳል (ሮሜ 4፡15)። አራተኛ፥ «ሕግ» የሚለውን ቃል በመጠቀም አሁን ክርስቲያኖች ለመጠበቅ የማይገደዷቸውን የብሉይ ኪዳን ሃይማኖታዊ ትእዛዛት ይገልጻል። አምስተኛ፥ አንድ ሰው በሚያከናውናቸው ተግባራትና እግዚአብሔርን ለማስደሰት በሚያደርጋቸው ጥረቶች ምክንያት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትንና ድነትን እንደሚያገኝ የሚያስተምረውን የእምነት ሥርዓት ለመግለጽ «ሕግ» የሚለውን ቃል ይጠቀማል (ሮሜ 10፡3፤ ገላ. 2፡21)። ይህ እግዚአብሔር ያቀረበውን የክርስቶስን መሥዋዕት በማመን፥ ድነት የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ተረድተን ከምንቀበልበት መንገድ የሚቃረን ነው። ስለ ብሉይ ኪዳን የተሳሳተ ግንዛቤ ያለው ይህ የእምነት ሥርዓት ብዙ ሰው ሠራሽ ሕግጋትን ያካተተ ነበር። ሰዎች እነዚህን ሕግጋት በመጠበቅ ከእግዚአብሔር ሞገስ እናገኛለን ብለው ያስቡ ነበር።
ጳውሎስ፥ ሰው በትክክል ከተረዳቸው የብሉይ ኪዳን ሕግጋት መልካም መሆናቸውን ገልጾአል። እግዚአብሔር ሰዎች ሕግጋቱን ሙሉ በሙሉ በመጠበቅ እንዲታበዩና ለዚሁ ተግባራቸው የእግዚአብሔርን ምሕረት እንደ ደመወዝ ይቀበላሉ የሚል አሳብ አልነበረውም። ጳውሎስ ብሉይ ኪዳን ማንም ሰው ሙሉ ለሙሉ ሕጉን ሊጠብቅና ሊድን እንደማይችል የሚያስተምር መሆኑን ያስረዳል። ሁሉም ኃጢአትን ስለሠራና አንድም ጻድቅ ስለሌለ ሰዎች ሁሉ ለቅጣት ተጋልጠዋል (ሮሜ 3፡10-11፥ 23)። እግዚአብሔር ሕግን ከሰጠባቸው ምክንያቶች አንዱ ሰዎች ኃጢአተኝነታቸውን ተረድተው የእግዚአብሔርን ምሕረትና ጸጋ ለመቀበል እጃቸውን እንዲዘረጉ ለማገዝ ነበር (ሮሜ 3፡21፤ ገላ. 3፡24)። ስለሆነም የትኛውም የትምክህትና «እግዚአብሔር ይህን ስላደረግሁ ይቀበለኛል» የሚል አመለካከት ስሕተት ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ዛሬ አንዳንድ ኦርቶዶክሶችና ወንጌላውያን ክርስቲያኖች የተወሰኑ ሕግጋትን በመጠበቅ እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙና ተቀባይነትን ሊያገኙ እንደሚችሉ የሚያስቡባቸውን መንገዶች ዘርዝር።
ድነት ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ስጦታ ቢሆንም የእግዚአብሔር ሕግጋት አያስፈልጉንም ማለት ግን አይደለም። ነገር ግን በክርስቶስ አምኖ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነና መንፈስ ቅዱስ በልቡ ውስጥ የፈሰሰለት ሰው፥ ከብሉይ ኪዳን ሕግጋት የሕጉን አገላለጽና መመሪያዎች በማጤን እርምጃውን ያስተካክላል።
- እምነት ያላቸው ሰዎች የተመረጡ የእግዚአብሔር ሕዝብ አካላት ናቸው። አይሁዶች የአብርሃም ልጆችና እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ለአብርሃም የሰጠው የተስፋ ቃል ተቀባዮች መሆናቸውን አጽንተው ያምኑ ነበር። ስለሆነም፥ በአይሁድነታቸው ይመኩ ነበር። አይሁዳዊ ሆኖ መወለድ የእግዚአብሔርን በረከት የሚያረጋግጥላቸው ይመስላቸው ነበር። በሌላ በኩል፥ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ሁሉ ከዚህ ልዩ የእግዚአብሔር ሞገስ ተለይተው የተረገሙ ናቸው የሚል እምነት ነበራቸው። ጳውሎስ፥ እግዚአብሔር በሥጋ አይሁዳውያን ለሆኑት አሁንም ልዩ ዕቅድ እንዳለው ቢገነዘብም (ሮሜ 9-11)፥ ልዩነት የሚያመጣው ነገር ሥጋዊ ውርስ ሳይሆን መንፈሳዊ እምነት እንደሆነ አመልክቷል። እንደ አብርሃም ዓይነቶቹ የእምነት ሰዎች እውነተኛ የእግዚአብሔር ሰዎችና የአብርሃም ልጆች ናቸው። በብሉይ ኪዳን እንደ አብርሃምና ሣራ፥ ይስሐቅ፥ ሳሙኤል፥ ዳዊት፥ ዖዝያን፥ ኢሳይያስ፥ ወዘተ… ባሉት ሰዎች አማካኝነት የሚተላለፈው የእምነት ሐረግ፥ በአዲስ ኪዳን በክርስቶስ በሚያምኑ ሰዎች ሁሉ ሕይወት ይቀጥላል።
- ክርስቶስ የእግዚአብሔርን የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎች ፈጻሚ መሢሕ ነው። ጳውሎስ ክርስቶስ ሞቶ በተነሣ ጊዜ በታሪክ አንድ ታላቅ ነገር እንደተከሰተ በጥብቅ አምኗል። ጳውሎስ የእግዚአብሔር «ምሥጢራዊ» ዕቅዶች ብሎ የሚጠራቸው፥ አሕዛብንና አይሁድን እንደ አንድ ሕዝብ የማካተቱ ተግባር በክርስቶስ ነበር የተገለጠው። ክርስቶስ ሰው ብቻ ሳይሆን ፍጹም አምላክም ነበር። አምላክ (ክርስቶስ)፥ በሰው አምሳል ወደ ምድር መጥቶ ለጠፉት ሰዎች ይቅርታን ለማስገኘት ሲል ቢሞትም እንኳን፥ አሁን በእግዚአብሔር ቀኝ በክብር ተቀምጦአል እንድ ቀን ሁሉም ሰው ክርስቶስን ለማምለክና ጌትነቱን ለመቀበል ይገደዳል (ፊልጵ. 2፡6-11)።
- የክርስቶስ መስቀል፥ ጳውሎስ ሰዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ሊታርቁ፥ የኃጢአት ይቅርታ ሊያገኙና የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት ሊሆኑ እንደሚገባ አስተምሯል። ሌሎች የሰው ልጅ ፍላጎቶች ከዚህ ዘላለማዊ ፍጻሜን ከሚወስነው ጉዳይ በኋላ የሚታሰቡ ናቸው። ለጳውሎስ ሁልጊዜም የድነት ምንጩ እግዚአብሔር እንጂ ሰው አይደለም። ጳውሎስ ትኩረት ያደረገው እግዚአብሔር እኛን ፈልጎ በማግኘቱ ላይ እንጂ እኛ እርሱን በማግኘታችን ላይ አይደለም። እግዚአብሔር ለችግራችን የሰጠው መፍትሔ «መስቀል» በሚለው ቃል ይጠቃለላል። ሙሉው የወንጌል መልእክት «የመስቀሉ ስብከት» በመባል ይገለጻል (1ኛ ቆሮ. 1፡18)። በሰብአዊ ግንዛቤ መስቀሉ የሽንፈት ስፍራ ቢመስልም፥ እግዚአብሔር ግን የድነት ስፍራ አድርጎታል። ምክንያቱም ክርስቶስ እዚያው በመስቀል ላይ በመሞት ኃጢአታችንን ተሸክሟል። በዚህም ምክንያት ቅዱስና ጻድቅ የሆነው እግዚአብሔር ይቅር ሊለን ችሏል።
ጳውሎስ፥ መስቀሉ እግዚአብሔር ለይቅርታ ፍላጎታችን የሰጠው መልስ ብቻ ሳይሆን፥ በሕይወታችን ኃጢአትን የምናሸንፍበት ቁልፍ እንደሆነም ገልጾአል። ሰይጣን በሰዎች ላይ የነበረውን ኃይል እግዚአብሔር በመስቀሉ አሸንፎታል (ቆላ. 1፡20፤ 2፡13-15)። በሕይወታችን ላይ የነበረው የኃጢአት ኃይል በመስቀሉ ላይ ስለተሰበረ አሁን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ በነጻነት ለመኖር እንችላለን (ገላ. 5፡24)። ለዚህም ነው ጳውሎስ ለእኔ ትልቁ ነገር መስቀሉ ብቻ ነው የሚለው (ገላ. 6፡14)።
- ቤተ ክርስቲያን፡- ብዙውን ጊዜ በስብከታችን ላይ ትኩረት የምንሰጠው በክርስቶስ በማመን ግለሰቦች በሚያገኙት በረከት ላይ ነው። ጳውሎs ግን የእግዚአብሔር ዕቅድ ግለሰቦችን ከመባረክ የሚያልፍ እንደሆነ ገልጾአል። እርሱ አጽንኦት የሰጠው «ቤተ ክርስቲያን» ወይም «የክርስቶስ አካል» ብሎ ለሚጠራቸው አዲስ የእግዚአብሔር ሕዝብ ነው። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ሕንፃ አልገለጸም። ይህም ከዛሬው ግንዛቤያችን የተለየ ነው። የጥንት ክርስቲያኖች የሚሰባሰቡት ለአምልኮ በተሠሩት ሕንፃዎች ውስጥ ሳይሆን በግለሰብ ቤቶችና በተመሳሳይ ስፍራዎች ነበር። ሕንፃው ክርስቲያን የሆኑት የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሚሰባሰቡት ስፍራ ብቻ ነበር።
በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ፥ የክርስቶስ አካል የሆነችው ሕያው ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ ሊያከናውን ለሚፈልገው ተግባር መፈጸሚያ ስፍራ ነች። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአሕዛብና የአይሁድ ይሁን፥ የጥቁሮችና የነጮች፥ ወይም የአማራና የኦሮሞ ዘረኝነት ሊወገድ ይገባል። በክርስቶስ አካል ውስጥ ሁላችንም አንድ ሆነናል (ኤፌ. 2፡15-16)። እያንዳንዱ አማኝ አካሉ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን በማገልገል ክርስቶስን ያገለግል ዘንድ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለአማኞች አካል ሰጥቷል። እንዲሁም፥ ቤተ ክርስቲያን ወንጌሉን ወደ ዓለም ሁሉ በመውሰድ የእግዚአብሔር ቃል አቀባይነቱን ተግባር ልትወጣ ይገባል።
- የእግዚአብሔር ሕዝብ በተለወጠ ሕይወት እምነታቸውን ያሳያሉ፡– ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚታዩት ችግሮች አንዱ እምነታችንንና አምልኮአችንን ከአኗኗራችን መነጠላችን ነው። ብዙ ክርስቲያኖች ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው በተሟሟቀ ስሜት ይዘምራሉ። ነገር ግን በሥራቸው፥ በአኗኗራቸውና ከሌሎች ጋር በሚዛመዱባቸው መንገዶች ከማያምኑ ሰዎች ብዙም አይሻሉም። እኛ የአሮጌው ፍጥረት ማሻሻያዎች ሳንሆን አዲስ ፍጥረት ነን (2ኛ ቆሮ. 5፡17)። በመሆኑም፥ ሕይወታችን ሙሉ ለሙሉ መለወጥ አለበት። የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን እግዚአብሔርን ልንመስልና (ኤፌ. 5፡1) እንደ እርሱ ቅዱሳን ልንሆን ይገባል። አዲሱ የተለወጠ ሕይወታችን የሚገለጥበት ትልቁ ቁም ነገር ፍቅራችን፥ ራስ ወዳድነት የሚጎላበት ግላዊ ፍላጎታችንን ለሌሎች መተዋችን ነው (1ኛ ቆሮ. 13)። ይህም ሌሎችን እናገለግል ዘንድ ራሳችንን ማዋረዳችንን ያካትታል (ፊልጵ. 2፡5-1)። ወሲባዊ ንጽሕናችንን መጠበቅ፥ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በስምምነት መኖር፥ ችግር ያለባቸው ድሆችን መርዳትንም ያካትታል። መንፈስ ቅዱስ ሕይወታችንን ለመሙላቱ ዐቢዩ መረጃ በልሳን እንደ መናገር ዓይነት አስደናቂ ነገሮች መከሰታቸው ሳይሆን፥ መንፈስ ቅዱስ የሚያመጣቸው እንደ ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት የመሳሰሉ የባሕርይ ለውጦች መታየታቸው ነው (ገላ. 5፡22-23)። ጳውሎስ በክርስቶስ ካመንን በኋላ ሕይወታችን በከፍተኛ ደረጃ ካልተለወጠ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት መጠራጠር እንዳለብን ይመክራል።
- የመጨረሻው ዘመን፡– በጳውሎስ መልእክቶች ሁሉ ውስጥ የሚገኝ ዘላቂ ጭብጥ ቢኖር የክርስቶስ መመለስ ማረጋገጫ ነው። ክርስቶስ የተሰቀለ አዳኝ ብቻ ሳይሆን ከሞት የተነሣና አንድ ቀን ተመልሶ የሚመጣ ጌታም ነው። እርሱ ሲመለስ ሰይጣንን፥ ክፉ ገዥዎችንና የማያምኑ ሰዎችን ጨምሮ የእግዚአብሔር ጠላቶች ሁሉ ለእርሱ ለመገዛትና እውነተኛው ጌታ ክርስቶስ ብቻ እንደሆነ ለመቀበል ይገደዳሉ። በዚያን ጊዜ የምድር ላይ አኗኗራችን ከፍተኛ ውጤት ይኖረዋል። በክርስቶስ አምነው ሕይወታቸውን ለማስገዛት ያልፈለጉት ዓለማውያን ዘላለማዊ ፍርድን ይጋፈጣሉ። የአማኞችም ሕይወት ይመዘናል። አማኛች የምድራዊ መንግሥት አባላት መሆናቸው ሲታወቅም፥ ጳውሎስ ቀዳሚው ቤታችን በሰማይ እንደሆነና የዘላለማዊ መንግሥት ዜጎች መሆናችንን ማስታወስ እንዳለብን ያስተምራል (ፊልጵ. 3፡20)።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ 8 ዐበይት አስተምህሮዎች ዛሬ ለክርስቲያኖች ለምን እንደሚያስፈልጉ አብራራ። ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ እነዚህ አስተምህሮዎች የሚቀርቡበትን ሁኔታ ግለጽ። ሐ) የምእመናን እምነት በእግዚአብሔር ቃል ላይ ይመሠረት ዘንድ ቤተ ክርስቲያንህ በእነዚህ እውነቶች ላይ የምትሰጠውን ትምህርት እንዴት ልታሻሽል ትችላለች?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት